- Details
- Category: Property Law
- Hits: 5920
ግዙፋዊ ህልውና ያላቸውና የሌላቸው ንብረቶች (corporeal and incorporeal things)
የዚህ ዓይነት የንብረት ኣመዳደብ የንብረቱ ግዙፋዊ ህልውና /ተጨባጭነት/ያለው መሆን ወይም አለመሆን መሰረት ያደረገ ነው።
ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው ነገሮች (corporeal things)
ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው ነገሮች /ንብረቶች/ የሚባሉ ይናስም ይብዛም ሊዳሰሱ /ሊጨበጡ/ የሚችሉ ናቸው። እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሊለኩ፣ ሊመዘኑ፣ ሊቆጠሩ…ወዘተ የሚችሉ ሆኖው እንደ እህል፣ ጨርቅ፣ መፅሓፍ፣ መኪና፣ ቴሌቪዥን፣ ራድዮ፣ ቤቶች፣ እንስሳት…ወዘተ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል። ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው ነገሮች የሚንቀሳቀሱ ወይም የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሊሆኑ ይችላሉ።
የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችም ልዩ ተንቀሳቃሽ እና ከልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት ውጨ ያሉትን በሚል መልኩ ማስቀመጥ ይቻላል። ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚባሉት እንደ አውሮኘላን፣ መኪና፣ ባቡር፣ መርከብ ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ የእነዚህ ዓይነት ንብረቶች የባለቤትነት መብት ወደ ሌላ ለማስተላለፍ ምዝገባና የባለቤትነት ደብተር ስለሚያስፈልግ ነው። ልዩ ያልሆኑ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የምንላቸው ግን ከእነዚህ ልዩ ከሆኑ ተንቀሳቃሽ ነገሮች ውጭ የሆኑት ሁሉም ተንቀሳቃሽ ነገሮች ናቸው።
ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው ነገሮች አላቂ እና ኣላቂ ያልሆኑ (consumable and non-consumable) በሚል መልኩም ሊገለፁ ይችላሉ። እንዲሁም ዓይነቱ ተለይቶ ሊታወቅ የሚችል ነገር (fungible goods) እና ዓይነቱ ተለይቶ ሊታወቅ የማይችል (non-fungible goods) በሚል ሁኔታም ይገለፃሉ። ዓይነቱ ተለይቶ የሚታወቅ ማለት በመጠን፣ በቁጥር፣ በመለኪያ ሊታወቅ የሚችልና ለተመሳሳይ ዓላማ እርስ በራሱ ሊለዋወጥ የሚችል ነው። ለምሳሌ ገንዘብ መጥቀስ ይቻላል። ዓይነቱ ተለይቶ የማይታወቅ ነገር ግን በማንኛውም መለኪያ ሊመዘን፣ ሊለካ ወዘተ የማይችል ነው። ለምሳሌ፦ የኪነ ጥበባት ስራዎች የቀለም ቅብ ወዘተ።በሌላ መልኩ ደግሞ በባለቤትነት ወይም በይዞታ በሰው እጅ የገቡ ነገሮች (things appropriated) እና በሰው እጅ ያልገቡ ወይም ባለቤት የሌላቸው (things which have no owner or not appropriated) ሆኖው ነገር ግን በባለቤት ሊያዙ የሚችሉ (things which are susceptible of ownership or appropriation) ለምሳሌ፦ በባለቤትነት /በይዞታነት/ ያልተያዘ ንብ መጥቀስ ይቻላል።
ግዙፋዊ ህልውና የሌላቸው ነገሮች (Incorporeal things) (ፍ/ሕግ ቁጥር 1128 እና 1129)
ይህ ዓይነት ንብረት በዓይን ሊታይ ወይም በእጅ ሊዳሰስ የማይችል ተጨባጭነተ የሌለው ነገር ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነቱን ንብረት በሕግ እንዳለ ይገመታል ወይም እውቅና የተሰጠው እንጂ ኣካላዊ ህልውና ያለው ወይም በእውን /በርግጥ/ ያለ ነገር አይደለም። በዚህ ስር የመጠቃለሉት የንግድ መልካም ስም (good will) እና ሌሎች በንግድ መደብር ውስጥ የሚገኙትን ነገሮ (የንግድ ሕግ ቁጥር 124 እና 127 እና ሌሎች የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች ይመለከተዋል) ፣ክሌምስ (claims) ፣ የመድን ፖሊሲዎች፣ ቅርፃቅርፆች፤ የአእምሮ ንብረት ለምሳሌ የፓቴንት እና የቅጅ መብቶች … ወዘተ ናቸው። እነዚህ የንብረት መብቶች እንደሌሎች ግዙፍነት ያላቸው የንብረት መብቶች በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40(2) ላይ ሽፋን እንዲያገኙ ተደርገዋል። በዚሁ አንቀፅ ስር ዜጎች በመፍጠር ችሎታቸው ያፈሩት የተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖሮው ዋጋ ያለው ውጤት ነው በሚል መልኩ ተደንግጎ እናገኘዋለን። በፍትሃብሄር ሕጋችን ዓምቀፅ 1128 እና 1129 እነደተመለከተውም የገንዘብና ሌሎችም ግዙፋዊነት የሌላቸው መብቶቸ ላምጪው በተሰጠው ሰነድ ውስጥ ሲገኙ፤ እንዲሁም እንደ ኤሌከትሪሲቲ ያሉት የኢኮኖሚ ዋጋ ያላቸው የተፈጥሮ ሓይል ነገሮቸ ተቃራኒ የሕግ ድንጋጌ ከሌለ በቀር በሰው ገዢነት ውስጥ ያሉና ለሰው አገልግሎት ስራ የተደረጉ ከሆኑ እንደተንቀሳቃሽ ነገሮች ሆነው እንደሚቆጠሩ ተደንግጎ ይገኛል:: የንብረት ሕጉ ላምጪው በሚሰጥ ሰነድ ውስጥ የሚገኝ መብት አካትቶ ሲያበቃ ለምን ስሙ ለተጠቀሰው ሰው (specified name) ወይም ለታዘዘለት ሰው (to order) የሚተላለፉ ሰነዶችን በሚመለከት ሳያካትት እንደቀረ ግን ግልፅ አይደለም::(የንግድ ሕግ ቁጥር 719 ይመለከተዋል):: ግዙፋዊ ህልውና ወይም ተጨባጭነት ጠባይ የሌላቸው የንብረት ዓይነቶች የማፍራት ብቻ ሳይሆን የዚህ ዓይነት መብት የማስተላለፍ መብትም በፍ/ሕግ ቁጥር 2411 ተካትቶ ይገኛል።
ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው የሌላቸው በሚል ከፋፍሎ የማየት አስፈላጊነት
የዚህ ዓይነት ክፍፍል ያስፈለገበት ምኽንያት ሊዳሰስ የሚችልና የማይችል፣ በዓይን ሊታይ የሚችልና የማይችል ወዘተ ብሎ ለመለየት ይጠቅማል። በሁለቱ መካከል የንብረት መብት የሚገኝበትና የሚተላለፍበት አግባብ የተለያየ በመሆኑ፤ ይኸውም ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው ንብረቶች እነዚህ ንብረቶች በመቀበል /ማግኘት/ ወይም በሰነድ ምዝገባ አማካኝነት ሊተላለፉ የሚችሉ ሲሆን፤ የተጨባጭነት ጠባይ የሌላቸው የንብረት መብቶች ከአንድ ወደ ሌላ ሰው ለማስተላለፍ የሞቻለው ግን በፅሑፍ ብቻ ነው።
ከንብረት ባለቤትነት አንፃር ሲታይ የግል እና የህዝብ ሃብት በሚል ይከፋፈላል
የግል ሃብት (private property) የሚባለው አንድ ወይም ጥቂት ሰዎች በባለቤትነት የያዙት ሆኖ ካለ ሌላ ኣካልና ሕግ ጣለቃ ገብነት ወደ ሶሰተኛ ወገን ሊተላለፍ የሚችል ሆኖ በቅን ልቦና ይዞታ በማድረግና በይርጋ ጊዜ የባለሃብትነት መብት ሊያስገኝ የሚችል ነው። በህዝብ ባለሃብትነት ስር የሚገኙ ንብረቶች ግን የህዝብ ንብረቶች ተብለው የሚታወቁ ሆኖው ወደ ግል ባለሃብት ሊተላለፉ የሚችሉት ህዝብን ወክሎ በሚያስተዳድረው መንግስት አማካኝነት ነው። የዚህ ዓይነት ንብረት በቅን ልቦና እና በይርጋ ጊዜ ባለቤት መሆን አይቻልም።
በአጠቃላይ ንብረት በተለያየ መንገድ ሊመደብ /ሊከፈል/ እደሚችል አይተናል:: ይኸውም ዋና ዋናዎቹ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት አንዱ ሆኖ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የምንላቸው በራሳቸው ወይም በሰው ጉልበት ተፈጥሮአዊ ባህሪያቸውን ሳይለውጡ ሊጓዙ ወይም ሊጓጓዙ የሚችሉ ሲሆን፤ የማይንቀሳቀስ ንብረት የምንላቸው ደግሞ በተፈጥሮአቸው የማንቀሳቀሱ፣ ተንቀሳቃሽ ሆኖው ከማይንቀሳቀሱ ነገሮች ባላቸው ግንኙነት ምክንያት እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚቆጦሩ እና መበቶችን ከማስከበር አንፃር እንደማንቀሳቀሱ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው:: ሌላው የክፍፍል ዓይነት ከንብረት ባለቤትነት አንፃር ሲታይ የግልና የህዝብ በሚል እና እንዲሁም ከተጨባጭነት አነፃር ሲተይ ግዙፋዊ ህልውና /ተጨባጭነት/ ያላቸው እና የሌላቸው በሚል የሚደረግ ክፍፍል ናቸው:: የዚህ ዓይነት የንብረት ክፍፍል አስፈላጊነትም በዋናነት የንብረት ማግኛና ማስተላለፍያ መንገዶች እና በማስረጃ ጉዳይ ላይ ልዩነት የሚታይባቸው በመሆኑ ነው::