- Details
- Category: Property Law
- Hits: 32730
ህገ-መንግስታዊ መሰረቱ
መንግስት በህገ-መንግስቱ ለህዝብ የገባቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግዴታዎች ለመፈፀም ደግሞ የግድ በይዞታው ስር አድርጐ የሚያዝበት መሬት ሊኖረው ይገባል፡፡ ለምን ቢባል መንግስት ያለ እንደዚህ ያለ የኢኮኖሚ መሳርያ ዘላቂ ልማት፣ ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት ጠንካራ ኢትዮጵያን ሊገንባ አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህን ይሁለንተናዊ ዘላቂ የልማት መሰረት የሆነውን መሬት በመንግስት አስተዳደር ስር ከማድረግ ውጪ መንግስት ከባለይዞታው እየገዛ በከተሞች መሰረተ ልማት የመስፋፋትን ሰራም ሆነ ለግል የከተማ ልማታዊ ባለሃብት መሬት በማቅረብ በተፈለገው ደረጃ ፍጣንና ዘላቂ ሁሉም ዜጎች በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማት ማመጣት ይችላል ብሎ ማሰብ ካለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ያፈነገጠ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ልማት ከሌለ ሰላም ስለማይኖር የመበታተን አደጋን ሊያስከትል የሚችል የተሳሳተ የጥፋት አቅጣጫም ነው፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት በአንቀፅ 40(3) ፤ (6) እና አንቀፅ 89 (5) ላይ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሆኖ አስተዳደሩን በሚመለከት የመንግስት መሆኑን የደነገገበት ዋናው አላማም ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቃ ወደ ልማት አዙሪት በመግባት በ20ና 30 ዓመታት ጊዜ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ በመሰለፍ ፈጣንና ዘላቂ የህዝቦቿ በእድገት ጎዳና የመጓዝ ራእይ ነው፡፡ ይህን የመንግስት ንብረት የማስተዳደር ስልጣንና አገሪቱን ወደ እድገት አዚሪት በማስገባት ዜጐች በየደረጃቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ልማት የማስመዝገብ ስትራተጂ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ከንብረት አስተዳደር ጋር የተያያዙ አዋጆችን በማውጣት ግዴታውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ አሁን ከያዝነው የንብረት ህግ ተያያዥነት ያላቸውን የገጠር መሬት አስተዳደርንና አጠቃቀምን፣ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝን እና ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ ስለሚለቀቅበትና የካሳ አከፋፈልን በሚመለከት የወጡ አዋጆችና ደንብ ወስደን ስናይ መንግስት የቱን ያህል ለቀየሳቸው የልማት ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ተፈፃሚነት ቁርጠኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የንብረት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተብለው ከተካተቱት መካከል በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 40 ላይ አንዱ መሰረታዊ መብት በመሆን ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ የከተማ መሬት ባለቤትነት መብት (ownership right) የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደሆነና አስተዳደሩን በሚመለከት በአንቀፅ 89(5) ላይ የከተማ ቦታም ቢሆን በመንግስት ይዞታ ስር ሆኖ ለህዝብ ጥቅም መዋል እንዳለበት ሲደነግግ አጠቃቀምና ጥበቃውን በሚመለከት መንግስት ህግ ማውጣት እንዳለበት በአንቀፅ 51(5) ላይ ተደንግጓል ፡፡ መንግስት ይህን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችን ህዝቦች ንብረት የሆነን መሬት በይዞታው ስር አድርጐ በሚያስተዳድርበትና ለልማት በዋና መሳሪታነት በሚገለገልበት ጊዜ ዜጐች በከተማ ቦታ ላይ ስለሚኖራቸው የንብረት መብት በተመለከተም የባለይዞታነት መብታቸውን ህገ-መንግስታዊ ዋስትና በሚሰጥ መልኩ አንቀፅ 40 (7) ላይ "ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት የመሸጥ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ የመሬት ተጠቃሚነት ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት ባለቤቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብትን ያካትታል . . . " ሲል ደንግጓል፡፡ ከዚህ ህገ-መንግስታዊ የንብረት ባለይዞታነት መብት ጥበቃ መገንዘብ የሚቻለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ- መንግስት ከአሁን ቀደም በአገሪቱ ከነበሩ ህጎች በበለጠ ሁኔታ የዜጎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት እንደሚያረጋግጥ ነው፡፡ ስለሆነም የከተማ ቦታን የመንግስትና የህዝብ የማድረጉ ፖሊሲና አላማ የሚመነጨው መንግስት በህዝብ ወኪልነቱ የህዝቦች የጋራ ሃብት የሆነውን የከተማ ቦታ በአኩልነት ለማዳረስ፣ ለመቆጣጠር፣ ለማስተዳደር፣ ስርዓት ለማስያዝና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ተግባራት ለማከናወን እንዲችል ከማድረግ ጋር ተያይዞ የአገሪቱን መፃኢ እድል ከሚወሰኑ አበይት ጉዳዮች አንዱ አድርጐ ከሚወሰድ ህገ-መንግስታዊና ሀገራዊ ረእይ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ተግባራዊ በማድረጉ ሂደት የፍትህ አካላት በህገ- መንግሰቱ አንቀፅ 13 የተጣለባቸውን ግዴታ በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡
ከአዋጅ ቁጥር 272/94 አንፃር
ይህ አዋጅ የከተማ መሬትን የመጠቀም መብትን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ሊዝ ዋነኛ የመሬት ይዞታ ስሪት እንዲሆን መመረጡንና የከተማ ቦታ የመጠቀም መብት በውል የሚተላለፍ ወይም የሚያዝ መሆኑን የከተማ ቦታ ለመኖርያ ቤት እንዲያዝ የሚፈቅድ መሆኑን አካቷል፡፡ የከተማ ቦታ በሊዝ የተፈቀደለት ሰውም የሊዝ ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንደሚሰጠውና ዘመኑም እንደየ አገልግሎቱ ዓይነት ሊለያይ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ይህ የከተማ ቦታ ባለይዞታነት መብት የይዞታ ዘመኑ በሚያልቅበት ግዜም ሊታደስ እንደሚችል ስለሚደነግግ ዜጐች ይዞታቸውን በአግባቡ በመያዝ ለበለጠ ልማት እንዲያውሉት የሚያደፋፍርና በይዞታቸው በዘላቂነት የመገልገል መብታቸው የህግ ዋስትና እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ የከተማ ልማት ፖሊሲና ሰትራተጂ መሰረት በማድረግ የወጣ ህግ ነው፡፡
አዋጅ ቁጥር 272/94 በአንቀፅ 2(1) ላይ “ ‘’ሊዝ’’ ማለት የከተማ ቦታ በመጠቀም መብት በውል የሚተላለፍበት ወይም የሚያዝበት የመሬት ኪራይ ይዞታ ስሪት ነው፡፡” ሲል ይደነግጋል፡፡ ከዚህ የህግ ትርጉም (statutory definition) መረዳት የሚቻለው የሊዝ መብት መሰረቱ (subject matter) የማይንቀሳቀስ ንብረት ማለትም የከተማ ቦታ እንደሆነና የመብቱ ምንጭም በሊዝ ተቀባዩና በሊዝ ሰጪው የአከባቢ መስተዳድር መካከል የሚደረግ የሊዝ ውል እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ውል ህግ ፊት ዋጋ ያለው ውል እንዲሆን በአዋጁ አንቀፅ 9 መሰረት ውሉ መፈረም ይኖርበታል ከዚያም በኃላም በአንቀፅ 5 መሰረት ውል ተቀባዩ በሊዝ የቦታ ባለይዞታ መሆኑን የሚያረጋግጥለት የሊዝ ይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የከተማ ቦታ በሊዝ በሚያዝበትና በሚተዳደርበት ግዜ መንግስት በሚያገኘው ገቢ ተጨማሪ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሰራ አቅም የሚፈጥርለት ዋና የገቢና እድገት ምንጭም ነው፡፡
የሊዝ ውል ተቀባይ መብቶችና ግዴታዎች
በሊዝ ጨረታ የመሳተፍና አሸናፊ ሲሆንም የሊዝ ውሉን በመፈረም ተገቢውን ክፍያ ከፍሎ ቦታውን የመረከብ መብት አለው፡፡ (አንቀፅ 4 እና 9)
የግል ባለሃብት ከሆነ በክፍያ መሬት የመጠቀም መብት ያለው ስለመሆኑና ዝርዝሩ በሌላ ህግ እንደሚወሰን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀፅ 40(6) ስለሚደነግግ ኢንቨስተሮች ለኢንዱስትሪ መስፋፋት የሚጠይቁት የከተማ ቦታ አዋጅ ቁጥር 272/94 በሚደነግገው መሰረት መሬት አግኝተው ባለ ይዞታ የመሆን መብታቸው ህገ-መንግስታዊ ነው፡፡ እንደየሚሰማሩበት የልማት ስራ ዓይነትና ደርጃ ለረጅምና አጭር ጊዜ በሊዝ የከተማ ቦታ የማግኘት መብትም አላቸው፡፡ (የአዋጁ አንቀፅ 6)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 55(2) (ሀ) መሰረት በማድረግ አዋጅ ቁጥር 272/94 በማውጣቱ የከተማ ነዋዎች የሚኖራቸው የከተማ ቦታ ባለይዞታነት መብት በህግ ተረጋግጦላቸዋል፡፡
የአገሪቱ የልማት ፖሊሲና ስትራተጂ ተግረባራዊ ለሚያደርጉ ልማታዊ ባለሃብቶች ወይም ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የከተማ መሬት ከሊዝ ክፍያ እስከ በነፃ መሬት የማግኘት መብት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የሚመለከተው አካል ሲፈቅድለት የሊዝ ባይዞታው የተፈቀደለትን የአገልግሎት ዓይነት ወይም የልማቱን ስራ ዓይነት መቀየር ይችላል፡፡(አንቀፅ 12(2) )
የሊዝ ባለይዞታ መብቱን ወደ 3ኛ ወገን የማስተላለፍ፣ በዋስትና የማስያዝ (surety) ወይም የፈፀመውን ክፍያ በካፒተል አስተዋፅኦነት (capital contribution) ለመጠቀም የሚያስችል መብት አለው፡፡ (አንቀፅ 13)
ለህዝብ ጥቅም ተብሎ የሊዝ ባለይዞታነቱ በሚለቀቅበት ግዜ ካሳ በቅድሚያ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ህገ-መንግስት አንቀፅ 409(8) እና የአዋጁ አንቀፅ 16)
በአዋጅ ቁጥር 272/94 መሰረት የተገኘው የከተማ ቦታ ሊዝ አስተዳደርን መሰረት በማድረግ በአዋጁ ለተቋቋሙ የአስተዳደር አካላትና በይግባኝ እስከ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሄድ መብት አለው፡፡ (በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀፅ 37 እና የአዋጁ አንቀፅ 17፤18 እና 19)
በመጨረሻም የሊዝ ባለይዞታነት ውል ዘመኑ ሲያልቅ ውሉን የማደስ መብት አለው፡፡ (የአዋጁ አንቀፅ 7) እንደ ግዴታም የሚከተሉት ግዴታዎች አሉት ::
በከተማ ቦታ ሊዝ ውል መሰረት የተተመነለትን ኪራይ በወቅቱ የመክፈል ግዴታ አለው፡፡
በደንቡ መሰረት የተሰጠውን የከተማ ቦታ ለታለመለት ስራ ወይም አገልግሎት በወቅቱ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ግዴታ አለው፡፡(አንቀፅ 12 (1) )
የሊዝ መሬት ከተሰጠበት አገልግሎት ለተለየ ስራ እንዲውል ሲፈቀድለት በተለወጠው ውል መሰረት የሊዝ ኪራይ መክፈል ይኖርበታል፡፡ (አንቀፅ12 (2) እና (3) )
የሊዝ ባለይዞታው እንደማንኛውም ዜጋ የሊዝ አዋጅን ለማስፈፀም በሚድረግ ማናቸውም እንቅስቃሴ ትብብር የማድረግ ግዴታ አለው፡፡ (አንቀፅ 21)
የሊዝ ውል ሰጪ መብቶችና ግዴታዎች
በአዋጅ ቁጥር 272/94 መሰረት በማድረግ በሚወጣ ደንብ መሰረት የሊዝ ኪራይ ከተጠቃሚዎች የመሰብሰብ መብት አለው፡፡
እንደየሁኔታው የችሮታ ግዜ የመስጠትም የመከልከልም ስልጣን የከተማ ቦታ ሊዝ አስተዳደሩ ነው፡፡
ሁኔታዎች ተሟልተው ሲገኙ ፈቃድ ይሰጣል ፡፡
ለህዝብ ጥቅም ሲባል መለቀቅ ያለበትን የሊዝ ይዞታ ካሳ በመክፈል ለማስለቀቅና ለመረከብ ይችላል፡፡ አስፈላጊም ሲሆን የፖሊስ ኃይልን ይጠቀማል፡፡
በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን የከተማ ቦታ የማስለቀቅ መብት አለው፡፡
የሊዝ ቦታን መሰረት በማድረግ ክርክር ሲነሳ በከሳሽነትም በተካሽነትም የመከራከር መብት አለው፡፡ ከግዴታ አንፃርም የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩታል::
ለህዝብ ጥቅም ሲባል አንድን የሊዝ ባለይዞታ በሚያስለቅቅበት ግዜ ተመጣጣኝ ካሳ የመክፈል ግዴታ አለው፡፡
የሊዝ ባለይዞታነት ሲፈቀድና ውሉ ሲፈረም የባለይዞታነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመስጠት ግዴታ አለው፡፡ (አንቀፅ5(1))
የሊዝ ውል ስለመቋረጥና ውጤት
የከተማ ቦታ ሊዝ ውል ቀረ የሚሆነው የውሉ ዘመን ሲያበቃና ሊዝ ተቀባዩ የአዋጁ አንቀፅ 7 በሚደነግገው የግዜ ገደብ ውስጥ ውሉ እንዲታደስለት ሳያመለክት ሲቀር የሊዝ ውሉ ይቋረጣል፡፡
ተዋዋዩ ወገን በሊዝ የተሰጠውን የከተማ ቦታ ህግ በሚያዘው መሰረት ጥቅም ላይ ካላዋለው ውሉ ሊቋረጥ ይችላል፡፡
በሊዝ የተሰጠው የከተማ ቦታ ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ለሌላ ስራ ወይም አገልግሎት እንዲውል ሲወሰን የሊዝ ውሉ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ በመቋረጡም የሚከተሉትን ህጋዊ ውጠቶችን ያስከትላል፡-
የሊዝ ውሉ የተሰጠውን የከተማ ቦታ ስራ ላይ ባላማዋሉ የሚቋረጥ ከሆነ ተገቢውን ወጪና መቀጮ በመቀነሰ የሊዝ ክፍያው ለሊዝ ተቀባዩ ይመለሰለታል፡፡
የሊዝ ውሉ የተቋረጠው ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከሆነ የሊዝ አስተዳደሩ ለሊዝ ተጠቃሚው በአዋጁ አንቀፅ 17 መሰረት ተመጣጣኝ ካሳ በመክፈል ያስለቅቀዋል፡፡
ውሉ እንዲታደስለት ካላመለከተ በስተቀር የሊዝ ባለይዞታው እስከ አንድ ዓመት ባለ ግዜ ወስጥ በቦታው ላይ ያስፈረውን ንብረት በማንሳት ላስረከበው አካል ቦታውን መልሶ መስጠት ይኖርበታል፡፡
ስለዚህ የከተማ ቦታ በሊዝ የማግኘት መብት ከህገ-መንግስቱና ሌሎች ዝርዝር ህጐች ለመረዳት እንደሚቻለው በሊዝ ውል የሚገኝ የከተማ የማይንቀሳቀስ ንብረት የይዞታ መብት ነው፡፡ ይህም የከተማ ልማት ስትራተጂ ግቡን እንዲመታ እየተሰራበት ያለ የልማት ዘርፍ ሲሆን የዜጐች መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን መኖርያ ቤት ዋስትና ከማረጋገጡ ባሻገር የግሉ ዘርፍ ኮንሰትራሽንና የመንግስት የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ከፍተኛ የሆነ እድገት እያሳዩበት ያለ አብዛኛውን የከተማ ነዋሪ በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ ያለ ህግ ነው፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 10266
አገራችን ኢትዮጵያ አሁን እየተከተለችው ባለ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 8(1) “የኢትዮጵያ ብሄር-ብሄረሰቦች ህዝቦች የኢትዮጵያ ልኡላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡” በማለት የሚደነግግ ሲሆን የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 40(3) እንደዚሁ ከንብረት ባለቤትነት መብት አንፃር “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው ፡፡” በማለት ይደንግጋል፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰልጣን የሚገኘው በህዝባዊ ምርጫ እንደመሆኑ መጠን ህዝቡ በተወካዮቹ በቀጥታ በሚያደርገው ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት እንደሆነ በአንቀፅ 8(3) ላይ በግልፅ ሰፍሯል፡፡ ከነዚህ ህገ-መንግስታዊ መርሆች መገንዘብ የሚቻለው የመንግስት ስልጣን መሰረቱ ህዝብ እንደሆነና መንግስት በአንቀፅ 89(2) የተሰጠውን የኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለማሻሻል እኩል እድል እንዲኖራቸው ለማድረግና ሀብት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታውን ለመወጣት ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራተጂ ነድፎ ዜጐች በያደረጃቸው የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሰፊው እየሰራበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የኢኮኖሚውን ፖሊሲና ሰትራተጂ ከግብ ለማድረስና ኢንቨስትመንትን ለማሳድግ መንግስት መሬትንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን የህዝቡ የጋራ ንብረት አድርጐ ማስተዳደሩ የአገሪቱ ተጨባጥ ሁኔታ የሚጠይቀው ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 89(5) መሰረት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን በህዝቡ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለህዝብ የጋራ ጥቅምና እድገት እንዲውል የማድረግ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የፍ/ብሄር ህግ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት ከመውጣቱ በፊት በአፄው ዘመነ መንግስት የወጣ በመሆኑ እነዚህን መሰረታዊ የመሬትና የተፈጥሮ ሃብቶች የህዝብ ንብረቶች ስለመሆናቸው የህገ-መንግስቱን መርሆች ተከትሎ የወጣነው ባይባልም የንብረት ህጉ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1444 እስከ 1459 ባሉ ድንጋጌዎች የህዝብ ንብረት አገልግሎት የሚላቸውን ንብረቶች ኣካቶ የያዘ ለመሆኑ ከፍ/ብሄር ህጉ ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡
የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1445 (ሀ) እና (ለ) አንድ ንብረት መቼ የህዝብ ንብረት መባል እንዳለበት ሲገልፅ “ንብረቱ አንድም ህዝብ እንዲገለገልበት በቀጥታ የተመደበ ወይም የተተወ መሆን እንዳለበት ወይም ንብረቶቹ በተፈጥሯቸው ወይም በተደረገላቸው ለውጥ ምክንያት ለተለየ የህዝብ አገልግሎት ብቻ ወይም በይበልጥ ለዚሁ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረጉ እንደሆኑ የህዝብ ንብረት ይባላሉ፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡ በሌላ አነጋገር ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን መስፈርቶች የማያሟሉ ሆነው ግን ደግሞ በመንግስት እጅ ያሉ ንብረቶች በፍታብሄር ህጉ አነጋገር የህዝብ ንብረት ሳይሆኑ የመንግስት የግል ንብረቶች ተብለው እንደሚወሰዱ የሚደነግግ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ህግ አነጋገር የህዝብ ንብረት የሚባሉት በፍ/ብ/ህ/ቁ 1446-1447 እና 1220-1256 ተዘርዝረው የምናገኛቸው ሲሆኑ እነዚህን እንደ ጥርግያ መንገዶች፣ ካናሎች፣ የውሃ መስመሮች፣ የመብራት መስመሮች፣ ሃይቆች ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ንብረቶች ናቸው፡፡
የህዝብ ንብረት (public domain) መብት መሰረቱ (subject matter) የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሆነው የዚህ መብት ምንጭ (source) ህግ ነው፡፡ ይህም አሁን ባለው ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ከህገ-መንግስቱ አንስቶ ከህገ-መንግስት መውጣት በኃላ የህዝብ ንብረትን በማስመልከት የወጡ አዋጆችን ያየን አንደሆነ የህዝብ ንብረት መብት ምንጩ ህግ ነው ለሚለው አባባል ዋቢ ናቸው፡፡ አንድ ዜጋ ይህን የህዝብ ንብረት (public domain) የሆነን ንብረት በቀን ልቦና ባለይዞታነት (possession in good faith or usucaption) ወይም በመያዝ (occupation or accession) የባለቤትነት ይሁን የባለ ይዞታነት መብት ሊያገኝ አይችልም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1454-1455) ይህ ማለት ግን መንግስት እንደ ህዝብ አስተዳዳሪነቱ አንድን የህዝብ ንብረት የነበረን ንብረት የህዝብ ንብረትነቱ ቀርቶ የግል ንብረት እንዲሆን ማድረግ አይችልም ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ መንግሰት ለህዝብ ጥቅም ሲባል አንድን የግል የሆነን ይዞታ በማስለቀቅ (expropriation) or (alignment) ያንን ንብረት የህዘብ ንብረት ማድረግ የሚችል ሲሆን በዚህ ሁኔታ የሚገኝ የህዝብ ንብረት በሚመለከት የግል ባለ ንብረቱ ተመጣጣኝ ክፍያ በቅድሚያ ማግኘት እንዳለበት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግስት አንቀፅ 40(8) ፣ ፍ/ብ/ህ/ቁ.1453/3፣ 1470-1477 እና አዋጅ ቁጥር 455/1997 አንቀፅ 7- 8 ላይ ተደንግጐ የምናገኛቸው ቢሆኑም አሁን ተፈፃሚነት ያላቸው ህጐች ግን ህገ-መንግስቱን መሰረት በማድረግ የወጡት አዋጅ ቁጥር 455/97 እና ደንብ ቁጥር 135/99 ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ሊወሰድ የሚችለው የኋልኞቹ ህጎች ያለውን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት መሰረት በማድረግ የወጡና ያለውን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዲገዙ የአገሪቱን ሁለንተናዊ የዘላቂ ልማት ሰትራተጂ ታሳቢ በማድረግ የተደነገጉ በመሆናቸው እነዚህ ድንጋጌዎች የፍ/ብሄር ህጉን ድንጋጌዎች በግለፅ ባይሽሩም መፈፀም ያለባቸው እነሱ በመሆናቸውና ወደ ፍ/ብሄር ህጉም የሚያስኬድ በቂና ህጋዊ ምክንያት ስለሌለ ነው፡፡ አንድ የህዝብ ንብረት የህዝብ ንብረትነቱን ቀሪ የሚሆንበት እና ወደ ግል ንብረትነት ሊዛወር የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች በሁለት ከፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን እነሱም፡-
1.በህግ የህዝብ ንብረትነቱ ቀርቶ ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘወር በህግ ስልጣን በተሰጠው አካል ሲወሰን ለምሳሌ፡- የመብራት አገልግሎት ኢ.መ.ኃ.ኮ መሆኑ ቀርቶ በግል ኩባንያ እንዲያዝ የሚያደርግ የመንግስት ውሳኔ ሲተላለፍ፡፡
2.ንብረቱ በራሱ ግዜ ለህዝብ አገልግሎት መዋሉ ሲቋረጥ ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጥርግያ መንገድ ለህዝብ አገልግሎት መዋሉ ሲቋረጥና ጥርግያ መንገድ መሆኑ ሲቀር ወደ ግል ይዞታነት ሊቀየር ይችላል፡፡
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የህዝብ አገልግሎት ንብረት ለህዝብ ጥቅም ሲባል መንግስት የግል ይዞታን በማስለቀቅ ወያም በተፈጥሮ ይዞታና አጠቃቀማቸው ሊገኝ የሚችል ሲሆን በዋናነት እውቅና የተሰጣቸውን የዜጎች የንብረት መብቶችና ሃገሪቱ የምትከተለውን የማህበረ-ኢኮኖሚና የመሰረተ-ልማት ፖሊሲና ስትራተጂ ተግባራዊ ለማድረግና ዜጐች በየደረጃው የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግን እንደግብ በመውሰድ መንግስት ከህዝብ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት ግዴታውን እንዲወጣ የሚያስችለው የመንግስትና የህዘብ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው ህገ-መንግስታዊ ሰርዓት የህዝብ ንብረት ሲባል በፍታብሄር ህጉ ከተዘረዘሩት ነገሮች ሰፋ ባለመልኩ የገጠርና የከተማ መሬት ባለቤትነትንም ጭምር የሚያካትት መሆኑ ግለፅ ሊሆን ይገባል፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9140
የንብረት አገልግሎት ስለ ሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ጥቅም በአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚጣል ግዴታ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1359) የንብረት አገልግሎት መሰረቱ (subject matter) የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን የመብቱ ምንጮች (sources) ህግ፣ ውልና ተፈጥራዊ አቀማመጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ቀደም ሲል እንደ አላባ መብት በሚንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት በሌላቸው እንደ ፈጠራ፣ የቅጅ መብትና፣ የኢንዱስትሪ ንድፍ በመሳሰሉ ንብረቶች ላይ ሊመሰረት አይችልም፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ሊመሰረት የሚችለው ግዙፍነት ባለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ነው፡፡
የንብረት አገልግሎት በፍ/ብሄር ህጉ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1359 እስከ 1385 ባሉ ድንጋጌዎች የሚገዛ ሆኖ በጐረቤታሞች መካከል የመቻቻል፣ የመረዳዳት መሬቶቻቸውንና ግንባታዎቻቸውን የተሻለ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል መልኩ እንዲገለገሉበት የሚያስችል መብት በመሆኑ ለሰዎች መልካም ግንኙነት ያለው ፋይዳ እጅግ የጐላ ነው፡፡ ይህ መብት ሰውን በመከተል ሊፈፀም የሚችል መብት (real right) ሲሆን በዋናነት መሰረቱ መሬት ነው፡፡ ይሄውም የንብረት አገልግሎት ግዴታ ያለበት የማይንቀሳቀስ ንብረት የግዴታ አገልጋይ (Servient tenament) ባለቤት በንብረቱ ላይ ያለውን መብት ለአገልግሎት ተቀባዩ (Dominant tenament የማይንቀሳቀስ ንብረት ጥቅም ሲባል መብቱ የሚገደብበት ዓይነት የንብረት አገልግሎት ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለ ግንኙነት ነው፡፡
የንብረት አገልግሎት መብት የሁለት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና የሁለት የተለያዩ ሰዎች መኖርን ታሳቢ የሚያደርግ ቢሆንም እነዚህ ሁለት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሁሉ ግዜ ጥግ ለጥግ (contiguous) ወይም ተጓዳኝ (adjacent) መሆን አለባቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ይህም ማለት የተወሰነ ርቀት ኖራቸውም እንደ እንሰሳትን ውሃ ማጠጣት (watering animals) ግጦሽ፤ (pasture) እንጨት መቁረጥ (cutting wood) ወይም እይታ (view) ወ.ዘ.ተ. ባሉ ሁኔታዎችም የንብረት አገልግሎት ሊመሰረት ይችላል፡፡ የንብረት አገልግሎት በግዴታ አገልጋይ (Servient tenement) የባለቤትነት መብት ላይ ተፅእኖ የሚፈጥር ነው፡፡ ለምሳሌ የንብረት አገልግሎቱ የማለፊያ መንገድን መሰረት ያደረገ በሚሆንበት ግዜ ከመሬቱ ቀንሶ ለመንገድ የሚሆን መሬት እንዲሰጥ:: የንብረት አገልግሎቱ የእይታ መብት (right to view) በሚሆንበት ግዜ ደግሞ ግርዶሽ የሚፈጥር ግንባታ ከማካሄድ እንዲቆጠብ ይገደዳል፡፡ የንብረት አገልግሎት አስፈላጊነት መለኪያው ለአገልግሎት ተቀባዩ (dominant tenament) ምን ያህል ጠቃሚ ነው የሚል ነው፡፡ አንድ ሰው ለሌላ ሰው የግዴታ አገልጋይ (Servient tenement) እንዲሆን የሚገደደው የንብረት አገልግሎት ተቀባዩ (Dominant tenement) የማይንቀሳቀስ ንብረት ያለ እንደዚያ ያለ አገልግሎት የማይንቀሳቀስ ንብረቱ ጥቅም ላይ የማይውል መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የንብረት አገልግሎት ግንኙነት ሊመሰረት አይችልም፡፡ በመሆኑም የንብረት አገልግሎት የሚሰጠው ለመሬቱ እንጂ ለሰው አይደለም፡፡ ሌላው መስፈርት በግዴታ አገልጋዩና በንብረት አገልግሎት ተቀባዩ መካከል የተፈጥሮ ትስስር (natural relationship) መኖር አለበት፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ከማይንቀሳቀሰው ንብረት ተለይቶ አገልግሎት ላይ ሊውል የማይችል የዋናው መብት ተጨማሪ (accessory) ነው፡፡ ይህ መብት በተፈጥሮ ቀጣይነት ያለው (perpetual) ሲሆን መሰረቱ ውል (convention) ወይም ህግ ነው፡፡ የመበቱና ግዴታው መሰረት ውል በሚሆንበተ ጊዜ ተዋዋዮች ግዴታው የሚቆይበትን ጊዜ በውላቸው ላይ በማስፈር ሊሰማሙ ይችላሉ፡፡ መብቱና ግዴታው የሚመነጨው ከህግ በሆነበት ጊዜ ደግሞ ህጉ በሚያዘው መሰረት ይፈፀማል፡፡ የንብረት አገልግሎት የግዴታ አገልጋይ ያለበትን ግዴታ ልዋጭ በመስጠት (redemption) ካልሆነ በስተቀር ካሳ (indemnity) በመስጠት ቀሪ ሊያደርገው አይችልም::
የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች (Kinds of Servitude)
የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች ሶስት ሲሆኑ እነሱም፡፡
Øአንደኛው ተፈጥራዊ የንብረት አገልግሎት (natural servitude) የሚባለው ሲሆን መነሻው የንብረት አገልግሎት ተቀባዩ (dominant tenament) እና የንብረት አገልግሎት ግዴታ አገልጋይ (servient tenament) ጆግራፍያዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ እንደ በዝቅተኛ ቦታ ያለ ሰው ውሃ የማግኘት መብት ወይም እንደ በሁለት ማሳዎች ድንበር ወይም አጥር ባሉ ነገሮች ላይ የሚመሰረት የንብረት አገልግሎት ዓይነት ነው፡፡ ይህም የጆግራፊ አቀማመጣቸው የግዴታ አገልግሎት መሰጠትን የግድ ሲል ህግ በራሱ እውቅና (recognition) የሚሰጠው መብት ነው፡፡
Øሁለተኛው ህጋዊ የንብረት አገልግሎት (legal servitude) የሚባል ሲሆን ይህ ዓይነት የንብረት አገልግሎት ህግ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚፈጥረው ነው፡፡ ይህ የሚከሰተው መውጫ መግብያ የሌለው መሬት (enclave land) በሚኖርበት ግዜ ህግ መውጫ መግብያ እንዲኖረው ሲያስገድድ ወይም የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የቴሌ፣ የጋዝ መስመር ዝርጋታ ሲኖር በሌላው መሬት ላይ የዝርጋታ ስራው እንዲከናወን ህግ ሲያስገድድ የሚኖር የንብረት አገልግሎት ዓይነት ነው፡፡
Øሶስተኛው በውል የሚመሰረት የንብረት አገልግሎት (conventional or juridical servitude) የሚባለው ሲሆን የዚህ ዓይነት የንብረት አገልግሎት በሁለት እና ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚመሰረት ወይም አንድ ሰው በግሉ (unilaterially) እንደ ኑዛዜ ባለ ሁኔታ ሊመሰረት የሚችል ነው፡፡ ከፍ ብለን ካየናቸው ሁለት የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች የሚለየው የዚህ ዓይነት ንብረት አገልግሎት ህጋዊ ውጤት እንዲኖረውና በተዋዋዮች መካከል በፍ/ህ/ቁ/1731 መሰረት ህግ ሆኖ እንዲያገለግል ከተፈለገ ውሉ በፅሁፍ መሆንና ስልጣን በተሰጠው አካል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1723 መሰረት መመዝገብ ይኖርበታል ፡፡ ካልሆነ ግን የአስገዳጅነት ውጤት አይኖረውም::
የንብረት አገልግሎት አተገባበር (Servitude in Modes of Exercise)
vግልፅና ግልፅ ያልሆነ የንብረት አገልግሎት (apparent and non-apparent servitude) ግልፅ የንብረት አገልግሎት የሚባለው የሚገለፀው በሚታዩ ስራዎች (visible works) እንደ መስኮት፣ መዝጊያ፣ ሰርጥ (channel) እና ከመሬት በላይ የተዘረጋ ባምቧ ባሉ ዓይነቶች ነው፡፡ ግልፅ ያልሆነ የንብረት አገልግሎት በመሬት ላይ የሚታይ እንደ ያለመገንባት ወይም ከተወሰነ ከፍታ በላይ ያለመገንባት ባሉ ሁኔታዎች የሚገለፅ የንብረት አገልግሎት ነው፡፡ በሁለቱም የንብረት አገልግሎቶች መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ በሆነው የንብረት አገልግሎት በይዞታ ለ10 ዓመት በእጅ በማቆየትና ግብር በመክፈል (usucaption) የንብረት አገልግሎት መብት ማግኘት የሚቻል ሲሆን ግልፅ ባልሆነው የንብረት አገልግሎት በዚህ መልኩ መብትን ማግኘት አይቻልም፡፡
vቀጣይነት ያለውና ቀጣይነት የሌለው የንብረት አገልግሎት (continuous and discontinuous servitude) ቀጣይነት ባለው የንብረት አገልግሎት መብቶቹ ስራ ላይ ለማዋል የሰውን ጣልቃ ገብነት የማይጠይቁና አንድ ግዜ ከተዘረጉ በኋላ በራሳቸው ግዜ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ የውሃ ቧንቧ (pipes of water) የቆሻሻ ማስወገጃ (sewerage) እና አለመገንባት (not to build) ወይም ከተወሰነ ከፍታ በላይ አለመገንባት (not to build beyond a certain height) ያሉት ናቸው፡፡ ቀጣይነት የሌለው የንብረት አገልግሎት የሚባለው በመብቱ ለመገልገል የሰውን ጣልቃ ገብነት ወይም አንቀሳቃሽነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህም እንደ የመንገድ መብት (the right to way)፣ ውሃ መቅዳት (drawing water)፣ ግጦሽ (pasture) እና ከመሬት እንደ ድንጋይና መአድን ማውጣት (extracting minerals) ወ.ዘ.ተ. ያሉት ናቸው፡፡
vአዎንታዊና አሉታዊ የንብረት አገልግሎት (positive and negative servitude)
አዎንታዊ የንብረት አገልግሎት (positive servitude) በግዴታ አገልጋዩ (servient tenement) መሬት ላይ ገብቶ ሲገለገል የሚከሰት የንብረት አገልግሎት ሲሆን በግዴታ አገልጋዩ የንብረት ባለቤትነት ጣልቃ የመግባት (interference) ውጤትን የሚያስከትል ቢሆንም ከተገልጋዩ መብት አኳያ ሲታይ እንደ አዎንታ የሚወሰድ ነው፡፡
አሉታዊ የንብረት አገልግሎት (negative servitude) የሚባለው የግዴታ አገልጋይ (servient tenement) በሌላኛው የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ጫና ሳይፈጥር (without imposition) በባለቤቱ ተፈጥራዊ የባለቤትነት መብት (inherent ownership right) ተፅእኖ ላለመፍጠር በመብቱ ላይ ገደብ ሲጣልበት የሚከሰት እንደ ከተወሰነ ከፍታ በላይ ያለመገንባት ወይም ጭራሽ ያለመገንባት የሚገለፅ በግዴታ አገልጋይ ላይ ገደብ የሚጥል በመሆኑ ከግዴታ አገልጋዩ የባለይዞታነት መብት አንፃር ሲታይ አሉታዊ ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡
ስለዚህ የንብረት አገልግሎት መብት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ብቻ የሚመሰረት ሆኖ ከዜጐች በንብረት የመገልገል መብት ጋር ትስስር ያለው በግዴታ አገልጋይ የባለቤትነት መብት ላይ በመጠኑም ቢሆን ተፅእኖ የሚያሳርፍ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ የንብረት አገልግሎት ከአላባ ጋር በንፅፅር ሲታይ ልዩነታቸው የአላባ መሰረቶች የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ግዙፍነት ያላቸው ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው ንብረቶች ሲሆኑ የንብረት አገልግሎት መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ብቻ መሆኑ አንዱ የሚለያቸው ነጥብ ነው፡፡ ሌላው ልዩነታቸው አላባ በግዚያውነት የሚተላለፍ እና ከንብረቱ ተለይቶ (independently) ሊተላለፍ የሚችል መብት ሲሆን የንብረት አገልግሎት ከማይንቀሳቀስ ንብረት ተለይቶ ሊሰራበት የማይችልና ዘላቂ ግንኙነትን የማስከተል ውጤት ያለው በመሆኑ የንብረቱ መከፋፈል ሊያስቀረው የማይችል ነው፡፡ እንደዚሁም የንብረት አገልግሎት የሚኖረውም ለባለቤቱ ጥቅም ሲባል ሳይሆን መብቱ የሚኖረው ለሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መብትና ጥቅም ሲባል ነው፡፡ የአላባ መብት ግን ለባለቤቱ ጥቅም ሲባል የሚደረግ ሊሆን ይችላል፡፡ የአላባ መብት ጉዳይ (object) የማይንቀሳቀስ፣ የሚንቀሳቀስና ግዙፍነት የሌለው የንብረት ባለቤትነት መብት ሲሆን የንብረት አገልግሎት ጉዳይ (object) ግን የማንቀሳቀስ ንብረት በተለይ የመሬት ባለይዞታነት መብት ነው፡፡ የንብረት ባለቤትነት መብት ለብቻው ሊተላለፍ የሚችል ሲሆን የንብረት አገልግሎት ግን ከማንቀሳቀስ ንብረቱ ተነጥሎ (dismemberedly) ሊተላለፍ (assign) ወይም ሊከበር (attach) የሚችል ባለመሆኑ በሁለቱም መካከል ልዩነት አለ፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9415
የአላባ መብት ከአንድ ግዙፍነት ያለው የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም ግዙፍነት ከሌለው የባለቤትነት መብት ተቀንሶ በንብረቱ ለመገልገል (usus) ወይም ፍሬውን የመሰብሰብና መውሰድ (fructus) መብት በመስጠት የሚቋቋም የንብረት ግንኙነት ነው፡፡ ይሄውም አንድ ሰው ካለው የባለቤትነት መብት ቀንሶ ለሌላ ሰው የሚያስተላልፈው መብት ነው፡፡ አንድን ንብረት በአላባ የማስተላለፍ መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 40/1/ ". . . ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል" በሚለው ስር የሚወድቅ ህገ-መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው መብት ነው፡፡ አላባ ከፍ/ብ/ህጉ አንፃር ሲታይም ከቁጥር 1309-1358 ባሉ ድንጋጌዎች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት የምናገኘው በንብረት የመገልገል ወይም ፍሬው የመሰብሰብና የመውሰድ ወይም ሁለቱ መብቶች አንድ ላይ ተዳብለው ልናገኛቸው የምንችል የንብረት ማስተላለፍያ አገባብ ነው፡፡
የአላባ መብት መሰረቱ (subject matter) ግዙፍነት ያላቸው (corporeal things) የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው (incorporeal things) እንደ ቅጅ መብትና ፈጠራ ያሉ የንብረት መብቶች ናቸው፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1204/1/፣ 1126፣ 1309/1/ /2/ እና 1347 እና ቀጠቀዮቹ) የአላባ መብት ምንጭ (source) ውል፣ ኑዛዜ ወይም ሕግ ሊሆን ይችላል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1184 እና 1185) የአላባ መብት መሰረት የሚንቀሳቀስ ንብረት በሆነ ግዜ ተጠቃሚው ንብረቱን በእጅ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1186/1/) የአላባ መብት መሰረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜ ግን የአላባ መብት ምንጭ የሆነው ውል ወይም ኑዛዜ መመዝገብ ስለሚኖርበት በይዞታው ስር በማድረግ ብቻ የአላባ ተጠቃሚነትን መብት ሊያገኝ አይችልም፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1184 እና 1185) በኢትዮጵያ ፍ/ብሄር የፍትህ ስርዓት የአላባ መብት ከህግ የሚመነጨው ከማይንቀሳቀስ የውርስ ሃብት ጋር በተያያዘ መንገድና፣ ለአካለ መጠን ባላደረሰ ልጅና ሞግዚቱ ወይም በባልና ሚስት መካከል ያለን ግንኙነት መሰረት በማድረግ ሲሆን የሚተላለፍበት ስርዓትም በማግኘት (acquisition, Possession etc.) በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1310 እና 1311 ላይ በተደነገገው መሰረት ነው፡፡
የንብረት ባለቤትነት መብት (ownership right) ሶስት መሰረታዊ መብቶችን ማለትም የሌሎችን መብት ሳያውኩ (ሳይነኩ) (without impairing any one’s right) እንደፈለጉ ማድረግ (abusus right) በንብረት የመገልገልን (usus) እና ፍሬውን የመሰብሰብና የመውሰድ (fructus) መብቶችን የሚያጐናፅፍ ሲሆን የአላባ መብት የንብረቱ ባለቤት (owner) የባለቤትነት መብቱን (ownership right or abusus right) ለራሱ በማስቀረት የተቀሩትን ሌሎች ሁለት መብቶች ማለትም በንብረቱ የመገልገልና (right of using) እና ፍሬውን ሰብስቦ የመውሰድ (enjoying the thing) ለአላባ ተጠቃሚው በማስተላለፍ የሚገኝ መብት ነው፡፡ የአላባ መብት ተጠቃሚው በሂወት አስካለ ድረስ ሊገለገልበት የሚችል መብት እንጂ እንደሌሎቹ የንብረት መብቶች ወደ ተወላጆቹ ወይ ወላጆቹ በውርስ ሊተላለፍ የሚችል መብት አይደለም፡፡ይህ ማለትም አንድ ሰው በንብረት ያላውን የባለቤትነት መብቱን ተጠቅሞ የአላባ መብት ለሌላ ሰው በኑዛዜ መስጠት የሚችል ቢሆንም ይህ የአላባ ተቀባይ በሚሞትበት ጊዜ ይህን የአላባ መብቱ ለወራሾቹ በኑዘዜ ማሰተላለፍ አይችልም ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322(1)) አንዱ የአላባ መብት ማስገኛ መንገድ ውል እንደምሆኑ መጠን የአላባ መብት በአላባ ሰጪና ተቀባይ መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚቋቋም የንብረት መብት በሚሆንበት ጊዜ በተዋዋዮቹ መካከል በርካታ መብቶችና ግዴታዎች (bundle of rights and duties) ያሉበት ነው፡፡
የአላባ ተጠቃሚ መብትና ግዴታ
Øበአላባ የተሰጠውን መብት ለመገልገል ንብረቱን በራሱ ወይም በወኪሉ አማካይነት በይዞታው ስር ማድረግና በዚህ መብቱ ለመስራት በባለቤቱ፣ በወራሾቹ ወይም ንብረቱን በእጃቸው ላይ ባደረጉ 3ኛ ወገኖች ላይ የባለይዞታነት ክስ (possessory action) የመመስረት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1311 እና 1341)
Øየማይንቀሳቀስው ንብረት ለህዝብ ጥቅም ሲባል በመንግስት በሚወሰድበት ግዜ የአላባ ተጠቃሚው በመልቀቅ ምክንያት የተሰጠውን ካሳ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319(2))
Øየአላባ ተቀባዩ ያለውን መብት መሰረት በማድረግ የመድን ሽፋን የመግዛትና ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320 እና ን/ህ/ቁ 654)
Øፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 የአላባ ተጠቃሚው የአላባ ንብረቱን በቁጥጥር ስር ማደረግ አለበት ሲል እንደሚደነግግ ሁሉ የአላባ ተጠቃሚው ይህን የአላባ መብት የሚያገኘው ከህግ ከሆነ መብቱን የሚያገኘው ወድያውኑ (automatic) ነው፡፡ መብቱ የመነጨው ከውል በሆነ ጊዜ ስመምነቱ እንደተፈፀመ፣ በውርስ ከሆነም ውርሱ ሲከፈት፤ በኑዛዜ ከሆነ ደግሞ የውርስ ንብረት የማጣራቱ ስራ እንዳለቀ የአላባ መብቱን ያገኛል፡፡
Øየአላባ መብቱ መሰረት የሆነው ነገር የፍጆታ እቃ (consumable good) ከሆነና ሳይጐዳ በመብቱን ሊሰራበት የማይችል በሆነ ግዜ የንብረቱ ባለቤት ይሆናል፡፡ ይህ ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት እንደፈለገ ያረገዋል(will have the right to dispose) ማለት ነው:: ለምሳሌ፡- የአላባ መብቱ የተሰጠው በወይን ላይ ከሆነ ወይኑን የመጠጣት፣ የድንጋይ ከሰል ከሆነ በድንጋይ ከሰሉ የመገልገልና የመጨረስ፣ ገንዘብ ከሆነም ገንዘቡን ወደ ሌላ የማስተላለፍ መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1327(1))
Øየአላባ መብቱ የተሰጠው ፍሬ ለመሰብሰብ ከሆነ የአላባ ተቀባዩ የተፈጥሮ ፍሬዎች (natural fruits) እንደ ጥጃዎች (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1171 እና 1328(1)) ፣ ሲቪል ፍሬዎች (civil fruits) እንደ ኪራይ፤ ወለድ ወይም የተጣራ ትርፍ (interests, arrears or dividends) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331 እና 1347) እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች (periodical products) (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1170/2/ እና 1333) የመሰብሰብ መብት ይኖረዋል፡፡
Øየአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ሃብቶች ወይም የአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ነገሮች (pre-mature things) ሲበስሉ ወይም ውሉ ሲቋረጥ የበሰሉ ካሉ የአላባ ተጠቃሚው እንደሆኑ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1328(1))
Øየአላባ ንብረቱ ለምሳሌ እንደ ቤተ መፅሐፍ ፣ ፈረስና የቤት እቃ ያለ ሲሆን የአላባ ተጠቃሚው ይህንን ንብረት ለሌላ 3ኛ ወገን በኪራይ (lease) የመስጠት መብት ይኖረዋል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331)
Øበአላባ የተሰጠን ንብረት መሬት ወይም ቤት ሲሆን ከተኸራየ በኋላ የገዛ ወይም በዋስትና የያዘ ሰው ቢኖሩም ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት የአላባ ተጠቃሚው በአላባ መብቱ ይሰራበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1332(2))
Ø
Øአላባ ተቀባዩ የዋስትና (mortgage) ዋናው እዳ (principal debt) የመክፈል ግዴታ የለበትም፡፡ የከፈለ እንደሆነ ግን አላባ ሰጪውን ገንዘቡ እንዲመልስለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1340 (2))
Øየማይንቀሳቀስ ንብረት ማስለቀቅንና የመድህን ካሳ ክፍያን መሰረት በማድረግ በሚነሱ ክርክሮች መብት አለኝ ብሎ በክርክሩ ውስጥ ልግባ የማለት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 ፤1341፣ ን/ህ/ቁ. 654 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 33(2))
Øበአላባ በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ነገር የሰራው ካለ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ነቅሎ የመውሰድ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346(2))
Øበአላባ የተሰጠው ንብረት ከእጁ ወይም ከይዞታው ከወጣ እንዲመለስለት ወይም ሁከቱ እንዲወገድለት የባለ ይዞታ ክስ (possessry action) የመመስረት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1149፡ 1311፡1341 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 33(2))
Øበአላባ የተሰጠው ንብረት ቢወድምም የአላባ ተጠቃሚው በትራፊው ወይም በቀሪው ዎና (ruins) መገልገል ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1344)
Øበአላባ የተሰጠውን ንብረት የመስጠትና የኪራዩን ገቢ የመስብሰብ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331) ስለዚህም የአላባ ግንኙነት እጅግ በርካታ መብቶችን ሊያስገኝ የሚችል የንብረት ግንኙነት እንደሆነ ከንብረት ህጉ ይዘት ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ከግዴታ አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ነው፡፡
vበአላባ የተሰጠውን ንብረት ደረጃውን ጠብቆ በቅን ልቦና የማስተዳደርና የተቋቋመበትን አላማ መሰረት በማድረግ በአላባ መብቱ የመገልገል ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1312 ፣ 1326 ፤ 1328 እና 1330)
vእንደ የጣራ ማፍሰስ፣ መለስተኛ የግንብ መሰንጠቅ፣ የቀለም ቅብ ያሉ ተራ የጥገና ስራዎች የመስራት ግዴታ አለው፡፡ የአላባ መብቱ የተገኘው በውርስ (inheritance) ሲሆን የአላባውን ንብረት ዕዳ ወይም ወለድ የመክፈል ግዴታና መደበኛ ወጪ እንደ ግብር ያሉ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የግብር መክፈል ግዴታ በመፈፀም ላይ ያለ የአላባ ተጠቃሚ ለተከታታይ 15 ዓመታት ቢከፈልም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1168 በመያዝና መገልፈገል ብቻ (usucaption) የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ አያደርገውም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1313 እና 1314)
vየአላባ ውሉ ሲቋረጥ የአላባው ንብረት በሂደት የሚመጣውን መጥፋትና መበላሸት (loss and deterioration) ሳይጨምር እንደነበረው ለባለቤቱ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1317 ፣ 1326፤ 1327(2) ፣1343 ፤ 1346 እና 2027)
vየአላባ ተጠቃሚ በአላባ የተሰጠውን ንብረት በሚንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (pledge)፣ በማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (mortgage)፣ በንብረት አገልግሎት (servitude) ወይም ለሌላ ሰው በአላባ የመሰጠት ወይም የማስተላለፍ መብት ቢኖረውም ይህን መብቱን በስራ ላይ በሚያውልበት ግዜ የባለቤቱን መብት መጉዳት (impair) የለበትም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 እና 1324)
vየአላባ መብት ቀሪ በሚሆንበት ግዜ የንብረቱን ዋጋ ሳይሆን ንበረቱን በዓይነት ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)
vበአላባ የተሰጠው ንብረት በሶስተኛ ወገኖች እጅ ሲገባወይም የጣለቃ መግባት (interference) ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ለባለቤቱ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1342)
vበአላባ የተሰጡት እንስሳት በሚሆንበት ግዜና ከእነዚህ የተወሰኑት በአደጋ ወይም በበሽታ ያለቁ እንደሆነ የነዚህን ምትክ ከሚወለዱት የመተካት ግዴታ አለበት፡፡ እነዚህ እንሰሳት በጠቅላላ በአደጋው ወይም በበሽታው ካለቁ ግን ቆዳቸውን የማስረከብ ወይም የቆዳውን ዋጋ ለባለቤቱ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1345)
vመሰረታዊ ለውጥ ያለማድረግ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1330)
vንብረቱን የማቀብ (preserve) ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1309)
vለንብረቱ ለማስተዳደር፡ ፍሬውን ለማግኘትና ለመጠቀም የሚያስፈልገውን ወጪና ወለድ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1313) ስለዚህ አንድ የአላባ ተጠቃሚ በርካታ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ግዴታዎችም ያሉበት ነው፡፡
የአላባ ሰጪ መብትና ግዴታ
ü የአላባ ውል ግዜው ሲያልቅ ንብረቱን የመረከብ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322 እና 1327)
ü በአላባ መብትነት በሰጠው ንብረትና በመብቱ ላይ ተፅእኖ (jeopardy) አለ ባለ ግዜ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብቶ መብቱ እንደነበረው እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324)
ü ልዩ ወጪዎች እንዲከፍል በሚጠየቅበት ግዜና ይህን ወጪ የአላባ ተጠቃሚው በብድር መልክ የማይሰጠው ከሆነ በአላባ ሰጥቶት ከነበረው ንብረቱ ገሚሱን በመሸጥ እዳውን የመክፈል መብት፡፡
ü በአላባ የሰጠውን ንብረት በዋስትና (mortgage) የመስጠት መብት፡፡
ü በአላባ ተጠቃሚው ዋስትና (Securities) እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324)
ü የአላባ ተቀባዩን መብት ሳይጋፋ በንብረቱ የማዘዝ መብት አለው ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323)
ü የባለቤትነት መብቱን መሰረት በማድረግ የመድን ዋስትና የመግዛትና የመድን ሽፋን የተሰጠው አደጋ እውን ሲሆን (whenever the risk materialises) ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320)
ü በአላባ ከተሰጠው ንብረት ጋር ያለአግባብ የተላለፈ ንብረት ካለ የማስመለስ መብት፡፡
ü ለአላባ ተቀባይ እንዲሆን ከተወሰነው በላይ ፍሬ ወይም ትርፍ ከተገኘ የመውሰድ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1328(2) እና 1348)
ü በአላባ በተሰጠው መሬት ውስጥ የተቀበረ ገንዘብ (treasure) ከተገኘ ባለቤት በመሆኑ የመውሰድ መብት፡፡( ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1329)
ü የአላባ ተጠቃሚው በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ስራ ሰርቶ ከሆነ የአላባ መብቱ ከተቋረጠ ግዜ ጀምሮ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ንብረቱን ለማንሳት ካልጠየቀ አላባ ሰጪው የዚህ ተጫማሪ ስራ ባለቤት ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346/2/ ) ከግዴታ አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩታል፡፡
በአላባ የሰጠውን ንብረት ለአላባ ተጠቃሚው የማስረከብ ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)
የአላባ ውሉ በፅሑፍ እንዲሆንና እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ አለው፡፡
በአላባ የተሰጠው ንብረት ጥገና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ሲሆን ወጪውን የመሸፈን ግዴታ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1338)
የጦርነት መዋጮ፣ የሰራዊት ሰፈር፣ ቆሻሻ ማስወገጃ ወጪ ወይም ረግረጐች የማድረቅ የመሳሰሉ ልዩ ወጪዎች (extra ordinary charges) የመክፈል ግዴታ የአለባ ሰጪው ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.
በመደበኛ አገልግሎት ምክንያት ዋጋው ቢቀንስ (depreciation caused by ordinary wear and tear) የንብረትን ማሽቆልቆል መሰረት በማድረግ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረግ ወጪ ቢኖር የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1326 )
የአላባ ግንኙነት ቀሪ ስለመሆን
የአላባ ተጠቃሚው በውሉ ያሉትን ግዴታዎች የጣሰ አንደሆነ የአላባ መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 (3) እና 1324)
የአላባ ተጠቃሚው ሲሞት የአላባ መብት በውርስ የሚተላለፍ መብት ባለመሆኑ ምክንያት ቀሪ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የአላባ ተጠቃሚነት መብቱ የተሰጠው ለባልና ሚስት በጋራ በሆነ ጊዜ የአንደኛው መሞት የአላባ ተጠቃሚነቱን መብት ሙሉ ለሙሉ ቀሪ አያደርገውም፡፡ በሌላ አነጋገር በሂወት ካለው ስው ጋር የአላባ ግንኙነቱ ይቀጥላል ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)
የአላባ ውሉ ግዜ ሲያልቅ በአላባ ተጠቃሚ የመሆን መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)
የአላባ መብት ተጠቃሚነት መብት የተሰጠበት ነገር እንደ ጥሬ ገንዘብ ባሉ አላቂ ነገሮች (consumable goods) ሲሆንና ሲያልቁ የአላባ መብት የተቋቋመበት ውል ቀሪ ይሆናል፡፡
የአላባ ተጠቃሚው በራሱ ፍላጐት በግልፅ የአላባ ተጠቃሚነት መብቱን ሲተው (express waiver) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323(2))
በአላባ የተሰጠው ንብረት ሙሉ ለሙሉ ሲወድም የአላባ ጥቅም መሰረት (subject matter of the usufract) በሌለበት ሁኔታ መብቱ ሊኖር ስለማይችል የአላባ ግንኙነቱን እንዲቀር ያስገድዳል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319፣ 1343) ስለዚህ የአላባ ግንኙነት እንደ ሁሉም በህግ ፊት ዋጋ ያለው ተግባር ወይም ከህግ የሚመነጭ መብት በአንድ ወቅት ሊቋረጥ የሚችል ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በመቋረጡ የሚኖረው ውጤትም፡-
vከአላባ ተጠቃሚው ጋር የተደረጉ ውሎች ውጤት አልባ (extinguished contracts) ይሆናሉ፡፡
vበአላባ የተሰጠው ንብረት የማይንቀሳቀስ ንብረት በሆነበት ግዜና ተከራይቶ ወይም በዋስትና ተሰጥቶ ከቆየ የውሉ ግዜ በማለቁ ብቻ የአላባ መብቱ ቀሪ ሊሆን ስላማይቻል 3ኛ ወገኞች ለሶስት ዓመት የግድ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የአላባ መብት ግዙፍነት ባላቸው የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም ግዙፍነት በሌላቸው የንብረት መብቶች ላይ ሊመሰረት የሚችል ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው የዜጐች በንብረት የመገልገል፤ፍሬ የመሰብሰብንና መውሰድን መብት የሚያጎናፅፍ ከውል ፤ ከህግ ወይም ከኑዛዜ የሚመነጭ ግንኙነት ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከውል፤ ከህግና ከኑዛዜ የሚመነጩ በርካታ የአላባ ተጠቃሚና አላባ ሰጪ መብቶችና ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ንበረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት (juridical acts) ወይም ከህግ የሚመነጩ መብቶች (legal rights) ተመስርቶ ቆይታው ይርዘም ይጠር ሰዎች በመብቱና ግዴታው ሲሰሩበት ከቆዩ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ቀሪ የሚሆን ንብረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነትም ነው፡፡