አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 ምን አዲስ ነገር ይዟል - በወፍ በረር
የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር የተቋቋመ 15 ከፍተኛ የሕግ ባለሙያዎችን በአባልነት ያካተተ የዳኝነት ሥርዓት አማካሪ ጉባኤ ረቂቁ ተዘጋጅቶ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራሮች፣ በሕግ ባለሙያዎች እና በሕዝብ ተሳትፎ ዳብሮ ከሁለት አመታት ቆይታ በኋላ ጥር 13 ቀን/ 2013 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።
ይህ አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 ከነባሩ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 25/88 እና ይህን አዋጅ ካሻሻሉት ሌሎች አዋጆች ቁጥራቸው 138/1991፣ 254/1993፣ 321/1995 እና 454/1997 ከሆኑት አዋጆች ምን የተለየ አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል? እንዲሁም ለአዳዲሶቹ ሕጎች መነሻ ዋና ዋና ምክንያቶቹስ ምን ምን ናቸዉ የሚለዉን በወፍ በረር እንመልከት።
1. መሰረታዊ የሕግ ስህተት መተርጎም - አንቀጽ 2(4)
ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚቀርብ የመጨረሻ ውሳኔ «መሠታዊ የሆነ የሕግ ስህተት» አለበት ወይስ የለበትም የሚባለው በምን መለኪያ ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይዞ የመጣዉ አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 በአንቀጽ 2(4) ስር የሚከተለዉን ድንጋጌ ዝግ (Exhaustive) በሆነ መንገድ አስቀምጧል። አስቀምጧል።
አንቀጽ 2(4) - “መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት” ማለት ቀጥሎ ከተዘረዘሩት መካከል አንዱ እና ፍትህን የሚያዛባ ጉልህ የሕግ ስህተት ያለበትን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 10 መሰረት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ሊታይ የሚችልን የመጨረሻ ዉሳኔ፣ ፍርድ፣ ብይን፣ትእዛዝ፣ ናቸዉ።
ሀ) የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚቃረን
ለ) ሕግን አላግባብ የሚተረጉም ወይም ለጉዳዩ አግባብነት የሌለውን ሕግ የሚጠቅስ
ሐ) ለክርክሩ አግባብነት ያለው ጭብጥ ሳይያዝ ወይም ከክርክሩ ጋር የማይዛመድ አግባብነት የሌለው ጭብጥ ተይዞ የተወሰነ፤
መ) በዳኝነት ታይቶ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ዉድቅ በማድረግ የተወሰነ፤
ሠ) በፍርድ አፈጻጸም ሂደት ከዋናው ፍርድ ጋር የማይገናኝ ትእዛዝ የተሰጠበት፤
ረ) ጉዳዮን አይቶ የመወሰን የዳኝነት ሥልጣን ሳይኖር የተወሰነ ፤
ሰ) የአስተዳደር አካል ወይም ተቋም ከሕግ ዉጭ የሰጠው ውሳኔ
ሸ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ በመቃረን የተወሰነ፤
እስካሁን በነበረዉ አሰራር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አጣሪ ችሎት ላይ የሚሰየሙ ሦስት ዳኞች የመጨረሻ ውሳኔው መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለው ወይም የለውም ብለው ትዕዛዝ ለመስጠት መነሻ የሆነ የሕግ ማእቀፍ አልነበራቸዉም። አንዳንድ ጊዜ በሰበር ኣጣሪ የሚሰየሙ ሦስት ዳኞች መሠታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለበት ወይም ያስቀርባል በማለት ትዕዛዝ የሰጡበት የስር ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ አምስት ዳኞች የሚሰየሙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከቀረበ በኋላ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ የሚወሰንበት ጊዜም ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ሦስት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር አጣሪ ችሎት ዳኞች መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አለበት ብለው ትዕዛዝ የሰጡበት ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የለበትም ተብሎ በአምስት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኞች ውድቅ የሚደረገውን ያህል መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለባቸው ነገር ግን አያስቀርቡም የተባሉ ጉዳዮች ሊኖሩ አይችሉም ማለት ያስቸግራል፡፡
መሠረታዊ የሕግ ስህተት በአዋጁ ላይ ትርጉም እንዲኖረው ማድረጉ ከፍ ሲል የተጠቀሰውን በሰበር አጣሪ ዳኞች ወጥ ባልሆነ መንገድ የሚሰጥ ዉሳኔ ችግር በጉልህ ለማቃለል ከማገዙም በተጨማሪ ባለጉዳዮችም በተሰጠባቸው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የሰበር አቤቱታ ከማቅረባቸው በፊት አቤቱታቸው የሚያዋጣ መሆን አለመሆኑን በቅድሚያ ለመመዘን ያስችላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአዋጁ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ለሚለው ሀረግ ትርጉም እንዲገባ ተደርጓል፡፡
2. የሰበር - ሰበር በተወሰነ ደረጃ መከልከሉ - አንቀጽ 10
በክልል ፍርድ ቤቶች የመጨረሻ ዉሳኔ የተሰጠበት ወይም ያለቀ ዉሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በሚል ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ሊቀርብ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉ ጥያቄ ወይም የሰበር ሰበር ይፈቀዳል ወይስ አይፈቀድም የሚለዉን ክርክር ሙሉ በሙሉ የሚመልስ ባይሆንም አዋጁ የተለየ አቀራረብን ይዟል። በተሻረዉ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ አንቀጽ 10 ላይ በግልጽ የሰበር ሰበር ሙሉ ሙሉ ይፈቅድ ነበር። አዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ግን የሰበር ሰበርን በከፊል ይከለክላል።
አንዳንድ ምሁራን «የሰበር ሰበር» በኢፌድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 80(3)(ሀ) መሰረት ተፈቅዷል በሚል ሲከራከሩ ለዚህም የሚያነሱት ነጥብ ማንኛዉም መሰረታዊ የሕግ ስህተት ያለበትን ጉዳይ ለማረም የሰበር ስልጣን እንዳለዉ የሚገልጸዉን የህገ-መንግስት አንቀጽ 80(3)(ሀ) በማንሳት እና በአንዳንድ ክልሎች የሰበር ችሎት ያለመቋቋምንም እንደተጨማሪ ምክንያት በመጥቀስ በክልል ጉዳዮች ላይ የፌደራል ሰበር መሰረታዊ የሕግ ስህተት የማረም ስልጣን ሊኖረዉ ይገባል ይላሉ።[1] በሌላ በኩል ደግሞ የህገ-መንግስቱን አንቀጽ 80(1)ን በመጥቀስ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌደራል ጉዳዮች ላይ የበላይ እና የመጨረሻ ስልጣን ይኖረዋል መባሉ በክልል ጉዳዮች ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ስልጣን አይኖረዉም በማለት የሚከራከሩ አሉ።[2] በተጨማሪም የፌደራል ስርዓቱ የተዘረጋዉ በፌደራል እና በክልል መንግስታት ትይዩ በሆነ መንገድ ስለሆነ አንዱ በሌላዉ ጣልቃ እንደማይገባ በህገመንግስቱ አንቀጽ 50(8) የሚደነግግ በመሆኑ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልል ጉዳዮች ምንም አይነት የዳኝነት ስልጣን ሊኖረዉ አይገባም በማለት ይከራከራሉ።[3] በአዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 አንቀጽ 10 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደሚደነግገዉ። የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የወሰነዉ ዉሳኔ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች ወይም አስገዳጅ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ዉሳኔዎችን በመቃረን የተወሰነ ከሆነ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ሊቀርብ እንደሚችል በአንቀጽ 10(1) ተደንግጓል። የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ዉሳኔ የተወሰነዉ የክልል ሕግን ያላግባብ በመተርጎም እና ጉዳዩ የሕዝብ ጥቅም የሚመለከት ወይም ሀገራዊ ፋይዳ ያለዉ ከሆነ ብቻ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት ቀርቦ ሊታረም ይችላል ማለት ነዉ። ከተጠቀሱት ዉጭ የሰበር ሰበር አልተፈቀደም።
3. በፍትሐ ብሄር ጉዳዮች የፌደራል ፍርድ ቤቶች የስረ-ነገር ስልጣን - አስር ሚሊዮን ብር
አንቀጽ 11 እና 14
በተሻረዉ አዋጅ 25/88 መሰረት የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የፍትሓብሄር የስረ ነገር ስልጣን እስከ አምስት መቶ ሽህ ብር (500,000 ብር) የነበረ መሆኑ ይታወሳል። በአዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 አንቀጽ 11(1) እና 14 መሰረት አዋጁ ከጸደቀበት ቀን ከጥር 13/2013 ጀምሮ በሚቆጠር ከ6 ወር[4] በኋላ ተፈጻሚ የሚሆን የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የስረ-ነገር ዳኝነት ስልጣን እስከ አስር ሚሊዮን ብር (10,000,000 ብር) ሲሆን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣን ደግሞ ከ አስር ሚሊዮን ብር (10,000,000 ብር) በላይ ነዉ። ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካካል የሚከተሉት ይገኙበታል።
- የዋጋ ግሽበት ማለትም የቀድሞዉ አዋጅ 25/88 ሲጸድቅ ከ25 ዓመት በፊት የነበረዉ አምስት መቶ ሽህ የመግዛት አቅም አሁን ላይ በምን ያክል ጨምሯል የሚለዉ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ነዉ፤
- በአዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 አንቀጽ 5(1)(ደ) ስር እንደተደነገገዉ እስከ አምስት መቶ ሽህ የሚደርሱ ገንዘብ፣ዉል እና ብድር ክርክሮች ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች የተሰጡ በመሆናቸዉ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ የፍታብሄር ጉዳዮች በተወሰነ መጠን የሚቀንስ መሆኑ፣
- የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚያስተናግዱት የጉዳይ አይነት ከበፊቱ የበለጠ እንደሚጨምር ቢታመንም አብዛኛዎቹን የፍታብሄር ጉዳዮችን ወደ ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲወርዱ ማድረግ የይግባኝ እድልን ከማስፋት በተጨማሪ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚታየዉ የጉዳዮች ፍሰት የፒራሚድ ቅርጽ እንዲይዝ በማድረግ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ እና ሰበር የሚቀርቡ ጉዳዮች ይቀንሳል። በዚህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች አነስተኛ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ጥራት ያላቸዉ ዉሳኔዎችን እንዲሰጡ እንዲሁም ለጥናት እና ምርምር የሚሆን በቂ ጊዜ እንዲኖራቸዉ ያስችላል።
4. ለአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ ፍርድ ቤቶች የተሰጡ የፍታብሄር ጉዳዮች -አንቀጽ 5(1)(ደ)
አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች በቻርተር አዋጅ የተሰጣቸዉ የፍታብሄር ዳኝነት ስልጣን ማለትም በወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መታወቂያ ወረቀት ሕግ መሰረት በሚሰጥ ሰነድ ጋር በተያያዘ፣ ከስም ለዉጥ፣ ከመጥፋት፣ የፍርድ ክልከላ፣ የባልነት ሚስትነት የአሳዳሪነት የሞግዚትነት ማስረጃ ይሰጠን ጉዳይ፣ የከተማዉ አስተዳደር ከሚያስተዳድረዉ ቤት ጋር በተያያየዘ በሚነሳ የይዞታ ወይም የባለቤትነት ወይም ሌላ ማንኛዉም ክርክር፣ በከተማዉ ዉስጥ ከሚገኝ እድር ጋር በተያያዘ የመዳኘት ስልጣን እንዳላቸዉ ይታወቃል።[5] በተጨማሪ በከተማ አስተዳደሮቹ በሚኖሩ ግለሰቦች መካከል የሚደረጉ እስከ ብር 500,000(አምስት መቶ ሽህ) የገንዘብ፣ ዉል፣ እና ብድር ክርክሮች የሚመለከቱ የፍታብሄር ክርክሮች በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሚዳኙ ይሆናል በሚል የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 በአንቀጽ 5(1)(ደ) ስር ተደንግጓል።
5. ማንኛዉም ይመለከተኛል የሚል አካል የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በቀጥታ ለፍርድ ቤት አቅርቦ ማስወሰን - አንቀጽ 11(4) –Public Interest Litigation
በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1134/2013 አንቀጽ 11 ንኡስ 3-5 ባሉት ድንጋጌዎች የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፍርድ ታይተዉ ሊዎሰኑ የሚችሉ በህገ መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ስር የተመለከቱ መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን ለማስከበር ለጉዳዩ ተገቢ የሆነ ፍርድ፣ትዕዛዝ ወይም ዉሳኔ የመስጠት ስልጣን እንዳለዉ ይደነግጋል። እንዲሁም ማንኛዉም ጉዳዩን ለማቅረብ በቂ ምክንያት ያለዉ ሰዉ መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን ለማስከበር ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ መብት እንዳለዉ ተገልጿል። የዚህ አይነቱን ጉዳይ ለማስተናገድ ጉዳዩ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የፍታብሄር ስነ-ሥርዓት ሕግ ቁጥር ከ177-179 እንደ አግባብነቱ ሊጠቀም ይችላል። ስለሆነም በጉዳዩ ላይ መብት ወይም ጥቅም ያለዉ ሰዉ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመዉሰድ በቂ ምክንያት ያለዉ ማንኛዉም ሰዉ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊሄድ ይችላል። ለምሳሌ፡ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር የተቋቋሙ የሲቪክ ማህበራት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሲኖሩ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢወስዱ በቅድሚያ ማሳየት የሚጠበቅባቸዉ ከተቋቋሙበት አላማ ጋር የሚገናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ ጉዳዩን ለማቅረብ በቂ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
6. የምድብ ችሎት ተጠሪ ዳኞች እና ሰብሳቢ ዳኞች የሚያከናዉኗቸዉ ተግባራት - አንቀጽ 21፣ 22 እና 23
የፌዴራል ከፍተኛ እና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተሞች ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ምድብ ችሎቶች አሏቸው፡፡ በተግባር እነዚህን ምድብ ችሎቶች የሚያስተባብሩት የየምድቡ ተጠሪ ዳኞች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የምድብ ችሎት ተጠሪ ዳኞች ደግሞ በምድብ ችሎቱ ያለዉን የእለት ከእለት ክንዉን የሚከታተሉ እና የሚቆጣጠሩ በመሆናቸዉ የሕግ እዉቅና ያስፈልጋቸዋል።ከሦስት በላይ ዳኞች በሚያስችሉ ችሎቶች ደግሞ ሰብሳቢ ዳኞች መኖራቸዉ እሙን ነዉ። ሰብሳቢ ዳኞች የግራ እና ቀኝ ዳኞችን ተሳትፎ የመቆጣጠር ኃላፊነት ሊሰጠዉ ያስፈልጋል።ስለሆነም ለተጠሪ ዳኞች እና ሰብሳቢ ዳኞች እዉቅና በመስጠት እና ሚናቸዉን በዝርዝር በማስቀመጥ ዳኞች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና ተገልጋዩ ሕዝብ በየእለቱ የሚያጋጥሟቸዉን ችግሮች በቅርበት በመከታተል መፍትሄ የሚሰጥ እንደመሆናቸዉ መጠን በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 ዉስጥ ተካቷል። ለዚህም ሦስትና ከሦስት በላይ የሆኑ ዳኞች በሚያስችሉባቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ችሎቶች ውስጥ ሰብሳቢ ዳኛ ሆነው የሚሰሩ ዳኞች ተግባራቸው ምን መሆን እንዳለበት የሚጠቅሱ እና አዋጅ ቁጥር 25/1988 ውስጥ ያልነበሩ ስለችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ሥልጣንና ተግባራቸው የሚጠቅሱ አዳዲስ አንቀጽ 22 እና 23 በ አዋጁ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ አንቀጽ 23 ላይ ሰብሳቢ ዳኛ የችሎቱ ሥራ በሕግ መሠረት መካሄዱን እና በችሎቱ የሚወሰኑ መዝገቦች በሁሉም የችሎቱ ዳኞች ግንዛቤ የወሰደባቸው መሆኑን ማረጋገጥ እንዲሁም ሁሉም የችሎቱ ዳኞች በችሎቱ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በማዘጋጀት ተመጣጣኝ ተሳትፎ ማድረጋቸውን መከታተል ያለባቸው መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ሰብሳቢ ዳኛው የተጠቀሱትን ተግባራት የችሎቱን ሌሎቹን ዳኞች የዳኝነት ነፃነት በማይጋፋ ሁኔታ መፈፀም እንዳለባቸውም ተጠቅሷል፡፡
7. የሰበር ፓናል ችሎት መቋቋም - አንቀጽ 26
በአዲሱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 ከአንቀጽ 26-28 ሰበር ችሎትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በዝርዝር ደንግጓል። በተሻረዉ አዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2(4) ላይ የሰበር ችሎቱ በአንድ ወቅት የሰጠዉን ዉሳኔ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ የተለየ ትርጉም ሊሰጥበት እንደሚችል የሚጠቅስ ነበር። ይህንንም ድንጋጌ መነሻ በማድረግ የፌደራል ሰበር ችሎት በተመሳሳይ ጭብጥ ላይ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የሕግ ትርጉሞችን ሲሰጥ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ቀድሞ የተሰጠዉ ትርጉም በግልጽ ሳይሻር እና መሻሩ አንኳን ሰይታወቅ በሰበር ችሎት የተሰጠ ሌላ የሕግ ትርጉም የሚገኝበት ጊዜ ስለነበር የሕግ ማህበረሰቡ በተለምዶ እርስ በርሱ የሚቃረን የሰበር ዉሳኔ አለ እስከማለት ደርሷል፡፡ ስለሆነም ይህን ችግር ለማስቀረት በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመታየት ላይ ካለ ጉዳይ ጋር ተመሣሣይነት ያለው አስቀድሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጡ አስገዳጅነት ያላቸው ውሳኔዎች የተለያየ አይነት የሕግ አተረጓጎም ይዘዉ ሲገኙ (እርስ በርሳቸዉ የሚቃረኑ ሆነዉ ሲገኙ) ጉዳዩ ከሰባት ያላነሱ ዳኞች በሚሰየሙበት የሰበር ችሎት ታይቶ ሊወሰን እንደሚችል በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጁ አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ (1) ላይ ተደንግጓል። ልብ ሊባል የሚገባዉ ጉዳይ ግን ይህ አንቀጽ በሰበር ዉሳኔ ተሰጥቶባቸዉ ያለፉ ጉዳዮች በድጋሚ ተንቀሳቅሰዉ እንዲታዩ አያደርግም።
8. የፌደራል ፍርድ ቤቶች የስራ ጊዜ - አንቀጽ 38
የፌደራል ፍርድ ቤቶች እና ዳኞች የስራ ሰዓት ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች የስራ ሰዓት ጋር ተመሳሳይ እንደሚሆን ይገልጽና የፌደራል ፍርድ ቤቶች በየአመቱ ከነሐሴ 1 እስከ መስከረም 30 ድረስ ዝግ መሆናቸዉን ይደነግጋል። የዳኞች የረፍት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕግ ማእቀፍ ወጥቶለት ሕዝብ አዉቆት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ አንድ ነገር ሆኖ ፍርድ ቤቶች ዝግ በሚሆኑበት ጊዜ የሚቀርቡ ጉዳዮች እጣ ፋንታ ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ለዚህ መፍትሄ አዋጁ ያስቀመጠ ሲሆን በትርፍ ጊዜ በሚሰሩ ዳኞች ፍርድ ቤቶቹ ከስራ ጊዜ ዉጭ አስቸኳይ ጉዳዮችን አንዲያስተናግዱ ይደነግጋል። ዝርዝሩ ጉዳዮችም በመመሪያ እንዲወሰኑ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰጥቷል።
9. የአስተዳደር ሰራተኞች ከሲቪል ሰርቪስ መዉጣት - አንቀጽ 39
ለዳኝነት ሥርዓቱ የሥራ ቅልጥፍናና ውጤታማነት የሰው ሀብት አስተዳደር ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአንቀጽ 39(1) መሠረት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የአስተዳደር ሠራተኞቻቸውን “የመመልመል የመቅጠርና የማስተዳደር ነፃነት አላቸው” ፡፡ ይህን ማሳካት ይቻል ዘንድ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች “ምልመላ፣ ምደባ፣ ዕድገት፣ ዝውውር፣ ሥልጠና፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ የጥቅማ ጥቅም ክፍያ” እና የዲሲፕሊን ጉዳይ የሚመራበትን ሕግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ለማስፈጸም በሚያወጣዉ ደንብ መሆኑን አንቀጽ 39(2) ይደነግጋል፡፡
ምንም እንኳን ደንብ የማዉጣት ስልጣን በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 77(13) መሰረት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተሰጠ ቢሆንም ፍርድ ቤት ነጻ እና ገለልተኛ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ይህንኑ ነጻነቱን ለማስጠበቅ በአስፈጻሚዉ በኩል ሕግ ሊወጣለት እንደማይገባ ግንዛቤ ተወስዷል። ስለሆነም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጁን ለማስፈጸም ደንብ ሊያወጣ እንደሚችል ተደንግጓል።
10. ለሴቶች፣ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች የተፋጠነ ፍትህ እና የሕግ ባለሙያ ድጋፍ -አንቀጽ 19(1)(ሰ)
የፌደራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች የጾታ ጥቃት የተፈጸመባቸዉ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ህጻናት እና አረጋዉያንን አስመልክቶ በፍርድ ቤቶች የሚከፈቱ መዝገቦች በተፋጠነ ፍትህ አገልግሎት እልባት እንዳየገኙ እና የሕግ ባለሙያ ድጋፍ እንዲሰጣቸዉ የማድረግ ግዴታ በአዋጁ አንቀጽ 19(1)(ሰ) ተጥሎባቸዋል። ይህም ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች የተሻለ የፍትህ ተደራሽነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል።
11. አስገዳጅ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ለፍትሓብሄር ጉዳዮች -አንቀጽ 45-48
የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ማለት መደበኛዉን የክርክር ሂደት መከተል ሳያስፈልግ በማስማማት ሙያ በተካኑ ኤክስፐርቶች እገዛ ተደርጎላቸዉ ግራ ቀኙ ተስማምተዉ ጉዳያቸዉን በአጭሩ እልባት እንዲያገኝ የሚደረግበት ሥርዓት ነዉ። ምንም እንኳን ባለጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት ከመምጣታቸዉ በፊት አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚለዉ ግንዛቤ እንዳለ ቢሆንም የፌዳርለ ፍርድ ቤቶች በበኩላቸዉ ባለጉዳዮቹ እንዲስማሙ ሁኔታዎችን አመቻችተዉ ወደ ክርክር ሂደት ሳይገባ በአማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴ ወይም አስማሚነት(Mediation) እልባት እንዳየገኙ ይደረጋል። እንደሚታወቀዉ ፍርድ ቤት መር አስማሚነት የሚሰጠዉ አገልግሎት አስማሚዎች በማስማማት ሙያ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የመስማሚያ ቢሮዎችን ማመቻቸት፣ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቶ የስምምነት አንቀጾችን አንዲጸድቁ ማድረግ እንዲሁም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ ሲሆን በፌደራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 አንቀጽ 45(1) እንደተመላከተዉ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እና ከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ ጉዳዮች በዋናነት የፍታብሄር ጉዳዮች ዉስጥ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያወጣዉ መመሪያ የሚወሰኑ በፍርድ ቤቶቹ በሚቋቋም የፍርድ ቤት መር አስማሚነት በኩል እንዲያልፉ ይደረጋል በማለት ደንግጓል። ይህ ማለት አንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት ክርክር ከመስተናገዱ ቀደም ብሎ በፍርድ ቤት መር አስማሚነት በኩል እልባት እንዲያገኝ እድል ያገኛል። መስማማት የባለጉዳዮቹ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሲሆን በፍርድ ቤት መር አስማሚነት በኩል ማለፍ ግን ለአንዳድ የፍታብሄር ጉዳዮች እንደ ግዴታ ይሆናል ማለት ነዉ።
በአዋጁ እንደተደነገገዉ ተከራካሪ ወገኖች በፍርድ ቤት መር አስማሚነት በኩል ጉዳያቸዉን በስምምነት ካልጨረሱ ይህንኑ የሚገልጽ በአስማሚዎቹ የተፈረመ ደብዳቤ ለፍርድ ቤት በማቅረብ የፍርድ ሂደቱ እንዲቀጥል ይደረጋል። የተስማሙ ከሆነ የስምምነቱ ሁኔታዎች በአስማሚዉ በግልጽ ተለይተዉ ከቀረቡ እና ተከራካሪዎቹ ከፈረሙበት ቡሃላ አስማሚዉ ይህን ሰነድ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ስምምነቱ ለሕግ እና ለሞራል ተቃራኒ አለመሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ እንዲጸድቅ ያደረጋል። የጸደቀዉ የስምምነት ሰነድ እንደማንኛዉም የፍርድ ቤት ዉሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል። በአንደኛዉ ተከራካሪ ወገን ያለመቅረብ ምክንያት የመስማማት ሂደቱ ካልተሳካ አስማሚዉ ይህንኑ በመግለጽ ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት ያደርጋል። መደበኛዉ የፍርድ ሂደትም ይቀጥላል።
ሌላዉ ከአስማሚነት ጋር ተያይዞ አዋጁ ከያዛቸዉ ጉዳዮች አንዱ በፍርድ ቤት መር አስማሚነትም ይሁን በሌላ አማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴ ግራ ቀኙ ከተስማሙ በደንቡ መሰረት ወጭዎች ተቀንሰዉ ባለጉዳዮች የከፈሉት የዳኝነት ክፍያ ተመላሽ ይደረግላቸዋል። ይህም ባለጉዳዮች በአማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴ ጉዳያቸዉን እንዲፈቱ የሚያበረታታ ድንግጌ ነዉ። የዚህን ድንጋጌ ለማስፈጸም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዝርዝር መመሪያ ያወጣል።
በአዋጁ አንቀጽ 46 ስር የአስማሚነት መርሆችን የያዘ ሲሆን በፍርድ ቤት መር አስማሚነት የሚደረገዉ ማንኛዉም ሂደት በእኩልነት እና በባለጉዳዮቹን ሙሉ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።በማስማማት ሂደቱ ተከራካሪ ወገኖች የሚሰጡት የእመነት ቃሎች ወይም ማንኛዉም ንግግሮች ለፍርድ ቤት በማስረጃነት አይቀርቡም። ለዚህም አስማሚዉ ማረጋገጫ ይሰጣል። በፍርድ ቤት አስማሚነት በኩል የሚደረጉ ማናቸዉም የሃሳብ ልዉዉጦች ሚስጥራዊነት የተጠበቀ ነዉ።
አንቀጽ 47 ደግሞ ስለ አስማሚዎች የደነገገ ሲሆን የአስማሚነት ስልጠና ወስደዉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያወጣዉን ምዘና ያለፉ ቢያንስ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸዉ እና ከአምስት አመት ያላነሰ ጊዜ በሕግ ሙያ ያገለገሉ አስማሚ ሆነዉ ሊመረጡ ከመቻላቸዉም በላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያዘጋጀዉ የአስማሚዎች ሮስተር መዝገብ ዉስጥ መካከተት እንዳለባቸዉ ይገልጻል። ይህ በግልጽ እንደሚያሳየዉ ብቁ የሆነ አስማሚ የሚገባበት የማስማማት ስራ ስኬታማነቱ አያጠራጥርም። ማስማማት ልዩ ሙያ እንደመሆኑ መጠን የስነ-ልቦና፣ ሕግ፣ ስነ-ምግባር እና ብስለትን የሚፈልግ ነዉ። ስለሆነም የአስማሚነት ክህሎት በቂ ስልጠና ያገኘ እና ተመዝኖ ብቁ የሆነ የሕግ ባለሙያ ብቻ አስማሚ ሊሆን እንደሚገባ እሙን ነዉ። የባለ ጉዳዮችንም በማን መስማማት እንዳለባቸዉ እንዲለዩ ለማድረግ የብቁ አስማሚዎችን ስም ዝርዝር የያዘ ሮሰተር መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑን ቢገልጽም አንዳንድ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ቋሚ የሆኑ ወይም በጊዜያዊነት ብቁ አስማሚዎችን ሊቀጥር እንደሚችል በአንቀጽ 47 ስር ተካትቷል።
አዋጁ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ክፍያን በሚመለከት በአንቀጽ 48 ስር የደነገገ ሲሆን። አስማሚዎችም ይሁን ተስማሚዎች የሚፍሏቸዉ የክፍያ አይነቶች እንደሚኖሩ ይገልጻል። አስማሚዎች የጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያወጣዉ መመሪያ የሚወሰን ለአስተዳደራዊ ጉዳይ እና አመታዊ ክፍያ ሊከፍሉ ይችላሉ። ይህም በብዙ ሀገሮች የሚተገበር ሲሆን ለአስተዳደራዊ ወጭዎች የሚሸፍን አነስተኛ ክፍያ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይህ አይነት አሰራር በሀገራችንም አዲስ አይደለም። ለምሳሌ የአእምሮአዊ ንብረት ጽ/ቤት የንግድ ምልክት ምዝገባ ወኪሎችን መዝግቦ ለመያዝ በአዋጅ ቁጥር 501/1998 አንቀጽ 44 እና ደንብ ቁጥር 273/2005 በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት የምዝገባ እና አመታዊ ክፍያ 1655 ብር ገደማ እንዲከፍሉ ይደረጋል። ሌላዉ የክፍያ አይነት በማስማመቱ ሂደት ዉስጥ የሚያልፉ ባለጉዳዮች ለፍርድ ቤት መር አስማሚነት የሚከፍሉት ሲሆን የክፍያዉ መጠን እና ሁኔታ በመመሪያ የሚወሰን እንደሚሆን በአዋጁ አንቀጽ 48 ተገልጿል። ተገቢዉን አመታዊ ክፍያ ከፍለዉ በሮስተር የተካተቱ አስማሚዎች በባለጉዳዮች ተመርጠዉ የማስማማት አገልግሎት ከሰጡ ተገቢዉ ክፍያ እንደሚከፈላቸዉ በአንቀጽ 48(2) ተደንግጓል። የፍርድ ቤት መር አስማሚነት ቀጣይነት እንዲኖረዉ አስማሚዎች ክፍያ ሊያገኙ እንደሚገባ መደንገጉ ተገቢ ነዉ። እዚህ ላይ ሊታሰብበት የሚገባዉ ጉዳይ አስማሚዎች የሚከፈላቸዉ ዝቅተኛ መጠን እና ባለጉዳዮች መክፈል የሚገባቸዉ ያገልግሎት ክፍያ ተመጣጣኝ እንዲሆን ጠቅላይ ፍርድ ቤት መመሪያ በተጠና መንገድ መሆን ይኖርበታል።
12. የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እና አዉቶሜሽን - አንቀጽ 49 እና አንቀጽ 50
የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡላቸዉን ጉዳዮች የሚስተናገዱበት ወይም የሚጠናቀቁበትን የጊዜ ሰሌዳ ገደብ ባለማስቀመጣቸዉ አንድ ጉዳይ መች ተጀምሮ መች እንደሚያልቅ ግልጽ የሆነ የጊዜ መጠን የላቸዉም። በዚህም ምክንያት የፍርድ ቤት ጉዳይ ማለቂያ ጊዜ ተገማች ያልሆነ እና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ነበር። ሆኖም በ አዋጁ አንቀጽ 49 ስር አንድ ጉዳይ ተጀምሮ እስከ ሚያልቅ ድረስ የጊዜ ሰሌዳ እንዲቀመጥ የሕግ ማእቀፍ በመስጠት የፍትህ አሰጣጥ ስርዓቱ የተሳለጠ እና ጥራቱ የሚረጋገጥበት የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስችል አንቀጽ ተካቷል። ለዚህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለማስፈጸም ዝርዝር መመሪያ እንደሚወጣ ይደነግጋል።የፌደራል ፍርድ ቤቶች በማንኛዉም የፍርድ ቤት ደረጃ የሚቀርቡ የፍታብሄር ወይም የወንጀል ጉዳይ ክርክሮች አዳዲስ የመረጃ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ዳጂታል ወይም አዉቶሜትድ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ ሥርዓት ሊዘረጉ እንደሚችሉ በአዋጁ አንቀጽ 50 ተቀምጧል ። ስለሆነም በቀጣይ ጊዜ ባለጉዳዮች ዶሴ ተሸክመዉ ፍርድ ቤት ከመምጣት ይልቅ የመረጃ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የክስ ጉዳይም ማንኛዉም አቤቱታ በዲጂታል መንገድ ወይም በሶፍት ኮፒ ለፍርድ ቤቱ በማስገባት በዘመነ መንገድ እንዲስተናገዱ ለማስቻል የሕግ መሰረት ተቀምጦለታል። ለዚህም ተከራካሪ ወገኖች በተዘረጋዉ ስርኣት መሰረት ክርክሮቻቸዉን የማካሄድ ግዴታ እንዳለባቸዉ በአዋጁ ተካቷል።ለዚህም ዝርዝሩ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መመሪያ መዉጣት እንዳለበት ግልጽ ነዉ።
13. የዉጭ አማካሪ ምክር ቤት ማደራጀት - አንቀጽ 53
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከቀድሞ የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ከፍተኛ ልምድ እና ብቃት ካላቸዉ የሕግ ባለሙያወች፣ ከዩኒቨርስቲ ምሁራን የተዉጣጡ ያለክፍያ የሚሰሩ የዉጭ አማካሪዎችን በመምረጥ የዳኝነት ሥርዓት የዉጭ አማካሪ ምክር ቤት ሊያደራጅ እንደሚችል አዋጁ በአንቀጽ 53 ይደነግጋል። በተጨማሪም የአማካሪ ምክር ቤቱ የፍርድ ቤቱን የዳኝነት ሥርዓት ለማሻሻል የሚረዱ አስገዳጅ ያልሆነ ምክር ሃሳቦችን በማመንጨት እንዲሁም ሌሎች በፍርድ ቤቱ የሚሰጡትን ስራዎች በማከናወን የፍርድ ቤቱን አስተዳደር ለማገዝ መሆኑን ያትታል። እንደሚታወቀዉ አዋጆችን ለማዘጋጀት ተመሳሳይ ምክር ቤት በርካታ ተግባራትን አከናዉኗል። አዋጁ በግልጽ እንደደነገገዉ አማካሪ ምክር ቤቱ ስራዉን በሚያከናዉንበት ጊዜ የዳኝነት ነጻነትን እና የዳኝነት ስነምግባርን በማይጻረር መልኩ በጥብቅ ዲስፕሊን እና በከፍተኛ ሀላፊነት ስራቸዉን ማከናዎን ይጠበቅበታል። ስለሆነም የዳኝነት ነጻነትን በማይጻረር መልኩ መስራት እንዳለበት መደነገጉ ተገቢ ነዉ።
14. የወንጀል ቅጣት - አንቀጽ 52 እና 53
በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ አንቀጽ 52 ላይ የተካተተዉ ንዑስ አንቀጽ (1) አዲስ ሲሆን ይዘቱም በማንኛውም የፌዴራል ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ እና ትዕዛዝ በህገ መንግሥቱ ላይ በተጠቀሰ ፍርድ ቤት ወይም ፍርድ ሰጪ አካል እስካልተሻረ ድረስ የፀና ሆኖ ተፈፃሚ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች የሚሰጧቸዉን ዉሳኔዎች ወይም ተእዛዞች በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ዉስጥ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 51 ላይ ተደንግጓል፡፡ በማንኛዉም ክልል ዉስጥ የሚገኝ የመንግስት አካል፣ተቋም ወይም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ወይም ማንኛዉም ሰው ውሳኔዎቹን ወይም ትእዛዞቹን የመፈጸም እና የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸዉ በአዋጁ መካተቱ የፍርድ ቤት ዉሳኔ ተፈጻሚ የሚሆንበትን የሕግ ሽፋን በመያዙ ከበፊቱ የተሻለ ነዉ።
በተለይም ማንኛዉም ሰዉ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ የተጣለበትን ግዴታ የማይወጣ ከሆነ በዚህ አዋጅና አግባብ ባለው ሌላ ሕግ ተጠያቂ ይሆናል። የፍርድ ቤት ወይም የዳኞችን በነጻነት መስራት የሚጋፋ ወይም በዳኞች ላይ ተጽእኖ የሚያደርግ ወይም ለማድረግ የሞከረ ማንኛው ሰዉ በሌላ ሕግ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ከሦስት ወር እሥራት ባላነሰ ከሁለት አመት ባላበለጠ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ በአንቀጽ 52(1) ስር ተካቷል። በተጨማሪም አንቀጽ 52(2) በግልጽ እንደሚያስቀምጠዉ የፍርድ ቤትን ትእዛዝ ወይም ዉሳኔ የማይፈጽም ወይም ለመፈጸም መሰናክል የሚፈጥር ወይም ሲጠየቅ ለመፈጻም ተባባሪ የማይሆን ማንኛዉም ሰዉ በሌላ ሕግ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ከሁለት አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ ገንዘብ እንደሚቀጣ ይደነግጋል። ይህ የቅጣት ድንጋጌ አዋጁ ጥርስ የሌለዉ አንበሳ እንዳይሆን ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሕግ ማእቀፍ ነዉ ተብሎ ይታመናል።
[1] Muradu Abdo, Review of Decisions of State Courts over State Matters by the Federal Supreme Court, Mizan Law Review, Vol. 1 No.1, June 2007, Page -
[2] ዝኒ ከማሁ።
[3] መሃሪ ረዳኢ፣ የሰበር ሰበርና ተግዳሮቶቹ በኢትዮጵያ፣ሚዛን ሎወ ሪቪዉ፣ 2015፣ ቅጽ 9፣ ቁጥር - 1፣ ገጽ 185.
[4] የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ 1234/2013 - አንቀጽ 56(2) እና አንቀጽ 58 መሰረት ከአንቀጽ 11-15 ተፈጻሚ የሚሆነዉ ከሀምሌ 13/2013 ጀምሮ ይሆናል ማለት ነዉ።
[5] የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ 361/1995.
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments