- Details
- Category: Property Law
- Hits: 13417
የምዝገባ አላማዎች
በኢትዮጵያ የፍ/ብሄር ፍትህ ስርዓት የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በዜጎች የንብረት መብት ጥበቃ ፋይዳው የጎላ ቢሆንም እምብዛም ፍታብሄር ህጉ በሚደነግገው መሰረት ሲሰራበት አይታይም:: የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን በማስመልከት የተለያዩ አገሮች የተለያየ አሰራር ይከተላሉ:: ለምሳሌ ፈረንሳይ transcription የሚባለውን እሰራር ስትከተል አውስትራልያ matriculation የሚባለውን አሰራር ትከተላለች:: በአገራችን ያለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ስር’ዓትም በተዋዋይ ወገኖች የቀረበውን ሰነድ ቅጂ ተቀብሎ የመዝገቡ አካል የማድረግ አሰራርን የሚከተል በመሆኑ የ transcription አሰራር የሚትከተል ነው ማለት ይቻላል :: የማይንቀሳቀስ ንብረቶች ምዝገባን በሚመለከት በፍ/ብሄር ህጉ ከቁጥር 1553-1646 ባሉ ድንጋጌዎችና በፍ/ብ/ህ/ቁ በ1723፤ 2878 እና 3052 ተደንግጐ የምናገኘው ሲሆን ህጉ ለማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ልዩ ጥበቃ መስጠት የፈለገበት ምክንያት እነዚህ ንብረቶች ባለይዞታው መብቱን ሲያገኝ ወይም በሆነ ምክንያት ወደ ሌላ ሶስተኛ ወገን በሚያስተላልፍበት ወቅት የመመዝገብ ስልጣን በተሰጠው መንግስታዊ አካል ካልተመዘገበ ህግ ፊት የሚፀና መብት እንዳይኖረው በማድረግ ዜጐች በዚህ ግዙፍነት ያለው ንብረት ያላቸው መብት ከፍላጐታቸው ውጪ በሆነ መንገድ እንዳያጡ ጥበቃ ለመስጠት ነው፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በርካታ የራሱ አላማዎች ያሉት ቢሆንም ዋና ዋናዎቹን ወስደን ያየን እንደሆነ:-
1.ዜጐች በማይንቀሳቀስ ንብረት ያላቸው መብት በተለይ ወደ ሌላ ወገን በሚያስተላልፉበት ግዜ በፈቃዳቸው የተከናወነ መሆኑን ከመዝጋቢው አካል ፊት ቀርበው የሚከናወን በመሆኑ ንብረታቸው ከዚህ አሰራር ውጭ የማያጡ መሆኑን ተገንዝበው ሙሉ ዋስትና እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
2.የማይንቀሳቀስ ንበረትን መሰረት በማድረግ የሚከናወኑ የሽያጭና ግዢ ውሎችን በምዝገባው አስረጂነት የኢኮኖሚ ግንኙነትቱን የተቀላጠፈና አስተማማኝ እንዲሆን በማድረግ በተዋዋዮቹ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖርና መጥፎ ልቦና ቢፈጠርም እንኳ አስተማማኝ ማስረጃ ሆኖ ስለሚያገለግል ሌላውን ወገን ከመጀመርያው ጀምሮ አስቦበት እንጂ ዘው ብሎ እንዳይገባ የማድረግ አላማ (refraining objective) ያለው ነው፡፡
3.የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን ከፍ/ብ/ህ/ቁ.1723 ይዘት አንፃር ስንመለከተው የምዝገባው ውጤት ውሉ ዋጋ እንዲኖረው (ad validitatum) የሚያስፈልግ እንጂ ለማስረጃ ብቻ (ad probtionum) የሚያስፈልግ ባለመሆኑ ከህጉ በስተጀርባ ያለው (rationale) ህዝባዊ ፖሊሲ ለማይንቀሳቀስ ንብረት መብት ከፍተኛ ጥበቃ የሚሰጥ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
-
- 4.የማይንቀሳቀስ ንብረት ካለው የኢኮኖሚ ፋይዳ በመነሳት ህግ ልዩ ጥበቃ ሲያደርግለት የንብረት ባለይዞታነት መብት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በምናስተላልፍበት ግዜ በንብረት መዝገብ ላይ ንብረቱ በመያዣ ተይዟል አልተያዘም? በዕዳ ታግዷል ወይስ ነፃ ነው? ንብረቱ የግል ነው ወይስ የጋራ ንብረት? ንብረቱ የተገኘበት አግባብ በግዢ፣ በሊዝ፣ በውርስ፤ በስጦታ፣ በምሪት? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ዙርያ ለሶስተኛ ወገኖች ግልፅ የሆነ መረጃ (information) የመስጠት አላማም ያለው ነው፡፡ በመሆኑም የምዝገባው መኖር:-
የሰነድ መሰረዝ መደለዝን ያስቀራል::
ማጭበርበርን ይከላከላል::
በሀሰት የሚዘጋጁ ሰነዶችን ይከላከላል::
በንብረት ጥቅም ላይ ሊመጡ የሚችሉትን አደጋዎች ይከላከላል::
ስለዚህ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ አላማ ከንብረት ዋስትና ጋር፣ ከህዝባዊ ፖሊሲ፤ ከማስተላለፊያ ስርዓትና የሶስተኛ ወገኞች መብት አንፃር ሲታይ የኢኮኖሚ ፋይዳው ሳንካ ያልበዛበት ምቹና የባለቤትነት ዋስትና ያለው ህበረተሰባዊ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ከፍ/ብሄር ህግ አንፃር
ቀደም ሲል እንደተገለፀው የማይንቀስቀስ ንብረት ምዘገባን በማስመልከት በፍ/ብሄር ህጉ ከቁጥር 1553-1646 ባሉ ድንጋጌዎችና የማንቀሳቀስ ንብረትን ከአንዱ ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍን ስርዓት መሰረት በማድረግ በፍ/ህ/ቁ. 1723፤2878 እና 3052 ላይ ተደንግጐ የምናገኘው ነው፡፡ የፍ/ብሄር ህጉ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በንጉሱ ግዜ የነበረውን አደረጃጀት ታሳቢ በማድረግ በየአውራጃው እንደሚቋቋምና ሁለት የተለያዩ መዘገቦች ማለትም አንዱ የባለቤትነት መዝገብና ሌላው የመያዣ መዝገብ እንደሚኖር ይደነግጋል፡፡ እነዚህ መዛግብት ከቦታ ቦታ መዘዋወር እንደማይፈቀድና ለህዝብ ግልፅ መሆን አለባቸው የሚል ለሶስተኛ ወገኖች ጥበቃ የሚሰጥ መርህን የተከተለ ነው፡፡
የባለቤትነትን መብት መሰረት በማድረግ የሚቋቋም መዝገብ የአንድ ወይም ብዙ ባለመብቶች መብት ለማወቅ፣ ለማስተላለፍ፣ ለመለወጥ፣ ለማስቀረት በሂወት ወይም በሞት ግዜ የተደረጉ ውሎችን በግልፅ ይሁን በግል የተደረጉ በመዝገቡ መፃፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም በባለሃብትነት መዝገቡ ላይ የተደረገ ሽያጭ፣ ኑዛዜ፣ ስጦታ፣ የኑዛዜ ስጦታ መሰረት ያደረጉ ውሎች እና እነዚህ ውሎች የተሰረዙበት፣ የተሻሩበት ወይም የሚያስቀሩ በፍርድ ቤት የተሰጡ ፍርዶች ካሉ እንዲሁም በመፋለም ክስ ላይ ፍ/ቤት የሰጠው ፍርድና ገንዘብ ጠያቂዎች ባስያዙት የማይንቀሳቀስ ንብረት የሐራጅ ሽያጭ ላይ የተሰጡ ፍርዶችን በመዝገቡ መፃፍን እንደ ግዴታ የሚጥል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአላባ ጥቅምን መስጠት፣ መቀነስ፣ መሰረዝና የንብረት አገልግሎት (servitude) ለማቋቋም፣ ለማሳወቅ፣ ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት የሚደረጉ ፅሁፎች በመዝገቡ መፃፍ ይኖርባቸዋል፡፡
በማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መዝገብ ላይም የመያዣ መብት ለማቋቋም፣ ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት የሚደረጉ ፅሁፎችና የመያዣ ዋስትና ለመረጋገጥ የተፃፈውን ፅሁፍና የዚህ መብት በህግ የታወቀበትን የቅደም ተከተል መብት ለማስተላለፍ የተፃፉትን ፅሁፎች ያካተተ መሆን አለበት፡፡
ከፍ ብሎ እንደተገለፀው የፍ/ብሄር ህጉ ሁለት ዓይነት የንብረት ምዝገባ እንደሚኖር ከመደንገጉ በተጨማሪ የአመዘጋገብ ስርዓቱን በማስመልከት የህዝብ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት እና የጋራ ንብረት በሚል ይከፍላቸዋል:: አንድ የህዝብ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት እላዩ ላይ ግዙፍነት ያላቸው እንደ ህንፃ ወይም ተክሎች ከሌሉበት በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ መመዝገብ እንደሌለበት ሲደነግግ የጋራ የሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትን ምዝገባ በማስመልከት በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ የእያንዳንዳቸው ሰም ያለበት በተለያየ ገፅ ላይ መመዝገብ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ንብረቱ የተፈጥሮ ሰው ሃብት በሆነበት ግዜ እንዲመዘገብለት ጥያቄ የቀረበለት ወገን፣ የማይንቀሳቀስ ንብረቱን ለመለየት አስፈላጊ ከሆነ እንደ የቦታው አዋሳኝ፤ ንብረቱ የሚገኝበት የአስተዳደር ክልል፣ ወዘተ የመሰሉ መግለጫዎች፣ የንብረቱ ባለቤት ሙሉ ስም፣ የባለሀብትነት መብት ማረጋገጫ ሰነዶች ዓይነት በማጣቀሻ ቁጥራቸው እና ተያያዥነት ያላቸው ማጣቀሻ ፅሁፎች ከነቁጥራቸው ይመዘግባል፡፡ የማይንቀሳቀስ ንብረቱ የህጋዊ ሰውነት መብት ያለው ተቋም በሚሆንበት ግዜ ደግሞ የድርጅቱ መጠርያ ስም በመዝገቡ ላይ መመዝገብ ይኖርበታል፡፡
የምዝገባ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኃላ ንብረት መዝጋቢዎች ፍ/ብ/ህ/ቁ 1562 እና 1563 በሚያዘው መሰረት ባለሃብቶቹ ስለንብረታቸው ምዝገባ በማስመልከት መግለጫ እንዲሰጣቸው በሚጠይቁበት ግዜ የተፈላጊው ሰነድ ግልባጭ መሰጠት አለባቸው፡፡ በመሆኑም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብቶች ይህን ሰነድ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ይህም ጠቅለል ባለመልኩ ሲታይ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ የአንድን ንብረት ባላቤትነት (ባለይዞታነት) ከማረጋገጡ ባሻገር በዚህ መብት የሚከናወኑ ስራዎችን እንደ የባለቤትነት መብት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍ መብት፤ ዕዳና መያዣ የመሳሰሉ በመያዝ ሶስተኛ ወገኖች ከባለንብረቱ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተና አስተማማኝ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ እነዚህ ለህዝብ ግልፅ መሆን ያለባቸው መዛግብት የራሳቸው የአመዘጋገብ ስርዓትና ፎርም ያላቸውና ጥንቃቄን የሚጠይቁ የመሆናቸውን ያህል የሚከናወኑት በሰዎች እንደመሆኑ ለተለያዩ ግድፈቶችና ከመጥፎ ልቦና በመነሳት ችግር ለሚፈጥሩ የግል ጥቅም አሳዳጆች በእጅጉ የተጋለጡ በመሆናቸው በማስረጃነት በሚቀርቡበት ጊዜ የፍትህ አካላት ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ሊመዝኗቸው ይገባል፡፡
የምዝገባ ፅሁፎችን ማቃናትና መሰረዝ
ከአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ጋር የተያያዘ የህትመት ጉድለት ካለ ዓቃቤ መዝገቡ ማቃናት የሚችል ቢሆንም ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1622 ከሚያዘው ውጭ የሚደረግ ማቃናት ግን ፈራሽ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ውጭ የሚደረግ የማቃናት ስራ መከናወን ያለበት በፍ/ቤት ትእዛዝ ብቻ ነው፡፡ የማቃናቱ ስራ ሲከናወን የነበረውን ቃል መሰረዝ የግድ እንደሚል ሁሉ ተሰርዟል የሚል ቃልም ይፃፍበታል፡፡ የዚህ መቃናት ህጋዊነት ለማረጋገጥ በፍ/ቤት የተሰጠው ፍርድ ከአስረጂው ጋር በቤተመዛግብት መቀመጥ አለበት፡፡ የዚህ መቃናት ህጋዊ ውጤት መቆጠር የሚጀምረው የማቃናቱ ስራ ከተከናወነበት ቀን ጀምሮ ሲሆን መቃናቱ ዋጋ አልባ የሚሆነው በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1628 የተዘረዘሩት መስፈርቶች ሳይሟሉ የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ እነዚህ አንድን ምዝገባ ዋጋ አልባ ወይም ፈራሽ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በተሟሉበት ሁኔታ ማንኛውም ባለመብት ነኝ የሚል ወገን የተደረገውን መቃናት እንዲሰረዝለት ለፍ/ቤት ሲያመለክት ፍ/ቤት መቃናቱ እንዲሰርዝ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንደዚህ በሆነበት ግዜ በታተመው ፅሁፍ ላይ የተሰረዘበትን ቀንና ትእዛዙን የሰጠው ፍ/ቤት ሰም በሁለት የተመሳቀሉ መስመሮች ማሃል ተሰርዟል የሚል ቃል ይፃፍበታል፡፡ ቀደም ሲል ሁለት መዘገቦች እንደሚኖሩ እንደተጠቀሰው ሁሉ የመያዣ መብትን መሰረት በማድረግ ለተወሰነ ግዜ የተደረገ ምዝገባ በሚሆኑበት ግዜና ምዝገባው በፍ/ብ/ህ/ቁ 3058(2) መሰረት ካልተራዘመና በፍ/ብ/ህ/ቁ 3068(1) መሰረት አስር ዓመት ካለፈው የአስራረዙ ስርዓት ፍ/ብ/ህ/ቁ.1632 በሚያዘው መሰረት ሲሆን ይሄውም ለመሰረዝ የፍ/ቤት ትእዛዝ ሳያስፈልገው ባለስልጣኑ በራሱ ሊሰርዘው ይችላል፡፡ ስለሆነም ዓቃቤ መዝገቡ አንድን የህትመት ቃል መሰረዝና ማቃናት የሚቻል ቢሆንም ህጉ ከሚያዘው ውጭ ማቃናት ስርዙን ዋጋ አልባ ወይም ፈራሽ ሊያደርገው እንደሚችልና ለማቃናት የፍ/ቤት ትእዛዝ መኖርን እንደሚጠይቅ ለመሰረዝም የማይንቀሳቀስ ንብረትን መሰረት ያደረገ መያዣን የሚመለከት ካልሆነ በስተቀር ስርዙ መከናወን ያለበት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1630 መሰረት በፍርድ ቤት ነው፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ውጤት
የማይንቀሳቀስ ንብረት መመዝገብ በህግ ፊት ለሚነሳ ክርክር የማስረጃነት፣ የንብረቱን አስተዳደር የሚመለከት ለፍ/ቤት፣ 3ኛ ወገኖች፣ ባለጥቅሞች መረጃ የመስጠት ውጤት ያለው ሲሆን ከነዚህ ጠቅለል ያሉ ውጤቶች በተጨማሪ ዝርዝር ውጤቶችም ያሉት ነው፡፡ ከነዚህ ጥቂቶቹን ወስደን ያየን እንደሆነ:-
በማይንቀሳቀስ መዘገብ ላይ አንድ ፅሁፍ በመፃፍ ብቻ ሌላው ወገን የይርጋ ጥያቄ እንዳያነሳ አይከለክለውም:: ይህ የሚሆንበት ምክንያትም የዚያ ፅሁፍ መመዝገብ ብቻ የባለመብትነት መብት ስለሚያስገኝ ወይም ስለሚያሳጣ ነው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1637 እና 1639)
አንድ ተከራካሪ ወገን በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ የተመዘገበውን ፅሁፍ አላውቅም በማለት ብቻ በመከላከያነት አቅርቦ ሊከራከር አይችልም:: ሆኖም ግን ሊያውቅ ያልቻለው በአመዘጋገቡ ላይ የአቃቤ መዝገቡ ወይም በመንግስት ጉድለት ምክንያት ከሆነ ሃላፊነቱን የሚወሰዱት እነሱ ይሆናሉ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1640)
በሁለት ፅሁፎች ክርክር ቢነሳ መጀመርያ በማይንቀሳቀስ መዘገብ ያስመዘገበው ሰው የባቤትነት መብቱን የሚያገኝ ሲሆን ሁለቱ የተመዘገቡት በአንድ ቀን በሚሆኑበት ግዜ በማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ የማንኛቸው ቁጥር እንደሚቀድም በማየትና የቀደመውን ቁጥር በመውሰድ መብቱ የቀደመ ቁጥር ላገኘው ሰው ይሰጣል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ1642)
የባለቤትነት፣ ግዙፍነት መብት የሚያረጋግጡ፣ የሚያስተላልፉ፣ የሚለውጡ ወይም የሚያስቀሩ ፍርዶች የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚገኝበት ስፍራ ባለ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዘገብ መመዝገብ ይኖርበታል ካልተመዘገበ ውጤት አይኖረውም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1643)
በመጥፎ የማይንቀሳቀስ ንብረት መዝገብ ላይ ማስመዘገብ በዚህ መመዝገብ ጉዳት ደርሶብኛል የሚል ወገን የደረሰበት ጉዳት መሰረት በማድረግ የጉዳት ኪሳራ ከሚጠይቅ በስተቀር ምዝገባውን ዋጋ አልባ የማድረግ ውጤት አያስከትልም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1644)
የአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት በመዝገብ ባለመመዝገቡ ምክንያት ሶስተኛ ወገኖች መቃወሚያ ሊሆናቸው ባልቻለበት ጊዜ ማናቸውም ሰው ለሶስተኛ ወገኖች የሚሆን መብት ካላስመዘገበው ሰው ሊያገኝ አይችልም፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ መብቱን ያገኘበት ሰነድ ከማስመዝገቡ በፊት መብቱን የሰጠው ሰው ያንን የማይንቀሳቀስ ንብረት መብት ያገኘበትን ሰነድ ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1645)
የማይንቀሳቀስ ንብረት መዘገብ አቃቤ መዘገብ በባለሀብቱ የቀረበውን መዝግቦ ስለተደረገው ምዝገባ በ8 ቀን ግዜ ውስጥ ግልባጩን የማሳወቅ ግዴታ ያለው ሲሆን ይህን ባለማደረጉ በሶስተኛ ወገኖች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሃላፊ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ1646)
ስለዚህ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባን ከፍ/ብሄር ህጉ አንፃር ስናየው በርካታ ጥቅሞች የሚያስገኝ፣ መብቶችና ግዴታዎችን የሚጥል የራሱ የሆነ ህጋዊ ውጤት ያለው ነው:: ያለው አሰራር የቱን ያህል የህጉን አካሄድ የተከተለ ነው ብለን ያየን እንደሆነ ግን በመዝጋቢ አካልም ሆነ በፍ/ቤቶች አካባቢ እምብዛም ሲሰራበት የሚታይ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና በንብረት መብትና ግዴታ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑን በማጤን ስራ ላይ ልናውለው የሚገባን ነው፡፡
ከአዋጅ ቁጥር 456/97 አንፃር
1. የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቓቀምን መሰረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 456/97 የገጠር መሬት ምዝገባን መሰረት በማድረግ በአንቀፅ 6/1/ ላይ
በግል፣ በወል፣ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይዞታዎች ያሉ የገጠር መሬቶች እንደ ሁኔታው ባህላዊና ዘመናዊ የቅየሳ መሳሪያዎችን በመጠቀም የመሬት ስፋታቸውና የለምነት ደረጃቸው በክልልና በየደረጃው በተቋቋሙ የመረጃ ማእከላት እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡ ሲል በአንቀፅ 6/5/ ላይም
የገጠር መሬት በማን ይዞታ ስር እንደሚገኝ ከማን መሬት ጋር እንደሚዋስን፣ ደረጃው ምን ዓይነት እንደሆነ፣ ለምን አገልግሎት እንደሚውልና ባለይዞታው ምን መብትና ግዴታዎች እንዳለበት የሚገልፅ መረጃ ተመዝግቦ አግባብ ባለው ባለስልጣን እንዲያዝ ይደረጋል፡፡
በማለት የገጠር መሬት የማይንቀሳቀስ ንብረት እንደመሆኑ መጠን በምዝገባ በአርሶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መካከልና መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በአጠቃላይ በአጐራባች መሬት ሊነሳ የሚችለውን ውዝግብና ከባለይዞታነት መብት የንብረት መፋለም ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ የሚችሉ ችግሮች በሚቀርፍ መልኩ የመሬት ባለይዞታነት መብት ምዝገባ እንደሚከናወን ይደነግጋል:: ይህን ምዝገባ መሰረት በማድረግ የባለይዞታነት ማረጋገጫ ደብተር እንደሚሰጥና የማይንቀሳቀስ ንብረቱ የጋራ ንብረት በሚሆንበት ግዜም የሁሉንም ባለሃብቶች ስም ዘርዝር በመያዝ የጋራ ባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ተዘጋጅቶ እንደሚሰጥ በአንቀፅ 6(3) (4) ላይ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አዋጅ መገንዘብ የሚቻለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 40፣ 51(5)፣ 55(2) (ሀ)ን 85(5)ን መርሆች በመከተል በአሁኑ ጊዜ የዜጐች የገጠር መሬት ባለይዞታነት መብት ስለሚመዘገብበት ሁኔታ ከፍ/ብሄር ህጉ ለየት ባለ ሁኔታ ማለትም በርስትንና የመሬት ባለቤትነት መብት ምትክ በመሬት ባለይዞታነት የመጠቀም መብትን መሰረት በማድረግ የተደነገገ ህግ መሆኑን ነው፡፡
2. የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት እውቅና ያገኘውን መብት ተግባራዊ በሚያደርግ መልክ የአርሶ አደሩን፣ ከፊል አርብቶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በመሬት የባለይዞታነት መብት በሚያረጋግጥ መንገድ የወጣ ህግ በመሆኑ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ግንኙነትን ታሳቢ በማድረግ የአገሪቱ ዜጎች የመሬት አኩል ተጠቃሚነት መብት ያረጋገጠ ህግ ነው:: በፍ/ብሄር ህጉ ካለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ተጠቃሚነት መብትም ለየት ባለ መልኩ የወጣ ነው፡፡ በራሱ ውጤት ባይሆንም የዘላቂ ልማት መሳርያ በመሆን የአገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ከሚወሰኑ የልማት ግብአቶች አንዱ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በምዝገባ ጥበቃ እንዲያገኝ የተደረገበት ዋናው ምክንያትም ይሄው ነው፡፡
ስለዚህ የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ በዜጐች መካከል የሚከሰተውን ውዝግብ ከማስወገድ ተልእኮው በተጨማሪ ውዝግብ በሚነሳበትም ግዜ በአስተማማኝና መንግስታዊ አካል በሚሰጠው ማስረጃ ላይ ተመስርተው ዳኞች ፍትህ እንዲሰጡ የሚያስችል በመሆኑ ዜጐች በንብረት ላይ ያላቸውን ያለመደፈር መብት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዲመሰረት የሚያደርግ ነው:: በመሆኑም ጠቀሜታ እጅግ የላቀ ነው ብቻ ሳይሆን በማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን ለማረጋገጥም ሆነ በማንኛውም ህግ በሚፈቅደው አግባብ ለማስተላለፍ ምዝገባ ማከናወን በህግ የተጣለ ግዴታም ጭምር ነው፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 51997
ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታው የሚለቅ ሰው በቅድሚያ ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት መብት ሕገ- መንግስታዊ መብት ነው፡፡ የዚህን የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 40(8) መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 በአንቀጽ 7 ላይ የካሳ መሰረትና መጠን በሚል ርእስ ስርና በአንቀጽ 8 ላይ የማፈናቀያ ካሳ በሚል ስር ሁለት ዓይነት የካሳ ክፍያዎች እንዳሉ በሚገልጽ መልኩ ተደንግጓል፡፡
እነዚህን ሁለት ድንጋጌዎች ለየብቻ ማየት ኢትዮጵያ የምትከተለውን የካሳ አከፋፈል ስርዓት በግልፅ ለመረዳት ስለሚያስችል በሚከተለው መንገድ ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡
በአንቀፅ 7 መሰረት የካሳ መሰረት ሆኖ የሚወሰደው እንዲለቅ በሚመለከተው አካል የተወሰነበት ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ለሚገኘው ንብረት እና በመሬቱ ላይ ላደረገው ቋሚ ማሻሻል የሚከፈል ካሳ ነው፡፡ በሚለቀቀው የመሬት ይዞታ ለሚገኝ ንብረት የሚከፈል ካሳ ንብረቱን ባለበት ሁኔታ ለመተካት የሚያስችል ሲሆን በመሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል የሚከፈለው ካሳ መሰረቱ በመሬቱ ላይ የዋለው ገንዘብና የጉልበት ዋጋ የሚተካ የካሳ መጠን ነው፡፡ እንዲለቅ እየተደረገ ያለው ንብረት መልሶ በመትከል አገልግሎት ለመስጠት የሚችል በሚሆንበት ግዜ ከፍ ብለው ከተጠቀሱት ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የሚተካ ካሳና በመሬቱ ለተደረገ ቋሚ መሻሻል የወጣ ገንዘብንና የጉልበት ዋጋ በካሳ መልክ ከሚከፈለው በተጨማሪ የንብረቱ ማንሻ፣ የማጓጓዣና መልሶ ለመትከል የሚጠይቀውን ወጪ እንዲሸፍን የሚከፈለው ካሳ ነው፡፡ ይህም ማለት ለሁሉም ሰው ከይዞታው በመልቀቁ ምክንያት በመሬቱ ለሚገኝ ንብረት ካሳ የማግኘት መብት ያለው ሲሆን ለተደረገ ቋሚ መሻሻልና መልሶ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚከፈል ካሳ ግን እንደየ ሁኔታውና የንብረቱ ዓይነት እየታየ የሚከፈል ካሳ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የመጀመሪያው የካሳ ዓይነት አንድ ሰው ባለይዞታ ከሆነበት መሬት በመልቀቁ ምክንያት ከዚያ መሬት ያገኝ የነበረውን ጥቅም የማግኘት መብት ስላለው ለሁሉም የሚሰጥ ሲሆን ሌሎቹ ግን አንድ ሰው በመሬቱ ያደረገው ቋሚ መሻሻል ከሌለ በዚህ መልኩ የሚገለፅ የሚያገኘው ካሳ አይኖርም ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም እንዲለቅ የተደረገው የአገልግሎት መስጫ መልሶ በመትከል እንደገና አገልግሎት መስጠት የማይችል ከሆነ በመጀመሪያው የካሳ ስሌት ማለትም ንብረቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ለመተካት የሚያስችል ካሳና ያደረገው ቋሚ ማሻሻ ካለ የነዚህ ካሳ ይሰጠዋል እንጂ የማንሻ የማጓጓዣና መልሶ መትከያ የሚወጣ ወጪ ስለማይኖር በዚህ መልኩ የሚከፈለው ካሳ አይኖርም ማለት ነው፡፡
የገጠር መሬት የካሳ አከፋፈል
በአዋጁ አንቀጽ 8 መሰረት የሚከፈል የማፈናቀያ ካሳ ከፍ ብለን አንቀጽ 7 መሰረት በማድረግ እያየናቸው ከመጣን የካሳ አከፋፈሎችና (modes of compensation) የካሳ መሰረቶች (Bases of Compensation) በተጨማሪ አንድ ሰው ከይዞታው በመፈናቀሉ ብቻ የሚከፈል የሁሉም ባለይዞታዎች መብት ነው፡፡ አፈፃፀሙን ማለትም የካሳ አከፋፈል ስሌቱንና ለማፈናቀያ ካሳ መሰረት የሚሆነውን መሰረት በማድረግ የተለያየ አካሄድን የሚከተል ሲሆን ዝርዝሩም እንደሚከተለው ነው:: በቋሚነት እንዲለቀቅ የሚደረገው የገጠር መሬት ባለይዞታ ሲሆን እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት የነበረውን ገቢ በአስር ተባዝቶና በአዋጁ አንቀጽ 7 ማግኘት የሚገባው ካሳ ታክሎበት ካሳ ይከፈለዋል፡፡ በአጭሩ የካሳው አከፋፈል ቀመር :-
- ቋሚ የማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x በ10 + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ ወይም
- ቋሚ የማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x በ10 + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ ወይም
- ቋሚ የማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x በ10 + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ + የንብረቱ ማንሻ፣ ማጓጓዣና መልሶ መትከያ ወጪ የካሳ አከፋፈል ቀመርን የሚከተል ነው፡፡
ለተወሰነ ጊዜ ከገጠር መሬት ይዞታው ለሚለቅ ባለይዞታ ወይም ለወል መሬት ባለይዞታዎች (Holders of Common land) እንዲለቁ ከመደረጉ በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት ያገኙት አማካይ ዓመታዊ ገቢ መሬቱ እስኪመለስ ባለው ግዜ ታስቦ በአንቀጽ 7 የሚከፈለው ካሳ ተጨምሮበት የመፈናቀያ ካሳ ይከፈላቸዋል፡፡ ይህም ማለት፡-
- የተወሰነ ጊዜ ማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ ተፈናቅሎ የሚቆይበት ዓመት + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ ወይም
- የተወሰነ ጊዜ ማፈናቀያ ካሳ = ባለፈው 5 ዓመት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ x ተፈናቅሎ የሚቆይበት ዓመት + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ ወይም
- = x ተፈናቅሎ የሚቆይበት ዓመት + ንብረቱ ባለበት ሁኔታ መተክያ + የቋሚ ማሻሻያ ገንዘብና የጉልበት ዋጋ + የንብረቱ ማንሻ ሟጓጓዣና መትኪያ እንደ ስሌት የሚጠቀም ሲሆን ህጉ ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ ከይዞታ መልቀቅን በተመለከተ ለቋሚ መልቀቅ ከተከተለው ስሌት ጋር ሲታይ ከተወሰነ የብዜት መሰረት (base) ለውጥ ውጨ ሌላ ልዩነት የሌለው ቢመስልም በአንቀፅ 8(2) መጨረሻ ላይ በአንቀፅ 8(1) ያልተጠቀመበትን “… ሆኖም ይህ ክፍያ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (1) መሰረት ከሚከፈለው ካሳ መብለጥ የለበትም፡፡” ሲል የካሳ ክፍያውን ጣርያ ገድቦታል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለውም ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግ መልቀቅ በአንቀፅ 8(1) ለካሳው ብዜት መሰረት ከሆነም 10 ዓመት ለሚበለጥ ጊዜ በጊዚያዊነት ከይዞታው ለቆ መቆየት እንደሌለበት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከመሬቱ ለቆ የሚቆይበት ጊዜ ከ10 ዓመት በላይ ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ ከገጠር መሬት ይዞታ መልቀቅ መሆኑ ቀርቆ እንደ ቋሚ ከገጠር መሬት ይዞታ መልቀቅ ይቆጠራና የካሳ አከፋፈሉም በቋሚ መልቀቅ አከፋፈል ስርዓትን የተከተለ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ህጉ ከፍ ብለን እያየናቸው ከመጣን የካሳ አከፋፈል ስሌቶች በተጨማሪ አንድ ሰው ካለው የገጠር መሬት ይዞታ ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንዲለቅ በሚደረግበት ጊዜ ሌላ አማራጭ የካሳ አከፋፈል ስርዓትን በአንቀፅ 8(3) ይደነግጋል:: ይሄውም ተመጣጣኝ ገቢ የሚያስገኝና በቀላሉ ሊታረስና ምርት ሊያስገኝ የሚችል ተተኪ መሬት እና መሬቱ እንዲለቅ ከመደረጉ በፊት በነበሩት 5 ዓመታት ያገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢውን ያህል በካሳነት ይከፈለዋል ይላል፡፡
ስለዚህ ህጉ የገጠር መሬት ይዞታን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ማስለቀቅንና የካሳ አከፋፈሉን በተመለከተ በቋሚነት ለሚለቅ በመሬት ላይ ለሚገኘው ንብረት የተደረገ ቋሚ መሻሻል ካለ ለዚህ የተደረገን ወጪና እንደየ ሁኔታው የንብረት ማንሻ፣ ማጓጓዣና መልሶ መትክያ ወጪን የሚሸፍን ካሳና ከዚህ በተጨማሪ እንደየ ሁኔታው የሚከፈል የመፈናቀያ ካሳን የመክፈል ስርዓትን (compensation schem) የያዘ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ቋሚ መልቀቅንና ለተወሰነ ጊዜ መልቀቅን መሰረት በማድረግ የተለያየ የማፈናቀያ ካሳ አከፋፈል ስርዓትን የሚከተልና ተተኪና የሚመጥን መሬት ባለበት ሁኔታም ለየት ያለ የካሳ አከፋፈል ስርዓት የሚከተል ህግ ነው፡፡
የከተማ ቦታ ካሳ አከፋፈል
እንደሚታወቀው በአገራችን የከተማ ቦታን በሊዝና ከሊዝ ውጭ ባሉ የከተማ ቦታ ይዞታ የማግኛ መንገዶች እንደ በግል የከተማ ቦታ ምሪትና የቆየ የከተማ ቦታ ይዞታ ወዘተ ባሉ የባለይዞታነት መብት ማግኘት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ህጉ በአንቀፅ 7(3) ላይ እንዲለቅ የተደረገው ባለይዞታ የከተማ ነዋሪ በሚሆንበት ጊዜ የሚሰጠው ካሳ ክልሎች በሚያወጡት ስታንዳርድ የሚወሰን ቢሆንም አንድ የቁጠባ ክፍል ሊያሰራ ከሚችል የገንዘብ መጠን ግን ማነስ እንደሌለበት የሚደነግገው፡፡ አንቀፅ 8(4) ይህን ሀሳብ በማጠናከር “በዚህ አዋጅ መሰረት የመሬት ይዞታው እንዲለቅ ለተደረገ የከተማ ነዋሪ ለንብረቱ ከሚከፈለው ካሳ በተጨማሪ ማለትም ንብረቱን ባለበት ሁኔታ ለመተካት የሚያሰችል ካሳ ከሚከፈለው በተጨማሪ መጠኑ በከተማው አስተዳደር የሚወሰን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ምትክ የከተማ መሬት ይሰጠዋል፡፡ እንዲሁም የፈረሰው የመኖሪያ ቤት የአንድ ዓመት ኪራዩ ግምት ተሰልቶ የመፈናቀያ ካሳ ይከፈለዋል ወይም የከተማው አስተዳደር ንብረት የሆነ ተመጣጣኝ ቤት ለአንድ ዓመት ያለ ኪራይ ክፍያ እንዲኖርበት ይደረጋል፡፡ “ ሲል ይደነግጋል
ስለዚህ ከሊዝ ውጪ በሆነ መንገድ የከተማ ቦታ ባለይዞታ የሆኑ ሰዎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንዲለቁ በሚደረጉበት ጊዜ የሚኖረው የካሳ አከፋፈል ስርዓት የከተማ ነዋሪ የይዞታ ማስለቀቅያ ካሳ ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የሚተካ ካሳ + ምትክ የከተማ መሬት + የአንድ ዓመት ኪራይ የመፈናቀያ ካሳ ወይም ያለኪራይ ክፍያ የአንድ ዓመት በመንግስት ቤት መገልገል ይሆናል፡፡ ይህ መብት ለመንግስት መስሪያ ቤትም ተፈፃሚነት ያለው የካሳ አከፋፈል ነው፡፡
ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከይዞታው የሚለቅ የሊዝ ባለይዞታን በሚመለከት ህጉ ለየት ባለ ሁኔታ በአንቀፅ 8(6) እስካሁን እያየነው የመጣነውን በአንቀፅ 7 እና 8 ያለው የማስለቀቅያ ካሳ አከፋፈል ስርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ በተጨማሪ ለቀሪው የሊዝ ዘመን የሚጠቀምበት ተመጣጣኝ የመሬት ኪራይ ከመጀመሪያው የመሬት ኪራይ ያነሰ በሚሆንበት ጊዜም በመሬቱ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲጠቀምበት በማድረግ ያካካስለታል፡፡ ሌላው አማራጭም የሊዝ ባለይዞታው በምትክነት የተሰጠውን መሬት መረከብ ካልፈለገ የቀረው የሊዝ ዘመን ኪራይ ተሰልቶ እንዲመለስለት በማድረግ የሊዝ ግንኙነቱ እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የአንድ በሊዝ የከተማ ቦታ ባለይዞታ የሆነ ሰው ከይዞታው እንዲለቅ በሚወሰንበት ጊዜ ከይዞታው የመልቀቅያ ካሳ አከፋፈል ሰርዓት በአጭሩ ያየን እንደሆነ:-
የከተማ ሊዝ ይዞታ መልቀቅያ ካሳ = የአዋጁ አንቀፅ 7 እና 8 የሚያስገኙት የካሳ መብት + ለቀሪ ዘመን የሚጠቀምበት ምትክ መሬት መስጠት ሲሆን ሌሎቹ የአፈፃፀም ስርዓቶች እንደየ ሁኔታው የሚፈፀሙ ስሌቶች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡
ስለዚህ በአገራችን ያለውን የመሬት ይዞታ ለህዝበ ጥቅም ሲባል ማስለቀቅያ ህግ የገጠር መሬትና የከተማ መኖሪያና የሊዝ ኪራይ ባለይዞታነትን መስረት በማደረግ ንብረቱን ባለበት ሁኔታ የመተካት አሰራርን እንደ መሰረታዊ ለሁሉም ከይዞታቸው እንዲለቁ የተወሰነባቸው ሰዎች የንብረት ካሳ ማስግኛ መብት በመውሰድ ሌሎች ተጨማሪ ክፍያዎች እንደየ ሁኔታው የሚወሰኑ በርካታ የካሳ አከፋፈል ስርዓቶችን (Compensation Schems) ያካተተ ህግ ነው፡፡ ይህም በደንብ ቁጥር 135/1999 ላይ በዝርዝር የምናገኘው ነው::
ከደንብ ቁጥር 135/99 አንፃር
ከፍ ብለን እንዳየነው የመፈናቀያ ካሳ አተማመንና ቀመር በደንቡ ላይ በዝርዝር የተደነገገ ስለሆነ የደንቡን ይዘት በሚከተለው መልኩ ለማካተት ተሞክሯል::
የካሳ አተማመን
ሀ. የቤት ካሳ አተማመን
1. የቤት ካሳ የሚሰላው ተመጣጣኝ ደረጃ ያለውን ቤት ለመስራት የሚየስፈልገውን የወቅቱን የካሬ ሜትር ወይም የነጠላ ዋጋ በማውጣት ይሆናል፡፡
2. የቤት ካሳ ተመን
2.1 ከቤቱ ጋር ተያያዥነት የላቸውን የግቢ ንጣፍ፣ ሴፕቲክ ታነክና ሌሎች ስትራክቸሮች ለመስራት የሚያሰፈልገውን የወቅቱን ዋጋ እና
2.2 ቤቱ በመነሳቱ ምክንያት የተገነቡ የአገልግሎት መስመሮችን ለማፍረስ ለማንሳት መልሶ ለመገንባት፣ ለመትከልና ለማገናኘት የሚያስፈልጉትን ወጭዎች ግምት ይጨምራል::
3. ቤቱ የሚፈርሰው በከፊል ሲሆን የቤቱ ባለቤት ቦታውን ለመልቀቅ ከመረጠ ለቤቱ ካሳ
የማግኘት መብት አለው፡፡
4.ቤቱ የሚፈርሰው በከፊል ሲሆንና የቤቱ ባለቤት በቀሪው ቦታ ላይ ለመቆየት ከመረጠ ለፈረሰው የቤት አካል ብቻ ተሰልቶ ካሳ ይከፈለዋል፡፡ ሆኖም የቤቱ ባለቤት በቀሪው የቤቱ አካል የመቆየት ምርጫ አግባብ ባለው የከተማው ፕላን ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት፡፡
ለ.የአጥር ካሳ አተማመን
የአጥር ካሳ የሚሰላው ከሚፈርሰው አጥር ጋር በዓይነቱ ተመጣጣኝ የሆነ አጥር ለመስራት የሚያሰፈልገውን የወቅቱን የካሬ ሜትር ወይም የነጠላ ዋጋ በማውጣት ይሆናል፡፡
ሐ. የሰብል ካሳ አተማመን
1. የሰብል ካሳ የሚሰላው ሰብሉ ለመሰብሰብ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ሊሰጥ የሚችለውን ምርት መጠንና ምርቱ ሊያወጣ ይችል የነበረውን የአካባቢውን የወቅቱ የገበያ ዋጋ መሰረት በማድረግ ይሆናል፡፡
2. ሰብሉ ለመሰብሰብ የደረሰ ከሆነ ባለንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሰረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለትም በ90 ቀን ውስጥ ሰብሉን ሰብስቦ መውሰድ ይችላል፡፡
መ. የቋሚ ተክል ካሳ አተማመን
1. የቋሚ ተክል ካሳ የሚሰላው ተክሉ ፍሬ መስጠት ያልጀመረ ሲሆን ተክሉ በሚገኝበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጪ ግምት በማስላት ይሆናል፡፡
2. ቋሚ ተክሉ ፍሬ ለመስጠት የጀመረ ከሆነ ካሳው የሚሰላው ተክሉ በአንድ ዓመት የሚያስገኘውን ምርት በወቅቱ የአካባቢውን የገበያ ዋጋ በማባዛት እንዲሁም የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪን በመደመር ይሆናል፡፡
የዛፍ ካሳ አተማመን
1. የዛፍ ካሳ የሚሰላው በዛፋ የዕድገት ደረጃ ላይ ተመስርቶ የወቅቱን የነጠላ ወይም የካሬ ሜትር ዋጋ በማውጣት ይሆናል፡፡
2. ባለንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሠረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለትም በ90 ቀናት ውስጥ ዛፋን ከመሬቱ አንስቶ መውሰድ ይችላል፡፡
ረ. የጥብቅ ሳር ካሣ አተማመን
- የጥብቅ ሳር ካሳ የሚሰላው የመሬቱን የሳር ምርታማነትና የሳሩን የወቅቱን የካሬ ሜትር የገበያ ዋጋ መሠረት በማድረግ ይሆናል፡፡
- ባለንብረቱ በካሳ ክፍያ ፋንታ በአዋጁ አንቀጽ 4. መሠረት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለትም በ90 ቀናት ሳሩን ከመሬቱ ላይ አንስቶ መውሰድ ይችላል፡፡
ሸ. በገጠር መሬት ላይ የተደረገ ቋሚ ማሻሻያ አተማመን
በገጠር መሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ ማሻሻያ ካሳ የሚተመነው ለምንጣሮ፣ ለድልደላና እርከን ለመስራት እንዲሁም ውኃ ለመከተርና ለሌሎች የግብርና መሰረተ ልማት የወጡትን የመሳሪያ፣ የጉልበትና የዕቃዎች የወቅቱ ዋጋ በማስላት ይሆናል፡፡
ቀ. ተዛውሮ የሚተከል ንብረት ካሳ አተማመን
ተዛውሮ ለሚተከል ንብረት የሚከፈለው ካሳ ለንብረቱ ማንሻ፣ ማዛወርያና መልሶ መትከያ የሚያስፈልጉ የባለሙያ፣ የማቴሪያልና የማጓጓዣ ወጭዎችን ግምት በወቅቱ የገበያ ዋጋ መሠረት በማስላት ይሆናል፡፡
በ . ለማዕድን ባለፈቃድ ስለሚከፈል ካሳ አተማመን
ለማዕድን ስራ በማዕድን ባለፈቃድ የተያዘ መሬት በአዋጁ መሠረት የሚለቀቅ ሲሆን የሚከፈለው ካሳ አግባብ ባለው የማዕድን ህግ መሠረት የሚፈፀም ይሆናል፡፡
ተ. ለመካነ መቃብር ስለሚከፈል ካሳ
1. ለመካነ መቃብር ስለሚከፈል ካሳ መካነ መቃብሩን ለማንሳት፣ ተለዋጭ ማረፊያ ቦታ ለማዘጋጀት፣ አፅሙን ለማዘዋወርና ለማሳረፍ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለሚደረግ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት ማስፈጸሚያ የሚያስፈልጉት ወጪዎች ያጠቃልላል፡፡
2. ከፍ ብለው በተራ ቁጥር 1 የተጠቀሱት ወጪዎች የአካባቢውን የዕቃ፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የጉልበት የወቅቱን የገበያ ዋጋ መሠረት በማድረግ ይሰላሉ፡፡
የካሳ ስሌት ቀመር
በአዋጁና በዚህ ደንብ መሠረት የሚከፈል የንብረት ካሳ መጠን የሚሰላበት ቀመር እንደሚከተለው ይሆናል፣
1. የቤት ካሳ = የግንባታ ወጭ (በወቅቱ ዋጋ)
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
+ የቀሪ ዘመን የመሬት ሊዝ ተመላሽ ክፍያ
2. የሰብል ካሳ = የቦታው ስፋት (በካሬ ሜትር)
x የሰብል የገበያ ዋጋ በኪሎ ግራም
x በአንድ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ የሚገኝ ምርት በኪሎ ግራም
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
3. ፍሬ መስጠት ያልጀመረ ቋሚ ተክል ካሳ = የተክል ብዛት (በእግር)
x በአንድ እግር የወጣ ወጪ ግምት
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
4. ፍሬ መስጠት የጀመረ ቋሚ ተክል ካሳ = ተክሉ በአንድ ዓመት የሚያስገኘው ምርት
ብዛት (በኪሎ ግራም)
x የቋሚ ተክሉ ምርት የወቅቱ የገበያ ዋጋ
+ የመሬት ቋሚ ማሻሻያ ወጪ
5. ተዛውሮ የሚተከል ንብረት ካሳ = የንብረቱ ማንሻ ወጪ
+ የማዛወሪያ ወጪ
+ የመልሶ መትከያ ወጪ
6. የጥብቅ ሳር ካሳ = ሳሩ የሸፈነው ቦታ በካሬ ሜትር
X የሚመረተው የሳር ምርት ወቅታዊ የገበያ ዋጋ በካሬ ሜትር ይሆናል::
ምትክ ቦታና የመፈናቀያ ካሳ
- ለከተማ ቦታ ምትክ ስለመስጠት
ለህዝብ ጥቅም ሲባል ይዞታውን እንዲለቅ ለተደረገ የከተማ ነዋሪ የሚሰጠውን ምትክ ቦታ በአዋጁ አንቀጽ 14 (2) መሰረት ክልሎች በሚያወጡት መመሪያ መሰረት ይወሰናል፡፡
- ለገጠር መሬት ምትክ ስለመስጠት
ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሰብል፣ የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሸ መሬት እንዲለቀቅ ሲደረግ ለተመሳሳይ አገልግሎት የሚውል ምትክ መሬት በተቻለ መጠን ይሰጣል፡፡
- ለሰብልና ቋሚ ተክል መሬት ስለሚከፈል የመፈናቀያ ካሣ
1 እንዲለቀቅ የተደረገ የሰብል ወይም የቋሚ ተክል መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሠረት ምትክ መሬት የተሰጠ ከሆነ፣
ሀ. ከሰብሉ የሚገኘውን አማካይ ዓመታዊ ገቢ የሚያህል፣ ወይም
ለ. ከቋሚ ተክሉ የሚገኘውን አማካይ ዓመታዊ ገቢ ተክሉ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ በሚወስደው ዓመታት ቁጥር ተባዝቶ የሚገኘውን መጠን የሚያህል፣ የመፈናቀያ ካሣ ይከፈላል፡፡
2. እንዲለቀቅ የተደረገ የሰብል ወይም የቋሚ ተክል መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሰረት ምትክ መሬት መስጠት ካልተቻለ የሚከፈለው የመፈናቀያ ካሳ ሰብሉ ወይም ተክሉ ያስገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ በ10 ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ይሆናል፡፡
3. የሰብል ወይም የቋሚ ተክል አማካይ ዓመታዊ ገቢ የሚሰላው፣
ሀ. መሬቱ ከመለቀቁ በፊት በነበሩት አምስት አመታት በተገኘው ገቢ ላይ፣ ወይም
ለ. ሰብሉ ወይም ቋሚ ተክሉ ገቢ ያስገኘው ከአምስት ዓመት ላነሰ ጊዜ ከሆነ በነዚሁ ዓመታት በተገኘው ገቢ ላይ፣ ወይም
ሐ. ሰብሉ ወይንም ተክሉ ዓመታዊ ገቢ መስጠት ያልጀመረ ከሆነ በአካባቢው ባለው ተመሳሳይ የይዞታ መጠን ከተመሳሳይ ሰብል ወይም ቋሚ ተክል በአምስት ዓመታት በሚገኝ ገቢ ላይ፣ ተመስርቶ ይሆናል፡፡
- ለጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬት ስለሚከፈል የመፈናቀል ካሣ
1. እንዲለቀቅ የተደረገ የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሰረት ምትክ መሬት የተሰጠ ከሆነ፣ ከጥብቅ ሳሩ ወይም የግጦሽ መሬቱ የተገኘውን አማካይ አመታዊ ገቢ የሚያህል የመፈናቀያ ካሳ ይከፈላል፡፡
2. እንዲለቀቅ የተደረገ የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬትን በተመለከተ በዚህ ደንብ አንቀጽ 15 መሰረት ምትክ መሬት መስጠት ካልተቻለ የሚከፈለው የመፈናቀያ ካሳ ጥብቅ ሳሩ ወይም የግጦሸ መሬት ያስገኘው አማካይ ዓመታዊ ገቢ በ10 ተባዝቶ የሚገኘው መጠን ይሆናል፡፡
3. የዚህ ደንብ አንቀጽ16 ንዑስ አንቀጽ 3 ድንጋጌዎች የጥብቅ ሳር ወይም የግጦሽ መሬት አማካይ ዓመታዊ ገቢን ለማሰላት በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
- ለተወሰነ ጊዜ ለሚለቀቅ የገጠር መሬት ስለሚከፈል የመፈናቀል ካሣ
የገጠር መሬት እንዲለቀቅ የተደረገው ለተወሰነ ጊዜ ከሆነ የመፈናቀያ ካሳው ስሌት ማባዣ መሬት እስኪመለስ ድረስ ያሉት ዓመታት ቁጥር ይሆናል፡፡ ሆኖም በዚህ መንገድ ተሰልቶ የሚገኘው ካሳ በዚህ ደንብ አንቀጽ 16 ወይም 17 መሠረት ከሚከፈለው መጠን መብለጥ የለበትም፡፡ እስካሁን ካሳ የሚከፈልበትን ስርዓትና የምንጠቀምበትን ቀመር እያየን መጥተናል ይህ ማለት ግን ሁሌ ካሳ ይከፈላል ማለት አይደለም ለምሳሌ በአዋጁ መሰረት መሬቱ የሚለቀቅ ስለመሆኑ የተሰጠው ውሳኔ ለባለይዞታው ከደረሰ በኋላ ለተሰራ ወይም ለተሻሻለ ቤት: ለተዘራ ሰብል ለተተከለ ቋሚ ተክል ወይም በመሬት ላይ ለተደረገ ቋሚ ማሻሻያ ካሳ አይከፈልም:: ስለዚህ በህገ መንግስቱ የተረጋገገጠው ቅድሚያ ካሳ የማግኘት መብት ቀጥሎ በወጣ አዋጅና ደንብ በዝርዝር እንዴት መፈፀም እንዳለበት ከፍ ብሎ ባየነው መልኩ የተደነገገ ቢሆንም ህግ ከሚፈቅደው ውጭ በመሆን ማለትም ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከቦታው እንደሚለቅ እየተነገረው በዚህ መሬት ላይ ለሚያፈራው ንብረት ካሳ የማይከፈልበት መሆኑን ከግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል ምክንያቱም እንደዚህ ባለ ሁኔታ ለተገኘ ንብረት ካሳ መክፈል ማለት ከህግ ልእልና (rule of law) መርህ ጋር የሚፃረር ስራን መስራት ነው የሚሆነው :: ስለዚህ አሁን ባለው ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከቦታው የሚፈናቀል የገጠርም ሆነ የከተማ ነዋሪ ካሳ የማግኘት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህግ-መንግስት የተረጋገጠ መብት ሲሆን ዝርዝር አፈፃፀሙ የህግ-መንግስቱን መርህ ተከትለው በወጡ አዋጅ ቁጥር 555/97 እና ደንብ ቁጥር 135/99 ተደንግጎ የምናገኘው የዜጎች መብት ነው::
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 16191
ህገ መንግስታዊ መስረቱ
የኢ ፌ.ዲ.ሪ ህገ - መንግስት የመሬት ባለይዞታነትን በማስመልከት ቀደም ሲል ለመዳሰስ እንደተሞከረው በአንቀፅ 40 እና 89(5) ላይ ዜጉች በገጠርን ሆነ በከተማ መሬት አጠቃቀም ስለሚኖሩዋቸው መብቶችና ግዴታዎች እንዲሁም አስተዳደሩን በማስመልከት የመሬት ባለቤትና የመንግስትና የህዝብ መሆኑን በእርግጠኛነት የሚደነግግ መሆኑን እያየን መጥተናል፡፡ አሁን ከያዝነው ርእስ ጉዳዩ አኳያም አንቀፅ 40(8) ላይ ‘’የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀሆኖ መንግስት ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘዉ ተመጣጣኝ ካሳ በቅድምያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመወስድ ይችላል ፡፡’’ በማለት ይደነግጋል ከዚህ ህገ - መንግስታዊ ድንጋጌ ለመረዳት የሚቻለው ማንኛውም ዜጋ ንብረት የማፍራት፣ ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳለውና ይህ የግል ሆነ የጋራ ባለንብረትነት መብት በህግ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚወስድበት ሰው በቅድምያ ካሳ የማግኝት መብት እንዳለው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህም መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው የሚለውን ህገ-መንግሰታዊ መርህ መሰረት በማድረግ ዜጎች በመሬት ላይ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ሰለሚሰሩት ቤት ወይም ስለሚያፈሱት ሃብት የሚኖራቸው መብት የባለቤትነት መብት በመሆኑ ለዚህ የግልም ሆነ የጋራ ንብረት ካሳ የማግኘት መብታቸውን በማስመልከት የሚደነግግ ህግ ነው፡፡ ካሳ ይከፈለኝ ብለው በልበሙሉነት እንዲከራከሩ የሚያስችላቸውም ነው፡፡ የአቅማቸውን ያህል በመሬቱ ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ፡ ጉልበታቸውን፤ ጥረታቸውንና እውቀታቸውን እንዳያፊሱ ከሚኖር ሰጋት ተላቀው ህግ-መንግስትና እሱን መስረት በማድረግ የወጡ ሕጎች ዋስትና ሰጪነታቸውን ተገንዝበው የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ነው፡፡ በመሆኑም ህግ - መንግስቱ ግዴታን ብቻ ሳይሆን መብቱም ያቀፈ በመሆኑ ከዚህ አቅጣጫ ሲታይ የዜጎችን የንብረት መብት እጦት ስጋት የቀረፈ ነው ፡፡
የአዋጅ ቁጥር 455/97 አላማዎች
Øየከተማ መሬትን ማልማት
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 40(8) የያዘዉን ህገ መንግስታዊ መርህ መስረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 455/97 በመግብያው ላይ
የአገሪቱ ከተሞች ከግዜ ወደ ግዜ እያደጉና የነዋሪዎችም ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ በከተሞቹ ፕላን መስረት ለመኖርያ ቤት ግንባታ ለመሰረተ ልማት፤ ለኢንቨስትመንትንትና ሌሎች አገልግሎቶች የሚውል የከተማ መሬትን መልሶ ማልማት አስፈላጊ በመሆኑ እንዲሁም በገጠር ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች መሬት አዘጋጅቶ ማቅረብ በማስፈለጉ፤
በማለት የአዋጁን አስፈላጊነት ይገልፃል፡፡ የከተሞች የልማት ስትራተጂ ውጤታማ ለማድረግ ልማቱ በራሱ የሚጠየቀው የመሬት ግብአት እንዳለና ይህን ደግሞ አንድም ከቆየው የከተማ ቦታ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ባለይዛታውን ካሳ እየከፈሉ በማስለቀቅ አልያም በከተምች አከባቢ ያለን የገጠር መሬት ለህዝብ ጥቅም ሲባል ማስለቀቅ የግድ ነው፡፡ በመሆኑም የከተማ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት፣ ለኢንዱስትሪና የገበያ ቦታዎች ሲባል እንዲሁም ለመኖርያ ቤት ሲባል የከተማ ቦታን በማስለቀቅ ወይም ሌላ ተጨማሪ የገጠር መሬት ወደ ከተማ ክልል በማስገባት ማልማት የሚጠይቅ ነው ፡፡
Øየገጠር መሬትን ማልማት
የዚህ አዋጅ ሌላው አላማ የገጠር ልማት ስትራተጂው ተግባራዊ ለማድረግ ለምሳሌ የገጠር መስረተ ልማት ስራዎችን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለማስፋፋት የግድ የገጠር መሬትን መጠቀም ስለመሚጠይቅ እነዚህን የልማት ስራዎች ማለትም እንደ ገጠር ኢንቨስትመንት ለማከናወን ስራው የሚጠይቀው የገጠር መሬት ለህዝብ ጥቅም ሲባል ማስለቀቅ እንደሚቻል በመገንዘብ የገጠር መሬት ልማትን ማእከል ያደረገ ህግ እንዲወጣ መደረጉ ለልማት ሲባል ዜጎች በዚህ ይዞታቸው የመገልገል መብት ላይ የተጣለ ህጋዊ ገደብ ቢሆንም ለዘላቂና ዋስትና ላለው ልማት ሲባል የሚደረግ ስለሆነ ህ/ሰቡን የሚጐዳ አይደለም፡፡
Øየካሳ አከፈፈል ስርዓት መዘርጋት
የከተማ ይሁን የገጠር መሬት ለዝህብ ጥቅም ሲባል ባለይዞታውን ማስለቀቅ እንደሚቻል ሁሉ በህግ መንግስትና ከዚያ በታች ባሉ ህጉች ጥበቃ ያገኘውን ቅድምያ ካሳ የማግኘት መብትን እንዴት ባለ ሁኔታ ከይዞታው እደሚለቅና በሚለቅበት ግዜም ስለሚኖሩ የካሳ አከፋፈል ስርዓቶች በአዋጁ አንቀፅ 7 እና 8 እንዲሁም በደንብ ቁጥር 135/99 ከአንቀፅ 3 እሰከ 18 በዝርዝር የተደነገገ በመሆኑ በየጊዜው ይከሰት የነበረውን ወጥነት የሌለው የካሳ አከፋፈል ስርዓት ቢያንስ የተቀራረበ እንዲሆን የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ የጉላ ነው ፡፡
Ø
በዚህ ርእሰ ጉዳይ ተደጋግመው የሚነሱና ለዓመታት በህግ ባለመያዎች መካከል ሳይቀር ልዩነት ሲፈጥሩ የሚስተዋሉትን እንደ “ ካሳና ” “ የህዝብ ጥቅም ” ያሉ በማያሻማ መንገድ መተርጐሙ ለአፈፃፀም ካለዉ ፈይዳ አንፃር ብቻ ሳይሆን አፈፃፀሙ በዜጎች መብት ላይ ከሚፈጠረው ተፅእኖ አንፃርም ጭምር ሲመዘን የህጉ አቀራረፅና አላማ መፍትሔ ሰጪነቱ ብእጅጉ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርግ ነዉ፡፡ ለዚህም አዋጁ በአንቀፅ 2(1) ላይ ‘’ካሳ ማለት የመሬት ይዞታውን እንዲለቅ ለሚወሰንበት ባለይዞታ በመሬቱ ላይ ለሰፈረው ንብረት በዓይነት ወይም በገንዘብ ወይም በሁሉቱም የሚከፈል ክፈያ ነው ፡፡ ’’ በማለትና በአንቀፅ 2(5) ላይ ደግም ‘’የህዝብ ጥቅም ማለት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ህዝቦች በመሬት ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ማሕበራዊና ኢኮኖምያዊ ልማትን በቀጣይነት ለማጎልበት አግባብ ያለው አካል በከተማ መዋቅራዊ ፕላን ወይም በልማት እቅድ መስረት የህዝብ ጥቅም ብሎ የሚወስነው ነው፡፡’’ ሲል ደንግጓል፡፡ ይህ ከአሁን ቀደም የነበረውን የህዝብ ጥቅም ምንድን ነው? የሚል የአረዳድ ችግር በሚያስወግድ መልኩ መተርጎሙ በእጀጉ ጠቃሚና መፍትሄ ሰጪም ነው፡፡ ዜጎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል መሬታቸውንና ለዓመታት ለፍተው ያፈሩትን ንብረት ለቀዉ እንዲሄዱ ሲወስንባቸው ከጥራጥሬ ነፃ ሆነው ያለማንገራገር ለሚመለከተው አካል እንዲያስረክቡ ካልሆነም ጉዳያቸውን በህግ ሰልጣን ወደ ተሰጠው አካል አቅርበው ፍትህ እንዲያገኙ የሚያስላቸውም ነው፡፡
የባለይዞታዎች መብት
ü ተመጣጣኝ ካሳ በቅድምያ የማግኘት መብት ማንኛውም ባለሃብት መሬቱንና በመሬቱ ላይ ያስፈሪውን ሃብት ለህዝብ ጥቅም ሲባል እንዲለቅ በሚመለከተው አካል ሲወስንበትና ይህን መስረት በማድረግ ማሰጠንቀቅያ ሲደርሰው ከ 90 ቀን ባላነስና ባልበዛ ግዜ ውስጥ ቦታውን ለሚመለከተው አካል ማስረከብ ቢኖርበትም ለንብረቱ ተመጣጣኝ ካሳ በቅድምያ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ (ህገ መንግስት አንቀፅ 40(8) እና የአዋጁ አንቀፅ 7 እና 8 እና ደንብ ቁጥር 135/99)
ü ካሳን መስረት በማድረግ አቤቱታ የማቅረብ መብት፡፡ አንድ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ይዞታው እንዲለቅ የሚደረግ ስው በሚወስነው የካሳ መጠን ላይ አንሷዋል የሚል ከሆነ ወይም ያለተገመተ ንብረት ቀርቷል ወ.ዘ.ተ. በሚል ምክንያት የገማቾችን ውሳኔ በመቃወም አብዮቱታውን በገጠር የመሬት ነክ አብዮቱታ ሰሚ አሰተዳደራዊ አካል ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ባልተደራጀበት ሁኔታ ስልጣን ወዳለው መደበኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ማንኛውም ዜጋ ከህግ ውጭ የንብረት መብቱን እንደማያጣና በየደረጃው ባሉ አስተዳደር አካላት በሚሰጡት ውሳኔዎች ላይ ይግባይ በማለት ቀጥሎ ወዳለው ይግባይ ሰሚ መደበኛ ፍርድ ቤት መሄድ እንደሚችል ነው ፡፡ (አንቀፅ 10 እና 11) የመሬት ባለይዞታ ካሳ የማግኘት መብት እንዳለው ሁሉ ካሳዉን ተቀብሎ መሬቱን የማስረከብ ግዴታም አለበት፡፡ ለዚህም የአዋጁ አንቀፅ 4 “አንድ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከይዛታው እንዲለቅ የተወስነበት ስው ካሳውን ተቀብሎ በ90 ቀናት ውስጥ መሬቱን ለወረዳው ወይም ከተማው አስተዳደር ማስረከብ አለበት፡፡” ሲል ይደነግጋል ይህም የሚያሳየው የመብትና ግዴታ ያለመነጣጠልን ነው፡፡”
የአስተዳደር መብትና ግዴታ
በከተማም ሆነ በገጠር ያለ አስተዳደር ለህዝብ ጥቅም ሲባል የከተማ ቦታን ወይም የገጠርን መሬትን በሚያስለቅቅበት ግዜ ለባለ ይዞታው ማሳወቅ፣ ካሳ የመክፈልና ባለይዞታው ካሳውን ለመቀበል ፊቃደኛ ባለሆነበት ግዜም ሂሳቡን በዝግ የባንክ ሂሳብ በማስቀመጥ የሚለቀው ዜጋ በተቻለ መጠን እንዲቋቋም የማድረግና የሚለቀቀውን ንብረት መስረት ያደረገ መረጃ የመያዝ ግዴታዎች ያሉት ሲሆን ባለይዞታው ለመልቀቅ ፊቃደኛ ባልሆነበት ግዜ የፓሊስ ኃይል ተጠቅሞ ማስለቀቅ እንደሚችል አዋጁ በአንቀፅ 4(5) በግልፅ ይደነግጋል ፡፡
ስለዚህ አዋጅ ቁጥር 455/97 ለህዝብ ጥቅም ሲባል ስለሚለቀቅ የገጠር መሬት ወይም የከተማ ቦታ በሚለቀቅበት ግዜ የማሳወቅ ስርዓት፣ የመገመት፣ ካሳ ማለትም የንብረት ግምትና የመፋናቀያ ካሳ ስለሚከፈልበት ሰርዓትና በተወስነው ካሳ ያለተስማማ ባለይዞታ አቤቱታውን ወደሚመለከተው አካል የማቅረብና አሁንም በተስጠው ውሳኔ ቅር ከተስኘ ይግባይ ብሎ የመሄድን መብት ባካተተ መንገድ የህገ-መንግስቱን አንቀፅ 40(8) ካሳ በቅድምያ የማግኘት መርህ ተከትሎ የወጣ ህግ በመሆኑ ዜጋች የንብረታቸው የወደፊት እጣ ፋንታ ግልፅ የሆነ የባለቤትነት ስሜት ኑራቸው በልማቱ መስክ በሙሉ አቅማቸው እንዲስሩ የሚያደርግ ነው፡፡
ለህዝብ ጥቅም ሲባል ከመሬት ባለይዞታነት ማስለቀቅን በሚመለከት ከገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/97 አንፃር ሲታይ ከፍ ብለን እንዳየነው ከህገ-መንግስቱና አዋጅ ቁጥር 455/97 ባልተለየ መልኩ በአንቀፅ 7(3) ላይ ፡-
‘’የገጠር መሬት በላይዞታነት ለህዝብ ጥቅም ሲባል መሬቱን በመንግስት እንዲለቅ ሲደረግ በመሬቱ ላይ ላደረገው ማሻሻያና ላፈራው ንብረት ተመጣጣኝ ካሳ ይከፈለዎል፡፡ ወይም ለለቀቀው መሬት ምትክ በታቻለ መጠን ሌላ ተለዋጭ መሬት እንዲያገኝ ያደረጋል’’ ሲል የሚደነግግ ሲሆን የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣዉ ኣዋጁ ቁጥር 272/1994 እንደዚሁ ተመሳሳይ በሆኑ መንገድ በአንቀፅ 16 ላይ ፡-
አግባብ ያለው ኣካል ለህዝብ ጥቅም ይውላል ብሎ በሚወስነው መስረት ለሚመለከተው ስው የማስለቀቅያ ትእዛዝ ወይም ማስጠንቀቅያ በፅሁፍ በመስጠት የሚፈለገውን የከተማ ቦታ ማስለቀቅና መርከብ ይችላል ፡፡ ትእዛዙንም አመቺ በሆነ ሌላ መንገድ ይፋ ያደርጋል፡፡
በማለትና ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ሲለቀቅ ካሳ መከፈል እንዳለበት በአንቀፅ 15(1)(ለ) ላይ ቦታው ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ለሌላ ስራ ወይም አግልግሎት እንዲውል ሲወስን በሚል አገላለፅ ካሳ እንደሚከፈል አንቀፅ 15 ላይ ከወጣው የሊዝ ይዞታ ማቋረጥና ካሳ አከፋፈል ከሚለው ርእስ መረዳት ይቻላል ፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚችለውም ለህዝብ ጥቅም ሲባል ሊለቀቅ የሚችለው መሬት የገጠር መሬት ወይም በሊዝ ይዞታነት ያለ የከተማ ቦታ ሊሆን እንደሚችልና ሁሉም ሰለሚኖራቸው የካሳ አከፋፈል መብት ሰፋ ባለ መልኩ በአዋጅ ቁጥር 455/97 እና ደንብ ቁጥር 135/99 ላይ በዝርዝር ተደንግጎ የምናገኘው መሆኑን ነው ፡፡
- Details
- Category: Property Law
- Hits: 43352
ህገ-መንግስታዊ መሰረቱ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት የገጠር መሬት ባለይዞታነትን መብት መሰረት በማድረግ አጅግ በርካታ ለሆኑ የንብረት መሰረታዊ መብቶች እውቅና የሰጠ ነው ፡፡ በአገራችን ለአመታት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን መሰረት በማድረግ እዚህም እዚያም ይነሱና ለግጭት መንስኤ በመሆን ዜጎች እርስ በርሳቸው ደም እንዲቃቡ ያደርጉ የነበሩትን ችግሮች በሚቀርፍ መንገድ መልስ የሰጠና በህዝብ ይሁንታ ያገኘ የፖሎቲካና የህግ ሰነድም ነው፡፡ የገጠር መሬትን መሰረት በማድረግ የተደነገጉትን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችን በዝርዝር ሰናይ የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 40(1) የግለ ንብረትን በማሰመልከት ዜጎች የግል ንብረት ባለቤትነት መብታቸው እንደሚከበርላቸውና ይህ መብት ሊገድብ የሚችለው ለህዝብ ጥቅም ሲባል ብቻ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ስለሆነም ግለሰቦች በዚህ ግል ንብረት የመያዝና የመጠቀም መብት እንዳላቸው አፅንኦት በመስጠት የሌላን ዜጋ መብት እስካልተቃረኑ ድረስ የግል ንብረታቸውን ማለትም በመሬት ላይ የገነቡትን ወይም በጉልበታቸውና በገንዘባቸው የፈሩትን የመሸጥ፣ የማውረስ፣ ወይም በሌላ መንገድ ማስተላለፍ እንደሚችሉም ይደነግጋል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ዜጎች ንብረት የማፍራትና ከግዜ ወደ ግዜ በሚያሳዩት እድገት ተጠቃሚ የመሆን ዋስትና ያላቸው መሆኑን ተገንዝበው አገሪቱ ለተያያዘችው ፊጣንና ዘላቂ ልማት ሳይታክቱ እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ህገ-መንግስታዊ የገጠር መሬት ባለይዞታነት መብት አርሶ አደሮች ከፊል አርብቶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በየደረጃው የልማቱ ተጠቃሚ የመሆንን ስትራተጂ እውን ለማድረግ የሚያስችል የማአዝን ድንጋይ ነው፡፡ ቀጥሎ ያለው ድንገጌ ስለ ግለሰቦች፣ ቡዱኖችና የተለያዩ ማህበረ-ሰቦች በጋራ የንብረት ባለቤት ስለሚሆኑበትና እነዚህ በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭነት ያለው ወይም ተጨባጭነት የሌለው ግን ደግም በገንዘብ ሊተመን የሚችል ዋጋ ያለው ንብረት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ የሚደነግግ ሲሆን ከአንቀፅ 40 (2) መገንዘብ የሚቻለው የንብረት ባለቤትነት እንዴት እንደሚገኝ የሚደነግግ መሆኑ ነው፡፡ ከመሬት ባለቤትነት መብት አንፃር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት በሽግግር መንግስቱ ወቅት የግል ሃብት መሆን አለበት በሚሉ ወገኖችና የመንግስት እጅ መሆን አለበት በሚሉ ወገኖች መካከል የነበረውን የደራ ክርክር መቋጫ እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው” በማለት የደነገገ በመሆኑ ለክርክሩ እልባት ሰጥቷል ብቻ ሳይሆን ከዚህ ባለፈም አሁን አገራችን እየተከተለችው ያለውን የልማት ፖሊሲና ስትራተጂ የገጠር መሬት በግል ሃብትነት በተያዘበት ኢኮኖምያዊ ማህበረ ሰብ ሊተገበር የማይቻል መሆኑ አሁን ያለንበት ሁኔታ በራሱ የሚያረጋግጠው ሐቅ ነው፡፡ ለዚህም በዋና ምክንያትነት ሊጠቀስ የሚችለው መሬት በግል ሃብትነት ይያዝ ቢባል ሰፊው አርሶ አደር ያለችውን መሬት እየሸጠ መሬት በጥቂት ባለሃብቶች እጅ እንዲገባ በማድረግ አርሶ አደሩና ሌላው የህበረተሰብ ክፍል የቀረችውን ጉልበቱ በርካሽ እየሸጠ ወደ ከፍ ድህነት እንዲገባ ከሚያደርገው በቀር ለስፊው አርሶ አደር ከፊል አርበቶ አደርና አርበቶ አደር የሚፈይደው ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ የልማት ዋስትና ያጣ አርሶ አደር ሆነ ሌላ የህብረተሰብ ክፍል ይዞ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ዘላቂ ልማትም ሆነ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ፈፅሞ ሊታሰብ የሚችል አይደለም፡፡ በሌላም በኩል መንግስት ለሚያከሂደው ኢንቨስትመት መሬት ከአርሶ አደሩ እየገዛ ያከናውን ቢባልም መንግስት በግብርና በተለያዩ መንገዶች ያገኛትን ጥሪት አሟጦ ለልማት በማዋል ፈንታ በመሬት ግዠና ሽያጭ ገንዘቡ እንዲታጠር በማድረግ ኢንቨትመንትን የሚያቀጭጭ ሁኔታ ስለሚፈጥር ተመራጭ ኣይደለም ብቻ ሳይሆን የተሳሳተ የፖሊሲ አቅጣጫን ተከትሎ አገሪቱ በልማት፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲ እጦት ወደ ባሰ ያለመረጋጋትና ስርዓት አልባነት እንድታመራ የሚያደርግ ፀረ-ሰላም አቅጣጫም ነው፡፡
ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር እንደመሆኗ መጠን የህዝቦቿ ኣኗኗርም የተለያየ ነው፡፡ ይህን የህዝቦቿ ብዝሀነት (divesity) ለማስተናገድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 40(5) “የኢትዮጵያ ዘላኖች ለግጦሽ ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነፃ የማግኘት የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው ዝርዝር አፈፃፀሙ በህግ ይወሰናል” ሲል ይደነግጋል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ህገ-መንግስቱ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከአኗኗራቸው ጋር የሚሰማማ የመሬት አስተዳደር በመከተል የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአርሶ አደርነት ቋሚ ቦታ ኑሯቸው የመሰረተ ልማት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በማስቻልና በጋማ ከብት ዘመናዊ እርባታ ዘርፍ ስፊና ዘመናዊ የእንሰሳ እርሻ ልማት በመፍጠር አርብቶ አደሮቹ የልማቱ ተሳታፊና በየደርጃቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ስለሚፈጥር ለገጠር ልማት ሰተራተጂው ግብ መምታት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል ብቻ ሳይሆን ዜጎች በፌደራሊዝም ስርዓት ማዕቀፍ በዘላቂነት አበረው አንዲኖሩ የሚያደርግም ነው ፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት የመሬት ባለይዞታነት የሚገኘው በሁለት መንገድ እንደሆነና ይሄውም በነፃ ወይም በክፍያ ሊሆን እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ ጠቅላል ባለ መልኩ ሲታይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት የገጠር መሬት የህዝብና የመንግስት እንዲሆን ማድረጉ ሰፊው አርሶ አደር፤ ከፊል አርብቶ አደር፤ አርብቶ አደርና በእርሻ ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለ ሃብቶች የገጠር መሬት በነፃ ወይም በክፍያ በማገኘት የባለይዞታነት መብት እንደሚያገኙና መንግስት የህዝብ ወኪል እንደመሆኑ መጠን መሬትን በህዝብ ስም እንዲያስተደደር የሚያስችለው ነው:: አሁን ባለው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የህዝብ ንብረት ሆኖ አንድ የገጠር መሬት ባለ ይዞታ አዋጅ ቁጥር 455/97 እና ደንብ ቁጥር 135/99 በሚደነግጉት መስረት በቅድሚያ ተመጣጣኝ ከሳ ተከፍሎት ብቻ ሊለቅ እንደሚችል ከዚህ ውጭ ግን በህጋዊ መንገድ ያገኘውን የገጠር መሬት የማልማትና በፍሬው ተጠቃሚ የመሆን መብቱ በህገ መንግስቱና ይህን መሰረት በማድረግ በወጡ ሌሎች ህጎች የተረጋገጠ መብት ነው፡፡ ይህ ህገ-መንግስታዊ የገጠር መሬት ባለይዞታነት መብት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘላቂ ሰላም በማምጣት አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠርን አላማ መሰረት በማድረግ በህዝብ ይሁንታ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሰፊውን አርሶ አደር ፣ ከፊል አርብቶ አደርና አርብቶ አደርን በየደረጃው ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቆ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን በማስቻል ያለ ህገ-መንግስታዊ መርህ ነው፡፡
ከአዋጅ ቁጥር 456/97 አንፃር፡-
የአዋጁ አላማዎች
የገጠርን መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሰረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 456/97 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስትና ይህን መሰረት በማድረግ የወጡ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎች ተግባረዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የወጣ ህግ ነው:: ከአዋጁ መግብያ መረዳት የሚቻለውም በርካታ የገጠር ልማት አላማዎችን የያዘ መሆኑ ነው፡፡
vዘላቂ ልማት (sustainable development)
የገጠር መሬት አስተዳደርንና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/97 በመግብያው ላይ፡-
በተለያዩ የሃገሪቱ የስነ-ምህዳር ቀጠናዎች ላይ ተመስርቶ ዘላቂ የገጠር መሬት አጠቃቀም እቅድ በማውጣትና በመተግበር የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘላቂ በመጠቀምና በልማት ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ በማስፈለጉ ነው፡፡ ሲል ይገልፃል
የዚህ አዋጅ መግብያ መሰረተ ሓሳብ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃና ልማት ኮሚሽን “sustainable development” ለሚለው ሐረግ ከሰጠው ትርጉም
“Development that meets the needs of the present with out compromising the ability of the future generation to meet their own needs.”
ጋር የሚሰማማ ከመሆኑም በላይ ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ የአሁኑና የወደፊቱን ትውልድ ፍላጎት አጣጥሞ አሁን ያለውን ንፁህ ውሃ፣ አየር፣ አፈር፣ እፅዋት በአጠቃላይ በአላማቸን የሰው ልጅ በሂወት ለመኖር አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች በሚገባ ይዘን ስርዓት ባለው አስተዳደርና አጠቃቀም ተገልግለንባቸው ከትውልድ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ የአሁኑ ትውልድ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ የሚጠይቅ ነው:: ይህ አለማቀፋዊ የልማት መርህ በአሁኑ ትውልድ ላይ ከፍተኛ ተጠያቂነትን የሚያሰከትል የዘላቂ ልማት መርህ ነው፡፡
አለማችን ከዘላቂ ልማት አንፃር ያላት ገፅታ ምን ይመስላል? ብለን ያየን እንደሆነ የአሁኑ ትውልድ ያለውን ሃብት በሚገባ በመጠቀምና ዘላቂ ልማት በማረጋገጥ የመጪው ትውልድ የሂወት ተስፋ ሊሆን ይቅርና አሁን ያለው ትውልድ ራሱ ለከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ችግር ተጋልጦ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህም ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በፊት የነበራት የአካበቢ ስነ-ምህዳርና አሁን ያለችበት ደረጃ ሲታይ በክፍተኛ ደረጃ የተመናመነ መሆኑ ለዚህ ዋቢ ነው፡፡ በመሆኑም የዘላቂ ልማት ፅንስ ሀሳብ ታሳቢ የሚያደረገውን የአሁኑ ትውልድ የልማት ፍላጎት ሳይገታ ግን ደግሞ የመጪው ትውልድ የልማት ፍላጎት ሳይጎዳ ልማትን እንዲያፋጥን ከተፈለገ ለዚህ ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂ መጠቀም የግድ የላል፡፡ ይህንን አባባል ከአገራችን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር አያይዘን ስናየው አሁን ያለው አርሶ አደር፤ ከፊል አርበቶ አደርና አርብቶ አደር ይሁን ኢንቨስተር የገጠርን መሬት ለልማት ስራ በሚያውሉበት ግዜ ውሃው እንዳይደርቅ፣ አፈሩ እንዳይሸረሸርና ደኑ እንዳይጨፈጨፍ የውሃ ማቆር፣ የአፈር ጥበቃና ችግኝ ተከላ ስራን በተጓዳኝ ካላከናወነ አለማችን ካላት የተፈጥሮ ሃብት ውሰንነትና የህዝቧ ብዛት ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣት ጋር ተያይዞ ሲታይ ለመጪው ትውልድ የልማት ፍላጎት የሚተርፍ ነገር ይቅርና አሁን ላልው ትውልድም ያለው የምግብ እጥረት እያየለ መጥቶ ለርሀብና የእርሰ በርስ ጦርነት መንስኤ በመሆን የሰው ልጅ መክፈል የማይገባውን የሚሊዮኖች ሂወት እንዲከፈል የሚጠይቅ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ አደጋ ለመውጣት ኢትዮጵያ እየተከተከችው ያለውን የገጠር ልማት ስትራተጂ የማኣዝን ድንጋይ የሆነውን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ ፅንስ ሀሳብ በአዋጁ መግብያ እንደ አላማ መውሰዱ መንግስት ለነደፈው የልማት ስትራተጂ ተግባራዊንት የቱን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ የሚያሳይ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መተግበር ያለበት ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 456/97 ይህን የዘላቂ ልማት ፅንሰ-ሃብን እንደ አላማ ይዞ ሲታወጅ አርሶ አደሩ ከፊል አርብቶ አደርና አርብቶ አደሩም ሆነ ኢንቨስተሩ የተረጋገጠ ይዞታ (tenure security) እንዲያገኝ እና በተሰጠው መብት ተጠቅም መሬትን ሲያለማ ሊከተላቸው ስለሚገባ የመሬት አጠቃቀም ስርዓቶች የሚደንገግ በመሆኑ ኋላ በዚህ ርእሰ ጉዳይ የምናያቸው በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ነው፡፡
አርሶ አደሩ በመሬት ላይ ያለውን የንብረት መብት ማጠናከር
ከአዋጁ መግብያ ለመረዳት እንደሚቻለው የንብረት መብት መነሻና መድረሻ በባህል ደንቦች ወይም መንግስት በሚያወጣቸው ህጎች እንደሚወሰን ነው፡፡ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህግ-መንግስትም ሆነ በአዋጅ ቁጥር 456/97 መሰረት አርሶ አደሩ፤ ከፊል አርበቶ አደሩና አርበቶ አደሩ በመሬት ላይ የሚኖራቸው መብት የይዞታ መብት ሲሆን በዚህ መሬት በሚያደርጉት ኢንቨትመንት ላይ ግን የባለቤትነት መብት እንደሚኖራቸው ነው፡፡ አርሶ አደሩ ከፊል አርብቶ አደሩና አርብቶ አደሩ በዚህ የልማት ዋነኛ መሳርያ በሆነው መሬት ያለቸው መብት የይዞታ መብት ሲሆን የዚህ መሬት ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ናቸው፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለውም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ- መንግስት መሰረት መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ የህዝብ ንብረት መሆኑ ነው፡፡ ይህ መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚለው ህገ-መንግሰታዊ መርህ በራሱ ግን የልማት ዋስትና እንዲያጡ የሚያደርጋቸው አይደለም፡፡ ለምን ቢባል ህገ-መንግሰቱና ሌሎች ህጎች ከባለቤትነት በመለሰ በንብረቱ የመገልገልና የፍሬው ተጠቃሚነት እስከተረጋገጡላቸው ድረስና በይዞታ መብቱ ላይ ችግር ሲፈጠር የሚተዳደሩበት ህግ እስካላቸው ድረስ የንብረቱ ባለቤት ሆኖ የተጠቃሚነት መብቱ ከተነጠቀበት የመሬት አስተዳደር ስርዓት (land tenure system) የበለጠ ነው:: የመብቱ ማጠንጠኛና ቋጠሮው ያለው እዚህ ላይ በመሆኑ የመሬት ስርዓቱ ፍትሐዊነት መመዘኛ መሆን ያለበት መሸጥ መፈቀዱና አለመፍቀዱ ሳይሆን ለህብረተሰቡ የሚሰጠው ጥቅም ወይም የሚያስገኘው ፋይዳ መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል ፡፡
የምግብ ዋስትና
አዋጅ ቁጥር 456/97 የምግብ ዋስትና የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ የሚጋራው በአዋጁ ቁጥር 2(10) ላይ “አነስተኛ የይዞታ መጠን “ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሚተረጉምበት ግዜ ሲሆን የድንጋጌው ይዘትም፤-
“አነስተኛ የይዞታ መጠን” ማለት ምርታማነቱ የአንድ አርሶ አደር፣ ከፊል አርብቶ አደር እና አርበቶ አደር ቤተሰብ የምግብ ዋስትና ሊያረጋግጥ የሚችል የገጠር መሬት ይዞታ ወይንም ለሰብል እርሻ፣ ለቋሚ ሰብል፣ ለግጦሽ፣ ለመኖርያ ቤትና ለጓሮ የሚበቃ የገጠር መሬት ይዞታ መጠን ነው፡፡” የሚል ነው::
የዚህ ድንጋጌ ይዘት የኢትዮጵያ መንግስት በፅናት ይዞ እየሰራበት ያለውን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ስትራተጂን ታሳቢ በማድረግ አርሶ አደሩ ከፊል አርብቶ አደሩና አርብቶ አደሩ ያለባቸውን የመልካም አስተዳደር እጦት ደረጃ በደረጃ እየፈቱ ተረጋግተው በልማት ስራው ላይ ጠንክረው በመሰረትና ከድህነት በመላቀቅ በአለም ምግብና እርሻ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የተሰጠውን ትርጉም ማለትም
- በቂ የሆነ ምግብ
- ጤናማ ሕይወት ለመምራት የሚየስችል
- የተመጣጠነ ምግብ
- የተመጋቢዎችን ፍላጎት የሚያረካ ምግብ
- ወቅት ሳይለይ በማንኛውም ግዜ ተመልቶ እንዲገኝ ለማስቻል እየሰራበት ያለውን የልማት ፖሊስ መሰረት በማድረግ የወጣ ነው፡፡
ሴቶች በመሬት ላይ ያለቸውን መብት ማረጋገጥ
እንደሚታወቀው ሴቶች አሁን ባለው የህዝብ ብዛት ቁጥራቸው ከግማሽ በላይ ቢሆንም እስካለፈው ሩብ ምእተ ዓመት በኢትዮጵያ ሴቶች የመሬት ባለ ይዞታነት መብት ተጠብቆላቸው የመብቱ ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በወጣበት ግዜ ሴቶች የልማቱ ግማሽ ሐይል ወይም ከዚያም በላይ እንደሆኑ በማመን እነዚህን የህብረተሰቡ ክፍሎች ለዓመታት ሲታገሉለት የቆየውን የመሬት በላይዞታነት መብት እውን ለማድረግ የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 35(7)
ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣የመቆጣጠር የማስተላለፍ መብት አላቸው፡፡ በተለይ መሬትን በመጠቀም በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋረ እኩል መብት አላቸው እንዲሁም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው፡፡
በማለት ይደነግጋል:: የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀምን መሰረት በማደርግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 456/97 የህገ-መንግስቱን የሴቶች የእኩልነት መርህን በመከተል በቁጥር 6(4) ላይ “መሬቱ የባልና ሚስት የጋራ ከሆነ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በሁሉም የጋራ ባለይዞታዎች ስም መዘጋጀት አለበት፡፡” ሲል ይደነግጋል ከነዚህ የሴቶችን የመሬት ባለይዞታነት መብት መሰረት በማድረግ የወጡ ህጎች መረዳት የሚቻለው ሴቶች በመሬት አስተዳደረና አጠቃቀም ከወንደች ጋር እኩል መብት እንዳላቸውና በዚህ መብታቸው ተጠቅመው እንደ ወንዱ ባለይዞታ መሆንና በፍቺ ግዜም ድርሻቸውን ይዘው የመሄድ መብት እንዳላቸው ነው፡፡ ይህ ከአሁን ቀደም ይገጥማቸው የነበረውን የኢኮኖሚ ተፅእኖ በማስቀረት ብዙሃኑን የሴት አርሶ አደሮች ከፊል አርብቶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉልበት ለልማት በማዋል ዜጎች በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዘላቂና ፈጣን ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራተጂ ተግባራዊ በማድረግ ሴቶች በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡
ማሕበራዊ ደህንነት ማረጋገጥ
የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 456/97 የዜጎችን ማሕበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ በአንቀፅ 5(1) (ለ) ላይ
ዕድሚያቸው ከ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነና በግብርና ሙያ ሊተዳደር የሚፈልግ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በገጠር መሬት የመጠቀም መብቱ የተረጋገጠ ሆኖ እናትና አባታቸውን በሞት ወይም በሌላ ሁኔታ ያጡ ልጀች 18 ዓመት እሰኪሞላቸው ድረስ በህጋዊ ሞግዚታቸው አማከይነት በገጠር መሬት የመጠቀም መብት አላቸው ሲል ይደነግጋል፡፡
ከዚህ ህግ መገንዘብ የሚቻለው የገጠር መሬት ለማግኘት 18 የሞላው ሆኖ በግብርና ስራ ለመተዳደር የወሰነ ሰው መሆኑን እንደመስፈርት የሚጠቀምና በልዩ ሁኔታ ከ18 ዓመት በታች ሆነው ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆት ግን ያላአሳዳጊ እንዳይቀሩ ህጉ ልዩ ማህበራዊ ዋስትና እንደሚሰጣቸው ነው፡፡ ይህ ማህበራዊ ደህንነት በአገራችን እየተስፋፋ ካለው የኤች. አይ. ቪ. ኤይድስና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ወላጅ አልባ እየሆኑ ካሉበት ሁኔታ አንፃር ሲታይ እንደዚህ ያለ የመሬት ተጠቃሚነት መብት ከ18 ዓመት በታች ላሉ ህፃናት በልዩ ሁኔታ መፈቀዱ ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
አዋጁ ከዚህ በተጨማሪ በአንቀፅ 5(4) ላይ ለአርሶ አደሮች ከፊል አርብቶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቅድሚያ በመስጠት በግብርና ልማት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፖሊሲውንና ሕጎችን መሰረት በማድረግ የገጠር መሬት ሊሰጣቸው እንደሚችልና የዚህ መብት ተጠቃሚ ለሚሆኑ ድርጅቶች ማህበራዊ ኢኮኖምያዊ ተቋሞች የያዙትን ዓላማ ያሳኩ ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ሰፋት እንደየተሰማሩበት ስራ አስፈላጊነቱ እየታየ በገጠር መሬት ይጠቀሙ ዘንድ ሊሰጣቸው እንደሚችል መደንገጉ በራሱ ለአርሶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቅድሚ መሰጠቱ የቱን ያህል የመሬት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያስችላቸው የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህ ህግ ግብርና መር ኢንዱስትሪያዊ ልማት ስትራተጂን መሰረት በማድረግ ለነዚህ ማሕበረሰቦች ከፍተኛ የማህበራዊ ደህንነት ዋስትና በመስጠት የስትራተጂው ግብ መምታት በሰፊ ህዝባዊ መሰረት ላይ እንዲጣልና አስተማማኝ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡
አጥጋቢ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ማረጋገጥ
የገጠር መሬትን መሰረት በማድረግ የእያንዳዱ ባለይዘታ ስም፣ አድራሻ የመሬቱ ስፋትና አዋሳኝ ለይቶ ግዴታውን በመመዝገብ አንዱ ባለይዞታ ከሌለው ባለይዞታ ተለይቶ እንዲታወቅ በሚያስችል መልኩ የገጠር መሬት አስተዳደር ማህደር አያያዝ ስርዓትን መዘርጋት አላማ ያደረገ አደረጃጀት ነው፡፡ እንደዚህ ያለ አስራር በገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ መዘርጋት በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ሲሆን ከብዙ በጥቂቱ ወስደን ብናይ አሁን ያለው የይዞታ ግጭትና እሰጥ አገባ በማስወገድ አርሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና በገጠር ልማት ኢንቨስትመንት የተሰማራው ባለሃብት በሰላም ግዜያቸውን ለልማት በማዋል ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፡-
- አሁን በስፋት የሚታየው ከመሬት ጋር ተያየዞ የሚነሳውና የፍ/ቤቶችን ስራ እያጨናነቀ ያለውን የስራ ጫና በመቀነስ ባለቸው ግዜ ጥራት፤ተገማችነትና ህዝባዊ አመኔታ ያለው ፍትህ እንዲሰጡ ያስችላል፡፡
- መንግስትንና ባለጉዳዮችን ካላስፈላጊ ወጪ ይከላከልላቸዋል፡፡
- በመንግስት የተመዘገበ መረጃ በመሆኑ የፍትህ አካላት አሁን እያጋጠማቸው ካለው የመረጃ ምዘና ችግር ተላቀው በቀላሉ ፍትህ የሚሰጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
-
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት ባለው መንገድ እንዲመራና መንግስትም ሆነ ተጠቃሚዎች በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው የት አካባቢ ምን ቢያመርቱ የበለጠ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከግዜ ወደ ግዜ ግንዘቢያቸውን እያስፉና እየተበረታቱ እንዲሄዱ የሚያስችላቸው በመሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
ቀልጣፋ የገጠር መሬት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት
አዋጅ ቁጥር 456/97 በትርጉም ክፍሉ አንቀፅ 2(2) ላይ “የገጠር መሬት አስተዳደር” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲተረጉም
በገጠር መሬት ይዞታ ላይ ዋስትና የሚሰጥበት የገጠር መሬት አጠቃቀም እቅድ የሚተገበርበት በገጠር መሬት ተጠቃሚዎች መካከል የሚነሱት ግጭቶች የሚፈቱበትና ማንኛውም የገጠር መሬት ተጠቃሚ መብትና ግዴታዎች የሚተገበርበት እንዲሁም የባለይዞታዎች ማሳዎችንና የግጦሽ መሬትን መረጃ በመሰብሰብና በመተንተን ለተጠቃሚዎች እንዲዳረሱ የሚደረግበት ሂደት ነው፡፡ ይላል
ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው የመሬት አስተዳደር ለማከናወን በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚጠይቅና እነዚህን ስራዎች ለመስራት የራሱ ተቋማዊ አደረጃጀትና ምርምርን እንደሚጠይቅ ነው፡፡ ስለሆነም የገጠር መሬት አስተዳደር መኖር በራሱ ግብ ባይሆንም የዘላቂ ልማት ፖሊሰና ስትራተጂዎች የሆኑትን እንደ የገጠር መሬት ዋስትና ማረጋገጥ፣ የገጠር መሬት ክርክርን መቀነስ የመሳሰሉትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል በመረጃና በእውቀት የዳበረ አሰራርን ተከትሎ ለበለጠ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ስኬታማነት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግና በሂደት የገጠር ልማት ፖሊውንና ስትራተጂውን የራስ ማድረግ (owning) የሚጠይቅ መሆኑን ነው፡፡
ስለዚህ አዋጅ ቁጥር 456/1997 ዓ.ም በርካታ አላማዎችን በመያዝ የገጠር ልማት ፖሊሲንና ስትራተጂን እውን ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የወጣ አዋጅ እንደመሆኑ መጠን በየደረጀው ያሉ የፍትህ አካላት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ለተፈፃሚነቱ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የአስተሳሰቡ ባለቤት በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን በብቃት እንዲወጡና የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡
የባለ ይዞታዎች መብትና ግዴታ
በገጠር መሬቱ የመጠቀም መብት
አርሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩና አርብቶ አደሩ በተሰጣቸው መሬት እንደ አርሰው ሰብል የመዝራትና ፍሬውን የመስብሰብ፣ ዛፎች በመትከልና ቆርጦ በመሸጥ፣ ቤት በመስራት፣ ከብቶችን በማርባት ወ.ዘ.ተ. ባሉ መንገዶች የመሬታቸው ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው፡፡
1.መሬቱን የማከራየት መብት
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የገጠር መሬት ባለይዞታ የሆነ አርሶ አደር መሬቱን የማከራየት መብቱ በአዋጅ ተረጋግጦለታል፡፡ ለማን ያከራያል? ለስንት ግዜ ያከራያል? የኪራይ ወሉ እንዴት መደረግ እንዳለበትና ሌሎች ከገጠር መሬት በኪራይ መሰጠትና ከባለሀብት ጋር በመሆን እንዴት ማልማት እንደሚቻል ህጉ በዝርዝር በአንቀፅ 2(4)፣ 8(1)(2)(3) ላይ ደንግጎት የምናገኘው የአርሶ አደሩ መብት ነው፡፡
2.የገጠር መሬትን በስጦታ ማስተላለፍ
አዋጁ በአንቀፅ 5(2) ላይ
ማንኛውም በገጠር መሬት የመጠቀም መብት ያለው አርሶ አደር፣ ከፊል አርብቶ አደር፣ አርብቶ አደር ቤተሰብ አባል ከቤተሰቡ በስጦታ ወይም በውርስ ወይም አግባብ ባለው ባለስልጣን የገጠር መሬት በይዞታ ሊያገኝ ይችላል፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡
ይሄውም የገጠር መሬት በይዞታ መብት የሚተላለፈው ጠበብ ባለ መልኩ በቤተሰብ መካከል መሆኑን የሚያሳይ ነው:: አባል የሚባለው ማን እንደሆነ በትርጉም ክፍሉ አንቀፅ 2(5) ላይ ‘’የይዞታ ባለመብቱን መተዳደርያ ገቢ በመጋራት በቋሚነት አብሮ የሚኖር ማንኛውም ሰው ነው፡፡’’ በማለት በስጦታ ለማስተላለፍ ያለው መስፈርት ከደማዊ ወይም ጋብቻዊ ትስስር ወጣ ባለመልኩ ባለው ኢኮኖምያዊ ትስስር ላይ ብቻ ተመሰርቶ አንዱ ያለውን በገጠር መሬት ባለይዞታነት የመጠቀም መብቱን በስጦታ ማስተላለፍ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ የማውረስ መብት የአዋጅ አንቀፅ 2(4) ‘’የይዞታ መብት ማለት አረሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩና አርብቶ አደሩ የገጠርን መሬት ለቤተሰቡ አባል ወይም ሌሎች በህግ መብት ለተሰጣቸው ወራሽች ለማውረስ የሚኖረው መብት ነው’’ ሲል በአንቀፅ 8(5) ላይ ደግሞ “ማንኛውም ባለይዞታ በገጠር መሬት የመጠቀም መብቱን ለቤተሰቡ አባላት የማውረስ መብት አለው ሲል ይደነግጋል፡፡ እነዚህን ድንጋጌዎች አያይዘን ስናይ የሚወረሰው በገጠር መሬት የመጠቀም መብት እንደሆነና ይህም አርሶ አደሩ ሆነ ከፊል አርብቶ አደሩና አርብቶ አደሩ የማውረስ መብታቸው የተጠበቀላቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህ ለገጠር ልማት ስትራተጂ ግብ መምታት ያለው ፋይዳ ሲታይ እነዚህ የተለያዩ የህ/ሰብ ክፍሎች በይዞታቸው ያለውን የገጠር መሬት ለማልማት የሚያወጡትን ጉልበትና ገንዝብ ለወራሾቻቸው የሚተላለፍ መሆኑን ተገንዝበው በጥሪታቸው ላይ የባለዋስትናነትና የአመኔታ ስሜት በመፍጠር የበለጠ ለማልማት እንዲተጉ የሚያደርጋቸው ነው፡፡ የባለይዞታዎች ግዴታዎችን ስንመለከትም፤
መሬቱን በኣግባቡ የመጠቀምና የመንከባከብ ግዴታ
አንድ አርሶ አደር፣ ከፊል አርብቶ አደር ወይም አርብቶ አደር በይዞታው ስር ያለን የገጠር መሬት በአግባቡ የመጠቀም እና የመንከባከብ ግዴታ አለው:: አዋጁ በአንቀፅ 10(1) ላይ ግዴታውን በአግባቡ ካልተወጣና በመሬቱ ላይ ጉዳት ካደረሰ የመሬት ተጠቃሚነት መብቱን ሊያጣ እንደሚችልም ይደነግጋል፡፡ ይህን ድንጋጌ ከዘላቂ ልማት አኳያ ስናየው የአሁኑ ትውልድ ያለውን ሃብት (resource) በማባከን ከሚገባው በላይና ያለኣግባብ የሚጠቀም ከሆነ ዘላቂ ልማት የሚባል ነገር ሊታሰብ አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ የነገው ትውልድ ተስፋ እንዲጨልም ስለሚያደርግ ህጉ የዚህ ዓይነት ግዴታ በባለይዞታዎቹ ላይ መጣሉ አገራችን የተያያዘችውን የልማት አቅጣጫ ታሳቢ ያደረገ ለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡
የአዋጁ አንቀፅ 10(2) በሚከተለው መልኩ
የመስኖ ቦዮችና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች በሚዘረጉበት ወቅት በባላይዞታው መሬት ላይ የሚያልፍ ከሆነ ይህን የመቀበል ግዴታ አለበት’’ ሲል የንብረት አገልጋይነት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል:: ይህ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ህግ በባለይዞታው ላይ ጫና እንደፈጠረ ነገር ግን ያለዚህ የንብረት አገልግሎት ግዴታ የመሰረተ የልማት ስራን በማከናወን የከተማም ሆነ የገጠር ልማቱን ወደተፈለገው ደረጃ ለማድረስ ስለማይቻል ዜጎች ሊከፍሉት የሚገባ የልማት ዋጋ ነው፡፡
የመተባበር ግዴታ
አንድ የገጠር መሬት ባለይዞታን በማስመልከት በአንቀፅ 10(3) ላይ “ባለይዞታው አግባብ ባለው ባለስልጣን የገጠር መሬቱ እንዲለካ ወይም የቅየሳ ስራ እንዲካሄድበት ሲጠየቅ የመተባበር ግዴታ አለበት” በማለት ይደነግጋል ይሄውም ያለ እንደዚህ ያለ ግዴታ የገጠር መሬት አስተዳደርን ስርዓት ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማደራጀትም ሆነ የባለይዞታነት ማስረጃ መስጠት አደጋች ሰለሚሆን ህግ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዚህ ዙርያ ከአሁን ቀደም ይከሰት የነበረውን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ችግር በማስቀረት ለልማት ስትራጂው ተግባራዊነት በሚያገለግል መልኩ በዘመናዊና የተደራጀ አግባብ ለመምራት የተጣለ ግዴታ ነው፡፡
የማሳወቅ ግዴታ
“ማንኛውም የገጠር መሬት ባለይዞታ በመሬቱ የመጠቀም መብቱን ሲተው አግባብነት ላለው ባለስልጣን የማሳወቅ ግዴታ ኣለብት” ይሄውም አንቀፅ 10(4) እንደዚህ ያለ ግዴታ ሲጥል አንድ የመሬት ባለይዞታ መሬቱን በሆነ ምክንያት የማያለማውና የማይጠቀምበት ከሆነና ዝም ብሎ ያለአገልግሎት እንዲቀር የሚየያደርግ ከሆነ በእጅጉ ልማቱን እንደሚጎዳ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ልማት ወደ ኃላ የሚጐትት ነው፡፡ የልማት መሳርያ የሆነን መሬት ጥቅም ላይ እንዳይውል ማድረግ የገጠር መሬት ተጠቃሚነትን የሚፃረር በመሆኑ ሊስተናገድ የሚችል ግድፈትም አይደለም፡፡ ስለዚህ ግዴታው ህዝባዊ ፖሊሲን መሰረት ያደረገ መሆኑ ልንገነዘብ ይገባል ፡፡
የመተባበር ግዴታ
ቀደም ሲል እንደተገለፀው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን መሰረት በማድረግ ለዚህ አዋጅ ተፈፃምነት ሲባል የራሱ አደረጃጀት እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ዜጐች በገጠር መሬት የመጠቀም መብታቸውን ለማስከበር እንደሚጥሩ ሁሉ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን ስርዓት ባለው መንገድ ለመምራት ከሚደራጀው ቢሮክራሲ ጋር ተባብረው ካልሰሩ በአንድ እጅ ማንጨብጨብ ስለሚሆን የግድ መተባበርና አብሮ ለልማቱ ስኬት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ (አንቀፅ 18)
የባለይዞታነት መብት ቀረ ስለመሆን
1.ባለይዞታዎቹ የሞቱና ወራሽ የሌላቸው ከሆኑ በይዞታቸው ስር የነበረው መሬት በሽግሽግ ለሌላ ሰው ሲሰጥ ወይም በመንግስት እጅ ሲሆን መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡
2.በሰፈራ ወይም ሌላ ምክንያት ከአካባቢያቸው በህግ ከተወሰነው ግዜ በላይ የሌሉ መሆኑ ሲረጋገጥና መሬታቸው በአካባቢው የገጠር መሬት አስተዳደር ለሌላ ሰው ሲታደል፡፡
3.ለገጠር መሬት የመስኖ አገልግሎት ፍትሃዊ አጠቃቀም ሲባል ሽግሽግ ሲደረግ መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡
4.ባለ ይዞታው በአንቀፅ 10(1) ያለውን ግዴታ ሳይወጣ ሲቀርና በዚህ ምክንያት የባለይዞታነት መብቱን እዲያጣ ሲወሰንበት መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡
5.በአንቀፅ 7(2) መሰረት የሌሎች ባለይዞታዎች በገጠር መሬት የመጠቀም መብት ፀንቶ የሚቆይበት የጊዜ ገደብ በክልሎች የገጠር መሬት አስተዳደር ህግ መሰረት ሲወሰን የገጠር መሬት ባለይዞታዎች የጊዜ ገደቡ ሲያልቅ የባለይዞታነት መብታቸው ቀሪ ይሆናል፡፡
ስለዚህ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/97 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት የገጠር መሬት ባለይዞታነት መርህን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለውን የገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራተጂ ከግብ የማድረስ አላማ ያለው ነው፡፡ ይህ አዋጅ የመሬት ስርዓቱ አደራጃጀት፣ የባለይዞታዎች መብትና ግዴታ ግልፅ በሆነ አግባብ በመደንገግ ከአሁን ቀደም የነበሩትን የአዋጅ ቁጥር 89/89 ግድፈቶች በሚያስወግድ መልኩ የወጣም ነው፡፡ ስልጣኞች የአዋጁን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች ተረድተው ለተግባራዊነቱ ያለስለስ ጥረት እንዲያደርጉ የዜግነትም የሙያም ግዴታ እንዳለባቸው በማወቅ በትጋት እንዲሰሩና የህገ መንግስቱን መርሆችና ሌሎች ህጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡