Font size: +
5 minutes reading time (1082 words)

የኢትዮጵያ ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት - የኢትዮጵያ ዜግነትን ያለባለሥልጣኑ (ኤጀንሲው) ውሳኔ መልሶ ማግኘት የማይቻል ስለመሆኑ

ሰሞኑን የአቶ ጀዋር መሐመድን ኢትዮጵያዊ ዜግነት መልሶ የማግኘት ጉዳይ በኦፌኮ እና በምርጫ ቦርድ መካከል ክርክሮችን ማስነሳቱን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየሰማን እንገኛለን፡፡ በመሆኑም የዜግነት ሕጉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት መልሶ ስለማግኘት ስላሰቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና ዜግነት መልሶ ማግኘት ስለሚረጋገጥበት መንገድ ያለኝን መረዳት ለማካፈል ወደድኩኝ፡፡

አቶ ጀዋር መሐመድ አስቀድመው የኢትዮጵያ ዜጋ የነበሩ በመሆናቸው ነገር ግን በሕግ ዜግነታቸውን ከቀየሩ በኋላ መልሰው ዜግነታቸው እየጠየቁ በመሆኑ ለዚህ ጉዳይ ተገቢነት ያለው ድንጋጌ ስለዜግነት የሚደነግገው የአዋጅ ቁጥር 378/96 አንቀፅ 22 እና 23/2/ሐ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም ኢትዮጵያዊ የነበረ ነገር ግን በሕግ የሌላ ሀገር ዜግነት ያገኘ ሰው የሚከተሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች ከተሟሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን መልሶ ያገኛል፤

  • አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ የነበረ መሆኑ፤
  • ወደኢትዮጵያ ተመልሶ በመምጣት መደበኛ መኖሪያውን በኢትዮጵያ ውስጥ ከመሠረተ፤
  • ይዞት የነበረውን የሌላ ሀገር ዜግነት ከተወ፤
  • ዜግነቱ እንዲመለስለት ለኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ባለሥልጣን ካመለከተ፤
  • ጥያቄው ለዜግነት ጉዳይ ኮሚቴ ቀርቦ በባለስልጣኑ ተቀባይነት ካገኘ፡፡

ከፍ ሲል በዝርዝር የተመለከቱ ጉዳዮች አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን መልሶ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታዎች በመሆናቸው እና እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የተሟሉ መሆን አለመሆናቸውን የማረጋገጥ እና የውሳኔ ሐሳብ የመሰጠት ሥልጣን ደግሞ የዜግነት ጉዳይ ኮሚቴ በመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 23/3 መሠረት የዜግነት ይመለስልኝ ጥያቄው በባለሥልጣኑ አማካኝነት ለኮሚቴው ቀርቦ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ለባለሥልጣኑ አቅርቦ መወሰን ይገባዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከፍ ሊል የተገለፁ ዝርዝር ጉዳዮች ራሳቸውን ችለው በርካታ የሕግ እና የማስረጃ ጥያቄ ሰለሚያስነሱ በአጭሩ ማብራራት አስፈላጊ ነው፡፡

አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ መሆን

የኢትዮጵያ ዜግነት የሚገኘው በሁለት መሠረታዊ መንገዶች ሲሆን አንደኛው ከኢትዮጵያውያን ወላጆች በመወለድ የሚገኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሕግ የሚገኝ ነው፡፡ በሕጉ በግልፅ በሕግ ዜግነት ስለማግኘት በተደነገገው የሕጉ ክፍል ባይካተትም አንደ ሰው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ካጣ በኋላ መልሶ ጠይቆ ሲያገኝም ራሱን የቻለ ዜግነት የማግኛ መንገድ በመሆኑ እንደ ሦስተኛ ዜግነት ማግኛ መንገድ ሊቆጠር ይችላል ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንደ ሦስተኛ መንገድ መቆጠር አለመቆጠሩ በውጤት ደረጃ የሚያሰከትለው ሕጋዊ ውጤት ስላለ እንዲሁ እንደተፈለገ የሚበየን ጉዳይ ባለመሆኑ በዚህ የጽሑፍ ክፍል አቋም ከመያዝ እቆጠባለሁ፡፡ የመጀመሪያውን መንገድ በተመለከተ አንድ ሰው ከኢትዮጵያውያን ወላጆች መወለዱን በማረጋገጥ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያገኛል፡፡ (እዚህ ጋር ሕጉ በኢትዮጵያ ውስጥ በመወለድ ብቻ ኢትዮጵያዊነት እንደሚገኘ በሥራ ላይ ያለው ሕግም ሆነ የቀደመው ሕግ ስለማይደነግግ ወላጆቹ ራሳቸው ኢትዮጵያውያን መሆናቸው በምን ይረጋገጣል የሚል ጥያቄ ቢቀርብ አጥጋቢ መልስ በሕጉ ላይ አናገኝም፡፡ ምክንያቱም በሕጉ መሠረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሚገኘው ከኢትዮጵያዊያን በመወለድ ከሆነ ወላጆቹ ኢትዮጵያውያዊነታቸውን እንዴት አገኙ የሚል የማያልቅ እና ለመመለስ አስቸጋሪ የሆነ ጥያቄ ስለሚያሰነሳ ነው) ስለዚህ ጉዳዮ የነበረን ዜግነት መልሶ የማግኘት ጉዳይ በመሆኑ አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማረጋገጥ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ሁለተኛው እና በሕግ ዜግነትን የማግኘት ጉዳይ ዝርዝር እና በርካታ ጉዳዮች የያዘ በመሆኑ እና ለዚህኛው ጽሑፍ ዓላማ ጠቃሚ ባለመሆኑ አልፌዋለሁ፡፡

መደበኛ ኑሮን ኢትዮጵያ ውስጥ መመሥረት

ሌላኛ ቅድመ ሁኔታ መደበኛ ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ መመሥረት ሲሆን መደበኛ ኑሮን በኢትዮጵያ ውስጥ መመሥረት ማለት ደግሞ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 183 ላይ በተገለፀው አግባብ ጠያቂው በኗሪነት አይነት ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖር ሐሳብ የጉዳዮቹ እና የጥቅሞቹ ዋና ስፍራ ኢትየጵያ ውስጥ ማድረግ እና ይህኑ ማረጋገጥ ነው፡፡ በኗሪነት በመኖር ሃሳብ እና ዋና ጥቅምን በኢትዮጵያ ውስጥ ማድረግ የሚለው የሕግ አነጋገር አካራካሪ እና በቀላሉ ለመወሰንም አስቸጋሪ ነው፡፡ የቃላቶቹ ጥቅልነት ሕጉ ለቃላቶቹ ግልፅ የሕግ ትርጉም አለመስጠቱ ደግሞ በዚህ ዙሪያ ብቻ በርካታ የሕግ እና የማስረጃ ክርክሮች ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች የፍሬ ነገር እና የሕግ ጉዳዮች በመሆናቸው ከፍ ሲል በተገለፀው አግባብ አመልካቹ መደበኛ ኗሪነቱን ለኮሚቴው በማስረጃ ማረጋገጥ ይኖርበታል በዚህ ጊዜ ታዲያ በርግጥ በመኖር ሃሳብ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው? ዋና ጥቅሞቹስ ኢትዮጵያ ውስጥ ናቸው? ዋና ጥቅሞች የሚባሉት ምን ምን ናቸው? የሚሉት ጉዳዮች በኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የሌላ ሀገር ዜግነትን መተው

ዜግነትን መልሶ ለማግኘት ሌለኛው ቅድመ ሁኔታ አስቀድሞ የያዘውን ዜግነት መተው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ጥምር ዜግነትን የማትፈቅድ ሀገር እንደመሆኗ የኢትዮጵያን ዜግነት መልሶ ለማግኘት የቀደመውን ዜግነቱን መተውን የሚጠይቅ በመሆኑ ዜጋ ነበር የተባለበት ሀገርን ዜግነት የተው ስለመሆኑ በቃል ከመግለፅ ባለፈ በተጨባጭ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ አስቀድሞ ዜጋ የሆነባት ሀገር ዜግነትን ለመተው ቅድመ ሁኔታ ያሰቀመጠች ከሆነ ይህው ቅድመ ሁኔታ መሟላቱ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ምን አይነት ቅድመ ሁኔታ ካላስቀመጠች ደግሞ የቀደመ ዜግነቱን መተውን ብቻ ለባለስልጣኑ በማሳወቁ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው የኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ትቷል ለማለት ዜግነቱን መተውን ባለስልጣኑ ባስቀመጠው ወይም ባዘጋጀው ቅፅ መሠረት ለባለስልጣኑ ማሳወቅን ይጠይቃል፡፡ በተለይ ደግሞ በሕግ የተጣለበት ብሄራዊ ግዴታዎች ካሉበት እነሱን ካልተወጣ ወይም በወንጀል ተከሶ ወይም ተቀጥቶ ከሆነ ከክሱ ነፃ ካልሆነ ወይም ቅጣቱን ካልፈፀመ በስተቀር መልቀቂያ አይሰጠውም በሚል የአዋጁ አንቀፅ 19/4 ይደነግጋል፡፡ ሌሎች ሀገሮችም የየራሳቸው ቅድመ ሁኔታ ያላቸው እንደ መሆኑ አንድ ሰው የቀደመ ዜግነቱን ትቷል ለማለት የጠያቂውን የቀደመ ዜግነት ሕግ ፈትሾ በዚሁ አግባብ ዜግነቱን መተውን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ የማስረጃ እና የሕግ ጉዳዮችን ስለሚያስነሳ የዜግነት ኮሚቴው መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ የሚሰጥት ነጥብ ይሆናል፡፡

ዜግነቱ እንዲመለስለት ለባለስልጣኑ ማመልከት

ይህኛው ቅድመ ሁኔታ የጠያቂውን ለባለስልጣኑ ማመልከትን የሚጠይቅ ብቻ በመሆኑ እና ባለስልጣኑም እንዲህ አይት ጥያቄ ሲቀርብለት ጉዳዩን ለዜግንት ጉዳይ ኮሚቴ የመምራት ግዴታ ያለበት በመሆኑ ጠያቂው ማመልከቻውን ለባለስልጣኑ በማቅረቡ ብቻ የሚረጋገጥ ፍሬ ነገር በመሆኑ የሚያስነሳው የተለየ አከራካሪ ጉዳይ ላይኖር ይችላል፡፡

ባለለስልጣኑ (ኤጀንሲው) ጥያቄውን ስለመቀበሉ

የመጨረሻው ዜግነት መልሶ የማግኘት ቅድመ ሁኔታ የቀረበው ማመልካች በዜግነት ጉዳዮች ኮሚቴ ማመልከቻው ተመርምሮ ከፍ ሲል የተገለፁ ጉዳዮች በሕግ እና በማስረጃ ረገድ መሟላታቸው ሲረጋገጥ ኮሚቴው በአብላጫ ድምፅ ወይም እኩል ድምፅ ከሆነ ሰብሳቢው ድምፅ የሰጠበት አመልካቹ ዜግነቱን መልሶ ለማግኘት የሚጠበቅበትን ያሟላ ስለመሆኑ የውሳኔ ሃሳብ ለባለስልጣኑ መስጠት ይኖርበታል፡፡

ባለስልጣኑ (ኤጀንሲው) የውሳኔ ሃሳብ ሲቀርብለት ስለሚያደርገው ነገር በሕጉ ያልተገለፀ በመሆኑ ጉዳዩ አካራካሪ መሆኑ የሚጠበቅ ቢሆንም ጉዳዩ በሕግ ያልተደነገገ ክፍተት በመሆኑ ወይም በመመሪያ መሸፈን ሲገባው መመሪያ ባለመውጣቱ (መመሪያውን በስንፍናየ ወይም በሚመለከተው አካል ድክመት መኖሩን ባለማወቄ የለም ብየ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ) የተፈጠረ ክፍተት ስለሚሆን ኮሚቴውም ሆነ ባለስልጣኑ የአመልካቹን መብት ወይም ሕጉ ሊከላከከለው የፈለገውን ዓላማ ሳይጎዳ አንድ ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በዚህ ጸሐፊ እምነት ኮሚቴው የሚያቀርበው የውሳኔ ሃሳብ ብቻ እንጅ ውሳኔ ባለመሆኑ በመጨረሻ የኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳብ መነሻ በማድረግ ውሳኔ የሚሰጠው ባለስልጣኑ መሆኑን ከሕጉ መንፈስ መረዳት ይቻላል፡፡ ኮሚቴው የተዋቀረው ከፍትሕ ሚንስቴር በአሁኑ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፤ በውጭ ጉዳይ፤ በፌደራል ፖሊስ እና በራሱ በባለስልጣኑ (ኤጀንሲው) በመሆኑ የኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳብ በግልፅ ከሕግ ጋራ የሚቃረን ካልሆነ በቀር የመቀበል ግዴታ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ የውሳኔውን ሃሳብ ከተቀበለ ደግሞ ለአመልካቹ ማመልከቻውን በመቀበል ኢትዮጵያው ዜጋ መሆኑን የሚያሳይ ማስርጃ ሊሰጠው ይገባል፡፡

ስርተፍኬት መስጠት አለመስጠትን በተመለከተ ብሎም የኮሚቴውን የውሳኔ ሃሳብ መቀበል አለመቀበልን በተመለከተ ሕጉ የሚለው ነገር ባለመኖሩ በመመሪያ ክፍተቱ መሙላት እንደተጠበቀ ሆኖ መመሪያ ባይወጣም በሕጉ መንፈስ እና ዓላማ ላይ በመመሥረት ባለሥልጣኑ ውሳኔ የመስጥት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ከፍ ሲል እንደተብራራው ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መልሶ ማግኘት እንደተጠየቀ ወይም ቸአመነልካቹ በራሱ የሚጠበቅብኝ አሟልቻለሁ ብሎ በማሰቡ ወዲያውኑ የሚገኝ ሳይሆን ሟላቱን የማረጋገጥ ሥልጣን የተሰጠው ኮሚጠየ የሚመረምረው በመሆኑ ከምርመራው በኃለሰ ማመልከቻው ተቀባይነት ያገኘ ወይም ያላገኘ መሆኑን በተመለከተ ማስረጃ መስጠጥ ደግሞ የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህ ባለስልጣኑ ጥያቄውን ከተቀበለ መቀበሉን እና ካልተቀበለም አለመቀበሉን በፅኁፍ አረጋግጦ ማሰረጃ ለአመልካቹ ወይም ማሰረጃውን ለሚፈልግ አካል የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባር ደግሞ ወደፊት በጉዳዩ ላይ የሚነሱ ክርከሮችን አስቀድሞ እልባት ስለሚሰጥ በተለይ ደግሞ አመልካቹ በውሳኔው ቅር ከተሰኘ መብቱን በሌላ የሕግ አግባብ እንዲያስከብር ከምርመራው በኃላ የማመልከቻውን ውጤት የሚገልፅ ማስረጃ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ማስረጃ መስጠት አለመስጡ አካራካሪ ነው ቢባል እንኳ በማመልከቻው ላይ ውሳኔ የመሰጠት የማይታለፍ ሥልጣን ግን የባለስልጣኑ እና የዜግነት ጉዳይ ኮሚቴው መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡

በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ለባለስልጣኑ (ለኤጀንሲው) በፃፈው ደብዳቤ ምንም እንኳ ጉዳዩን መርምሬ ከአዋጁ አኳያ ውሳኔ ማሳረፍ ብችልም በማለት የገለፀው ሐረግም ሆነ ኦፌኮ በአዋጁ መሠረት አመልካቹ የሚጠበቅባቸውን ስላሟሉ ኢትዮጵያዊ ሆነዋል በማለት በደብዳቤቸው ላይ የገለፁት አነጋገር በሕግ በግለፅ ለዜግነት ኮሚቴ እና ለኤጀንሲው የተሰጠን ሥልጣን መጋፋት በመሆኑ ተገቢነት የለውም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የዜግነት ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ የቅድመ ሁኔታዎቹ ቅድመ ሁኔታ ስ...
የውርስ ጉዳይን የተመለከቱ የይርጋ ገደቦች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024