- Details
- Category: Employment and Labor Law
- Hits: 25838
የአሰሪና ሠራተኛ ሕግ ትርጉም
ትርጉም
የአሰሪና ሠራተኛ ህግ በመሰረቱ በአሰሪና በሰራተኛ መካከል በሚደረግ የስራ ውል ላይ ተመስርቶ የሚፈጠሩ ግንኙነቶችን የሚመራ፣ የሚቆጣጠር ህግ ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ አሰሪ እና ሠራተኛ የሚሉት ስያሜዎች ሲታዩ ጠቅለል ያሉ ስያሜዎች ስለሆኑ እንደየሁኔታው የተለያዩ ሕጎችን የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አንድ ወገን አሠሪ ሌላኛው ወገን ደግሞ ሠራተኛ ሊሆኑበት የሚችሉ በርካታ ዘርፎች ሲኖሩ እነዚህን ግንኙነቶች የሚመሩ የተለያዩ ህጎች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በፍትሀብሔር ሕጉ የተመለከቱተን የስራ ግንኙነቶች በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ የማይሸፈኑ እስከሆነ ድረስ ይህው ህግ ሲመራ የመንግሰት አስተዳደር ሠራተኞችን (civil servants) የመንግስት አሰተዳደር ሰራተኞች ሕግ ይመራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 የሚመራው የአሰራሪና ሠራተኛ ግንኙነት ይገኛል፡፡ ስለዚህም ይህ አዋጅ የትኞቹን አይነት የስራ ግንኙነቶች እንደ ሚመለከት ለመለየት በተፍታታ ሁኔታ ማየቱ አግባብነት ይኖረዋል፡፡
የስራ ውል
የስራ ውል ትርጉም በ1952ቱ የፍታብሔር ሕግም በአዋጅ ቁጥረ 377/96 ስርም ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የፍታብሔር ሕጉ ቁጥር 2512፡-
}የስራ ውል ማለት ከተዋዋዮቹ ወገን አንዱ፡ ሰራተኛው፤ ለሌላዉ ወገን ለአሰሪው አንድ ጉዝፍነት ያለው ወይም የአእምሮ ስራ በተወሰነ ወይም ባልተወሰነ ጊዜ ውስጥ አሰሪው ሊከፍለው በተገደደበት አንድ ደሞዝ በርሱ አገልግሎትና በርሱ መሪነት ስራውን ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ነው፡፡~
በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ ትርጉም የስራ ውል ሁለት ወገኞች አንዱ አሰሪ ሌላኛዉ ሠራተኛ ሆነው አሠሪው ቁጥጥር እያደረገ ሠራተኛው ለሚሰራለት የጉልበት ወይም የዕወቅት ስራ ደሞዝ የሚከፍልበት የስራ ግንኙነት የሚፈጥር ስምምነት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሕጉ አዋጂ ቁጥር 377/96 በአንቀጥ 4/1/ ስር የስራ ውል አመሰራረትን ሲያትት፡
ማንኛውም ሰው ደመወዝ እየተከፈለው በአሰሪ መሪነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ወይም የተወሰነ ስራ ለአሰሪው ለመስራት ቢስማማ በሁለቱ መካከል የስራ ውል ይመሠረታል፡፡
በማለት የስራ ውልን ትርጉም ይሰጣል፡፡ እንደሚታየው ሁለቱም ህጎች በተመሳሳይ ሁኔታ የስራ ውል ትርጉምን ያቀርባሉ፡፡
የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚያቀርቡት የስራ ውልን ከሌሎች ውሎች ለመለየት አምስት ሁኔታዎች መሟላታቸው ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ እነዚህም ከሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች አንዱ በሕጉ መሰረት አሠሪ ነው ተብሎ የሚወሰድ ሲሆን ይህ ወገን ለሚያገኘው አገልግሎት ተገቢውን ደሞዝ የሚከፍልና አገልግሎቱም በእርሱ ቁጥጥር የሚመራ ነው፡፡ ሁለተኛው ወገን አገልግሎት የሚሠጠው ሠራተኛ ሲሆን በአሠሪው ቁጥጥር መሠረት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በመሆኑም አንደኛው ወገን አሠሪ፣ ሁለተኛው ወገን ሠራተኛ ሲሆን አሰሪው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ቁጥጥር ማድረግ መቻሉ፣ እና ደሞዝ የመክፈል ግዴታው እንዲሁም ሠራተኛው በራሱ አገልግሎት መስጠቱ የስራ ውልን ከሌሎች ውሎች በአጠቃላይ መለየት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ሲሆኑ በተለይ የአሰሪው ቀጥታ ቁጥጥር ማድረግ እንደ ውክልና ከመሳሰሉ ሌሎች የውል ግንኙነቶች የሚለየው ነው፡፡
የአሰሪና ሠራተኛ ማንነት
ስለ ስራ ውል የተሰጠው ትርጉም አዋጅ ቁጥር 377/96 የሚመለከተው የትኞቹን የስራ ውሎች ለመሆኑ የተሟላ መልስ አይሰጥም፡፡ በመሆኑም በአዋጁ የሚገዙት የትኞቹ አሰሪዎች እና ሰራተኞች ናቸው ከሚል አቅጣጫ የአሰሪና የሰራተኛውን ማንነት መፈተሽ ያሰፈልጋል፡፡
አዋጁ አንቀጽ 2/3/ ስር }ሰራተኛ ማለት በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ከአሰሪ ጋር በቅጥር ላይ የተመሰረተ የስራ ግንኙነት ያለው ግለሰብ ነው~ በማለት አዋጁ ስለሚገዛው ሰራተኛ ማንነት ያሰቀምጣል፡፡ በመሆኑም ይህ ሰራተኛ ለአሰሪው በአሰሪው ቁጥጥር ስር አሰሪው ለሚከፈለው ደሞዝ በራሱ የጉልበት ወይም የዕውቀት አገልግሎት ለተወሰነ ጊዜ ወይም ስራ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ትርጉም እላይ ስለስራ ውል ባየነው ትርጉም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የሚጨምረው አዲስ ነገር አይታየም፡፡ በመሆኑም አዋጁ የሚመለከተው የትኛውን ሰራተኛ ነው ለሚለው ጥያቄ መፍቻነት እምብዛም አያገለግልም፡፡
በመሆኑም ጥያቄውን ከአሰሪው ማንነት አቅጣጫ ለማየት እንሞክራለን፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 2/1/ ስር } አሰሪ ማለት አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆነ ሰዎችን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ቀጥሮ የሚያሰራ ግለሰብ ወይም ድርጅት ነው፡፡~ በማለት የአሰሪን ማንነት ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህም ትረጉም ምንም እንኳ ወደ የስራ ውል ትርጉም የሚመራን ቢሆንም በአዋጁ የሚሸፈነው የስራ ውል የውሉ አንደኛው ወገን የሆነው አሰሪው ግለሰብ ወይም ድርጅት ሊሆን እንደሚችል በመግለጽ ድርጅት የሆነውን አሰሪ በማየት ጥያቄውን ሊፈታ የሚችል ተጨማሪ ነጥብ ሆኖ ይገኛል፡፡ በመሆኑም አሰሪው ግለሰብ ወይም ድርጅት ሲሆን የስራ ውሉ ግንኙነት በአዋጁ የሚገዛ መሆኑን አሰሪው ከነዚህ ውጭ ከሆነ እነደሁኔታው የሌሎች ህጎች ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት የሚኖራቸው ይሆናል ሊባል ይችላል፡፡
አሰሪው ግለሰብ በሚሆንበት ጊዜ የስራ ውል ስር ከተመለከትነው ትርጉም የተለየ የሚጨመረው ነገር ባለመኖሩ በዚሁ እናልፍና በአዋጁ መሰረት አሰሪ ሊባል የሚችል }ድርጅት~ ምን ዓይነት እንደሆነ ቀጥለን እናያለን፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2/2/ ስር እንደተተረጎመው }ድርጅት ማለት ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለእርሻ ፣ለኮንሰትራክሽን ወይም ለሌላ ህጋዊ ዓላማ የተቋቋመ በአንድ አመራር የሚካሔድ ተቋም ነዉ፡፡~
በዚህ ትረጉም ስር አሰሪ ድርጅት ሊሆኑ ከሚችሉ ተቋማት ውስጥ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የእርሻ፣ የኮንሰትራክሽን ተቋማት በስም ተጠቅሰው ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት በአብዛኛው ትርፋማ ለመሆን የሚቋቋሙ ናቸዉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በአዋጁ መሰረት አሰሪ ሊሆን የሚችል ድርጅት ትርፍ ለሚያስገኝ ስራ የተቋቋመ ሲሆን ነው፡፡ በመሆኑም በአዋጁ መሰረት የሚገዛ የስራ ውል አንደኛው ወገን የሆነው አሰሪው ትርፍ በሚያስገኝ ስራ የተሰማራ ሊሆን ይገባል የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አሰሪ ሊሆኑ የሚችሉት ድርጅቶች በስም የተጠቀሱት ብቻ ሳይሆኑ
… ለሌላ ሕጋዊ ዓላማ…~ የተቋቋሙትንም የሚመለከት በመሆኑ አሰሪ ድርጅት ለትርፍ ስራ የተቋቋመ ብቻ ነው ብሎ መውሰድ ይህንን የድንጋጌውን ሓረግ }...ለሌላ ህጋዊ የትርፍ ዓላማ... ~ ወደሚል መቀየር ስለሚሆን አግባብ ያልሆነ ፍቺ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ሌሎች ተቋማት እንዲሁም በስም የተጠቀሱት የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የእርሻ፣ የኮንሰትራክሽን ተቋማት ሆነውም ትርፍ ከማግኘት አላማ ውጭ ለሌላ ሕጋዊ አላማ ለምሳሌ ለምርምርና ልማት ( Research and Development ) ሊቋቋሙ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ሥለዚህም አሰሪው ለትርፍ የቆመ መሆን አለበት የሚለው አቋም አግባብ አይደለም የሚል አቋም ይታያል፡፡
የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን
ከላይ እንደተገለጸው የተለያዩ ዓይነት በቅጥር ላይ የተመሰረቱ የስራ ግንኙነቶች ይኖራሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ይህ አዋጅ በየትኞቹ ላይ ተፈጻሚነት ሊኖረው እንደሚችል በዋነኝነት የሚመራው የአዋጁን የተፈጻሚነት ወሰን የደነገገው አነቀጽ 3 ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ሶስት ቁምነገሮችን ያቀፈ ሲሆን እነሱም በሶስቱ ንዑሳን አንቀጾች ስር በተናጠል ስፍረው እናገኛቸዋለን ፡፡
የመጀመሪያው ንዑስ አንቀጽ፡ በንዑስ አንቀጽ 2 ስር በበስተቀርነት የተደነገጉት እንደተጠበቁ ሆነው ይህ አዋጅ በአሰሪና ሰራተኛ መካከል በሚደረግ በቅጥር ላይ በተመሰረተ የስራ ግንኙነት ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡ ስለዚህም በቅጥር ላይ የተመሰረተው ግንኙነት በአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ 2 ስር ከተዘረዘሩት ውስጥ የሚወድቅ ከሆነ የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች የማይፋጸሙባቻው መሆኑን በአንድ መልኩ ከዚህ ድንጋጌ ስንረዳ በሌላ መልኩ ደግሞ ከነዚህ ውጭ ባሉ በአሰሪና ሰራተኛ መካካል በሚፈጠሩ ማንኛውም ግንኙነት ላይ አዋጁ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው እንረዳለን፡፡
ሁለተኛው የአንቀጹ ዋና ፍሬ ነገር በንኡስ 2 ስር የተደነገገው ሲሆን ይህም ምንም እንኳ ግንኙነታቸው በቅጥር ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በዝርዝር በሚያስቀምጣቸው የስራ ግንኙነቶች ላይ አዋጁ የማይፈጸም መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ እነዚህም ለአስተዳደግ ሲባል፡ ከህመም ለመዳን፡ ወይም እንደገና ለመቋቋም፤ ለትምህርትና ለስልጠና (የሙያ መልምጃ ትምህረትን ሳይጨምር) የሚደረጉ የስራ ውሎችን፡ የስራ መሪን ፣ ለትርፍ በሚካሔድ ስራ ላይ ያልተመሰረተ የግል አገልግሎት ቅጥርን ፤ በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ እንደ የጦር ኀይል ባልደረቦችን፡ የመንግስት አስተዳደር ሰራተኞችን፡ ዳኞችን፡ ዐ/ሕጎችን፡ ፖሊሶችን እና ሌሎችንም እንዲሁም በራሱ የንግድ ስራ ወይም በራሱ የሙያ ኀላፊነት የሚሰራ ስራ የሚያከናውን ተዋዋይ ያለበት ግንኙነቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም አዋጁ በነዚህ ግንኙነቶች ላይ የማይፈጸም መኆኑን ያመላክተናል፡፡
ሦስተኛው የአንቀጹ ፍሬ ነገር የስራ ግንኙነቱ በንዑስ አንቀጽ ሁለት ስር የሚወድቁ ባለመሆናቸዉ በአዋጁ አንቀጽ 1 መሰረት በቀጥታ ሊፈጸምባቸው የሚችል ቢኆንም በንኡስ አንቀጽ 3 ስር በተገለጹት ሁኔታዎች መሰረት ከአዋጁ ሽፋን ውጭ ሊደረጉ የሚችሉ የስራ ግንኙነቶችን የሚመለከት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ኢትዮጰያ ውስጥ የሚሰሩ የድፒሎማትክ ሚሲዮኖች ወይም አለምአቀፍ ድርጅቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚመሰርቱት የስራ ግንኙነት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደነብ መሰረት ወይም ኢትዮጵያ በምትፈርማቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት በአዋጁ ላይሸፋኑ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደነብ መሰረት በሃይማኖት ወይም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚመሰረቱ ግንኙነቶች ፤ እንዲሁም በግል አገልግሎት የስራ ሁኔታ የሚመሰረቱ የስራ ግንኙነቶች ላይ አዋጁ ተፈጻሚነት እንዳይኖረዉ ሊያደርግ ይችላል፡፡
ስለዚህም በአጭሩ ሲገለጽ አዋጁ በአጠቃላይ በአሰሪና ሰራተኛ መካካል በሚቋቋም በቅጥር ላይ በተመሰረተ የስራ ግንኙነት ላይ ተፈጻሚነት የሚኖረው ቢሆንም በአዋጁ በግልጽ በተደነገጉ ሌላ ህግ በሚገዛቸው ግንኑነቶች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ በተጨማሪም አሁንም አዋጁ የሚሸፍናቸው የስራ ግንኙነቶች ሊሆኑ ቢችሉም ነገር ግን የሚንስትሮች ምክር ቤት ወይም ኢትዮጵያ የምትፈርማቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች በሚወስኑት መሰረት ከአዋጁ ሽፋን ውጭ ሊደረጉ የሚችሉ መሆኑን ተመልክቷል፡፡