ቼክ ጥሬ ገንዘብን ተክቶ በመገበያያነት አገልግሎት ላይ የሚውል የሚተላለፍ የንግድ ወረቀት አይነት ነው። በሀገራችን በቼክ መገበያየት እጅግ የተለመደ ተግባር ሲሆን ቼክም ሌሎች የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ካላቸው እውቅናና ተቀባይነት በላቀ አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለ እና በህብረተሰቡም ዘንድ እውቅና ያለው ሰነድ ነው። በሰነዱ ላይ ህብረተሰቡ የጣለው እምነትና በስፋት አገልግሎት ላይ መዋሉም በሰነዱ ላይ በተለያዩ ጊዜያት እና በስፋት የፍርድ ቤት ክርክሮች እንዲነሱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ እሙን ነው። ታዲያ በዚህ ሰነድ በስፋት አገልግሎት ላይ መዋልና በሕጋችን ውስጥ ሰነዱን አስመልክቶ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ማሻሻል እና ክፍተቱን መሙላት አስፈላጊና ለሰነዱ ቀጣይነትም አስተማማኝ ዋስትና ነው።