- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 16212
በስራ ምክንያት ስለሚመጣ በሽታ
ትርጉም
በሥራ ምክንያት የሚመጣ በሽታን ትርጉም ማወቅ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከበሽታዎች ውስጥ የትኛው በስራ ምክንያት እንደሚመጣ የትኞቹ ደግሞ በተለመደው ሁኔታ የሰውን ልጅ የሚያጠቁ ከሥራ ጋር ያልተያያዙ እንደሆኑ ለመለየት ይረዳል፡፡ በኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ ህግ መሠረት በሥራምክንያት የሚመጣ በሽታ ማለት
“ሠራተኛው ከሚሠራው የሥራ ዓይነት ወይም ሠራተኛው ከሚያከናውነው ሥራ አካባቢ የተነሣ በሽታው ከተከሰተበት ዕለት አስቀድሞ በነበረው የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በፊዚካል፣ ኬሚካል ወይም ባዮሎጂካል ነገሮች አማካኝነት በሠራተኛው ላይ የሚደርስ የጤና መታወክ ነው” [አንቀጽ 98(1)]
በዚህ ትርጉም የሥራ ላይ በሽታው ምክንያት
- የሥራው ዓይነት ነው
- የሥራው አካባቢ ሁኔታም ነው፡፡
በሁለቱም መንገዶች ቢሆን በሽታው ከሥራው ጋር ግንኙነት አለው፡፡ ከሌሎች በሽታዎች የሚለየውም በሽታው ለሥራው የተለመደ ወይም የሚታወቅ ውጤትን የሚያስከትል መሆኑ ነው፡፡ አስም ማንኛውንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ቢሆንም ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ለረጅም ጊዜ የሠራ ሰው ለዚህ በሽታ የተጋለጠ ነው፡፡ይህ የሆነውም በሥራው ዓይነት ምክንያት ነው፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታም ከፍተኛ ድምጽ ያለበት ቦታ የሚሰራ ሰው የመስማት ሀይሉ ሊቀንስ ወይም ላይኖር ይችላል፡፡ ስለሆነም በእንዲህ ያሉ ሁኔታዎች የሚመጣው በሽታ “የሥራ ላይ በሽታ” ሲባል ተጠቂ ለመሆን ያበቃው ምክንያትም የሥራው ዓይነት ነው ማለት ይቻላል፡፡
የሥራው አካባቢ ሁኔታ ስንልም በሽታው ከሥራው ጠቅላላ ባህሪ የሚመነጭ ወይም በሥራው ባህሪ ምክንያት የሚመጣ ሳይሆን ሠራተኛው እንዲሠራ የሚጠበቅበትን የሥራ ተግባር ተደጋጋሚ በሆነ የማከናወን ሂደት ሲፈጽም ለአንድ ወይም ለሌላው በሽታ የሚጋለጥበት አጋጣሚ ማለት ነው፡፡ በምሳሌ ለመግለጽ ያህል አንድ የቀበሌ የህብረት ሱቅ ሠራተኛ ቆሻሻ የሚቃጠልበት ቦታ አካባቢ ለረጅም ጊዜ በመስራቱ የአስም በሽተኛ ሆኗል፡፡ የህብረት ዕቃዎች መሸጥ በመደበኛ ሁኔታ የአስም በሽታን አያስከትልም፡፡ ሠራተኛው ለዚህ ችግር የተጋለጠው እንዲሠራ የተመደበበት የሥራ አካባቢ ሁኔታ በበሽታው ለመጠቃት ምክንያት ስለሆነው ወይም ተጋለጭነቱን ስላሰፋው ነው፡፡ ስለሆነም በተመሣሣይ ሁኔታ የሥራ አካባቢ ሁኔታዎች በመደበኛ ሁኔታ ችግሩን ያስከትላሉ ባይባልም እንደተጠቀሰው ባለ ልዩ አጋጣሚዎች በሥራ ምክንያት ለሚመጣ በሽታ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
የሥራ ላይ በሽታዎችን በተመለከተ የሠራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስቴር አግባብ ካለው ባለሥልጣን ጋር በመምከር በሥራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ዝርዝር በመመሪያ እንዲያወጣ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ዝርዝር በየአምስት ዓመቱ ሊሻሻል የሚችል ነው፡፡ ዝርዝሩ በጅምላ የሚወጣ ሳይሆን እንደየሥራ ባህሪው እየተለየ የሚገለፅ ነው፡፡ ለአንዱ የሥራ መስክ የሥራ ላይ በሽታ የሚባለው ለሌላው የሥራ መስክ የሥራ ላይ በሽታ ላይባል ይችላል፡፡ ስለሆነም ዝርዝሩ ከየሥራ መስኮቹ ባህሪ አንፃር እየታየ የሚዘጋጅ ነው፡፡
ዝርዝሩ ከተዘጋጀ በኃላ በዝርዝሩ ውስጥ ካሉት ባንዱ በሽታ የተጠቃ ሰው በሽታው እንዳለበት ሲረጋገጥ የሥራ ላይ በሽታ እንደያዘው ማስረጃ ሊሆነው ይችላል፡፡ ከተገለፁት ውጪ በሆነ በሽታ የተጠቃ ሰው ግን
- የተጠቃው በሥራ ላይ በሽታ ስለመሆኑ
- ለተገለፁት በሽታዎችም ቢሆን መንስኤ ናቸው የተባሉት ችግሮች ሌላ መገለጫ ያላቸው ስለመሆኑ ማስረጃ በማቅረብ የሥራ ላይ በሽታ ተጠቂ መሆኑን የማስረዳት ዕድል አለው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡በዝርዝሩ ውስጥ የተካተተ ባይሆን እንኳን ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በአንድ የተወሰነ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ብቻ በተደጋጋሚ የሚይዝ በሽታ አንድን ሰራተኛ የያዘው መሆኑ ሲታወቅ የተጠቃው በስራ ላይ በሽታ እንደሆነ ይቆጠርለታል፡፡ ይህ በራሱ (prima facie) በሽታው ከስራው ጋር አንድ አይነት ትስስር እንዳለው ማስረጃ ነው፤ በስራው እና በበሽታው መካከል ያለውን ግንኙነት በጊዜው የቴክኖሎጂ ደካማነት የተነሣ መረዳት በማይቻልበት ሁኔታ በሰራተኛው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሣይካስ እንዳይቀር ለማድረግ ይህ ጥሩ መንገድ ነው፡፡
የቴክኖሎጂው ዕድገት የሣይንሱን ምጥቀት እየተከተለ ዝርዝሩ በየአምስት ዓመቱ እንዲዘጋጅ መደረጉም ከማስረጃ አቀራረብ አንፃር ሰራተኛው በቀድሞው ዝርዝር ውስጥ ያልነበሩትን የስራ ላይ በሽታዎች ለማስረዳት የሚኖርበትን ችግር የሚያቃልልለት ነው፡፡
የስራ ላይ በሽታ የደረሰበትን ጊዜ ስለመወሰን
ስለበሽታው ከፍ ሲል በተገለፀው መንገድ ከተነጋገርን አሁን ደግሞ የስራ ላይ በሽታው መቼ እንደደረሰ መነጋገሩ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በጉዳቱ ምክንያት የሚገኘውን የካሣ ጥያቄ ለማቅረብ የሚቻል መሆን አለመሆኑን ለመወሰን፤ መጠየቅ የሚቻል ሲሆን እንኳን የካሣው ተጠቃሚ ለመሆን ጥያቄው በምን ያህል ጊዜ መቅረብ እንዳለበት ለመወሰን ይረዳል፡፡
ስለሆነም በስራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ጉዳት የደረሰበት ዕለት በሽታው በግልጽ የታወቀበት ቀን ይሆናል፡፡ በሽታው በግልጽ ታውቋል የሚባለውም
- ሰራተኛው የመስራት ችሎታውን ያጣበት ቀን
- በሽታው በሐኪም ተመርመሮ መኖሩ የታወቀበት የመጀመሪያው ዕለት
- ሰራተኛው በበሽታው ምክንያት የሞተበት ዕለት ነው፡፡
እነኚህ ሁኔታዎች ሰራተኛው በበሽታው የተያዘበት ጊዜያት እንደሆኑ ይቆጠራል፡፡ “እንደሆነ ይቆጠራል” መባሉም በሽታው በአንድ ጊዜ የሚከሰት ሣይሆን በሂደት የሚገለጥ በመሆኑ ትክክለኛውን በበሽታው የተለከፈበትን ዕለት ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡
በሥራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ጉዳት የደረሰበትን ዕለት ስንወስን ይህን ተከትሎ የሚመጣው የመጀመሪያው ጥያቄ ሠራተኛውን በሽተኛ ለማድረግ ያበቃው ሰበብ በሽታው ከተከሰተበት ዕለት አስቀድሞ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህን ለመመለስ ወደ ትርጓሜው መለስ ስንል በሽታው ከተከሰተበት ዕለት አስቀድሞ በነበረው የተወሰነ ጊዜ ውስጥ በፊዚካል፣ ኬሚካል ወይም ባዮሎጂካል ነገሮች አማካኝነት የሚደርስ የጤና መታወክ ሲል ይገልፀዋል “የተወሰነ ጊዜ ውስጥ” የሚለው እንደየበሽታው ጠባይ ሊለያይ የሚችል በመሆኑ ወጥ የሆነ ጊዜ ማስቀመጥ አይቻልም፤ ግን ደግሞ ይህን የተወሰነ ጊዜ ልክ ማን ይወስናል? ሚኒስትሩ መመሪያ እንደሚያወጣ የተነገረው በስራ ምክንያት የሚመጡ በሽታዎችን ዝርዝር ነው፡፡ እነኝህ የተዘረዘሩ በሽታዎች በምን ያህል ጊዜ ሲከሰቱ የስራ ላይ በሽታ እንደሚሆኑ ሊወስን እንደሚችል የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ስለሆነም ይህ ጊዜ በሐኪሞች እንዲረጋገጥ የተተወ ነው? ወይስ የማሕበራዊና ሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር የስራ ላይ በሽታን ዝርዝር ሲያወጣ በሽታው በስራ ምክንያት የመጣ ነው ለማሰኘት አንዱ አስፈላጊ ነገር የበሽታው በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መገለጥ ጭምር በመሆኑ ሚኒስትሩ ይህን ጊዜ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ከዝርዝሩ ጋር አብሮ ያወጣዋል? ክርክር በተፈጠረ ቁጥር ሐኪሞች በየጊዜው እየተጠየቁ የሚሰጡት ማረጋገጫ ሣይሆን በኃለኛው መንገድ የሰራተኛ እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የሥራ በሽታ ዝርዝርን ሲያወጣ አብሮ ጊዜውን የሚወስን እንደሆነ ማሰቡ ትክክለኛው መስመር ይመስላል፡፡
ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሣው ጥያቄ ሰራተኛው በአንድ በሽታ የተለከፈው ሰራተኛ ከመሆኑ በፊት የሚሆንበት አጋጣሚ ነው፡፡ ሰራተኛ ከመሆኑ በፊት የተለከፈ ሰው ሰራተኛ ከሆነ በኃላ የሚሰራው ስራ ለበሽታው መባባስ ምክንያት በሚሆንበት ጊዜ በሽታው የሥራ ላይ በሽታ ሊባል ይችላል ወይ? የሚለው ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚለው የተለከፈበትን ወይስ የተባባሰበትን ዕለት ማለት ነው? አንድ ምሣሌ ለመጨመር ያህል ለሶስት ዓመት በጨርቃ ጨርቅ ፋበሪካ ውስጥ የሰራ ሰው የአስም በሽታ ሊይዘው እንደሚችል ቢገለጽና አንድ ስራተኛ በሁለተኛ ዓመቱ ለዚሁ በሽታ በተፈጥሮው በቀላሉ የሚጠቃ በመሆኑ በሁለተኛ ዓመቱ በአስም ቢያዝና ይህም ሦስት ዓመት ከመሙላቱ በፊት ቢታወቅ የሥራ ላይ በሽታ አይባልም፡፡ በሽታው እየተባባሰ በመሄዱ ግን በአራተኛ ወይም በአምስተኛ ዓመቱ የተመደበበትን ሥራ ለመሥራት እንዳይችል ቢሆን የተባባሰው በዝርዝሩ ከተወሰነው ጊዜ በፊት በመሆኑ ብቻ የተባባሰበትን ጊዜ ከግምት ሳናገባ በጉዳቱ ምክንያት የሚያገኘውን ክፍያ ማሳጣት ተገቢ ይሆናል?