- Details
- Category: Non-Contractual Liability (Tort Law)
- Hits: 10870
ከስም እና ከክብር ጋር በተያያዙ መብቶች ላይ የሚፈፀም ጥፋት ቁጥር /2044/
ይህ ድርጊት በፍትሐብሔርም በወንጀል ሕግም ጥፋት ነው የወንጀል ሕግ ቁጥር 613ን ተመልከቱ እነዚህ ቁጥሮች በኘሬስና ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ሕገ መንግስታዊ መብት ላይ የተደረጉ ገደቦች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 39 /3/ ስር የኘሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት መረጋገጡን ደንግጉ አንቀፅ 29/6/ ስር የሰውን ክብርና መለካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በእነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ ይላል፡፡ ስለሆነም በዚህ ገደብ አማካኝነት ጥበቃ የተደረገላቸው መልካም ስምና ክብር ናቸው፡፡
ይህን ያህል ለመግቢያ ካልን አንዳንድ ነጥቦችን አንስተን እንወያይ የስም ማጥፋት ድርጊት የሚፈፀምበት ሰው በሕይወት ያለ መሆን አለበት ይህም የሰም ማጥፋት የሚደረገው ስሙ የጠፋው ሰው እንዲጠላ ወይም እንዲዋረድ ወይም እንዲሳቅበትና ብሎም ስሙ በጠፋው ሰው ላይ ሌላው እምነት እንዳይኖረው ለማድረግ ወይም መልካም ዝናው ወይም የወደፊት ዕድሉ እንዲበላሽ ለማድረግ ነው፡፡ ይህን ያደረገ ጥፋተኛ ነው፡፡
አንዳንድ ምሳሌዎችን እንውሰድ፡፡ አንድ ሰው በወንጀል ሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል ሳይፈፀም ሰርቷል ወይም አንድን የሕክምና ዶክተር ችሎታ እያለው ችሎታ የለውም ማለት አንድን ነጋዴ ሳይከስር ዕዳውን ለመክፈል አይችልም ማለት ተላላፊ በሽታ ሳይኖርበት እንዳለበት አድርጐ ማውራት ለስም ማጥፋት እንደምሳሌ ልንወስዳቸው እንችላለን፡፡ እንዲሁም ነገሩ እውነት ሆኖም ሰውዬውን ለመጉዳት ብለን ካደረግነው ድርጊታችን ጥፋት ይሆናል፡፡ /የወ.ሕግ 613/
አንድ ቃል ወይም አረፍተ ነገር ስም ማጥፋት ነው እንዲባል ቃሉ ወይም ዐረፍተ ነገሩ ለሶስተኛ ሰው ሊነገር ይገባል፡፡ ለሶስተኛ ሰው ሳይሆን ለራሱ ለተበዳዩ ቀጥታ የተነገረ እንደሆነ ስም ማጥፋት ሳይሆን ስድብ /insult/ ነው የሚሆነው፡፡
ስም የማጥፋት ድርጊት በቃል ሊሆን ይችላል፡፡ በፅሁፍና እንዲሁም በሌላ ዘዴ /ለምሳሌ ሌላ የኪነ ጥበብ ውጤት / ሊሆን ይችላል፡፡ ስም ማጥፋት አለ ለማለት የግድ የመጉዳት ሃሳብ መኖር የለበትም፡፡ 2045 /1/ እንዲሁም ቁጥር 2ዐ45/2/ ስር እንደተደነገገው በብድን ስም /group defamation/ የለም፡፡ ስለሆነም አንድ ሰው ስም አጠፋ ለማለት በንግግሩ ወይም በፅሁፍ የማንንም ሰው በተለይ ካልገለፀ በቀር ስም እንዳጠፋ አይቆጠርም፡፡ ሆኖም ግን ይህ አድራጉቱ ሌላ ሰው እንዲጉዳ አስቀድሞ ለመረዳት መቻሎ ከተረጋገጠ አላፊ ሊሆን እንደሚችል ቁጥር 2ዐ41/3/ ይደነግጋል፡፡
ቀጥለን መከላከያዎችን እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው መከላከያ ቁጥር 2ዐ46 ስር የተደነገገው የሕዝብን ጥቅም በሚነኩ ጉዳዩች ላይ አሳብን መግለፅ ነው፡፡ ይህ የተገለፀው ሃሳብ ሌላውን ሰው በሕዝብ ዘንድ የሚያስወቅስ እንኳን ቢሆን እንደስም ማጥፋት አይቆጠርም ሆኖም ስም አጠፋ የተባለው ሰው ጠፋ የተባለው ሰው ላይ የሰጠው አስተያየት ሃሰት መሆኑን በእርግጠኝነት ካወቀ ጥፋተኛ ይሆናል፡፡
ሁለተኛው መከላከያ ደግሞ የተነገረው ነገር እውነት መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም በማስረጃ ማረጋገጥ አለበት ሆኖም ግን የተባለው ነገር እውነት ቢሆንም ስሙ ጠፋ የተባለውን ሰው ሆን ብሎ ለመጉዳት ቃሉን ወይም ዓረፍተ ነገሩን የተናገረው ተከሣሽ ጥፋተኛ ይሆናል፡፡ /በቁጥር 2ዐ47/
ሶስተኛ መከላከያ ደግሞ የማይደፈር መብት በእንግሊዝኛው /immunity/ የሚባለው ነው፡፡ ይህ መብት ለተወሰኑ ሰዎች የተሰጠ ነው ለፖርላማ አባላትና በፍርድ ቤት ፊት ለሚከራከሩ ወገኖች፡፡ አንድ የፖርላማ አባል በፖርላማ ውስጥ በሚደረግ ውይይት ሀሳቡን ሲገልፅ ግለሰብን አንስቶ ሊናገር ይችላል፡፡ ይህ ግን የፖርላማ አባሉን በስም ማጥፋት ተጠያቂ ሊያደርግው አይችልም፡፡
በፍርድ ሂደት ክርክርም የሰዎች ስም ሊነሳ ይችላል ለፍትህ አሰጣጥ የግድ ከሆነ ግለሰብ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህን ያነሳ ተከራካሪ በስም ማጥፋት ጥፋተኛ አይባልም፡፡
በተጨማሪም ቁጥር 2ዐ45/2/ ስር እንደተደነገገው በምክር ቤት ወይም በፍርድ ቤት የተደረገን ንግግርና ክርክር እንዳለ /እንደወረደ እንደሚባለው/ የገለጠ ሰውም በአላፊነት ሊጠየቅ የሚችለው ስሙ በውይይቱ ወይም በክርክሩ የተነሳውን ሰውዬ ለመጐዳት ብቻ አስቦ ከሆነ ብቻ ይሆናል፡፡
በመጨረሻም የስም ማጥፋት ተግባር በጋዜጣ ላይ ሊደረግ ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ስም አጠፋ የተባለው ሰው ፋጥተኛ የሚሆነው፣
- አንድን ሰው ለመጉዳት ብሎ አስቦ ከሆነ
- ይህንንም የፈፀመው በከፍተኛ ቸልተኝነት ከሆነ
- ወዲያውኑ መልሶ ይቅርታ ካልጠየቀ ነው፡፡
በሌላ አባባል ስም ማጥፋቱን የፈፀመ አንድን ሰው ለመጉዳት ሆን ብሎ አስቦ ሳይሆንና በቸልተኝነት ካልሆነ ይህንንም ካደረገ በኃላ ወዲያውኑ መልሶ ይቅርታ ከጠየቀ ጥፋተኛ አይሆንም፡፡ 2ዐ49/1/
ቁጥር 2ዐ49 /2/ እና /3/ የይቅርታው አጠያየቅ ጊዜ እና በምን ላይ መሆን አለበት የሚለውን ይመልሳሉ፡፡ በንዑስ ቁጥር ሁለት መሠረት ስም ማጥፋት ድርጊቱ የተደረገው ከአንድ ሳምንት በበለጠ ጊዜ በሚወጣ ጋዜጣ ላይ ከሆነ ይቅርታው የግድ የሚቀጥለው ጋዜጣ እስኪወጣ መጠበቅ የለበትም ይህ ከሆነ ተበዳዩ ይጉዳል፡፡ የጠፋውንም ስምና ጉዳቱንም ማስተካከል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሊደረስ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይቅርታው ተበዳዩ በሚመርጠው ጋዜጣ ላይ መውጣት አለበት፡፡ ይህ ጋዜጣ የበዳዩም ሊሆን ይችላል፡፡ የሌላ ሰወ ጋዜጣም ሊሆን ይችላል፡፡ ተበዳዩ ጋዜጣ ካልመረጠ በንዑስ ቁጥር ሶስት መሠረት የስም ማጥፋቱ ነገርና የይቅርታው መጠየቁ የሚታተመው ስምን ማጥፋቱ በወጣበት ተከታይ ዕትም ላይ ይሆናል፡፡