በቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት ያለመቅረብ ውጤቶች
ተከራካሪ ወገኖች እራሳቸው ወይም በተወካያቸው አማካይነት ፍርድ ቤት በሚወስነው በማንኛውም ቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከሳሽ አንድ ጊዜ ጉዳዩን ይዞ ከቀረበ በኋላ ተከታትሎ ከዳር ማድረስ መቻል ያለበት ሲሆን ተከሳሽም በእያንዳንዱ ቀጠሮ እየቀረበ የቀረበበትን ክስ በአግባቡ መከላከል መቻል አለበት፡፡ ክስ ያቀረበ ሰው በሁሉም ቀጠሮዎች እንዲገኝ የሚጠበቅበት ቢሆንም በተያዘው ቀጠሮ ባለመገኘቱ ምክንያት ያቀረበውን ክስ መዝጋት ጨምሮ እንደ ቀጠሮው ምክንያት ሌሎች ትእዛዞች ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ክሱ ሊዘጋ የሚችለው ሕጉ ለይቶና ዘርዝሮ ባስቀመጣቸው ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ብቻ ነው፡፡ የፍርድቤት ክርክር በከሳሽ እና ተከሳሽ ይሁንታ ላይ ተመስርቶ በፈለጉ ቀን የሚቀርቡበት ደስ ካላላቸው ደግሞ የማይቀርቡበት ሂደት አይደለም፡፡
አንድን ጉዳይ ለማየት የተሰየመ ፍ/ቤት የተለያዩ ክንዋኔዎችን ለመፈፀም በርካታ ቀጠሮዎች እንደሚሰጥ የታወቀ ነው፡፡ በሙግት ሂደት ፍርድ ቤት የተለያዩ ጉዳዮች መከናወናቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ቀጠሮዎችን ይሰጣል ይላል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 14184፡፡ አንድን ጉዳይ አይቶ ውሣኔ ለመወሰን በርካታ ቀጠሮዎችን ፍርድ ቤት እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህ በርካታ ቀጠሮዎች መካከል በአንዱ ወይም በሌላኛው ወይም በሁለቱም አለመቅረብ ምክንያት ፍርድ ቤት የተለያዩ ትዕዛዞችን እንደሚሰጥ አትቶታል መዝገቡ፡፡ የቀጠሮ አለመከበር ቀጠሮ ከተሰጠበት ምክንያት ተነጥሎ የሚታይ ባለመሆኑ የቀጠሮውን ምክንያት ከግምት በማስገባት የሚሰጠውም ትእዛዝ የተለያየ ነው፡፡
አንድ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ተከራካሪ ወገኖች ክሱ በማንኛውም ደረጃ ላይ ባለበት ጊዜ መቅረብ ባይችሉ ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ድንጋጌዎች እነዚህን ሁኔታዎች በቅጡ ለመገንዘብ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን የከሣሽ ና/ወይም የተከሣሽ አለመቅረብ (non-appearance of parties) አስመልክቶ ያስቀመጠውን ሥርዓት ከአጠቃላይ የሙግት ሂደት ጋር አገናዝቦ መመልከቱ ጠቃሚ ነው ይላል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጉዳዩን በተመለከቱ ፍርዶቹ፡፡
በዚህ ጽሑፍም ፍርድ ቤት ከሚሰጣቸው የተለያዩ ቀጠሮዎች እና ውጤታቸው ጋር በተያያዘ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉን ድንጋጌዎች እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎችን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
ተከሣሹ መልስ ለመቀበል በተያዘ ቀጠሮ ሳይቀርብ ቢቀር ፍርድ ቤቱ ምን ያደርጋል?
የተከሳሽን መልስ ለመቀበል የሚሰጠው ቀጠሮ ፍርድ ቤት የሚሰጠው የመጀመሪያ ቀጠሮ ነው፡፡ በዚህ ቀጠሮ ተከሳሽ መከሰሱን አውቆ ፤ የተከሰሰበትን ምክንያት ተረድቶ መልሱን አዘጋጅቶ እንድቀርብ ፍርድ ቤቱ የከሳሽን የክስ ማመልከቻ ግልባጭ እና የፍርድ ቤቱን መጥሪያ መልሱን የሚያቀርብበት ቀን ወስኖ ይልክለታል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተከሻሽን መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ተከራካሪ ወገኖች ካልቀረቡ ስለሚወሰደው እርምጃ በመዝገብ ቁጥር 14184 እንደሚከተለው ሰፋ ያለ ትንታኔ ሰጥቶታል፡፡
“ጉዳዩ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ከሳሽ (እንደነገሩ ሁኔታ ይግባኝ ባይ) ወይም ተከሣሹ (የይግባኝ መልስ ሰጪ) ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ለሚሰጠው ትእዛዝ መሠረት የሚሆን ሌላ የሕግ ድጋፍ መኖር ይኖርበታል፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ ከ192 እስከ 199 ባሉት ቁጥሮች ፍርድ ቤት እንዲፈፀሙ ያዘዛቹው ጉዳዮች ሳይፈፀሙ ሲቀሩ ስለሚሰጡ ትእዛዞች የተለያዩ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ በቁጥር 199 ሥር ያለው ድንጋጌ አሁን ለያዝነው ጉዳይ በተለይ አግባብነት ያለው ነው፡፡ ቁጥር 199(1) ለቀጠሮው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ሳይፈፀም የቀረው ከተከራካሪዎቹ ወገኖች በአንደኛው ጉድለት የሆነ እንደሆነ መፈፀም ይገባው የነበረው ጉዳይ ያልተፈፀመ ቢሆንም እንኳ ፍርድ ቤቱ የጉዳዩን መፈፀም ሳይጠብቅ በዚያው ቀነ ቀጠሮ የመሰለውን ውሣኔ ለመስጠት ይችላል በማለት ይደነግጋል፡፡ የዚሁ ቁጥር ንዑስ ቁጥር (2) ደግሞ ለቀጠሮው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ሳይፈፀም የቀረው በተከራካሪዎቹ ወገኖች ጉድለት ያልሆነ እንደሆነ ግን ፍርድ ቤቱ ሌላ ቀጠሮ ይሰጣል ፡፡’’
ስለሆነም አንድ ጉዳይ የተከሣሽን መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ከሳሽ ወይም ተከሳሽ ያልቀረቡ እንደሆነ ፍርድ ቤቶች ትእዛዝ መስጠት የሚገባቸው በአንቀፅ 199 መሠረት መሆኑን ፍርድቤቱ ከሰጠው የፍርድ ሀተታ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከድንጋጌው ንዑስ አንቀጽ አንድ ለማየት እንደሚቻለው ለቀጠሮ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ሳይፈፀም በቀረ ቁጥር መዝገብ የሚዘጋበት ሁኔታ እንደሌለ ግልጽ እንደሆነ አሰቀምጦታል፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ትእዛዝ የሚሰጠው አንድ ጉዳይ እንዲፈጽም የታዘዘው ወገን ያን የታዘዘውን ጉዳይ ሳይፈጽም የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ በዚህም መሠረት መልሱን እንዲያቀርብ የታዘዘ ተከሣሽ ይህን ክንውን ሳይፈጽም ቢቀር ፍርድ ቤቱ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የመሰለውን ይወስናል፡፡
ፍርድቤቱ የመሰለውን ውሳኔ ይሰጣል ሲባል ግን መዝገቡን ከመዝጋት ውጭ ያለ ውሳኔ መሆን አለበት፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ አንቀፅ 199ን እንደ መፍትሄ ቢያስቀምጥም የመሰለውን ሰለሚል ብቻ ተለጥጦ መተርጎም የለበትም፡፡ ስለዚህ ፍርድቤቱ ሊሰጥ የሚችለው ትእዛዝ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠት ነው፡፡ በፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 194 እንደተገለፀው በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ መከናወን ያለበት ድርጊት በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ካልተከናወነ ዋጋ እንደሌለው ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መልሱን እንዲያቀርብ የታዘዘ ተከሣሽ መልሱን ከማቅረብ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥቅሞች ይቀሩበታል፡፡ በቀጣዩ ሂደት ከመሳተፍ አይከለክልም፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ለመልስ በተቀጠረ ቀን ተከሣሹ መልሱን ሳያቀርብ ቢቀር የጽሁፍ መልስና የማስረጃ ዝርዝር የማቅረብ እድሉን ከሚያጣ በቀር ከክርክሩ ውጪ እንዲሆን መታዘዝ እንዳልነበረበት ከፍርድ ሀተታው መረዳት ይቻላል፡፡
ከሣሹ መልስ ለመቀበል በተያዘ ቀጠሮ ሳይቀርብ ቢቀር ፍርድ ቤቱ ምን ያደርጋል?
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 14184 በሰጠው ውሳኔ መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ከከሳሽ በኩል የሚጠበቅ ክንዋኔ እንደሌለ ቢያስቀምጥም ተከሳሽ መልሱን ይዞ ካልቀረበ የፍርድቤቱ ጥያቄ የሚሆነው ለተከሳሽ መጥሪያው የደረሰው መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ተከሳሽ ያልቀረበ እንደሆነ ፍርድቤቱ ከሁሉ በፊት መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ተከሳሽ መጥሪያው በትክክል ደርሶታል ወይም አልደረሰውም የሚለው ይሆናል በማለት አስቀምጦታል ፕሮፌሰር አለን ሴድለር የኢትዮጵያ ፍትሀ ብሁር ሥነ ሥርዓት ሕግ ማብራሪያ በሚለው መጽሐፉ፡፡
ስለዚህ በዚህ ቀነቀጠሮ ፍርድቤት ቀርቦ ማከናወን ያለበት ነገር አለ ማለት ነው፡፡ቀርቦ መጥሪያ ያደረሰ መሆኑን ወይም ያላደረሰ ከሆነ ያላደረሰበትን ምክንያት የሚያሥረዳው በዚሁ ቀን ነው፡፡ፍርድቤቱ የላከው መጥሪያ ለተከሳሽ የደረሠ መሆን አለመሆኑን ባላረጋገጠበት ሁኔታ የሚሰጠው ትዕዛዝ ምን መሆን እንዳለበት ግልፅ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው መጥሪያ እንድያድርስ የታዘዘው አካል ከሳሽ በማይሆንበት አጋጣሚ የጠቅላይ ፍርድቤቱ አቋም ሊሰራ ይቸላል፡፡ ችግር የሚፈጠረው መጥሪያ እንድያደርስ በፍርድቤቱ የታዘዘው ከሳሽ ከሆነ እና በቀጠሮው ካልቀረበ ነው ችግር የሚፈጠረው፡፡ ለመልስ መቀበል በተቀጠረበት ቀን ከሳሽ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት ምክንያት የተከሣሽን መልስ ለመቀበል እና መጥሪያ እንድያደርስ ታዞ ከሆነ ያደረሰ መሆኑን የሚረጋገጥ ማስረጃ ሲያቀርብ ለመጠባበቅ ሲሆን ካላደረሰ ደግሞ ያላደረሰበትን ምክንያት እንድያቀርብ ነው፡፡ ተከሳሽ መልሱን ይዞ ቀርቦ ከሳሽ በእለቱ ባይገኝ ፍርድ ቤቱ ለሚሰጠው ትዕዛዝ አይቸገርም፡፡
ተከሳሽ መልሱን በጽሑፍ አዘጋጅቶ እንድቀርብ በታዘዘ ቀን የከሳሽ መቅረብ የሚጠቅመው ራሱን ከሳሹን ነው፡፡ ተከሳሽ ለክሱ የሰጠውን መልስ ቀጥታ ከችሎቱ እንድቀበል ይረዳዋል፡፡
ከሣሹ ለመልስ በተቀጠረበት ቀን ባይቀርብ እና ተከሳሹ መልሱን ይዞ ከቀረበ ቀጣዩን ክንውን አስመልክቶ ትእዛዝ ከመስጠት ውጪ የከሣሹን መዝገብ መዝጋት የሚያስችል አይደለም፡፡ በመሆኑም የተከሣሽን መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሣሹ ያልቀረበ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የተከሣሹን የጽሁፍ መልስ ከማህደሩ ጋር አያይዞ ጉዳዩ የሚሰማበትን ቀነ ቀጠሮ ወስኖ ለዚሁ አስፈላጊ ትእዛዞችን መስጠት አለበት፡፡
መልስ ለመቀበል የሚያዝ ቀጠሮ ተከሣሹ የጽሁፍ መልሱን ለማቅረብ እንዲችል የሚያዝ ቀጠሮ እንጂ ሕጉ እንደሚያዘው ጉዳዩ የሚሰማበት ቀነ ቀጠሮ አይደለም፡፡ በመሆኑም መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሣሹ ሳይቀርብ ቢቀር ጉዳዩ ለማሰማት በተቀጠረበት ቀን ሳይቀርብ ቀረ ተብሎ መዝገቡ ሊዘጋበት የሚችልበት የሕግ መሠረት የለም፡፡ በመሠረቱ መልስ ለመቀበል ቀጠሮ የሚያዘው በአንድ ጉዳይ ክስ የተመሠረተበት ሰው በጉዳዩ ላይ የቀረበበትን ክስ ያምን ወይም ይክድ እንደሆነ ሃሣቡን በጽሁፍ እንዲያቀርብ ማስረጃም ካለው የማሰረጃውን ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ ለማድረግ ነው፡፡ ተከሳሹ በትእዛዙ መሰረት መፈፀም ከቻለ ከሻሹ ለራሱ ጥቅም ሲል የተኩሳሹን የጽሑፍ መልስ ከሬጅስትራር ከመቀበል ቀጥታ ከችሎት ከመቀበል በስተቀር ከከሣሹ የሚጠበቅ ክንዋኔ የለም፡፡ ከሣሹ ሳይቀርብ ቀረ እንኳን ቢባል በፍርድ ቤቱ የሥራ ሂደት ላይ የሚያስከትለው መስተጓጐል ሊኖር አይችልም፡፡ በመሆኑም መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ከሣሹ ባይቀርብ የተከሣሹን መልስ ተቀብሎ ለተከታዩ ክንውን ጉዳዩን ከማዘጋጀት አልፎ መዝገቡን ለመዝጋት በቂ ምክንያት የለም፡፡
ከሳሽ እና ተከሳሽ መልስ ለመቀበል በተያዘ ቀጠሮ ሳይቀርቡ ቢቀሩ ፍርድ ቤቱ ምን ያደርጋል?
መልስ ለማቅረብ በተቀጠረበት ቀን ሁሉም ተከራካሪ ወገኖች ሳይቀርቡ የቀሩ እንደሆነ ፍርድቤት ሊሰጥ የሚችለው ወይም ሊሰጥ የሚገባው ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ሕጉ ላይ በግልፅ አልተቀመጠም፡፡በዚህ ቀጠሮ ከሳሽ ወይም መጥሪያ እንድያደርስ የታዘዘ አካል ቀርቦ መጥሪያው ለተከሳሹ የደረሰው መሆኑን ማረጋገጥ ሲኖርበት ተከሳሹ ደግሞ መልሱን በጽሑፍ አዘጋጅቶ ይዞ መቅረብ መቻል አለበት፡፡ በዚህ የቀጠሮ ቀን እነኝህ ነገሮች መፈፀም ሲገባቸው ተከራካሪ ወገኖች ባለመቅረባቸው ካለተፈፀሙ ፍርድቤቱ የቀጣይ ስራውን ለማከናወን በዚህ ቀን የሚሰጠው ትእዛዝ ይቸገራል፡፡ከሳሽ ባለመቅረቡ መዝገብ መዘጋት የሌለበት መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት በሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔወቹ በተደጋጋሚ ተገልጧል፡፡ ስለሆነም ከሳሽ ባለመቅረቡ እሱን ሊጎዳ የሚችል ውሳኔ መስጠት አይቻልም፡፡ተከሳሽ መጥሪያ ደርሶት መልሱን ይዞ አለመቅረብ ይችላል፡፡ አሁን ባለው የፍርድቤቶች የተግባር ስራ አንፃር መጥሪያ እንድያደርስ የሚታዘዘው ከሳሽ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዚህ ቀጠሮ የከሳሽ መቅረብ ለፍርድቤቱ ቀጣይ ስራ አስፈላጊ ቢሆንም ባለመቅረቡ ግን የሚያጣው መብት የለም፡፡
ከላይ ተከሳሽ ብቻውን መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን ካልቀረበ ሰበር ሰሚ ችሎቱ መፍትሄ ነው ብሎ ያስቀመጠው አንቀፅ 199 ለዚህ ጉዳይም ማለትም ከሳሽ እና ተከሳሽም ሳይቀርቡ ሲቀሩ መጠቀም ያለብን አግባብነት ያለው ድንጋጌ ይመስለኛል፡፡ በዚህ አንቀፅ መሰረት ፍርድቤቱ መልስ ለመቀበል ቀጠሮ በያዘበት ቀን ከሳሽ ወይም መጥሪያ እንድያደርስ የታዘዘ አካል ቀርቦ መጥሪያው ለተከሳሹ የደረሰው መሆኑን ኩላስረዳ እና ተከሳሹም መልሱን ይዞ ካልቀረበ ከተከሳሹ በኩል ጉድለት አለ ማለት አይቻልም፡፡ ተከሳሹ መጥሪያው እንደደረሳው ፍርድቤቱ ካላረጋገጠ እንዳልደረሰው መገመት የተሻለ ነው፡፡ ስለሆነም መልስ ለመቀበል በተቀጠረ ቀን ከሳሹን የሚጎዳ ትእዛዝ መሰጠት እንደሌለበት ሰበር ሰሚ ችሎቱ ያሳወቀ በመሆኑ እና መጥሪያው ለተከሳሽ እንደደረሰው ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ተከሳሹን የሚጎዳ ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ስለማይሰጥ ፍርድ ቤቱ ሊሰጥ በሚችለው ትአዛዝ ላይ ይቸገራል፡፡ስለዚህ ፍርደቤቱ መዝገቡን ከመዝጋት ውጭ የሆነ የመሰለውን ውሳኔ የመስጠት ነፃነት ያለው በመሆኑ መጁመሪየ ሊያደርግ የሚገባው የከሳሽ የክስ ማመልከቻ ግልባጭ እና የፍርድቤቱ መጥሪያ ለተከሳሹ መድረስ አለመድረሱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይሄ ደግሞ ከሳሹ ወይም መጥሪያ እንድያደርስ ታዞ የነበረው አካል ማድረሱን ወይም አለማድረሱን እንድያረጋግጥ መጥሪያ በመላክ ወይም በሌላ ማንኛውም ዘዴ ማረጋገጥ አለበት፡፡ተከሳሹ የደረሰው መሆኑን ካረጋገጠ የመጀመሪያ ክስ ለመስማት ቀጠሮ መስጠት የሚችል ሲሆን ተከሳሹ ካልደረሰው ደግሞ ድጋሚ መጥሪያ ለተከሳሹ መላክ ይኖርበታል፡፡
ፍርድቤቶች በተግባር እየሰሩበት ያለው አግባብ ግን መዝገቡን የመጀመሪያ ክስ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠት ነው፡፡ ይህ አሰራር ደግሞ ተከሳሹ መጥሪያው እንደደረሰው ግምት በመውሰድ የሚሰጥ ትእዛዝ ነው፡፡ ተከሳሹንም በእጅጉ የሚገዳ ነው፡፡ ምክንያቱም መከሰሱን ያላወቀ ተከሳሽ ክስ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ካልቀረበ አልቀረበም ተብሎ ጉዳዩ በሌለበት (exparte proceeding) ስለሚቀጥል ነው፡፡ ተከሳሹ በአግባቡ መከላከል እየቻለ መከሰሱን ባለማወቁ ትልቅ መብት እና ጥቅም ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም ፍርድቤቶች እንደዚህ አይነት ተከሳሹን ሊጎዳ የሚችል ትእዛዝ፤ ብይን ወይም ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት የከሳሽ የክስ ማመልከቻ ለተከሳሽ የደረሰው መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
ፍርድቤት ክርክሩ እንድሰማ በወሰነው ቀነ ቀጠሮ ተከራካሪ ወገኖች አለመቅረብ
ክስ ለመስማት ፍርድቤት የሚሰጠው ቀጠሮ ሁለተኛ ቀጠሮ ነው፡፡ ክስ መስማት በውስጡ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ሂደት ነው፡፡ ከስነ ስርዐት ሕጉም አደረጃጀት አንፃር ሲታይ ክስ ስለመስማት በአንድ ምዕራፍ ስር ተቀርፆ ሁለት ክፍሎችን ይዟል፡፡ የመጀመሪያው ክፍል የሚያወራው ስለ መጀመሪያ ክስ መስማት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ስለዋናው ክስ መስማት የተለያዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ክፍል ነው፡፡
መጀመሪያ ክርክር ሲከፈት የሚደረገው የመጀመሪያው ክስ መስማት ወደ ዋናው የክስ መስማት ሂደት መግባት አስፈላጊ መሆን አለመሆኑ የሚለይበት ደረጃ ነው፡፡በዚህ ስርዓት ወደ ዋናው ክስ መስማት ገብቶ ማከራከሩ (ክሱን በማስረጃ ማጣራቱ) አስፈላጊ ሆኖ ካላገኘው ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ ይሰጣል፡፡ የክሱ መሰማት መቀጠል አለበት ብሎ ካመነ ፍርድቤቱ ተከራካሪወችን በቃል ጥያቄ በመመርመር ጉዳዩን በሚገባ የሚረዳበት እና አስፈላጊውን ጭብጥ በመያዝ ማስረጃ ማቅረብ ያለበት ተከራካሪ ወገን የሚለይበት እና ምን አይነት ማስረጃም መቅረብ እንዳለበት የሚለይበት ደረጃ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ፍርድ ቤቱ ባለጉዳዮቹን ወይም ወኪሎቻቸውን ይመረምራል(አንቀፅ 241)፡፡ ምርመራው የሚደረገው ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ ያምን ወይም ይክድ እንደሆነ ነው፡፡ ካመነ ወደ ዋናው ክስ መግባት ሳያሰፈልግ ፍርድ ቤቱ ወድያውኑ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ካለመነ ደግሞ የክርክሩን ጭብጥ ይይዛል(አንቀፅ 247)፡፡ ስለ ክርክሩ መነሻ እና ከክርክሩ ጋር አግባብነት ያላቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በመሰለው ዘዴ የቃል ጥያቄ በማቅረብ ተከራካሪ ወገኖችን ይመረምራል፡፡ በዚህ ደረጃ ምርመራውን የሚያከናውነው ፍርድ ቤቱ ነው፡፡ ባለጉዳዮች ሙግት አይጀምሩም፡፡ክሱ በሚከፈትበት ጊዜ ተከራካሪ ወገኖች እንድብራራላቸው የሚፈልጉት ጉዳይ ካለ ፍርድቤቱ እንድጠይቅላቸው ለማመልከት ይችላሉ፡፡
አንቀፅ 241 የመጀመሪያ ክስ መስማት እለት የሚከናወኑ ድርጊቶችን ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም መሰረት የጽሑፍ ክስ እና መልስን በንባብ ማሰመት፤ ተከራካሪ ወገኖች ላይ ምርመራ ማድረግ፤ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን መስጠት እና ለክሱ አወሳሰን የሚረዱ ጭብጦችን መያዝ ነው በማለት ዘርዝሮ አስቀምጧል፡፡በዚህም መሰረት ክሱ መሰማት በሚጀምርበት ቀን ፍርድ ቤቱ የባለጉዳዮቹን ማንነት ካረጋገጠ በኋላ ክሱን ና መልሱን እንደሚያነብ ና ተከሣሹ መልሱ ላይ የካደውን ነገር ያምን ወይም ይክድ እንደሆነ በቃል እንደሚጠይቀው ይገልጻል፡፡የዚሁ ንዑስ ቁጥር 2 ደግሞ ወይም ስለሱ ሆኖ የቀረበውን ሰው ለክርክሩ መነሻ የሆኑት ጉዳዮች ወይም ሌሎች ነገሮች አብራርቶ ለማስረዳት ጠቃሚ ና ተገቢ መስሎ በገመተው ዘዴ የቃል ጥያቄ በማቅረብ ፍርድ ቤቱ ሊመረምራቸው እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ከሣሽ ወይም ተከሣሹ እንዲብራራለት የሚፈልገው ጉዳይ ካለ በፍርድ ቤቱ በኩል እንዲጠየቅለት ማድረግ እንደሚችልም በዚሁ ድንጋጌ ላይ በግልጽ ሰፍሯል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም በጉዳዩ ላይ በመዝገብ ቁጥር 14184 እንደሚከተለው አትቷል፡፡ ’’................የመሰማት ሂደት የከሣሽ ና የተከሣሽ መገኘት የግድ የሚል ተሟጋቾቹም ጭምር የሚሣተፉበት ሂደት መሆኑን ነው፡፡ ይህ ሂደት ፍርድቤቱ ባለጉዳዩችንም ጭምር በማነጋገር ጉዳዩን ለዋናው የሙግት ደረጃ የሚያዘጋጅበት በመሆኑ በከሣሹ ና የተከሣሹ (ወይም የወኪሎቻቸው) መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከሁለቱ የአንዱ አለመገኘት ለሂደቱ መስተጓጐል የሚኖረው ተጽእኖም ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ከሌሎች ቀጠሮዎች ይበልጥ ባለጉዳዩች ጉዳዩ እንዲሰማ ቀጠሮ በተያዘበት እለት ባይቀርቡ የሚከተለው ውጤት ከሌላው የበለጠ ጠንካራ መሆኑ አስፈለጊ ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ምእራፍ 2 (ከቁጥር 241 - 273) ያሉት ሁሉም ድንጋጌዎች የተሟጋቾች አለመገኘት የሚያስከትለውን ውጤት ከመሰማት ሂደት ጋር አያይዘው የሚያቀርቡትም በከፊል በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ’’
ከሕጉ አደረጃጀት ባሻገር የክስ መስማትን የሚመለከተው የሙግት ሂደት በሁለት የተከፈለ ሲሆን ሁለቱም የከሣሽ ና የተከሣሽን መገኘት የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያ ክስ የከሣሽ ና የተከሣሽን መገኘት የሚጠይቅ ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያ ክስ ሲከፈት የሚፈፀመውን ሥነ ሥርዓት (First hearing) ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡ የክሱ መስማት መጀመር ለዋናው የክስ መስመት የሚረዱ ጉዳዮች የሚዘጋጀበት የመጨረሻ ደረጃ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ለመስማት ቀጠሮ የተያዘበት ቀን ከሌሎች ቀጠሮዎች በተለየ ሁኔታ እንዲታይ ሕግ አውጪው መፈለጉ ግልጽ ነው፡፡
ዋናው የክስ መስማት ሂደት ክርክሩን መስማት እና ማስረጃ የሚመረመርበት ሂደት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ተከራካሪዎች ሙግታቸውን ያሰማሉ፤ ምስክሮቻቸውን አቅርበው ያሰማሉ፤ በቀረበው ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ፍርድ ቤቱ ፍርድ ይሠጣል፡፡
ጉዳዩን ለመስማት በተቀጠረበት ቀን የተከራካሪ ወገኖች አለመቅረብ ውጤቶች የሥነ ሥርዓት ህጋችን በዝርዝር እና ግልፅ በሆነ መልኩ አስቀምጦታል፡፡ ይህንን ቀጠሮ በተመለከተ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው በአንቀፅ 69፤ 70 እና 73 የተቀመጡት ህጋዊ ውጤቶች ተግባራዊ የሚደረጉት የመጀመሪያው ክስ መስማት በተቀጠረበት ቀን ተከራካሪ ወገኖች ካልቀረቡ ብቻ ነው ወይስ ዋናውን የክስ መስማት ሂደት ማለትም ፍርድቤቱ ፍርድ እስከሚሰጥ ባለው ሂደት ውስጥ ባለጉዳዮች ካልቀረቡ ተመሳሳይ ነው ወይ ውጤቱ የሚል ነው፡፡ አንቀፅ 69 ’’ ነገሩን ለማየት’’ ፍርድቤቱ በወሰነው ቀጠሮ ተከራካሪ ወገኖች ካልቀረቡ ፍርድቤቱ መዝገቡን መዝጋት እንዳለበት የደነገገ ሲሆን አንቀጽ 70 ደግሞ ’’ክርክሩ እንድሰማ ’’ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ከሳሽ ቀርቦ ተከሳሽ ያልቀረበ እንደሆነ ጉዳዩን በሌለበት ከማየት ጀምሮ ዝርዘር ህጋዊ ውጤቶችን አሰቀምጧል፡፡ አንቀጽ 73 በተመሳሳይ ’’ ክርክሩ እንድሰማ ’’ ፍርድቤቱ በያዘው ቀጠሮ ከሳሽ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ተከሳሹ ቀርቦ አንደኛ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል ያመነ እንደሆነ ከሳሹ በሌለበትም ቢሆን ባመነው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን ተከሳሹ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ የካደ እንደሆነ ግን መዝገቡን በመዝጋት ያሰናብተዋል በማለት ነው ያስቀመጠው፡፡
በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 69፣70፣73 እና ሌሎች ተዛማጅ ድንጋጌዎች ከተከራካሪዎች አንዱ ወይም ሁለቱም ጉዳዩን ለመስማት (hearing) በተቀጠረበት ቀን ያልቀረቡ እንደሆነ ብቻ ተፈጻሚ ስለሚሆኑ ከዚያ በኋላ ባሉት የቀጠሮ ቀኖች ከሳሽ (እንደ ነገሩ ሁኔታ ይግባኝ ባይ) ወይም ተከሣሹ (የይግባኝ መልስ ሰጪ) ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ለሚሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የሚሆነው ተከሳሽ መልስ ለመቀበል ለተያዘው ቀጠሮ መሰረት የሆኑት የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ከ192 እስከ 199 ባሉት ቁጥሮች የተቀመጡት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
ስለሆነም አንቀፅ 69፤ 70 እና 73ን በመጠቀም መዝገብ ሊዘጋ የሚቸለው የመጀመሪያው ክስ መስማት ቀጠሮ ቀን ተከራካሪ ወገኖች ካልቀረቡ ነው፡፡ ከዚያች ቀጠሮ ቀን በኋላም ሆነ በፊት ባሉት ቀጠሮዎች ተከራካሪ ወገኖች ካልቀረቡ ፍርድ ቤቶች ትእዛዝ ወይም ውሳኔ ሊሰጡ የሚችሉት አንቀፅ 199ን በመጠቀም ነው፡፡ በዚህም መሰረት ለቀጠሮው ምክንያት የሆነው ጉዳይ ያልተፈፀመበትን ምክንያት በመመርመር ፍርድ ቤቱ የተለያዩ ትዕዛዞችን ይሰጣል ማለት ነው፡፡
አንቀፅ 233 vis-a- vis አንቀፅ 70( ሀ)
በዚህ ጽሑፍ ከተያዘው ጉዳይ ጋር ተያይዞ በባለሙያዎች ዘንድ የክርክር ምንጭ ከሆኑት የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች መካከል አንቀፅ 233 እና 70(ሀ) ይገኙበታል፡፡የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በድንጋጌዎቹ ዙሪያ በመዝገብ ቁጥር 15835 በተዋረድ ላሉ ፍርድቤቶችም ሆነ ለሌሎች በሕግ ሙያ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ይረዳ ዘንድ ሰፋ ያለ ትንታኔ ሰጥቶታል፡፡የተከሳሽን መልስ ለመቀበል በተቀጠረበት ቀን መልሱን ይዞ ካልቀረበ በአንቀፅ 233 መሰረት ጉዳዩ በሌለበት መሰማት እንዳለበት የተቀመጠ በመሆኑ ሌላ ትእዛዝ መሰጠት እንደሌለበት አቋም ያላቸው ፍርድ ቤቶች እና ባለሙያዎች ስላሉ የሕጉን መንፈስ እና የሠበር ሠሚ ችሎቱን ትርጉም በዚህ ርእስ ስር ለማየት ተሞክሯል፡፡
የፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 233 አንድ ተከሣሽ ጉዳዩ ለመልስ በተቀጠረበት እለት መልሱን ይዞ ካልቀረበ ክርክሩ በሌለበት የሚሰማ መሆኑን ፍርድቤቱ በሚልክለት መጥሪያ ላይ እንደሚገልጽለት ደንግጓል፡፡ መልሱን ሳያቀርብ የቀረ ተከሣሽ በ233 መሠረት በሌለበት ጉዳዩ እንደሚሰማ አስቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል የፍ.ሥ.ሥ.ሕ.ቁ 70 (ሀ) ክርክሩ እንዲሰማ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ከሣሽ ቀርቦ ተከሣሽ ያልቀረበ እንደሆነ ተከሣሹ ያልቀረበው የተላከለት መጥሪያ ደርሶት ከሆነ ተከሣሹ በሌለበት የነገሩ መሰማት እንደሚቀጥል ይደነግጋል፡፡ ሁለቱም ድንጋጌዎች የሚያወሩት ስለ ክስ መስማት ነው፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ ደግሞ በአንድ ሕግ ውስጥ የተለያዩ አንቀፆችን መጠቀም የሕግ አረቃቅ መርህም አይፈቅድም፡፡ ስለሆነም ለእነዚህ ሁለት አንቀጾች የተለያየ ትርጉም መሰጠት አለበት፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 15835 በሰጠው ውሳኔ የሁለቱም ድንጋጌዎች የአማርኛ ቅጂ የሚያስከትሉት ውጤት ተመሳሳይ እንደሚመስል አስፍሯል፡፡ የፍርድቤቱን የፍርድ ሐተታ ቃል በቃል ለማስቀመጥ ያህል ’’እነዚህ ሁለት ድንጋጌዎች ሁለት በተለያዩ ጊዜ የሚከናወኑ የሙግት ደረጃዎችን የሚመለከቱ ቢሆኑም የተከሣሽን መቅረት አስመልከቶ የሚያስከትሉት ውጤት ተመሳሳይ ይመስላል፡፡የጽሁፍ መልሱን ሳያቀርብ የቀረ ተከሣሽ በ233 መሠረት በሌለበት ጉዳዩ እንደሚሰማ ጉዳዩ ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ያልቀረበ ተከሣሽም በተመሳሳይ ሁኔታ ጉዳዩ በሌለበት እንደሚሰማ በቁጥር 70(ሀ) መሠረት ትእዛዝ የሚሰጥበት ይመስላል፡፡ የሁለቱም ድንጋጌዎች የአማርኛ ቅጂ ለመልስ በተቀጠረበት ቀን መቅረት ና ጉዳዩ እንዲሰማ በተቀጠረበት ቀን መቅረት አንድ አይነት ውጤት ያላቸው እንደሆነ የሚገልጹ ቢሆኑም የሁለቱም የእንግሊዝኛ ቅጂዎች ግን የተለየ ጽንሰ ሃሳብ የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ የ70(ሀ) የእንግሊዝኛ ድንጋጌ ስለ Ex-parte ሲናገር የ233 ግን የሚደነግገው ስለ default proceeding ነው፡፡ሁለቱም የተለያየ ይዘት የተለያየ ውጤት ያላቸው ናቸው፡፡’’ በማለት አስቀምጧል፡፡
የ70(ሀ) የእንግሊዝኛ ቅጂ
where the plaintiff appears and defendant does not appear when the suit is called on for hearing (a) if it is proved that the summons was duly served, the suit shall be heard ex-parte
በማለት ሲደነግግ አግባብነት ያለው የ233 ክፍል ደግሞ
…. The court shall cause… requiring him to appear with his statement of defense to be fixed in the summons and informing him that the case wile be proceeded withnotwithstanding that he does not appear or that he appears without his statement of defense. በማለት ይደገግጋል፡፡
ከድንጋጌዎቹ የእንግሊዝኛ ቅጅ በመነሳት ፍርድ ቤቱ አንቀፅ 233ን እንደሚከተለው ተርጉሞታል፡፡ ’’የ233 ድንጋጌ መልሱን ባያቀርብም የጉዳዩ መሰማት እንደሚቀጥል (default proceeding) ከሚያሳይ በቀር ተከሣሽ ከክርክር እንዲወጣ የሚያደርግበት ሥርዓት አለመኖሩን ያሳያል፡፡’’ አንቀፅ 233 የሚነግረን የፍርድ ቤቱ መጥሪያ ፍርድ ቤቱ በሰጠው የቀጠሮ ቀን ከጽሑፍ መልሱ ጋር እንድቀርብ የሚገልፅ መልዕክት ሊኖረው እንደሚገባ ነው፡፡ ስለሆነም የአንቀፅ 233 (default proceeding) መሟላት ተከሳሽን ከክርክር እንድወጣ ለማድረግ መንደርደሪያ ነው እንጅ በራሱ ከክርክር ሊያስወጣው አይችልም፡፡ ስለሆነም አንቀፅ 233 ለተከሳሹ ግንዘቤ ከመፍጠር ባለፈ ከክርክሩ ሊያስወጣ አይችልም፡፡ ተከሳሹ መልሱን ይዞ ካልቀረበ እና በቀጣይ በሚሰጠው ክስ ለመስማት ቀጠሮ ላይ ካልቀረበ ብቻ ነው ከክርክሩ የሚወጣው፡፡መልሱን ይዞ እንድቀርብ በታዘዘበት ቀን ተከሳሹ ሳይቀርብ ቢቀር ከክርክሩ ሊወጣ አይገባም፡፡
ከላይ የተጠቀሰው መዝገብ ሲያጠቃልልም ከሕጉ ቁጥሮች 69፣70፣73 ለመገንዘብ እንደሚቻለው ሕጉ በተከራካሪ ወገኖች አለመቅረብ ምክንያት አንድ መዝገብ እንዲዘጋ ወይም ተከሣሹ በሌለበት የነገሩ መሰማት እንዲቀጥል ትእዛዝ የሚሰጠው ከሣሽ ወይም ተከሣሹ ወይም ሁለቱም ጉዳዩ እንዲሰማ በተቀጠረው ቀን ሳይቀርቡ የቀሩ እንደሆነ ነው በማለት ነው፡፡
ስለዚህ አንቀፅ 233 ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት በፍትሐብሔር ጉዳይ የተከሳሹ መልስ ይዞ መቅረብ እና መከራከር ጉዳዩን ለመቀጠል የግድ እንዳለሆነ ነው፡፡ ተከሳሹ መከሰሱን እያወቀ መልሱን ይዞ ካልቀረበ እና ካልተከራከረ በአንቀፅ 70(ሀ) መሰረት ተከሳሹን ከክርክሩ ውጭ በማድረግ የሚቀጥል መሆኑን ለማስገንዘብ የተቀመጠ ድንጋጌ ነው፡፡
ብዙ ተከራካሪ ወገኖች ያለመቅረብ
ከሳሾች ከአንድ በላይ መሆናቸው ፍርድ ቤት አለመቅረብ ጋር በተያያዘ የተለየ ውጤት የለውም፡፡ ፍርድ ቤት ያለመቅረቡ ችግር በክሱ ላይ በዛ ያሉ ወገኖች በሚኖሩበት ጊዜም ቢሆን የሚነሳ ጉዳይ እንደሆነ ፕሮፌሰር አለን ሴድለር የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ማብራሪያ በሚለው መፅሀፉ አስቀምጦታል፡፡
የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 75 እንደደነገገው ከብዙ ከሳሾች መካከል አንዱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ከሳሾች ሳይቀርቡ የቀሩ እንደሆነ እና የቀረቡት ከሳሾች ክርክሩ እንድቀጥል የፈለጉ እንደሆነ ፍርድቤቱ ሁለት ምርጫ ይኖረዋል፡፡አንደኛው ሁሉም ከሳሾች እንደቀረቡ በመቁጠር ክርክሩ እንድሰማ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ የተለየ ትእዛዝ መስጠት ነው፡፡
ፕሮፌሰር አለን ሴድለር የኢትዮጵያ ፍትሀ ብሁር ሥነ ሥርዓት ሕግ ማብራሪያ የሚለውን መፅሀፉ ሳሙኤል ጣሰው እንደተረጎመው እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡’’የተከራካሪዎች አለመቅረብ ፍርድ ቤቱ መብታቸውን አስመልክቶ ለመወሰን የሚኖረውን ስልጣን የሚያሳጣ አይደለም፡፡ ሆኖም በክርክሩ ውስጥ የግደታ ተካፋይ ወገኖች ሆነው መቅረብ ያለባቸው ሳይቀርቡ የክሱ መሰማት ስርዓት ሊቀጥል የማይችል በሆነ ጊዜ እነርሱን በተመለከተ የቀረበውን ክስ መዝጋት ወይም ማቋርጥ የሚቻል ቢሆንም ከቀረቡት ከሳሾች መብት አኳያ ተገቢ ባለመሆኑ ክርክሩ እንድቀጥል መደረጉ ትክክል ይሆናል፡፡ነገር ግን ከሳሦች ያቀረቡት ክስ ያልተገናኘ እና ራሱን የቻለ የሆነ እንደሆነ ያልቀረቡት ከሳሾች ክስ የቀረቡትን ከሳሾች ክስ እስካልነካ ድረስ መዝጋቱ ወይም እንደቋረጥ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡’’
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 55078 በሰጠው ውሳኔ በስር ፍርድ ቤት የክስ ማመልከቻ ሲያቀርቡ ዘጠኝ የነበሩ ከሳሾች ክርክሩ ሊሰማ ቀነቀጠሮ በተያዘበት እለት የቀረቡት ግን ሶስት ከሳሾች በመሆናቸው ምክንያት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤቱም ከተከሳሽ በኩል በቀረበለት ክርክር መሰረት የቀሩትን ከሳሾች ከክሱ ውጭ እንድሆኑ አድርጎ ሲያበቃ በሚቀጥለው ቀነ ቀጠሮ በመቅረባቸው ምክንያት ትእዛዙን በማንሳት በክርክሩ ውስጥ እንዳሉ በመቁጠር ውሳኔ ሰጥቷል፡፡እዚህ ላይ ትከረት የሚሻው ጉዳይ ፍርድቤቱ ትእዛዙን ሲያነሳ በአንቀፅ 74 መሰረት ያልቀረቡት ከሳሾች ማመልከቻ አቅርበው ያልቀረቡበት ምክንያት ተመዝኖ ሳይሆን ችሎት በሚቀጥለው ቀጠሮ በመገኘታቸው ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ሰበር ሰሚው በሰጠው ውሳኔ ተከሳሽ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድቤቱ የሰጠው ውሳኔ ክስ ሊሰማ በተቀጠረው ቀን ያልቀረቡትን በሚመለከት እንድፈፅም እንደማይገደድ አስቀምጧል፡፡ከዚህ መረዳት የምንችለው ከብዙ ከሳሾች ውስጥ ክርክሩ ሊሰማ በተቀጠረበት ቀን ካልቀረቡ ክርክሩ በቀረቡት ከሳሾች ይቀጥል እና የውሳኔው ባለመብት መሆን የሚችሉት ግን ቀርበው የነበሩት ከሳሾች ብቻ እና የፍርድ ባለእዳውም ላልቀረቡት ከሳሾች መፈፀም እንደማይገደድ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ፍርድቤት የተለያዩ ክንውኖችን ለመፈፀም ወይም ተፈፅመው ሲቀርቡ ለመጠባበቅ የተለያዩ ቀጠሮዎችን ይሰጣል፡፡ በቀጠሮው ምክንያት ላይ ተመርኩዞ አለመፈፀማቸው የሚያስከትሉት ህጋዊ ውጤትም የተለያዬ ነው፡፡
ስለሆነም የቀጠሮዎቹን ምክንያት ምክንያት መሰረት በማድረግ የፍትኀ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን የተለያዩ ውጤቶችን ያስቀመጠ ሲሆን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ ያሉትን ድንጋጌዎች ክፍተት በመሙላት እና ግልፅነት የጎደላቸውን ድንጋጌዎች ሰፊ ትርጉም በመስጠት ችግሩን ያቃለለው ቢሆንም የፍርድቤቶች አሰራር አሁንም ወጥ መሆን አልቻለም፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments