Font size: +
14 minutes reading time (2702 words)

የኑሮ ውድነት እና የሸማቾች መብት ጥበቃ በኢትዮጵያ ሕግ

በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 51 እና 55 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የፌደራል መንግሥቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እንደ ኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር 2006 ዓ.ም የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃን በአንድ የሚመራ የሕግ ማዕቀፍ ያዘጋጀ ሲሆን የዚህ ሕግ አላማ ተደርገው በአዋጅ ቁጥር 813/2006 መግቢያ ላይ ከተቀመጡ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው ነገር ለሸማቹ ማህበረሰብ ጤናማ የሆነ የግብይት ሥርዓት መዘርጋት እና ከአወጣው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የንግድ እቃ ወይም አገልገሎት እንዲያገኝ ማስቻል ነው። ይህን ጠቅላላ አላማም በአዋጁ ውስጣዊ ክፍሎች በተካተቱ በርካታ የሸማቾች መብቶች እና የንግዱ ማህበረሰብ ግዴታዎች ድንጋጌ ተደራሽ ለማድረግ ተሞክሯል።

ሆኖም ግን ከዚህ አዋጅ እሳቤ እና ጠቅላላ አላማዎች በተለየ መልኩ በተለያዩ ጊዜአት ለሸማቹ ማህበረሰብ ጀሮ የሚሰጥ እና በአዋጁ የተደነገጉ መብቶቹን አክብሮ የሚያስከብርለት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ ምክንያት በተለያዩ ወቅቶች ቅርፅ እና ምክንያታቸውን እየለዋወጡ በሚከሰቱ የኑሮ ውድነት ሰቆቃዎች ገፈት ተሸካሚ ሆኖ ቆይቷል አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ላይ ይገኛል። የእራሱ የኑሮ ሁኔታ የታችኛውን እንዳያይ ከልክሎት ይሆን ሀላፊነቱን ካለመገንዘብ የሕግ አስፈፃሚው አካልም ከወሬ የዘለለ ተግባር ውስጥ ሲሳተፍ አይስተዋልም አንዳንድ የተወሰዱ እርምጃዎችን ብንመለከትም ዘላቂነት የሌላቸው ለፕሮፖጋንዳ እና ለሚድያ ሽፋን ብቻ ታይተው የሚጠፉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሸማቾ ህይወት ዘወትር ከድጥ ወደ ማጡ ነው ጀሮ ሰጦ ለመፍትሄው የሚሰራለት ቆራጥ የሆነ አካል ማግኘት ተስኖታል። የዚህች አጭር የግል ምልከታን መሠረት ያደረገች የሕግ እና ማህበረሰብ ተኮር ፅሁፍ አላማም ከወቅቱ የዋጋ ግሽበት እና ኑሮው ውድነት አኳያ የኢትዮጵያ የሸማቾች ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍ በመንግሥ፣ በእራሱ በሸማቹ ማህበረሰብ እና በነጋዴው ላይ የሚጥላቸውን ሃላፊነቶች ማመላከት እና ለተግባራዊነታቸው የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማጠየቅ ነው።

1. የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት ወቅታዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ

አሁን ባለንበት የገብያ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን የሀገራችንን ሁኔታ ስንገመግመው የሸቀጦች፣ የአዝርት፣ የአገልግሎቶት እንዲሁም የተለያዩ ለእለት ፍጆታ የሚያስፈልጉ እቃዎች ዋጋ ከእለት ወደ እለት አላግባብ እያሻቀበ ያለበትን ሁኔታ በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን። ይህንም የዋጋ ንረት ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ወገኖቻችን የሚያገኙት እለታዊ ገቢ ከቀደሙ ጊዜያት በባሰ ሁኔታ የእለት ፍጆታቸውን መሸፈን ከማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት በኑሮ ውድነት እሳት ውስጥ ገብተው እየተቃጠሉ ይገኛሉ።

የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ተከትሎ እለታዊ ገቢው አብሮ እየተቀየረ የማይመጣ በርካታ የማህበረሰብ ክፍል በሚኖርባት ሀገር ውስጥ እንደዚህ አይነቱ ያልታሰበ ዱብዳ ይዞ የሚመጣው ሰብዐዊ ቀውስ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። የታችኛውን ማህበረሰብ በሚጎዳ መልኩ እና ይህ ማህበረሰብ መብቱን ጠይቆ ከነጋዴው እኩል ተደራድሮ ጥቅሙን ማስጠበቅ በማይችልበት ሁኔታ ላይ እንዳለ እየታወቀ የንግዱን ማህበረሰብ ያለ ማሰሪያ ገመድ በስመ ነፃ የገብያ ስርዐት ለቆ የሸማቹን ማህበረሰብ መሠረታዊ ደህነነት አደጋ ላይ ሲጥል ቆሞ እንደመመልከት የሚያሳዝን እና ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ የለም።

የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት አስመልክቶ የነጋዴው ማህበረሰብ ዘንድ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እንደ መንስኤ ተደርጎ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይስተዋላል። ሆኖም ግን ይህ የነጋዴዎች ተልካሻ ምክንያት ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም። እኛ ፈልገነው የመጣ የዋጋ ጭማሪ አይደለም እኛም የግድ ሆኖብን ነው የነዳጅ ዋጋ ላይ መንግሥት የጨመረውን ታሪፍ ተመልከቱ ነዳጅ ጠፍቷል በዚህም ምክንያት የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ጭማሪ ተደርጉአል የሚሉ እና ተመሳሳይ ነገሮች ነጋዴዎች በተደጋጋሚ ለሸማቹ የለምን ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ ነው ይህም የሚገኘው ፀባየኛ ነጋዴ ከተገኘ ነው አንዳንዱ ግን መልስም ሳይሻ በቀጥታ ከፈለግህ ግዛ ካልፈለግህ ተወው ነገ ስትመጣ በእጥፍ ጨምሮ ይጠብቅሀል የሚል ዛቻ አዘል መልስን ከወዮልህ ማስጠንቀቂያ ጋር ሸማቹን ግራ በማጋባት ውስጡ ያላመነበትን ክፍያ ፈፅሞ እንዲሄድ ያደርጉታል።

በተደጋጋሚ ወደ ሚነሳው ምክንያት ስንመጣ ነጋዴዎች ሁሉንም ጥፋት መንግሥት ላይ በመጫን እራሳቸውን ከደሙ ንፁህ አድርገው የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እየሆነ ላለው ነገር ሁሉ ሀላፊ እንዲሆን ሲከሱ ይታያሉ። የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው፣ የሸቀጥ እቃ የሚያሰራጨው፣ ቸርቻሪው እንዲሁ የብዕር ሰብሎች ሻጩ ሁሉም የነዳጅን ዋጋ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪውን በምክንያትነት ይዘው ጥብቅ ይላሉ። ነገርግን ይህ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪም ሆነ የትራንስፖርት ዘርፉ የታሪፍ እድገት በምንም መልኩ አሁን ለአለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት መከሰት ሁኔታ በየትኛውም መመዘኛ አሳማኝ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ አይችልም። ምክንያቱም በእየዘርፉ የተደረጉ የዋጋ ጭማሪዎች በነዳጅ ላይ ከተደረገው የዋጋ ጭማሪ እና የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሸያ እርምጃ አንፃር ስንመዝናቸው ተነፃፃሪ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ፈፅሞ የማይገናኙ የብዙ እጥፍ ልዩነት የታየባቸው ግልፅ ሆኖ ብዝበዛ የሚስተዋልባቸው የተጋነኑ ጭማሪዎች ናቸው። በአንዳንድ ዘርፎች የተደረገውን ጭማሪ ስንመለከት እንዲያውም በነጋዴው ዘንድ ኢሰብዓዊነት እንዴት እንደወረደ እና ማንአለብኝነት እንደገነነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። የተወሰኑ ዘርፎች ደግሞ ከነዳጅ ጋር ምንም የማይገናኙ ሆኖም ግን እኩል ምክንያትን ሲጠቅሱ ማስተዋል ትንሽ ፈገግ የሚያስብል ነገር ነው።

አሁን በሀገራችን የሚታዩ የዋጋ ግሽበቶች ነዳጅን እንደመነሻ ምክንያት አድርጎ በሕዝብ ላይ እየተፈፀሙ ያሉ አይን ያወጡ ዝርፊያዎች ናቸው። የነዳጅ ዋጋን እንደመነሻ ወሰዱት እንጅ የእቃ ወይም አገልግሎት ክፍያን ሲተምኑ እንደማነፃፀርያ አልተጠቀሙበትም። በእያንዳንዱ እቃ እና አገልገሎት ላይ የተጨመረው ዋጋ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ሊጨምር ይገባ ከነበረው ጭማሪ በብዙ እጥፍ የላቀ ነው። ስለሆነምን የነዳጅ ዋጋን እያነሱ ሕዝብን ለማታለል መሞከር ማንም ማሰላሰል የሚችል አዕምሮ ያለው ሰው ሊቀበለው የማይችለው ነገር ነው።

ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከተመለከትን በኋላ ከውስጣችን ሊፈጠር የሚችለው ጉዳይ የብዙው ሰውም ጥያቄ ሊሆን የሚገባው እንደ ሀገር እንደዚህ አይነት ችግር ሲፈጠር ችግሩን በሙሉ ሊቀርፍ የሚችል ወይም ደግሞ ባይቀርፈው እንኳ ሊያረጋጋ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ አለን ወይስ የለንም ከአለንስ ለተግባራዊነቱ እስከምን ድረስ ሄደናል የሚለው ይሆናል። የዚህ ፅሁፍ ቀጣይ ክፍልም ለእነዚህ ጥያቄዎች በተቻለ መጠን ምላሽ ሰጥቶ የሚያልፍ ይሆናል።

2. የኑሮ ውድድነትን ለመቆጣጠር የሚረዱ የኢትዮጵያ ሸማቾች ጥበቃ ሕግ ድንጋጌዎች

ከላይ በመግቢያችን ላይ ለማመላከት እንደሞከርነው በኢትዮጵያ አሁን ላይ ተግባራዊነት ያለው እና በሌሎች የንግድ ሥራን በተመለከቱ የሕግ ማዕቀሮች እየተደገፈ የሸማቾችን ጉዳይ እንዲገዛ በሥራ ላይ ያለው ዋነኛ ሕግ በ2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፀድቆ የወጣው አዋጅ ቁጥር 813/2006 ነው። ይህም ሕግ በውስጡ ሸማቹን ከነጋዴው ማህበረሰብ ያልተገባ እንቅስቃሴ ይጠብቃሉ ያላቸውን የሕግ ድንጋጌዎች በውስጡ አቅፏል። ስለ ንግድ ውድድር በመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች የሕጉ ክፍል የተደነገጉ ጉዳዮች ለሸማቾች ጥበቃ ቀጥተኛው ያልሆነ ጉልህ ሚና ያለቸው ቢሆንም በዋነኝነት ለሸማቾች ጥበቃ የተዘጋጁት የሕጉ ድንጋጌዎች የሚገኙት ግን የአዋጁን ሶስተኛ ምዕራፍ ከአንቀጽ 14 ጀምሮ ስንመለከት ነው።

እነዚህ የሸማቾች ጥበቃን የተመለከቱ የአዋጁ ድንጋጌዎች ለሸማቹ ማህበረሰብ በግብይት ወቅትም ሆነ ከግብይት በኋላ ምን አይነት ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ የሚያመላክቱ ናቸው። አዋጁ ለሸማቹ ማህበረሰብ በርካታ መብቶችን እና ለነጋዴው ማህበረሰብ ተነፃፃሪ ግዴታዎችን ያካተተ ሲሆን የእነዚህ ድንጋጌዎች መከበር ደግሞ በህገመንግሥቱ እና በተለያዩ አለም አቀፍ የቃልኪዳን ሰነዶች የሰፈሩ ሰብዓዊ መብቶችን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።

ከእነዚህ በርካታ የሸማቾች መብቶች ድንጋጌዎች መካከል የተወሰኑትን ወስደን ስንመለከታቸው ሸማቹን የዋጋ ንረትን ተከትሎ ከሚመጣ የኑሮ ውድነት መጠበቅን ታሳቢ አድርገው እንደወጡ መረዳት እንችላለን። ከላይ እንደተገለጸው አዋጁ ሥራ ላይ ከዋለባቸው አላማዎች አንዱ ዋነኛው አላማ የሸማቹን ማህበረሰብ ጤናማ የግብይት ሁኔታ ማረጋገጥ እና ከከፈለው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እቃ ወይም አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል እስከሆነ ድረስ እነዚህን መብትና ግዴታዎች ማካተቱ ተገቢና በስመ የገብያ ሥርዓት አግባብነት በሌለው ሁኔታ የግል ኪሳቸውን በድሆች ህልውና ላይ ለመሙላት የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለመቆጣጠር አመች ሁኔታን ይፈጥራል። እነዚህን የመብት እና ግዴታ ድንጋጌዎች ከያዝነው ርዕሰ ጉዳይ አኳያ ከሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን። በግብይት ወቅት ነጋዴው ለሸማቹ ሊተገብራቸው የሚገቡ ተግባራት እና የኑሮ ውድነቱ ከመከሰቱ በፊት ወይም በኋላ በመንግሥት ደረጃ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ብለን።

ሀ. በግብይት ሂደት ነጋዴው የሸማቹን መብት ከማስከበር አኳያ ሊከተላቸው የሚገቡ አሠራሮች

እነዚህ አሰራሮች በዋነኝነት የሸማቾች መሠረታዊ መብቶች መከበር ጋር የሚገናኙ ሲሆን የእነርሱ መከበር እና አለመከበር ደግሞ ሸማቾች ለአልተገባ ዋጋ ጭማሪ መዳረግ እና አለመዳረግ ጋር ጥብቅ ቁርጠኝነት አለው ይህን ተከትሎም የኑሮ ውድነት አደጋን ለመቀነስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። በዋነኝነት ነጋዴው ለሸማቹ የተሰጡ መብቶችን በሥርዓት ቢተገብር ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የማድረግ እድሉ ጠባብ ስለሚሆን አሁን የገባንበት አጣብቂኝ ውስጥም አንገባም ነበር ብንገባም ምክንያቱ ነጋዴው ሳይሆን ሌላ ውጫዊ ምክንያቶች በሆኑ ነበር።

ወደ መጀመሪያ የሆነው የዚህ ክፍል የመብት ድንጋጌ ስንሻገር በግብይት ወቅት ነጋዴው ለሸማቹ በበቂ ሁኔታ ስለሚገዛው እቃ በቂ መረጃ የመስጠት፤ አማርጦ እንዲገዛ እድል የመስጠት እንዲሁም በትህትና የማስተናገድ ግዴታ ያለበት ሲሆን እነዚህ መብቶች መከበራቸው ሸማቹ ተረጋግቶ የእቃውን ጥራት እንዲያስተውል ከማስቻሉም በላይ የእቃውን ደረጃ ከተጠራበት ዋጋ ጋር አመዛዝኖ አስፈላጊውን ድርድር አድርጎ የነጋዴውን የአቅርቦት ወጭ እና ትርፍን ታሳቢ ያደረገ ክፍያን እንዲፈፅም ያስችለዋል።

የበለጠ ለማብራራት ያክል አንድ ሸማች ወደ ንግድ መደብር ሲገባ ጀምሮ የሚዋከብ አማራጭ የለኝም ከገዛህ ግዛ የሚባል ከሆነ ስለእቃው ሁኔታ በዝርዝር ካልተገለፀለት ሻጩ የነገረውን ዋጋ አሜን ብሎ ከመቀበል በአለፈ ምክንያታዊ የሆነ ድርድር አድርጎ ዋጋውን የሚያስቀይርበት አማራጭ አይኖረውም ይህ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ነጋዴው የሚፈልአገው ብቻ እንዲሆን መንገዱን ስለሚያመቻች ለአልተገባ የዋጋ ንረት ከዚያም አልፎ የኑሮ ውድነትን ያስከትላል። አሁን በሀገራችን ያለው ሁኔታም አንዱ እና ዋነኛው መሠረቱ ነጋዴዎቻችን ከሸማቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የቃኙበት የተዛባ አካሄድ ነው። በእየ ንግድ መደብሩ ያለው የደንበኞች መስተንግዶ ደንበኛ ክቡር ነው የሚለውን የተለመደ ብሂል እንኳ ማስቀጠል ያልቻለ ሸማቾች በገንዘባቸው ለሚገዙት እቃ በነፃ እንደጠየቁ እየተሰደቡ እየተዋረዱ የሚስተናገዱበት አሰራር ነው ያለው። ይህ በሆነበት ሁኔታ ነጋዴዎቻችን ዋጋን አላግባብ መጨመርን እንደ መብት የሚቆጥሩበት ሰዓት ላይ መድረሳችን ሊያስገርመን አይገባም።

በሁለተኛ ደረጃ በዚህ ክፍል ልንጠቅሳቸው የሚገቡ ድንጋጌዎች ደግሞ ከነጋዴው የእቃዎችን ዋጋ ዝርዝር የንግድ መደብሩ ላይ በሚታይ መልኩ የመለጠፍ እና የእቃውን ዝርዝር ሁኔታ የሚያሳይ የፅሁፍ መግለጫ በአማረኛ/በእንግሊዝኛ ወይም በሌሎች አግባብነት ባለው ቋንቋ የማቅረብ ግዴታዎች ናቸው። እነዚህ ሁለት መሠረታዊ ድንጋጌዎች የእቃን/የአገልግሎትን ዋጋ ለአንዱ ከፍ ለሌላው ዝቅ እያደረጉ እንደ ነፋሱ አብረው የሚነፍሱ እና ከሰው ሰውን እየለዩ አላግባብ ትርፍን የሚሰበስቡ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር እና እርሱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችልን የዋጋ ግሽበት ለመከለል ሁነኛ መንገዶች ናቸው። በተለየ መልኩ ደግሞ የእቃ ዝርዝር መግለጫው ሸማቹ የእቃውን ዋጋ ከዝርዝር ሁኔታው አንፃር ገምግሞ የመግዛት እድል ስለሚኖረው ከመጀመሪያው ነጋዴው የዋጋ ተመን ሲሰራ የሸማቹን ስለእቃው የሚኖረውን እውቀት ከግምት ውስጥ ያስገባል።

አሁን በሀገራችን ያለውን አሰራር ስንመለከት ግን የዋጋ ዝርዝርን ከእቃው መግለጫ ጋር የማቅረብ ሁኔታ በነጋዴዎቻን ዘንድ አይታይም የፈለገውን ዋጋ ይጠራል ያልሰለቸ እና የነጋዴው ግልምጫ ፊቱን ያልመታው ተከራክሮ ሲያሰቀንስ ሌላው ደግሞ የተባለውን በመክፈል ከነጋዴው ጭቅጭቅ ለመዳን ሲጥር የብዝበዛው አካል ይሆናል። ከእነዚህ ድንጋጌዎች ጋር በተገናኘ በተጨማሪ ነጋዴዎች በንግድ መደብራቸው ለሽያጭ የቀረበን እቃ አልሸጥም የአገልግሎት መስጫን ይዘው አገልግሎት አልሰጥም ማለት እንዲሁም መደብራቸው ላይ ከተለጠፈው ዋጋ ጨምሮ መሸጥ አይችሉም። እነዚህ ግዴታዎችም በተመሳሳይ በእየቀኑ የሚጣሱ እና አሁን ለአለንበት የኑሮ ውድነት ችግር ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው።

ሌላኛው የአዋጁ ለዚህ ክፍል ጠቃሚ የሆነ ድንጋጌ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የሸማቾች መብቶች እና የነጋዴዎች ተነፃፃሪ ግዴታዎች በሽያጭ ውል ህጋችን አንቀጽ 2272 ከተገለጸው በተለየ መልኩ በሻጩ እና በሸማቹ ስምምነት ቀሪ ሊደረጉ የማይችሉ መሆናቸውን መደንገጉ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም ነጋዴዎች ከሸማቾች አንፃር የተሻለ የገብያ እውቀት እና የመደራደር አቅም ሊኖራቸው ስለሚችል ይህን የሸማቾች የእውነት እና የአቅም ማነስ ተጠቅመው እራሳቸውን ከሀላፊነት እንዳያሹ እና የሸማቾችን የመብት ጥሰት አስመልክቶ ለሚመለከተው አካል አቅርበው የማስወሰን እድል ቀሪ እንዳያርጉ ለመከለል ነው። ይህም የተዋዋይ ወገኖች የውል ሁኔታዎችን በተመለከተ በነፃነት የመወሰን መብት አንድ ልዩ ሁኔታ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን ሆኖም ግን ነጋዴዎች መብቶች መኖራቸውን እንኳ ከግምት ውስጥ በማይከቱበት የግብይት ሥርዓት ውስጥ እየኖርን ሥራየ ተብለው እነዚህን መብቶች ለማስወገድ የውል ይዘት ይቀርፃሉ ተብሎ አይታሰብም ሆኖም ግን የሸማቹም ሆይ የነጋዴው ንቃተ ህሌና እያደገ ሲሄድ ይህም ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑ አይቀርም።

ለ. በመንግሥት ደረጃ ከኑሮ ውድነቱ አስቀድሞ ወይም እንደተከሰተ ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች

መንግሥት የኑሮ ውድነት በሚከሰትበት ወቅት ገብያውን ለማረጋጋት እና ሚዛን የጠበቀ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ሊወስድ ከሚገባቸው የኢኮኖሚ እርምጃዎች ጎን ለጎን የሸማቾችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና በተከሰተው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ውስጥ የከፋ ጉዳትን ሳያስተናግዱ እንዲያልፉ ለማድረግ ሊወሰዱ የሚገባቸው ህጋዊ መፍትሔዎች በእየሀገራት የሸማቾች ጥበቃ ህጎች ላይ ተካተው እንመለከታለን። እነዚህ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆኑት በነፃ ገብያ እና በመንግሥት ጣልቃ ገብነት መካከል የተሰመረውን መስመር በመጣስ ይሆናል። ይህም የሚሆነው መንግሥት በዜጎቹ ላይ የተጋረጠን አደጋ ለመከላከል ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ውስጥ አንዱ በመሆኑ እና በስመ ነፃ ገብያ ዝቅተኛውን ማህበረሰብ በመበዝበዝ ተግባር ላይ የተሰማሩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ለመከላከል አስፈላጊ ስለሆነ ነው። በዚህም ምክንያት ይህ አይነቱ ጣልቃ ገብነት ምክንያታዊ እና አስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሸማቾች ጥበቃ የሕግ ማዕቀፍም ለእንደዚህ አይነቱ ምክንያታዊ የሆነ የመንግሥት በጣልቃ ገብነት በተወሰነ መልኩ እውቅና ሰጥቶ እንመለከታለን። የአዋጅ ቁጥር 813/2006 ድንጋጌዎችን ከአንቀጽ 23 ጀምሮ እስከ 26 ስናነብ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር የአልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ ሲኖር እና የሸማቹን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠር በመንግሥት ሊወሰዱ የሚገባቸውን ተገቢ እርምጃዎች ሕጉ ለማካተት እንደሞከረ ነው። እነዚህንም እርምጃዎች ለመወሰድ እና ለማስፈፀም በዋነኝነት ሥልጣን የተሰጠው በፌደራል ደረጃ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር በክልሎች ደግሞ የንግድ እና ገብያ ልማት ቢሮዎች ናቸው።

በአዋጁ ለእነዚህ የመንግሥት አካላት ከተሰጧቸው ሥልጣን እና ሃላፊነቶች መካከል በነጋዴዎች የሚደረግ ያልተገባ የእቃ ክምችትን ወይም ¾መደበቅ ተግባርን መቆጣጠር፤ ገብያ ላይ እጥረት ያለባቸውን የንግድ እቃዎች በሕዝብ ማስታወቂያ መግለፅ እና እነዚህን እቃዎች የሚደብቁ ወይም የሚያከማቹት ላይ ተገቢ የሆነ ህጋው እርምጃ መውሰድ እንዲሁም በመሠረታዊ የንግድ እቃዎች ወይም አገልግሎቶች ላይ ዋጋ መወሰን /price fixing/ እና ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት ዋነኞቹ ናቸው።

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ተግባራት ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ እያስገባ መንግሥት የሸማቹን ጥቅም እንዲያስጠብቅ በሕግ የተሰጡት ስልጣኖች ሲሆኑ አሁን ሀገራችን ከአለችበት ሁኔታ አንፃር ስንመለከታቸው በጣም አስፈላጊ እና አሁን ለአለንበት ያልታሰበ የኑሮ መመሳቀል ሁነኛ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ እርምጃዎች ናቸው። አሁን ሀገራችን እያስተናገደችው የምትገኘውን የዋጋ ንረት ተከትሎ የመጣ የኑሮ ውድነት እነዚህ እርምጃዎች ያንሱበታል እንጅ የሚበዙት ወይም እስኪ ቲንሽ እንየው የሚባልበት ወቅት አይደለም። ገብያውን እንዲቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የሀገሪቱ የመንግሥት አካል የተሰጠውን ሥልጣን ከወረቀትነት ወደ ተግባራዊነት ሊቀይር የሚገባበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው።

ሸማቹ አላግባብ ተዘንግቷል እና ወዴት ነህ ልንለው ይገባል። በየትኛውም አለም እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያለች በማደግ ላይ ያለ ሀገር ይቅር እና በበለፀጉት ሀገራትም ነፃ ገብያ ሥርዓት ከመርህ የሚወጡ አካላትን ለመቆጣጠር ቲንሽ ቁንጠጣን ይፈልጋል። ለዚህም ነው ሀገራት የሸማቾችን መብት የሚደነግግ ልዩ ሕግ አውጥተው የሚሰሩት እኛ ሀገርም በሕግ ደረጃ መብቶችን የማስቀመጥ ሥራ የተጀመረ ቢሆንም እስካሁን ግን ተግባራዊነቱ አጠያያቂ እንደሆነ ነው። በዚህ ዘርፍ ላይ ከነጋዴው ጋር ተጋፍጦ ለመሥራት በመንግሥት ሰዎችን ዘንድ ከባድ መዘናጋት አለ ከዚህ እንቅልፍ ልንወጣ ግድ ይለናል። የማንተገብረው ከሆነ ሕግ ሆኖ መውጣቱ አጉል ድካም ነውና። እጥረት ሳይኖር እጥረት የአለ አስመስለው ከሸማቹ የተጋነነ ዋጋ የሚጠይቁ እና ለአልተገባ ወጭ የሚዳርጉት እጥረት እንዳለባቸው በመንግሥት የተረጋገጡ እና የዋጋ ተመን የተወሰነላቸው እንደ ነዳጅ እና የመሳሰሉትን ደግሞ ደብቀው አቆይተው ከእጥፍ በላይ ዋጋ እየጨመሩ በጓሮ በር የሚቸበችቡት ላይ መንግሥት ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር አድርጎ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ሊያስተካክላቸው ግድ ይለዋል። በሚድያ እና በተለያዩ የመናገሪያ አውታሮች ወጥቶ ከመዛት በአለፈ በአይን የሚታዩ ተግባራዊ የሆኑ እርምጃዎችን ይሻሉ።

መሠረታዊ የንግድ እቃዎችን በተመለከተም መንግሥት በአዋጁ በተጣለበት ሀላፊነት መሠረት አስፈላጊውን የገብያ ጥናት በአጭር ጊዜ ውስጥ አድርጎ ዝርዘር የሆነ የመሠረታዊ እቃዎች እና አገልግሎቶች የዋጋ ተመንን ለሕዝብ ይፋ ሊያደርግ ይገባዋል። ለተፈፃሚነቱም ከሕዝብ ጋር ተባብረው የሚሰሩ ሀቀኛ ሰራተኞችን አሰማርቶ በንቃት ሊንቀሳቀስ ግድ ይለዋል ምክንያቱም የዋጋ ተመን ማውጣቱ ብቻውን መፍተሔ ሊሆን ስለማይችል። እነዚህን እና ሌሎች መሰል ተግባራትን መፈፀም ካልተቻለ ግን ልክ ከአሁን በፊት ሲከሰቱ እንደነበሩ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነቶች ድሀውን ሸማች አክስሞ የንግዱን ማህበረሰብ አላግባብ አበልፅጎ የሚያልፍ ሁነት ነው የሚሆነው። አሁን ያለንበት ወቅት ለመብቱ የሚታገል ሸማች፣ የሸማቹንን ሮሮ የሚያዳምጥ የሥራ አስፈፃሚ እንዲሁም ነባራዊ ሁኔታዎችን እየገመገመ ከስር ከስሩ መፍትሔ የሚሰጥ መንግሥት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን መለቃቀሰ ብቻ ነው የሚሆነው ስለዚህ ሁሉም በንቃት ሊንቀሳቀስ ይገባዋል።

3. የሸማቾች መብት ጥሰቶች እና የመንግሥት ሕጋዊ እርምጃዎችን አለመፈፀም ስለሚያስከትላቸው ሃላፊነቶች

አዋጅ ቁጥር 813/2006 የሸማቹን ማህበረሰብ መብት እና የነጋዴዎችን ግዴታዎች እንዲሁም በመንግሥት አካል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሊወሰዱ የሚገባቸው በነፃ ገብያ ሥርዓት ላይ የሚወሰዱ የመንግሥት ቁጥጥር ሥርዓት ጣልቃ ገብነቶች ከመዘርዘር ባለፈ እነዚህን የሕግ ድንጋጌዎች በሚተላለፉ የንግድ ማህበረሰቦች ላይም ሊወሰዱ የሚገባቸውን የፍታብሔር፣ የወንጀል እና አስተዳደራዊ ሃላፊነቶችን አካቶ ይዟል። የፍታብሔር ተጠያቂነቶች በግለሰብ ደረጃ አንድን ነጋዴ በሕጉ የተቀመጡ የሸማቾች መብቶች እና ግዴታዎችን በመጣሱ ምክንያት የሚደርሱ ከውል የመነጩ ወይም ከውል ውጭ ሃላፊነቶች የሚመለከት ሲሆን የወንጀል እና የአስተዳደር ተጠያቂነቶች ደግሞ የንግዱ ማህበረሰብ በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መሠረት አድርጎ መንግሥት እንደ ሕዝብ እንደራሴነቱ እና የሕዝብን ደህንነት የማስጠበቅ ሀላፊነቱን ታሳቢ በማድረግ ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን የሚአካትቱ ናቸው። እነዚህንም እርምጃዎች የፌደራል ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስተር ከሸማቾች ባለሥልጣን እንዲሁም ከክልል ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ለተፈፃሚነታቸው መሥራት ይጠበቅበታል።

የፍታብሔር ተጠያቂነት የግለሰቦችን ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም መንግሥት ሸማቹን ከማንቃት አንፃር እንዲሁም ነፃ ገለልተኛ እና ፈጣን የሆነ የፍትህ ሥርዓት በመዘርጋት ሸማቹ ብዙውን ሳይቸገር መብቱን እንዲጠይቅ የሚአስችል ሁኔታን ሊፈጥር ይገባል። የአስተዳደራዊ እና የወንጀል ተጠያቂነቶችንንም ለማስረፅ እያንዳንዱ ሸማች ለመንግሥት ተባባሪ ሊሆን ግድ ይለዋል መንግሥትም ይህን ከማድረግ አንፃር እና ሸማቹን ከማነቃነቅ አንፃር በርትቶ ሊሰራ ይገባል። ሸማቹም ለሚደርሱበት በደሎች እምቢ ባይነትን ሊለማመድ ግድ ይለዋል። መንግሥትም ሕግን አውጥቶ መብት እና ግዴታን ከማስቀመጥ በአለፈ ለተፈፃሚነቱ ጥብቅ ቁጥጥር እና እርምጃ የሚወስዱ ለተጎዳው ወገን የሚቆሙ አስፈፃሚዎችን የአካተተ ተቋምን መገንባት አለበት። ሕግ ያለ ጠንካራ አስፈፃሚ ተቋማት ምንም ነውና።

አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ግን አብዛኞቹ እንቅስቃሴዎች በጠንካራ መሠረት ላይ የቆሙ ሳይሆን ለይስሙላ የሚመስሉ የሸማቹን ብሶት ግንዛቤ ውስጥ ያላስገቡ አካሄዶች ናቸው። ዛሬ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሰጠውን መግለጫ ነገ እታች ድረስ ወርዶ የሰው ሀይል አሰማርቶ ካልፈፀመው ፋይዳ ቢስ ነው የሚሆነው። ሸማቹም ከቁዘማ ወጥቶ ለመብቱ የሚጮህበት ነጋዴውም እርሱም በሌላ ዘርፍ ሸማች መሆኑን ተገንዝቦ እንዲሁም ለህሌናው ሲል የሸማቹን መብት በፍቃደኝነት የሚአከብርበት ኢትዮጵያዊ ባህሪን የተላበሰ ሁኔታን ሊከተል ይገባል። ዛሬ በአንዱ የሚደርስ የመብት ጥሰት ነገ በፈፃሚው ላይ የማይደርስበት ሁኔታ ስለሌለ ከመገፋፋቱ መተሳሰቡ ይበጀናል። የማንኛውም ሸማች መብት ሲጣስ ዝም ብሎ ማለፍም ተገቢነት የለውም ነገ ተረኛ ተጠቂ ስለሚያደርግ እና የንግዱ ማህበረሰብን ማንአለብኝነት ስለሚያሰፋ።

4. ማጠቃለያ

ከላይ በዝርዝር ለማየት እንደተሞከረው በአሁኑ ስዓት የኢትዮጵያ ሸማቾች በነጋዴው ማህበረሰብ በሚደረግ አላግባብ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እና የኑሮ ውድነት በትር ክፉኛ እየተወቀሩ ይገኛሉ። አብዛኛው ማህበረሰብ የሚያገኘው ገቢ ከኑሮ ሁኔታው ጋር አብሮ የማይጣጣም እና ውስን በመሆኑ አሁን መሬት ላይ ያለው የኑሮ ውድነት እጅጉን እየደቆሰው ነው። ለዚህ ችግር እንደ መነሻ ምክንያት ተደርጎ በነጋዴዎች የሚገለፀው የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና እጥረትም አሁን እየተተገበረ ካለው የንግድ እቃዎች እና አገልግሎቶች ዋጋ ጭማሪ አንፃር ስንመዝነው ውሀ የማይቋጥር ከንቱ ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን።

ሀገራት የሸማቹን ማህበረሰብ እንደዚህ ካሉ መሠረታዊ ችግርች ለመጠበቅ እንደ መሳሪያ ከሚጠቀሙባቸው ነገሮች አንዱ የሸማቾች መብት ጥበቃ ሕግ ማውጣት እና ለተፈፃሚነቱም በርትቶ መሥራት ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጲያም ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ የሸማቾች ጥበቃን በልዩ ሁኔታ የሚመለከቱ ህጎችን ማውጣት ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል። አሁን በሥራ ላይ ያለው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ በውስጡ ከአካተታቸው የሸማቾች መብት ጥበቃን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ውስጥም የዋጋ ንረትን ተከትሎ የሚመጣን የኑሮ ውድነት ችግር ለመከላከል የሚረዱ በግብይት ወቅት እና ከግብይት በኋላ በሸማቾች፣ በነጋዴዎች እንዲሁም በመንግሥት አካላት ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ይገኙበታል። እዚህም እርምጃዎች በነጋዴው እና በሸማቹ ሊተገበሩ የሚገቡ እና በመንግሥት ሊወሰዱ የሚገባቸው ተግባራት በማለት ከሁለት ተከፍለው ከላይ ተካተዋል። ሆኖም ግን ሕጉ እነዚህን እርምጃዎች እያንዳንዱ ሀላፊነት የተሰጠው አካል እንዲወጣ ያስቀመጠ ቢሆንም መሬት ላይ ያለው እውነታ የዚህ እሳቤ ተቃራኒ ነው።

ነጋዴው ሸማቹ መንግሥት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ለዘርፉ የሰጡት ትኩረት ተስፋ የሌለው ነው።የሸማቹ ማህበረሰብ መብቱን ለማስከበር ያለው ቁርጠኝነት አናሳ መሆን መንግሥትም ሕግ ከማውጣት በአለፈ ለተግባራዊነቱ የዘረጋው ተቋማዊ አደረጃጀት ደካማ መሆን እንዲሁም የነጋዴው መረን አልባ ስግብግብነት አሁን ለአለንበት አስጨናቂ የኑሮ ሁኔታ ሸማቹን ዳርጎታል። ስለዚህ ሸማቹ አጉል ይሉንታውን ትቶ ለመብቱ በጋራ በመቆም መንግሥትም የሸማቹን የእውቀት አድማስ በማስፋት እና ከእራሱ የሚጠበቁ እርምጃዎችን በመውሰድ እያንዳንዱ ነጋዴም እርሱም በሌላ ዘርፍ ሸመች መሆኑን ባልዘነጋ መልኩ እንዲሁም በሕግ የተጣለበትን ሀላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሸማቹ አሁን ከገባበት ቅራንቅር እንዲወጣ እና ለወደፊቱም ከእንደዚህ አይነት ችግሮች እራሱን የሚከላከልበት ሁኔታን ለመፍጠር መሥራት ይገባል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የተሻረው እና አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ድንጋጌዎች ንጽጽር በተለይም በጨው ...
የሚንቀሳቀሱ ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ ብድር የመስጠት የባንኮች ኃላፊነት

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 21 November 2024