የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅና መመሪያ ይዘት አጭር ማብራሪያ
መንግሥት ብቻውን የሀገሪቱን የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሥራዎች ማከናወን የማይችል ከመሆኑ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሥራዎች ላይ የራሱን የሆነ ድርሻ ሊወጣ የሚገባው መሆኑን ተከትሎ በዚህ ረገድ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚኖረውን የሥራ ግንኙነት ለመወሰን እና በሕግ አግባብ ለመምራት ይቻል ዘንድ መዉጣቱ ይታወሳል፡፡
አዋጁም ዋና ዓላማ አድርጎ የያዛቸው ጉዳዮች በአዋጁ አንቀጽ 3 ስር እንደተመላከቱት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ሊያግዙ የሚችሉ እና በግል ባለሀብቶች ፋይናንስ ሊደረጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን መደገፍ፤ የሕዝብ አገልግሎት ተግባርን የአቅርቦት መጠን እና ጥራት ማሻሻል፤ እና የመንግሥት የዕዳ ዕድገትን በመቀነስ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ማድረግ የሚሉ ጉዳዮችን ነው፡፡
የአዋጁ የተፈፃሚነት ወሰንም በአዋጁ አንቀጽ 4 ላይ እንደተቀመጠው በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሚተገበሩ የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክቶች ላይ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2(9) ስር ተተርጉሞ እንደሚገኘው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ማለት ደግሞ ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግሥት በጀት የሚተዳደር ማናቸውም የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤት ነው፡፡
ከይዘት አንፃር አዋጁ በዋናነት ሊገዛቸው የፈለጋቸው የመንግሥትና የግል አጋርነት ግንኙነቶች መካከል የመንግሥትና የግል አጋርነት ዓይነቶች፤የመንግሥትና የግል አጋራነት አስተዳደር፤ የቦርድ ኃላፊነት፤ የተዋዋይ ባለሥልጣን ተግባርና ኃላፊነት፤ የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት የማዘጋጀትና የማፀደቅ ሂደት፤የግል ባለሀብት መረጣ ሂደት፤ የጨረታ ዓይነቶች፤ የፕሮጀክት ኩባንያ አመሰራረት፤ወዘተ ዓይነት ድንጋጌዎች ይገኙበታል፡፡
አዋጁን ተከትሎ የወጣው ሌላኛው የሕግ ማዕቀፍ ደግሞ የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅ ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር 55/2010 ሲሆን የመመሪያው ዋና ዓላማም አዋጁን ማስፈፀም ሲሆን የተፈፃሚነት ወሰኑም የአዋጁ የተፈፃሚነት ወሰን ነው፡፡
መመሪያው ከያዛቸው ዝርዝር ድንጋጌዎች መካከልም የመንግሥትና የግል አጋርነት የቦርድ አባላት ብዛት፤ ስብጥር ፤የአሰራር ሥርዓት፤ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘው የመንግሥትና የግል አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ሊኖረው የሚችለው የቴክኒክ ድጋፍ ዓይነቶች፤ የተዋዋይ ወገን ተግባርና ኃላፊነት፤ የፕሮጀክት አስተዳደር ቡድን የአሰራር ሥርዓት፤ የፕሮጀክት ልየታ ሥርዓት፤ የፕሮጀክት አዋጭነት ጥናት፤ የግል ባለሀብት የመረጣ ሂደት፤ የመወዳደሪያ ሃሳቦች የግምገማ ሥርዓት፤ ወዘተ ዓይነት ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡
ከሌሎች ሕጎች በተለየ ሁኔታ የመንግሥትና የግል አጋርነትን አዋጅ ቁጥር 1076/2010 ከአንቀጽ 44-63 ድረስ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅ ማስፈፀሚያ መመሪያ ቁጥር 55/2010 ከአንቀጽ 26 እስከ 28 ድረስ የጨረታው አሸናፊ የግል ባለሀብት የሚጠበቅበትን ኩባንያ ካቋቋመ በኋላ ኩባንያው ከመንግሥት ጋር ውል ሲገባ የውሉ ይዘት ምን መምሰል እንዳለበት የሚወስኑ ድንጋጌዎችን ይዘዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የተቋቋመው ኩባንያ ከመንግሥት ጋር ውል ሲገባ ውሉ በዋናነት ሊያዘቸው የሚገባ ድንጋጌዎች ናቸው ተብለው በአዋጁ ከተዘረዘሩት መካከል የስምምነቱ የቆይታ ጊዜ፤ ዋጋ፤ የስምምነቱ ገዥ ሕግ፤ ከመንግሥት ስለሚደረገው ድጋፍ፤ ስለ ንብረት ባለቤትንት፤ የሥራ አፈፃፀም ዋስትና፤ ወዘተ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ኩባንያ የማቋቋም ሂደቱም በተሻሻለው የኢትዮጵያ የንግድ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1243/2013 ድንጋጌዎች እና የመንግሥትና የግል አጋርነትን አዋጅ ቁጥር 1076/2010 አንቀጽ 44 መሠረት የሚመራ ይሆናል፡፡
የመንግሥትና የግል አጋርነት ፕሮጀክትን በአስተዳዳሪነት በበላይ የሚመሩ አካላትን በተመለከተም የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅ ቁጥር 1076/2010 እና ማስፈፀሚያ መመሪያው መመሪያ ቁጥር 55/2010 ዝርዝር ድንጋጌዎችን ይዘዋል፡፡ በአዋጁ ከተዘረዘሩት የአስተዳደር አካላት መካከል የመንግሥትና የግል አጋርነት ቦርድ፤ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘው የመንግሥትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄነራል፤ ተዋዋይ ባለስልጣን እና በተዋዋይ ባለስልጣን ስር የሚገኝ የፕሮጀክት አስተዳደር ቡድን የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የአስተዳደር አካላቱ ተግባርና ኃላፊነትም በአዋጁም በመመሪያውም በዝርዝር ተመላክቶ ተቀምጧል፡፡
ይህን ዘርፍ ለየት የሚያደርገው ሌላኛው ጉዳይ ዘርፉ ከመደበኛው የመንግሥት የግዥ ሂደት በተለየ መልኩ የሚመራ የግዥ ሥርዓት የሚከተል መሆኑ ነው፡፡ ይህም ሲባል ፕሮጀክቶች የሚመሩት በተለየ የፕሮጀክት ልየታ ስርዓት፤የአዋጭነት ጥናት፤ የቦርድ ማፀደቅ፤ እና የጨረታ ሂደትን የሚከተሉ በመሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተቀመጡ የጨረታ ዓይነቶችን ለመጥቀስ ያህል በግልፅ ጨረታ ዘዴ ባለሀብትን መምረጥ፤ በሁለት ደረጃ ጨረታ ባለሀብቱን መምረጥ እና በውድድር ላይ የተመሠረተ ውይይት የሚካሄድበት የግዥ ሂደት የሚሉት ናቸው፡፡ አዋጁ የግዥ መንገዶችን በዚህ መልኩ ካስቀመጠ በኋላም እያንዳንዱ የግዥ መንገድ በምን ዓይነት ሥርዓትና ሂደት መመራት እንዳበትም ጭምር ደንግጓል፡፡
በአጠቃላይ አዋጁም መመሪያውም የራሳቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎን ቢኖራቸውም በአንፃራዊነት ዘርፉ የተሻለ የሕግ ማዕቀፍ እንዳለው ይታመናል፡፡
ሆኖም እስካሁን ድረስ በዚህ ዘርፍ በሀገሪቱ ውጤታማ የሆነ ፕሮጀክት እምብዛም ባይታይም ሥራዎችን ግን በአጋርነት ከመስራት አንፃር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸው እሙን ነው፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments 1
ይህ የብሎግ ልጥፍ አስደናቂ ነው፣ ብዙ ጠቃሚ ቅርጸ-ቁምፊዎችን ሰጠኝ።