In Response to the comment given by a Fitsum Yifrashewa
ፍጹም ይፍራሸዋ ለሰጠኀኝ አስተያየት እና ለላክልኝ ጽሁፍ አመሰግናለሁ፡፡ በጽሁፋ ላይ ለማንሳት የወደድኩት የንግድ ምልክት በኢትዮጵያ ህጎች ደረጃ ቀለል ባለ ሁኔታ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያህል ነው፡፡ በሌላው ጸሃፊ የተጻፈውንና አንተም የላክልኝን በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ ስለ ንግድ ምልክት የተጻፈውን ጽሁፍ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ጸሃፊው በንድግ ምልክቶች ላይ የጻፈው ጽሁፍ ጠቃሚና ስለንግድ ምልክቶች ለማወቅ የሚረዳ መሆኑን ለማስገንዘብም እወዳለሁ፡፡ ይህም በጽ/ቤቱ በስራ ባሳለፍኩባቸው ግዝያቶች አጠቃላይ ከሚታዩ ሁኔታዎች ይልቅ በአሰራርና ህጉን በተገቢው መንገድ በኢንተርናሽናል ደረጃና ከህጉ አላማ አንጻር መሬት ላይ ለማውረድ ችግር ወደፈጠሩት ሁኔታዎች ትኩረት ሰጥቸ እንድጽፍ አነሳስቶኛል፡፡ሆኖም ግን በጽሁፉ ላይ መስተካከል ይገባቸዋል የምላቸውን ነገሮች ከዚህ በታች እንደሚከተለው ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
የንግድ ምልክት ማለት የአንድ ምርት ወይም አገልግሎት መይም ምንጭ(Origin) በማስመዝገብ እንደ ብቸኛ መለያ(Exclusive sign) ተወስዶ ሰዎች አንድን ምርት መይም አገልግሎት ከሌላው ምርት ለመለየት የሚያገለግል ምልክት ሆኖ ማሳከር(Confusion) የማስወገድ አላማ ያለው ነው፡፡ ተብሎ በጸሃፊው በተቀመጠው ላይ ከዚህ በታች ያሉት ማስተካከያዎች መግባት እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡
በመጀመሪያ “የንግድ ምልክት ማለት የአንድ ምርት ወይም አገልግሎት መይም ምንጭ(Origin) በማስመዝገብ……” ተብሎ የተጠቀሰው በንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ 501/1998 አንቀጽ 6(ሸ) ላይ በተጠቀሰው መሰረት የአንድን ምርት ወይም አገልግሎት የመነጨበትን ቦታ በንግድ ምልክቱ የቀረበ እንደሆነ የንግድ ምልክቱ ለምዝገባ ብቁ እንደማይሆንና ይህም ሁኔታ በዚሁ አዋጅ በአንቀጽ 6(2) መሰረትም ስናየው በምንም አይነት መልኩ በአንቀጽ 6(ሸ) ላይ የተቀመጠው የህግ አግባብ exception እንደሌለውም በግልጽ ሲያሳይ ይታያል፡፡ የአንድን ምርት ወይም አገልግሎት የመነጨበትን ቦታ በምልክትነት ማስመዝገብ የሚቻለው በንግድ ምልክት ሳይሆን በወል የንግድ ምልክት እንደሆነና በሁለቱ መሃከልም ብዙ ልዩነት እንዳለ ማጤኑም ተገቢ ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡
በሁለተኛነት “እንደ ብቸኛ መለያ (Exclusive sign) ተወስዶ ሰዎች አንድን ምርት መይም አገልግሎት ከሌላው ምርት ለመለየት የሚያገለግል ምልክት ሆኖ…” የሚለው አገላለጽ ጠቦ መተርጎም ብቻ ሳይሆን መስተካከልም አለበት ብየ አምናለሁ፡፡ ይህንንም ለማለት የፈለኩት አንድ የንግድ ምልክት ከሌሎች ምርቶች ወይም አገልግሎቶች ሳይሆን ሌሎቹ ንግድ ምልክቶቹ ካልተመዘገቡ አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ ከሆኑ የንግድ ምልክቶች የተለየ እንዲሆን የሚጠበቅበት ሲሆን በሌላ መንገድ ደግሞ ሌሎቹ የንግድ ምልቶች ከተመዘገቡ እንደሆነ ደግሞ አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ ከሆኑ ምርቶቻቸው ወይም አገልግሎቶቻቸው በተጨማሪ በዕቃወቹ ወይም አገልግሎቶቹ መካከል ግንኙነት እንዳለ በማያሳይ መልኩ መቅረብ እነዳለበት እንጂ በአጠቃላይ ከሌላው ምርት ጋር መለየት አለበት ተብሎ መቀመጥ እንደሌለበት መታወቅ አለበት ፡፡
በሌላው የጸሃፊው የጽሁፍ አካል ውስጥ “የንግድ ምልክት ህጋዊነት የሚመሰረተው ወይም ጥበቃ የሚያገኘው በምዝገባ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 4፣5፣15 እና 16 መረዳት የሚቻል ሲሆን……” ተብሎ የተገለጸው ውስጥ ከዚህ በታች በተገለጸው መልክ መታረም አለበት እላለሁ፡፡
በአዋጁ አንቀጽ 4 ላይ በተቀመጠው መሰረት በሶስተኛ ወገኖች ላይ የንግድ ምልክት መብት አለኝ የሚባለው የምስክር ወረቀት ሲገኝ ነው እንጅ የሚለው ያልተመዘገበ የንግድ ምልክት ባለቤት በሶስተኛ ወገኖች ላይ የመብት ይያቄ ማንሳት አይችልም፣ የንግድ ምልክቱም ህጋዊነት የለውም ወይም ጥበቃ አይደረግለትም ማለት አይደለም፡፡ ይህንንም በአዋጁ አንቀጽ 7(1) እና 7(2) መረዳት ይቻላል፡፡ በአንቀጽ 7(1) ላይ አንድ የንግድ ምልክት በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የንግድ ምልክት ማመልከቻ መዝገብ ላይ በመስፈሩ ብቻ( የፎርማሊቲ ወይም የስነ-ነገር ምርመራ ሳይካሄድበት) ከሌሎች ኃላ ከመጡ አመልካቾች first come first served የሚለውን ፕሪንስፕል በመጠቀም ጥበቃ እንደሚያገኝ ገልጻል፡፡ በአንቀፅ 7(2) መሰረት ደግሞ አንድ የንግድ ምልክት በሚገባ የሚታወቅ ሲሆን(የአዋጁ አንቀጽ 23) ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ግልጋሎት ላይ ከዋለ ከሌሎች አንድ አይነት ወይም ሊያሳስቱ በሚችሉ ደረጃ ተመሳሳይ ከሆኑ የንግድ ምልክቶች ህጋዊ መሰረቱን በማጽናት ጥበቃ እንደሚያገኙ አጽንኦት ሰጥቶ አልፋል( አንቀጽ 7(2) (በአንቀጽ 7(2) ላይ ያለው ተግባራዊ ሚሆነውም አንድ አይነት ወይም ተመሳሳይ በሆኑ ዕቃዎችና አገልግሎት ላይ ነው)፡፡
ከዚሁ ጋርም በተያያዘ አንቀጽ 5 በተመለከተ እንደ ጸሃፊው ህጋዊነት ወይም ጥበቃ በምዝገባ ይገኛል የሚል ሳይሆን በአጠቃላይ የፎርማሊቲ መስፈርቶችን በሚመለከት መልኩ (ገና የስነ-ነገር ምርመራ ሳይደረግበት) በምርመራው ለምዝገባው ይረዳ ዘንድ የንግድ ምልክቱ ከሌሎች የንግድ ምልክቶች ግልጽና የተለየ ወይም Distnictive nature እንዲኖረው፣ አመልካቾችም በጥቁርና በነጭ ቀለማት ለማስመዝገብ ቢመጡ ጥበቃው ከማንኛውም የቀለም ቅንብር እንደሚሆንላቸው በተለያዩ ቀለማት ካመጡ ደግሞ የቀረበውን የቀለማት ቅንጅት መሰረት በማድረግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው እና ጥበቃ የማይደረግላቸውን ምልክቶች ( ሁሉም ሰው መጠቀም የሚችላቸው) ለማሳሌ በአለም አቀፍ የእቃዎችና አገልግሎቶች ምድብ(ኒስ ክላስፊኬሽን) ምድብ 43 ላይ ለሆቴል እና ሬስቶራንት አገልግሎት ሆቴልና ሬስቶራንት ብሎ ከንግድ ምልክቱ ጋር ማቅረብ ወይም በ አለም አቀፍ የእቃዎችና አገልግሎቶች ምድብ 44 ላይ ለሆስፒታል አገልግሎት ከንግድ ምልክቱ በተጨማሪ ሆስፒታል የሚለውን ማቅረብ የንግድ ምልክቱን ልዩ ባህሪይ እስካልቀነሰ ድረስ ወይም የሌላውን ሰው መብት እስካልጣሰ ድረስ በ Disclaimer ሞልቶ መጠቀም እንደሚችል እንጂ የንግድ ምልክት ህጋዊነት የሚያገኝበትንም ሆነ ጥበቃ የሚያገኘው በምዝገባ ነው የሚል እንድምታ የለውም ምክንያቱም አንድ ሰው ከሌሎች ተመሳሳይ ወይም አንድ አይነት ዕቃ ከሚያመርቱ ወይም አገልግሎት ከሚያቀርቡ ሰዎች በግልጽ የሚለይ የንግድ ምልክት ለዕቃዎቹ ወይም ለአገልግሎቶቹ የተጠቀመ እንደሆነ ወይም በጥቁርና ነጭ ምልክቱን እየተጠቀመበት እንፈደነበረ ካስረዳ ወይም በጋራ መጠቀሚያ የሆኑ ምልክቶች የኔ ብቻ ናቸው ብሎ ካላተሟገተ በስተቀር የንግድ ምልክቱ ባይመዘገብም እንኳን በኢትዮጵያ ውስጥ በግልጋሎት ላይ ከዋለ ወይም ታዋቂ የሆነ ከሆነ ጥበቃ የማያገኝበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አንቀፅ 15 እና 16 ያሉት የሚያመለክቱት ስለምዝገባ፣ ስለምስክር ወረቀት አሰጣጥ እና ምዝገባውን ጽ/ቤቱ ለህዝብ ስለሚያሳውቅበት ሁኔታ እንጅ የንግድ ምልክቱ ህጋዊነቱን የሚላበሰው እና ጥበቃ የሚደረግለት በምዝገባ ብቻ ነው የሚል ሃሳብ የላቸውም፡፡
ሌላው የነጻ ገበያ መርህን መሰረት ጤናማ ውድድር እንዲኖር በአዋጅ ቁጥር 329/95 መሰረት የንግድ አሰራርን መርህ መከተል አለበት ተብሎ ለተጻፈው የንግድ ምልክት አዋጁ አንቀጽ 48 ላይ ንግድ ምልክቶችን በተመለከተ ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ህጎችና አሰራሮች የተጻፈውን ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ይህን ስል ግን ህጎቹ በእኩል ደረጃ ላይ ያሉ በመሆናቸውና የሚያስፈጽሙአቸው አካላትም አንዱ ለአንዱ ተጠያቂም ሆነ ተጠሪ ባለመሆናቸው ምክንያት እርስ በርስ የሚፋለሱ ህግጋት በተመሳሳይ ሰአት ተግባራዊ ይሁኑ እያልኩ ሳይሆን በጸሃፊው የተገለጸው አባባል የንግድ ምልክት ህጉ የሸማቾችና የንግድ አሰራር አዋጁን መርህ መከተል አለበት የሚል መልእክት ያስተላልፋል ብየ ስላመንኩ መስተካከል አለበት በሚል እሳቤ ነው፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘም ይህ ጽሁፍ የተለቀቀው በዚሁ በያዝነው አመት በየካቲት ወር ሲሆን በፅሁፉ ላይ የተጠቀሰው አዋጅ( አዋጅ ቁጥር 329/95) ግን በአዋጅ ቁጥር 685/2002 በነሃሴ ወር 2002 ላይ የተሻረ አና በአሁኑ ሰአት ተፈጻሚነት እንደሌለው ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
በሌላው የጸሃፊው ጽሁፍ ላይ የሶስተኛ ወገኖችን መብት በመጠበቅ የንግድ ምልክት እንዳይደረግ ተብሎ የተገለጹት ነጥቦች የተሟሉ መስሎ አይታየኝም ምክንያቱም አስቀድመው በንግድ ምልክት ማመልከቻ መዝገብ ውስጥ ስለሰፈሩና ለምርመራ(ፎርማሊቲ እና የስነ-ነገር) ስለቀረቡ የንግድ ምልክቶች(አንቀጽ 7(1))፣ ባይመዘገቡም እንኳን በኢትዮጵያ ውስጥ ግልጋሎት ላይ በመዋላቸው ምክንያት ወይም ታዋቂ በመሆናቸው(አንቀጽ 23) ምክንያት(አንቀጽ 7(2)) ከሶስተኛ ወገን ስለሚጠበቁ የንግድ ምልክቶች ሳያነሳ በማለፉና ስለተመዘገቡ የንገድ ምልክቶችና የስነ-ጽሁፍ፣የኪነ-ጥበብ ወ.ዘ.ተ የንግድ ምልክት ጥበቃ ስላላቸው ነገሮች ብቻ ስለጠቀሰ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስለ ተመዘገቡ የንግድ ምልክቶች ሲጠቅስ ስለ ንግድ ምልክቶቹ መመሳሰል ወይም በትርጉም መመሳሰል እንጅ ስለ አገልግሎቶቹ ወይም በእቃዎቹ መሃከል በፊጠር መመሳሳል ወይም አለመመሳሰል በተነሳ ከንግድ ምልክቶቹ ጋር አቆራኝቶ አልተጠቀሰም፡፡
በስተመጨረሻም ጸሃፊው የንግድ ምልክት ሊታደስ፣ ሊተውና በጥቅም ላይ ባለመዋሉ ምክንያት ስለሚሰረዝበትና በዚሁ መብት የመጠቀም በሙሉ ወይም በከፊል መብት በመስጠት ወይም ፈቃድ በመስጠት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ስለሚችልበት ስርአት ህጉ(በአንቀጽ 20፣25፣34፣35፣28) በዝርዝር ጸደንግኋል…..ተብሎ የተቀመጠው ላይ እንደዚሁ በንግድ ምልክቶች እና በወል የንግድ ምልክቶች መሃል ያለውን ልዩነት ያለመረዳትን ያሳያል ለምሳሌ አንቀጽ 20 የሚናገረው ስለ ወል የንግድ ምልከቶች ነው፡፡ የወል የንግድ ምልክቶች ባለቤቶች ከንግድ ምልክት ባለቤቶች የተለዩ ናቸው ከተሰረዙ በኃላም የሚያስከትሉት ውጤት እንደዚሁ የተለየ ነው ሌላው እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው መብት ማስተላለፍ ላይ ነው በአዋጁ አንቀጽ 29 ላይ የወል የንግድ ምልክቶችን ማከራየትን እንኳን የሚከለክል አዋጅ መብቱን በሙሉ እንደ ንግድ ምለክቶች በአንቀጽ 28 እንዲያስተላልፍ ይፈቅዳል ማለት ዘበት ነው፡፡የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትም እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችን አስተናግዶ አያውቅም ምክንያቱም የወል የንግድ ምልክቶች እና በባለቤትነት የሚይዙት ማህበራት የተለየ ቁርኝት ስለሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ ምሳሌ የማረቆ በርበሬን በባለቤትነት መያዝ የሚችሉት በማረቆ አካባባ በዚሁ ተግባር ላይ ተሰማርተው ኑሮአቸውን ለሚገፉ በማህበር ለተደራጁ የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments