የፍርድ ቤቶች የእግድ ትእዛዝ ተፈፃሚነት እስከየት ድረስ ነው?
ለአንድ ሀገር ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነትና ፍትሕ መረጋገጥ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶች መከበር በሕግ አግባብ የተቋቋሙ ገለልተኛ፣ ነፃ፣ ተጠያቂነት ያለባቸው እና በሕዝብ ዘንድ አመኔታን ያተረፉ ፍርድ ቤቶች ሚና የጎላ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ያለሕግ እና ያለፍርድ ቤቶች ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ የሕግ የበላይነትና ፍትሕ በአንድ ሀገር ውስጥ ይኖራል ብሎ መገመት አይቻልም፡፡
እነዚህ ፍርድ ቤቶች አሁን ባለው የሀገራችን ሕገ-መንግሥት ነፃ ሆነው መቋቋማቸውን እና በሀገሪቱ ውስጥ በፌዴራልም ሆነ በክልል ግዛቶች ሥር ብቸኛው የዳኝነት አካል እንደሆኑ ሕገ-መንግሥታዊ ማረጋገጫ አግኝተዋል፡፡ በዚህም አግባብ ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በሰዎችም መካከል አለመግባባት ሲፈጠር በሰላማዊ መንገድ በስምምነት፣ በድርድር ወይም በሽምግልና ወይም በእርቅ ለመፍታት ካልቻሉ ሥልጣን ወዳላቸው መደበኛ ወይም ሕጋዊ እውቅና ወደተሰጣቸው ፍርድ ቤቶች እንደሚሔዱ ይታወቃል፡፡
ፍርድ ቤቶችም በተከራካሪ ወገኖች ጠያቂነት ክርክሩ የመጨረሻ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የተለያዩ ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዞችን ሲሰጡ በሰፊው ይስተዋላል፡፡ ይህም ተገቢና የሕግ የበላይነትን ማስከበሪያ አንዱ ስልት ነው የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት የእግድ ትዕዛዝ በፍርድ ቤቶቹ ትዕዛዝ መሠረት እንደወረደ በአስፈፃሚው አካል ይፈፀማሉ ማለት ግን አይቻልም፡፡
ለዚህም ጽሑፍ መነሻ ምክንያት የሆነው ጸሐፊው እና ሌሎች ጠበቆች በሥራ አጋጣሚ እና ባለጉዳዮች በተለያዩ ጊዜያት ፍርድ ቤቶች የሰጡትን የተለያዩ የእግድ ትእዛዞችን ለማስፈፀም ጥረት ሲያደርጉ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመዳሰስና ችግሮቹ ወደ ፊት የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን “ጥርስ የሌለው አንበሳ” እንዳያደርጋቸው ስጋት ስላለኝ፣ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን በአስፈፃሚው አካል “ቢሮክራሲያዊ” አሠራር እንዳይሸራረፍና የዜጎች መብት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ችግሮቹን ጠቆም ለማድረግና በአንባቢያን እና በሕግ ባለሙያዎች ዘንድ ውይይት እንዲደረግበትና ሀላፊነት በሚሰማው በሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲበጅለት በማሰብ ነው፡፡
የእግድ ትዕዛዝ
እግድ ማለት አንድን ነገር እንዳያደርጉ፣ እንዳይፈፅሙ ወይም እንዳያከናውኑ ወይም አንድ ነገር እንዳይጠፋ፣ እንዳይበላሽ ወይም አንድ ተግባር እንዲፈፀም ወይም እንዳይፈፀም ለተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ ትዕዛዝ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የእግድ ትዕዛዝ በተለያዩ ተቋማት የሚሰጥ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በፖሊስ፣ በፍርድ ቤት፣ በዓ/ሕግ መስሪያ ቤትና ወ.ዘ.ተ. ይጠቀሳሉ፡፡ ለዚህ ፅሁፍ አላማ ሲባል በፍርድ ቤት የሚሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ላይ እናተኩራለን፡፡
በመሰረቱ ዕግድ የሚሰጠው ለክርክሩ መነሻ የሆነው ንብረት የሚጠፋ፣ የሚበላሽ፤ ተከሳሹ ለሌላ ሰው አሳልፎ ለመስጠት፣ ለመሸጥ ወይም በሌላ ዘንድ በተሰጠ ውሳኔ ንብረቱን ያለአግባብ አዛውሮ ለመስጠት ወይም ለመሸጥ ያቀደ፣ መሆኑ ወይም የባለመብቱ ጥቅም ለመጉዳት ለሌላ ሰው አሳልፎ ለመስጠት የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩን ፍርድ ቤቱ ከተገነዘበ አስፈላጊውን ትዕዛዝ የሚሰጥ ስለመሆኑ ከፍ/ብ/ስ/ስ/ሕ/ቁ.154 (1) መረዳት ይቻላል፡፡ የድንጋጌው መሰረታዊ ዓላማም ዳኝነት እንዲሰጥለት የጠየቀ ወገን በፍርዱ ሂደት ረቺነቱ ቢረጋገጥለት የተሰጠውን ፍርድ ለማስፈፀም ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርለት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በወንጀል ጉዳይም እግድ የሚሰጥበት አግባብ ያለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሚጠቀሰው አንድ ሰው ከሀገር እንዳይወጣ የሚሰጠው የእግድ ትእዛዝ ተጠቃሽ ነው፡፡ በአፈፃፀም ክርክር ላይም አንድ ሰው የፍርድ ባለዕዳ ሆኖ እንደፍርዱ ለመፈፀም ፍቃደኛ ባለመሆን ከሀገር ለመሸሽ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ፍርድ ቤት ከተረዳው ይህ ግለሰብ ከሀገር እንዳይወጣ የእግድ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡
የእግድ አይነቶችና የአፈፃፀም ተግዳሮቶቹ
ፍርድ ቤቶች የተለያዩ እግዶችን እንደሚሰጡ ይታወቃል ከእነዚህ ውስጥ መኖሪያ ቤት ፣ ተሽከርካሪ፣ በባንክ ውስጥ ያለ ገንዘብ፣ በአንድ ማህበር ውስጥ ያለ የአክሲዬን ድርሻ…ወዘ.ተ እንዲታገድ፣ እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥ እና በማናቸውም መንገድ እንዳይንቀሳቀስ ወይም ወደ ሌላ 3ኛ ወገን ተላልፎ እንዳይሰጥ የሚሰጠው የእግድ ትዕዛዝ ዋነኛው ነው፡፡ ፍርድ ቤት የሚሰጧቸው የእግድ ትእዛዞች እንደወረዱ በወቅቱ ይፈፀማሉ ማለት ግን አይቻልም፡፡ ፍርድ ቤቶች የእግድ ትዕዛዙን ከሰጡ በኋላ እግዱን ለማስፈፀም መሬት ላይ ያለው ችግር እንደሚከተለው ይዳሰሳል፡፡ ችግሮቹ ግን ከስር የተመለከቱት ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ
ፍርድ ቤቶች በተለመደው የአቤቱታ ቀን አሰራራቸው ካለባቸው የሥራ ጫና በተጨማሪ የእግድ አቤቱታዎች ሲሆኑ በየቀኑ በማስተናገድ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ተገቢ ነው ብሎ ሲያምን የእግድ ትዕዛዝ ይሰጣሉ፡፡ ካለባቸው የሥራ ጫና አንፃር ለዚህ አገልግሎታቸው ፍርድ ቤቶችና ሰራተኞቻቸው በእጅጉ ሊመሰገኑ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የእግድ ትዕዛዝ በአስቸኳይ “ከሴክሬተሪዎች” ተገልብጦ ከወጣ በኋላ እግዱን አንድ ባለጉዳይ ወይም ወኪሉ ይዞ ወደ አስፈፃሚ አካላት (የአስተዳደር መስሪያ ቤት) በሚሄድበት ወቅት እግዱ በባህሪው አስቸኳይ መሆኑ ይቀርና መጀመሪያ የፍርድ ቤቱን የእግድ ትዕዛዝ በመዝገብ ቤት ወይም በሀላፊው ፅ/ቤት በኩል አስፈርሞ ገቢ መደረጉ እና እንደ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እግዱ መፈፀሙ ይቀርና “የንብረቱ” ፋይል ይውጣ ይባላል፣ ከዛ ፋይሉን ለማውጣት የንብረቱ ካርታ ይጠየቃል፣ ካርታ ካልያዙ የፍርድ ቤቱ እግድ ተፈፃሚነቱ ውሀ ይበላዋል፡፡ ከአንድና ሁለት ቀናት ምልልስ በኋላ ፋይሉ ከወጣ በኋላ “ሀላፊው ይመራበታል” ይባልና ሀላፊው የለም፣ ሀላፊው ሲመጣ፣ መዝገብ ቤት ገቢ አድርገው ይባልና መጀመሪያውኑ መፈፀም ያለበት ተግባር ሳይፈፀም እግዱ ላይ ሳይመራበት ይታለፋል፣ ፋይሉ ተገኝቶ ለሚመለከተው “ባለሙያ” ሲላክ ባለሙያው “የፍርድ ቤት እገዳ አገልግሎት ክፍያ መመሪያ ስላለ ብር 200 ከፍለህ ትመጣለህ ይላል”፣ ክፍያው ከተፈፀመ በኋላ ስለመታገዱ የፅሁፍ ምላሽ ለመውሰድ ነገ ና ትባልና ነገ ስትመጣ አልቆ ይጠብቀኛል ስትል እዛው ባለህበት “ትንሽ አረፍ በል ተብለህ”- መፃፍ ይጀመራል- “ንብረቱ ሳይታገድ እንዴት እንደሚታረፍ እኔንጃ ”፣ የፍርድ ቤቱ የእግድ ትዕዛዝ አስፈፃሚ አካላት ጋር ሲደርስ ንብረቱ ሳይታገድ ከአምስት ቀን በኋላ በመጨረሻ ንብረቱ መታገዱን የሚገልፅ ደብዳቤ በፍርድ ቤቱ አድራሻ የተፃፈ ደብዳቤ ይሰጡሀል-የእግድ ትዕዛዙ ላይ ፍርድ ቤቱ ስለመታገዱ በፅሁፍ ምላሽ ስጡኝ አለማለቱን ልብ ይሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ የእግድ ትዕዛዙን በሰጠበት ቀን ወይም ቢበዛ በነጋታው ንብረቱ ካልታገደ በዚህ ተገቢ ያልሆነ የፍርድ ቤትን ሥልጣን እና የንብረቱ አለመታገድ የሚያመጣውን የጥቅም ኪሳራ ከግምት ያላስገባ በግለሰቦች የተፈጠረ ቢሮክራሲ ንብረቱን ለሌላ 3ኛ ወገን ተላልፎ ሊሰጥ የሚችልበት ሂደት ሰፊ በመሆኑ ይህ ጉዳይ በሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በዚህ አሰራር ምክንያት ንብረቱ ወደሌላ ሰው ስም ተዘዋውሮ ሲያጋጥም ወደ ሌላ ክስ ወይም ወደ ሌላ የሕግ አማራጭ የሚገቡ ባለጉዳዬችና ባለሙያዎች ቀላል አይደሉም፡፡ ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚፈጥረው የሥራ ጫና ቀላል አይደለም፡፡
የሚንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ
ከሚንቀሳቀሱ ንብረቶች መካከል ከተሽከርካሪ እግድ ጋር በተያያዘ እንደ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማሳገድ ከሚገጥመው ችግር ያን ያህል ችግር አይታይም፡፡ ያለው ችግር “ለእግድ የአገልግሎት ክፍያ ብር 500 ይከፈላል” የሚባለው “ አዲስ መመሪያ” ነው፡፡ የፍርድ ቤት የእግድ ትእዛዝን ለመፈፀም ምንም አይነት ክፍያ መፈፀም የለበትም የሚል አቋም አለኝ፡፡ ነገር ግን ይህ አቋሜ አስፈፃሚ አካላት እግዱን ለመፈፀም ሰነዶችን የማጣራት፣ በባለሙያዎች ለሚወጣው ጉልበትና ጊዜ ተገቢው ተመጣጣኝ ዋጋ ቢከፈል ግን ተቃውሞ የለኝም፡፡ ከዚህ ቀደም ተሽከርካሪ በሚመለከተው የአስተዳደር መ/ቤት ለማሳገድ የሚከፈለው የእግድ አገልግሎት ክፍያ ብር 20 (ሀያ ብር) ሲሆን በአሁን ሰዓት ከወጣ ወራቶች ሆነውታል በተባለው “መመሪያ” መሠረት ብር 500 (አምስት መቶ) ካልተከፈለ የፍርድ ቤቱ የእግድ ትእዛዝ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡
የፍርድ ቤት እግድን ለመፈፀም የማይንቀሳቀስ ንብረትን ለማገድ ብር 200 እየተጠየቀ ተሽከርካሪ ለማገድ ብር 500 መጠየቅ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ተቀባይነት አለው ቢባል እንኳን ከሚወስደው የጊዜና የጉልበት ወጪ እና ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝነት የሌለውና በድጋሚ ሊታይ የሚገባው የአገልግሎት ክፍያ ዋጋና መመሪያ ነው፡፡ በጥናት ላይ ተመስርቶም የወጣ መመሪያ አይመስለኝም፡፡
በምንም አይነት መስፈርት ለአንድ ሚለዮን ብር ክርክር ለሚታገደው ተሸከርካሪ እና ለአምስት ሺህ ብር ክርክር ለሚታገደው ተሽከርካሪ ተመሳሳይ የእግድ አገልግሎት ክፍያ ብር 500 መጠየቁ ተገቢነት የለውም፡፡ በፍርድ ቤት እንኳን ለጠቀሰው የገንዘብ መጠን ክርክር ተመሳሳይ የዳኝነት ክፍያ አይከፈልም፡፡ መመሪያውን ማሻሻል ጊዜ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን የገንዘብ መጠን መክፈል የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ባሉበት ሀገር እግዱን ተግባራዊ ካደረጉ በኋላ ብሩ የሚከልበት አግባብና አሰራር በመመሪያው ውስጥ ቢያንስ ሊካተት ይገባል፡፡ ይህ ጉዳይ ለማይንቀሳቀስ ንብረት እግድ አገልግሎትም በተመሳሳይ ሊፈፀም ይገባል፡፡ ለምሳሌ በፍርድ ቤቶቻችን “ደሀ” የሆነ ሰው ደሀ ስለሆነ ብቻ ፍትሕ የማግኘት መብቱ አይገደብበትም ምክንያቱም በደሀ ደንብ ክስ አቅርቦ መብቱን የማስከበር እድሉ አለው፡፡ መጨረሻ ላይም የገንዘብ ጥቅም ካገኘ የዳኝነቱ ክፍያ እንዲከፈል ይደረጋል፡፡ ይህ የፍርድ ቤቶች ጥሩ ተሞክሮ ተሽከርካሪዎችን በሚያግደው ተቋም ሊተገበር ይገባዋል፡፡
የተሽከርካሪ እግድ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወደዚህ ተቋም ይዞ የሄደ ባለጉዳይ ብር አልያዝኩም እግዱን አግዱልኝ እና ብሩን ላምጣ ሲል “ብሩን ስትይዝ ተመለስ፣ የእግድ ትዕዛዙ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት እንዲታገድ በሀላፊው ለባለሙያዎች የተመራው ይሰረዛል ነው የተባለው”፡፡
እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ለመቀበል (ለመፈፀም) ፍቃደኛ ያልሆነው ሰው ላይ ለፍ/ቤቱ በአቤቱታ አሳውቆ ፍ/ቤቱ የሚሰጠውን ትእዛዝ በፖሊስ ረዳትነት ማስፈፀም ነው የሚቀለው ወይስ የባለጉዳዬችን መብትና ጥቅም አስፈፃሚ አካሉ በሚጠይቀው መስፈርት መሠረት ያለምንም ተቃውሞ በአስቸኳይ ማስፈፀም?
በሌላ በኩል የገንዘብ አቅም የሌለው ሰው ቢኖር የተሽከርካሪው ስመ-ሀብት በቀላሉ ወደ ሌላ 3ኛ ወገን ሊተላለፍ ስለሚችልና ባለመብቱ ላይ ከፍ ያለ ሊካስ የማይችል ጉዳት ሊደርስ ስለሚችል የደሀ-ደንብ አሰራር እና የፍርድ ቤትን እግድ በአስቸኳይ የማስፈፀም ባህል በአስፈፃሚው መስሪያ ቤት በኩል ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡
እንደማጠቃለያ
ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ማናቸውም የእግድ ትዕዛዝ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ መሆን ቢችል፣ ስለእግድ ትዕዛዞች አስፈላጊነት እና አስቸኳይነት በሚመለከታቸው የፍርድ ቤት አካላት ለአስፈፃሚው አካል ወይም በአስፈፃሚው አካል ውስጥ በሚሰሩ የሕግ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ቢሰጥ፣ አስፈፃሚ አካላትም የሚያወጡትን መመሪያ በሕግ ባለሙያዎች ቢያስተቹና የፍርድ ቤት እግድ ወዲያውኑ እንዲፈፀም ቢያደርጉ፣ የሕግ ባለሙያዎችም እግዱ ተፈፃሚ እንዲሆን የተቻለንን ጥረት ማድረግና ፍ/ቤቶችም ያላቸውን ሥልጣን ለማስከበርና በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን የሀገር ፍላጎት ለማሳካት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንደ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለመፈፀም ፍቃደኛ የማይሆኑትን የአስፈፃሚ አካላት ሰራተኞችና ሀላፊዎች ወይም ማንም ሰው በህጉ መሠረት አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ፍ/ቤቶች መሥራት ያለባቸው ተግባር ሆኖ የፍርድ ቤቶችን ክብርና ተቋማዊ ነፃነት ለማረጋገጥ የሚሰጡትን ማናቸውንም የእግድ ትዕዛዝ በመፈፀምና በማስፈፀም ሁላችንም ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የበኩላችንን እንወጣ የሚል እምነት አለኝ!!!
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments