- Details
- Category: Property Law
- Hits: 7601
የባለሃብት መብቶችና ግዴታዎች
ዋና ዋናዎቹ የባለሃብት መብቶች (ፍ/ሕግ ቁ. 1204(1) 1205(1) (2))
የባለቤትነት መብት ከሁሉም የሰፋ መብት መሆኑን ተመልክተናል። በዚህ ሰፊ የአዛዥነት መብት ተጠቃሚ የሆነ አንድ ሰው ንብረቱን ከሕግ ውጭ ቢወስድበት ወይም ቢነጠቅ የንብረቱ ባለቤት እንደባለቤትነቱ የመፋለም ክስ (petitory action) ለፍርድ ቤት በማቅረብ ንብረቱ እንዲመለስለት ወይም የባለቤትነት መብቱ እንዲታወቅለት ለመጠየቅ ይችላል። በተጨማሪም ባለሃብቱ ከንብረቱ ሊያገኝ ይገባው የነበረና የተቋረጠ ጥቅም በካሳ ወይም በኪሳራ መልክ እንዲተካለት ለመጠየቅ የሚችል ይሆናል። እንዲሁም ከንብረቱ ጋር በተያያዘ ማናቸውም የሓይል ተግባር ለመቃወም ይችላል /ፍ/ሕግ ቑ.1206/።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት /ህንፃ/ ባለሃብት የመሆን መብት አለው።
በሕግ ወይም በሕጋዊ ተግባር መብቱን የተገደበበት ሰው ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ሰው በሂወቱ እያለም ይሁን ከሞተ በኃላ ተግባራዊ የሚሆን ኑዛዜ በመተው ንብረቱ ለፈለገው ሰው ወይም ለህዝብ /መንግስት/ የማስተላለፍ መብት አለው /ለምሳሌ ፦ ፍ/ሕግ ቁ. 1205፣ 483፣ 857…፣ 2427…/
በንብረቱ የመጠቀም (የመገልገል) ፣ ከንብረቱ የተገኘ ፍሬ የመሰብሰብ፣
በንብረቱ ላይ አደጋ የሚደርስ መስሎ ሲታየው ወይም ጣልቃ ገብነት ሲያጋጥመው ይህንን ለማስወገድ/ለማስቀረት/ ተመጣጣኝ ሓይል የመጠቀም መብት በሕግ ተጠብቆለታል (ፍ/ሕግ ቁ.1206፣ 2053/2054)
ንብረቱ የተወሰደበት ፣ በንብረቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ወዘተ እንደሆነ ክስ የመመስረት መብት ኣለው (ፍ/ሕግ ቁ.1206)
ንብረቱ ለሚፈልገው ሰው የመሸጥ መብት አለው።
ንብረቱን እስከ መጣል ወይም መተው የሚደርስ መብት አለው። ሆኖም ግን በወንጀል ሕግ አንቀፅ 494 የተደነገገውን እንደተጠበቀ ነው።
እነዚህ መብቶች ከኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40-ጋር-ተያያዞ-መታየት አለበት።
የባለሃብት ግዴታዎች (ፍ/ሕግ ቁ.1204 (2))
መብትና ግዴታ የማይነጣጠሉ ተዛማጅ የሆኑ ፅንስ ሓሳቦች ናቸው። በአብዛኛው የአንዱ መብት ለሌላው ሰው ግዴታ ሲሆን እንዲሁም አንዱ ግዴታ ለሌላው ሰው መብት ይሆናል። በዚህም መሰረት የንብረት ባለሃብትነት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም የያዘ ነው። ግዴታዎቹ ወይም ገደቦቹ ከስምምነት ወይም ከሕግ ሊመነጩ ይችላሉ። ከግዴታዎቹ/ገደቦቹ/ መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
ባለሃብቱ ንብረቱ በሚጠቀምበት ጊዜ ለጐረቤቱ በማይጐዳ መልኩ መሆን አለበት (ፍ/ሕግ ቁ.1225, 1226) ንብረቱ ሕጋዊ ላልሆነ ተግባር ሊጠቀምበት አይገባም።
በወንጀል ሕግ (ለምሳሌ ከአንቀፅ 494-497 መጥቀስ ይቻላል) እና በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40(1) ስርም የተደነገጉ ግዴታዎች ኣሉት።
ከቤቱ /ከቆርቆሮው/ ላይ የሚወርደውን የዝናብ ውሃ የጐረቤቱን መብት እንዳይነካ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል (ፍ/ሕ ቁ. 1245)
ንብረቱ በሌላ ሰው ኣካል ወይም ህይወት ወይም ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ የጉዳት ካሳ የመክፈል (ፍ/ሕ ቁ. 2071-2089)
ንብረቱ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ ወይም በዕዳ እንዳያዝ በፍ/ቤት ትእዛዝ የተከበረ /የታገደ/ እንደሆነ ይህ ትእዛዝ የማስከበር (ፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁ. 154 ይመለከተዋል)
ከንብረቱ ከሚያገኘው ገቢ ወይም በሌላ ሁኔታ በመጠቀሙ ምክንያት ግብር የመክፈል (የግብር ኣዋጅ ይመለከተዋል)
መንግስት ተመጣጣኝ ካሳ በመክፈል የአንድ ሰው ንብረት ለህዝብ ጥቅም ብሎ የወሰደ እንደሆነ ባለንብረቱ ይህ ነገር ሲመጣበት የመቀበል (ኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40(8)፣ ፍ/ሕግ ቁ. 1460-1488 እና ሌሎች ኣዋጆች)
ሌሎች በርከት ያሉ ግዴታዎችም ሊኖሩት ይችላሉ።