Font size: +
13 minutes reading time (2680 words)

የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ማቆም መብትና ሕገወጥ ተግባሮች ምንነት በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ የሲቪል አቪዬሽን ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማና የፌዴራል ፖሊስ የእስር ዕርምጃ ተከትሎ በተለያዩ ሚዲያዎች በመንግሥት በኩል በተወሰዱት ዕርምጃዎች ዙሪያ እየቀረቡ ያሉ ሕግ ነክ አስተያየቶች ውይይቶች፣ ሰሞነኛ ክርክሮችንና ተያያዥ ነጥቦች መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች ሕጋዊ የሥራ ማቆም መብት የሕግ ወሰን እስከ የት ድረስ ነው? የሚለውን ጥያቄ ከሕገ መንግሥት መሠረታዊ መርሆች አንፃር በመመልከት በመብቱ አፈጻጸም ላይ የሚነሱ አንዳንድ የሕግ ጉዳዮችን በአጠቃላይ በአገሪቱ የተለያዩ የአሠሪና ሠራተኛ መብትና ግዴታዎችን አስመልክቶ በፌዴራል መንግሥት በኩል ከወጡ ሕጎች አንፃር በመጠኑ መዳሰስ ነው፡፡

የሥራ ማቆም መብት ጽንሰ ሐሳብና በሕግ የተሰጠው ጥበቃ

የሥራ ማቆም አድማ ሠራተኞች በሕግ ዕውቅና ተሰጥቶት ያለ የኅብረትና በነፃነት የመደራጀት ሰፊ የሆነው መሠረታዊ መብት አንዱና ወሳኝ ከሚባሉት ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሥራ ማቆም ዕርምጃ ሠራተኞች ለአንድ የተወሰነ ወቅት የሚሠሩትን ሥራ እንዲቋረጥ በማድረግ ለጋራ ፍላጎታቸው በአንድነት በመሆን አቋማቸውን የሚገልጹበት የመታገያ ሥልት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ ከሥራቸው ጋር በቀጥታ በሚገናኙ ማንኛውም ጉዳዮች በተለይም ደግሞ ከተቋማዊ፣ ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ በቀጥታ በሚያያዙ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ጥያቄያቸውን ሕጉን ተከትለው ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ ውሳኔ ሰጪ አካላት የሚያቀርቡበትና ድምፃቸውን ለማሰማት የሚችሉበት የመደራደሪያ ሕጋዊ ሥልቶች ነፀብራቅ እንደሆነ ከሠራዊቶች የቡድን መብቶች ታሪካዊ አመጣጥና ከዳበሩት የሕግ ፍልስፍናዎች የተጻፉ ዓለም አቀፍ የሕግ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ይህም ሲባል መብትና ጥቅማቸውን አንድም በሚመሠርቱት የሠራተኛ ማኅበሮች በኩል ወይም በጋራ በመሆን አሠሪዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያስችላቸው ሕጋዊ መንገድ እንደሆነ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች መብትን ለማስጠበቅ ከወጡ ስምምነቶች መገንዘብ ይቻላል።

 የዓለም አቀፉን የሠራተኞች መብት በሕግ ጥበቃ ለማሰጠት ከወጡት የተለያዩ ስምምነቶች እንዲሁም አገሮች አባል የሆኑበት የበላይ ጠባቂ የሆነው ተቋም (International Labor Organization (ILO)) አማካይነት በየጊዜው ስለሠራተኞች በነፃነት የመደራጀትና የሠራተኛ ማኅበራት የመመሥረት መብት (Right to Organize & Collective Bargaining Convention (1948/51)) & Freedom of Association & Protection of the Right to Organize Convention) (1948/51)) አስመልክቶ በዝርዝር ከፀደቁት የሕግ ሰነዶች እያንዳንዱ አገሮች በውስጥ የሕግ ማዕቅፎቻቸው ተጨባጭ ሁኔታዎቻቸውን መሠረት በማድረግ ለመብቱ አፈጻጸምና አተገባበር ልዩ ሕጎች በማውጣት ሕጋዊ ጥበቃና ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጥሩ ግዴታዎችን ያስቀምጣሉ፡፡   በተለይም ኢትዮጵያ አባል የሆነችበትና በ1987 ዓ.ም. በፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ 3 አካል የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶችን ለመደንገግ የወጣው የቃል ኪዳን ሰምምነት (International Convenant on Economic, Social, and Cultural Rights (ICESCR)) የሠራተኞች አጠቃላይ መብቶችን በሚመለከት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ከመሆኑም በተጨማሪ በቃል ኪዳን ስምምነት ሰነዱ አንቀጽ 8 ውስጥ የሥራ ማቆም ዕርምጃ የመውሰድ መብት የየአገሮቹን ገዥ ሕጎች ተከትሎ በሁሉም መስክ የሚገኙ ሠራተኞች ገደብ ሊጣልባቸው ከሚችሉት ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፖሊስና ከመንግሥት የአስተዳደር ሠራተኞች በስተቀር መብቱ ሳይሸራረፍና ያለአድልኦ በእኩልነት ሊከበር እንደሚገባው ዋስትና ይሰጣል፡፡ ሆኖም አባል አገሮች በውስጥ ባላቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር በማገናዘብ በሕጎቻቸው ላይ የተወሰኑ ገደቦች እንዲሁም የሥራ ማቆም ዕርምጃ ፈጽሞ ማድረግ የማይቻልባቸውን ዘርፎች በሚመለከት በዝርዝር ሕግ መከልከል እንደሚችሉ ነገር ግን የሠራተኞች የጋራ መብት ፍፁምነት የሌለው ቢሆንም፣ እንኳን ገደብም ሆነ ክልከላ ለማድረግ የሚቻለው ቢያንስ ቢያንስ ግልጽ የሆኑትን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ ሕጋዊ መሥፈርቶችንና አሠራሮች ጋር ተጣጥሞና መሠረታዊ የሆነውን የመብቱን ዓላማ በማይቃረን መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በአጠቃላይ ለሁሉም ዓይነት ሠራተኞች ማለትም በግሉ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሠሩትም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤት የሚያገለግሉ ሠራተኞች የጋራ መብታቸውን ሊያስጠብቁበት የሚያስችልላቸው ማኅበሮችን የመመሥረት እንዲሁም በፈቀዱት መንገድ በኅብረት ሆነው በመደራጀት መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበርና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም የሚያጎናፅፋቸውን ተቋማዊና ሕጋዊ አሠራሮችን ጥበቃ እንደሚሰጠው ያረጋግጣል፡፡ በተለይም ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 42 (1) (ለ) መሠረት የሥራ ማቆም አድማ የማድረግ ወይም ዕርምጃዎችን የመውሰድ መብትን በጠቅላላው ዕውቅና የሰጠ ቢሆንም፣ የመብቱ ተጠቃሚ የሚሆኑትን ሠራተኞች በተመለከተ በሕግ አውጪው በሆነው አካል (የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት ደረጃ) በዝርዝር ሕግ እንደሚወሰን ይጠቁማል። በዚሁ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ፊደል (ሐ) ላይ በማያሻማ ሁኔታ ተቀምጦ እናገኘዋለን። በዚህም መሠረት በተለይ የዚህ መብት አፈጻጸምን በሚመለከት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች ገደብ ሊደረግባቸው እንደሚችል በግልጽ ያመላክታል።

የሠራተኛ መብትና ግዴታዎችን በሚመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ዓይነት የሕግ ማዕቀፎች ያሉ ሲሆን፣ አንደኛ የግሉን ዘርፍና የተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚመለከቱና በአዋጅ ቁጥር 377/96 የሚተዳደሩ፣ ሁለተኛ ሙሉ በሙሉ በሲቪል ሰርቪስ መዋቅር የሚተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች (በፌዴራል ደረጃ ያሉትን በሚመለከት) አዋጅ ቁጥር 1064/2010 የሚተዳደሩና ሦስተኛ ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ለምሳሌ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ባልደረቦች፣ የፍርድ ቤት ዳኞችና ዓቃብያነ ሕጎች፣ የፓርላማና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት፣ እንዲሁም ከሥራው ባህሪ የተነሳ ልዩ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት የሚያስፈልጋቸው አካላትን ለምሳሌ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ወዘተ. በሚመለከት የተለየ ሕግ ወጥቶላቸው የሚተዳደሩ ስለመሆኑ ይታወቃል። ለአብነትም ያህል የፌዴራል የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 የሕጉን የተፈጻሚነት ወሰን በሚደነግገው አንቀጽ 3 (2) በፊደል (ሠ) ላይ እንደተገለጸው በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ እንደ ጦር ኃይል ባልደረቦች፣ የፖሊስ ሠራዊት ባልደረቦች፣ የመንግሥት የአስተዳደር ሠራተኞች (“Employees of State Administration”)፣ የፍርድ ቤት ዳኞች፣ የዓቃብያነ ሕግና ሌሎችንም የሚመለከት ሲሆን፣ በተጠቀሱት ዝርዝር የቅጥር የሥራ ግንኙነት አስመልክቶ ተፈጻሚ እንደማይሆን ተመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አዋጅ ቁጥር 1064/2010 በሚመለከት ሊሰመርበት የሚገባው ዋና ነጥብ በመሠረቱ አዋጁ ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ለመምራትና ለመቆጣጠር ታስቦ የወጣ ሕግ ነው፡፡ የተገለጸውን ሐሳብ የበለጠ የሚያጠናክርልን በአዋጁ ውስጥ ሰፊ ትርጓሜ ከተሰጣቸው ሁለት አንኳር ጉዳዮችን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡ አንደኛ በአንቀጽ 2 (1) መሠረት የመንግሥት ሠራተኛ ማለት በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም በዚህ ትርጉም ውስጥ የማይሸፈኑ አምስት ዝርዝሮችን ማለትም የአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን የማይመለከታቸውና በሌሎች ልዩ ሕጎች ለየብቻ የሚተዳደሩ የመንግሥት ተቋማት እንደማይካተቱ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሁለተኛ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የትኞቹ ናቸው? ለሚለው ደግሞ በአንቀጽ 2 (3) ሥር የተቀመጠው ትርጉም መሠረት ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመና ከመንግሥት በሚመደብለት በጀት የሚተዳደር የፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው በማለት ተመልክቷል፡፡ ይሁን እንጂ በአዋጁ ውስጥ በግልጽ እንዲገለሉ ከተደረጉት ዘርፈ ብዙ የመንግሥት ተቋማት ዓይነትና ሕጉ ሊያሳካ ከፈለገው አጠቃላይ ዓላማዎች አንፃር ከተመለከትነው የሕጉ የተፈጻሚነት ወሰን በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ ብቻ ተገድቦ የሚገኝ እንጂ በስያሜው ላይ እንደተገለጸው ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞች የሚገዛ አይደለም፡፡ ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት በመሠረቱ በአስተዳደር መሥሪያ ቤትና በመንግሥት መሥሪያ ቤት መካከል ሰፊ የሕግ ልዩነት በመኖሩ ነው፡፡ በተለይም የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ተብለው የሚታወቁት በባህሪያቸው በሕግ የሚሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ልዩ የሆኑ የሕግ አውጪነትና የዳኝነት ሚናን በተደራቢነት የሚይዙ ናቸው፡፡ ሆኖም ከዚህ በተቃራኒ ይህንን ዓይነት ሥልጣን ሳይኖራቸው ለአንድ የተወሰነ ግብና ፖሊሲ ለማሳካት ተብሎ የሚቋቋሙ በርካታ መሥሪያ ቤቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የመንግሥት የአስተዳደር ሠራተኞች (Civil Servants) በአስተዳደር መሥሪያ ቤት የተቀጠሩ ሠራተኞችን የሚወክል ሲሆን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች (Public Employees or Government Employees) ግን በሁሉም በመንግሥት በተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የተቀጠሩ ሠራተኞች የሚጠሩበት ስያሜ ነው፡፡ (አብርሃም ዮሐንስ፣ አሠሪና ሠራተኛ ሕግ፣ 2009፣ ገጽ 35 እስከ 36 ይመልከቱ)፡፡

በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች 

በሁለቱም የተገለጹት ሕጎች የግልም ሆነ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችን በሚመለከት አንድ ወጥና ጠቅላላ ተፈጻሚነት ካላቸው አዋጆች ውስጥ የማይታቀፉ ነገር ግን በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ የመንግሥት ተቋማት እንዳሉ ከላይ በጨረፍታ ለመጠቆም ተሞክሯል፡፡ ሆኖም አሁን ለተያዘው ርዕሰ ጉዳይ የበለጠ ለማብራራት አስፈላጊ ነው ብዬ ስለማምን ጥቂት ነጥቦችን በአጭሩ ለማስቀመጥ እሻለው፡፡ እዚህ ላይ አንባቢ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያስፈልገው ነገር አሁን በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ቢያንስ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ብቻ ተወስነን ከተመለከትነው በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ ሠራተኞችና በእነሱ ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑት ሕጎች በቁጥርም ሆነ በዓይነት እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥትና ሠራተኞቹ መካከል ያለውን ወይም የሚኖራቸውን የሥራ ግንኙነት የሚገዙት ሕጎች ወጥነት በእጅጉ የሚጉድላቸው እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ እየተለመደ የመጣው አሠራር እንደሚያስረዳን እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በሚወጡት ሕጎች መሠረት የራሱን የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ እንዲኖራቸው እየተመረጠ ያለው አዝማሚያ ልጓም ሊበጅልት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከተያዘው ጉዳይ ለመወሰን ያህል እነዚህን የተበታተኑና ወጥነት የሚጎድላቸው የልዩ ሕጎች በሦስት ዘውግ ከፍለን መመደብ ይቻላል፡፡ አንደኛ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል በሚወጡ አዋጆች፣ ሁለተኛ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል በሚወጡ ደንቦችና በመጨረሻም የመንግሥት መሥሪያ ቤቱ በራሱ በሚያወጣቸው መመርያዎች የሚተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞች በማለት ጠቅልለን ልንገልጻቸው እንችላለን፡፡ 

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባቸው ዋና ዋና የሕግ ፍሬ ጉዳዮችን በጥቂቱ ማስፈር አስፈላጊ ነው፡፡ አንደኛ የመንግሥት ሠራተኞችና የመንግሥት የአስተዳደር ሠራተኞች ልዩነት በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ በምን መልኩ ይገለጻል? የሚለው ሲሆን፣ ይህም ደግሞ የሚፈጥረው የሕግ ትርጉም በቀጥታ የሚገናኘው ሐሳብ ከመነሻውም ቢሆን በአገራችን የሕግ ሥርዓት መሠረት የመንግሥት መሥሪያ ቤትና የመንግሥት የአስተዳደር መሥሪያ ቤት ወይም በሕግ የተቋቋመ መንግሥታዊ ተቋም ከሚለው መሠረታዊ የሕግ ማዕቀፍ ልዩነት ጋር የሚመነጭና በተግባርም የሕግ አፈጻጸም ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ የሆነው ውዝግብ እንዲሁም የተዘበራረቁ እርስ በርሱ የሚጋጩ አስተሳሰቦች በተለያዩ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ጭምር ሲንፀባረቅ የሚስተዋለው ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛ በመሠረቱ በሕግ አተረጓጎም አግባብ ካየነው ሁሉም የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቢሆኑም፣ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግን የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች አይደሉም፡፡ ይህንን ነጥብ ሰፋ አድርገን ከተመለከትነው የችግሩን ምንጭ የበለጠ ለማሳየት ያህል የተጠቀሱትን ፍሬ ጉዳዮች ከላይ በጨረፍታ እንደተጠቆመው የእንግሊዝኛ ቋንቋ አቻ ስያሜዎቻቸው ላይ የሚገኘው ግልጽ የትርጉም ልዩነት እዚህ ጋ ለማነፃፀሪያነት መጥቀሱ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ሦስተኛ ሌላው ወሳኝ ነጥብ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ሆነው ደግሞ በልዩ ሕግ የሚተዳደሩ ልዩ ልዩ ተቋማትን የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህም በግልጽ በአዋጆቹ ትርጓሜ በሚይዘው ክፍል ውስጥ እንዲገለሉ የተደረጉ ሠራተኞች በልዩ የሕግ ማዕቀፍ ማለትም በአዋጅ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቦችና በተለያዩ መመርያዎች የሚተዳደሩና የተፈጻሚነት ወሰኑም ለብቻው ተነጥሎ መብትና ግዴታዎችን የሚገዙ ሕጎችን ይመለከታል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የሲቪል አቪዬሽን ሠራተኞች በሦስተኛ ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፣ እንደ መንግሥታዊ ተቋም ሠራተኝነታቸው ደግሞ የሚጠበቅባቸው ግዴታዎችና የሚኖራቸውን መብቶች በሚመለከት አጠቃላዩን የመንግሥት ሠራተኞች ደረጃ ከግምት ውስጥ ያስገባ ይሆናል፡፡ ለዚህም የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤትን በድጋሚ ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 616/2001 ውስጥ የዋናው ዳይሬክተር ሥልጣንና ተግባር የሚደነግገው አንቀጽ 12 (2) (ሠ) ሥር እንደሚከተለው ይነበባል።

‹‹የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ሕጎችን መሠረታዊ ዓላማ ተከትሎ በመንግሥት በሚፀድቅ መመርያ መሠረት የባለሥልጣኑን ሠራተኞች ይቀጥራል፣ ያስተዳድራል፤››  ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ነጥብ የሲቪል አቪዬሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 616/2001 በፊት የነበረውና የተሻረው አዋጅ ቁጥር 273/1994 ውስጥ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሠረት የሚተዳደሩ ስለመሆኑ በአንቀጽ 9(2) (ሠ) ሥር በግልጽ ተቀምጦ ነበር። አሁን በድጋሚ ሲሻሻል ከተቀየሩት ወሳኝ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በልዩ ሕግ እንደሚተዳደሩ ስለሚያመላክት የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅም ሆነ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ስለመሆኑ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ይሁን እንጂ አዋጅ ቁጥር 616/2001 አንቀፅ12 (2) (ሠ) መሠረት ይወጣል የተባለው መመርያ ስለመፅደቅ አለመፅደቁ በግሌ ለማረጋገጥ ያደረግኩት ጥረት የተሳካ ባለመሆኑ የተነሳ፣ እዚህ ላይ የአቪዬሽን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በምን የሕግ ማዕቀፍ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ሲተዳደሩ እንደነበረ የተሟላ መረጃ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ ከዚህ አንፃር የሥራ  ማቆም ዕርምጃዎች በሚመለከት በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው የሚሠሩ ማንኛውም ሠራተኞች በሕግ ጥበቃ ተስጥቷል አልተሰጠም የሚለውን አንኳር ጥያቄ ለመመለስ ይቻል ዘንድ በሚቀጥለው የጽሑፉ ክፍል ሰፋ አድርገን መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡

ሕጋዊና ሕገወጥ የሥራ ማቆም ዕርምጃዎች የሕግ ወሰኑ

የሰሞኑን የአቪዬሽን ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ ፌዴራል ፓሊስ በአድማው ውስጥ የተሳተፉ ሠራተኞችን ማሰሩን በነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በአገሪቱ የዜና ማሠራጫ ጣቢያዎች መንግሥታዊም ሆነ የግል ሚዲያዎች ሰፊ የዜና ሽፋን አግኝቶል ማለት ችለናል። ሆኖም ግን ከዜና ዘገባ ባለፈ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ መብታቸውን በጋራ ለማስጠበቅ ጥያቄ ያቀረቡት ሠራተኞች በወንጀል ተጠርጥረው ለእስር ሊዳረጉ የቻሉበት ዋነኛ ምክንያት ከፌዴራል ፖሊስ መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው ከሆነ ሕገወጥ የሆነ የሥራ ማቆም ድርጊት ላይ በመሳተፋቸው ስለመሆኑ ይገልጻል። ለዚህም በይፋ ባይገለጽም እየቀረበ ያለው የሕግ አስተያየትና ምክንያት በዋናነት የወንጀል ሕጉ ውስጥ በአንቀጽ 421 ላይ የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ድርጊት ሕገወጥ ተግባር ተደርጎ እንደሚወሰድና የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትል የሚሰጡ የተለያዩ ትንታኔዎችን ማስተዋል ይቻላል።

ይሁን እንጂ ከላይ አጠር ባለ መልኩ ስለኢትዮጵያ የሠራተኞች መብትና ግዴታዎች ጋ በተገናኘ ለማቅረብ ከተሞከረው የሕግ ማዕቀፎች አንፃር የመንግሥት ሠራተኞችን የሥራ ማቆም አድማ በዝርዝር የሚከለክል የተለየ ሕግ ከሌለ የአቪዬሽን ሠራተኞች ደግሞ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ሥር የማይተዳደሩ ስለሆነ በምን መልኩ ነው አድማው ሕገወጥ ሆኖ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ውስጥ ሊገባ ወይም ሊታቀፍ የሚችለው? የሚለው ጥያቄ በጥልቀት ሊመረመርና ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ ነው። የእኔ ምልከታ ዋና ነጥብም ከላይ በአጭሩ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት የሚያተኩረው የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ የሥራ ማቆም አድማና ሌሎች የጋራ መብቶችን ዕውቅና በመስጠት ዝርዝር ሕጉን ለሕግ አውጪው የተተወ ስለሆነ በአጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች መብት በሕግ የተከለከለ ተደርጎ በመወሰድ ላይ ያለው አረዳድ ወይም የክርክር አዝማሚያ ውስጥ የሚስተዋሉትን ግልጽ ግድፈቶች ወይም ክፍተቶች ላይ ትችቶችን በማቅረብ ሕጉ በምን መልኩ መተርጎም ይኖርበታል? የሚለውን ወሳኝ ጉዳይ በማብራራት የተሻለ ሊያግባባን ወደሚያስችለን ድምዳሜና የመፍትሔ ሐሳብ ነቅሶ በማውጣት መጠቆም ነው። ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸውና ፀድቀው የአገሪቱ የሕግ አካል ከሆኑት የዓለም አቀፍ ስምምነቶች መነሻ በማድረግ የሥራ ማቆምን አጠቃላይ መብት ዕውቅና መስጠቱን ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ የሚያከራክር ባይሆንም እንኳን፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን እነዚህን መብቶች የተቀመጡበትን አግባብ በተወሰነ መልኩ በጥልቀት መፈተሽ የሚያስፈልጋቸው አንዳንድ ነጥቦች ማንሳት ያስፈልጋል። በዋናነት መነሳት ያለበት ነጥብ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 42(1)(ሐ) መሠረት የትኞቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በመብቱ መጠቀም የተፈቀደላቸው እንደሆኑ እንዲሁም የትኞቹ የተከለከሉ እንደሆኑ ለማብራራት የሚያስችል ወይም የዚህ መሠረታዊ መብት ላይ ገደብ ማድረግ የሚያስፈልገው ከመሆኑ አኳያ በሕግ አውጪው ሥልጣን ወሰን ላይ ጠቅለል ያለ የትርጓሜ መርህ ሆኖ የሚያገለግል መሥፈርት ባልተቀመጠበት ሁኔታ ዝርዝር የአፈጻጸም ሕግ እንዲወጣ የሚያመላክት እንጂ በደምሳሳው የሥራ ማቆም አድማ የማይፈቀድ ነው የሚል አይደለም። ለዚህም ነው በግሉ ዘርፍ ወይም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችንና የመንግሥት የልማት ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችን ለማስተደደር ከወጣው አዋጅ መንፈስ እንደሚያስረዳን የሥራ ማቆም መብት አፈጻጸምን በሚመለከት የሕጉን እሳቤና መርሆዎች ለማነፃፀሪያ ብንመለከተው የተወሰኑ የሥራ ዘርፎችን በመለየትና በተጨማሪም መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ተብለው በተለዩት የሥራ ዓይነቶች እንደ አንድ ገዥና ጥቅል መሥፈርት በመጠቀም ተከፋፍሏል፡፡ ከዚህም በላይ ሕግ አውጪው በተሰጠው ሥልጣንና በጉዳዩ ላይ ተቀባይነት ያገኙትን ተሞክሮዎችን በቀጥታ በመጠቀም እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሁሉም ሠራተኞች በአጠቃላይ የሥራ ማቆም ዕርምጃን በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ፈጽሞ የማይፈቀድና በጥብቅ የተከለከሉ ሕገወጥ ተግባሮች ስለመሆናቸው ሕግ አውጪው በግልጽና ዝርዝር በሆነ መልኩ ስለመብቱ አፈጻጸም በአዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ደንግጎ እናገኘዋለን።

ከአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ጋር በተገናኘ የሚመነጩ የሥራ ክርክሮችን ግጭት የሚፈታባቸው ሕጋዊ መንገዶችን በሚመለከት ዝርዝር መርሆዎችን በሚደነግገው የሕጉ ዘጠነኛው ክፍል በአንቀጽ 136 (2) የተቀመጠውን ትርጓሜ የሥራ ማቆም መብት አፈጻጸምን ሕጋዊ ወሰን እንዲሁም ሕግ አውጪው መብቱ ክልከላ ወይም ገደብ የሚደረግበትን አግባብ የተጠቀመበትን አጠቃላይ መሥፈርቶች ምንነት ብሎም ሕጋዊ ምክንያቶቹን በሚገባ የሚያስረዳ ፍሬ ነገሮች ያዘለ ስለሆነ እዚህ ጋር እንዳለ ማስፈር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት ድርጅቶች›› (Essential Public Services Undertakings) ማለት ለሕዝብ የማያቋርጥ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በአጠቃላይ የሚመለከት ሲሆን፣ በተለይም የሚከተሉትን ዝርዝር የአገልግሎት ዘርፎች በልዩ ሁኔታ በቀጥታ ይጠቅሳል፡፡

እነዚህም የአየር መንገድ አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ መብራት ኃይል አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፣ የውኃ አገልግሎት የሚሰጡና የከተማ ፅዳት የሚጠብቁ ድርጅቶች፣  የከተማ አውቶብስ አገልግሎት፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የመድኃኒት ማከፋፈያ ድርጅቶችና የመድኃኒት መሸጫ ቤቶች፣ የእሳት አደጋ አገልግሎትናየቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት የተሰማሩ ሁሉም ድርጅቶች (የግልም ይሁን የመንግሥት) ናቸው፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ንዑስ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ ሥራ ማቆም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲያስረዳ የሚከተለውን ትርጉም ተሰጥቶት እናገኛለን፡፡ “ሥራ ማቆም” ማለት ቁጥራቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ሠራተኞች በኅብረት በመሆን የአሠሪና ሠራተኛን ክርክር በሚመለከት ጉዳይ አሠሪያቸው ማናቸውንም ዓይነት የሥራ ሁኔታን እንዲቀበል በግድ ጥቅምን ወይም የሚፈልጉትን ውጤት ለማግኘት ተፅዕኖ በማድረግ ከአሠሪው ፍላጎት ውጪ ለጊዜው ከመደበኛው የሥራ መጠን መደበኛው የሥራ ውጤት እንዲቀንስ ሥራቸውን በማቀዝቀዝ ወይም ባለመሥራት የሚወስዱት ዕርምጃ ነው፡፡

በተጨማሪም በተጠቀሰው አዋጅ በአንቀጽ 157 ሥር ደግሞ ሠራተኞች በሕጉ ውስጥ በተመለከቱት ሁኔታዎች መሠረት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሥራ ማቆም ዕርምጃ መውሰድ መብት እንዳለቸው ያረጋግጣል፡፡ ነገር ግን መብቱ ተፈጻሚ የሚሆንበትን የሕግ ወሰን በሚመለከት ለሁሉም ዓይነት ሠራተኞችም ሆነ ሁሉም የሥራ ዘርፎች ላይ ባጠቃላይ እንደማይሠራ በንዑስ ቁጥር 3 ላይ በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ይህም ከፍ ብሎ እንደተገለጸው “እጅግ አስፈላጊ የሕዝብ አገልግሎት ድርጅቶች” ("Essential Public Services Undertakings") ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችን በአጠቃላይ የማይመለከት እንደሆነ በተለይም በልዩ መንገድ በሚመለከት በተሰጠው ትርጉም መሠረት የሥራ ማቆም መብት ተዘርዝረው በሚገኙት ሰባት የአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች በጥብቅ የተከለከሉ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕጋዊ የሥራ ማቆም ዕርምጃ ተደርጎ ሠራተኞች መብታቸውን ሊገለገሉ የሚችሉባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን አስመልክቶ በአዋጁ ውስጥ የተቀመጡ ሲሆን፣ እነዚህም ሕጋዊ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶችን በመወጣት ወይም በማክበር ተሟልተው ሲገኙ ብቻ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡ በዚህም መሠረት የሥራ ማቆም መብትን ለመጠቀም በቅድሚያ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን፣ ለሚመለከተው አካል ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ ወሳኝ እንደሆነ፣ ማስጠንቀቂያው ለማን፣ መቼና በምን መልኩ መሰጠት እንደሚገባው እንዲሁም በመብቱ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ ሠራተኞች የሚወስዷቸው ማንኛውም ዓይነት ዕርምጃዎች በየትኛውም መንገድ ቢሆን ለመፈጸም ከመሞከር እንዲታቀቡ ወይም ተፈጽመው ከተገኙ ሕገወጥ ድርጊቶች ተደርገው የሚያስቆጥሩ በወንጀል የሚያስጠይቁ ነጥቦችን በማካተት ሕጉ በጥብቅ የተከለከሉ ዝርዝር ተግባሮችን ግልጽ መሥፈርቶች መኖራቸውን ከይዘቱ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

ከሥራ ማቆም አድማ ወይም ዕርምጃዎች ጋር ተያይዞ ሊነሱ የሚችሉ የወንጀል ተጠያቂነት ጉዳዮች

ከላይ በአጭሩ ለማመላከት እንደተሞከረው በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ከሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ወይም መብታቸውን በጋራ ለማስፈጸምና ለማስጠበቅ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚወስዷቸውን ዕርምጃዎች የሚገዛው ብቸኛ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ውስጥ በተሸፈኑት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ተወስኖ እናገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ በተለያየ ጊዜ እየተሻሻለ ከወጣው የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞችን የሚመለከተው አዋጅን በሚገባ በመፈተሽ የመረመርን እንደሆነ መገንዘብ የምንችለው ነጥብ ይህንን መሠረታዊ መብት ቀርቶ በአጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች በኅብረት ሆነው የጋራ መብትና ጥቅማቸውን በሕጋዊ መንገድ ማስጠበቅ የሚቻልበት የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ምክንያት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕግ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጠውን የሥራ ማቆም መብት የሚፈጸምበትን ሁኔታና በመብቱ መጠቀም የማይችሉ የመንግሥት ሠራተኞች እንደየሥራ ዘርፋቸው ለይቶ ከማስቀመጥ ይልቅ በዝምታ ነው የሚያልፈው። ይህ ደግሞ ሥራ ማቆም አድማ ማድረግ እንደ ተከለከለ ሕገወጥ ተግባር የሚያስቆጥር ሊሆን አይችልም። ምንም እንኳን የሲቪል ሰርቪስ አዋጅ የመብቱን አፈጻጸም ባያስቀምጥም ሕግ አውጪው ቢያንስ በተለየ የሕግ ማዕቀፍ የሥራ ማቆም አድማ ዝርዘር አዋጅ ከማውጣት የሚገድበው ነገር የለም።

ከዚህ አንፃር በ1997 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኩል ፀድቆ የወጣውና አሁን በሥራ ላይ ያለው የወንጀል ሕግ በአንቀፅ 421 መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ሕገወጥ የሥራ ማቆም ድርጊት መፈጸም የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያስከትልና ጥፋቱም እሰከ ስድስት ወር የሚደርስ የእስራት ቅጣት እንዳለው ያስቀምጣል፡፡ ይሁን እንጂ ከድንጋጌው ይዘት እንደምንረዳው ሕገወጥ የሥራ ማቆም አድማ ተብለው የሚቆጠሩ ድርጊቶች ምንነትና በየትኞቹ የመንግስት መ/ቤት ሠራተኞች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል የሚለውን ወሳኝ ጥያቄዎች አይመልስም። በዚህም መሠረት በወንጀል ሕግ መሠረታዊ መርሆዎች አንፃር የወንጀል ድርጊትን በአናሎጂ መፍጠር የሚከለክል እንደመሆኑ መጠን የሲቪል አቭዬሽን ሠራተኞች ጉዳይ በየትኛው የሕግ ማዕቀፍ ነው የሚስተናገደው? ሕገ መንግሥታዊ መብቱስ ያለ ዝርዝር ሕግ እንዴት ወደ የወንጀል ድርጊት ሊቆጠር የሚችለው? የሚሉት ተያያዥ ጥያቄዎች በሚገባ መልስ ማግኘት አለባቸው። ሲጠቃለል በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችም ሆነ በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ተቀባይነት ያገኙ የመንግሥት ሠራተኞች በአጠቃላይ በነፃነት የመደራጀት መብት የሚያስጠብቅ ልዩ የሕግ ማዕቀፍ በሥራ ላይ እንዲውል ባልተደረገበት፣ እንዲሁም ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት እንዲሁም ከሥራ ሁኔታዎቻቸው ጋር በተገናኘ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብትና ጥቅሞቻቸውን ለማስከበርና ተፅዕኖ መፍጠሪያ መንገዶች ውስጥ ወሳኝነት ያላቸው የኅብረት ድርድር መብት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ፣ ከሥራ ጋር በተገናኘ በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች በሕጋዊና ሰላማዊ መልኩ በጋራ ሆነው የሠራተኛ ማኅበራትን ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ልዩ የሕግ ማዕቀፍ ባልተዘረጋበት ሁኔታ የሥራ ማቆም መብት አፈጻጸም አደጋ ውስጥ ይከተዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Active Participation of Children in Hostilities
Why Party-Appointed Arbitrators: A reflection

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 21 November 2024