Font size: +
21 minutes reading time (4132 words)

ሺሻን ለሽያጭ ከማቅረብና ከመጠቀም ጋር ተያይዘው የሚፈፀሙ ወንጀሎች

በልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ሺሻ በማስጨስ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ግለሰቦች እና የማስጨሻ ቤቶች መኖራቸውን የተረዳው የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና በሥሩ የሚገኙ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎችን እና ሺሻ ሲያስጨሱ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውለዋል፡፡ ሺሻን ሲያስጨሱ የነበሩ ግለሰቦች ላይም የወንጀል ምርመራ የተጣራባቸው ሲሆን በምርመራ መዛግብቱ ላይ በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ በኩል ተገቢውን የሕግ አስተያየትና ውሳኔ መስጠት ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ፍርድ ቤቶችና በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ሲታይ ያልነበረ በአንፃሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶችና በከተማ ነክ ፍትሕ ጽ/ቤቶች የአቤቱታ ምርመራና የክስ አቀራረብ ንዑስ የሥራ ሂደት ሲታዩ የነበረና ሺሻን አስመልክቶ በቂ መረጃና የሕግ ማዕቀፍ ያልነበረ በመሆኑ በተጣሩት የምርመራ መዛግብት ላይ ተገቢውን የሕግ አስተያየት እና ውሳኔ ለመስጠት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በመሆኑም የሺሻን ምንነት፣ ሺሻ የሚይደርሰውን ጉዳት፣ ሺሻን መጠቀም፣ ማስጠቀም እና ወደ አገር አስገብቶ ማከፋፈል ከሕግ አንፃር የሚያስከትለው ኃላፊነት ስለመኖሩ፣ ፖሊስና የወረዳ (ቀበሌ) አስተዳደር ሠራተኞች ሺሻ የሚያጨሱና የሚያስጨሱ ግለሰቦችን እንዲሁም የማስጨሻ ዕቃዎችን የሚይዙበትና ማስጨሻ ቤቶችን የሚዘጉበትን እንዲሁም ዐቃቤ ሕግ ሺሻ በሚያስጨሱ ግለሰቦች ላይ የተጣሩ የምርመራ መዛግብት ላይ የሕግ አስተያየት እና ውሳኔ የሚሰጥበት አግባብ ላይ እንደ አጠቃላይም ከሺሻ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ በማቅረብ ላይ ያተኮረ አነስተኛ ጥናት ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ በዚሁ መሠረትም ይህ አነስተኛ ጽሑፍ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

 የሺሻ ምንነት

ሺሻ የሚለው ቃል “ሺሼ” /Shishe/ ከሚለው የፐርሺያ ግንድ ካለው የአረቢኛ ቋንቋ የተወሰደ ቃል ሲሆን የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም በጠርሙስ ውስጥ ያለ ውሃ ማለት ነው፡፡ ሺሻ ከጠርሙስ ውስጥ ካለ ውሃ ውስጥ በቀጭን አየር ማስተላለፊያ ቱቦ በአፍ የሚሳብ የትምባሆ ምርት ነው፡፡ ሺሻ ለማጨስ ሁለት ነገሮች የሚያስፈልጉ ሲሆን እነርሱም የማጨሻ ዕቃውና የሺሻ ትምባሆው ናቸው፡፡ የሺሻ ትምባሆው በሺሻ ማጨሻ ዕቃው አናት በኩል ባለው ጎድጓዳ ሠሀን በኩል ተጨምሮ አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ ሺሻ ከ3ዐዐ ዓመታት በፊት በሠው ልጆች የሚታወቅ የትምባሆ ምርት ሲሆን ከባህላዊው ትምባሆ የሚለየው በተጨማሪነት መልካም መዓዛ ከሚሰጡ እና ጣፋጭነት ካላቸው ንጥረ ነገሮች ጋር ተቀይጦና ተደባልቆ አገልግሎት ላይ በመዋሉ ነው፡፡ በሺሻ ውስጥ የሚገኘው የትምባሆ መጠን ከ10 እስከ 20 ግራም የሚመዝን ሲሆን በሶስት ዓይነቶችም ይከፈላል፡፡ እነዚህም ሙአስል ወይም ማስል /Mu’essel or Maasel/፣ ቱምባክ ወይም አጃሚ /Tumbak or Ajami/ እና ጁራክ /Jurak/ ይባላሉ፡፡ ሙዜል /Mu’essel/ የሚባለው የሺሻ ዓይነት 3ዐ% ትምባሆ እና 7ዐ% ጣፋጭነት ያለው በፖም፣ በማንጐ፣ በሙዝ፣ በእንጆሪ፣ በብርቱካን፣ በወይን፣ በሜንታ፣ በካኘቹኖ ወይም በሌሎች ቃናዎች የሚዘጋጅ የሺሻ ዓይነት ሲሆን በተለያዩ ፍራፍሬዎች ምስል ባሸበረቀ ካርቶን ወይም የኘላስቲክ ከረጢት ታሽጐ ለገበያ ይቀርባል፡፡ ቱምባክ ወይም አጃሚ /Tumbak or Ajami/ የተሰኘው የሺሻ ዓይነትም ሙሉ በሙሉ ከንጹህ ጥቁር ትምባሆ የተዘጋጀና ሌላ ነገር የማይቀየጥበት የሺሻ ዓይነት ነው፡፡ ሶስተኛውና ጁራክ /Jurak/ ተብሎ የሚጠራው የሺሻ ዓይነት ደግሞ ከሕንድ እንደመጣ የሚታመንና በብዛት ህንድ ውስጥ የሚዘወተር እና በመካከለኛነት የሚመደብ ፍራፍሬዎችን የሚይዝ ከጣፋጭነቱ ጋር በተያያዘ የየትኛውም ፍራፍሬ ጣዕም እንዳይኖረው ተደርጐ የሚዘጋጅ የሺሻ ዓይነት ነው፡፡ ከሶስቱ የሺሻ ዓይነቶች መካከልም ሙዜል ወይም ማዜል የተባለው የሺሻ ዓይነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ በርካታ ተጠቃሚዎችን አፍርቷል፡፡

  • የሺሻ ማጨሻ መሣሪያ ራስ ከብረት የተሠራ አካል፣ ጠርሙስ፣ ከሰው አፍ ጋር የሚገናኝ ተጣጣፊ ተያያዥ ቱቦ አለው፡፡
  • የዕቃው ራስ ጎድጓዳ ሳህን ያለው ሲሆን በሚያጤሱበት ወቅት ከሰሉንና ትምባሆውን በመሸከም ያገለግላል፡፡
  • ጎድጓዳው ሳህን ትምባሆ ከተሞላ በኋላ በብልጭልጭ ወረቀት ወይም በብረት ይሸፈናል፡፡ ከሰልም ትምባሆውን እንዲያሞቅ በአናቱ ላይ ይደረጋል፡፡
  • ዝርጉ ሳህን ከጎድጓዳው ሳህን በታች የሚቀመጥ ሲሆን አስቀድሞ አገልግሎት ላይ የዋለ ከሰል ማስቀመጫ በመሆን ያገለግላል፡፡
  • ብረታማ አካሉ ቱቦ ያለው ሲሆን ከውሃው መያዣ ጃምባ ጋር በማገናኘት ያገለግላል፡፡

ሺሻ የሚያደርሰው ጉዳት

በዓለም ላይ በቀን ውስጥ ከ1ዐዐ ሚሊዮን ሕዝቦች በላይ ሺሻ የሚያጨሱ ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ፣ በቱርክ፣ በሕንድ፣ በፓኪስታን፣ በባንግላዲሽ እና በተወሰኑ የቻይና ክፍሎች ውስጥ ሺሻ ማጨስ የተለመደ እና ተራ የሆነ ተግባር ነው፡፡ በተወሰኑ የመካከለኛው ምስራቅ ክፍሎች ውስጥም ከሲጃራ ይልቅ ሺሻ የተሻለ ተመራጭነት ያለውና በብዙሀኑ የሕብረተሰብ ክፍል አገልግሎት ላይ የሚውል የትምባሆ ምርት ነው፡፡

አንድ ጊዜ ሺሻን ማጨስ ሀያ አራት ወይም አንድ ፓኮ ሲጃራ ከማጨስ ጋር የሚስተካከል ሲሆን የተለያዩ ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶች ሺሻ ሲጃራ ማጨስ ከሚያስከትለው የጤና ችግር ጋር ተመሳሳይ የሆነ የጤና ችግር እንደሚያስከትል ይጠቁማሉ፡፡ በዚሁ መሰረትም ሺሻን ማጨስ በዋናነት ሁለት ዋነኛ የሰውታችንን ክፍሎች እነሱም ሳምባችንን እና ልባችንን እንደሚጐዳ ተረጋግጧል፡፡ የሳምባ ካንሰር፣ የምግብ ማስተላለፊያ ቧንቧ ካንሰር፣ ቋሚ የሆነ የሳምባ በሽታ፣ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች፣ የሳንባ ምችና የአተነፋፈስ ችግሮች ሺሻ ማጨስ በጤና ላይ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሲጃራ ማጨስ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች በተጨማሪነት ሺሻ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች ያሉ ሲሆን የማጨሻ ቱቦውን በጋራ መጠቀም ለተላላፊ በሽታዎች ማጋለጡ እና በትምባሆ ላይ የሚጨመሩ አልኮል ወይም አነቃቂ ንጥረ ነገሮችን መጠቀም በተጨማሪነት የሚጠቀሱ ሺሻ በማጨስ የሚመጡ ጉዳቶች ናቸው፡፡ ሌላው ሺሻ መጠቀምን አሳሳቢ የሚያደርገው ቀደም ሲል ሺሻ አገልግሎት ላይ የሚውለው እንደ እነ ሕንድና ፓኪስታን ባሉ አገራት በገጠር አካባቢ በሚኖሩ አዛውንቶች ሲሆን አሁን አሁን ግን ሺሻ በተለያዩ አሕጉራትና አገራት በሰፊው ጥቅም ላይ ውሎ ይገኛል፡፡ በርካታ ምግብ ቤቶችና መዝናኛ ቦታዎችም ሺሻን ለደንበኞቻቸው ከሌሎች አገልግሎት ጋር በተጨማሪነት የሚያቀርቡ በመሆኑ የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በርካታ ወጣቶችም ሺሻ መጠቀምን እንደ መዝናኛ፣ ዘመናዊነትና አስደሳች ተግባር እየቆጠሩት መጥተዋል፡፡ ሺሻ እንደ አርሰኒክ፣ ኮባልት፣ ክሮሚየም እና ሊድ የመሳሰሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከባድና አደገኛ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የሚይዝ የትምባሆ ምርት ሲሆን ሺሻን መጠቀም ለአፍ እና የሽንት ከረጢት ካንሰር የሚያጋልጥ ከመሆኑም በተጨማሪ የወንዶችን የዘር ፍሬ ብዛትም እንደሚቀንስ በሺሻ ላይ የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሺሻ በነፍሰጡሮች በእርግዝና ወቅት በእናቲቱ ሲጨስ ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች በቀላሉ ወደ ፅንሱ ስለሚገቡ በፅንሱም ሆነ በእናትየዋ ላይ ጉዳት ያደርሳል ከጉዳቶቹ መካከልም እናቶች ፅንስ መሸከም ያለመቻል እና ለውርጃ የመጋለጥ እድላቸው የሠፋ ሲሆን ፅንሱ ቢወለድ እንኳን ከሚጠበቀው በታች የሆነ ክብደት ያለው ሕፃን ይሆናል የአተነፋፈስ ስርዓቱም የተዛባ መሆኑና ድንገተኛ ሞት በሕፃኑ ላይ ማስከተሉ በዋናነት የሚጠቀሱ ጉዳቶች ናቸው፡፡

ሺሻ በሁለተኛ አጫሾች /Passive Smokers/ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተም ሺሻ ከሚያጨሱ ሰዎች አካባቢ የሚገኙና የማያጨሱ ሰዎች ላይ ከሚያደርሳቸው ጉዳቶች መካከል የዓይንና የአፍንጫ ማቃጠልና ማስለቀስ፣ የጉሮሮ መከርከር፣ ከፍተኛ የራስ ምታት፣ የሳንባ ካንሰር፣ ድንገተኛ የልብ ምት ማቆም፣ የሳንባ ኢንፌክሽን፣ አስም፣ ብሮንካይትስ አለርጂክ እና ካንሰር አምጪ ለሆኑ ኬሚካሎች በእጥፍ መጋለጥ ይገኙበታል፡፡ 

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሺሻ በብዛት የሚጨሰው በጫት ማስቃሚያ ቤቶች ውስጥ በመሆኑ አጫሾችን በተለይም ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል ለሺሻና ሌሎች ተያያዥ ሱሶች ተጋላጭ የሚያደርግ ከመሆኑም በተጨማሪ ሺሻ የሚጨስባቸውና ጫት የሚቃምባቸው ቤቶች የወንጀል ፈጻሚዎች ዕቅድ መንደፊያና መሸሸጊያ ቦታ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡

ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ ከብሄራዊ የትምባሆ ድርጅት አክሲዮን ማህበር እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም በአገራችን ሺሻ በማጨስና በማስጨስ ተግባራት ላይ ያሉ ግለሰቦች ከሺሻ ምርት ጋር ካናቢስ /Cannabis/ የተባለ ሀሺሽ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1991 ዓ/ም በተፈረመ ስምምነት መሰረት ቁጥጥር የሚደረግበትን ሕገ-ወጥ የሆነ አደንዘዥ ዕፅ እና ሌሎች ባዕድ የሆኑ ነገሮች ቀላቅለው ጥቅም ላይ ያውላሉ፡፡ የሀሺሽና ሌሎች አደንዛዥ ዕጾች አጫሾችም የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈጸም የሕብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ እንዲያደፈርሱ አልፎ ተርፎም በአገረቷ ውስጥ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳይኖር የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡

ሺሻን መጠቀም፣ ማስጠቀም እና ከውጭ አገር አስገብቶ ማከፋፈል ከሕግ አንጻር የሚያስከትለው ኃላፊነት

የሺሻን ምንነትና የሚያደርሰውን ጉዳት ከተመለከትን በኢትዮጵያ ሕግ ሺሻን ማጨስ ወይም ማስጨስ የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት ስለመኖሩ መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሺሻ ከትምባሆ ምርቶች ውስጥ የሚመደብ ስለመሆኑ ብሄራዊ የትምባሆ ድርጅት አክሲዮን ማህበር ለጽ/ቤታችን በጻፈው ደብዳቤ ያረጋገጠ ሲሆን አክሲዮን ማህበሩ በአዋጅ ቁጥር 371/1985 አንቀጽ 1ዐ መሠረት የትምባሆ ምርቶችን /ውጤቶችን/ ከውጭ ለማስመጣት፣ ወደ ውጭ ለመላክ፣ ለመሸጥ፣ ለማዘጋጀትና በፋብሪካ ሰርተው ለማውጣት ለሚፈልጉ ሰዎችና ድርጅቶች ፈቃድ የመስጠት ስልጣን ያለው ስለመሆኑ ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሠረት ሺሻ ከትምባሆ ምርቶች የሚመደብ በመሆኑ አክሲዮን ማህበሩ ሺሻን አስመልክቶ ከፍ ብለው የተጠቀሱትን ተግባራት ማከናወን ለሚፈልጉ ግለሰቦች ፍቃድ የመስጠት ስልጣን አለው፡፡ ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት /ኢትዮጽያ/ አክሲዮን ማህበርም ይህንኑ ስልጣኑን መሰረት አድርጐ ሺሻ ወደ አገር ውስጥ ማስገባትና ማከፋፈል የሚፈልጉ ግለሰቦች የሚስተናገዱበትን ሁኔታ የሚያብራራ እ.ኤ.አ ከመስከረም 16 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን እየተሰራበት የሚገኝ መመሪያ አውጥቷል፡፡ እስከአሁን ድረስም ሺሻን ለአንድ ጊዜ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያስገቡ ከማህበሩ ፍቃድ የተሰጣቸው afrah  Tobacco እና Wambely Transport Service የተባሉ ሁለት ድርጅቶች ብቻ መሆናቸውን ከድርጅቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም ሺሻን መጠቀም እና ከብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት በሚገኝ ፍቃድ መሰረት ሺሻን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ማከፋፈል በሕግ ያልተከላከለ ይልቁንም ሺሻን በህጋዊ መንገድ ወደ አገር ማስገባትና ማከፋፈል እንዲሁም መጠቀም እንደሚቻል ሕጉ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሺሻ የሚያጨሱ፣ የሚያስጨሱ እና ከድርጅቱ ፍቃድ አግኝተው ወደ አገር አስገብተው የሚያከፋፍሉ ሰዎችም የሕግ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አይኖርባቸውም፡፡

በመሆኑም ሺሻ የሚያጨሱ እና ሺሻውን ከንግድ ዓላማ ውጭ የሚያስጨሱ ግለሰቦች ሺሻውን በማጨሳቸው ወይም በማስጨሳቸው ብቻ የሚተላለፉት የሕግ ድንጋጌ የለም፡፡

በሺሻ ላይ የተጣሩ የምርመራ መዛግብት ከዚህ ቀደም ሲታዩ የቆየበት ሁኔታ

    

ሺሻ በሚስጨሱ ግለሰቦች ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር በሚገኙ የተለያዩ የፖሊስ መምሪያዎችና ጣቢያዎች ተጣርተው የቀረቡ የምርመራ መዛግብትን ሲያዩ የቆዩት  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ጽ/ቤቶች የአቤቱታ ምርመራና የክስ አቀራረብ ንዑስ የሥራ ሂደቶች ሲሆኑ በተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ሲቀርብባቸውም ሆነ ሲቀጡ የነበረው አዋጅ ቁጥር 67/1989 አንቀጽ 21/1/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ያለንግድ ፍቃድ የንግድ ሥራ ሠርታችኋል በሚል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡       

በአዋጅ ቁጥር 67/1989 ከ 3 ዓመት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣ የነበረው ያለንግድ ፍቃድ ንግድ ላይ የመሰማራት ተግባር በአዋጅ ቁጥር 686/2002 ከ 7 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲያስቀጣ ተደርጎ ከተሸሻለ በኋላ ሺሻ ሲያስጨሱ እና ያለንግድ ፍቃድ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ በፖሊስ የተጣሩ የምርመራ መዛግብት ከዚህ ቀደም ሲሰሩበት እንደነበረው በምርመራ መዛግብቱ ላይ እንዲወስኑበት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልደታ ፍትሕ ጽ/ቤት የአቤቱታ ምርመራና የክስ አቀራረብ ንዑስ የሥራ ሂደት የምርመራ መዛግብቱ ሲቀርቡላቸው ቀደም ሲል ተመሳሳይ ጉዳዮችን በአዋጅ ቁጥር 67/1989 ሲሰሩ የነበረ መሆኑን ሆኖም ይሕ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 686/2002 የተሻሻለ መሆኑንና በአዲሱ አዋጅ ስልጣኑ የእነሱ አለመሆኑን ገልፀው ሺሻ ያስጨሳሉ የተባሉ ግለሰቦች ላይ የተጣሩ የምርመራ መዛግብት በፍትሕ ሚኒስቴር የልደታ ፍትሕ ጽ/ቤት በኩል እንዲያስወስን ለአብነት አከባቢ ፖሊስ ጣቢያ በመግለፅ የምርመራ መዛግብቱን መልሰዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች እና የከተማ ነክ ፍትሕ ጽ/ቤቶች የንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸው ገንዘብ እያስከፈሉ ሺሻ ሲያስጨሱ የነበሩ ሠዎችን አስመለክቶ የተጣሩ የምርመራ መዛግብትን በአዋጅ ቁጥር 67/1989 አንቀጽ 21/1/ መሠረት ሲከሱ እና ጉዳዩን ሲመለከቱ የቆዩበት ሥልጣን በራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ ይኸውም በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀጽ 28 (1) ላይ እንደተመለከተው የከተማው የዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት በከተማው ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሥር ማለትም በአዋጁ አንቀጽ 41 (2) ሥር በተመለከቱት የወንጀል ጉዳዮች እነዚህም በቻርተሩ አንቀጽ 52 በተመለከቱ የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ በሚነሱ ወንጀሎች፣ በደንብ መተላለፍ ጉዳዮች (በወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 778 እስከ አንቀጽ 865 የተመለከቱት ላይ)፣ በፌዴራል ወንጀሎች ላይ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ የጊዜ ቀጠሮ እና የዋስትና ጉዳዮች፣ በከተማው አስተዳደር አስፈፃሚ አካላት የሚጣሉ የደንብ መተላለፍ ጉዳዮችን የማስፈፀም ጉዳዮች) ላይ ብቻ ሊሰሩ እንደሚገባ በሕጉ በግልፅ ተመልክቶ ሳለ በእነዚህ ዝርዝር ውስጥ በማይካተቱ በሺሻ ማስጨስ ተግባር ላይ ተጣርተው የቀረቡ፣ በአዋጅ ቁጥር 67/1989 የሚሸፈኑ፣ በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 46 (1) መሠረት ከ 3 ዓመት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚያስቀጡ እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ሊታዩ የሚገባቸውን የምርመራ መዛግብት ሥልጣንና ተግባራቶቻቸውን ለመወሰን በወጣውን ሕግ ከተሰጣቸው ሥልጣን ውጭ በመውጣት ሲሰሩ መቆየታቸውን መመልከት ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልደታ ፍትሕ ጽ/ቤት የአቤቱታ ምርመራና የክስ አቀራረብ ንዑስ የሥራ ሂደት በሺሻ ላይ የተጣሩ የምርመራ መዛግብት ላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን የንግድ ፍቃድ ሳይኖራችሁ በንግድ ላይ ተሰማርታችኋል በሚል ከ 3 ዓመት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት በሚያስቀጣው በአዋጅ ቁጥር 67/1989 አንቀጽ 46 (1) መሠረት ሲከስና ሲያስቀጣ የነበረበት አግባብ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልደታ ምድብ ችሎት እነዚሁኑ ጉዳዮች ተቀብሎ ሲመረምርና ሲወስን የነበረበት አካሄድ ስልጣንና ተግባራቶቻቸውን የሚወስነውን አዋጅ ቁጥር 361/1995፣ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶችና ለፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ሥልጣን የሚሰጡትን አዋጅ ቁጥር 25/1988 እና አዋጅ ቁጥር 471/1998 (በአዋጅ ቁጥር 691/2003 እንደተሻሻለው) ላይ ስለ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወንጀል ዳኝነት ሥልጣን እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴርን ሥልጣን የተመለከቱትን ድንጋጌዎች የጣሰ፣ የትኛውንም ሕግ መሠረት ያላደረገ እና ከሥልጣናቸው በላይ ሲሰሩ የነበረ መሆን መረዳት ይቻላል፡፡  

ሺሻ የሚያጨሱና የሚያስጨሱ ሰዎች እንዲሁም የማስጨሻ ዕቃዎች የሚያዙበት የማስጨሻ ቤቶችም የሚዘጉበት የሕግ አግባብ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑትንና ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ ፖሊስ ሺሻ በማጨስና በማስጨስ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንና የማስጨሻ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ሲያጣራ ቆይቷል፡፡ ሺሻ ማጨስም ሆነ ማስጨስ በየትኛውም ሕግ ያልተከለከሉ ተግባራት እንደመሆናቸው ያጨሱም ሆነ ያስጨሱ ሰዎች እንዲሁም የማስጨሻ ዕቃዎች ግለሰቦቹ በማጨሳቸው ወይም በማስጨሳቸው ብቻ ሊያዙ የሚችሉበት የሕግ አግባብ የለም፡፡ ሆኖም ሺሻ የሚያጨሱ ወይም የሚያስጨሱ ሰዎች ሺሻ ከማጨሳቸው ወይም ከማስጨሳቸው ጐን ለጐን የሚተላለፏቸው ሌሎች ሕጉች እንዲሁም የሚፈጽሟቸው ሌሎች ወንጀሎች ካሉ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ላይ በተቀመጠው ሥነ-ሥርዓት መሰረት ሊያዙ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ቅድመ ሁኔታ ውጭ ግን ፖሊስ ሺሻ አጫሾችንም ሆነ አስጫሾችን እንዲሁም የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎችን መያዝ የሚችልበት የሕግ መሰረት የለውም፡፡ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ አስተዳደር ሠራተኞችም ሺሻ አጫሾችን፣ አስጫሾችና የማስጨሻ ዕቃዎችን ይዘው ለፖሊስ የሚያስረክቡበት እንዲሁም ሺሻ ሲጨስባቸው ነበር የሚባሉ ቤቶችን ሺሻ ስለሚጨስባቸው ብቻ የሚያሽጉበት የሕግ መሠረት የላቸውም፡፡ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 33 መሠረት የፍ/ቤት የብርበራ ማዘዣ በማውጣት ወይም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 32 (2) (ለ) መሠረት ከሺሻ ማጨስ ወይም ማስጨስ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል የተባለው ወንጀል ከ3 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ እንደሚችል በማረጋገጥ ወንጀሉ የተፈጸመበት ነገር ማስጨሻ ቤት ውስጥ ይገኛል የሚል ጥርጣሬ ሲኖርና ፖሊስ የብርበራ ማዘዣ እስኪቀበል ድረስ ወንጀል ተሰራበት የተባለው ነገር ካለበት ቦታ ይወስዳል ተብሎ በበቂ ምክንያት የታመነ ሲሆን ብቻ ፖሊስ የሺሻ ማስጨሻ ቤቶችን ለመበርበርና እንደአግባብነቱ የማስጨሻ ዕቃዎችን ለመያዝ ይችላል፡፡ የሺሻ አጫሾችንም ሆነ አስጫሾችን ሺሻ ከማጨስ ወይም ማስጨስ ጋር በተያያዘ ሌላ ወንጀል ፈጽማችኋል በሚል ለመያዝም ፖሊስ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 53 መሰረት ከፍ/ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣት ወይም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 5ዐ መሰረት ሺሻ ከማጨስ ወይም ማስጨስ ጋር በተያያዘ ከ3 ወራት ቀላል እስራት በማያንስ እስራት የሚያስቀጣ ሌላ ወንጀል እጅ ከፍንጅ ሲፈጽሙ ማግኘት አለበት፡፡

ከእነዚህ በሕጉ ከተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ውጭ ግን ፖሊስ ሺሻ አጫሾችንም ሆነ አስጫሾችን እንዲሁም ማጨሻ ዕቃዎችን መያዝ የሚችልበት የሕግ መሠረት የለውም፡፡ የመያዣ ወይም የመበርበሪያ ትዕዛዝ የሚሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ፍ/ቤቶችም ትዕዛዙን ከመስጠታቸው በፊት ከፍ ብለው የተጠቀሰውትን ነጥቦች ከግምት ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡   

ሺሻ ማስጨስን አስመልክቶ የተጣሩና በፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ የምርመራ መዛግብት ሁኔታ

በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሥር በሚገኙ የአብነት አከባቢ እና የልደታ (ባልቻ) አከባቢ ፖሊስ ጣቢያዎች ብቻ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ሺሻ ያስጨሳሉ የተባሉ ግለሰቦች ላይ የተጣሩ የምርመራ መዛግብት ያሉ ሲሆን ከምርመራ መዛግብቱ መረዳት እንደሚቻለው ሺሻ የሚያስጨሱ ግለሰቦች አጫሾችን አንድ ጊዜ ለማጨስ በአማካይ ከአምስት እስከ ስምንት ብር ያስከፍላሉ፡፡ ይሕ አድራጎትም ሺሻ ማስጨስን አገልግሎት ከሚሰጥባቸው የንግድ ተግባራት ውስጥ ያስመድበዋል፡፡ አንዳንዶቹ ሺሻ አስጫሳችኋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 27 (2) መሠረት ለፖሊስ ቃላቸውን ሲሰጡ ሺሻ እንደማያስጨሱ ገልፀው ጫት የሚያስቅሙ መሆኑን ብቻ ያስረዳሉ፡፡ አያይዘውም ከቀበሌ (ወረዳ) የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት የተሰጣቸውን ጫት በችርቻሮ ለመሸጥ የሚያስችል የንግድ ፍቃድ ከምርመራ መዝገቡ ጋር አያይዘዋል፡፡ ተጠርጥረው የቀረቡት ግለሰቦች ሺሻ እያስከፈሉ አስጭሰዋል ወይስ አላስጨሱም የሚለው የሚወሰነው በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ከቀረቡት ማስረጃዎች አንፃር ሆኖ ጫት የማስቃም አገልግሎት በራሱ በሕግ ዕውቅና የተሰጠውና ማስቃም ለሚፈልጉ ሰዎች በመንግስት በኩል የንግድ ፍቃድ የሚሰጥ ስለመሆኑ ማጣራቱ አስፈላጊ ነው፡፡

በንግድ ሕጉ አንቀጽ 5 ላይ ከተዘረዘሩት ተግባራት መካከል አንዱን በማከናወን  ዕቃ በመሸጥ ወይም አገልግሎት በመስጠት ተግባር ላይ በመሰማራት ተግባሩን ሙያው አድርጎ ተሰማርቶ ጥቅም ወይም ገቢ ለማግኘት በማሰብ የሚሰራ ሰው ነጋዴ ሊባል እንሚችል ተመልክቷል፡፡ በአንቀጽ 5 ሥር ከተዘረዘሩት ተግባራት ውጭ ያሉትን ሌሎች የንግድ ተግባራት በሙያነት ለትርፍ መሥራት በነጋዴነት ያስመድባል ወይስ አያስመድብም የሚለው ጥያቄ ሲነሳ የነበረና የሚነሳ ጥያቄ ቢሆንም በአሰራር ደረጃ በአንቀጽ 5 ከተዘረዘሩት ተግባራት ውጭ ላሉ ሌሎች የንግድ ተግባራት በመንግስት በኩል ፍቃድ እየተሰጠ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም በአንቀጽ 5 ሥር ከተመለከቱት ተግባራት ውጭ ያሉ ሌሎች የንግድ ተግባራትን በሙያነት ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ፍቃድ ወስዶ በተግባራቱ ላይ መሰማራት ይቻላል፡፡ ሆኖም እንደ ሺሻ ማስጨስ፣ ጫት ማስቃም፣ ቁማር ማጫወት ላሉ የንግድ ተግባራት ተግባራቱ በአንቀጽ 5 ሥር ከተዘረዘሩት ውጭ ቢሆኑም በመንግስት በኩል በእነዚህ የንግድ ተግባራት ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ሠዎች የንግድ ፍቃድ አሰጥም፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልደታ ክፍለ ከተማ ሥር ከሚገኙት የወረዳ 1 እና የወረዳ 4 የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤቶች ለመረዳት እንደተቻለው ሺሻ ለሚያስጨሱ እና ጫት ለማስቃም ለሚፈልጉ ግለሰቦች በመንግስት ደረጃ የንግድ ፍቃድ አይሰጥም፡፡ ሺሻ የማስጨስ እና ጫት የማስቃም ተግባራት ሕብረተሰቡን በተለይም ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል ለሱስ ተገዥ በመሆን አምራች እንዳይሆን እና ምግባረ ብልሹነት እንዲስፋፋ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ በመሆኑ በመንግስት ዕውቅና ያልተሰጣቸው እና የንግድ ፍቃድ የማይሰጥባቸው የንግድ ተግባራት ናቸው፡፡ በመሆኑም ሺሻ የማስጨስና ጫት የማስቃም ተግባራት በመንግስትና በሕግ ዕውቅና ያልተሰጣቸው ተግባራት ናቸው፡፡

በንግድ ሕጉ አንቀጽ 24 (1) ላይ በሕግ የተከለከሉ የንግድ ተግባራት ላይ መሰማራት በወንጀል ሊያስጠይቅ እንደሚችል በግልፅ የተመለከተ ቢሆንም ሺሻ የማስጨስና ጫት የማስቃም ተግባራት ላይ መሰማራት እንደማይቻል ወይም ስለመከልከሉ የሚደነግግ ሕግ የለም፡፡ ሆኖም አንድ የንግድ ተግባር ላይ መሰማራት እንደማይቻል ወይም የተከለከለ ስለመሆኑ የሚደነግግ ሕግ ስለሌለ እንደተፈቀደ ተቆጥሮ መሰማራት ይቻላል ሊባል ቢችልም የወረዳ (የቀበሌ) የንግድና ኢንዱስትሪ ጽ/ቤቶች ፍቃድ ለሚፈልጉ ሠዎች የንግድ ፍቃድ የሚሰጡት በየትኛዎች የንግድ ተግባራት ላይ እንደሆነ የሚያመላክት ዝርዝር የንግድ ተግባራቶችን የያዘ ሠነድ ያለ ሲሆን አመልካች ልሰማራበት ብሎ የጠየቀው የንግድ ተግባር በዚህ ሰነድ ውስጥ ከተመለከቱት ውስጥ ካለ ብቻ ፍቃድ ይሰጠዋል ተግባሩ ከዝርዝሩ ውስጥ ከሌለ ግን የንግድ ፍቃድ አይሰጠውም በንግድ ሥራ ላይም መሰማራት አይችልም ማለት ነው፡፡

ከዚህ የአሰራር ሁኔታ አንፃር ሺሻ የማስጨስና ጫት የማስቃም ተግባራትን ለመመለከት ያህል ሁለቱ ተግባራት ላይ መሰማራት እንደማይቻል የሚገልፅ ሕግ የሌለ ቢሆንም በመንግስት የንግድ ፍቃድ ሰጭ አካላት አሰራር መሠረት ፍቃድ የማይሰጥባቸው የንግድ ተግባራት ሲሆኑ በእነዚህ ተግባራት ላይ መሰማራት እፈልጋለሁ የሚል ግለሰብ ካለ ለንግድ ፍቃድ ሰጭ አካላት በሕጉ መሠረት የንግድ ፍቃድ እዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ፍቃድ ሊሰጥበት የማይችል የንግድ ተግባር መሆኑ ሲገለፅለት መሰማራት አይኖርበትም፡፡ ሆኖም ከፍቃድ ሰጭ አካል በሺሻ ማስጨስ ወይም በጫት ማስቃም የንግድ ተግባራት ላይ መሰማራት እንደማይቻል ተገልፆለት ወይም ከመጀመሪያው ፍቃድ ለማውጣት ጥያቄ ሳያቀርብ በእነዚህ ተግባራት ላይ የተሰማራ ነጋዴ የፀና የንግድ ፍቃድ ሳይኖረው በሕገ ወጥ መንገድ በንግድ ላይ እንደተሰማራ ይቆጠራል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ሺሻ በሚያጨሱ እና በሚያስጨሱ ግለሰቦች ላይ የተጣሩ የምርመራ መዛግብት ላይ የሕግ አስተያየት እና ውሳኔ የሚሰጥበት እንዲሁም ምርመራ እንዲጣራ የሚያዝበት አግባብ

ሺሻ ማጨስም ሆነ ማስጨስ በሕግ ያልተከለከሉ ይልቁንም በሕግ ድጋፍ ያላቸው ተግባራት በመሆናቸው ሺሻ አስጭሳችኋል ወይም አጭሳችኋል በሚል የተከሰሱና ምርመራ የተጣራባቸው ግለሰቦች ካሉ በማጨሳቸው ወይም በማስጨሳቸው ብቻ የፈጸሙት ወንጀልና የተላለፉት ሕግ ባለመኖሩ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23 /1/ እና /2/ መሠረት ሕገ ወጥነቱና አስቀጪነቱ በሕግ ያልተደነገገ እንዲሁም ወንጀልን ከሚያቋቁሙ ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ሕጋዊ ፍሬ ነገር ያልተሟላ በመሆኑ በዐቃቤ ሕግ በኩል የክስ አያስቀርብም ውሳኔ ተሰጥቶ የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች ተይዘው ከሆነ ለባለንብረቱ እንዲመለሱ መደረግ ይኖርበታል፡፡

ሆኖም ሺሻ ከማጨስ ወይም ከማስጨስ ተግባራት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የተለያዩ ወንጀሎች ያሉ በመሆኑ በፖሊስ በኩል ምርመራ ከመጣራቱ በፊት እንዲሁም በዐቃቤ ሕግ በኩል በምርመራና በሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ በሚሰጥበት ወቅት ተያያዥ ወንጀሎች የተፈፀሙ ስለመሆናቸው በጥንቃቄ ሊፈተሹ ይገባል፡፡ ሺሻ ከማጨስ ወይም ማስጨስ ተግባራት ጋር በተያያዘ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከልም አደንዛዥ ዕጾችን ማዘዋወር ወይም መጠቀም፣ የንግድ ፍቃድ ሳያወጡ ሺሻ እያስጨሱ ገቢ በማግኘት በንግድ ስራ ላይ መሰማራት፣ ሺሻንና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን ያለፍቃድ ከውጭ ማስመጣት ወይም ለሽያጭ ማቅረብ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ከሺሻ ማጨስና ማስጨስ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እንዴት እንደሚፈፀሙ፣ ወንጀሎቹ ከተፈፀሙ እና ምርመራ ከተጣራ በኃላ በየትኞቹ ሕጎች ጉዳዮቹ እንደሚሸፈኑ ማየቱ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሚከተለው ተብራርተዋል፡፡

ሀ.አደንዛዥ ዕጾችን ማዘዋወር ወይም መጠቀም

ከፌዴራል ፖሊስ እና ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የተገኙት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የሺሻ ማስጨሻ ቤቶች ውስጥ ሺሻ ከተለያዩ አደንዛዥ ዕጾች በተለይም እንደ ካናቢስ ካሉ አደንዛዥ ዕጾች ጋር ተቀላቅሎ አገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን አደንዛዥ ዕጾችን ልዩ ፍቃድ ሳይኖር መግዛት፣ በሽያጭ ማቅረብ፣ ማሰራጨት፣ ማዘዋወር፣ ይዞ መገኘት፣ መጠቀም፣ መኖሪያ ቤትን ወይም ይዞታን ለአደንዛዥ ዕፆች መሸጫነት መስጠት፣ ማከራየት ወይም መፍቀድ በራሱ አደንዛዥ ዕፁን ለተጠቃሚዎች ባቀረቡት፣ በተጠቃሚዎች፣ ይዘው በተገኙና ቤታቸውን ወይም ይዞታቸውን አደንዛዥ ዕፁን ለሚሸጡ ሰዎች በፈቀዱ፣ ባከራዩና በሰጡ ሰዎች ላይ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 525 የተለያዩ ንዑስ ቁጥሮች ላይ በተመለተው መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡

በማስረጃ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይም ከሺሻ ማስጨሻ ዕቃው አናት ላይ ከሚገኘው ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ ከሚገኘው የሺሻ ትምባሆ ላይ አደንዛዥ ዕፅ ስለመኖሩ ወይም ከሺሻ ስለመቀላቀሉ ከኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስመርምሮ በሰነድ ማስረጃ ማረጋገጡ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ የተቀረው በበቂ ሁኔታ በሚያስረዱ የሰው ማስረጃዎች ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ 

ለ. የንግድ ፍቃድ ሳያወጡ ሺሻን በማስጨስ ገቢ እያገኙ በንግድ ስራ ላይ መሰማራት 

ሺሻን ከማስጨሻው ዕቃው ጋር ለአጫሾች አቅርቦ ላጨሱበት ክፍያ እንዲከፍሉ ማድረግ ሺሻ ማስጨስን አገልግሎት ከሚሰጥባቸው የንግድ ዘርፎች ውስጥ ያስመድበዋል፡፡ አንድ ሰውም ከአጫሾች /ከተጠቃሚዎች/ በተጠቀሙት የሺሻ ማጨስ መጠን ልክ ገንዘብ እየተቀበለ ለማስጨስ ከፈለገ ስልጣን ካለውና ከሚመለከተው አካል የፀና የንግድ ፍቃድ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ ቀደም ሲል በአዋጅ ቁጥር 67/1989 አንቀጽ 21/1/ ላይ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 686/2ዐዐ2 አንቀጽ 31/1/ ላይ እንደተመለከተው ማንኛውም ሰው የፀና የንግድ ፍቃድ ሳይኖረው የንግድ ስራ መስራት አይችልም፡፡ በመሆኑም ሺሻ የማስጨስ የንግድ ስራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል የፀና የንግድ ፍቃድ ያላቸው ስለመሆኑ ከአስጫሾች እና ስልጣን ካለው ከሚመለከተው አካል ማጣራቱ አስፈላጊ ነው፡፡ ሺሻ አስጫሽ ግለሰቦችም እያስጨሱ ገንዘብ የሚቀበሉ ስለመሆኑ ለማስረዳት አጫሾችን በማስረጃነት መጠቀሙ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

በመሆኑም ሺሻ አስጫሽ ግለቦች ሺሻ እያስጨሱ ገንዘብ ስለመቀበላቸው እንዲሁም ይህንን ለማከናወን የሚያስችል የፀና የንግድ ፍቃድ የሌላቸው ስለመሆኑ ማስረዳት ከተቻለ አስጫሾች በአዋጅ ቁጥር 686/2ዐዐ2 አንቀጽ 6ዐ/1/ መሰረት የወንጀል ክስ ሊቀርብባቸውና ፍ/ቤት ሲወስንም የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች ሊወረሱ፤ በአንቀጽ 31/2/ መሰረት አግባብ ባለው ባለስልጣን የንግድ ድርጅቱ ሊዘጋባቸው እንዲሁም በሌላ የንግድ ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል የንግድ ፍቃድ ኖሯቸው ሺሻ በማስጨስ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ በአንቀጽ 39/1/ለ መሰረት የንግድ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ ማድረግ ይገባል፡፡ 

ሐ. ከፍቃድ ውጭ መሥራት

አንድን የንግድ ሥራ ለመስራት የሚያስችል የንግድ ፍቃድ የተሰጠው ሠው ለመሰማራትና ለመስራት የሚችለው የተፈቀደለትን የንግድ ሥራ ብቻ ሲሆን ከዚህ ከተፈቀደለት የንግድ ሥራ ውጭ በሌሎች ተያያዥ በሆኑና ባልተፈቀዱለት የንግድ ተግባራት ላይ መሰማራት የለበትም፡፡ ጫት በችርቻሮ ለመሸጥ ብቻ የሚያስችል የንግድ ፍቃድ የተሰጠው ሠው ከዚህ ፍቃዱ በመውጣት በችርቻሮ በሚሸጥበት የንግድ ቤት ውስጥ ጫት ሲያስቅም ወይም ሺሻ ሲያስጨስ ቢገኝ ፈቃዱን ከተሰጠበት ዓላማ ውጭ ሲገለገልበት ወይም ተገቢ ያልሆነ የንግድ ሥራ ሲሠራበት የተገኘ በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 39 (1) (ለ) መሠረት ፍቃዱ በሚመለከተው አካል በኩል እንዲሰረዝበት ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 433 መሠረት ተጠያቂ እንዲሆነ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡

መ. ሺሻንና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን ያለ ፍቃድ ከውጭ ማስመጣት ወይም ለሽያጭ ማቅረብ 

ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት /ኢትዮጵያ/ አክሲዮን ማህበር ትምባሆና የትምባሆ ውጤቶችን ለመግዛት፣ ለመቀመም በፋብሪካ ሰርቶ ለማውጣት፣ ለመሸጥ ወደ አገር ለማስገባትም ሆነ ወደ ውጭ ለመላክ ብቸኛ ልዩ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 37/1985 አንቀጽ 9 ላይ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም ይህ የአክሲዮን ማሕበሩ ብቸኛ ሥልጣን (exclusive power) በአንቀጽ 1ዐ ላይ እንደተመለከተው ድርጅቱ ትምባሆና የትምባሆ ምርቶችን ከውጭ ማስመጣት እና ለሽያጭ ማቅረብን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን ለሚያከናውኑ አካላት ፍቃድ ሊሰጥ እንደሚችልም ተመልክቷል፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 11 ላይም እነዚህን ተግባራት ያለ ፍቃድ ማከናወን እንደማይቻል ያስረዳል፡፡ ሺሻም የትምባሆ ምርት /ውጤት/ እንደመሆኑ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ሺሻን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እና ለሽያጭ ማቅረብ ከፈለጉ ከብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት አክሲዮን ማህበር በአዋጅ ቁጥር 37/1985 አንቀጽ 1ዐ እና ድርጅቱ ሺሻ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚፈልጉ ድርጅቶችና ግለቦች የሚስተናገዱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ባወጣው መመሪያ አንቀጽ 2 መሰረት ፍቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም የሺሻ ምርት ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት /ኢትዮጵያ/ አክሲዮን ማህበር ፍቃድ ካልሰጠ በስተቀር ወደ አገር እንዳይገባ ወይም ከአገር እነዳይወጣ ወይም እንዳይተላለፍ ገደብ የተደረገበት ዕቃ ነው፡፡

በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91 (1) (2) እና (3) መሠረትም በሕግ መሠረት ሥልጣን ከተሰጠው አካል ፍቃድ ካልሰጠ በስተቀር ወደ አገር እንዳይገባ ወይም ከአገር እንዳይወጣ ወይም እንዳይተላለፍ ገደብ የተደረገበት ዕቃ ወደ ጉምሩክ ክልል ማስገባት ወይም ከጉምሩክ ክልል ማስወጣት እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ የተገኙ ዕቃዎች መሆናቸውን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባ ይህንኑ ዕቃ ወደ አገር ማስገባት፣ ማስወጣት፣ ማጓጓዝ፣ ማከማቸት፣ ለሽያጭ ማቅረብ እና መግዛት ወንጀል መሆኑ ተደንግጎ ከባድ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ ሺሻም ያለ ብሔራዊ የትምባሆ ድርጅት /ኢትዮጵያ/ አክሲዮን ማህበር ፍቃድ ወደ አገር እንዳይገባና አገልግሎት ላይ እንዳይውል እንዲሁም እንዳይዘዋወር ገደብ የተጣለበት ዕቃ ነው፡፡ በመሆኑም ያለ ትምባሆ ድርጅት ፍቃድ የሺሻ ምርት ወደ አገር ማስገባት፣ ማስወጣት፣ ማጓጓዝ፣ ማከማቸት፣ ለሽያጭ ማቅረብ እና መግዛት የሚያስጠይቅ በመሆኑ በብርበራ ወቅት የሺሻ ምርት የተገኘባቸው ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ካሉ የሺሻ ምርቱን ወደ አገር ለማስገባት ወይም ለማዘዋወር የሚያስችል ፍቃድ እንዳላቸው ለማስረዳት ወይም ፍቃዳቸውን ለማሳየት ካልቻሉ በጉምሩክ አዋጁ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡

 

የሺሻ ምርቶችን ጨምሮ ሌሎች ገደብ የተደረገባቸውን ዕቃዎች ያለፍቃድ ወደ አገር አስገብተው የሚያከማቹ፣ የሚያዘዋውሩ እንዲሁም ሌሎች በአዋጅ ቁጥር 622/2001 ላይ የተመለከቱን ድንጋጌዎች የሚተላለፉ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ ምርመራ የማጣራት እና ለሕግ አቅርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የጉምሩክ ሹም እና ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡ በመሆኑም ሺሻን አስመልክቶ ከጉምሩክ ጋር ተያይዘው የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በመመርመርና ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ አቅርቦ ከማስቀጣት አኳያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሺንም ሆነ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣን አይደለም፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽ ፖሊስ እና የፍትህ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ ከሺሻ ጋር በተያያዘ በሥልጣናቸው ሥር የሚወድቁ ጉዳዮችን በሚመረምሩበት ወይም በሚመለከቱበት ወቅት ከጉምሩክ ጋር የተያያዘ ወንጀል መፈፀሙን ከተረዱ መረጃ ሳይባክን ይህንኑ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የጉምሩክ ሹምና ዐቃቤ ሕግ በማሳወቅ እንዲከታተሉት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል፡፡          

ከአዋጅ ቁጥር 622/2001 በስተቀር የተቀሩት ሕጎች ማለትም የአዋጅ ቁጥር 37/1985 አንቀጽ 11 እና 13 እና በብሐየራዊ ትምባሆ ድርጅት የወጣው መመሪያ ሲጣሱ ምርመራ የማካሄድና ወንጀል ፈፃሚዎችን ተጠያቂ የማድረግ ኃላፊነት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽ ፖሊስ እና የፍትህ ሚኒስቴር በመሆኑ ሺሻን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባትን በተመለከተ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልን የጉምሩክ ሹምና ዐቃቤ ሕግ ጋር የሥልጣን መደራረብ ይኖራል፡፡ ሆኖም የሺሻ ምርትን ያለፍቃድ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት፣ የማከማቸት፣ የማጓጓዝ፣ ለሽያጭ የማቅረብና የመግዛት ወንጀሎች አፈፃፀም ባህሪ በዋናነት ከጉምሩክ አሠራር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህንኑ በማረጋገጥ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲታይ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡  

በአጠቃላይ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች በመመሪያው መሰረት ከትምባሆ ድርጅት ፍቃድ ሳይኖራቸው የሺሻ ምርት ከውጭ አስመጥተው ለሽያጭ ያቀረቡት፣ ያከማቹት ወይም ያዘዋወሩት መሆኑን ማስረዳት ከተቻለ የመመሪያውን አንቀጽ 2፣ የአዋጅ ቁጥር 37/1985 አንቀጽ 11 እና 13 እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 622/2001 አንቀጽ 91 (1) (2) ወይም (3) መሠረት በማድረግ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ክስ ሊቀርብባቸው ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

 

ሺሻ መጠቀም በጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር ለተለያዩ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መንስኤ መሆኑ በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ ሺሻ ማጨስንም ሆነ ማስጨስን የሚከለክል ሕግ የሌለ ይልቁንም ሺሻ አገልግሎት ላይ የሚውልበት ሁኔታ ላይ ዝርዝር ሕግ ያለ በመሆኑ ሺሻ ማጨስም ሆነ ማስጨስ የተፈቀደ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም ሺሻ ሲያጨሱም ሆነ ሲያስጨሱ የሚገኙ ሠዎችን እንዲሁም የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎችን ሺሻ በማጨሳቸው ወይም ማስጨሳቸው ብቻ የሚያዙበት የሕግ መሠረት የለም፡፡

ሆኖም አደንዛዥ ዕፅ ይዞ መገኘት እና መጠቀም፣ ያለ ፍቃድ ንግድ መነገድ እና ገደብ የተጣለበትን ዕቃ (ሺሻ) ያለፍቃድ ወደ አገር ማስገባት ከሺሻ ማጨስ እና ማስጨስ ተግባራት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በመሆናቸው ወንጀሎቹ መፈፀማቸውን በመለየት ፈፃሚዎችን ለሕግ ማቅረቡ አስፈላጊ ነው፡፡

የመፍትሔ ሃሳቦች

ሺሻ ከማጨስና ማስጨስ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙትን ወንጀሎች ከመለየትና ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ አቅርቦ ተጠያቂ ከማድረግ ባሻገር ሺሻ በማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መንስኤ እንዳይሆን በመንግስት በኩል የተለያዩ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል፡፡ በመንግስት ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች መካከል የሺሻን አሻሻጥ እና አጠቃቀም አስመልክቶ በቂ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ ማዋል ዋነኛው ነው፡፡ የሺሻ አሻሻጥ እና አጠቃቀምን አስመልክቶ ሕግ ማውጣትን በተመለከተም ካደጉት አገራት ከእነ እንግሊዝ እና አሜሪካ እንዲሁም በማደግ ላይ ካሉት ከእነ ሱዳን ልምድ መቅሰም ይቻላል፡፡

በእንግሊዝ የሺሻ አመራረትን እና አሻሻጥን በተመለከተ የሺሻ አምራቾችና አስመጪዎች የሚያመርቱትና የሚያስመጡት የሺሻ ምርት በትክክል ኮድ የተሰጠው፣ በውስጡ የያዛቸውን ንጥረ ነገሮች የሚዘረዝር፣ ጤንነትን በተመለከተ ሺሻ ማጨስ ጉዳት እንደሚያደርስ የሚገልፁ ማስታወቂያዎች የተለጠፈበት፣ የተመረተበት እና አገልግሎት ላይ የሚውልበት ጊዜ የተጠቀሰበት እና ተገቢው ቀረጥና ግብር የተከፈለበት እንዲሆን የሺሻ አጠቃቀምን አስመልክቶም ሺሻና ሌሎች የትምባሆ ምርቶች ለህዝብ ግልፅ በሆኑ ስፍራዎች በተለይም በሲኒማ ቤቶች፣ በሕዝብ የትራንሰፖርት መጓጓዣ ስፍራዎች፣ በካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የሥራ ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ለሕዝብ ክፍት በሆኑ ቦታዎች ወይም ከእነዚህ ስፍራዎች በቅርብ ርቀት ላይ ማጨስ፣ ሺሻን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሠዎች ለሽያጭ ማቅረብ በሕጉ መከልከሉ እንዲሁም እነዚህን የተከለከሉ ተግባራትን መፈፀም በተለይም በተከለከሉ ቦታዎች ማጨስ፣ ማጨስ እንደማይቻል የሚገልፁ ማስታወቂዎችን እንዲለጠፉ በታዘዘበት ቦታዎች አለመለጠፍ እና ለባለንብረቶች በተከለከሉ ቦታዎች ሲያጨሱ የተገኙ ሠዎችን አለመከልከል ከ30 ፓውንድ እስከ 2500 ፓውንድ ቅጣት ሊቀጡ እንደሚችሉ በሕጉ መደንገጉ እንደ ጥሩ ልምድ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በተለይም በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሺሻ በብዛት የሚጨሰው ትምህርት ቤቶች አከባቢ በሚገኙ የጫት ማስቃሚያ ቤቶች ውስጥ በመሆኑና በርካታ ወጣት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው ላይ የሚያሰናክልና ለአላስፈላጊ ሱስ የሚጋብዝ በመሆኑ በትምህርት ቤቶች ዙሪያና አከባቢ ሺሻ ማስጨስም ሆነ የጫት ማስቃሚያም ሆነ መሸጫ ቤቶች መክፈት ክልክል መሆኑን የሚደነግግ ሕግ ማውጣቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ሺሻንም ሆነ ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት እንዲያጨሱ ወይም እንዲጠቀሙ በሽያጭም ሆነ በሌላ መልክ የሚያቀርቡ ሠዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ እንዲሁም ሺሻ እንዲያስጨሱ ፍቃድ የሚሠጣቸው ሠዎች (ቤቶች) ቢኖሩ እንኳን በማስጨሻ ቤቶች ውስጥ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ሠዎች ሺሻ ለሽያጭ እንደማይቀርብ የሚገልፅ ማስታወቂያ እንዲለጥፉ የሚስገድድ ሕግ ማውጣቱም ሕፃናት በሱሱ ተጠቂ እንዳይሆኑ በመከላከሉ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

The Police and Human Rights in Ethiopia
Qualities of Effective Leadership and Its impact o...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 24 November 2024