ግዴታ ህጋዊ ግንኙነት ሲሆን መሰረታዊ መርሁም የሚያካተው አንድ ዕዳ ያለበት ሰው ወይም ባለዕዳ ለአበዳሪው ዕዳውን የሚፈጽምበት ሂደት ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት ውስጥ ባለዕዳው ለአበዳሪው አንድን ነገር ለማድረግ ፣ ለመስጠት ወይም ላለማድረግና ላለመስጠት የሚያደርገው ህጋዊ ግዴታ ነው፤ በተቃራኒው ደግሞ አበዳሪው ከባለዕዳው የሚገባውን እና በሕግ የተፈቀደለትን ጥቅም የሚያገኝበት ሁነት ነው፡፡ ግዴታዎች ከሁለት ምንጮች ይቀዳሉ፤ የመጀመሪያው ከውል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሕግ ነው፡፡ ከውል የሚመነጭ የግዴታ አይነት በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ላይ የሚመሰረት ሲሆን ስምምነቱም በተዋዋይ ወገኖቹ ላይ እንደ ሕግ እንደሚያገለግል የፍትሐብሔር ህጉ አንቀጽ 1731 ያትታል፡፡ ሁለተኛው የግዴታ ምንጭ ደግሞ ከሕግ የሚመዘዝ ነው፤ የዚህ አይነት ግዴታዎች በቀጥታ ከሕግ የሚመነጩ ሲሆን ግዴታውም በባለዕዳው እና አበዳሪ ሰዎች ሊቀየር ፣ ሊሻሻል እንዲሁም ሊቀር አይችልም፡፡