- Details
- Category: Criminal Law
- Hits: 9969
የአስክሬን ምርመራ (Forensic pathology)
ፎረንሲክ ፖቶሎጂ ወይም የአስክሬን ምርመራ የአንድን ሰው አሟሟት በአጋጣሚ፣ ራስን ማጥፋት፣ በተፈጥሮ ወይም በሰው እጅ የሞተ መሆኑን የሚገልጽ የፎረንሲክ ሳይንስ ጥበብ ነው፡፡ ፎረንሲክ ሳይንስ የተጀመረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ44ኛ ዓመት ዓለም ነበር፡፡ በወቅቱም ትልቅ ስምና ዝና የነበራቸውን የንጉሳውያን ቤተሰቦች አሟሟት ለማጣራት ነበር የተጀመረው፡፡ የፎረንሲክ ፓቶሎጂ መጀመርና በብዙ ሰዎች መለመድ በመቻሉ ለጂዲ ኤን.ኤ እውቅናና አሁን ለደረሰበት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የዘርፉ ባለሞያዎች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
የመጀመሪያው የአስክሬን ምርመራን የሚያትት መጽሀፍ በ1247 ሶንግቺ በተባለ ፀሀፊ ተጽፏል፡፡ በዚህም የፎረንሲክ ህክምና ሳይንስ አባት ለመባል በቅቷል አምስት ህትመቶቹን (በዚያንጅሉ) xiyanjilu, ርዕሶች ለንባብ አብቅቷቸዋል፡፡
በአውሮፓ የመጀመሪያው የአስክሬን ምርመራን የሚያትት መጽሀፍ ለንባብ የበቃው በ1507 ባምበርድ ኮድ አፓርድ በሚል ርዕስ የወጣው ነበር፡፡ በዚህም የሞት መንስኤ፣ የግድያ ወንጀሎችና በመርዝ የሚሞቱ ሰዎችን መለየት የተጀመረበት ወቅት ነበር፡፡
የአስክሬን ምርመራ ሳይንስ የህክምና ሳይንስ ዘርፍ ሲሆን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሞት መንስኤዎችን የሚያረጋግጥ መሳሪያ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ ይህ የምርመራ ሳይንስ ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ተሰጥቶት አገልግሎት ላይ የዋለው እ.ኤ.አ 1959 በአሜሪካን ሀገር ነበር፡፡ ከዚህ ዓመት በኋላ በዚሁ ሀገር የሞት መንስኤን ለማጣራት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በርካታ የአሟሟት መንስኤዎችም ታውቀው ለህግ የተላኩ ሲሆን በፍርድ ቤቶችም ተቀባይነት በማግኘት የሟቾችን የአሟሟት መንስኤ በማረጋገጥና አጥፊዎች እንዲቀጡ ተደርጓል፡፡
አሁን አሁን በአሜሪካን ሀገር ድንገተኛ ሞትን፣ የተፈጥሮ፣ ያልተጠበቁ እንዲሁም በመርዝ የሚሞቱ ሰዎችን የሚያጠና የህክም ዘርፍ ሲሆን ፅናትን ቆራጥነትንና ፍጹም የሰው ልጆችን የሞት መንስኤዎችን ለማጥናት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ብቻ ሊገቡበት የሚገባ የህክምና ዘዴ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት በኋላ በአሜሪካን ሀገር የአስክሬን መርማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ በእጅጉ እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ መኖሩን በዚሁ ሀገር የሚገኘው ‘’National Acadamy of science’’ የተባለው ተቋም እየገለፀ ይገኛል፡፡ ይህ ተቋም በ2009 ባወጣው ሪፖርት መሠረት በአሜሪካን ሀገር በሁሉም ግዛቶች ከ500 ያልበለጡ ሙያተኞች ብቻ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በዓመት ከ500 ሺህ በላይ የሞት መንስኤን እንዲመረምሩ በመደረጉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ ብዙ የባለሙያዎች አስተያየት የአስክሬን ምርመራ ባለሙያ እጅግ ሊያንስ የቻለው ከአራት ዓመታት የህክምና ትምህርት በኋላ ለሶስት ዓመት የአጠቃላይ የሰውነት አካል ትምህርት ስለሚሰጥና የሙያ ሰርተፍኬት ለማግኘት የፅሁፍና የተግባር ፈተና መስጠታቸው እንዲሁም በየ10 ዓመት ፍቃዳቸው እንዲታደስ በመደረጉ ሰልጣኞች ወደዚህ ሙያ ሊመጡ እንዳላስቻላቸው ይነገራል፡፡ በተጨማሪም በስልጠና ተቋም የሚገኙ መሳሪያዎች ተመጣጣኝ አለመሆናቸው፣ ወደዚህ ሙያ እንዲገቡ የሚያማልሉ ነገሮች አለመኖራቸውና የክፍያ ማነስ ባጠቃለይ ለአስክሬን ምርመራ ሙያ አዳጋች ሁኔታን መፍጠሩን በሙያው ለ40 ዓመታት ያገለገሉት ዶ/ር ቪሴን ዲማሪዬና ሳን አንቶኒዮ ይናገራሉ፡፡
በተፈጥሮ የአስክሬን ምርመራ ባለሙያ በማህበረሰቡ የሚገለል፣ በቤተሰቡ ላይ ሀዘን የሚፈጥርና ሁልጊዜ ከሞቱ ሰዎች ጋር የሚያገናኝ ሙያ በመሆኑ የራሱ የሆነ ተጽእኖ በባለሙያው ላይ መፍጠሩ አይቀርም ነገር ግን ክቡር የሆነውን የሰው አካል በምን ምክንያት እንደሞተና ለፍትህ አካል የሚያቀርብ በመሆኑና አጥፊዎችን የሚያስቀጣ በመሆኑ ሊወደድና ከፍተኛ ክብር ሊሰጠው የሚገባ ሙያ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በአገራችን የአስክሬን ምርመራ ከተጀመረ ጥቂት ዓስርት ዓመታትን ብቻ አሳልፏል፡፡ እስከ ቅርብ ዓመት ድረስ ይህ አገልግሎት የሚሰጠው በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ብቻ ነበር፡፡ ያውም በሁለት የአስክሬን ምርመራ ባለሙያዎችና በአንዲት ኩባዊት ባለሙያ ከየሀገሪቱ ክልል መንገድ ላይ የሞቱ፣ በአደጋ፣ በሰው እጅ የተገደሉ ሰዎች ወደዚሁ ሆስፒታል ለምርመራ ይላካሉ፡፡ በዚህም በከፍተኛ ጫና ውስጥ እየሰሩ እንዳሉ መገንዘብ አያዳግትም፡፡
የአስክሬን ምርመራ ውጤት ለፍርድ ሂደት እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚሰጥ አያጠያይቅም በአንፃሩ ደግሞ የተዛባ ውጤት በፍርድ ሂደቱ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ይታወቃል ስለዚህ በአገራችን በርካታ ባለሙያዎችን በበቂ ሁኔታ ማሰልጠን እንዲሁም የአስክሬን ምርመራ ሆስፒታሎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ያስፈልጋል፡፡ በቅርቡ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ከመቀሌ ሆስፒታል ጋር በመተባበር የአስክሬን ምርመራ እንደጀመሩ ይታወቃል፤ ሌሎች ክልሎችም በአካባቢያቸው ካሉ የኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ሙያተኞችን በማሰልጠን አገልግሎቱን መጀመር ይገባቸዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታልም ይህን አገልግሎት ለመጀመር እቅድ እንዳለው የተገለፀ ሲሆን አገልግሎቱን ሲጀምር በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ላይ ያለውን ጫና ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአስክሬን ምርመራ ውጤት ለህግ አካላት የሟቹን የሞት መንስኤ በአደጋ፣ በሰው እጅ፣ በተፈጥሮ በመርዝ መሆኑን የሚገልጽ የህክምና ዘዴ በመሆኑ በእጅጉ ይጠቅማቸዋል፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው አካል በመላ-ሀገሪቱ አንድ የምርመራ ጣቢያ በመክፈትና ባለሙያዎችን በማሰልጠን የፍርድ ስርዓቱን ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ (ይህ ጽሑፍ በፖሊስና ርምጃው መጽሔት ለመጀመሪያ ጊዜ መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም ተጽፏል)