ሰሞኑን በአንድ ካፌ ገብቼ የተደረደሩ ቀን ያለፈባቸው ጋዜጦች ስመለከት የሪፖርተር ጋዜጣ በሚያዚያ 1/2009 የእለተ-እሁድ እትሙ ላይ “ሰበር ሰሚ ችሎት በክራውን ሆቴል የንግድ ምልክት ላይ የሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል ተባለ” በሚል ርእስ ባወጣው ዘገባ ላይ ዐይኔ አረፈ። ከዚህ በፊት በርካታ ጉዳዮች ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ስለመቅረባቸው አውቃለሁ። በሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ክርክር ተነስቶበት ወደ ጉባኤው ስለመቅረቡ ሳነብ ግን የመጀመሪያዬ ነው። ምናልባት እኔ ያላወቅኳዋቸው ተመሳሳይ ጉዳዮች ከዚህ በፊት ቀርበው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ርእሰ ጉዳዩ ቀልቤን ስለሳበው ባለጉዳዮቹ ስለተከራከሩበት ጉዳይና የችሎቱ ውሰኔ ለማወቅ ጉጉት አደረብኝ። እናም ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ስለተወሰደው የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔና ስለክርክሩ ከሥሩ ለማየት ወሰንኩ። ስለሆነም የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ቅጂ ፈልጌ በመመልከት የሚከተለውን የግል እስተያየቴን ለመጻፍ ውደድኩኝ።