ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት (የግዴታ ሥራ) እንደ ወንጀል ቅጣት
ጣልያንን ለዘጠኝ ዓመታት የመሩት የቀድሞው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የኤሲ ሚላን እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንትና ባለቤት እንዲሁም ቢሊየነሩ ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ በተከሰሱበት የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በሚላን ከተማ የሚገኘው ፍርድ ቤት ቤርሎስኮኒ የአራት ዓመታት እስራት ቢፈረድባቸውም የእስራት ቅጣቱ በተለያዩ ምክንያቶች ቀርቶ በተቃራኒው ቤርሎስኮኒ በአረጋውያን ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት እንዲሰጡ እ.ኤ.አ. በ2013 መወሰኑ ይታወቃል፡፡ በውሳኔው መሠረትም ቤርሎስኮኒ ሴሴኖ ከተማ ውስጥ በሚገኘውና ከ2000 በላይ በእድሜያቸው የገፉ፣ የአእምሮና የአካል ጉዳተኛ የሆኑ አረጋውያን በሚገኙበት ማዕከል ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል በሳምንት ለአራት ሠዓታት በማዕከሉ እየተገኙ አረጋውያኑን እንዲመግቡ፣ እንዲንከባከቡ፣ እንዲያንሸራሽሩ እንደ አጠቃላይም በማንኛውም መልኩ ከአረጋውያኑ ጎን እንዲሆኑ ተወስኖባቸው ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎቱን ፈፅመው አጠናቀዋል፡፡
ታዋቂው አሜሪካዊ የሙዚቃ አቀንቃኝ ቦይ ጆርጅም በመኖሪያ ቤቱ የኮኬይን ዕፅ ይዞ መገኘትና በሀሰት የመኖሪያ ቤቴ ተዘርፏል በሚል ካቀረበው የሀሰት ጥቆማና ሪፖርት ጋር በተያያዘ እ.ኤ.አ. በ2006 በማንሀተን የወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ የተወሰነበት ቅጣት ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት እንዲሰጥ ይኸውም በኒውዮርክ ከተማ ለአምስት ቀናት ያህል የከተማዋን መንገዶች እንዲያፀዳ ሲሆን ከኒውዮርክ ከተማ የፅዳት አገልግሎት ክፍል ጋር በመሆን የከተማዋን አውራ ጎዳናዎች ለአምስት ቀናት ያህል በማፅዳት ቅጣቱን ፈፅሟል፡፡
ሆላንዳዊው የእግር ኳስ ተጫዋች የነበረውና ለአያክስ አምስተርዳም፣ ኤሲ ሚላንና ባርሴሎና እግር ኳስ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ፓትሪክ ክላይቨርትም የ19 ዓመት ወጣት በነበረበትና ለአያክስ አምስተርዳም እግር ኳስ ክለብ በሚጫወትበት ወቅት በአምስተርዳም ከተማ ከፍጥነት ወሰን በላይ መኪና ሲያሽረክር ባደረሰው የመኪና አደጋ የቲያትር ዳይሬክተር የነበሩ የ56 ዓመት ጎልማሳ ሕይወታቸው እንዲያልፍ በማድረጉ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ ዕድሜው ገና 19 ዓመት የነበረና ተስፈኛ ስፖርተኛ መሆኑ ከግምት ገብቶ የተጣለበት የሶስት ወራት የእስራት ቅጣት በሁለት ዓመት የፈተና ጊዜ እንዲገደብ፣ ለ18 ወራት መኪና ከማሽከርከር እንዲታቀብ እና ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት እንዲሰጥ ተወስኖበታል፡፡ በሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎቱም ፓትሪክ ክላይቨርት ለ240 ሰዓታት ታዳጊ ሕፃናትን በእግር ኳስ ስፖርት እንዲያሰለጥንና ለሕፃናቱ መልካም አስተዳደግ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ተወስኖበት ቅጣቱን መፈፀሙም ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ሠዎች በተጨማሪ ሌሎች ሠዎችም ለፈፀሙት የወንጀል ድርጊት ቅጣት እንሆን ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት እንዲሰጡ ሲወሰንባቸው ይታያል፡፡
ለመሆኑ የወንጀል አጥፊዎች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ምን ዓይነት ናቸው? ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ ምን ዓይነት ቅጣት ነው? ዓላማውስ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግስ ሽፋን ተስጥቶታል ወይ? ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ የሚወሰነው ምን ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው? ስንት ዓይነት የግዴታ ስራዎች አሉ? ፍርድ ቤቶችስ የግዴታ ስራን አስመልክቶ በሕግ ተለይቶ የተሰጣቸው ሥልጣን ምንድን ነው? ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራን አስመልክቶ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ምንድን ናቸው? የሚሉና ተያያዥ ነጥቦችን በዚህ ፅሁፍ በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡
በወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ሠዎች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ምን ዓይነት ናቸው?
በወንጀል ጉዳይ ተከሰው በእምነት ቃላቸው ወይም በቀረበባቸው ማስረጃ መሠረት በፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉ ሠዎች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች ዓይነታቸው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ እነዚህም አጥፊውን በሞት ቅጣት እንዲቀጣ የሚወሰንበት፣ ነፃነትን በሚያሳጣ የቀላል ወይም ፅኑ እስራት ቅጣት የሚቀጣበት ወይም በገንዘብ መቀጮ የሚቀጡበት እንዲሁም የግዴታ ሥራ እንዲቀጣ የሚደረግባቸው የቅጣት ዓይነቶች ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተጨማሪም እደ ተግሳፅና ወቀሳ፣ ከመብት መሻር እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ ምን ዓይነት ቅጣት ነው?
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ በፍርድ ቤት ውሳኔ ጥፋተኛ የተባለ ወንጀል ፈፃሚ ሕብረተሰቡ ላይ ላደረሰው በደልና ጥፋት መካሻ እንዲሆን ያለክፍያ ለሕብረተሰቡ ጠቀሜታ ያለው ሕዝባዊ አገልገሎት እንዲሰጥ የሚደረግበት አጥፊው በእስራት ከሚቀጣ ይልቅ በአማራጭነት የግዴታ አገልግሎት እየሰጠ እንዲቀጣ ለማድረግ የተቀመጠ የወንጀል ቅጣት ዓይነት ነው፡፡
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ ቅጣት ዓላማው ምንድን ነው?
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ እንደ ወንጀል ቅጣት የተጠቀመበት ዓላማ በአደገኝነት ዝቅተኛና መካከለኛ የሆኑ ወንጀል ፈፃሚዎች የሚጣልባቸው ቅጣት ነፃነታቸውን የሚያሳጣ እስር ከሚሆን ይልቅ የተበደለው ማሕበረሰብ ወንጀል ፈፃሚው ያለክፍያ በሚሰጠው ሕዝባዊ አገልግሎት ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል፣ ወንጀል ፈፃሚውን በማሰር የሚወጡ ወጪዎችን መቀነስ፣ ተቀጪውን ፍሬያማና አስተማሪ በሆነ መልኩ እንዲቀጣ ማስቻል መሆኑን በዘርፉ የተፃፉ ፅሁፎች ያስረዳሉ፡፡
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ እንደወንጀል ቅጣት የሚወሰነው ምን ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው?
በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 103 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ላይ እንደተመለከተው ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጥፋተኞች ላይ ሕዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድድ ውሳኔ ሊወስኑ የሚችሉት የሚከተሉት ሁኔታዎች በአስገዳጅነት ተሟልተው ሲገኙ ነው፡፡ እነዚህም፡ -
· ወንጀል ፈፃሚው ጥፋተኛ የተባለበት ወንጀል ከባድነት የሌለው ሲሆን፤
· ወንጀሉ የሚያስከትለው ቅጣት ከ6 ወራት የማይበልጥ ቀላል እስራት ከሆነ፤
· ጥፋተኛው የሚጣልበትን ሕዝባዊ የግዴታ ሥራ ለመስራት ከእውቀት፣ ጉልበትና ሌሎች መመዘኛዎች አንፃር የሚችል ከሆነ፤ እና
· ጥፋተኛው ለሕብረተሰቡ አደገኛ የማይመስል ከሆነ እንደሆነ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ መመዘኛዎች ባተሟሉበትም ሁኔታ ቢሆን ፍርድ ቤቶች ተቀጪው ላይ ነፃነትን በሚገድብ ሁኔታ የግዴታ ሥራ ቅጣትን መወሰን እንደሚችሉ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 104 ላይ ተመክልቶ ይገኛል፡፡
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ እንደ ወንጀል ቅጣት ሲወሰን ሊያካትት የሚገባቸው መሠረታዊ ነጥቦች ምንድን ናቸው?
ፍርድ ቤቶች በአንድ የወንጀል ጉዳይ ጥፋተኛ የተባለው ሠው ላይ ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠትን በቅጣት መልክ ከወሰኑ ውሳኔው በዋናነት የሚከተሉትን ነጥቦች ማከተት ይኖርበታል፡፡ እነዚህም፡ -
· ሕዝባዊ የግዴታ ሥራው የሚፈፀምበት ጊዜ ከአንድ ቀን እስከ 6 ወራት በሚደርስ ጊዜ ተለይቶ መጠቀስ አለበት፤
· የግዴታ ሥራው የሚፈፀምበት ስፍራ እና የሕዝባዊ አገልግሎቱ ዓይነት ተለይቶ መጠቀስ አለበት፤
· የግዴታ ሥራውን ተከታትሎ የሚያስፈፅመው አካልና የቁጥጥሩ ዓይነት መጠቀስ ይኖርበታል፡፡
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ እንደ ወንጀል ቅጣት ሲወሰን ተቀጪዎች የሚሰሯቸው ሥራዎች ምንድን ናቸው?
በወንጀል ሕጉ ላይ ተቀጪዎች በፍርድ ቤት ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ እንዲሰሩ ሲወሰንባቸው የሚሰሯቸው ሥራዎች ዓይነት ሕዝባዊ ጠቀሜታ ሊኖረው የሚገባ መሆኑ ከመመልከቱ ውጪ የሕዝባዊ አገልግሎቱ ወይም ስራው ዓይነት ተለይቶ አልተጠቀሰም፡፡ ሆኖም በሀገራችን እና በሌሎች ሀገራትም የተለመዱና ተቀጪዎች የሚሰሯቸው የግዴታ ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነዚህም፡ -
· የመንገድ ላይ ፅዳት፣
· የአትክልት ሥራዎች፣
· በየመንገዱ ያለአግባብ የተለጠፉ ማስታወቂያዎችና ሥዕሎችን ማንሳት፣
· የአከባቢ ጥበቃ ሥራ መስራት፣
· የቆሻሻ አወጋገድ ሥራ መስራት፣
· የሕዝብ ፓርኮችን አያያዝ ማሻሻል፣
· የበጎ አድራጎት ተቋማትና አካላትን የተለያዩ ሥራዎች ማገዝ፣
· የተለየ ድጋፍና እንክብካቤ በሚያሻቸው የሕፃናት፣ አረጋውያንና አእምሮ ሕሙማን መንከባከቢያ ተቋማት ውስጥ የተለያዩ የግዴታ ሥራዎች እንዲሰሩ ማድረግ፣
· እንደ ተቀጪው ልዩ ክሕሎት፣ ዕውቀትና ሙያ ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎችን ማሠራት የሚሉት ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ተቀጪዎች ላይ የሚወሰነውን ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ ተከታትሎ የሚያስፈፅው ማን ነው?
በወንጀል ሕጉ ወይም ሌላ ሕግ ላይ ፍርድ ቤቶች በአጥፊዎች ላይ የሚወስኑትን ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት ወይም የግዴታ ሥራ እንዲያስፈፅም በግልፅ ተለይቶ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም የለም፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ አየርላንድ እና የመሳሰሉ ሀገራት ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ በማሕበራዊ ሥራዎች በሰለጠኑ ባለሙያዎች የተደራጁ ወንጀልን በመከላከል፣ አጥፊዎችን በመከታተል፣ የወንጀል ተጎጂዎችን በመንከባከብ፣ በተፈፀሙ ወንጀሎች ዙሪያ አስፈላጊ ተግባራትን የሚፈፅሙ፣ እንደ ግዴታ ሥራ የመሳሰሉ ቅጣቶችን ከፖሊስና ሌሎች አካላት ጋር ሆነው በዋናነት የሚያስፈፅሙ ከፍርድ ቤቶች ጋር ቀጥተኛ የሥራ ግንኙነት ያላቸው ራሳቸውን የቻሉ መንግስታዊ ተቋማት በሕግ የተቋቋሙ ሲሆን በሀገራችን በዚህ አግባብ የተቋቋመ ተቋም የለም፡፡ ሆኖ በፍርድ ቤቶች በኩል አጥፊዎች ላይ ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት እንዲሰጡ ውሳኔ የሚሰጥበት አግባብ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም በጥቂት አጋጣሚዎች በተወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራዎችን ተከታትለው እንዲያስፈፅሙ የሚታዘዙት የወረዳ አስተዳደር ፅ/ቤቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቶች ሕዝባዊ የግዴታ አግልግሎት አሠጣጡን ውጤታማ ለማድረግ እንዲቻል ያመኑበትን ማንኛውንም ተቋም ወይም አካል የግዴታ ቅጣቱን ተከታትሎ እንዲያስፈፅምና ውጤቱን እንዲገልፅ ከማዘዝ የመከለክላቸው ሕግ የለም፡፡
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ እንዲሰራ የተወሰነበት ተቀጪ የተወሰነበትን የግዴታ ሥራ ቢያቋርጥ ምን ይሆናል?
ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ተቀጪ ላይ የሚወስኑት ቅጣት ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት በሚሆንበትና አጥፊው የተወሰነበትን ቅጣት መፈፀም ጀምሮ ካቋረጠ ውሳኔውን የሚስፈፅመው አካል በሚያቀርበው ሪፖርት ወይም በሌላ የሚመለከተው አካል ጠቋሚነት ተቀጪው ሳይሰራ በቀረው ጊዜ ልክ ቅጣቱ ወደ ቀላል እስራት ሊለወጥ እንደሚገባ የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 104 /3/ ያመልክታል፡፡ ሆኖም ተቀጪው የግዴታ ሥራውን በሚፈፅምበት ጊዜ የታመመ እንደሆነ ተቀጪው ከሕመሙ እስከሚድን ድረስ የግዴታ ሥራው ተቋርጦ ተቀጪው ከሕመሙ ሲድን የግዴታ ሥራውን ካቆመበት እንዲቀጥል እንደሚደረግ ነገር ግን ተቀጪው ከሕመሙ ካልዳነና የግዴታ ሥራውን መቀጠል ከጤንነቱ ጋር ተስማሚ የሆነ ሌላ ሥራ እንዲሰራ እንደሚያደርገው ተቀጪውም በድጋሚ የተሠጠውን ተለዋጭ ትዕዛዝ መፈፀም ካልቻለ ፍርድ ቤቱ ሌላ ቅጣት እንደማይሰጥበት ሕጉ ያስገነዝባል፡፡
በተቀጪዎች ላይ የሚጣለው የግዴታ ሥራ የት የት ሥፍራዎች ሊከናወን ይችላል?
በወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ተቀጪ ላይ የሚጣለው የግዴታ ሥራ ቅጣት የሚፈፀመው ተቀጪው ዘወትር በሚሰራበት ስፍራ ወይም በሕዝባዊ ተቋም ወይም ሕዝባዊ ሥራ በሚካሄድበት ሥፍራ ሊሆን ይችላል፡፡ /የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 103 /2// ተቀጪው በግዴታ ሥራነት እንዲሰራ የተወሰነበት ለዘወትር የሚሰራውን ሥራ ለተወሰነ ጊዜ በቅጣት መልክ እንዲሰራ ከሆነና ስራውን በመስራቱ ሊከፈለው ይችል ከነበረው የድካም ዋጋ /ደመወዝ/ ወይም በሥራው ፍሬ ከሚገኘው ጥቅም ላይ እስከ ሶስተኛ /ሲሶ/ የማይበልጠው ሒሳብ እየተቀነሰ ለመንግስት ገቢ መደረግ እንዳለበት ሕጉ ያስገነዝባል፡፡ ተቀጪው በሚሰራው የግዴታ ሥራ የሚገኝ ጥቅም ወይም ገቢ ካለም ከጥቅሙ ወይም ገቢው ላይ ሊቀነስ ስለሚገባው የገንዘብ ልክና ተያያዥ ዝርዝር ነጥቦች ውሳኔውን የሚሰጠው ፍርድ ቤት በፍርድ ላይ በዝርዝር የማስፈር ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
ስንት ዓይነት ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት አሠጣጥ አለ?
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ በወንጀል አጥፊዎች ላይ ሲወሰን ተቀጪው የግዴታ ሥራውን በሁለት መንገድ እንዲፈፅም ሊወሰን ይችላል፡፡ እነዚህም የግል ነፃነትን ከመገደብ ጋር የሚወሰን የግዴታ ሥራ እና የግል ነፃነትን የማይገድብ የግዴታ ሥራ ናቸው፡፡
· የግል ነፃነትን ከመገደብ ጋር የሚወሰን የግዴታ ሥራ
ተቀጪዎች ላይ የሚወሰነው የግዴታ ሥራ ቅጣት የተቀጪውን የግል ነፃነት በሚገድብ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ የግዴታ ሥራው ነፃነትን በሚገድብ መልኩ የሚሆነውም ውሳኔውን የሚሰጠው ፍርድ ቤት ነፃነት የማሳጣት ቅጣቱ ከግዴታ ሥራው ጋር መጣመር እንዳለበት አስፈላጊ ነው ተብሎ ከታመነ በተለይም በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 103 ወይም በዚህ ፅሁፍ የግዴታ ሥራን በቅጣትነት ለመወሰን መመዘኛ ተደርገው የተቀመጡ ግዴታዎችን ተቀጪው ሳያሟላ ከቀረ ወይም ተቀጪውን ከጎጂ አከባቢ ወይም መጥፎ ጠባይ ካላቸው ሰዎች ማግለል ሲያስፈልግ እንደሆነ በሕጉ ተመልክቷል፡፡
የግል ነፃነትን ከመገደብ ጋር የሚፈፀም የግዴታ ሥራ ተቀጪውን ከአንድ ቦታ ወይም ከአንድ አሰሪ ዘንድ ወይም ከአንድ የሥራ ተቋም ሳይለቅ ወይም ከመኖሪያ ስፍራው ሳይወጣ ወይም በመንግስት ባለስልጣኖች ተቆጣጣሪነት በሚጠበቅ ከአንድ የተወሰነ ስፍራ ሳይለይ የግዴታ ሥራውን እንዲያከናውን የሚያደርግ ሊሆን እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
· የግል ነፃነትን የማይገድብ የግዴታ ሥራ
ይህ የግዴታ ሥራ ዓይነት የተቀጪውን ነፃነት የማይገድብ ተቀጪው በተቆጣጣሪው አካል የግዴታ ሥራውን እየሰራና ቅጣቱን እየፈፀመ ስለመሆኑ ከሚደረግበት ክትትልና ቁጥጥር ውጪ የግል ነፃነቱ የማይገደብበት የግዴታ ሥራ ዓይነት ነው፡፡
ፍርድ ቤቶች ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራን አስመልክቶ ያላቸው ሥልጣን ምንድን ነው?
በፍርድ ጥፋተኛ የሚሰኙ አጥፊዎች ላይ በቅጣት መልክ የሚጣለውን የግዴታ ስራ አስመልክቶ ሙሉ ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች ሲሆኑ የመወሰን ስልጣናቸው ዓይነቱ ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ነው፡፡ ይኸውም፡ -
· ከመነሻው በተቀጪው ላይ ሊጣል የሚገባው ቅጣት እንደ ሕጉ ሁኔታ የሞት ቅጣት ወይስ የእስራት ቅጣት ወይስ የገንዘብ መቀጮ ወይስ ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም ሌላ መሆኑን ምክንያቱን በመዘርዘር የመወሰን፤
· ተቀጪው ምን ዓይነት ሕዝባዊ አገልግሎት መስራት እንዳለበት፤
· ተቀጪው ሕዝባዊ አገልግሎቱን ለምን ያህል ጊዜያት መስራት እንዳለበት፤
· ተቀጪው ሕዝባዊ አገልግሎቱን የት መስራት እንዳለበት፤
· ተቀጪው ሕዝባዊ አገልግሎቱን በማን ቁጥጥር ስር ሆኖ መስራት እንዳለበት፤
· ተቀጪው ሕዝባዊ አገልግሎቱን የሚፈፅመው ነፃነትን ከሚያሳጣ ሁኔታ ጋር ነው ወይስ ነፃነትን ከማያሳጣ ሁኔታ ጋር የሚለውን፤
· ተቀጪው በግዴታ ሥራነት እንዲሰራ የተወሰነበት ለዘወትር የሚሰራውን ሥራ ለተወሰነ ጊዜ በቅጣት መልክ እንዲሰራ ከሆነና ስራውን በመስራቱ ሊከፈለው ከሚችለው ከነበረው የድካም ዋጋ /ደመወዝ/ ወይም ከሥራው ፍሬው ከሚገኘው ጥቅም ላይ እስከ ሶስተኛ /ሲሶ/ ከማይበልጠው ሒሳብ ውስጥ ምን ያህሉ እየተቀነሰ ለመንግስት ገቢ መደረግ እንዳለበት የመወሰን ፍቅድ ስልጣን ተሠጥቷቸዋል፡፡
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራን አስመልክቶ የሚስተዋሉ ችግሮች ምንድን ናቸው?
· በፍርድ ቤቶች በኩል ወንጀለኛ ተብለው ጥፋተኛነታቸው በተረጋገጠ አጥፊዎች ላይ የእስር ቅጣትን መወሰንና አጥፊዎችን ማሰር እንደ ብቸኛና አስገዳጅ የቅጣት አማራጭ በመውሰድ የሚጣሉ እስራት ቅጣቶችን ወደ ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት ወይም የግዴታ ስራ መቀየር የሚቻልባቸውን የህግ ድንጋጌዎች በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ አለማድረግና ጥፋተኛ የተባሉ ሠዎችን በብዛት እንዲታሰሩ መወሰን፤
· በወንጀል ሕጉ ላይ ካሉ ጥቂት ድንጋጌዎች በስተቀር የግዴታ ስራን የሚመለከቱ ለአፈፃፀም አመቺነት ያላቸው ዝርዝር ሕጎች ያለመኖራቸው፤
· በፍርድ ቤቶች የሚወሰነውን ሕዝባዊ የግዴታ ስራ ተከታትሎ የሚያስፈፅም ስራውን እንደዋና ሥራ የሚሰራ በሕግ ተለይቶ የተቋቋመ ተቋም አለመኖሩ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡
የመፍትሔ ሀሳቦች
· የወንጀል ጥፋተኞችን የሚያርመው የግዴታ አጥፊዎችን በማሰር ብቻ አድርጎ ከማሰብ ይልቅ በተለይ የመጀመሪያ አጥፊዎች ሲኖሩና ከነገሮች አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር አጥፊዎች የበደሉትን ሕብረተሰብ በቀጥታ ሊክሱና ራሳቸውም ሊታረሙ የሚችሉባቸው ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠትን የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ የሚደረግበት ሁኔታ በፍርድ ቤቶች በኩል ተግባራዊ ቢደረግ፤
· ሕዝባዊ አገልገሎት ስለሚሰጥባቸው ሁኔታዎችና ተግባራዊ አፈፃፀሙን የሚመለከት ዝርዝር ሕግ ቢወጣ፤
· በፍርድ ቤቶች የሚወሰኑ ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት የመስጠት ውሳኔዎች በውጤታማነት ተከታትሎ የሚያስፈፅ ተቋም ቢቋቋም የሚሉት እንደመፍትሔ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments