- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9034
የጋራ ባለሃብትነት (Joint Ownership)
ህገ መንግስታዊ መሰረቱ
የንብረት መብት ከጥንት ሮማውያን ጀምሮ የህግ ጥበቃ ተሰጥቶት እንደየ ስርዓተ ማህበሩ ለዚያ የሚመጥን አሰራርና አደረጃጀት ተዘርግቶለት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሰው ልጆች የእውቀትና መስተጋብራዊ አድማስ መስፋት ጋር እያደገ የመጣ መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ነው፡፡ ይህ መብት አሁን ባለንበት ዘመነ ግሎባላይዘሽን ሳይቀር ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት አገሮች በህገ መንግስታቸውና ከዚያ በታች ባሉ ሌሎች ህጐች እንደ አንድ የዜጐቻቸው የሰብአዊ መብትና ነፃነት ማረጋገጫ ወስደው በተግባር እየሰሩበት ያለም ነው፡፡
የጋራ ባለሃብትነት መብት አሁን ኢትዮጵያ እየተከተለችው ካለው ህገ መንግስታዊ ስርዓት አኳያ ሲታይም ዜጐች ከመሬት ባለይዞታነት መብት (possessory right) ውጭ ባለ ሌላ ንብረት ላይ ሰፊ የሆነ የግል ይሁን የጋራ ባለቤትነት መብት (ownership right) በሚያጐናጽፍ መልኩ በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሶስት መሰረታዊ መብቶትና ነፃነቶች በሚለው ርእስ ስር ህገ-መንግሰታዊ እውቅና የተሰጠው የዜጐች መብት ነው፡፡ በመሆኑም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 40(1) ላይ፤
ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ/መሆኗ ይከበርለታል/ ይከበርላታል፡፡ ይህ መብት የህዝብን ጥቅም ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በህግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን ዜጐች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል፡፡
ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህን ህገ መንግስታዊ የንብረት ባለቤትነት መርህ ከአጠቃላይ የህገ መንግስቱ ይዘት ጋር በማገናዘብና ዘርዘር በማድረግ ለዜጐች የሚሰጠውን መብት ስንመለከት ህገ መንግስቱ የዜጐች የግልም ይሁን የጋራ የንብረት ባለቤትነት መብትን መርህ የሚከተል ሲሆን ለህዝብ ጥቅም ሲባል ግን በህግ መብቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ልክ በአንቀፅ 40/8/ ላይ እንደተደነገገው ሊገደብ የሚችል ነው፡፡ ዜጐች የንብረት ባለቤትነት መብት በህገ መንግስቱ ተረጋግጦላቸዋል ማለት አንዱ የሌለውን የሚንቀሳቀስ ይሁን የማይንቀሳቀስ ንብረት መብት ሲጥስ የፍ/ብሄር ወይም የወንጀል ሃላፊነት አያስከትልበትም ማለት እንዳልሆነና አንድ ሰው የሌለውን ሰው የንብረት መብት በማክበር ንብረት ለመያዝ፣ ለመጠቀም ለማውረስ፣ ለመሸጥ በሌላ መንገድ ለማስተላለፍ እንደሚችል የሚደነግግ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ንብረት መያዝ ሲል አንድ ዜጋ በሚንቀሳቀስ ንብረት ላይ የባለቤትነት መብት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ደግሞ በሁለት ከፍሎ እንደ ቤትና ሌሎች በመሬት ላይ የሚያፈራቸው ሃብቶችን በማስመለከት የባለቤትነት መብት እንዲሚኖረውና በመሬት ላይ ግን በአንቀፅ 40/3/ መሰረት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብቶች የህዝብና የመንግስት ንብረቶች ስለሆኑ የባለይዞታነት መብት ብቻ ኖሮት በመሬት የመጠቀም መብትን ብቻ የሚፈቅድ ነው፡፡ ንብረት መሸጥን በሚመለከትም በተመሣሣይ መንገድ አንድ ኢትዮጵያዊ በጉልበቱና በገንዘቡ ያፈራውን ቤት፤ ሰብል ወ.ዘ.ተ. መሸጥ የሚችል ሲሆን ከሚንቀሳቀስ ንብረት አኳያ ሲታይም እንደዚሁ የመሸጥ መብቱ የተጠበቀ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የመንግስትና የህዝብ ንብረት ብቻ የሆነውን መሬት ግን የህግ መንግስቱ አንቀፅ 40/3/ “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጽያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው፡፡” በማለት ስለሚደነግግ በአንቀፅ 40/1/ ያለው “የመሸጥ” የሚለው የህገ መንግስቱ ሃይለቃል መሬትን አይመለከትም፡፡ የግል ንብረትን ማውረስና ማስተላለፍ በሚመለከት ከመሬት በስተቀር ማንኛውም ዜጋ ፍ/ብሔር ህጉ በሚያዘው መሰረት ንብረቱን ያለ ኑዛዜና በኑዛዜ ማውረስ፤ በስጦታ፤ በአላባ ወ.ዘ.ተ. ማስተላለፍ የሚችል ሲሆን መሬት በውርስ የማግኘት ጉዳይ የሚወሰነው ግን በፌዴራልና ክልል መንግስታት የገጠርንና የከተማን ቦታ አስተደደርና አጠቃቀምን መሰረት በማድረግ በሚወጡ አዋጆችና ደንቦች ሆኖ ሕጉ በሚፈቅደው መሰፈርት ብቻ በውርስ የሚተላለፍ የንብረት መብት እንጂ እንደሌላው ንብረት ተወላጅ ወይም የኑዛዜ ወራሽ በመሆን መውረስ የማይቻል የንብረት መብት ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ በሌላ መንገድ ማስተላለፍ ሲልም በመሬቱ ላይ ያለውን የተጠቃሚነት መብት ወይም ሌላ እንደ ቤት ያለ የማይንቀሳቀስ ንብረትና ሌሎች የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች በመያዣ፣ በአላባ፣ በስጦታ፣ በኪራይ ወ.ዘ.ተ. ስለሚኖር የንብረት መብት ማስተላለፍ የሚመለከት ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት በንብረት ባለቤትነት መብት የሚከተለው መርህ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው ሲሆን አሁን ከያዝነው የጋራ ባለሃብትነት መብት አንፃር ህግ-መንግስቱ ምን ይላል? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ስናይ በአንቀፅ 40/2/ ላይ :-
ለዚህ አንቀፅ አላማ ‘’የግል ንብረት’’ ማለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም ህጋዊ ሰውነት በህግ የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ማህበራት ወይም አግባብ በአላቸው ሁኔታዎች በተለየ የጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማህበረሰቦች በጉልበታቸው በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና የተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት ነው፡፡
በማለት ይደነግጋል :: የያዝነው ርዕስ ጉዳይ ህገ-መንግስታዊነት (constitutional standing) ለማወቅ ይረዳን ዘንድ ‘’……በህግ በተለይ የጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማህበረሰቦች (communities) በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና (tangible) የተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት ነው (intangible property))” :: የሚለውን የህገ መንግስቱ ሃይለቃል ብቻ ብንወስድ የንብረት ባለቤትነት መብት በጋራም ሊቋቋም እንደሚችልና ዜጒች በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው (tallent) ወይም በገንዘባቸው የጋራ ባለሃብት በመሆን ተደራጅተው መስራት እንደሚችሉ የሚፈቅድ ነው:: የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረቶች ተጨባጭነት ያለቸው (tangible or corporeal chattles) ወይም ተጨባጭነት የሌላቸው የንብረት መብቶች (intangible or incorporeal chattles) አንደ ፈጠራ ስራ (patent) የቅጂ መብት (copyright) ወ.ዘ.ተ. ያሉ ንብረቶች ሊሆኑ እንደሚችሉም የሚያስገነዝብ ነው:: ሌላው ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለውን አንቀፅ 31ን ስንወስድ፤
ማንኛውም ሰው ለማንኛውም አላማ በማህበር የመደራጀት መብት አለው፡፡ ሆኖም አግባብ ያለውን ህግ በመጣስ ወይም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በህገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ይሆናሉ፡፡
ይላል ይሄውም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትለው ዜጐች በኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊም ሆነ በፖለቲካው መስክ ሊደራጁና በጋራ ሰርተው የውጤቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ የሚፈቅድ ነው፡፡ ዜጐች በጋራ የንግድ ማህበር መመስረት፣ የጋራ ባለሃብት የመሆንና በጋራ ሰርቶ የመበለፀግ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው የንብረት ባለቤት መሆን እንደሚችሉም የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ መብት ከማስጠበቅ አኳያ የመንግስትን ግዴታ በማስመልከት በአንቀፅ 89(1) ላይ ‘’መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊን የሀገሪቱ የተጠራቀመ እውቀትና ሃብት ተጠቃሚዎች የሚሆኑበትን መንገድ የመቀይስ ኃላፊነት አለበት::’’ ይላል እንዲሁም ዜጐች በግልም ሆነ በጋራ ለመሰራትና በውጤቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ሁኔታ የመፍጠር ግዴታ የመንግስት መሆኑን በሚያሳይ መልኩ በአንቀፅ 89(2)ላይ ”መንግስት የኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል እኩል እድል አንዲኖራቸው ለማድረግ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትን የማመቻቸት ግዴታ አለበት::” በማለት በዜጐች መካከል ፍትሓዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የማስቻል ግዴታ የመንግስት እንደሆነ ይደነግጋል :: በመሆኑም መንግስት ዜጐች ንብረት በማፍራት ሂደት በጋራም ሆነ በግል ሰርተው ባለሃብት ለመሆን እኩል እድል እንዲያገኙ የሚያስችል ህግና ደንብ ያወጣል፤ በዚህም ሂደቱ ስርዓት ባለው መንገድ እንዲከናወን የጨዋታውን ህግ ከማውጣት ባሻገር ተገቢውን ቁጥጥር ያደርጋል:: ስለዚህ ከህገ-መንግስቱ አንቀፅ 89 ይዘት መገንዘብ የሚቻለው መንግስት ሁኔታውን ያመቻቻል ዜጐች ደግሞ የተፈጠረውን ምቹ የልማት ሁኔታ ተጠቅመው በሙሉ አቅማቸው በመስራት የላባቸው ውጤት ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል የግልም ሆነ በጋራ የሃብት ባለቤት የመሆን መርህን መሰረት ያደረግ መሆኑን ነው፡፡ መንግስት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 89 ላይ የተዘረዘሩትን ኢኮኖሚ ነክ መብቶች ተግባራዊ ለማድርግና ህገ-መንግስታዊ ግዴታውን ለመወጣት በአንቀፅ 51/5/፣ 55/2//ሀ//ሰ/ እና 77/5/ የተደነገጉትን የግዙፍነት ያላቸውና ሌላቸው የንብረቶች መብቶች ለማስጠበቅ በርካታ ህጐች የህገ መንግስቱን የንብረት መብት መርሆች ተከትለው እንዲወጡና በስራ ላይ እንዲውሉ አድርጓል፡፡ የነዚህን ህጐች ዝርዝር ይዘት ቆይቶ በዚህ ፅሁፍ የሚካተት ቢሆንም ለመንደርደሪያነት ያገለግለን ዘንድ አጠር አድርገን ለማየት እንሞክራለን፡፡
የገጠር መሬት አስተደደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/97 የጋራ ንብረት መብትንና አጠቃቀምን በማስመልከት በአንቀፅ 2 (19) ላይ የአካባቢ ነዋሪዎች በጋራ ይዞታነት ለግጦሽ፣ ለደንና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲጠቀሙበት በመንግስት የገጠር መሬት ሊሰጣቸው እንዲሚችል ይደነግጋል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 5(3) እንደ የአስፈላጊነቱ የወል (የጋራ) ይዞታ የነበረውን የገጠር መሬት መንግሰት ወደ ግል ይዞታ ሊያዛውር እንደሚችል የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 51(5) እና 89(5) 52(2) መርሆችን መሰረት በማድረግ ይደነግጋል፡፡ እንደዚሁም የህገ-መንግስቱን የአንቀፅ 35(1) እና (2) መርህ በመከተል በአዋጁ አንቀፅ 6(4) ላይ መሬት የባልና የሚስት የጋራ ከሆነ ወይም በሌሎች በጋራ የተያዘ ከሆነ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተሩ ለሁሉም የጋራ ባለይዞታዎች ስም መዘጋጀት አለበት በማለት የፆታ እኩልነትና የጋራ ባለሃብትነት መብትን በሚያረጋግጥ መንገድ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አዋጅ ይዘት ለመረዳት የሚቻለው በገጠር መሬት የመጠቀም ወይም ባለይዞታነት መብት (possessory right or jus possidendi) በጋራ ባለ ሃብትነት ሊያዝና ሊተዳደር እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡
የፈጠራ፣ አነስተኛ ፈጠራና የኢንዱስትሪያዊ ንድፍ አዋጅ ቁጥር 123/87 እንደዚሁ በአንቀፅ 7(2) እና (5) ላይ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ሰዎች በጋራ አንድ የፈጠራ ስራ ካከናወኑ የጋራ ፖተንት መብት ይኖራቸዋል ሲል የሚደነግገው የህገ-መንግስቱን አንቀፅ 51(19) እና 55(2)(ሰ) እና 89(1) መርሆችን ተከትሎ ነው:: ይሄውም የግዙፍነት የሌለው የንብረት ባለቤትነት መብት በግልና በጋራ ሊያዝ እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡
የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/97 የህገ-መንግስቱን የንብረት መርሆች በመከተል በአንቀፅ 2(29) ላይ የጋራ ባለቤትነት ስራ ማለት ምን ማለት እንደሆነና በአንቀፅ 20(2) የጋራ ስራ አመንጪዎች መብት ፀንቶ የሚቆይበትን ጊዜና በአንቀፅ 21(2) የጋራ ስራ አመንጪነት መብት እንዴት እንደሚገኝ ይደነግጋል ይህም የቅጅና ተዛማጅነት ያላቸው የአእምሮ ንብረቶች በጋራ ለማመንጨትና በጋራ ባለሃብትነት ተጠቃሚ የመሆን መብት በህግ ጥበቃ የተሰጠው የግዙፍነት የሌለው ንብረት መብት እንደሆነ የሚያስረዳ ነው፡፡
የንግድ ምልክት ምዝገበና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 በአንቀፅ 18 ላይ ስለ የወል የንግድ ምልክት ለማን ሊሰጥ እንደሚችል በሚገልፅ አኳኋን የወል የንግድ ምልክትን ለማስመዝገብ ስለሚችሉ ሰዎች በሚል ርእስ ስር “የሰራተኛ ማህበራት፣ ወይም ፌዴሬሽኖች የአባሎቻቸውን መብት ለማስጠበቅ የወል የንግድ ምልክት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ፡፡” ሊል ይደነግጋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ግለሰቦች በተናጣል የጋራ የንግድ ምልክት ማስመዝገብና በዚያ የጋራ የንግድ ምልክት ተጠቃሚዎች ለመሆን እንደሚችሉና ለየት ባለ ሁኔታ በማህበር ተደራጅተው ተቋማዊ በሆነ መንገድ ግለሰቦች ማህበራቸው ስም የንግድ ምልክት የጋራ ባለቤት ለመሆን እንደሚችሉ ወይም ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ማህበራት በተሰጣቸው ህጋዊ ሰውነት አማካይነት በፌዴሬሽን ተደራጅተው የጋራ የንግድ ምልክት ባለቤት ለመሆን እንደሚችሉ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
የዕፅዋት አዳቃዮች መብት አዋጅ ቁጥር 481/98 የህገ-መንግስቱን አንቀፅ 51(19)፣ 55(ሰ) እና 91(3) መርሆች በመከተል በአንቀፅ 10(2) ላይ ዝርያው በጋራ በማዳቀሳቸው ወይም በጋራ ወራሾች በመሆናቸው ምክንያት ሁለት ወይም ከሁለት የበለጡ ሰዎች የዕፅዋት አዳቃዮች መብት ለማግኘት መብት ያላቸው በሆነ ጊዜ መብቱ ለሁሉ በጋራ ይሰጣቸዋል…” በማለት ይደነግጋል ይህም የሚያሳየው ዜጐች አእምሯቸውን ተጠቅመው፤ ጉልበታቸውንና መዋእለ ንዋያቸውን በጋራ በማፍሰስ ይህን የታለመውን የዕፅዋት አዳቃይነት ስራ ካከናውኑና ውጤቱ አዋጁ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቶ ከተገኘ በጋራ የዕፅዋት አዳቃይነት ግዙፍነት የሌለው የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት ሊያገኙ እንደሚችሉ ህጋዊ ጥበቃ የሚሰጥ ነው፡፡
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የጋራ ባለሃብትነት መብት ከፍ/ብሄር ህጉና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስትን መርህ ተከትለው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ግዙፍነት ያላቸውና የሌላቸውን የንብረት መብት ለማስጠበቅ ከወጡ አዋጆች አንፃር ሲታይ የጋራ ባለሃብቶቹ የከተማም ሆነ የገጠር መሬት በተመለከተ የባለይዞታነት መብት (Possessory right or jus possidendi) የተጠበቀ መሆኑና ህገ-መንግስቱም ሆነ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሰረት በማድረግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 456/97 እና የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 272/94 ለዜጐች የሚያስገኙት መብት በመሬት የመገልገለን መብት (Possessry right) እንደሆነና ከዚህ ውጭ ባሉ በሚንቀሳቀሱም፣ በማይንቀሳቀሱም ሆነ ግዙፍነት ባላቸውና በሌላቸው ንበረቶች ላይ በግልም ሆነ በጋራ የባለቤትነት መብት (Ownership Right) እንደሚኖራቸው በህገ-መንግስቱና ከዚያ በታች ባሉ ህጐች ጥበቃ የተደረገለት የንብረት መብት በኢትዮጵያ የንብረት ህግ ማዕቀፍ (legal frame work) እንዳለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡