ቼክና ዋስትና
በአንድ አገር የገበያ ሥርዓት ውስጥ ክፍያ የሚካሄድበት ደንብ አለ፡፡ የክፍያ ሥርዓቱም በዓይነት፣ በጥሬ ገንዘብ፣ በሰነድ ወይም በኤሌክትሮኒክስ ሊሆን ይችላል፡፡ በዓይነት ወይም በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ ግብይቶች በአብዛኛው ተጨማሪ ወጭ የሚጠይቁ፣ ለአያያዝ የማይመቹ እና የደህንነት ሥጋት ያለባቸው የክፍያ መፈፀሚያ ዓይነቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ሥጋቶች ለመቅረፍ እና የክፍያ ሥርዓቱን የበለጠ ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድረግ ክፍያ በቀላሉ ሊፈፀምባቸው የሚችሉ ተላላፊ የንግድ ሰነዶች ተፈጥረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የንግድ ህግ አራተኛ መፅሃፍ ሥርም ከአንቀጽ 715-895 ስለ ተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች ዓይነት፣ አጠቃቀም እና ኃላፊነት በዝርዝር ተደንግጓል፡፡ በንግድ ህጋችን እውቅና የተሰጣቸው ተላላፊ የሆኑ የክፍያ መፈፀሚያ ሥርዓቶች አራት ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በመጋዘን ለተቀመጡ ዕቃዎች የሚሰጥ ደረሰኝ (warehouse goods deposit certificate) እንደ ንግድ ወረቀት እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ግን የክፍያ መፈፀሚያ ሳይሆን፣ በመጋዘን የተቀመጡ ዕቃዎችን መጠየቂያ ነው፡፡ ከንግድ ህግ በተጨማሪም በፍትሃብሔር ህጉ እና የተለየ ህግ ወጥቶለት ይገኛል፡፡ የክፍያ መፈፀሚያ የንግድ ወረቀቶችም የሃዋላ ወረቀት፣ ቼክ፣ የተስፋ ሰነድ እና የመንገድ ቼክ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የክፍያ ሥርዓቶች ውስጥ በኢትዮጵያ ከሌሎች አንፃር በተሻለ በስፋት የሚሰራበት ቼክ ነው፡፡ ቼክ ለባንክ ወይም ለተመሳሳይ ተቋም እንደቀረበ ክፍያ የሚፈፀምበት እና ለሌላ አገልገሎት የማይውል ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ሮይ ጉድ የተባሉ የንግድ ህግ ምሁር ሲፅፉ፡-
“…It is primarily a payment direction, not a credit instrument, and is by its nature intended to be presented and paid almost immediately…” ብለዋል ትርጉሙም… የዱቤ ሰነድ ሳይሆን በቀጥታ ክፍያ የሚፅምበት እና በባህሪውም እንደቀረበ ወዲያውኑ የሚከፈል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ቼክን በተመለከተ በሚደረጉ ክርክሮችም፣ ቼክ ለባንክ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ወረቀት እንደሆነ እና ለሌላ አገልግሎት እንደማይውል መግባባት አለ፡፡ ይህ አቋም ግን አስገዳጅ የህግ ትርጉም የመስጠት ሥልጣን ባለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የተለወጠ ይመስላል፡፡ የዚህ ፅሑፍ ዓላማም በቼክ ባህሪ እና በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ምልከታ ለማድረግ ነው።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመሰረታዊ የህግ ትርጉም ስህተት ላይ ከ5 ባላነሱ ዳኞች የሚሰጠው ውሳኔ በሃገሪቱ የሚገኙ የዳኝነት እና ዳኝነት መሰል አካላት እንዲከተሉት በአዋጅ ቁጥር 1234/13 ተደንግጓል፡፡ በዚህ ሥልጣኑ መሠረት ፍ/ቤቱ በበርካታ ጉዳዮች በበታች ፍ/ቤቶች አስገዳጅነት ያላቸው የህግ ትርጉም ውሳኔዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ከሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ ከቼክ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በሚነሱ ክሶች ላይ በሠበር መዝገብ ቁጥር 24435 የካቲት 4/2000 ዓ.ም የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው ውሳኔ ነው፡፡
የጉዳዩ አመጣጥና የተሰጡት ውሳኔዎች በአጭሩ የሚከተለው ነው፡፡ በሰበር ችሎት አመልካች የሆኑት ግለሰብ ቁጥር 0574420 በሆነ ቼክ ብር 55,000 (አምሳ አምስት ሺ ብር) እንዲከፈልበት ለተጠሪ ፈርመው የሰጡ ሲሆን ቼኩ ለባንክ ቀርቦ ሳይከፈልበት ተመልሷል፡፡ ተጠሪ ከዚህ የቼክ ገንዘብ ውስጥ ብር 25,000 (ሃያ አምስት ሺ ብር) ተከፍሏቸው ብር 30,000 (ሰላሳ ሺ ብር) ያልተከፈላቸው ስለሆነ ይኸው ገንዘብ እንዲከፈላቸው ክስ ይመሰርታሉ፡፡ አመልካች ክሱ ሲቀርብባቸው በሰጡት መልስ ቼኩ የተሰጠው በተጠሪና አቶ ሙሳ መሐመድ መካከል በነበረው አለመግባባት በሽምግልና ጉባኤ በቀረበው ሃሳብ መሠረት ለሁለቱ ተከራካሪዎች መተማመኛነት የተሰጠ እንጂ ለክፍያ የተሰጠ አይደለም ብለዋል፡፡ ጉዳዩን መጀመሪያ ያየው ፍ/ቤትም ቼክ ግልጽ የሆነ የክፍያ ትዕዛዝ፣ በአውጭው ላይ የክፍያ ኃላፊነት የሚፈጥር የገንዘብ ሰነድ እንጅ በዋስትናነት የሚሰጥ አይደለም በማለት የአመልካችን ክርክር ሳይቀበል ገንዘቡን እንዲከፍሉ ወስኗል፡፡ ጉዳዩን በይግባኝ ያየው ፍ/ቤትም ቅሬታውን ሳይቀበል የሥር ፍ/ቤቱን ውሳኔ አፅንቷል፡፡
ከዚህ በኋላ ጉዳዩ የቀረበው ለፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ነው፡፡ የሃገሪቱ ፍ/ቤቶች የመጨረሻ የሆነው ይኸው ችሎትም ግራ ቀኝ ወገኖችን አከራክሮ በድምጽ ብልጫ በመ/ቁ. 24435 በ4/6/2000 በሰጠው ውሳኔ ቼክ በዋስትና ሊሰጥ የማይችል ለመሆኑ በንግድ ህጉ አልተደነገገም፣ በአመልካች እና ተጠሪ መካከል የዋስትና ውል ግንኙነት ያላቸው ለመሆኑ ስለተገለፀ እና ይህ ደግሞ የግል ግንኙነት ያላቸው ለመሆኑ ስለሚያመለክት እና ይህ ደግሞ የግል ግንኙነት (Personal relation) መኖሩን ስለሚያሳይ አመልካች በመቃወሚያነት ሊያቀርቡት ይችላሉ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ በአጭሩ በሰበር ውሳኔ መሠረት ቼክ በዋስትናነት ወይም መተማመኛነት ሊሰጥ የሚችል ሰነድ ነው ማለት ነው፡፡
እውን ቼክ በዋስትናነት ወይም መተማመኛነት ሊሰጥ የሚችል ሰነድ ነውን?
ቼክ እንደ ዋስትና
ቼክ ምንድን ነው? ዋስትና ምንድን ነው? ቼክን ከሌሎች ተላላፊ የገንዘብ ሰነዶች የሚለዩት ባህሪያት ምንድን ናቸው? የቼክ አይነቶች ምንድን ናቸው? የሚሉትን መመልከት መነሻችንን ለመረዳት ጠቃሚ ነው፡፡ ቼክን የተለያዩ ምሁራን በተለያየ መንገድ ይገልፁታል፡፡ ሁሉም የሚስማሙበት ትርጉም ግን ቼክ ገንዘብ የሚከፈልበት ተላላፊ ሰነድ መሆኑን ነው፡፡ ቼክ እውነተኛ ገንዘብን ተክቶ ክፍያን ለማቀላጠፍ የሚያስችል እንደቀረበ የሚከፈልበት እና ሃተታ የሌለበት ተላላፊ የንግድ ወረቀት እንደሆነ blacks law የተሰኘ የህግ መዝገብ ቃላት ተርጉሞታል፡፡ ይህ ትርጉም ተቀባይነት ያለውና በእኛ ሀገር የንግድ ህግም የተካተተ ለመሆኑ የንግድ ህግ ቁጥር 732፣ 827 እና 854 ገጣጥሞ በማንበብ መረዳት ይቻላል፡፡
ቼክ መብቱ ከሰነዱ ተነጥሎ አይሰራበትም፡፡ የቼኩ አውጭም ቼኩ ላይ ለተፃፈው ገንዘብ አከፋፈል ኃላፊነት አለበት፡፡ ቼክ ከሌሎች ተላላፊ የንግድ ወረቀቶች ያለውን አንድነት እና ልዩነት በአጭሩ መመልከት መልካም ነው፡፡ በንግድ ህግ ቁጥር 732(2) ላይ 5 ዓይነት የንግድ ወረቀቶች ተመልክተዋል፡፡
እነዚህም
- የሃዋላ ወረቀት (Bill of Exchange)
- የተስፋ ወረቀት (Promissory notes)
- ቼክ (chque)
- የመንገድ ቼክ (Travelers cheque)
- በመጋዘን ላሉ ዕቃዎች የሚሰጡ የምስክር ወረቀቶች (Warehouse certificate) ናቸው።
ቼክና የሃዋላ ወረቀት
ሁለቱ ሰነዶች በርካታ ተመሳሳይነት አላቸው። ሃዋላም ቼክም ሃተታ የሌለባቸው እና የመተላለፍ ጠባይ ያላቸው ናቸው፡፡ በኮመን ሎው የህግ ሥርዓት ተከታይ አግሮች ዘንድ ቼክ አንድ ዓይነት የሃወላ ወረቀት ነው፡፡ ልዩነቱ ከፋዩ ባንክ መሆኑ ነው። የሲቪል ሎው የህግ ስርዓት በሚከተሉ ሃገሮች ግን ቼክ እና ሃዋላ ራሳቸውን ችለው የቆሙ ናቸው፡፡ ተመሳሳይነታቸው የበዛ ቢሆንም የሚከተሉት ዋና ልዩነቶች አሏቸው።
- የቼክ ከፋይ ምን ግዜም ባንክ ነው፡፡ የሃዋላ ከፋይ ግን ባንክ ላይሆን ይችላል፡፡ (የንግድ ህግ ቁጥር 829)
- በሃዋላ ወረቀት ላይ ተከፋይ ወለድ ሊታዘዝ ይችላል፡፡ በቼክ ግን አስቀድሞ ሊታዘዝ አይችልም፡፡ በቼክ ወለድ የሚታሰበው ቼኩ ለባንክ ቀርቦ ሳይከፈል ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ ነው (የንግድ ህግ ቁጥር 739 እና 873)
- ቼክ የሚያዝ ሰው በባንክ ሂሳብ ሊኖረው ሲገባ ለሐዋላ ግን አስፈላጊ አይደለም፡፡
- የሃዋላ ወረቀት ለእሽታ (Acceptance) መቅረብ ሲገባው ቼክ ግን እሽታ አያስፈልገውም (የንግድ ህግ ቁጥር 757
- የሃዋላ ወረቀት በዋስትና ሊያዝ እንደሚችል በንግድ ህግ አንቀጽ 754 ላይ ተመልክቷል፡፡ ቼክ ግን በዋስትና ሊያዝ እንደሚችል በየትኛውም የህጉ ክፍል አልተመለከተም፡፡
ቼክና የተስፋ ሰነድ
ሁለቱም ሰነዶች ሃተታ የሌለባቸው እና ተላላፊ የንግድ ወረቀቶች መሆናቸው ያመሳስላቸዋል፡፡ በቼክ ሦስት ባለድርሻዎች ማለትም የቼኩ አውጭ (drawer) ባለመብት (holder) እና ከፋይ (ባንክ) ሲኖሩ በተስፋ ሰነድ ግን የሰነዱ ሰሪ (Maker) እና ተከፋዩ ብቻ ናቸው፡፡ የተስፋ ሰነድ ወደፊት ያለ ዕዳ ክፍያ ማረጋገጫ ሰነድ ነው፡፡ ሌሎች የንግድ ወረቀቶች ማለትም የመንገድ ቼክ እና የመጋዘን የምስክር ወረቀት ተላላፊ የንግድ ወረቀቶች መሆናቸው ከቼክ ጋር መሳስላችዋል፡፡
የቼክ ዓይነቶች
በአብዛኛው የሚታወቁት የቼክ ዓይነቶች
- ለአምጪው የሚከፈል ቼክ (Bearer cheque)
- የአምጪው ስም ያለተፃፈበት ቼክ (Blank cheque)
- የስርዝ ምክልት ያለበት (crossed cheque)
- ሲቀርብ እንደሚከፈልበት በአውጪው የተረጋገጠ ቼክ (ምልክት ያለው ቼክ) (Marked cheque or certified cheque)
- የሠረዝ ምልክት የሌለበት (open cheque)
- የትዕዛዝ ቼክ (order cheque)
- ማረጋገጫ ቼክ (Memorandum cheque) ናቸው።
ለአምጪው የሚከፈል ቼክ ማንነትን መነሻ ሳያደርግ ቼኩን ላመጣ ሰው ክፍያ የሚፈፀምበት ነው፡፡ ባዶ ቼክ ደግሞ የአምጪው ስም ያልተፃፈበት ሰነድ ነው፡፡ የሰረዝ ምልክት ያለበት ቼክ የሚከፈለው አምጪው ደንበኛ የሆነለት ባንክ ወይም ለራሱ ለባንኩ ደንበኛ ብቻ ነው፡፡ ምልክት ያለው ቼክ ደግሞ ለባንክ ሲቀርብ እንደሚከፈልበት በተጨማሪም በአውጪው የማረጋገጫ ምልክት የሚሰጥበት ነው፡፡ ግልጽ ቼክ ምልክት የሌለው እንደቀረበ የሚከፈልበት ነው፡፡ የትዕዛዝ ቼክ ለተወሰነው ሰው ወይም እሱ ለሚያዝለት ብቻ የሚከፈልበት ነው። የማረጋገጫ ቼክ ደግሞ ተበዳሪ ብድሩን እስኪከፍል በመተማመኛነት ለአበዳሪው የሚሰጥ ነው፡፡ በእኛ ሀገር የንግድ ህግ ውስጥ ዕውቅና የተሰጣቸው 1፣ 2፣ 3፣ 5 እና 6ኛ ላይ የተመለከቱት ናቸው [የንግድ ህግ ቁጥር 833፣ 848፣ 863]፡፡
በሰበር ችሎቱ ውሳኔ ላይ የቀረበ ትችት
የቼክ ባህሪያት እና ዓይነቶች ከላይ የተመለከቱት ከሆኑ፣ ቼክ በዋስትና ሊሰጥ ይችላል ወይ? የሚለውን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡ ዋስትና በራስ ወይም በንብረት ለአንድ ግዴታ መፈፀም የሚገባ ውል ነው፡፡ ዋስትና በራስ (surety) ወይም በንብረት ሊደረግ ይችላል፡፡ በራስ የሚሰጥ ግዴታ ባለዕዳ የሆነው ሰው ግዴታውን ሳይወጣ ቢቀር ዋሱ ባለዕዳውን ተክቶ ግዴታውን የሚወጣበት ሂደት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ዋስትና በአገራችን ፍትሐብሔር ህግ ከቁጥር 1920-1951 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የግል ዋስትናን በህጉ የተተረጎመው እንዲህ በሚል ሁኔታ ነው፡፡
‹‹ለግዴታው አፈፃፀም ዋስ የሚሆን ሰው ባለዕዳው ግዴታውን ያልፈፀመ እንደሆነ ለባለገንዘቡ ይህንን ግዴታ ሊፈፅም ይገደዳል›› (አንቀጽ 1920)
ስለዚህ በራስ የሚደረግ ዋስትና (Personal guarantee) ባለዕዳ የሆነው ሰው ግዴታውን መፈፀም ያልቻለ እንደሆነ ዋሱ በእርሱ እግር ተተክቶ ዕዳውን ለመክፈል የሚገደድበት የህግ ማዕቀፍ ነው፡፡
በንብረት የሚደረግ ዋስትና ደግሞ ንብረቱን የሚከተል ነው፡፡ በንብረቱ ዋስ የሆነው ባለዕዳ ግዴታውን ባይወጣ ዋሱ በመያዣ የሰጠው ንብረት ለግዴታው ማስፈፀሚያ ይሆናል፡፡ የዚህ ዓይነት ዋስትና ተንቀሳቃሽ ንብረት ወይም መሰል ንብረቶች መስጠትን (pledge)፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት በመያዣ መስጠትን (Mortgage)፣ የወለድ አገድ ውልን (Antichresis) የሚጨምር ነው።
ቼክ መብቱ ከሰነዱ ተነጥሎ የማይሰራበት፣ እንደቀረበ የሚከፈልበት፣ ተላላፊ ሰነድ ስለሆነ በንብረትነት ይያዛል፡፡ መደቡም በተንቀሳቃሽ ንብረት (Corporeal chattle) ስር ነው (የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1128)፡፡ ቼክ በተንቀሳቃሽ ንብረት ስር የሚመደብ ስለሆነ በህግ በዋስትና ሊሰጥ ይችላል ቢባል እንኳ ሊሰጥ የሚችለው በንብረት ዋስትናነት (Pledge) እንጅ በራስ ዋስትናነት (surety) አይደለም፡፡ ነገር ግን ቼክ በዋስትና ሊሰጥ ይችላልን? ቼክ እውነተኛ ገንዘብን ተክቶ ክፍያን ለማቀላጠፍ የሚያስችል እንደቀረበ የሚከፈልበት ሃተታ የሌለው ዋጋው ከፍ ያለ የንግድ ወረቀት መሆኑን አስቀድመን ተመልክተናል፡፡ ቼክ እንደቀረበ የሚከፈልበት ሰነድ መሆኑ በህግ ከተመለከተ እንዴት በዋስትና ሊሰጥ ይችላል? በእርግጥ በቼክ ላይ መቃወሚያ ማንሳት እንደሚቻል በንግድ ህጉ ቁጥር 717 እና 850 ላይ ተመልክቷል፡፡ የመቃወሚያ ዓይነቶችም የግል ግንኙነትን መነሻ የሚያደርጉ (Personal defences) እና በማንም ላይ ሊሰሩ የሚችሉ መከላከያዎች (real defences) ናቸው፡፡
በማንም አምጪ ላይ ሊነሱ የሚችሉ መቃወሚያዎች የሚባሉት ፊርማን በተመለከተ፣ ውክልናን በተመለከተ፣ የቼኩን ፎርም በተመለከተ፣ ችሎታን በተመለከተ፣ ክስ ለማቅረብ የሁኔታዎች አለመሟላትን በተመለከተ የሚነሱ ናቸው፡፡ የግል ግንኙነትን መነሻ የሚያደርጉ መቃወሚያዎች ግን በአምጪው (ከሳሽ) እና ከፋዩ (ተከሳሹ) መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ነው፡፡ የግል ግንኙነት ምንነት በህጉ በግልፅ ባይተረጎምም ለቼኩ መሠጠት መነሻ የሆነው ህጋዊ ድርጊት (juridical act) እንደሆነ በርካታ የህግ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ ለቼኩ መሰጠት ምክንያት የሆነው ነገርም ህጋዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በህጉ የተደነገገውን ግዴታ በመጣስ ቢዋዋሉ ስምምነታቸው ውጤት ሊሰጠው አይገባም፡፡ በንግድ ህግ ቁጥር 854 መሠረት ቼክ እንደቀረበ የሚከፈልበት ሰነድ ስለሆነ በዋስትና ሊሰጥ አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ቼክ የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል የሚሰጥ ሃተታ የሌለበት ትዕዛዝ (unconditional order to pay) እንደሆነ የንግድ ህግ ቁጥር 827 (ሀ) ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለትም በቼኩ ላይም ሆነ በሌላ ሰነድ የቼኩን ክፍያ ክፍያ በሁኔታ ላይ የተመሰረተ (conditional) ማድረግ አይቻልም፡፡ ቼኩ ለመተማመኛ ዋስትና ነው የተሰጠው የሚለው የአመልካች ክርክር የሚያመለክተው፣ ቼኩ ለክፍያ አለመሆኑን ነው፡፡ የቼኩ አውጭ ደግሞ ለአከፋፈሉ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከአከፋፈሉ ኃላፊነት ለመዳን በቼኩ ላይ ወይም በሌላ ሰነድ የሚደረግ ቃል ሁሉ ደግሞ ተቀባይነት የሌለው እና እንዳልተፃፈ የሚቆጠር እንደሆነ በንግድ ህግ ቁጥር 840 ላይ በአዛዥነት ተደንግጓል፡፡ ስለዚህ በዋስትና ተሰጥቶ ቢገኝ እንኳ እንዳልተፃፈ ተቆጥሮ ውድቅ መደረግ እንጅ በፍ/ቤት ፊት እንደ ግል ግንኙነት ታይቶ ውጤት ሊሰጠው አይገባም፡፡
ቼክ እንደቀረበ የሚከፈልበት መሆኑ በዋስትና እንዳይሰጥ የመከላከል ውጤት አለው፡፡ ዋስትና ገና ወደፊት ለሚፈፀም ግዴታ የሚሰጥና የዋሱ ግዴታ የሚደርሰው ዋናው ሲያቅተው ወደፊት የሚታይ ሲሆን ቼክ ግን ሲፈረም ግዴታው እንደበሰለ ስለሚቆጠር ሁለቱ ይለያያሉ፡፡ በሌላ በኩል ሌሎች ተላላፊ ንግድ ወረቀቶች በመያዣነት ሊያዙ እንደሚችሉ ሲገለፅ ለቼክ ግን አልተገለፀም፡፡ በንግድ ህግ ቁጥር 764 ላይ የሃዋላ ሰነድ (Bill of exchange) በመያዣ (pledge) ሊያዝ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ለተስፋ ሰነድም ተፈፃሚ እንደሚሆን በቁጥር 825(1)(4) ላይ የተደነገገ ስለሆነ ይህ ሰነድም በመያዛነት ሊሰጥ ይችላል፡፡ አብዛኛዎቹ የሃዋላ ሰነድ ድንጋጌዎች በቼክ ላይ የሚፈፀሙ ለመሆናቸው በንግድ ህግ ቁጥር 886 ላይ ሲነገር ስለመያዣ የሚደነግገው አንቀጽ 754 ግን በቼክ ላይ ተፈፃሚ አልሆነም፡፡ ስለዚህ ህጉ ራሱ ከተላላፊ የንግድ ወረቀቶች መካከል ቼክን በመያዣ ወይም በዋስትና ከሚያዙት ውጭ ያደረገው ስለሆነ ቼክ ለዋስትና ሊሰጥ አይችልም። በዓለም አቀፍ ደረጃም ሃተታ የሌለው እና እንደቀረበ የሚከፈልበት፣ የንግድ ልውውጥን ቀላል የሚያደርግ ሰነድ ነው፡፡ ቼክን በስፋት ከተጠቀምንበት ሽያጭን ግዢን ግዢን በማቀላጠፍ የገበያ ልውውጥ ያሳድጋል፡፡ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ይቀንሳል፡፡ በዚህም ለገንዘብ ኖቶችና ሳንቲሞች የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቼክ ግብይት እንደጥሬ ገንዘብ ለዝርፊያ እና ለስርቆት የተጋለጠ አይደለም፡፡ የቼክ ተጠቃሚውም ሂሳቡን በቀላሉ ለመቆጣጠር ይችላል፡፡ ይህን የመገበያያ መንገድ ግን በቂ የሕግ ጥበቃ ካላደረግንለትና በሕብረተሰቡ ካልታመነበት ዜጎች ቼክን በስፋት ስለማይጠቀሙበት ከላይ የተመለከቱትን ጥቅሞች ማግኘነት አይቻልም፡፡
በአጠቃላይ ቼክ ከባህሪውና ከአላማው አንፃር በዋስትና ሊሰጥ አይችልም፡፡ በህግም የተፈቀደ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቼክ በዋስትና ሊሰጥ ይችላል የሚለው ትርጉም ቼክን ከንግድ ማቀላጠፊያነት ማሰናበት ነው፡፡
ከላይ ከተዘረዘረው የቼክ ባህሪ አንፃር የፌራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በመ.ቁ. 24435 በ4/6/2000 ውሳኔ ትክክል ነው ወይ? እንደምታውስ? የሚለውን ቀጥለን እናያለን፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት በህግ ጉዳዮች ላይ ከ5 ባላነሱ ዳኞቹ የሚጠው ውሳኔ ለተመሳሳይ ጉዳዮች ገዥ (precedent) ነው፡፡ የበታች ፍ/ቤቶች ወይም መሰል አካላት ለተመሳሳይ ጭብጥ በተመሳሳይ መልኩ የመወሰን ግዴታ አለባቸው፡፡ የሰበር ችሎቱ ይህንን ሥልጣኑን በመጠቀም ቼክ በዋስትና ሊሰጥ ይችላል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል፡፡ የድምዳሜው መንደርደሪያም በቼኩ አውጭ እና ተቀባይ መካከል ያለውን የግል ግንኙነት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ በንግድ ህግ ቁጥር 717(1) ላይ የተመለከተው የግል ግንኙነት (Personal relations) ግን ከላይ ከተገለፀው የቼክ ባህሪ አንፃር የዋስትናን ግንኙነት ሊጨምር አይችልም፡፡ ዋስትና የወደፊት ቀጠሮ አለው ቼክ ግን የወደፊት ቀጠሮ የሌለው እንደተፃፈ/ የበሰለ በመሆኑ ከዋስትና ባህሪ ጋር አይጣጣምም፡፡ በሌላ በኩልም አመልካች ቼኩን ሰጠሁ የሚሉት ለክርክሩ 3ኛ ወገን ለሆነው አቶ ሙሳ መሀመድ ከተጠሪ ጋር ላላቸው ግልግል መተማመኛ (ዋስትና) ነው። ከቼክ ባህሪ አንፃር ለዋስትና ሊሰጥ አይችልም እንጅ የግል ግንኙነት ሥር ይወድቃል ተብሎ ቢደመደም እንኳ፣ የግል ግንኙነት እንደ መከላከያ ሊነሳ የሚችለው በከሳሹ እና ተከሳሹ መካከል ያለ ሲሆን ነው፡፡ አመልካች ያቀረቡት ክርክር ግን ከሁለቱ ውጭ ያለ ሦስተኛ ወገን ጋር ያለን የመተማመኛ ግንኙነት የሚጠቅስ ነው፡፡ የሰበር ችሎት ስለ አንቀጽ 717 እና 850 በአግባቡ ካብራራ በኋላ፣ ድምዳሜው ግን ማብራሪያውን የተከተለ አይደለም፡፡ መከላከያ እንዲቀርብ የሚፈቀደው በዕዳ ከፋዩና ሰነዱን በያዘው ሰው የግል ግንኙነት ላይ ብቻ ተወስኖ መሆን ይገባዋል፡፡ የአመልካች መከላከያ ግን ሶስተኛ ወገንን የሚጨምር ስለሆነ፣ ሊፈቀድላቸው አይገባም ነበር፡፡ የሰበር ችሎት የጠቀሰው ሌላው ነጥብ አከራካሪው ጉዳይ ሊተረጎም የሚገባው የንግድ ህግን ዓላማ የሚያሳካ እና ከተለመደው አተረጓጎም አንፃር መሆን እንዳለበት ገልጿል በእርግጥ ህግ ሲተረጎም የህጉን ዓላማ የሚያሳካ መሆን ይገባዋል፡፡ ቼክ እንደቀረበ የሚከፈልበት የንግድ ማቀላጠፊያ መሳሪያ ነው፡፡ አላማው ሊሳካ የሚችለው ቼኩ ውጤታማ ሲሆን ነው፡፡ ቼኩ ውጤታማ ከሆነ የንግድ ህጉ ዓላማ ይሳካል፡፡ የሰበር ችሎቱ የህግ አተረጓጎም ግን የቼክን ጠቀሜታ እና ተዓማኒነት የሚቀንስ ስለሆነ፣ የንግድ ህጉን ዓላማ ሊያሳካ አይችልም። የተለመደው አተረጓጎምም ቼክ እንደቀረበ የሚከፈልበት፣ ለዋስትና ሊሰጥ የማይችል፣ አውጪው ወይም በጀርባ ፈራሚዎች ለአከፋፈሉ ኃላፊነት ያለባቸው ናቸው የሚል እንጅ ቼክ ለዋስትና ሊሰጥ ይችላል የሚል አልነበረም።
የሰበር ችሎቱ የህግ ስህተት ተሰርቷል? አልተሰራም? የሚለውን የመመዘን እና የመተርጎም ሥልጣን አለው፡፡ ህግ ሲተረጎም ፍ/ቤቱ 3 ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ታዋቂው የህግ ምሁር ያስረዳሉ እነዚህም፡-
- የህጉን የተለያዩ ክፍሎች ወጥነት እና ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ (consistency and uniformity) ማየት፣
- ባልተፋለሰና እና ወጥ በሆነ ሁኔታ (Coherence) ማየት፣
- ውጤቱን (Consequence) መተንበይ ናቸው።
የሰበር ችሎቱ ቼክ ለመተማመኛ ሊሰጥ ይችላል በሚል የሰጠው ትርጉም ከላይ የተመለከቱትን መለኪያዎች የተከተለ አይደለም፡፡ የንግድ ህጉን የተለያዩ ክፍሎ ከቼክ ዓላማ እና ባህሪ ጋር በመመዘን ወጥነት ባለው ሁኔታ አልተረጎመውም፡፡ ቼክ ለመተማመኛነት ሊሰጥ ይችላል በሚል ትርጉም ሲሰጥ በኢትዮጵያ ወንጀል መቅጫ ህግ አንቀጽ 693 ላይ የቼክ አውጭ የሚያዝበት በቂ ስንቅ ሳይኖው ቼክ ጽፎ ከሰጠ እና ሳይከፈልበት ከተመለሰ በአታላይነት ይቀጣል በሚል ከተደነገገው ጋር ያለውን ወጥነት (Coherence) ግምት ውስጥ አላስገባውም፡፡ ቼክን ለዋስትና የሰጠ ተከሳሽ ይህንኑ በወንጀል ክስ ክርክር ጊዜ በማንሳት ከወንጀሉ ኃላፊነት መዳን ይችላል ወይ? የሰበር ችሎቱ ትርጉም መከላከያ አይሆነውም ወይ? የሚሉት ከወጥነቱ መርህ ጋር የሚያያዙ ናቸው።
ቼክ እንደቀረበ የሚከፈልበት ሃተታ የሌለበት ገንዘብን ተክቶ የሚሰራ እና ለንግድ ማቀላጠፊያ የሚውል አለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ሰነድ እንደመሆኑ መጠን በዋስትና ሰነድነት መተርጎሙ ዋጋውን የሚቀንስ እና የቼ ተጠቃሚዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው፡፡ ቼክ ዋጋው የማይከፈልበት ወረቀት ሊሆን እንደሚችል የሚረዳ የቼክ ተቀባይ እንዴት ቼክን አምኖ በክፍያነት ሊቀበል ይችላል? ስለዚህ የሰበር ችሎቱ የትርጉሙ ውጤት በሃገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያለውን ተፅዕኖ በቅጡ አላጤነውም፡፡
ችሎቱ ከሰጠው ውሳኔ ውስጥ አብዛኛውን ገጽ የሸፈነው የቼክ ክስ ሲቀርብ የግል ግንኙነትን ማንሳት የሚቻለው በማን እና በማን መካከል ነው በሚለው ላይ ነው፡፡ ዋናው ጭብጥ ቼክ በዋስትናነት ሊሰጥ ይገባል? አይገባም? የሚለው ስለሆነ በዚህ ነጥብ ላይ የሰፋ ትንታኔ ቢሰጥበት የተሻለ ይሆን ነበር፡፡
በዚህ ውሳኔ ላይ የልዩነት ሃሳብም አለ፡፡ የልዩነት ሃሳብ የሰጡት ዳኛ ቼክ በዋስትናነት ሊሰጥ አይገባም የሚለው ድምዳሜአቸው ህጉን የተከተለ እና ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የፍ/ብ/ህ/ቁ. 1920 በመጥቀስ የሙግታቸው መነሻ ማድረጋቸው ግን ትክክል አይደለም፡፡ የፍ/ብ/ሕሕቁ. 1920 የሚደነግገው ስለ ግል ዋስትና (Surety) እንጅ በንብረት (ለምሳሌ በቼክ) ዋስ ስለመሆን አይደለም፡፡ ስለዚህ የህጉ አንቀጽ ከተያዘው ጉዳይ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ ይኹን እንጅ መደምደሚያቸው ትክክለኛ ነው።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት እንደቀረበ የሚከፈልበትን፣ የቼኩ አውጭ ለአከፋፈሉ ግዴታ የሚገባበትን፣ ሃተታ የሌለበትን፣ ንግድን ለማቀላጠፍ በህጉ የተካተተውን ተዘዋዋሪ የንግድ ሰነድ ለመተማመኛ እንጅ ለክፍያ የሰጠሁት አይደለም ለሚሉ ተከሳሽ መከላከያ (defence) ሊሆናቸው ይችላል የሚል የህግ ትርጉም መስጠቱ የንግድ ህግ ቁጥር 827፣ 840 እና 854 የሚጥስ ነው፡፡ እንደ ፀሐፊው አስተያየት ችሎቱ የሰጠው ውሳኔ የህግ ትርጉም ሳይሆን አዲስ ህግ ማውጣት ነው፡፡ የተከበረው ሰበር ችሎት ደግሞ ህግ የመተርጎም እንጅ ህግ የማውጣት ስልጣን የለውም፡፡
ቼክ ለዋስትና ወይም ለመተማመኛ ሊሰጥ ይችላል የሚል መደምደሚያ በሀገራችን የንግድ ህግ፣ በህግ አውጭው እውቅና ያልተሰጠውን የማረጋገጫ ቼክ (Memorandum cheque) በህግ ስርዓቱ ውስጥ መጨመር ነው፡፡ የዚህ ውሳኔ ውጤት መቀጠል ቼክን ከንግድ ማቀላጠፊያ መሳሪያነት የማሰናበትን ያህል ነው፡፡ ስለዚህ ፍ/ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1234/13 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ውሳኔውን ቼክ ለክፍያ እንጅ ለመተማመኛነት ወይም ዋስትናነት አይሰጥም በሚል የህግ ትርጉም ይገባል፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments