Font size: +
15 minutes reading time (3070 words)

በኢትዮጵያ ሰው በፍርድ ቤት እና ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ስለሚያዝባቸው ሁኔታዎች

በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርአት ውስጥ የወንጀል ምርመራ አላማ ስለ ወንጀል የማወቅ፣ ወንጀል እንዳይፈፀም የማስቆም፣ ወንጀሉ ከተፈፀመ ጉዳቶችን የመቀነስ፣ የወንጀል ኢላማ የሆኑትን ሰዎች፣ ንብረቶች ወይም ጥቅሞችን የመከላከል፣ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ የማቅረብ ወይም የወንጀል ተጎጂዎችን መብቶችና ጥቅሞችን ማስከበር እንደሆነ የኢትዮጵያ ወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ይገልፃል፡፡

ጠበብ አድርገን ስናየው ደግሞ የወንጀል ምርመራ (Investigation) ማለት የአንድን ወንጀል መፈፀም ወይም አለመፈፀም እንዲሁም ማን እንደፈፀመው ለማረጋገጥ የሚረዳ ማስረጃን የማሰባሰብ ሂደት ነው፡፡ ፖሊስም ይህን ተግባር ሲያከናውን  ሕገ መንግስቱ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርአት ህጉና ሌሎች ህጎች ባስቀመጡት ድንጋጌዎች መሠረት ማከናወን የሚገባው ሲሆን፣ በዚህ ሂደት የሚኖር የመብት ጥሰት ካለም ተጠያቂነትን ያመጣል፡፡  ወንጀል ከተሰራ በኋላ ፖሊስ በሁለት መንገድ ምርመራ ሊጀምር ይችላል አንደኛው ግለሰቦች ወንጀል ተፈፀመብኝ ብለው በሚያቀርቡት አቤቱታ መሠረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የወንጀሉ ድርጊት ከፈተፈፀመ በኋላ ወንጀሉ ሲፈፀም ያዩ ወይም የሰሙ ግለሰቦች በሚያደርሱት ጥቆማ መሠረት ነው፡፡

ፖሊስ ከላይ በገለፅነው መልኩ መረጃ ደርሶት ምርመራ ሲያከናውን የምርመራው አካል የሆነው አንዱና በጥንቃቄም መከናወን ያለበት ተግባር ተጠርጣሪውን መያዝ ነው፡፡ ምክንያቱም የወንጀል ድርጊት እስከተፈፀመ ድረስ የህብረተሰቡን ህይወት፣ ንብረትና ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ወንጀል ፈፃሚዎችንና የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ፖሊስ እስርን ተግባራዊ ለማድረግ በሁለት መንገድ ማለትም በፍርድ ቤት ትእዛዝና ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ናቸው፡፡ በመርህ ደረጃ ያለመያዝ ወይም ያለመታሰር መብት ሕገ መንግስታዊ ከለላ ያገኘ መብት በመሆኑ ከመያዝ ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ተግባራት በጥንቃቄ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

በዚች አነስተኛ ጽሑፍ መያዝ (arrest) ምንነትና ጥቅሙ፣ መያዝ በሀገራችን እንዴት እንደሚተገበርና በሀገራችን ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማየት ጥረት የሚደረግ ሲሆን እንዲሁም በቀጣይ መያዝን አስመልከቶ ቢስተካከሉ ወይም በሕግ ደረጃ የሕግ ሽፋን ቢሰጣቸው የምላቸውን ሀሳቦች በአስተያየት መልኩ አቀርባለሁ፡፡

ስለመያዝ (arrest) ምንነት

ስለ መያዝ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርአት ሕግ ላይ ትርጉም ያልተሰጠው ሲሆን፣ በሌሎች የተለያዩ ሰነዶች ላይ የተሰጠውን ትርጉም ስንመለከት፣ ብላክ ሎው ዲክሽነሪ arrest የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ” it is a seizure or forcible restraint, the taking or keeping of a person in custody by legal authority especially in response to criminal charges”.  መያዝ ወይም በሀይል ይዞ ማቆየት ማለት አንድን ሰው በተለይ ለወንጀል ክስ መልስ እንዲሰጥ በህጋዊ ባለስልጣን ወደ ማቆያ መውሰድ ወይም መጠበቅ ማለት ነው በማለት ተርጉሞታል፡፡

በሌላ በኩል ዘ ፈሪ ኢንሳይክሎፒዲያ “An arrest is the act of depriving a person of his or her liberty usually in relation to the purported investigation or prevention of crime and presenting (the arrestee) to a procedure as part of the criminal justice system”. መያዝ ማለት ወንጀልን ለመከላከል ወይም ከምርመራ ስራ ጋር በተያያዘ የሰዎችን ነፃነት በመገደብ ሰዎችን  በወንጀል አስተዳደር ሥርአት መሠረት ወደ ሚፈለጉበት ቦታ ወይም ወደ ሚፈልጋቸው አካል  ማቅረብ ነው በሚል ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በሌሎች ፅሁፎች ላይም ተመሳሳይ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ከነዚህ ትርጉሞች መገንዘብ የሚቻለው መያዝ ማለት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል ከተጠረጠረበት ወንጀል ጋር በተያያዘ በፖሊስ ጣቢያ ወይም ወደሌላ ሕጋዊ ቦታ ቀርቦ ቃል እንዲሰጥ ወይም  በፍርድ ቤት ቀርቦ  በተከሰሰበት ጉደይ ምላሸ እንዲሰጥ ለማድረግ የሚከናወን ተግባር መሆኑን ነው፡፡

መያዝ (arrest) መሰረቱ  arrêt, ከሚለው የፈረንሳይኛ ቃል ጋር የሚገናኝ  ሲሆን ትርጉሙም (to stop or stay)  ማቆም ፣ ማቆየት ወይም ማገድ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ መያዝ የሚለውን በዚህ አግባብ ትርጉም ያልተሰጠው ሲሆን የመያዝ ተግባሩ እንዴት መፈፀም እንዳለበት ግን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀፅ 56 ላይ ተመልከቷል፡፡ በዚሁ መሠረት ፖሊስ ተጠርጣውን በቃል ወይም እጁን በመስጠት እንዲያዝ ጠይቆት ካልተስማማ ፖሊሱ ተጠርጣሪውን በመንካት ወይም በመጨበጥ መያዝ እንደሚችል ደንግጓል፡፡ ተጠርጣሪው ለመያዝ ፍቃደኛ ካልሆነ ወይም ለማምለጥ ከሞከረ ፖሊስ ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅሞ ሊይዘው ይችላል፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ሆነ ሥነ ሥርዓት ሕግ መያዝ ማለት ምን እንደሆነ ትርጉም ባይሰጠውም ከተግባር መገንዘብ የሚቻለው በሌሎች ሀገሮች የተሰጠው ትርጉም ለኢትዮጵያ የፍትሕ አስተዳደርም እንደሚያገለግል ሲሆን አፈፃፀሙ ደግሞ ከላይ በቀረበው መልኩ ነው፡፡

መያዝ በመንገድ ላይ እና በየተቋማቱ ከሚደረግ ድንገተኛ ፍተሻ የተለየ ነው፣ ምክንያቱም መያዝ (Arrest) የተጠርጣሪውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠርና በመግታት ለምርመራ ስራ (interrogation)  በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ማድረግ  ወይም በማረፊያ ቤት እንዲቆይ የሚደረግ ተግባር ሲሆን፣ በመንገድ ላይ የሚደረግ ድንገተኛ የአካል ፍተሸ ወይም አቁሞ መፈተሽ ግን አላማው ተፈታሹ የወንጀል ፍሬ የሆነ ነገር መያዝ አለመያዙን ለማረጋገጥ ወይም ለጥንቃቄ ወንጀል ከመስራት ሀሳብ እንዲታቀብ ለማድረግ ወይም አካባቢው ከማንኛውም የወንጀል ስጋት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ ተብሎ የሚከናወን ተግባር ነው፡፡

የመያዝ ጥቅም (purpose of arrest)

መያዝ (Arrest) ተጠርጣሪውን ወደ ሕግ ለማቅረብ ዓይነተኛ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት መሳሪያ ነው፣ ተጠርጣሪው ካልተያዘ የምርመራ ሥራ ለማከናወን በተለይም የተጠርጣሪውን ቃል መቀበል ስለማይቻል፣ ግለሰቡን በመያዝ ምረመራ ለማካሄድ፣ በፍቃደኝነት የሚሰጣቸው ማስረጃዎች ካሉም ለመቀበልና የምርመራውን አካሄድ ለመወሰን የግለሰቡ መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል መዝገቡ ወደ ፍርድ ቤት የሄደ ከሆነ ግለሰቡ ፍርድ ቤት መቅረቡን እርግጠኛ ለመሆን ዋናው መሳሪያ የግለሰቡ መያዝ ነው፡፡ ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም ቅጣቱን ለማስፈፀም የግለሰቡ መያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ  ዋናው የመያዝ ጥቅም ተገቢውን ምርመራ ለማድረግና ግለሰቡን ለፍትሕ ለማቅረብ ነው፡፡

ሌላው የመያዝ ጥቅም ተጠርጣሪው ሌላ ወንጀል እንዳይፈፅምና በእሱም ላይ ሌሎች አካላት ወንጀል እንዳይፈፅሙበት ተጠርጣሪውን ከህብረተሰቡ ገለል በማድረግ ለመከላከል ይረዳል፡፡ አደገኛ ወንጀል ፈፃሚ ከሆነ በቁጥጥር ስር ካልዋለ ሌላ ወንጀል የመፈፀም እድሉ ሰፊ ሲሆን በተለይም ወንጀል መፈፀሙ በፍትሕ አካል እንደታወቀበት ከተረዳ አጥፊ የሆኑ ተግባራትን ሊያከናውን ይችላል ስለዚህ ሌላ ጥፋት እንዳይፈፅም ለመከላከል አይነተኛ መሳሪያ ነው፡፡ እንዲሁም በሰዎች ላይ ወንጀል የፈፀመ ከሆነ ሌሎች ወንጀል የተፈፀመባቸው ሰዎች ወይም የተበዳይ ወገኖች በግለሰቡ ላይ የበቀል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ስለዚህ ተጨማሪ ወንጀል እንዳይፈፅም ወይም በራሱም ላይ ወንጀል እንዳይፈፀምበት በሕግ ከለላ ስር እንዲውል ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

እንዲሁም ለህብረተሰቡ የተያዘው ተጠርጣሪ በወንጀል ተጠርጥሮ መያዙን ለመግለፅ ወይም ለመንገር እንደመሣሪያነት ያገለግላል፡፡ ኅብረተሰቡ ከግለሰቡ እንዲጠነቀቅ ወይም ግለሰቡን በተመለከተ ከተያዘበት ወንጀል አንፃር ማስረጃ እንዲያቀርብ ፣ እንዲጠቁም ወይም ራሱ ምስክር ሆኖ እንዲቀርብ የተጠርጣሪው መያዝ አስፈላጊ ነው፡፡

መያዝ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርአት ውስጥ በሁለት መንገድ የሚፈፀም ሲሆን እነሱም በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሠረት መያዝና ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ ሲሆን በዝርዝር በቀጣይ የምንዳስሰው ሀሳብ ይሆናል፡፡

መያዝ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት

በመያዣ ትእዛዝ ስለሚያዝበት ሁኔታ

ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ማንኛውም ሰው የነፃነት መብት ያለው መሆኑን የደነገገ ሲሆን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መያዝ ወይም ማስርም በፍፁም ክልክል መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ይህንን ድንጋጌ ተመርኩዞ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶችን አካቶ የወጣው አለማቀፍ ሕግም እንዲሁ የነፀነት መብት የተከበረ መሆኑንና ማንም ይህን መብት መጣስ እንደሌለበት ያመለከተ ሲሆን፣ ከሕግ ውጪ ማንም ሰው መያዝ ወይም መታሰር እንደሌለበት አስቀምጧል፡፡ ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ምንም እንኳን አስገዳጅ ባይሆንም ሁሉም ሀገሮች የተቀበሉት በመሆኑ አስገዳጅ እንደሆነ እየተቆጠረ የመጣ ሲሆን፣ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብት ድንጋጌዎችን የያዘው ሕግ ደግሞ አስገዳጅ ሕግ ነው በሕጎቹ ላይ ሀገሮች በሕጎቻቸው ውስጥ አካትተው ለተግባራዊነታቸው በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውና የማስፈፀሚያ መሳሪያዎቹንም ማመቻቸት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡  

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስትም ማንም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ነፃነቱን እንደማያጣ፣ እንደማይያዝ እና ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት እንደማይታሰር ደንግጓል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ሕገ ወጥ እስር ወይም መያዝ ክልክል መሆኑን፣ ፖሊስ ተጠርጣዎችን በቁጥጥር ስር ሲያውል ሕግን ተከትሎ ብቻ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ የነፃነት መብት ሕገ መንግሥታዊ ከለላ ያለው መሆኑን እና ማንኛውም ሰው ይህንን መብት ማንም ጣልቃ ሳይገባበት ተግባራዊ ማድረግ ይችላል፡፡

የነፃነት መብት እና ከሕግ ውጪ ያለመያዝ መብት የአለማቀፋ ሕግና ሕገ መንግስታዊ ከለላ የተሰጣቸው መብቶች ቢሆኑም በሕግ መሠረት ገደብ ሊጣልባቸው እንደሚችል በነዚህ ሕጎች  ተመልክቷል፡፡ ሆኖም በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ፖሊስ ማንኛውንም ሰው መያዝ ሲፈልግ ከፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ፍቃድ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

የመያዝ ትእዛዝ ከፍርድ ቤት ለመጠየቅ ጊዜ ያላገኘ እንደሆነ ወይም አስቸኳይ ሁኔታ ሲያጋጥመው ለፍርድ ቤት በስልክ የመያዣ ትእዛዝ እንዲሰጠው ጥያቄውን አቅርቦ ማስፈቀድ የሚችል ሲሆን፣ በ 24 ሰአት ውስጥ ይህንን ጥያቄውን በፅሁፍ አድርጎ በስልክ ፍቃዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት ማቀረብ ይኖርበታል፡፡

ፖሊስ  የፍርድ ቤት ስልጣን ሳይገድበው በየትኛውም ቦታ ላለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ፍቃድ እንዲሰጠው መጠየቅ የሚችል ሲሆን ጥያቄው የቀረበለት ፍርድ ቤት ግን ትእዛዙን የሚሰጠው ጥያቄው የቀረበበት ቦታ ላለ የፖሊስ አካል መሆኑን ከሕጉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከሌላ ቦታ የመጣ የፖሊስ አካል የመያዝ ትእዛዝ እንዲሰጠው ራሱ በቀጥታ ከመጠየቅ ይልቅ ፍርድ ቤቱ ባለበት አካባቢ የሚገኘው የፖሊስ አካል እንዲጠይቅለት ማድረግ ተገቢ ይሆናል ምክንያቱም በህጉ መሠረት የመያዣ ትእዛዙን የሚሰጠው ፍርድ ቤቱ በሚገኝበት አካባቢ ላለው የፖሊስ አካል በመሆኑ ነው፡፡ ጥያቄው የቀረበለት ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዙን የሚሰጠው ሰውዬውን ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ  በሌላ መንገድ የማይቻል በሚሆንበት ጊዜና  መቅረቡም ፍፁም አስፈላጊ መሆኑን ሲያረጋግጥ ነው፡፡ ፖሊሱም የመያዣ ትእዛዙን ለማግኘት ጉዳዩን በሚገባ ማስረዳትና የወንጀል አድራጊው መያዝ ለትክክለኛ ፍትሕ አስፈላጊ መሆኑን ማሳመን አለበት፡፡ ጥያቄውን የሚያቀርበው ፖሊስ ይህንን ጉዳይ ለፍርድ ቤቱ የማስረዳት ሀላፊነት ይኖርበታል ምክንያቱም ስለተጠርጣሪው ሁኔታ እና ስለሚፈለግበት ጉዳይ ሙሉ መረጃ ያለው ፖሊሱ በመሆኑ ነው፡፡ የመያዣ ትእዛዙ ሲጠየቅ የጊዜ፣ የቦታ እና የሰአት ገደብም የለውም ስለዚህ በማንኛውም ጊዜና ሰዓት ሊቀርብ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ጉዳይ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ለፍርድ ቤት ከሚያቀርበው ጥያቄ ጋር ተያይዞ ስልጣኑን አላግባብ ቢጠቀም ወይም ከፍርድ ቤቱ የመያዝ ፍቃዱ ለማግኘት ሲል ተገቢ ያልሆነ መረጃ በመስጠት ሰውን አላግባብ ቢይዝ ፍርድ ቤቶቹ በምን አግባብ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ፖሊስ የሚያቀርበውን ማስረጃ አይቶ የመያዣ ትእዛዙን ከመስጠት ውጪ ሌላ ሊያጣሩ ወይም ሊያረጋግጡ የሚችሉበት ሁኔታ ስለሌለ የመያዣ ትእዛዙ ፖሊስ በሚሰጠው መረጃ እና ማስረጃ ላይ ብቻ ተመስርቶ ይሰጣል፡፡

ሆኖም አስቀድመን እንደገለፅነው የነፃነት ወይም ከሕግ ውጪ ያለመያዝ መብት ሕገ መንግስታዊ ከለላ ያለው መብት በመሆኑ ማንኛውም የመንግሥት አካል ይህን መብት የማክበር እና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለበት፡፡ ከላይ እንደተገለፀው ፖሊስም የመንግስት አስፈፃሚ አካል በመሆኑና የሕገ መንግስቱን ድጋጌዎች የማክበርና ሀላፊነት ስላለበት ይህንን መብት በአግባቡ ይጠብቃል የሚል ደምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በዚህ መብት ላይ የሚደረግ ጥሰት ካለ ግን አጥፊው በሕግ የሚጠየቅበት፣ ተበዳዩ ደግሞ በሕግ አግባብ ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት ከተጠያቂነት ነፃ የሚሆንበት ሥርዓት ስላለ በዚያው አግባብ እርምት የሚወሰድ ይሆናል፡፡

ሌላው ግንዛቤ መወሰድ ያለበተ ጉዳይ ፖሊስ ተጠርጣሪው ወንጀል መፈፀሙ ጥቆማ ሲደርሰው ከፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ከመጠየቁ በፊት እንደ ነገሩ ሁኔታ ተጠርጣሪውን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀፅ 25 መሠረት ፖሊስ ለጥያቄ እንደሚፈልገው፣ፈፀመ የተባለውን ወንጀል ድርጊት በመግለፅና ፖሊስ ጣቢያ መቼና በስንት ሰአት መቅረብ እንዳለበት በመግለፅ መጥሪያ ሊልክለት ይችላል፡፡ ሆኖም ተጠርጣሪው በተላከለት መጥሪያ መሠረት ወደ ፖሊስ ቀርቦ ለተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት ቃሉን ለመስጠት ያልተባበረ ከሆነና የሰራው የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪው በፖሊስ አስገዳጅነት መያዝ አስፈላጊ ከሆነ ፖሊስ በአንቀፅ 53 መሠረት ከፍርድ ቤት ተገዶ የመያዣ ትእዛዝ በማውጣት በቁጥጥር ስር ያውለዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት በተግባር ያለው አሰራር መርማሪ ፖሊስ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርአት ሕግ አንቀፅ 25 መሠረት ለተጠርጣሪው መጥሪያ የሚልከው ቀላል ወንጀሎች ሲፈፀሙ እና ተጠርጣሪው መጥሪያው ሲደርሰው የማይጠፋ ከሆነ ነው፡፡ ተጠርጣሪው መጥሪያው ሲደርሰው የሚጠፋ ከሆነ ወይም ሌላ ወንጀል የሚፈፅም ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳት ስለሚያመዝን በ 25መሠረት መጥሪያ መላኩ ተገቢ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም መካከለኛ እና ከባድ የሆኑ ወንጀሎች ለፈፀሙ ተጠርጣሪዎች በ25 መሠረት መጥራት ወንጀል ስለመፈፀማችሁ በፖሊስ ስለታወቅ ጥፉ ወይም ተደበቁ የሚል መልእክት ስለሚያስተላለፍ ፖሊስ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ኢዚህ ላይ የሚነሳው ጉዳይ መጥሪያውን ለተጠርጣሪው ማን እንደሚያደርሰው በህጉ ላይ በግልፅ ስላልተቀመጠ፣ መጥሪያውን ከማድረስ ጋር ተያይዞ ችግሮች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚጣሩ ወንጀሎች ምርመራ ሲጀመር ወይም ሲያካሄድ ለተጠርጣሪው የሚላከውን በጥሪያ በግል ተበዳይ በኩል ይልካል፡፡ ሲጀመር የግል ተበዳይ እና ተጠርጣሪው በመካከላቸው አለመግባባት ስለተፈጠረ ስለሆነ የግል ተበዳይ ፖሊስ ጣቢያ መጥተው ያመለከቱት፣ መጥሪያ ለተጠርጣሪው በግል አቤቲታ አቅራቢው በኩል መላኩ ተቀበለኝ አትቀበለኝ በሚል ንትርክ አለመግባባታቸው የበለጠ ሲካረርና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ይታያል፡፡ መጥሪያ ለምን ትሰጠኛለህ ወይም ለምን ከሰስከኝ በሚል ተገቢ አልሆነ አተካሮ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ በብዛት ይታያል፡፡ ስለዚህ የመጥሪያ አላላክን በተመለከተ ያለው ክፍተት መሞላት ይኖርበታል፡፡ ምናልባትም መርማሪው ራሱ መጥሪያውን ለማድረስ የሚያባክነው ጊዜ ከፍተኛ ስለሚሆን በስራ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር፣ በመዝገብ ቤት በኩል ቢላክ ለስራው መቀላጠፍና፣ በግል ተበዳይና በተጠርጣሪው መካከል ሊነሳ የሚችለውን ቀጣይ ግጭት ከማስወገድ አንፃር የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

ሌላው እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ፣ ተጠርጣሪው ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ እንደሰጠበት ሲሰማ የመያዣ ትእዛዝ ፍቃዱን ወደ ሰጠው ፍርድ ቤት ሄዶ ቢያመለክት ወይም ተእዛዙ ተገቢ አለመነሆኑን ቢያስረዳ ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ወይም ተጠርጣው በፖሊስ ከመያዙ በፊት ትእዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስትና መብት ቢጠይቅ በእኛ ሀገር በምን አግባብ ሊስተናገድ እንደሚችል የሕግ ሽፋን የለም፡፡ ሆኖም ትእዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት አቤቱታ የሚያቀርብ ተጠርጣሪ ካለ ፍርድ ቤቱ ትእዛዙን አንስቶ ቢያንስ በዋስ ሊለቀው የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ አሁን በተግባር የሚታየው ግን ተጠርጣሪው ከፖሊስ ጋር ሲቀርብ ብቻ የሚስተናገድት ሁኔታ ነው ያለው በርግጥ ተጠርጣሪው ብቻውን በፖሊስ ከመያዙ በፊት ትእዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት ያመለከተበት ሁኔታ ስለመኖሩ ፀሀፊው አያውቅም፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለ ነገር ቢያጋጥም ፍርድ ቤቱ ማስተናገድ ይኖርበታል በፖሊስ እስኪያዝ መጠበቅ የለበትም፣ ትእዛዙ የተሰጠበት አካል ከሚያቀርበው ማስረጃ አንፃር የተሰጠው ትእዛዝ ስህተት ሆኖ ሊገኝም ይችላል ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ቢያንስ በዋስ መልቀቅ ይኖርበታል፡፡

ያለመያዣ ትእዛዝ ስለሚያዝበት ሁኔታ

መያዝ ( መታሰር ) የነፃነት መብት ልዩ ሁኔታ ነው ምክንያቱም በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት እና ሌሎች ህጎች መሠረት ማንኛውም ሰው የነፃነት መብት እንዳለው በሕግ መሠረት  ካልሆነ በስተቀር ሊያዝ ወይም ሊታሰር እንደማይችል ተመልክቷል፡፡ ስለዚህ ነፃነት ወይም  አለመታሰር መርህ ቢሆንም ይህ መብት ልዩ ሁኔታ[ exception] የለውም ማለት አይደለም፣ በሕግ በተቀመጠው አግባብ መሠረት  ማንም ሰው ሊያዝ ወይም ሊታሰር ይችላል፡፡ በመያዝ ወይም መታሰር ልዩ ሁኔታ ውስጥ በፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ መርህ ሲሆን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ ልዩ ሁኔታ [ exception] ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርአት ህጉ መሠረት ፖሊስ ተጠርጣሪን ያለፍርድ ቤት መያዣ ትእዛዝ ሊይዝ እንደሚችል የሚያመለክቱት ድንጋጌዎች አንቀፅ 19፣20፣50 እና 51 ናቸው፡፡  ያለመያዣ ትእዛዝ መያዝ በፖሊስ ወይም በማንኛውም ሰው ሊፈፀም እንደሚችል የሥነ ሥርአት ህጉ ያስቀምጣል፡፡

በፖሊስ የሚደረግ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ

በአንቀፅ 51 ላይ እንደተመለከተው  በቁጥር 19 እና 20 በተመለከተው አግባብ የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙ ፖሊስ ወይም ማንኛውም ሰው ተጠርጣሪውን መያዝ ይችላል፡፡ በአንቀፅ 50 ላይ ደግሞ የእጅ ከፍንጅ ባልሆኑ ወንጀሎች ጊዜ ያለ መያዣ ትእዛዝ ማሰር ስለሚቻልባቸው ሁኔታ ይዘረዝራል፡፡ ይሁን እንጂ ወንጀል ፈፃሚውን ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ የሚቻለው የተፈፀመው ወንጀል ከሶስት ወር ባላነስ እስራት የሚያስቀጣ እንደሆነ ነው፡፡ በአንቀፅ 50ም ሆነ 51 ላይ የፖሊስ ሰራዊት ተጠርጣሪውን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ እንደሚችል የተገለፀ ሲሆን፣ የተፈፀመው ወንጀል ከሶስት ወር እስራት በታች የሚያስቀጣ ከሆነ ግን ፖሊሱ ተጠርጣሪውን ያለመያዣ ትእዛዝ ማሰር አይች‹-ልም፡፡ ተጠርጣሪው ወንጀሉን ሰርቶ ካመለጠ ወይም በጊዜው ካልተያ በአንቀፅ 51 መሠረት ፖሊስ ያለመያዣ ትእዛዛ መያዝ ይቻላል፡፡ በአንቀፅ 21(2) መሠረት የተፈፀመው ወንጀል የመንግስት ክስ የሚሆን ከሆነ እና የእጅ ከፍንጅ ወንጀል ከሆነ ፖሊስ ያለመያዣ ትእዛዝ ሊይዝ እንደሚችልም ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ በአንቀፅ 51 ላይ  የተገለፁት ነገሮች ተፈፅመው ሲገኙ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የመያዝ ስልጣኑ የፖሊስ ብቻ ሲሆን፣ በአንቀፅ 50 ላይ ያሉት ሁኔታዎች ሲሟሉ ደግሞ ፖሊስም ማንኛውም ሰው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ሊይዝ ይችላል፡፡

ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ወጪ ሌሎች ሕጎችን ስንመለከት ደግሞ፣ ማንኛውም ፖሊስ  አደገኛ ቦዘኔ ነው ብሎ የጠረጠረውን ሰው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ እንደሚችል አደገኛ ቦዘኔነትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው ሕግ ይደነግጋል፡፡ አደገኛ ቦዘኔ የሆኑ ሰዎች በጣም አደገኞችና ለኅብረተሰቡ በጣም አስጊ በመሆናቸው፣ እንዲሁም ፖሊስ በሰዓቱ በቁጥጥር ካላዋላቸው ለፍርድ ለማቅረብ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ ይችላል፡፡ አዋጅ በወጣበት ጊዜ የአደገኛ ቦዘኔነት ተግባር በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር፣ የሕግ አውጪው ሀሳቢ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለሕግ አስፈፃሚው አካል ሰፋ ያለ ሥልጣን ለመስጠት ያሰበ ይመስላል፡፡

በ2001 ዓ.ም የወጣው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅም የሽብር ድርጊት ተብለው በአዋጁ ላይ የተመለከቱትን ተግባራት ለመፈፀሙ ወይመ እየፈፀመ ያለ ስለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጥረውን ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ፖሊስ መያዝ እንደሚችል አመልክቷል፡፡  አንደሚታወቀው የሽብር ድርጊት ማለት የፖለቲካ፣ የሀይማኖታዊ ወይም  የአይዲኦሎጂ ዓላማን ለማራመድ  በማሰብ በመንግሥት ላይ ተፅእኖ ለማሳደር ኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት ወይም የሀገሪቱን መሠረታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ  ተቋማትን ለማናገት ወይም ለማፍረስ የሚደረግ ሕገ ወጥ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ተግባራት የሚፈፀሙ ከሆነ የሚያደርሱት አደጋ ምንያክል አደገኛ መሆኑን መረዳት ቀላል ነው፡፡ ስለዚህ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመያዝ የፍርድ ቤት መያዣ ትእዛዝ ያስፈልገዋል የሚባል ከሆነ አደጋው እንዲፈፀም የመፍቀድን ያክል ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሕጉ ፖሊስ ተጠረጣሪውን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲይዝ መፍቀዱ ከዚህ አንፃር ይመስላል፡፡

በማንኛውመ ሰው የሚከናወን ያለፍርድ ቤት መያዣ ትእዛዝ መያዝ ወይም ማሰር

ከላይ እንደገለፅነው በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት የተፈፀመው ወንጀል የእጅ ከፍንጅ ከሆነ ማንኛውም ሰው ወይም የፖሊስ ባልደረባ ወንጀል የፈፀመውን ግለሰብ ያለመያዣ ትእዛዝ ሊይዘው እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ማንኛውም ሰው የሚለው አገላለፅ  የፖሊስ አባል ያለሆነ ሰውም ከሶስት ወር ያማያንስ ቅጣት የሚያስቀጣ  የእጅ ከፍንጅ ወንጀል የሠራውን ሰው መያዝ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአንቀጽ 51 ላይ ለተዘረዘሩት ወንጀሎች ግን ተጠርጣሪውን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ የሚችለው የፖሊስ አባል ብቻ ሲሆን፣  በአንቀጽ 50 ላይ ያለው ተሟልቶ ከተገኘ ግን ማንኛውም ሰው ማለትም የፖሊስ ሰራዊት ያለሆነ ሰው ተጠርጣሪውን መያዝ ይችላል፡፡ ሆኖም ከያዘ በኋላ ቶሎ ብሎ ለፖሊስ ማስረከብ ወይም ወደ ፖሊስ ጣቢያ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ በሕግ ከተወሰነው ወይም በፖሊስ ከተዘጋጀው ማቆያ ውጪ ተጠርጣሪውን በአንድ ቦታ ለረጅም ጊዜ ማቆየት ተጠያቂነትን ያመጣል፡፡ በሀገራችን ከሦስት ወር በላይ የሚያሰቀጣ ወንጀል ሲፈፅም እጅ ከፍንጅ ያገኘውን ተጠርጣሪ ማንኛውም ግለሰብ መያዝ ይችላል፡፡ በሌሎች ሀገሮች ለምሳሌ በእንግሊዝ ግለሰቦችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ የሚችሉት ማንኛውም ሰው ሳይሆን ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ የእኛ ሀገር ግን ማንኛውም ሰው ስለሚል ዜጋም ሆነ አልሆነ ተጠርጣሪውን መያዝ የሚችል ሲሆን በአንዳንድ ሀገሮች ግን ከዜጋ ውጪ ሌላ ሰው ማሰር አይችልም፤ ይህም ለሀገሪቱ ዜጎች ትኩረት ለመስጠት ይመስላል ወይም ዜጎቻቸው በሌላ ሀገር ዜጋ እንግልት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ይመስላል፡፡

በእኛ ሀገር ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በፖሊስም ሆነ በማንኛውም ሰው የሚያዙበት ሁኔታ ከሌሎች ሀገሮች አንፃር ጠበብ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ ወንጀል ፈፅሞ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ ከእስር ያመለጠ ወንጀለኛ ወይም በፖሊስ ጣቢያ በዋስ ወጥቶ ዋስትናውን ሳይፈፅም በዚያው የጠፋ ሰው ዓቃቤ ሕግ ክስ መስርቶ በፍርድ ቤት ጉዳዩ እየታየ ያለ ወይም ተከሳሹ በሌለበት የሚታይ ጉዳይ ስላልሆ የዓቃቤ ሕግን ተከሳሹ በተገኘ ጊዜ ክሱን የማንቀሳቀስ መብት ጠብቆ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ቢያቋርጠውና በሌላ ጊዜ ተጠርጣሪው  ቢገኝ ያለ መያዣ ትዛዝ ፖሊስም ሆነ ማንኛውም ሰው ሊይዘው ስለሚችልበት ሁኔታ ግልፅ ድንጋጌ የለም፤ በተግባርም እያጋጠመ ያለ ችግር ነው፡፡ በአንድ በኩል ተጠርጣሪው ወይም ወንጀለኛው መብቱን በራሱ ጊዜ ስላጣ ወይም ፍርድ ቤት ተጠርጣሪው በተገኘ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ማንቀሳቀስ ይችላል ብሎ ትእዛዝ ስለሰጠ በተገኘ ጊዜ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ ይቻላል የሚሉ ሰዎች ሲኖሩ በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ አፈፃፀም ላይ ችግር ያመጣል ግለሰቡን እይዛለሁ የሚል አካል ስለ ግለሰቡ በእጁ ላይ ምንም ነገር ስለማይዝ ለምሳሌ የፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ስለሌለው ተጠርጣሪው በሚያዝበት ጊዜ አልያዝም ቢል ሌላ ችግር ይፈጠራል ስለዚህ ድጋሚ የፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ማውጣት ያስፈልጋል የሚሉ አሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አቋም የመጀመሪያውን ሀሳብ የሚደግፍ ነው ምክንያቱም ተጠርጣሪው ሲጠፋ ወይም ሳይቀርብ ሲቀር ራሱን ከፍትሕ እያራቀ በመሆኑ መብቱን በራሱ ጊዜ እንደተወ ይቆጠራል፣ ፍርድ ቤትም በችሎት ብይን የሰጠበት ጉዳይ ከሆነ ወይም የአቃቤ ሕግን ክስ የማንቀሳቀስ መብት ከጠበቀ ግለሰቡ ሲገኝ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ ይኖበታል፡፡ ያም ሆነ ይህ ችግሩ በግልፅ የሚታይ በመሆኑ ተገቢ የሕግ ድንጋጌ እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ማጠቃለያ

የነፃነት መብት እና ያለመያዝ መብት አለማቀፋዊና ሀገራዊ ሕጎች ከለላ ያገኘ መብት በመሆኑና በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እውቅና የተሰጠው በመሆኑ በመርህ ደረጃ ማንም ሰው የማይያዝ የማይታሰር ሲሆን በልዩ ሁኔታ ግን በሕግ መሠረት ማንኛውም ሰው ሊታረስ እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ማንኛውም ሰው ሲታሰር በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሠረት መያዝ የሚኖርበት ሲሆን የመያዝ ጥያቄውም በመርማሪ ፖሊስ ለማንኛውም ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችልና ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪው በሌላ በማንኛውም መንገድ መቅረብ እንደማይችልና የተጠርጣሪው መያዝ ለፍትሕ አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ የመያዣ ትዛዙን ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል በፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ መሠረት መያዝ መርህ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት ያለመያዣ ትእዛዝ ተጠርጣሪ ሊያዝ ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 19 እና 20 የእጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲፈፅም ከተገኘ እና በአንቀጽ 51 ላይ ከሀ-ሸ የተዘረዘሩት ወንጀሎች ሲፈፀሙ ነው፡፡ ከሥስት ወር የበለጠ ቅጣት የሚያስቀጣ የእጅ ከፍንጅ ወንጀል ሲፈፅም የተገኘ ተጠርጣሪ በፖሊስ አባል ብቻም ሳይሆን በማንኛውም ሰው ሊያዝ ይችላል፡፡

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ ወንጀል ፈፅሞ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ ከእስር ያመለጠ ወይም በፖሊስ ጣቢያ በዋስ ወጥቶ ዋስትናውን ሳይፈፅም በዚያው የጠፋ ሰው ቢገኝ ያለ መያዣ ትዛዝ ፖሊስም ሆነ ማንኛውም ሰው ሊይዘው ስለሚችልበት ሁኔታ ግልፅ ድንጋጌ የለም በተግባርም እያጋጠመ ያለ ችግር ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች  እንዳየነው እነዚህ ምክንያቶች ፖሊስም ሆነ ሌላ ፖሊስ ያለሆነ ሰው ግለሰቡን ለመያዝ በቂ ምክንያቶ ናቸው፡፡ ስለዚህ በሚሻሻለው ሥነ ሥርዓት ሕግ ወይም በሌላ ሕግ ላይ በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ ከእስር ያመለጠ ወይም በዋስ ወጥቶ ዋስትናውን ሳይፈፅም የጠፋን ግለሰብ ፖሊስም ሆነ ማንኛውም ሰው መያዝ እንዲችል ግልጽ ድንጋጌ ቢኖር ችግሩ ይቀረፋል፡፡

ሌላው የመያዣ ትእዛዝ ፍቃድ የተሰጠበት ግለሰብ በፖሊስ ከመያዙ በፊት ትእዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት ሔዶ ትክክል አለመሆኑን ካስረዳ ወይም የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ቢጠይቅ ፍርድ ቤቱ ይህንን ጉዳይ በምን አግባብ ማስተናገድ እንደሚችል የሕግ ሽፋን ስለሌለ ግልፅ የሆነ የሕግ ድንጋጌ ሊኖር ይገባል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣው በፖሊስ ከመያዙ በፊት ትእዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስትና መብት ቢጠይቅ ወይም አቤቱታ የሚያቀርብ ተጠርጣሪ ካለ ፍርድ ቤቱ ትእዛዙን አንስቶ ቢያንስ በዋስ ሊለቀው የማይችልበት ምክንያት ስለሌለ ወይም ሚከለክል ሕግ ስለሌለ በዚሁ አግባብ የሕግ ስፋን ሊኖረው ይገባል፡፡

ሌላው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 25 መሠረት መጠራት ያለባቸው ተጠርጣሪዎች በተግባር እንደሚታየው ሆን ተብሎ እነሱን ለማሸማቀቅ ወይም ለማስፈራራት ወይም ፖሊስ ከግል ተበዳዮች ጋር ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት በመፍጠር ተጠርጣሪዎቹን በ25 መሠረት ከመጥራት ይልቅ ከፍርድ ቤት መያዣ ትእዛዝ በማውጣት መታሰር የማይገባቸውን ሰዎች የማሰርና የማንገላታት ተግባር ሲፈፅም ይታያል፣ ስለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍ ፖሊስ በ25 መሠረት ስለሚጠራበትን በፍርድ ቤት ትእዛዝ ስለሚይዝበት ሁኔታ በግልፅ ቢደነገግ በተለይ ከ አንቀጽ 25 ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ሰፊ ሰለሆነ በዚሁ አግባብ ስለሚጠሩ ሰዎች ወይም ተጠርጣሪዎች በሕጉ በግልጽ ሊቀመጥ ይገባዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ወስላትነት በኢትዮጵያ ሕግ ምን ማለት ነው
ፍርድ ቤት ቅጣት ማቅለያን ወይም ማክበጃን በሌላ ማቅለያ ወይም ማክበጃ ቀይሮ ማ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024