- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 22602
የአሰሪና ሰራተኛ ህግ አስፈላጊነት
አሰሪና ሰራተኛ ህግ በርካታ ጥቅሞች የሚኖሩት ሲሆን ጠቅለል ተደርገው በሶስት ዋና ዋና ርእሶች ስር ተከፍለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሰራተኛውን ጥቅም ማስከበር ወይም ሰራተኛውን ከአሰሪው አግባብ ያልሆነ ጥቃቶች እና ብዝበዛ መከላከል ቀዳሚው የህጉ ፋይዳ ሲሆን የስራ ግንኙነቱን የሚመለከቱ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች በተግባር እንዲውሉ ማድረግ እና ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ ለእኮኖሚያዊ እድገት እና ልማት አስተዋጽኦ ማድረግ ሌሎች የህጉን መኖር አስፈላጊ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡
የሰራተኛን ጥቅሞች ማስከበር
ከካፒታሊስታዊው የኢኮኖሚ ስርዓት ቀደም ብሎ በነበሩት የኢኮኖሚ ስርአቶች አብዛኛው አገልግሎት ሰጭ ህዝብ በግብርና ስራ ላይ እንደ ጭሰኝነት እያገለገለ ወይም ሌሎች የጉልበት ስራዎች በባሮች ( Slaves ) እየተሰራ የሚኖርበት ነበር፡፡ ጭሰኞች ከሚያመርቱት ምርት የተወሰነውን እንደ የጉልበት አገልግሎታቸው ዋጋ እያስቀሩ አብዛኛውን ምርት ለባለመሬቱ በመስጠት ይኖርበት የነበረ ነው፡፡ በባሪያ አሳዳሪው ስርዓት ደግሞ ለጉልበት አገልግሎቱ ምግብና መጠለያ ከአሳዳሪው ያገኝ ከሆነ ነው እንጂ ይከፈለው የነበረ ሌላ ክፍያ አልነበረውም፡፡ ይሁን እንጂ በነዚህ ስርዓቶች ከባለመሬቱም ሆነ ከባሪያ አሳዳሪው አንጻር የጎላ የሀብት ክምችት ያልነበረ በመሆኑና አገልግሎት ሰጪው ክፍልም የተበታተነ ስለነበረ በተደራጀ መልኩ የአገልግሎት ሰጭውን ክፍያና ሌሎች ጥቅሞች በሕግ ለማስከበር የተደረጉ የጎሉ ጥረቶች አልታዩም፡፡
በመሆኑም ምንም እንኳ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሰራተኛውን የክፍያ መብት ለማስከበር የጣሩ ሕጎች ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ለምሳሌ በሀሙራቢ ዘመን ሳይቀር የነበሩ መሆኑ ቢጠቆምም የሰራተኛውን መብት በህግ ማስከበር ጎልቶ የወጣው በአዉሮፓ አህጉር ውስጥ የካፒታሊስት ስርዓት ማቆጥቆጥን ተከትሎ ነዉ፡፡
ይህ የኢኮኖሚ ስርዓት የ12ኛውን ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በአንጻራዊነት በወቅቱ ከነበሩ ሌሎች ስራዎች በሚያሰገኘው ከፍ ያለ ክፍያ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰራተኛ ሃይል ከገጠር ፋብሪካዎች ተሰባስበው ወደሚገኙበት የከተማ አከአባቢዎች እንዲኮበልሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ በወቅቱ በሰራተኛው እና በካፒታሊስቱ መካከል የነበረውን የስራ ግንኙነት በአግባቡ የሚመራ ሕግ ባለመኖሩ እና ከቀድሞ ስርአቶች በተለየ ሁኔታ ካፒታሊስቱ ሀብት በማከማቸት ላይ ብቻ በማተኮር ሰራተኛውን እንደ ያለእረፍት ለረጅም ሰዓት የማሰራት፡ ጉዳት በሚያስከትሉና ለጤና አስጊ በሆኑ አደገኛ ሁኔታዎች በማሰራት የካፒታሊስቱን ሀብት በማደራጀት ሰራተኛው ለከፍተኛ ብዝበዛና ጉዳቶች የተጋለጠበት ሁኔታ እነዲከሰት አድርጓል፡፡
ይሁንና በአንድ በኩል የሰራተኛው ክፍል የነበረበት አሰከፊ ሁኔታ እየተባባሰ መሄድና በሌላ በኩል ደግሞ የሰራተኛው ሀይል በአንድ አካባቢ (በከተሞች አካባቢ) በከፍተኛ ቁጥር ተሰባስቦ መገኘት ሰራተኛው ራሱ ለመብቱ መከበር ትግል እንዲያደርግ ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ ይህም ትግል ቀስ በቀስ እንዱስትሪያዊ ሰላምን በማደፍረሱ በየሀገራቱ ያሉ ህግ አውጭዎች ለሰራተኛው ክፍል ጥብቃ የማድረግን አስፈላጊነት በሂደት እንዲገነዘቡ በማድረጉ ከአመታት ትግል በኋላ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ መሰረታዊ ሕጎቻቸውን እንዲያሻሽሉ ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ በመሆኑም ከረጀም ጊዜ ሂደት በኋላ በአሁኑ ወቅት በአለማችን ላይ ሰራተኛውን አግባብ ካልሆነ ብዝበዛ የሚከላከሉ፡ ሰራተኛው ከስርአት ውጭ እንዳይባረር በማድረግ የስራ ዋስትናውን የሚያስከብሩ፣ የስራ ስንብት ክፍያ የሚገኝበትን ሁኔታዎች በግልፅ የሚያስቀምጡ፡ የስራ ሰዓት መጠንን፣ የዕረፍት ሁኔታዎችን እና ሌሎችንም ዝቅተኛ የስራ ሁኔታ መመዘኛዎችን የሚወስኑ የአሰሪና ሰራተኛ ህጎች ሊኖሩ ችሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሰራተኛው መብት አከባበር አለማቀፋዊ ሽፋን እንዲኖረው ሊያደርግ በሚችል መልኩ ከሰራተኛው መብት ጋር የተያያዘ በርካታ አለም አቀፍ ስምምነቶች በበርካታ አገሮች ፀድቀው በተግባር በስራ ላየ እየዋሉ ነው፡፡
በአገራችንም በዋነኛነት በአጠቃላይ የአገሪቱን ሕጎች በዘመናዊ መንገድ በማዋቀር ሂደት ውስጥ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት በስራ ላይ የዋለው የፍትሀብሄር ሕጉ የስራ ግንኙነትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን ያቀፈ ቢሆንም እነዚህ ድንጋጌዎች በቂ ሆነው ባለመገኘታቸው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 216/56 እና የስራ ሁኔታዎች ደረጃን ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 232/58 በስራ ላይ ውለው ነበር፡፡ በመቀጠልም ዘውዳዊውን ስርዓት በመገልበጥ የዕዝ ኢኮኖሚያዊ ስርአት እንደሚከተል ያወጀው ወታደራዊ መንግስት በሰራተኛው መብት ላይ ያተኮረ የአሰሪውን ፍላጎት ከግንዛቤ ያላስገባ ሊባል የሚችል የሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 64/68 እና ቦኋላ ላይ ደግሞ የሰራተኛ ማህበር አዋጅ ቁጥር 222/74 በስራ ላይ አዋለ፡፡ ይሁንና ኢሕአደግ ወታደራዊውን መንግስት ከስልጣን ካስወገደ በኋላ አገራችን ካፒታልስታዊ ምጣኔ ሀብት ስርዓትን መገንባት በመጀመሯ በአንድ በኩል የአሰሪውን የንብረት ባለቤትነት መብት ያከበሩ በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ ያየናቸውን ሰራተኛው በአለም አቀፍ ደረጃ በትግሉ የተጎናጸፈውን መብቶች ያከበሩ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን እና በቅድሚያ አዋጅ ቁጥር 42/85 በኋላም አዋጅ ቁጥር 377/96 ስራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ ታሪካዊ ዕድገት ሲቃኝ ዋነኛ እና መነሻ አላማው ኢንዱስተሪያዊ ሰላምን ማምጣት በሚያስችል መልኩ ለሰራተኛው ክፍል ተገቢውን ጥበቃ ማደረግ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት የአሰሪውን እና የሰራተኛውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለሁለቱ ወገኖች ስምምነት ብቻ መተው ሰራተኛውን በአንጻራዊነት የኢኮኖሚ አቅሙ ጠንካራ ለሆነው ለአሰሪው ጥቃቶች ሊያጋልጠው እንደሚችል እንረዳለን፡፡ ስለዚህም መንግስት እንደ የግንኙነቱ ሶስተኛ ወገን ሆኖ በግንኙነቱ ውስጥ እየገባ የሰራተኛውን መብት ለማስከበር እና ከአሰሪው አግባብ ያልሆነ ጥቃቶች መከላከል ይኖርበታል፡፡
የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ ከኢንቨስትመንት አንጻር
የሰራተኛውን መብት ማስከበር ማለት ሌላኛውን የግንኙነቱ አካል የሆነውን ሌላኛውን ወገን (አሰሪውን) የግድ መዘንጋት የሚፈልግ አይደለም፡፡ በተለይም በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የአሰሪና ሰራተኛ ህግ አላማ በአንድ በኩል ሰራተኛውን ክፍል አግባብ ካልሆነ ብዝበዛ እና ጥቃቶች መከላከል በሌላ በኩል ደግሞ የአሰሪውን የንብረት ባለቤትነት መብት በማክበር ሁለቱም ወገኖች በመተባበር የኢንዱስትሪ ሰላምን በመፍጠር ሁለንተናዊ ዕድገት እና ልማት ለማምጣት እንዲሰሩ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው አዋጅ ቁጥር 377/96 የአዋጁን መግቢያ ይህንኑ ሃሳብ በመግለጽ የሚጀምረው፡፡
የኢንዱስተሪያዊ ሰላም መስፈን በራሱ የሰራተኛውን ምርታማነት የሚጨምር መሆኑ የተረጋገጠ ዕውነታ ሲኖረው ይህ የምርታመነት መጨመር የአሰሪውን የንብረት ባለቤትነት መብት መከበር የሚያረጋግጥ እና ይህም የኢንቭስትመንት መስፋፋትን እንደሚያመጣ ይታመናል፡፡ የኢነቨስትመንት መስፋፋት ደግሞ ሰፋ ተደርጎና ከረጅም ጊዜ አንጻር ሲታይ የሰራተኛውን የስራ ዋስትና ሊያረጋግጥ እንደሚችል በኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ይታመናል፡፡
በአንድ አገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና የኢኮኖሚ ልማት እንዲኖር አገሪቷ የምትከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትክክለኛነት ወሳኝነት አለው፡፡ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ይህንን ከንግድ ፖሊሲ አንጻር እንደሚያስረዱት የአንዲት አገር የኢኮኖሚ ልማት የበለጠ እንዲፋጠን አገሪቷ አለም አቀፍ የንግድ አንቅስቃሴ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ማሳደግ ይኖርባታል፡፡ ይህም አገሪቷ እራሴን ችዬ እኖራለሁ ከምትል ይልቅ አንጻራዊ የተሻለ የማምረት ብቃት (Comparative advantage) በሚኖራት ምርቶች ላይ አትኩራ በማምረት እነዚህኑ ወደውጭ የመላክ እና ሌሎች ምርቶችን ወደ አገር የማስገባት የአለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ተሳታፊነትን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ሀሳብ በተለይም ከድሃ አገሮች አንጻር ሲፈተሸ በአንድ በኩል እድገትን የሚያፋጥን ነዉ የሚል በሌላ በኩል ደግሞ ድሀ አገሮች የበለጠ እንዲደኸዩ የሚያደርግ ነው የሚል ክርክር በባለሙያዎች ዘንድ ያለ ቢሆንም ከቦታም ከጊዜም አንጻር ሲታይ ክረክሩ ውስጥ በዝርዝር መግባት አስፈላጊ ባለመሆኑ እናልፈዋለን፡፡ ይሁን እነጂ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች ቀደም ብሎ ያልነበረ አንጻራዊ የተሻለ የማምረት ብቃት (Comparative advantage) አንዲት አገር እንዲኖራት ማድረግ የሚቻል መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም ይህን የተሸለ የማምረት ብቃት በማሳደግ አገሮች በውጭ ንግድ ውስጥ ያላቸውን እንቅስቃሴ ማሳደግ በዚህም መሰረት የኢኮኖሚ ልማታቸውን ማፋጠን እንደሚቻል የተለያዩ አገሮችን ተመኩሮ እያነሱ ያስረዳሉ፡፡ ይህንኑ አቋም መሰረት በማድረግ የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ የተሻለ አንጻራዊ የማምረት ብቃትን ከማምጣትና ከማጎልበት አንጻር የሚኖረውን ሚና ቀጥለን እናያለን፡፡
አንዲት አገር አንድን ምርት ከሌሎች ይልቅ የተሸለ የማምረት ብቃት (Comparative advantage) እንዲኖራት ከሚያደርጉ ሁኔታዎች ውስጥ ጥሬ ዕቃ፣ የሰለጠነ የሰው ኀይል፡ ካፒታል፡ ተቋማዊ ብቃት (Comparative institutional advantage) እና የመሳሰሉት እንደየሁኔታው ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር የተያያዘው ተቋማዊ ብቃት በመሆኑ ትኩረታችን በዚሁ ላይ ይሆናል፡፡
ተቋማዊ ብቃት ለአንዲት አገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወሳኝ ከሆኑ ግብአቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ በተለያዩ የማህበረሰብ ጥናቶች ውስጥ እያደገ የመጣ አመለካካት ነው፡፡ እነዚሁ ጥናቶች ተቋም (Institution) ማለት የገበያ ልውውጡ ሂደት የሚፈልገውን ወይም የሚያሰከትለውን ወጭ የሚወስኑ “የጨወታው ደንቦች” እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ “የጫወታ ደንቦች“ በአንድ በኩል የሚመለከታቸውን ወገኖች መሰረታዊ መብትና ግዴታዎችን ያካተቱ ሕጎችን በሌላ በኩል ደግሞ በሕጎቹ አፈጻጸም ውስጥ ድርሻ የሚኖራቸውን ለምሳሌ እንደ ፍርድ ቤቶች እና ሌሎች ተቋማትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
ከዚህ በመነሳት እነዚህ “የጫወታ ደንቦች“ በሚመለከታቸው ወገኖች መካካል የሚፈጠረው ግንኙነት የሚያሰከትለውን ወጭ በቀነሱ ቁጥር አገሪቷ ከሌሎች አገሮች አንጻር የሚኖራት ተቋማዊ አንጻራዊ ብቃት (Institutional Comparative advantage) መጨመሩ እንደማይቀር ይታመንበታል፡፡ ስለዚህም ወደ ርዕሰ ጉዳያችን በመመለስ አንድ የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ መሰረታዊ መብትና ግዴታዎችን አካቶ ከያዘና በአግባቡና በቅልጥፍና የሚያስፈጽሙት ፍ/ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ካሉ አገሪቱ ውጤታማ የአሰሪና ሰራተኛ ሕግ የሚኖራት ሲሆን ይህም በአሰሪውና ሰራተኛው መካካል የሚኖረውን የስራ ግንኙነት ገበያውን ወጭ በመቀነስ በአነስተኛ ወጭ ምርታማነት እንዲጨምር ሊያደርግ የሚችል ነው፡፡ በዚሁ መሰረት አንድን ምርት ቀደም ብሎ ህጉ ውጤታማ ከመሆኑ በፊት ከነበረው በአነስተኛ ወጭ ማምረት ስለሚቻል የአገሪቷን ከሌሎች የተሻለ የማምረት ብቃት (Comparative advantage) ማሳደግ ይቻላል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህም ለአገርቷ በተሻለ ሁኔታ ኢንቬስተሮችን የመሳብ እድል ይሰጣታል፡፡ ኢኮኖሚስቶች እንደሚያስረዱት የዚህ አይነቱ ተቋማዊ ብቃት ከሌሎች አንጻራዊ የመምረት ብቃትን ከሚያሰከትሉ ሁኔታዎች ጋር ከተቀናጀ አዳዲስ ኢንቬስተሮችን በመሳብ አዲስ ሀብት በስራ ላይ እንዲውል ከማድረጉም በላይ በሌሎች አከባቢ ያላቸውን ሀብት ወደዚህኛው አገር እንዲያዛውሩ የማድረግ አቅምም ይኖረዋል፡፡
የአሰሪና ሰራተኛ ሕግና ሕገመንግስቱ
የሰራተኞች መብት ረዘም ያለ ጊዜ በፈጀ ትግል የተከበረ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአለማችን የሚገኙ ብዙ አገሮች የሰራተኛውን መብት በዝርዝር ሕጎች ማካተት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ህጎች በሚመነጩባቸው ህገመንግስቶቻቸው ውስጥ መሰራታዊውን የዜጎች መብቶች በሚዘረዝር ክፍሎቻቸው ስር አካተው ይገኛሉ፡፡
የኛም ሕገመንግስት መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በሚለው በምዕራፍ ሶስት ስር ከሌሎች የዜጎች መብቶች ጋር ሰራተኞችን የሚመለከቱ መብቶችን አካቶ ይገኛል፡፡ ከነዚህ መብቶች ውስጥ ከፈሎቹ ከኢኮኖሚ መብት ጋር በመያያዝ ጠቅላላ የአገሪቷን ዜጎች የሚመለከቱ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በቀጥታ ሰራተኛውን ብቻ የሚመለከቱ ናቸዉ፡፡
በዚሁ መሰረት በቅድምያ በህገመንግስቱ አንቀጽ 41 ስር በሰፈረው የኢኮኖሚ ማህበራዊና የባህል መብቶች ስር ያለውን ብናይ ንዑስ አንቀጽ 1 እንደሚያስቀምጠው }ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመስራት መብት አለው~ ሲል ንዑስ አንቀጽ 2 ደግሞ }ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው~ በማለት ይደነግጋሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ድንጋጌዎች ከስራ ውል አቅጣጫ ሲታዩ ሁለት መሰረታዊ የሆኑ የሰራተኛውን መብት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ አነድ ሰራተኛ የመረጠውን የስራ አይነት የመስራት መብት ያለው መሆኑን የሚያረጋግጡ በመሆኑ የማይፈልገውን የስራ አይነት በማስገደድ ማሰራት የማይቻል መሆኑን ያስገነዝቡናል፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 4/1/ም ይህን ህገመንግስታዊ መብት በሚያረጋግጥ መልኩ የስራ ውል የሚመሰረተው የሰራተኛው ፈቃደኝነት ሲኖር እንደሆነ በመግለጽ ያስቀምጣል፡፡
ይህ ስራን የመምረጥ መብት በሁለተኛነት የሚያመለክተን ቁምነገር አነድ ሰራተኛ እየሰራ ባለው ስራ መቀጠል ባይፈልግ ስራውን የማቆም ወይም የስራ ውሉን የማቋረጥ መብት ያለው መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም ሰራተኛው በራሱ ፈቃድ የገባበት የስራ ውል ያልተስማማው ከሆነ አሁንም በራሱ ፈቃድ ሊያበቃው እንደሚችልና መቀጠል በማይፈልገው የስራ ውል እንዲቀጥልበት ሊገደድ የማይችል መሆኑን ያሳየናል፡፡ ይህንን የህገመንግስታዊ መብት ድንጋጌ በማንፀባረቅም የአዋጁ አንቀጽ 31 ሰራተኛው የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ በመስጠት በማናኛውም ምክንያት ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል ሲደነግግ አንቀጽ 32 ደግሞ ውሉን የሚያቋርጠዉ በአንቀጹ ስር በተደነገጉት ምንያቶች ከሆነ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ እንዳይኖርነት አድርጎ ይገኛል፡፡
በቀጥታ ሰራተኛውን ብቻ የሚመለከቱ የሕገመንግስቱን ድንጋጌዎች ወደማየት ስናልፍ ድንጋጌዎቹ የሚገኙት የሰራተኞች መብት በሚል ርዕስ የተቀመጠው የሕገመንግስቱ አንቀጽ 42 ስር ነው፡፡ እነዚህ መብቶች የሰራተኛውን በማህበራት መደራጀት፤ ሰራተኞች በሕብረት መብቶቻቸውን የሚያስከብሩበትን ሁኔታዎች እና መሰረታዊ የስራ ሁኔታዎችን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
ከሰራተኛው የመደራጀት መብት አንጻር አንቀጽ 42/1/ሀ/ ሰራተኞች ከሌሎች እንደ የአሰሪዎች ማህበራት ካሉ አካላት ጋር የመደራደርና ለድርድሩም ብቃት እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ በማህበራት የመደራጀት መብት አጎናጽፏቸው ይገኛል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሰራተኛው ቅሬታዎችን የማሰማት መብት ያለው መሆኑና ይህም ስራ እስከማቆም ባለ ድርጊት ሊፈጸም እንደሚችል በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ /ለ/ ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
የስራ ሁኔታዎችን በተመለከተ ለሰራተኞች በአግባቡ የተወሰነ የስራ ሰዓት ዕረፍት፡ የመዝናኛ ጊዜ፣ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የዕረፍት ቀኖች፣ ደሞዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በአላት፤ እንዲሁም ጤናማ እና አደጋ የማያደርስ የስራ አከባቢ የማግኘት መብቶች ተከብሮላቸው ይገኛል (በአንቀጽ 42/2/) ፡፡ በተጨማሪም ሴት ሰራተኞች ከወንዶች ጋር በተመሳሳይ ስራ ተመሳሳይ ክፍያ የማግኘት መብት እነዳላቸዉ በአንቀጽ 42/1/መ/ ስር ሰፍሯል፡፡
በአጣቃላይ ከነዚህ ድንጋጌዎች የምንረዳው ለረጅም ዘመናት ሰራተኛውን ሲያታግሉ የነበሩ መብቶች በሕገመንግስቱ የተከበሩ መሆኑንና ሕገመንግስቱ ሰራተኞች ተደራጅተው መብታቸውን ማስከበር እንዲችሉ ያመቻቸ እንዲሁም ለጥቃት ለብዝበዛና ለአደጋ ሊያጋልጣቸው የሚችሉ የስራ ሁኔታዎች እነዳይኖሩ የሚሻ መሆኑን ነው፡፡ እነዚህን መብቶች በአግባብ በስራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚይዘው አዋጅ ከህገመንግስቱ ድንጋጌዎች ምንም ሳይቀንስ አካቶ መያዝ የሚገባው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ህጉን በስራ ላይ የሚያውሉ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ወቅት እነዚህን የህገመንግስት ድንጋጌዎች ከግንዛቤ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እስካሁን ያየነው ከሰራተኛው አንጻር ያሉትን ህገመንስታዊ መብቶች ነው፡፡ ህገመንግስቱ ግን አጠቃላይ የዜጎችን መብት የሚያስከብር በመሆኑ በተጓዳኝ የአሰሪውም መብት ሊዘነጋ የሚገባ አይደለም፡፡ ስለዚህም አሰሪዎች እንደማንኛውም ዜጋ አንቀጽ 31 እንደሚደነግገው ለማንኛውም አላማ በማህበር የመደራጀት መብት ያላቸው ሲሆን በጉልበታቸው በዕውቀታቸው ወይም በካፒታላቸው የግል ንብረት የማፍራትና ባለቤት የመሆን መብት እንዳላቸው አንቀጽ 40 ስር ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የሰራተኛን መብት ለማስከበር ሲታሰብ በተጓዳኝ ሰራተኛውም ለአሰሪው ግዴታ የሚኖርበት መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ለዚህም ነው አዋጁ በመግቢያው ስር ለአገራችን ኢንዱስትሪያዊ ሰላምን በመፍጠር እድገትና ልማትን ለማምጣት ሲባል የአሰሪና ሰራተኛ የስራ ግንኙነት መሰረታዊ በሆነ መብትና ግዴታዎች ላይ የሚመሰረት መሆኑን እውቅና ሚሰጠው፡፡ በተጨማሪም ይኸው መግቢያ አሰሪዎችም ሰራተኛውም ውጤታማ የሆነ ድርድር ማድረግ የሚችሉት በየራሳቸው ማህበራት ተደራጅተው ሲገኙ እንደሆነ ያምናል፡፡ የአዋጁ ዝርዝር ጉዳዮችም ሲታዩ በአንድ በኩል የሰራተኛውን መብቶች ያስከበሩ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ የአሰሪውንም መብቶች ያስከበሩ ሆነው የሚታዩት፡፡ እዚህ ላይ ከላይ ከሰራተኛው አንጻር የተነሳውን በማንኛውም ምክንያት ስራ የመልቀቅ መብት ከሰራተኛው የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ ጋር መታጀቡን እነደምሳሌ ማንሳቱ በቂ ይሆናል፡፡ ሰራተኛው ስራውን የማቋረጥ መብት እንዳለው ሁሉ ሰራተኛው ስራውን የሚያቋርጠው በአንቀጽ 32 ስር በተገለጹት የአሰሪው በሆኑ ምክንያቶች ሳይሆን በራሱ ሌሎች ምክንያቶች ከሆነ በሰራተኛው መልቀቅ ምክንያት አሰሪው ጉዳት እንዳይደርስበት ለምሳሌ ተተኪ ሰራተኛን የማዘጋጀት አይነት የራሱን ዝግጅት ማድረግ እንዲችል ሰራተኛው የአንድ ወር ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ መደረጉ አግባብ ሆኖ ይታያል፡፡