አንዳንድ ነጥቦች ስለአዲሱ የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 395/2009
በየካቲት ወር 2008 ዓ/ም መዲናችን አዲስ አበባ ላይ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 ዓ/ም የሪከርድ አያያዝ ትግበራ መጀመሩን ተከትሎ የታክሲ የአሽከርካሪዎች ስራ የማቆም አድማ ነበረ፡፡ በዚህም መሰረት ተግባራዊ መደረግ ተጀምሮ የነበረው የሪከርድ አያያዝ ተግባራዊነቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ከአሽከርካሪዎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ የደንቡ መሻሻል አስፈላጊነት ታምኖበት ደንቡ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ በወቅቱ በአሽከርካሪዎች በኩል ሀገሪቱ ባላት የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ብቃት ደረጃ፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች፣ ልል የሆነ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ተጠያቂነት፣ የተቆጣጣሪዎች ስነምግባር ችግር እንዲሁም ከብዙ ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በደንብ ቁጥር 208/2003 ዓ/ም ላይ ሪከርድን የሚመለከተው ክፍል ወደ ተግባር የሚገባ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚፈጠርባቸው ለስራ ማቆም አድማው የተሰጡት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ደንቡ በ2003 ዓ/ም እንደመውጣቱ እሪከርድን የሚመለከተው ክፍል ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በ2008 ዓ/ም መሆኑ በራሱ የህግ አስፈጻሚውን ቸልተኝነት የሚያሳይ ሲሆን ደንቡን በመተግበር ረገድ ቀድመው የጀመሩ እንደ አማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያሉትን ደግሞ በክልላቸው የሚንቀሳቀሱትን አሽከርካሪዎች በሀገሪቷ ውስጥ ካሉ ሌሎች አሽከርካሪዎች በተለየ ሁኔታ ተጎጂ ሲያደርጋቸው ነበር፡፡ ይህ ጽሁፍ ደንቡ የተሻሻለበትን ምክንያቶች አግባብነት፣ ማሻሻያው ውስጥ የተጨመሩ እና ማስተካከያ የተደረገባቸውን አንቀጾች እንዲሁም የማሻሻያውን አንድምታ በተወሰነ መልኩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡
የደንብ ቁጥር 208/2003 መሻሻል አስፈላጊነት
የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 ዓ/ም / ከዚህ በኋላ "ደንቡ" እያለ ይቀጥላል / በርከት ያሉ ድንጋጌዎች ከያዙ እና የመንገድ ትራፊክ ፍሰትን ለማሳለጥ ከሚያስችሉ መሰረታዊ ህጎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ደንብ መሻሻል ገፊ ምክንያት የሆነው ከደንቡ የሪከርድ ክፍል ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ ቢሆንም ከጊዜ ቆይታ እና የሁኔታዎች ተለዋዋጭነት አንጻር እንዲሁም ደንቡ ቀድሞውንም ሲወጣ ከነበሩበት የህግ አወጣጥ ችግሮች ጋር በተያያዘ መሻሻል የነበረበት በመሆኑ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 395/2009 ዓ/ም /ከዚህ በኋላ "ማሻሻያው" እያለ ይቀጥላል /መውጣቱ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ይህ ደንብ ሲሻሻል ከግምት ውስጥ ሊያስገባ የሚገባው መሰረታዊ ነጥብ ቢኖር ሀገሪቷ በአሁኑ ሰአት ከየትኛውም አደጋ በላይ በአመት ከ5000 /አምስት ሺ/ የሚበልጥ የሰው ሂወት እየቀጠፈ እና ከባድ የሆነ የንብረት ውድመት እያስከተለ ያለውን የትራፊክ አደጋን መቀነስ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አብዛኞቹ የትራፊክ አደጋዎች የሚደርሱት በአሽከርካሪዎች ጥፋት መሆኑ እየታወቀ ሪከርድን የሚመለከተው የህጉ ክፍል የተሻሻለበት መንገድ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ከማስገባት ይልቅ በነበረው ተቃውሞ ተጽእኖ ስር ሆኖ የተሻሻለ ነው፡፡ ይህንን ከታች በዝርዝር እንመለከተዋለን፡፡ ሪከርድን ከሚመለከተው ክፍል ውጪ የተሻሻለው የደንቡ ክፍል ከነ ክፍተቶቹም ቢሆን ከዚህ ቀደም በደንቡ ላይ ግልጽነት የጎደላቸውን ድንጋጌዎች ለማስተካከል ከመሞከሩም በላይ አዳዲስ አንቀጾችን በመጨመር የደንቡን ክፍተቶች ጥሩ በሚባል መልኩ አስተካክሏል፡፡
መሰረታዊ ማሻሻያ የተደረገባቸው እና አዲስ የተጨመሩ ድንጋጌዎች በከፊል
- በደንቡ አንቀጽ 5/2/ሀ/ ላይ አሽከርካሪዎች በማንኛውም መንገድ ስልክ እያናገሩም ሆነ የጽሁፍ መልእክት እየላኩ ማሽከርከርን ተከልክለው የነበረ ቢሆንም በማሻሻያው ላይ ግን አሽከርካሪዎች ስልክ ማናገር የማይችሉት ስልኩን በእጃቸው ይዘው ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ አሽከርካሪ ስልክ በጆሮ ማዳመጫ እያናገረ ወይም መልእክት እየላከ ማሽከርከር ይችላል ማለት ነው፡፡ እዚህ ጋር ሊነሳ የሚገባው ነጥብ በደንቡ ላይ ስልክ ማናገር ወይም መልእክት መላክ ተከልክሎ የነበረው አሽከርካሪው እጁን ከመሪ ላይ ስለሚያስነሳው ብቻ ነበር ወይ? የሚለው ነው፡፡ በውጪው አለም አሽከርካሪዎች ስልክን በስልክ ማስቀመጫ ላይ አድርገው እያናገሩ ሲያሽከረክሩ የሚታይ እና ህጋዊ ተግባርም ነው፡፡ ወደኛ ሀገር ስንመጣ ግን ስልክ እያናገሩ ማሽከርከር የአሽከርካሪውን ሀሳብ እንዲሰረቅ በማድረግ ለአደጋ ማጋለጡ እንዳለ ሆኖ የእግረኛው ተጠቃሚ ስነምግባር ደካማ በሆነባት ሀገራችን ላይ ይህንን ችግር ወደጎን በመተው አሽከርካሪዎች በጆሮ ማዳመጫ ስልክ እያናገሩ እንዲሁም የጽሁፍ መልእክት እየላኩ እንዲያሽከረክሩ መፈቀዱ አግባብ አይደለም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በማሻሻያው ላይ ሊገለጽ ይገባው የነበረው አሽከርካሪዎች የጆሮ ማዳመጫ እንዲጠቀሙ ከተፈቀደ መጠቀም የሚችሉት በአንዱ የጆሮ ክፍላቸው ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ነው፡፡ ምክንያቱም አሽከርካሪዎች ሲያሽከረክሩ ከሌላ አሽከርካሪ የሚሰማን የጡሩንባ ድምጽ እንዲሁም ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚያሰሙትን የፊሽካ ድምጽ ለመስማት እንዲያስችላቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አንድ አሽከርካሪ ተሽከርካሪው ያልተገባ ድምጽ እያሰማ እንዳልሆነ እያረጋገጠ ማሽከርከር እንዳለበት ህጋዊ ግዴታ በደንቡ አንቀጽ 10/1/ለ/ ስር ስለተቀመጠበትም እንዲሁም በአንቀጽ 2/10/ እና 27/1/ሀ/ ላይ የአደጋ አሽከርካሪዎች የሚያሰሙትን የሳይረን ድምጽ መሰረት በማድረግ መንገድ መልቀቅ እንደሚገባቸው የተቀመጠውን ግዴታ ማሻሻያው ከግምት ማስገባት ነበረበት፡፡ ከላይ የተገለጹት ችግሮች እንዳሉ ሆነው ማሻሻያው ስልክ እያናገሩ ማሽከርከርን ከፈቀደ አይቀር ከቴክኖሎጂ እድገት አንጻር የጽሁፍ መልእክቶችን በድምጽ መቀበል እና መላክ የሚቻልበት ደረጃ ላይ ስለተደረሰ መልእክት መላክም ሆነ መቀበል እንደሚቻል መፈቀዱ ተገቢነት ያለው ነው፡፡
- በማሻሻያው አንቀጽ 5/8/መ/ አዲስ አንቀጽ የተጨመረ ሲሆን የፊትና የኋላ ሰሌዳ የሌለው ተሽከርካሪን ማሽከርከር እንደማይቻል ግዴታ ያስቀምጣል፡፡ በእርግጥ በአዋጅ ቁጥር 681/2002 ዓ/ም አንቀጽ 48/2/ለ/ ላይ ሰሌዳ የሌለውን ተሽከርካሪ ማሽከርከር የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚኖረው የሚያስቀምጥ ቢሆንም በደንብ መተላለፍም ማስቀጣቱ ተገቢነት አለው፡፡ በአሰራር እንደሚታየው ብዙ አዲስ ተሽከርካሪዎች የጉሙሩክ ሰነዶችን በማሳየት ብቻ ሰሌዳ ሳይለጥፉ በከተማዋ መንገዶች ላይ ሲሽከረከሩ ይታያል፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች አደጋ ቢያደርሱ ወይም ደንብ ቢተላለፉ የሰሌዳ ቁጥር ስለሌላቸው ህግን ለማስከበር ክፍተት ስለሚፈጥሩ ተገቢው ቁጥጥር የሚያስፈልገው ስለሆነ በደንቡ ውስጥም ይህ አንቀጽ መካተቱ አግባብ ነው፡፡
- በደንቡ አንቀጽ 24/2/ ቀጥሎ ንኡስ አንቀጽ 3 የተጨመረ ሲሆን በዚህ ንኡስ አንቀጽ መሰረት ማንኛውም አሽከርካሪ ባለአራት ጎን ቢጫ የትራፊክ መስመር በተቀባ መስቀለኛ መንገድ ላይ በተቃረበ ጊዜ ወደ ተቀባው የትራፊክ መስመር ቀድሞ ለገባው አሽከርካሪ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ በደንቡ አንቀጽ 22/1/ እና 24/1/ ላይ ማንኛውም አሽከርካሪ ከአንድ መስቀለኛ መንገድ በደረሰ ጊዜ መስቀለኛውን መንገድ ለማለፍ አስቀድሞ መስቀለኛ መንገድ ውስጥ ለገባው ተሽከርካሪ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ያስቀምጥ የነበረ ቢሆንም በማሻሻያው አንቀጽ 24/3/ የተጨመረው ንኡስ አንቀጽ ግን በሰንጠረዥ" ሀ" በአራተኛ ተራ ላይ ከተጨመረው ምልክት ጋር ነው፡፡ በሰንጠረዥ" ሀ" በአራተኛ ተራ የተጨመረው ምልክት ባለበት ቦታ መሀል ላይ ሳይቆም ሊያልፍ የሚችል መሆኑን ካላረጋገጠ በስተቀር አሽከርካሪው ቢጫ ቀለም ወደተቀባበት የመንገድ ክፍል መግባት እንደሌለበት ይገልጻል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መስቀለኛ መንገድ ሆነው የትራፊክ መብራት በሌላቸው መንገዶች ላይ አንዱ ላንዱ ቅድሚያ ባለመስጠት ተሽከርካሪዎች ተቆላልፈው የምናይበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ይህን ችግር ደግሞ ባለ አራት ጎን ቢጫ የትራፊክ መስመር ስለሚቀርፈው የንኡስ አንቀጹ መጨመር ተገቢ ነው፡፡
- ሌላው በማሻሻያው ለውጥ የተደረገው ትርፍ ሰው መጫንን በሚመለከት ነው፡፡ በደንቡ ትርፍ ሰው የጫነ አሽከርካሪ አንድም ሰው ትርፍ ጫነ ከዛም በላይ ልዩነት አልነበረውም፡፡ በማሻሻያው ላይ ግን የመጫን አቅሙ እስከ 25 ሰው የሆነ ተሽከርካሪ ከ 1-3 ሰው ትርፍ ከጫነ ቅጣቱ በሰንጠረዥ "ለ" በእርከን አንድ ላይ እንዲሁም ከ25 ሰው በላይ መያዝ አቅም ያለው ተሽከርካሪ ላይ ከ1-5 የሚሆን ሰው ከጫነ በሰንጠረዥ "ለ" በእርከን አንድ ላይ እንዲቀጡ የተደረገ ሲሆን ፤ በእርከን አንድ ላይ የተገለጹት ከ3 እና 5 ሰው በላይ ከጫነ ደግሞ በእርከን ሁለት ላይ ጥፋት እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በቅጣት ሰንጠረዡ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ቀድሞ "አንድም ሆነ ከአንድ በላይ ሰው ትርፍ መጫን አንድ ነው ቅጣቱ ስለዚህ አንድ ሰው ትርፍ ከጫንክ አይቀር ብዙ ሰው ጫን" የሚለውን አስተሳሰብ በተወሰነ መልኩ ቅጣቱን የተለያየ በማድረግ ለመገደብ ተሞክሯል፡፡
- በደንቡ ሰንጠረዥ "ለ" ላይ ከእርከን አንድ እስከ እርከን ስድስት ተዘርዝረው የነበሩት ጥፋቶች በማሻሻያው ላይ ማሸጋሸግ የተደረገባቸው ሲሆን አዳዲስ ጥፋቶችም እንዲጨመሩባቸው ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በደንቡ ሰንጠረዥ "ለ" እርከን አንድ ላይ የነበሩት የጥፋት ዝርዝሮች ብዛት ዘጠኝ የነበረ ሲሆን በማሻሻያው ላይ ግን እነዚህ ጥፋቶች ወደ ሀያ አራት ከፍ እንዲሉ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በእርከን ሁለት ላይ የነበሩት ጥፋቶች ብዛት ስድስት የነበረ ሲሆን በማሻሻያው ላይ ግን ወደ ሀያ አንድ ከፍ እንዲሉ ተደርጓል፡፡ ከእርከን ሶስት ጀምሮ እስከ እርከን ስድስት ያሉት የጥፋት ዝርዝሮች ደግሞ ብዛታቸው ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል፡፡
- በደንቡ በሰንጠረዥ "ለ" ባሉት በስድስቱም የጥፋት እርከኖች ላይ ጥፋት ያጠፋ አሽከርካሪዎች እርከኖቹ እንደተሰጣቸው ነጥብ እሪከርድ ይያዝበት የነበረ ቢሆንም በማሻሻያው ሰንጠረዥ "ለ" እርከን አንድ ላይ ላሉት ሀያ አራት ጥፋቶች እሪከርድ እንዳይያዝባቸው ተደርጓል፡፡ እነዚህ በእርከን አንድ ላይ ተዘርዝረው እንዲቀመጡ የተደረጉት ጥፋቶች ደግሞ አሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ የሚፈጽሟቸው ሲሆኑ በደንቡ መሰረት እሪከርድ የሚያዝ ከሆነ አሽከርካሪዎቹ ብዙ እሪከርድ እንዲያዝባቸው የሚያደርጉ ስለሆኑ እነዚህን ጥፋቶች በእርከን አንድ ስር በማድረግ እንዲሁም እርከኑን እሪከርድ እንዳይያዝበት በማድረግ የጥፋቶቹን ሁኔታ ሳይሆን የአሽከርካሪዎችን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ እንዲሄድ ተደርጓል፡፡
- አንድ ጥፋት በሪከርድነት የሚቆይት ጊዜ በደንቡ አንቀጽ 85/4/ መሰረት ሁለት አመት የነበረ ቢሆንም በማሻሻያው አንቀጽ 85/9/ መሰረት ግን የአንድ ጥፋት ሪከርድ ቆይታ ወደ አንድ አመት ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ እዚህ ጋር መታየት ያለበት ጉዳይ ደንቡ በሌሎች ሀገሮች የትራፊክ አጥፊነት ከተቀመጡ ቅጣቶች አንጻር ያስቀመጠው ቅጣት ለዘብ ያለ ነው፡፡ ሀገራችን በአመት ከ5000 ሺ ሰው በላይ በትራፊክ አደጋ እያጣች ባለበት ሁኔታ እሪከርድ የማይያዝባቸው ጥፋቶችን በማሻሻያው ላይ እንዲኖሩ መደረጉ እንዲሁም የሪከርድ ቆይታ ጊዜም ዝቅ ማለቱ ተገቢነት ያለው አይደለም፡፡ የሰው ሂወት እንዲጠፋ ከማድረግ አንጻር በማሻሻያው ሰንጠረዥ "ለ" እርከን አንድ ላይ የሰፈሩት ጥፋቶች ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆኑ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን በማሻሻያው ላይ በነዚህ ጥፋቶች ላይ ሪከርድ እንዳይኖር ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ እነዚህ ጥፋቶች በሰው ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ብቻ ሳይሆን ደንቡ በአንቀጽ 3 ላይ ያስቀመጠውን አላማ ማለትም "በመንገድ ላይ ደህንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የትራፊክ እንቅስቃሴ መኖሩን ማረጋገጥ" አንጻር የሚፈጥሩትን ተጽእኖ ማሻሻያው ከግምት ማስገባት ነበረበት፡፡
- ሌላው በማሻሻያው ለውጥ የተደረገበት ሪከርድን የሚመለከተው ክፍል በሪከርድነት የተያዙት ነጥቦች ላይ የሚጣለው ቅጣት ነው፡፡ በደንቡ ላይ ከ አስራ አራት እስከ አስራ ስድስት ነጥብ በሪከርድነት የተያዘበት አሽከርካሪ ለስድስት ወራት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ታግዶ የተሀድሶ ስልጠና እንዲወስድ ይደረግ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ከአስራ ሰባት እስከ አስራ ዘጠኝ ነጥብ ሪከርድ የተያዘበት አሽከርካሪም ለአንድ አመት የአሽከርካሪ ማረጋገጫ ፈቃዱ ታግዶ የተሀድሶ ስልጠና እንዲወስድ ይደረግ ነበር፡፡ በማሻሻያው ላይ ግን ነጥቦቹ ከፍ እንዲሉ ተደርገው ቅጣቱ ግን ቀድሞ ከነበረው የስድስት እና አንድ አመት እገዳዎች በግማሽ ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡ በደንቡ ከሀያ እስከ ሀያ አንድ ነጥብ ሪከርድ የተያዘበት አሽከርካሪ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ ይሰረዝ የነበረ ሲሆን በማሻሻያው ግን ከሀያ ስምንት ነጥብ በላይ ሪከርድ ያለበት አሽከርካሪ እንኳ ፈቃዱ ለአንድ አመት ብቻ ታግዶ ከተሀድሶ ስልጠና በኋላ መልሶ እንዲወስድ ይፈቅዳል፡፡
- በደንቡ ሰንጠረዥ "ለ" ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥፋት ሲፈጸም ቅጣቶቹ በሙሉ በገንዘብ የነበሩ ሲሆን በማሻሻያው ላይ ግን በእርከን ስድስት ላይ የተቀመጡት ሁለት ጥፋቶች ቅጣታቸው ስድስት ወር እና አንድ አመት እገዳ ሆኗል፡፡ እዚህ ጋር ማሻሻያው ያስቀመጠው አሽከርካሪዎች ማንኛውንም አይነት ጥፋት በመፈጸም ከባድ የአካል ጉዳት ሲያደርሱ ወይም ሰው እንዲሞት ሲያደርጉ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዳቸው እንደሚታገድ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እገዳ መጀመር ያለበት መቼ ነው? እገዳውስ በየትኛው አካል ሊወሰን ይገባል? የሚለው ጉዳይ ግልጽ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ አንድ አሽከርካሪ በማሻሻያው እርከን ስድስት ላይ ያሉ ጥፋቶችን ሲፈጽም ጥፋተኛ መባሉ መረጋገጥ ያለበት በፍርድ ቤት እስከሆነ ድረስ እገዳው ሊሆን የሚገባው ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ መሆን አለበት፡፡ ካለበለዚያ ግን ከደንብ መተላለፍ አልፈው የወንጀል ተጠያቂነት ያላቸው ጉዳዮችን ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እንዲወስኑባቸው የማድረግ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ አሽከርካሪ ያለምንም ቸልተኝነት ለሚያደርሰው አደጋ የወንጀል ተጠያቂነት አይኖርበትም፤ ነገር ግን አሽከርካሪው በሰው አካል ላይ ጉዳት ስላደረሰ ብቻ ፈቃዱ መታገድ አለበት የሚለውን ደንብ መተላለፍ ቅጣት በቀጥታ ትራፊክ ተቆጣጣሪ እንዲተገብረው ከተደረገ ውጤቱ ከቅጣት አላማ በእጅጉ ይርቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ማሻሻያው "ጥፋት በመፈጸም" የሚለውን አገላለጽ ጥፋቱ በማን መለኪያ እንደሆነ ማስቀመጥ ይገባው ነበር፡፡ ምክንያቱም አንድ አሽከርካሪ ደንብ ጥሶ አደጋ ቢያደርስም ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ ስላለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እገዳውስ መጀመር ያለበት መቼ ነው? የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ በእርከን ስድስት ላይ ለተቀመጡት ሁለት ጥፋቶች በወንጀል ህጉ ላይ ከ ስድስት ወር በላይ የሚያስቀጡ የእስራት ቅጣት ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አሽከርካሪዎች የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው መዝገባቸው ፍርድ ቤት እስኪቀርብ የሚታሰሩበት ጊዜ ፤ዋስትና መክፈል ካልቻሉ እና መደበኛ ክስ ተጀምሮ እስኪያልቅ ባለው ጊዜ ማረሚያ ቤት የሚቆዩ ከሆነ ወይም ክሳቸው በተፋጠነ የወንጀል ክስ ሂደት ቀርቦ ውሳኔ ከተሰጠበት እና ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ወይም ጥፋተኝነቱን ካልገደበላቸው በቀር የመታሰር እድላቸው ሰፊ የሆኑ አሽከርካሪዎች በእስር ላይ በሚቆዩበት ጊዜ እገዳው ታሳቢ ይደረጋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ጥፋት አድራሾች በህግ ቁጥጥር ስር በሚቆዩበት ጊዜ ሲጀመርም የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዳቸውን ሊጠቀሙበት እንደማይችሉ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በደንቡ ላይ ይህን የእገዳ ቅጣት ማስቀመጥ ባልተገባ ነበር፡፡ በመሆኑም በቅጣት እርከን ስድስት ላይ የተቀመጡት ጥፋቶች ቅጣታቸው ሊጀምር የሚገባው ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ እና አሽከርካሪው የወንጀል ቅጣቱን ጨርሶ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱን መጠቀም ከሚችልበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ምናልባትም ወደፊት ሊወጣ በሚችል መመሪያ ይህን ክፍተት ለመሙላት ቢሞከር መልካም ነው፡፡
- ሌላው በማሻሻያው አንቀጽ 86 ላይ አዲስ የተጨመረው ድንጋጌ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ተጠያቂነትን የሚለከት ነው፡፡
86 (1) ማንኛውም የትራፊክ ተቆጣጣሪ የዚህን ደንብ ድንጋጌዎች ሲያስፈፅም ከአድሎ በፀዳ ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ ሁኔታ መሆን ይኖርበታል፡፡
86(2) ማንኛውም የትራፊክ ተቆጣጠሪ የዚህን ደንብ ድንጋጌዎች ሲያስፈፅም ጥፋት የፈፀመ ስለመሆኑ የትራፊክ ተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት እምነት ያደረበት እንደሆነ በሌላ አግባብነት ባለው ህግ የሚጠየቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው “ሠንጠረዥ ሐ” መሰረት ከትራፊክ ተቆጣጣሪነት ስራ እንዲነሳ ይደረጋል፡፡
በማሻሻያው ላይ ይህ መደንገጉ ጥሩ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ግን ሊጤን ይገባል፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲም ሆነ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ ባለስልጣን ተቆጣጣሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 6/2000 ዓ/ም ስር የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቆጣጣሪዎች ከስራቸው ጋር በተያያዘ ለሚፈጽሟቸው ጥፋቶች የሚወሰዱባቸው እርምጃዎች እንደማንኛውም የከተማው የመንግስት ሰራተኞች በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንጻር በደንቡ ላይ ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከትራፊክ ተቆጣጣሪነታቸው ሲነሱ በሌላ ህግ ላይ ከተቀመጠባቸው ሀላፊነት ጋር ሊጣጣሙ የማይችሉ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡
- ሌላው በማሻሻያው ሰንጠረዥ "ለ" በእርከን አንድ ላይ እንዲካተት የተደረገው ቅጣት የብቃት ማረጋገጫ ሳይዙ ማሽከርከርን የሚመለከት ነው፡፡ በደንቡ በአንቀጽ 6 ላይ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖረው ማንኛውም ሰው ባለሞተር ተሽከርካሪን እንዲያሽከረክር ያልተፈቀደለት መሆኑን ቢገልጽም ይህንን የተላለፈ አሽከርካሪ ላይ ያስቀመጠው ቅጣት አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል በአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አዋጅ ቁጥር 600/2000 ዓ/ም አንቀጽ 17 እና አንቀጽ 21 ላይ ብቃት ማረጋገጫ ሳይዙ ማሽከርከርንም ሆነ ብቃት ማረጋገጫ ሳይኖር ማሽከርከርን በመከልከል ቅጣት አስቀምጧል፡፡ በዚህም መሰረት ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አዋጁን መሰረት አድርገው ቅጣት ይጥሉ ነበር፡፡ በማሻሻያው ላይ የህግ ደረጃዎችን ከመጠበቅ አንጻር መሰረታዊ ስህተት የተፈጸመው አዋጅ ቁጥር 600/2000 ዓ/ም ን በሚመለከት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ማሻሻያው ቅጣት ሰንጠረዥ ውስጥ በመክተት ጥፋት ናቸው የሚላቸውን ተግባራት በደንቡ የአንቀጽ ዝርዝሮች ውስጥ ተግባራቱን እንዳይፈጸሙ ወይም እንዲፈጸሙ ያካተተው ሊሆን ይገባል፡፡ ነገር ግን ብቃት ማረጋገጫ ሳይዙ ማሽከርከር በማሻሻያው ላይ በአንቀጽ ደረጃ ጥፋት ሆኖ ባልተገለጸበት ሁኔታ ቅጣት ዝርዝሩ ላይ ማስቀመጡ ቀዳሚው ስህተት ሲሆን፤ በአዋጅ የተሸፈነን ድንጋጌ ቅጣት በደንብ ደረጃ በማሻሻል ቅጣቱ በማሻሻያው ሰንጠረዥ "ለ" እርከን አንድ ስር እንዲካተት ማድረጉ ሌላኛው ስህተት ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 600/2000 ቅጣት ሰንጠረዥ "ለ" ላይ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይዝ ለሚያሽከረክር አሽከርካሪ 100/አንድ መቶ / ብር ፤ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖረው ለሚያሽከረክር ደግሞ የ5000/አምስት ሺ/ ብር፣ ተሽከርካሪውን የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለሌለው ሰው አሳልፎ ለሰጠ ማንኛውም ሰው ደግሞ 3000 ሺ ብር፣ የዕድሳት ጊዜ አሳልፎ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱን ለማሳደስ ለቀረበ አሽከርካሪ 150 ብር ቅጣት ተቀምጧል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በደንቡ ማሻሻያ ሰንጠረዥ "ለ" እርከን አንድ ላይ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ እያለው ሳይዝ ለሚያሽከረክር 100 ብር፣ "ሌሎች የደንብ መተላለፍ ጥፋቶች" በሚለው ክፍል በተራ ቁጥር ስድስት ላይ የዕድሳት ጊዜ አሳልፎ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱን ለማሳደስ የቀረበ አሽከርካሪ 150 ብር፣ በተራ ቁጥር አስራ አራት ላይ ላይ በባለቤትነት ወይም በይዞታው የያዘውን ተሽከርካሪ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለሌለው ሰው አሳልፎ የሰጠ ማንኛውም ሰው 3000 ሺ ብር፣ በተራ ቁጥር አስራ አምስት ላይ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖረው ተሽከርካሪ ላሽከረከረ ማንኛውም ሰው 5000 ሺ ብር ቅጣት ተቀምጧል፡፡ በእርግጥ ቅጣቶቹ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ባያመጡም በስራ ላይ ያለ አዋጅ ላይ የተቀመጠን ቅጣት በደንብ ማካተት ለተግባራዊነትም አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ትክክለኛ የህግ አወጣጥ ስረአትም አይደለም፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን በአዋጅ ቁጥር 600/2000 ዓ/ም ላይ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖረውም ሆነ ሳይዝ ማሽከርከር በተከለከለበት ሁኔታ በደንብ ቁጥር 208/2003 በአንቀጽ 6 ላይ ያለብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ማሽከርክር የደንብ መተላለፍ ሆኖ መቀመጥ አልነበረበትም፡፡ ደንቡ ከአዋጅ ቁጥር 600/2000 ዓ/ም በኋላ እንደመውጣቱ ይህን አንቀጽ ማካተት አያስፈልግም ነበር፡፡ በመሆኑም ይህን ድንጋጌ ከደንቡ ማሻሻያ ላይ ማውጣት ሲገባ ብቃት ማረጋገጫ እያላቸው ሳይዙ የሚያሽከረክሩትንም ማካተቱ መሰረታዊ የህግ ደረጃዎችን የሚቃረን ነው፡፡ ከሪከርድ አያያዝ ጋር በተገናኘም መሰረታዊ ግጭት ያስነሳል፡፡ ለምሳሌ በአዋጅ ቁጥር 600/2000 ዓ/ም ላይ የአንድ ሪከርድ የቆይታ ጊዜ ለቀላል ጥፋት አንድ አመት ሲሆን ለከባድ ጥፋት ደግሞ ሶስት አመት እንደሆነ በአንቀጽ 25 ላይ ተቀምጧል፡፡ በማሻሻያው አንቀጽ 85/9/ መሰረት ደግሞ የማንኛውም ሪከርድ ቆይታ አንድ አመት እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ በአዋጁ መሰረት ከሄድን የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይዝ የተቀጣ አሽከርካሪ ቅጣቱ አንድ አመት ሪከርድ የሚያዝበት ሲሆን በማሻሻያው ላይ ግን የብቃት ማረጋገጫ ሳይዝ የሚያሽከረክር አሽከርካሪ የሚቀጣው በእርከን አንድ ላይ ሰለሆነ ሪከርድ አይያዝበትም ይህ ደግሞ መሰረታዊ ግጭት ነው፡፡ ሲቀጥልም ማሻሻያው ሌሎች ደንብ መተላለፎች ለሚለው ክፍል እሪከርድን በሚመለከት ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 600/2000 ላይ ሶስት አመት ሪከርድ ይያዝባቸው የነበሩ ለምሳሌ ያለ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ማሽከርከር እና ማረጋገጫ ፈቃድ ለሌለው ሰው ተሽከርካሪውን አሳልፎ የሰጠ ሰው ከሪከርድ ነጻ ሆኑ ማለት ነው፡፡ በአዋጁ ላይ ሪከርዶች ተደምረው ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ያሰርዛል፡፡ በደንቡ ማሻሻያ ላይ ደግሞ ይህ የለም፤ ነገር ግን በአዋጁ ላይ ያሉ ተመሳሳይ ጥፋቶች የደንቡ ማሻሻያ ላይ እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡ አዋጅና ደንብ የሚቃረኑ በሆነ ጊዜ የአዋጁ ተፈታጻሚነት እርግጥ ቢሆንም ደንቡን በሚያስፈጽሙት አካላት የተለያዩ ቅጣቶች በተመሳሳይ ጥፋት ሊፈጸም እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ አዋጅ ቁጥር 600/2000 ዓ/ም በቅርብቡ በ አዋጅ ቁጥር 1074/2010 ዓ/ም የተሻሻለ ቢሆንም/ለጊዜው ማሻሻያውን ማግኘት አልተቻለም / ይህንን ችግር ሊፈታው የሚችለው የደንቡ ማሻሻያ ያካተታቸውን የአዋጁ ክፍሎች ከአዋጁ ላይ ማውጣት ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ ይህም ቢሆን እራሱን የቻለ ሌሎች ክፍተቶችን ያመጣል ፡የማይካደው ሀቅ ግን አዋጅ ቁጥር 600/2000 ሺ እነዚህን ማሻሻያዎች ቢያደርግም አመት ለሚሞላ ጊዜ ይህ መሰረታዊ ክፍተት የነበረ መሆኑ ነው፡፡
- በተሽከርካሪው ውስጥ የተሟላ የመጀመሪያ ዕርዳታ መስጫ ኪት እና የሚሰራ የድንገተኛ እሳት ማጥፊያ መሳሪያ ሳይኖረው የንግድ ተሽከርካሪ ያሽከረከረ በሚል በሰንጠረዥ "ለ "እርከን አንድ ላይ አስራ ሶስተኛ ሆኖ በጥፋተኝነት የተጨመረው ዝርዝር የንግድ ተሸከርካሪን ብቻ ማስገደዱ በየትኛውም አግባብ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህ መሳሪያዎች የንግድም ሆነ የንግድ ላልሆኑ ተሸከርካሪዎች አስፈላጊ ስለሆኑ ግዴታው ለሁሉም ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ በማሻሻያው ላይ በአንቀጽ ደረጃ በግልጽ ጥፋት መሆኑ ሳይገለጽም የጥፋት እርከኖች ላይ መስፈሩም አግባብነት የለውም፡፡ በአንቀጽ 85/1/ ላይ "የዚህን ደንብ ድንጋጌ ተላልፎ የተገኘ አሽከርካሪ ከዚህ ደንብ ጋር በተያያዘው ሠንጠረዥ ለ መሰረት ይቀጣል" ስለሚል ሰንጠረዡ ላይ የሚቀመጠው ቅጣት ደንቡ ላይ ጥፋት ሊባል ይገባል፡፡
- ከአሽከርካሪዎች ውጭ ያሉ የመንገድ ተጠቃሚዎችን እና ህብረተሰቡን በሚመለከትም በማሻሻያዎቹ ላይ የነበሩ ቅጣቶች በከፊል ሲሻሻሉ አዳዲስ ጥፋቶችም ተጨምረዋል እንዲሁም ቀድሞ በአንቀጽ ደረጃ የነበሩ ነገር ግን ቅጣት ላይ ያልተቀመጡ ተግባራትም ቅጣት እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ የጆሮ ማዳመጫ እያናገሩ መንገድ ማቋረጥ/አዲስ የተጨመረ/፣ ለመጫወቻና ለጊዜ ማሳለፊያ ተብሎ የተሰራ ብስክሌት ወይም በጫማ መልክ የሚጠለቅ ተንሸራታች ወይም ሌሎች መጫወቻዎችን በተሽከርከሪ መንገድ ላይ ማሽከርከር ወይም መጠቀም፣ ማናቸውም ለእግረኛ ክልክል ነው የሚል ምልክት ባለበት መንገድ ወይም እግረኛ እንዳያቋርጥ በተከለከለበት የማሳለጫ ወይም የቀለበት መንገድ ያቋረጠ ይገኙበታል፡፡ መሰረታዊው ጉዳይ ግን የደንቡ ማሻሻያ እግረኞችን በሚመለከት ቅጣት የሚፈጸምበትን መንገድ በዝምታ አልፎታል፡፡ ምናልባትም በመመሪያ የሚመለስ ካልሆነ በቀር ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ከሆኑት የደንቡ ክፍሎች መሀከል ከአሽከርካሪዎች ውጪ ያሉ ቅጣቶችን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ይህን በትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ብቻ ተግባራዊ ማድረግ ከባድ ነው፡፡
በማሻሻያው ግልጽነት እንዲኖራቸው የተደረጉ አንቀጾች በከፊል
- በደንቡ በአንቀጽ 2/12/ ላይ ለትራፊክ ተቆጣጣሪ ከተሰጠው ትርጉም በተሻለ እና ግልጽ በሆነ መልኩ በመሻሻያው አንቀጽ 2/12/ የተተካ ሲሆን ትራፊክ ተቆጣጣሪ ማነው? የሚለውንም በማሻሻያው አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 13 እና 14 ላይ ትርጉም ተሰቶታል፡፡ ይህም የፖሊስ አባል ከሆኑት ትራፊኮች ውጪ ያሉ ተቆጣጣሪዎችንም ግልጽ ሆነው እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡
- በአንቀጽ 19/1/ ላይ ከዚህ ቀደም አንድ አሽከርካሪ ምልክት ማሳየት ያለበትን እርቀት በማይገልጽ መልኩ ምልክት ማሳየት እንዳለበት ተደንግጎ የነበረ ቢሆንም በማሻሻያው ላይ ግን በከተማ ውስጥ በ25 ሜትር፣ ከከተማ ውጪ ደግሞ በ50 ሜትር ርቀት ምልክት ማሳየት ግዴታ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ በደንቡ ላይ በአንቀጽ ደረጃ ጥፋት የነበረው ምልክት አለማሳየት ብቻ ሲሆን በቅጣት ሰንጠረዡ ላይ ግን የምልክት ማሳያ ርቀቶቹ ተቀምጠው ነበር፡፡ በማሻሻያው ላይ ግን ይህ ወጥ እንዲሆን በማድረግ በአንቀጹም ላይ ሆነ በጥፋት ዝርዝሩ ላይ የምልክት ማሳያ ርቀቱ እንዲገለጽ ተደርጓል፡፡
- በደንቡ አንቀጽ 50/4/ ላይ ማንኛውም ሞተር ብስክሌት ሞተሩ ከሚችለው ሰው በላይ መጫን እንደማይችል ይገልጽ የነበረ ቢሆንም በማሻሻያው ላይ ግን በሞተር ሳይክል ላይ ከ አንድ ሰው በላይ መጫን ክልክል እንደሆነ ተቀምጧል፡፡
- የደንቡ አንቀጽ 40/2/ ላይ ከ13 አመት በታች የሆኑ ህጻናት በተሸከርካሪው የኋላ ወንበር መቀመጥ እንዳለባቸው በሚያዘው ክፍል " የኋላ ወንበር" የሚለው አገላለጽ ከአሽከርካሪው ጀርባ ካለው ወንበር ይጀምራል ወይስ የተሽከርካሪውን የመጨረሻ የኋላ ወንበር ለማለት ተፈልጎ ነው? የሚለው ለትርጉም ክፍት ነበር፡፡ በማሻሻያው ግን እድሜያቸው ከ 13 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በተሽከርካሪው የፊት መቀመጫ መቀመጥ እንደሌለባቸው በማስቀመጥ ድንጋጌውን ግልጽ አድርጎታል፡፡
- በደንቡ ላይ " የመንገድ ማመላከቻን" በሚመለከት ያልነበረ ሲሆን በማሻሻያው አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 30 ላይ ግን የመንገድ ማመላከቻ ትርጉም ተሰቶታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መካተቱ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘባቸው በርከት ያሉ አንቀጾች ላይም ተካቷል፡፡
እንደመውጫ በሀገራችን በቅርብ አመታት የሚወጡ ህጎች ረጅም ጊዜ ቆይታ የሌላቸው እየሆኑ ነው፡፡ ይህም የህግ ባህሪን ይቃረናል፡፡ ህጎቹ ለረጅም ጊዜ አንዳይቆዩ የሚያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት የሚያልፉበት የህግ አወጣጥ መንገድ ልል በመሆኑ ነው፡፡ ህጎቹ ረጅም ጊዜ ካለመቆየታቸውም በላይ በየጊዜው የሚሻሻሉ ህጎች ብዛት ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከትራንስፖርት ጋር የተያያዙ ህጎቻችንም ሰፊ የሆነ ክፍተት እና ግጭት ኪሚስተዋልባቸው ህጎች ውስጥ ቀዳሚ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ትራንስፖርትን የሚመለከቱት ህጎቻችን በራሳቸው እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ባይቀርፉትም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ግን ቁልፍ መሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ከዚህ አንጻር ደንብ ቁጥር 208/2003 ዓ/ም በደንብ ቁጥር 395/2009 ዓ/ም ሲሻሻል ይህን ከግምት በማስገባት እንዲሁም ደንቡ ከሌሎች ህጎች ጋር ያለውን ግጭት በቀነሰ መልኩ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡ ደንቡ ያሻሻላቸው ድንጋጌዎች መብዛታቸውም ደንቡን ከማሻሻል ይልቅ በአዲስ መልክ ማውጣት ደንቡን ለመረዳትም ሆነ ለምቹነት የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ በማሻሻያው የታየው መሰረታዊ ክፍተት እሪከርድን በመያዝ እና አሽከርካሪዎችን በማረም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረው የነበረውን የሪከርድ ክፍል ላይ በማሳነስ ለውጥ ለማምጣት መሞከሩ የህብረተሰቡን ችግር ቅድሚያ የሰጠ አለመሆኑ ነው፡፡ ይህም ደንቡን በማዘጋጀት ሂደት የነበሩ ተሳታፊዎችን ቅድሚያ ለሚገባው ጉዳይ ትኩረት አለመስጠትን በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ በተረፈ በማሻሻያው ላይ ለመንገድ ትራፊክ ፍሰቱ ጤናማነት አስፈላጊ የሆኑ ድንጋጌዎች መካተታቸው እና የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት መሞከሩ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ያልሸፈናቸው በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ እርግጥ ነው በትራፊክ ተቆጣጣሪ መሸፈን ያለበት የአዲስ አበባ ክፍል እንኳ ሀምሳ በመቶ ሳይሸፈን የህጎች መኖር ለውጡ እንብዛም ቢሆንም ከምንም በላይ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ላለው የትራፊክ አደጋ በቂ ትኩረት ሊሰጥ ስለሚገባ ህጎቻችን ሲወጡም ሆነ ሲሻሻሉ ቢፈተሹ መልካም ነው፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments