የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሥልጣናቸውን የተመለከቱ የተለያዩ ክርክሮች ተነስተዋል፡፡ ዋናው ክርክር በተቋቋመበት ወቅት የተነሳው የሕገ መንግሥታዊነት ጭብጥ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 78 እስከ 80 የዳኝነት አካሉን ሲያዋቅር በተለያዩ ደረጃዎች ያሉት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች እንደሚቋቋሙ በመግለጽ የፍርድ ቤት ሥልጣን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚወሰዱ ጊዜያዊና ልዩ ፍርድ ቤቶች እንደማይቋቋሙ ደንግጓል፡፡
በአሁን ሰዓት በሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ማለትም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የከተማ አስተዳደሮች ህጋዊ ጥንስሳቸው የአዲስ አበባ ከተማ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው ሲሆን የድሬዳዋ ከተማ ደግሞ የቻርተር መሰረት ያለው ነው፡፡ በዚህም መሰረት በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49 (1) መሰረት የፌዴራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው በማለት ለከተማው እውቅና ሰጥቷል፡፡ የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 (2) የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለውም ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/96 የድሬዳዋ ከተማን በማቋቋም እራሱን በራሱ እንደሚያስተዳድር ደንግጓል፡፡