- Details
- Category: Property Law
- Hits: 10253
ስለንብረት ሕግ በአጠቃላይ
እንደሌሎች መሰረታዊ መብቶች ሁሉ ለንብረት መብት ከፍተኛ ግምት የሰጠው የኢፊዴሪ ሕገ መንግስት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንደሚከበርለት፣ በሕግ መሰረት ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም፣ የሌሎች መብት ሳይቃረን ንብረቱ የማስተላለፍ መብቶችን ያጐናፀፈው ሲሆን የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብቻ ለንብረቱ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ እንደሚችል ነው መገንዘብ የሚቻለው።
የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 40 የግል ንብረት ሲል እንደ ዓላማ አድርጎ የወሰደው ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ማሕበራት ወይም ሌሎች በሕግ በተለየ በጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማህበረሰቦች በጉልበታቸው ፣ በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና ተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት መሆኑን ይገልፃል። ከዚህ ድንጋገ መገንዘብ እንደሚቻለው ሰዎች በሶሰት አግባቦች ንብረት ማፍራት የሚችሉ ሲሆን፤
ሀ/ ጉልበታቸው ተጠቅመው የሚያፈሩት፣
ለ/ በትምህርት ወይም በልምድ በሚያገኙት እውቅና ክህሎት ተጠቅመው የሚፈጥሩት ነገር፣
ሐ/ ካፒታላቸውን አፍስሰው ወይም ኢንቬስት አድርገው የሚያገኙት ትርፍ ወዘተ ሊሆን ይችላል።
እነዚህ የሃብት ማግኛ መንገዶች የሚፈጥሩት ወይም የሚያፈሩት ንብረት ተጨባጭነት ያላቸው (corporeal things) ወይም የተጨባጭነት ጠባይ የሌላቸው (incorporeal things) ሊሆኑ እንደሚችሉም ሕገ መንግስቱ በተጠቀሰው አንቀፅ ስር በግልፅ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው። (አንቀፅ 40(2) ይመለከተዋል) ።
1.1 የንብረት ትርጉም እና ታሪካዊ አመጣጥ
ንብረት ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ የንብረት ሕግ ምንነት ከማየታችን በፊት መልስ ማግኘት ያለበት ጥያቄ ነው። ንብረት የሚለው ቃል በእንግሊዝኛው “Property” እየተባለ የሚገለፀው ሆኖ “ Proprius” ከሚለው ላቲን ቃል መምጣቱ ይነገራል። proprius የራስ የሆነ ነገር ማለት ነው። የኢትዮያ ፍትሃብሄር ሕግ ስለንብረት ምንነት ያስቀመጠው ትርጉም ባይኖርም ከተለያዩ ፅሑፎችና ስለንብረት ሕግ ከሚደነግገው የፍትሃብሄር ሕግ መረዳት እንደሚቻለው ፤ንብረት ማለት፦
ሀ/ ሌሎችን በማይጨምር ሁኔታ አንድ ነገር በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል (appropriable) መሆን አለበት፣
ለ/ ይህ በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል ነገር ጠቃሚነት ያለው (useful) መሆን አለበት። ይህ ማለት ግን ሁሉም ጠቃሚ ነገሮች የንብረት ትርጉም ይሰጣቸዋል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ፦ ፀሓይ፣ አየር /ወደ ሌላ ሓይል ካልተቀየረ በስተቀር/
ሐ/ ያ ነገር ዋጋ ያለው ወይም ዋጋ የሚያወጣ መሆን አለበት። ይኸውም በገንዘብ ሊገዛ የሚችል ወይም በሌላ ንብረት ሊለወጥ የሚችል መሆን አለበት (The thing must have pecuniary value) ።
በአጠቃላይ ንብረት ማለት በባሌበትነት ሊያዝ የሚችል፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና ዋጋ ያለው ነገር ማለት ነው።
እንደ ሌሎች ሕጎች የንብረት ፅንሰ-ሓሳብም ቢሆን ሊያድግ የቻለው በሮማዊያን የሕግ ባለሙያዎች አማካኝነት መሆኑን ፅሑፎች ይጠቁማሉ:: በሮማዊያን የሕግ ስርዓት ከፍተኛ ግምትና ዕውቅና ሲሰጠው የነበረ የግል ንብረትን(private property) ነው:: የሕግ ባለሙያዎች ስለ ግል ንብረት /ባለሃብትነት/ የተዉት ትርጉም (definition) ባይኖርም የግል ንብረትን የሚመለከት ፅንሰ-ሓሳብ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበራቸውና ትልቅ ስራ የሰሩ ግን እነዚህ የሕግ ባለሙያዎች እንደነበሩ ነው:: ይሁን እንጂ ስራው ረዥም ግዜ የጠየቀና ቀስ በቀስ እየሰፋና እየነጠረ የመጣበት ሁኔታ እንደነበረ ነው:: የሕግ ባለሙያዎቹ ለመጀመሪያ ግዜ መረሬት የመንግስትና የጋራ (communual) ንብረት መሆኑን እና የግል ንብረት ምንነት ለያውቁ እንደቻሉ ነው ከተለያዩ ፅሑፎቸ መረዳት የሚቻለው::
የሮማዊያን ሕግ (The XII Tables) ስለንብረት ያካተተው ነገር ቢኖር ዶሚኔም (dominium) በሚል የሚታወቅ ሆኖ በቤት ውስጥ የሚገኙትን ሁሉም የንብረት ዓይነቶች የሚመለከት የነበረ ሲሆን የሁዋላ ሁዋላ ግን ንብረት የሚለው ፅንሰ-ሓሳብ ለብዙ ነገሮች ተፈፃሚ እንዲሆን እየተደረገ የመጣበት ሁኔታ እንደነበረ ነው::
በጥንታዊ የሮማዊያን ግዜ መሬት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ይዞታ ስር የነበረ ሲሆን ቀደም ሲል ጎሳዎች የሁዋላ ሁዋላ ደግሞ ቤተሰብ በጊዚያዊነት እየተሰጣቸው በይዞታቸው ስር አድርገው ይጠቀሙበት እንደነበርም ፅሁፎች ይጠቁማሉ::
ከቅደም ተከተል አንፃር ሲታይም መጀመሪያ ባርያና ተንቀሳቃሽ ነገሮች እንደንብረት ይቆጠሩ አንደነበርና ቀጥሎም መሬትና ሌሎች የማይንቀሳቀሱ ነገሮች እነደንብረት መቆጠር እንደጀመሩ ነው መገነዘብ የሚቻለው:
የንብረት ሕግ ትርጉም
የንብረት ሕግ ማለት የንብረት መብት እንዴት እንደሚገኝ፣ እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንዴት እንደሚቋረጥ፣ የባለሃብትና የባለይዞታ መብቶች ምን እንደሆኑ … ወዘተ የሚገዛ ሕግ ሆኖ በአንድ አገር ኢኮኖሚ /ምጣኔ ሃብት/ ሁኔታ የሚኖረው ቦታና የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
የንብረት መብት በጣም ትልቅ እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ሕጎች ጥበቃ የሚደረግለት ነው። በፅሑፉ መግቢያ እንደተመለከተው የአንድ አገር የበላይ ሕግ በሆነው ሕገ መንግስት አማካኝነት መሰረታዊ የሆኑትን የንብረት መብቶች ተለይተው ይደነገጋሉ፣ በወንጀል ሕግ ውስጥም ንብረትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በማካተት በእነዚህ ንብረቶች ላይ ወንጀል የሚፈፅሙ ሰዎች እንዲቀጡ ይደረጋል። ይኸውም በኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ በስድስተኛው መፅሓፍ ላይ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ከአንቀፅ 666-684፣ በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ከአንቀፅ 685-688፣ በሰው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ከአንቀፅ 689-691 እንዲሁም በንብረት መብቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ደግሞ ከአንቀፅ 692-705 በዝርዝር ተመልክተው ይገኛሉ።
1.3 ንብረት በሚመለከት የሚራመዱ አመለካቶች /አስተሳሰቦች/
1.3.1 አዳም ሰሚዝ (Adam Smith theory) ፦ ለግል ባለቤትነት ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው ይገባል ከሚል እምነቱ የመነጨ ሕግ አውጪ አካል ለግል ባለሃብትነት ትልቅ ግምት መስጠት አለበት ይላል።
1.3.2 ማርክሲስት ሰነ-ሓሳብ፦ የሶሻሊስት ስነ ሓሳብ የሚያራምድ እንደመሆኑ መጠን ህዝባዊ ባህሪ ላላቸው የንብረት ዓይነቶች ትልቅ ግምትና ጥበቃ ሊሰጣቸው ይገባል። እንዲህ ከተደረገ ብቻ ነው የግል ባለቤትና የካፒታሊስት ስርዓት ሊከስሙ የሚችሉ ይላል።
1.3.3 ሕጋዊ ንድፈ ሓሳብ (Legal Doctrine) ፦ ይህ ሓሳብ መሰረት የሚያደርገው የሕግ ሓይል በመሆኑ ይህ ንብረት በግል ባለቤትነት ይህ ደግሞ በጋራ ወይም በህዝብ ባለቤትነት ሊያዙ ይችላሉ ብሎ በሚያወጣው ሕግ መወሰን ያለበት ሕግ አውጪ ኣካል ነው ይላሉ።
1.3.4 ማሕበራዊ ጠቀሜታ (Social utility) መሰረት ያደረገ፦ አንድ ንብረት በግል ወይም በጋራ ባለቤትነት ሊያዝ የሚችል መሆኑን አለመሆኑን የሚወስነው ራሱ የንብረቱ ባህሪ /ተፈጥሮ/ ነው። ከግለሰብ ይልቅ ለህዝቡ የላቀ ጥቅም የሚሰጥ ከሆነ በጋራ ባለቤትነት የሚያዝ ይሆናል። በሕግ ውስጥ እንዲካተት ማድረግ እንጂ ሌላ ፋይዳ የለውም ይላሉ።
ሌሎች የሚራመዱ አመልካቶች፦
ስራን መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (Labour Doctrine) ፦ ይህ አስተሳሰብ የንብረት ባለሃብት መሆን የሚቻለው በስራ ነው። ሰርተህ ያገኘኸውን ነገር ባለቤት ትሆናለህ። በሌላ አባባል ማንኛውም ሰው ሰርቶ የሚያገኘውን ምርት፣ የሚያካብተውን ሃብት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚና ባለቤት ይሆናል። ይህ እምነት የመነጨው ደግሞ ካፒታል የስራ ውጤት ነው ከሚለው መሰረተ ሓሳብ ነው። በዚህ አስተሳሰብ እንደ ዋነኛ ሕግ (rule) ተደርጎ የሚወሰደው ስራ ሊበረታታ እንደሚገባና የንብረት ክፍፍሉም ምርታማነት ለማሳደግ ለሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት ነው።
የሃይማኖት እምነት መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (Theologician Doctrine) ፦ ንብረት በግል ወይም በጋራ ባለቤትነት ሊያዝ የሚችለው በእግዚኣብሄር ፈቃድ ነው። ሕግ አውጪውም መከተል ያለበት የእግዚኣብሄር ትእዛዝ ነው ይላል።
ተፈጥሮ መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (Naturalist theory) ፦ ይህ አስተሳሰብ የንብረት ባለቤትነት መብት የሚገኘው ከተፈጥሮ ነው። ተፈጥሮ ራሱ ንብረት እንዲኖረን ወይም እንዳይኖረን ይወስናል። የንብረት ባለሃብትነት የተፈጥሮ ፀጋ ነው ይላሉ።
አንድ ነገር እጅ ማድረግ መሰረት ያደረገ ንድፈ ሓሳብ (the occupation theory) ፦ ይህ ንድፈ ሓሳብ ከጥንት ጀምሮ የነበረና እስካሁን ድረስም ለግል ባለሃብትነት እንደ ትልቅ መከላከያ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ንብረቱ በእጁ /በቁጥጥሩ ስር/ አድርጎ የሚገኝ ሰው ለመጀመርያ ጊዜ ንብረቱ ያገኘና እጅ ያደረገ ነው ተብሎ ስለሚገመት ነው።
ለምሳሌ፦ ዓሳን በማጥመድ፣ እንስሳን በወጥመድ በመያዝ የሚገኝ ሃብት መጥቀስ ይቻላል።
ኢኮኖሚያዊ ንድፈ ሓሳብ (Economic theory) ፦ ምጣኔ ሃብት መሰረት ያደረገ የግል ባለሃብትነት መኖር ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ምክንያት ይሆናል። የተሳካለትና የላቀ ትርፍ የሚያገኝ የንግዱ ዓለም ሰው ውጤታማ የሆነ የገበያ ፍላጐት (demand) የማየት ችሎታው ከፍተኛ ነው። እንደዛ ዓይነት ችሎታ (power) የማይኖረው ከሆነ ግን ለድርጅቱ መውደቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
የግል ባለሃብትነት ፍፁም (absolute) አይደለም መሆንም የለበትም። ስለሆነም የግለሰብ መብት ውጤታማ ለማድረግና የሌሎች ጥቅም እንዳያውክ መንግስት ጣልቃ መግባት አለበት። አንድ ሰው ፍፁም (absolute) በሆነ ሁኔታ እንደፈለገው ንብረቱ ጫጫታ በሚፈጥር፣ መጥፎ ሽታ በሚያስከትል ወይም እሳት በሚያስነሳ ኣኳኋን ወዘተ… የሚጠቀምበት ከሆነ ሃብት/ንብረት የሚባለው ነገር ዋጋ ቢስ እንዲሆን ያደርገዋል። ስለዚህ የንብረት መብት በእውነት ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ በንብረት ባለቤቶች ላይ አንዳንድ ገደቦች (restrictions) ወይም ኣዎንታዊ ግዴታዎች በሕግ ሊጣልባቸው ይገባል።