ስም ሰዎችን ለመለየት የምንጠቀምበት ሁነኛ ዘዴ ነው፡፡ ይህም አንድን ሰው ከሌላ ሰው ለመለየት ለሰዎቹ ስያሜ በመስጠት በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡ የአገራችን ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 36 (1) (ለ) ስምን የመሰየም የሁሉም ህጻናት መብት ነው ሲል ያትታል፡፡ በተጨማሪም ICCPR አንቀጽ 24 (2) እንደሚደነግገው ሁሉም ህጻናት እንደተወለዱ ወዲያውኑ እንዲመዘገቡ እና ስም እንዲወጣላቸው ያዛል፡፡
ሕግ ጭራሽ ካለመከበሩ በከፋ ተመርጦ ሲከበር የበለጠ አልተከበረም፡፡ አሁን ባለን መረጃ ሀገሪቱ ከቻይና ጋር ስለገባነው የብድር ስምምነት የሚያትትውን 1000ኛውን አዋጅ ካወጀች ብኋላ እንኳ ከመቶ በላይ አዋጆች ወጥተዋል፡፡ ኑሮው፣ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ማህበራዊ ጉዳያችን ብዙ ነው እና ሕጎቹ በዙ አይደለም ጉዳዩ፡፡ ስንቱ በርግጥ ወጥቶ ሥራ ላይ ዋለ ነው ጥያቄው፡፡ የማናከብረውን እና የማንተገብረውን ሕግ ማውጣት ከሕግ አልባነት አይሻልም፡፡
የማስረጃ ሕግ የማስረጃን አግባብነት፣ የማስረጃን ተቀባይነት እንዲሁም የማስረጃን ክብደትና ብቃት የሚገዙ ደንቦችና መርሆዎች ጥርቅም ነው፡፡ ማስረጃ ተሟጋቾች በአቤቱታቸው አማካኝነት ፍርድ ቤት የያዘውን ጭብጥ የሚያረጋግጡበት ዘዴ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ማስረጃ ማለት ፍርድ ቤት የያዘውን አከራካሪ ጉዳይ ወይም ጭብጥ በሚሰማበት ጊዜ ተሟጋቾች የጥያቄውን አግባብነት፣ እውነትነት፣ በምስክሮች፣ በሠነድ፣ ተጨባጭነት ባላቸው ሌሎች ነገሮች፣ ወዘተ… ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ የሚያረጋግጡበት አሊያም ውድቅ የሚያደርጉበት ዘዴ ነው፡፡ ማስረጃ ሲባል የአንድን ፍሬ ነገር ህልው መሆን ወይም አለመሆን ለማረጋገጥ ያገለግል ዘንድ ክስ በሚሰማበት ጊዜ ወይም የክርክር ጭብጥ በሚጣራበት ወቅት በተከራካሪ ወገኖች ወይም ክርክሩን በሚያየው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አማካኝነት የሚቀርብ ማናቸውም ዓይነት የአስረጂነት ባህርይ ያለው ነገር ነው፡፡ ማስረጃ በምስክሮች (Witnesses)፣ በዘገባ (Record)፣ በሠነድ (Document)፣ ተጨባጭነት ባላቸው ሊታዩ ሊዳሰሱ በሚችሉ ነገሮች (Concrete Objects) እና በኤግዚቢት መልክ ሊቀርብ ይቸላል፡፡ አቀራረቡም በሕግ በተደነገገው ሥርዓት መሠረት ነው፡፡ የክርክሩን ጭብጥ ፍሬ ነገር እውነት ወይም ሀሰት መሆኑን የማሳመን ኃይል ያለው እንደመሆኑ እና በዚህም ወደ ውሳኔ የሚያደርሰው ስለሆነ ሊገኝም ሊቀርብም የሚገባው በሕግ አግባብ ነው፡፡ ማስረጃው ተቀባይነት ወይም ውድቅ የሚደረገው እንደዚሁም ሊሰጠው የሚገባው ክብደት የሚመዘነውም በሕግ አግባብ ነው፡፡
መኳንንት ከሕግ ትምህርት ቤት ተመርቆ ሲወጣ ግር ያለው ነገር የትምህርቱና የአተገባበሩ ልዩነት ነው፡፡ በአብዛኛው በንድፈ ሐሳብ አስተምህሮና ትንተና ላይ የሚተኮረው ትምህርቱ በተግባር ከሚታየው የፍርድ ቤት ነባራዊ ሁኔታ ጋር አልታረቅ ብሎት ተቸግሯል፡፡ ይህን ችግሩን ያባባሰው ደግሞ ከቤተሰቡ አንዱ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ከፍርድ ቤት እንዲሰጠው በማሰብ አቤቱታውን እንዲያዘጋጅለት ሲጠይቀው ነው፡፡ አቤቱታውን አዘጋጅቶ ለቤተሰቡ አባል ቢሰጠውም በአንዱ ክልል ከሚገኘው የወረዳ ፍርድ ቤት የገጠመው ነገር ሌላ ነው፡፡ ቤተ ዘመዱ በፍርድ ቤቱ አቤቱታው በትክክል አለመጻፉ ተነግሮት በፍርድ ቤቱ ደጃፍ ከሚገኙት ራፖር ጸሐፊ ተጽፎ እንዲመጣ ተመከረ፡፡ ሰውየውም የተባለውን ፈጽሞ አቤቱታው ተቀባይነት አግኝቶ የወራሽነት የምስክር ወረቀት አገኘ፡፡ የመኳንንትና የራፖር ጸሐፊው አቤቱታ ልዩነት ቀላል ነበር፡፡
የዚህ አጭር ጽሑፍ ዋና ትኩረቱን በድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/1996 ላይ በማድረግ አዋጁ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት በአንቀፅ 55(1) ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከተሰጠው ሕግ የማውጣት ስልጣን ጋር ያለውን ተቃርኖ እና የሕገ መንግስቱን የበላይነት ያላከበረ ስለመሆኑ እንዲሁም የድሬዳዋ አስተዳደር ተጠሪነት ላይ የሚነሱ የሕግ ጉዳዮችን በመዳሰስ መፍትሔውን ማስቀመጥ ነው፡፡
ከዚህ በፊት ባለው ጽሁፍ የሚከተሉትን ሃሳቦች አቅርቤ ነበር። በዋናነት የእነዚህ ሃሳቦች ተግባራዊነት ዉጤት፤ አሁን ተበጣጥሶ የሚገኘውን በገጠር መሬት ላይ የግብርና ውሳኔ መብት በአንጻራዊነት እንዲማከል ማድረጉ ነው። የግብርና ውሳኔ ማለት፥ በአንድ እርሻ ላይ ምን ላምርት? መቼ ላምርት? ምን አይነት እና መጠን ያለው ማዳበሪያ ልጠቀም? ምን አይነት የውሃ ቴኬኖሎጂ ልጠቀም? ምን አይነት ማረሻ፥ ማጨጃ፥ እና መውቂያ ልጠቀም? ምን አይነት የመሬትና አፈር ጥበቃና አስተዳደር አሰራሮችን ልከተል? እና የመሳሰሉት ናቸው። ከግብርና ውሳኔዎች ጋር የሚገናኙ የገበያ ውሳኔዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ፤ ምን ያህል ምርቴን፥ መቼ፥ ለማን ልሽጥ? ምን ያህል ገንዘብ፥ ከማን፥ በምን ያህል ወለድ ልበደር? እነዚህና የመሳሰሉት ገበያ ነክ ውሳኔዎች ካነሳኋቸው ነጥቦች ጋር በቀጥታ አይገናኙም። እኔ ያነሳሁት የግብርና ውሳኔዎችን ነው።
በየካቲት ወር 2008 ዓ/ም መዲናችን አዲስ አበባ ላይ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 ዓ/ም የሪከርድ አያያዝ ትግበራ መጀመሩን ተከትሎ የታክሲ የአሽከርካሪዎች ስራ የማቆም አድማ ነበረ፡፡ በዚህም መሰረት ተግባራዊ መደረግ ተጀምሮ የነበረው የሪከርድ አያያዝ ተግባራዊነቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ከአሽከርካሪዎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ የደንቡ መሻሻል አስፈላጊነት ታምኖበት ደንቡ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በወቅቱ በአሽከርካሪዎች በኩል ሀገሪቱ ባላት የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ብቃት ደረጃ፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች፣ ልል የሆነ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ተጠያቂነት፣ የተቆጣጣሪዎች ስነምግባር ችግር እንዲሁም ከብዙ ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በደንብ ቁጥር 208/2003 ዓ/ም ላይ ሪከርድን የሚመለከተው ክፍል ወደ ተግባር የሚገባ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚፈጠርባቸው ለስራ ማቆም አድማው የተሰጡት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ደንቡ በ2003 ዓ/ም እንደመውጣቱ እሪከርድን የሚመለከተው ክፍል ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በ2008 ዓ/ም መሆኑ በራሱ የህግ አስፈጻሚውን ቸልተኝነት የሚያሳይ ሲሆን ደንቡን በመተግበር ረገድ ቀድመው የጀመሩ እንደ አማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያሉትን ደግሞ በክልላቸው የሚንቀሳቀሱትን አሽከርካሪዎች በሀገሪቷ ውስጥ ካሉ ሌሎች አሽከርካሪዎች በተለየ ሁኔታ ተጎጂ ሲያደርጋቸው ነበር፡፡ ይህ ጽሁፍ ደንቡ የተሻሻለበትን ምክንያቶች አግባብነት፣ ማሻሻያው ውስጥ የተጨመሩ እና ማስተካከያ የተደረገባቸውን አንቀጾች እንዲሁም የማሻሻያውን አንድምታ በተወሰነ መልኩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
በሀገራችን እጅግ አሳሳቢ እና አነጋጋሪ ከሆኑት የወንጀል ድርጊቶች መካከል በአሽከርካሪዎች የሚፈጸመው ወንጀል ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል ለማለት ይቻላል፡፡ ከትራፊክ ፖሊስ ዕለታዊ ሪፖርት በየዕለቱ እንደምንሰማው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንኳን ያለበትን ሁኔታ ብንመለከት በንብረትና በሰው ላይ፣ ቢያንስ በአንደኛው ላይ አደጋ ሳይደርስ የዋለበት ቀን የለም ለማለት ይቻላል፡፡ የአደጋ ዜናው በ24 ሰዓት፣ በወርና በዓመት ስሌት ሲነገር ስንሰማው እጅግ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ በትርፊክ ፖሊስ የዘወትር ሪፖርት እንደምንሰማውም ብዙውን ጊዜ አደጋው የደረሰው ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል በአሽከርካሪ ጥፋት መሆኑን መዘገቡ የተለመደ ነው፡፡
የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 133/98 የተካው የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 ቀደም ሲል በሕግ ደረጃ ሽፋን ያላገኙ አዲስ ነገሮችን ይዞ እንደወጣ ይታወቃል፡፡ አዲስ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ በገጠር መሬት ላይ በሚነሱ ክርክሮች ላይ የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል ያስቀመጠው ነገር ነው፡፡ ይህ የይርጋ ድንጋጌ በሕጉ የተካተተ አዲስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ገና ከጅምሩ አከራካሪ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ አከራካሪነቱም በባለሙያዎች መካከል ሁለት ጫፍ የያዙ አቋም እንዲኖር ከማድረግ አልፎ አዲስ የክርክር ምክንያትም እየሆነ ነው፡፡ አዋጁ ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮም የገጠር መሬትን ተከትሎ የሚቀርቡ ክሶች ላይ የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚነት የለውም በሚል ብዙ ዶሴዎች ከተዳፈኑበት አቧራቸውን እያራገፉ በክስ መልክ እየቀረቡ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም በባለሙያዎች መካከል በይርጋው ተፈፃሚነት ላይ ባለ ሁለት ጫፍ የያዘ አቋም ምክንያት ከወዲሁ ተገማችነታቸውና ወጥነታቸው አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ ስለዚህም በጉዳዩ ዙሪያ የሚነሱ አቋሞችን እና ምክንያቶችን በማየት ሃሳቡን መመልከቱ አስፈላጊ እና ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ የፁሁፉ ዋና ትኩረትም በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ላይ የተቀመጠጠው የይርጋ ድንጋጌ ወሰን አለው ወይስ የለውም የሚል ይሆናል፡፡
በኅብረተሰብ ጤና ዘርፍ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል ለውጥ ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ የጤና አገልግሎትን በቀበሌ ደረጃ ለማስፋፋት፣ በተለይም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ማዕከል ያደረገና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተቸረውን የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር ተግባራዊ በማድረግ፣ የዓለም መንግሥታት ድርጅትን የጤና የሚሊኒየም ግቦችን ለማሳካት ችላለች፡፡ እንደ አብዛኛው ታዳጊ አገሮች ሁሉ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት የጤና ፕሮግራሞችና የአጋር ድርጅት ትኩረቶች ውስጥ ወባ፣ ኤችአይቪ/ኤድስና ሳንባ ነቀርሳ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ፣ እንዲሁም የሕፃናትና እናቶች ጤናን ማሻሻል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ የበሽታዎች ሥርጭት ሁኔታ በለውጥ ሒደት ላይ ያለ ሲሆን፣ በተለይም በከተማዎችና በዙሪያቸው ባሉ ሥፍራዎች በመስፋፋት ላይ የሚገኙት የልብ፣ የመተንፈሻ አካላት፣ ስኳርና ካንሰርን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ይጠቀሳሉ፡፡