- Details
- Category: Sentencing and Execution
- Hits: 18362
የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 1/2002
የመመሪያው አላማና ግብ
በመመሪያው አንቀጽ 3 የሚከተለው ተደንግጎ እናገኛለን
አንቀጽ 3 . የመመሪያው አላማና ግብ፣
1. የመመሪያው አላማ በወንጀል ፍትህ ስርአቱ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መልኩ ውጤታማና ተገማችነት ያለው ቅጣት የሚሰጥበትን ስርአት በመመስረት ወንጀል እንዳይፈጸም መከላከል ነው፡፡
2. መመሪያው የሚከተሉት ግቦች ይኖሩታል፡፡
ሀ. በተቀራራቢና ተመሳሳይ የወንጀል ጉዳዮች መካከል ተቀራራቢነት ያለው የቅጣት አወሳሰን (ወጥነትን) ማረጋገጥ፣
ለ. እንደወንጀሉ ክብደትና አደገኛነት መሰረት ተመጣጣኝ ቅጣት ያለው የቅጣት አወሳሰን ማረጋገጥ ነው፡፡
2. የቅጣት እርከን ሰንጠረዥ
በመመሪያው ቅጣትን ለመወሰን ዝርዝር ሰንጠረዦች ተዘጋጅተዋል፡፡ እነዚህም ነጻነትን የሚያሳጡ ቅጣት ሰንጠረዥ እና የገንዘብ መቀጮ ሰንጠረዥ በሚል ተከፋፍለዋል፡፡
2.1. ነጻነትን የሚያሳጡ ቅጣት እርከን ሰንጠረዥ
ይህ በመመሪያው አባሪ አንድ ሆኖ ተያይዞ የሚገኝ ሰንጠረዥ ሲሆን የወንጀል ሕጉን ዝቅተኛ የቅጣት መነሻ (1 ቀን የግዴታ ስራ) እና ከፍተኛውን የሞት ቅጣት መሰረት በማድረግ 39 ደረጃዎች ያሉት የቅጣት እርከኖች እንዲኖሩት ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡
አላማው አሁን በወንጀል ህጉ ያለውን በመነሻና በመድረሻ መካከል ያለውን ሰፊ ፍቅድ ስልጣን (discretion) በማጥበብ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 88 ንኡስ አንቀጽ 4 እንደተመለከተው ወጥነትንና ተመጣጣኝነትን ማረጋገጥ ነው፡፡
ሰንጠረዡ ሲዘጋጅ ለእያንዳንዱ የቅጣት እርከን መነሻና መድረሻ ያለው ሲሆን፣ የሚከተሉትን መሰረተ ሀሳቦች መሰረት ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ ነው፡፡
- የቅጣት መነሻቸው ከዝቅተኛው ጀምሮ ከፍ እያለ ሲሄድ በመነሻውና በመድረሻው መካከል ፍቅድ ስልጣን (range) እንዲኖር ሆኖ ተዘጋጅቷል፡፡ (ሬንጁ ዝቅተኛው 3 ወር ሲሆን ከፍተኛው 5 አመት ነው፡፡
የቅጣት እርከን 1 ሬንጁ 3 ወር(በትክክል 2 ወር ከሃያ ቀን) ሆኖ ደረጃ በደረጃ እያደገ ይሄዳል፡፡
ከቅጣት እርከን 12 ማለትም (ከ2 አመት- 2 አመት ከ6 ወር) ጀምሮ ሬንጁ ከስድስት ወር ያላነሰ ነው፡፡
ከእርከን 21 ማለትም (ከ5 አመት መነሻ) ጀምሮ ሬንጁ ከአንድ አመት ያላነሰ ነው፡፡
ከእርከን 29 ማለትም (ከ10 አመት መነሻ) ጀምሮ ሬንጁ ከሁለት አመት ያላነሰ ነው፡፡
ከእርከን 34 ማለትም (ከ15 አመት መነሻ) ጀምሮ ሬንጁ ከሶስት አመት ያላነሰ ነው፡፡
በየደረጃው ያለው የቅጣት እርከን መነሻ ሲቀመጥ፣ ከቅጣት እርከኑ ዝቅ ብሎ ከነበረው የቅጣት እርከን አማካይን መነሻ
በማድረግ የቅጣት መነሻና መድረሻው ተወስኗል፡፡
ለዚህ መመሪያ አላማ የአንድ ቀን እስራት ከአንድ ቀን (8 ሰአት) የግዴታ ስራ ጋር ተመጣጣኝ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
በቅጣት ማቅለያ ጊዜ የእስራት ቅጣት ወደመቀጮ እንደሚቀየር በወንጀል ሕግ አንቀጽ 179 የሚደነግግ በመሆኑ ወደመቀጮ
ሲቀየር ስንት ሊሆን እንደሚችል በሚያሳይ መልኩም የቅጣት እርከኑ ተዘጋጅቷል፡፡
2.2. የገንዘብ መቀጮን የሚመለከተው ሰንጠረዥ፣
የወንጀል ህጉን አንቀጽ 90 መሰረት በማድረግ የገንዘብ መቀጮም ደረጃ ወጥቶለታል፡፡
መነሻ ያደረገውም በአንቀጽ 90(1 እና 2) መሰረት ነው፡፡
ዝቅተኛ መነሻ ግን ለሁሉም ተመሳሳይ በህጉ የተመለከተው ነው፡፡ (10 ብር እና 100 ብር)
በዚህ መሰረት የገንዘብ መቀጮ ከዝቅተኛው ጣሪያ 1000 ብር እስከ ብር 500 ሺህ ሊደርስ በሚችል መልኩ
ተዘጋጅቷል፡፡
3. መመሪያው የሚመራባቸው አጠቃላይ ድንጋጌዎች፣
- በወንጀል ሕግ 189 ፍርድ ቤቶች ቅጣትን ሲወስኑ መጀመሪያ ማክበድ እንደሚገባቸው ቀጥለው ደግሞ ማቅለያ ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ማቅለል እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ይህም ቅጣቱን ለማክበድ በመጀመሪያ መነሻ ቅጣት ሊወስኑ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ዳኞች ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶችን መሰረት አድርገው ቅጣት ከመወሰናቸው በፊት መነሻ ቅጣት ማስቀመጥ እንደሚገባቸው ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ዳኞች በቅድሚያ መነሻ ቅጣት ሊያስቀምጡ እንደሚገባ መመሪያው ያስገድዳል፡፡
- በወንጀል ህጉ አንቀጽ 88 ንኡስ አንቀጽ 4 ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቅጣት አወሳሰን ወጥነትና ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ መመሪያ እንደሚወጣ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ወንጀሎችን በተመሳሳይ ደረጃ የሚያስቀምጣቸውን ባህርይ መሰረት በማድረግ ለተመሳሳይ ወንጀሎች ተመሳሳይና ተቀራራቢ ቅጣት መቅጣት፡፡ (ወጥነት)፣ እንዲሁም የወንጀል ፍሬነገሩ ተመሳሳይ ቢሆንም እንደወንጀሉ ከባድነትና አደገኛነት ደረጃዎችን በማውጣት ቅጣት መቅጣት ( ተመጣጣኝነት/ትክክለኛነት) ለማረጋገጥ እንዲቻል ለወንጀሎች የወንጀል ደረጃ ሊወጣላቸውና በዚህ መሰረት ቅጣቱ ሊወሰን እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡
- ህግ አውጪው ለእያንዳንዱ የወንጀል ድርጊት የቅጣት መነሻና መድረሻ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይህም እንደወንጀሉ ሁኔታ ከመነሻው ጀምሮ ቅጣቱን ሊወስን እንደሚችል የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም በወንጀሉ ከባድነት ወይም አፈጻጸም ቀላል የሚባለው ለወንጀሉ ከተቀመጠው መነሻ ቅጣት ጀምሮ እንደወንጀሉ ከባድነት ደረጃ በደረጃ እያደገ በሚሄድ መልኩ ቅጣቱ ሊወሰን እንደሚገባው ያስቀምጣል፡፡
- ህግ አውጪው በወንጀል ልዩ ክፍሉ ለእያንዳንዳንዱ ወንጀል ያስቀመጠው ጣሪያ ላይ የሚደረሰው ጠቅላላ ማክበጃ ምክንያቶች ሲኖሩ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ስለሆነም ማክበጃ ምክንያቶችን መሰረት አድርጎ ቅጣቱ ከመክበዱ በፊት የሚቀመጠው መነሻ ቅጣት የወንጀሉ ከባድነት ከፍ ያለ ቢሆንም (በህጉ ካልተወሰነ በስተቀር (ለምሳሌ ያህል በሞት ይቀጣል፣ በእድሜ ልክ እስራት ይቀጣል በሚል መልኩ ካልተቀመጠ) ጣሪያው ላይ አይሆንም፡
ቅጣቱ እንዲከብድ ህጉ በደነገገ ጊዜ (84) ለቅጣቱ ማክበጃ የሆኑትን ምክንያቶች አይነትና ብዛት እንዲሁም ወንጀለኛው የፈጸመውን ጥፋት ከባድነት በማመዛዘን ፍርድ ቤቱ በዚህ ሕግ ልዩ ክፍል በተመለከተው አግባብነት ባለው ድንጋጌ ከተወሰነው ቅጣት ጣሪያ ሳያልፍ ቅጣቱን ይወስናል፡፡ (አንቀጽ 183)
- በተመሳሳይ የቅጣት እርከን ላይ ለሚገኙ ወንጀሎች በቅጣት ማክበጃና ማቅለያ መሰረት የሚኖረው ጭማሪ ወይም ቅነሳ ተመሳሳይ ሊሆን ይገባል፡፡
- ዳኞች በተቀመጠው ፍቅድ ስልጣን (range) ከመነሻው እስከ መድረሻው በመመሪያው ያልተመለከቱ ሌሎች ምክንያቶችን መሰረት በማድረግ ለመወሰን ይችላሉ፡፡
- መመሪያው በወንጀል ህጉ የተቀመጡትን የቅጣት አወሳሰን ድንጋጌዎች ለማስፈጸም የሚወጣ በመሆኑ፣ በወንጀል ህጉ ውስጥ የተቀመጡትን አጠቃላይ መርሆዎችና ድንጋጌዎች መሰረት አድርጎ እየተተረጎመ ሊሰራበት እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡