- Details
- Category: Property Law
- Hits: 9141
የንብረት አገልግሎት(Servitude)
የንብረት አገልግሎት ስለ ሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ጥቅም በአንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚጣል ግዴታ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1359) የንብረት አገልግሎት መሰረቱ (subject matter) የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን የመብቱ ምንጮች (sources) ህግ፣ ውልና ተፈጥራዊ አቀማመጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ቀደም ሲል እንደ አላባ መብት በሚንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት በሌላቸው እንደ ፈጠራ፣ የቅጅ መብትና፣ የኢንዱስትሪ ንድፍ በመሳሰሉ ንብረቶች ላይ ሊመሰረት አይችልም፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ሊመሰረት የሚችለው ግዙፍነት ባለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ነው፡፡
የንብረት አገልግሎት በፍ/ብሄር ህጉ ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1359 እስከ 1385 ባሉ ድንጋጌዎች የሚገዛ ሆኖ በጐረቤታሞች መካከል የመቻቻል፣ የመረዳዳት መሬቶቻቸውንና ግንባታዎቻቸውን የተሻለ ጥቅም ሊሰጥ በሚችል መልኩ እንዲገለገሉበት የሚያስችል መብት በመሆኑ ለሰዎች መልካም ግንኙነት ያለው ፋይዳ እጅግ የጐላ ነው፡፡ ይህ መብት ሰውን በመከተል ሊፈፀም የሚችል መብት (real right) ሲሆን በዋናነት መሰረቱ መሬት ነው፡፡ ይሄውም የንብረት አገልግሎት ግዴታ ያለበት የማይንቀሳቀስ ንብረት የግዴታ አገልጋይ (Servient tenament) ባለቤት በንብረቱ ላይ ያለውን መብት ለአገልግሎት ተቀባዩ (Dominant tenament የማይንቀሳቀስ ንብረት ጥቅም ሲባል መብቱ የሚገደብበት ዓይነት የንብረት አገልግሎት ወይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለ ግንኙነት ነው፡፡
የንብረት አገልግሎት መብት የሁለት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና የሁለት የተለያዩ ሰዎች መኖርን ታሳቢ የሚያደርግ ቢሆንም እነዚህ ሁለት የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሁሉ ግዜ ጥግ ለጥግ (contiguous) ወይም ተጓዳኝ (adjacent) መሆን አለባቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ ይህም ማለት የተወሰነ ርቀት ኖራቸውም እንደ እንሰሳትን ውሃ ማጠጣት (watering animals) ግጦሽ፤ (pasture) እንጨት መቁረጥ (cutting wood) ወይም እይታ (view) ወ.ዘ.ተ. ባሉ ሁኔታዎችም የንብረት አገልግሎት ሊመሰረት ይችላል፡፡ የንብረት አገልግሎት በግዴታ አገልጋይ (Servient tenement) የባለቤትነት መብት ላይ ተፅእኖ የሚፈጥር ነው፡፡ ለምሳሌ የንብረት አገልግሎቱ የማለፊያ መንገድን መሰረት ያደረገ በሚሆንበት ግዜ ከመሬቱ ቀንሶ ለመንገድ የሚሆን መሬት እንዲሰጥ:: የንብረት አገልግሎቱ የእይታ መብት (right to view) በሚሆንበት ግዜ ደግሞ ግርዶሽ የሚፈጥር ግንባታ ከማካሄድ እንዲቆጠብ ይገደዳል፡፡ የንብረት አገልግሎት አስፈላጊነት መለኪያው ለአገልግሎት ተቀባዩ (dominant tenament) ምን ያህል ጠቃሚ ነው የሚል ነው፡፡ አንድ ሰው ለሌላ ሰው የግዴታ አገልጋይ (Servient tenement) እንዲሆን የሚገደደው የንብረት አገልግሎት ተቀባዩ (Dominant tenement) የማይንቀሳቀስ ንብረት ያለ እንደዚያ ያለ አገልግሎት የማይንቀሳቀስ ንብረቱ ጥቅም ላይ የማይውል መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የንብረት አገልግሎት ግንኙነት ሊመሰረት አይችልም፡፡ በመሆኑም የንብረት አገልግሎት የሚሰጠው ለመሬቱ እንጂ ለሰው አይደለም፡፡ ሌላው መስፈርት በግዴታ አገልጋዩና በንብረት አገልግሎት ተቀባዩ መካከል የተፈጥሮ ትስስር (natural relationship) መኖር አለበት፡፡ የንብረት አገልግሎት መብት ከማይንቀሳቀሰው ንብረት ተለይቶ አገልግሎት ላይ ሊውል የማይችል የዋናው መብት ተጨማሪ (accessory) ነው፡፡ ይህ መብት በተፈጥሮ ቀጣይነት ያለው (perpetual) ሲሆን መሰረቱ ውል (convention) ወይም ህግ ነው፡፡ የመበቱና ግዴታው መሰረት ውል በሚሆንበተ ጊዜ ተዋዋዮች ግዴታው የሚቆይበትን ጊዜ በውላቸው ላይ በማስፈር ሊሰማሙ ይችላሉ፡፡ መብቱና ግዴታው የሚመነጨው ከህግ በሆነበት ጊዜ ደግሞ ህጉ በሚያዘው መሰረት ይፈፀማል፡፡ የንብረት አገልግሎት የግዴታ አገልጋይ ያለበትን ግዴታ ልዋጭ በመስጠት (redemption) ካልሆነ በስተቀር ካሳ (indemnity) በመስጠት ቀሪ ሊያደርገው አይችልም::
የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች (Kinds of Servitude)
የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች ሶስት ሲሆኑ እነሱም፡፡
Øአንደኛው ተፈጥራዊ የንብረት አገልግሎት (natural servitude) የሚባለው ሲሆን መነሻው የንብረት አገልግሎት ተቀባዩ (dominant tenament) እና የንብረት አገልግሎት ግዴታ አገልጋይ (servient tenament) ጆግራፍያዊ አቀማመጥን መሰረት ያደረገ እንደ በዝቅተኛ ቦታ ያለ ሰው ውሃ የማግኘት መብት ወይም እንደ በሁለት ማሳዎች ድንበር ወይም አጥር ባሉ ነገሮች ላይ የሚመሰረት የንብረት አገልግሎት ዓይነት ነው፡፡ ይህም የጆግራፊ አቀማመጣቸው የግዴታ አገልግሎት መሰጠትን የግድ ሲል ህግ በራሱ እውቅና (recognition) የሚሰጠው መብት ነው፡፡
Øሁለተኛው ህጋዊ የንብረት አገልግሎት (legal servitude) የሚባል ሲሆን ይህ ዓይነት የንብረት አገልግሎት ህግ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚፈጥረው ነው፡፡ ይህ የሚከሰተው መውጫ መግብያ የሌለው መሬት (enclave land) በሚኖርበት ግዜ ህግ መውጫ መግብያ እንዲኖረው ሲያስገድድ ወይም የኤሌክትሪክ፣ የውሃ፣ የቴሌ፣ የጋዝ መስመር ዝርጋታ ሲኖር በሌላው መሬት ላይ የዝርጋታ ስራው እንዲከናወን ህግ ሲያስገድድ የሚኖር የንብረት አገልግሎት ዓይነት ነው፡፡
Øሶስተኛው በውል የሚመሰረት የንብረት አገልግሎት (conventional or juridical servitude) የሚባለው ሲሆን የዚህ ዓይነት የንብረት አገልግሎት በሁለት እና ከሁለት በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚመሰረት ወይም አንድ ሰው በግሉ (unilaterially) እንደ ኑዛዜ ባለ ሁኔታ ሊመሰረት የሚችል ነው፡፡ ከፍ ብለን ካየናቸው ሁለት የንብረት አገልግሎት ዓይነቶች የሚለየው የዚህ ዓይነት ንብረት አገልግሎት ህጋዊ ውጤት እንዲኖረውና በተዋዋዮች መካከል በፍ/ህ/ቁ/1731 መሰረት ህግ ሆኖ እንዲያገለግል ከተፈለገ ውሉ በፅሁፍ መሆንና ስልጣን በተሰጠው አካል በፍ/ብ/ህ/ቁ 1723 መሰረት መመዝገብ ይኖርበታል ፡፡ ካልሆነ ግን የአስገዳጅነት ውጤት አይኖረውም::
የንብረት አገልግሎት አተገባበር (Servitude in Modes of Exercise)
vግልፅና ግልፅ ያልሆነ የንብረት አገልግሎት (apparent and non-apparent servitude) ግልፅ የንብረት አገልግሎት የሚባለው የሚገለፀው በሚታዩ ስራዎች (visible works) እንደ መስኮት፣ መዝጊያ፣ ሰርጥ (channel) እና ከመሬት በላይ የተዘረጋ ባምቧ ባሉ ዓይነቶች ነው፡፡ ግልፅ ያልሆነ የንብረት አገልግሎት በመሬት ላይ የሚታይ እንደ ያለመገንባት ወይም ከተወሰነ ከፍታ በላይ ያለመገንባት ባሉ ሁኔታዎች የሚገለፅ የንብረት አገልግሎት ነው፡፡ በሁለቱም የንብረት አገልግሎቶች መካከል ያለው ልዩነት ግልፅ በሆነው የንብረት አገልግሎት በይዞታ ለ10 ዓመት በእጅ በማቆየትና ግብር በመክፈል (usucaption) የንብረት አገልግሎት መብት ማግኘት የሚቻል ሲሆን ግልፅ ባልሆነው የንብረት አገልግሎት በዚህ መልኩ መብትን ማግኘት አይቻልም፡፡
vቀጣይነት ያለውና ቀጣይነት የሌለው የንብረት አገልግሎት (continuous and discontinuous servitude) ቀጣይነት ባለው የንብረት አገልግሎት መብቶቹ ስራ ላይ ለማዋል የሰውን ጣልቃ ገብነት የማይጠይቁና አንድ ግዜ ከተዘረጉ በኋላ በራሳቸው ግዜ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ የውሃ ቧንቧ (pipes of water) የቆሻሻ ማስወገጃ (sewerage) እና አለመገንባት (not to build) ወይም ከተወሰነ ከፍታ በላይ አለመገንባት (not to build beyond a certain height) ያሉት ናቸው፡፡ ቀጣይነት የሌለው የንብረት አገልግሎት የሚባለው በመብቱ ለመገልገል የሰውን ጣልቃ ገብነት ወይም አንቀሳቃሽነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህም እንደ የመንገድ መብት (the right to way)፣ ውሃ መቅዳት (drawing water)፣ ግጦሽ (pasture) እና ከመሬት እንደ ድንጋይና መአድን ማውጣት (extracting minerals) ወ.ዘ.ተ. ያሉት ናቸው፡፡
vአዎንታዊና አሉታዊ የንብረት አገልግሎት (positive and negative servitude)
አዎንታዊ የንብረት አገልግሎት (positive servitude) በግዴታ አገልጋዩ (servient tenement) መሬት ላይ ገብቶ ሲገለገል የሚከሰት የንብረት አገልግሎት ሲሆን በግዴታ አገልጋዩ የንብረት ባለቤትነት ጣልቃ የመግባት (interference) ውጤትን የሚያስከትል ቢሆንም ከተገልጋዩ መብት አኳያ ሲታይ እንደ አዎንታ የሚወሰድ ነው፡፡
አሉታዊ የንብረት አገልግሎት (negative servitude) የሚባለው የግዴታ አገልጋይ (servient tenement) በሌላኛው የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ጫና ሳይፈጥር (without imposition) በባለቤቱ ተፈጥራዊ የባለቤትነት መብት (inherent ownership right) ተፅእኖ ላለመፍጠር በመብቱ ላይ ገደብ ሲጣልበት የሚከሰት እንደ ከተወሰነ ከፍታ በላይ ያለመገንባት ወይም ጭራሽ ያለመገንባት የሚገለፅ በግዴታ አገልጋይ ላይ ገደብ የሚጥል በመሆኑ ከግዴታ አገልጋዩ የባለይዞታነት መብት አንፃር ሲታይ አሉታዊ ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡
ስለዚህ የንብረት አገልግሎት መብት በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ብቻ የሚመሰረት ሆኖ ከዜጐች በንብረት የመገልገል መብት ጋር ትስስር ያለው በግዴታ አገልጋይ የባለቤትነት መብት ላይ በመጠኑም ቢሆን ተፅእኖ የሚያሳርፍ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ የንብረት አገልግሎት ከአላባ ጋር በንፅፅር ሲታይ ልዩነታቸው የአላባ መሰረቶች የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ግዙፍነት ያላቸው ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው ንብረቶች ሲሆኑ የንብረት አገልግሎት መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት ብቻ መሆኑ አንዱ የሚለያቸው ነጥብ ነው፡፡ ሌላው ልዩነታቸው አላባ በግዚያውነት የሚተላለፍ እና ከንብረቱ ተለይቶ (independently) ሊተላለፍ የሚችል መብት ሲሆን የንብረት አገልግሎት ከማይንቀሳቀስ ንብረት ተለይቶ ሊሰራበት የማይችልና ዘላቂ ግንኙነትን የማስከተል ውጤት ያለው በመሆኑ የንብረቱ መከፋፈል ሊያስቀረው የማይችል ነው፡፡ እንደዚሁም የንብረት አገልግሎት የሚኖረውም ለባለቤቱ ጥቅም ሲባል ሳይሆን መብቱ የሚኖረው ለሌላ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት መብትና ጥቅም ሲባል ነው፡፡ የአላባ መብት ግን ለባለቤቱ ጥቅም ሲባል የሚደረግ ሊሆን ይችላል፡፡ የአላባ መብት ጉዳይ (object) የማይንቀሳቀስ፣ የሚንቀሳቀስና ግዙፍነት የሌለው የንብረት ባለቤትነት መብት ሲሆን የንብረት አገልግሎት ጉዳይ (object) ግን የማንቀሳቀስ ንብረት በተለይ የመሬት ባለይዞታነት መብት ነው፡፡ የንብረት ባለቤትነት መብት ለብቻው ሊተላለፍ የሚችል ሲሆን የንብረት አገልግሎት ግን ከማንቀሳቀስ ንብረቱ ተነጥሎ (dismemberedly) ሊተላለፍ (assign) ወይም ሊከበር (attach) የሚችል ባለመሆኑ በሁለቱም መካከል ልዩነት አለ፡፡