Font size: +
20 minutes reading time (4094 words)

የልዩ ምርመራ ኦዲት ግኝቶችና የወንጀል ውጤታቸው

“I CAN’T DEFINE TAX EVASION, BUT I KNOW IT WHEN I SEE IT.”

— FRED T. GOLDBERG JR.

የታክስ ሥርዓት ከመንግስታዊ ስርዓት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ሲሆን መንግስት እንደ መንግስት ለመቀጠል ታክስ መጣልና መሰብሰብ እንዲሁም የሰበሰበውን ታክስ ለዜጎች ማህበራዊ አገልግሎት ማዋል ይኖርበታል፡፡ ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ ስልጣን የህግ መሰረት ሊኖረው የሚገባ ተግብር ሲሆን በዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ የዚህ ስልጣን ምንጭ በማህበራዊ ውል (social contract) መሰረት ዜጎች ለመንግስት የሚሰጡት ይሁንታ ነው፡፡

መንግስት ለሚመራው ህዝብ የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት አውታሮች እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማሟላት የሚያስፈልገውን ታክስ መሰብሰብ የሚችለው በሀገሪቷ ፍትኃዊ የታክስ ስርዓት ሲዘረጋና የታክስ ተገዢነት በሚፈለግ ደረጃ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡

የታክስ ተገዢነት በዜጎች ዘንድ በሚፈለግ ደረጃ ያለመስረፅ የታክስ ስርዓቱን ለበርካታ ተግዳሮቶች ሊያጋልጥ የሚችል ሲሆን የታክስ ስርዓት ለአደጋ ከሚያጋልጡ ችግሮች ዋነኛው ሆነተብሎ ለታክስ ባለስልጣን ሊከፈል የሚገባውን ታክስ ለማሳነስ ታስቦ በተለያዩ መንገዶች  የሚፈፀም የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር ነው፡፡

1. የታክስ ስወራ ወንጀል ምንነት

ታክስ ስወራ በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀፅ 125 ላይ በግልፅ የወንጀል ተግባር ሆኖ የተፈረጀ ሲሆን ታክስ ለመሰወር በማሰብ የሚደረግ ገቢን የመደበቅ ተግባር፣ታክስ ላለመክፈል የሚደረግ ንብረት የማሸሽ ተግባር እና በህግ ታክስ ቀንሶ የማስቀረት ግዴታ የተጣለበት ሰው ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ቀንሶ የያዘውን ታክስ ለገቢ ሰብሳቢው ባለስልጣን  መ/ቤት ያለማስተላለፍ ተግባራት በግልፅ እንደ ታክስ ስወራ ወንጀል ተመልክቷል፡፡

በሀገራችን በአብዛኛው የሚፈፀም የታክስ ስወራ ወንጀል አይነት ገቢን በመደበቅ የሚፈፀም የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር (evasion of assessment) ሲሆን ሁለተኛው የታከስ ስወራ ወንጀል አይነት በታክስ ሰብሳቢ መ/ቤት እና በግብር ከፋይ መካከል መጠኑን በሚመለከት ስምምነት ላይ የተደረሰውን ታክስ ላለመክፈል የሚደረግ ንብረት የማሸሽ ተግባር ነው፡፡

የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር ትርጉም ሀገራት በሚመሩበት የታክስ ህግን መሰረት በማድረግ የሚወሰን በመሆኑ ለቃሉ ወጥ የሆነ ትርጉም መስጠት አዳጋች ቢሆንም የዳበረ የታክስ ስነ-ህግ ባላቸው ሀገራት ለታክስ ስወራ የተሰጠውን ትርጉም ማየቱ አጠቃላይ የታክስ ስወራ ወንጀል ምንነትን ለመረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡

በታክስ ጉዳይ የዳበረ ስነ-ህግ ካላቸው ሀገራት አንዷ በሆነችው አሜሪካ ግብር ስወራን,-“ሆነተብሎ ገቢን በመደበቅ እና ታክስ ላለመክፈል የሚደረግ ጥረት በሚል በታክስ ኮዳቸው ትርጉም የተሰጠው ሲሆን የትርጉሙ ዋና ይዘት ገቢን የመደበቅ ተግባር እና ታክስ ላለመክፈል የሚደረግ ንብረት የማሸሽ ተግባራት ናቸው፡፡

ገቢን በመደበቅ የሚፈፀም የታክስ ስወራ ወንጀል (evasion of assessment)

ገቢን በመደበቅ የሚፈፀም የታክስ ስወራ ወንጀል በዋናነት ትክክለኛና ለመንግስት ልከፈል  የሚገባ ትክክለኛ ታክስ ስሌት ላይ የታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት እንዳይደርስ ለማድረግ በማሰብ ገቢን በመደበቅና ወጪ በማናር ልከፈል የሚገበውን ታክስ ለማሳነስ የሚደረግ ተግባር ነው፡፡

ንብረት ማሸሽ (evasion of payment)

ንብረት በማሸሽ የሚፈፀም የታክስ ስወራ ወንጀል በዋናነት በታክስ ሰብሳቢ መ/ቤት እና በታክስ ከፋይ መካከል በታክስ ስሌት ረገድ መተማመን ላይ የተደረሰበት ታክስ የሚመለከት ሲሆን ይህ የስወረ አይነት በዋናነት የሚፈፀመው ታክስ ከፋዮች የበሰለና ታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት የሚፈልገውን ታክስ ላለመክፈል ንብረት የማሸሽ ተግባር በሚኖርበት ወቅት ነው፡፡

በአጠቃላይ የግበር ስወራ ወንጀል ተግብር ስለመፈፀሙ ለማረጋገጥ የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር (affirmative act of tax evasion) የማጭበርበር ሀሳብ (intent to defraud) እና የተሰወረ ታክስ (tax due and owing) ስለመኖሩ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡

በሀገራችን የታክስ ስወራ ወንጀል ክስ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጥምረት የተደረጀውን  የምርመራ መዝገብ መሰረት በማድረግ በፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሚቀርብ ሲሆን የምርመራ ሂደቱ በወናነት ሶስት መንግስታዊ ተቋማትን ያሳትፋል፡፡ የምርመራ መነሻ ጥቆማ በሚሆንበት ወቅት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መ/ቤት የኢንተልጀንስ ዳይሬክቶሬት የቀረበለትን ጥቆማን በመቀበል፣ማስረጃን በማሰባሰብና በመተንተን ለሚመለከተው አካል የሚያስተላልፍ ሲሆን የእንቨስትጌሽን ኦዲት ዳይሬክቶሬት ደግሞ በቀረበው ጥቆማና የስጋት ስራ አመራር መርሆን መሰረት በማድረግ የወንጀል ተግባር መፈፀሙን ለማረጋገጥ የምርመራ ኦዲት በመስራት ይሳተፋል፡፡ ሌላኛው የታክስ ስወራ ወንጀል ምርመራ ተሳታፊ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የታክስ እና ጉምሩክ ወንጀሎች ምርመራ ቢሮ ሲሆን የተደራጀው መዝገብ ውጤት ይኖረው ዘንድ ተገቢውን ማስረጃ በማሰባሰብ መዝገቡን በማደራጀት ለሚመለከተው የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ የምርመራ መዝገቦችን የሚያቀርብ ይህ ተቋም ነው፡፡

2. የኢንቨስትጌሸን ኦዲት ምንነት

ኢንቨስቲጌሽን ኦዲት ልዩ ሙያዊ የምርመራ ስልትን በመጠቀም በታክስ ማጭበርበር ወንጀል በሚጠረጠሩት ታክስ ከፋዮች ላይ ተገቢውን ምርመራ በማድረግና ወንጀልን ለይቶ በማውጣት ህግ ፊት እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ በማስረጃ የተደገፈ ውጤት የሚቀርብበት የምርመራ ስራ ሲሆን ይህ ምርመራ መካሄድ ያለበት ህብረተሰቡ በግብር/ታክስ  ስርዓቱ ላይ ያለውን አመኔታ በሚያሳድግ መልኩ ነው፡፡

በልዩ ምርመራ ኦዲት ወቅት ኦዲተሮች ውሳኔ መስጠት ያለባቸው ከኢንቨስትጌሸን ኦዲት አለማ አንፃር ሲሆን የልዩ ምርመራ ኦዲት ዋና አለማ ተጠርጣሪ ግለሰብ ወንጀል መፈፀም አለመፈፀሙን በማስረጃ ማረጋገጥ ነው፡፡

ይህ ደግሞ ተጨባጭ ማስረጃዎችን (Fact and Evidence) በጥንቃቄ በማፈላለግ ሊፈፀም የሚገባ ተግባር ሲሆን የልዩ ምርመራ ኦዲት ዋና ተግባር ተብሎ ሊጠቀሱ የሚችሉት የሚከተሉት ናቸው፡-

  • የቀረበውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ መረጃውን በጥልቀት መገምገምና መተንተን፣
  • የወንጀሉን መገለጫዎች መለየት፣
  • የወንጀሉን ተዋናዮች መለየት፣
  • የኦዲት ግኝቶችን በሚገባ አደራጅቶ ለዐቃቤ ህግ ለውሳኔ በሚረዳ መልኩ ማቅረብና ሌሎች ተመሳሳይ ስራዎችን ማከናወን፡፡

3. የልዩ ምርመራ ኦዲት ግኝቶች እና የታክስ ስወራ ወንጀል

የኦዲት ግኝት በልዩ ምርመራ ኦዲት ሪፖርት ላይ በአኃዝ የተመለከተውን ግኝት ዘርዘር አድርጎ የሚያብራራ ሙያዊ ትንተና ሲሆን ዐቃቤ ህግ የምርመራ የኦዲት ግኝቶች የወንጀል ይዘት ያላቸው መሆን ያለመሆኑን የሚያጣራው በሪፖርቱ ላይ የተመለከቱትን ግኝቶች መሰረት በማድረግ ነው፡፡

በእያንዳንዱ የምርመራ ኦዲት ሪፖርት ላይ በቂና ዝርዝር የግኝቶች ማብራሪያ አለ ብሎ መደምደም ባይቻልም የምርመራ ኦዲት ዋና አለማ የቀረበውን ጥቆማ ወይም ስጋት በማስረጃ በማስደገፍ መተንተን እስከ ሆነ ድረስ የኦዲት ሪፖርት ከበቂ ማብራሪያ ጋር መቅረብ ይኖርበታል፡፡

ግብር ስወራ የሚፈጸመው የተለያየ የስወራ ዘዴ በመጠቀም በመሆኑ በእያንዳንዱ የምርመራ ኦዲት ላይ ተመሳሳይ እና ወጥ የሆነ ግኝት መጠበቅ አይቻልም፡፡ በዚህ ጽሁፍ የኦዲት ግኝቶች ከግብር ስወራ ጽንሰ ሀሳብ አንፃር የሚዳሰሱ ሲሆን ፅሁፉ በዋናነት ከወንጀል ተጠያቂነት አንፃር አሻሚ የሆኑ ግኝቶችን የሚመለከት ነው፡፡

  • ከማምረቻ/ገበያ ዋጋ በታች ሽያጭ ማከናወን፡-

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከዋጋ በታች ሽያጭ ማከናወን በልዩ ምርመራ ኦዲት ሪፖርት ላይ እንደ ግኝት መመልከት የተለመደ ሲሆን የግኝቶቹ መነሻና መሰረት ታክስ ከፋዮች ከማምረቻ/ገበያ ዋጋ በታች ይሸጣሉ የሚል ነው፡፡ ሀገራችን ከምትከተለው የነፃ ገበያ መርሆና ከታክስ ስወራ ወንጀል ግዙፋዊ ፍሬ ነገር አንፃር ከገበያ ዋጋ በታች መሸጥ በታክስ ከፋዩ ላይ ሊያስከትል የሚችል ተጠያቂነት ከፍትሐብሔር እና ከወንጀል ተጠያቂነት አንጻር መተንተን አስፈላጊ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚከተለው ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ከዋጋ በታች ሽያጭ ማከናወን እና የፍትሐብሔር ተጠያቂነት፡-

ገቢን በተመለከተ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ታክስ ከፋዮች ግብር ሊከፈልበት  የሚገባ ገቢ አግኝተዋል ለማለት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ካገኘ ታክስ በመጣል ይሰበስባል፡፡ታክስ ከፋዮች ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተጠለባቸው ታክስ ትክክለኛነት በሚመለከት ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት ስነ-ስርዓት በታክስ ህጎቻችን የተመለከተ ሲሆን ታክስ ከፈዮች በቅድሚያ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት በባለስልጣን መ/ቤቱ በተደራጀው የአቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ መሆኑን በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀፅ 55 ላይ በግልፅ ተመልክቷል፡፡ የቀረበው አቤቱታ በኮሚቴው ታይቶ የሚወሰን ሲሆን ታክስን በሚመለከት የኮሚቴው ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ አይደለም፡፡

በኮሚቴው ቅር የተሰኘ አካል አቤቱታውን ለፌደራል ግብር ይግባኝ ጉባኤ ማቅረብ የሚችል ሲሆን በግብር ይግባኝ ጉባኤ የሚሠጠው ውሳኔ የማስረጃ ምዘናን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ ነው፡፡

የታክስ ክርክር የህግ ክርክር ከለው ይግባኝ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ የሚቀርብበት አግባብ ስለመኖሩ በታክስ አስተደደር አዋጅ 983/2008 ክፍል 9 (ከአንቀፅ 52-60) ላይ በገልፅ ተመልክቷል፡፡

ከተያዘው ጉዳይ ጋር በሚገናኝ በ/ኮ/መ/ቁ 36860 ታህሳስ 16 ቀን 2004 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የፌደራል ጉምሩክና ሀገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣን እና በማግባዝን ሃ/የተ/የግ/ማህበር መካከል በነበረው የፍትሐብሔር ክርክር የተሰጠውን ውሳኔ ማየቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ የክርክሩ መነሻ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልበት ግብይት እሴት አወሳሰን የሚመለከት ሲሆን መዝገቡ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሊቀርብ የቻለው ማግባዝን ሃ/የተ/የግ/ማህበር በታክስ ሰብሳቢው ባለስልጣን ከታህሳስ 23 ቀን 1995 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 30 ቀን 1996 ዓ.ም የተጠየኩት የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ወለድ እና መቀጫ ያላግባብና ተገቢውን የታክስ ህግ መሰረት ያላደረገ ነው በሚል ለፌደራል የግብር ይግባኝ ጉባኤ አቅርቦ በነበረው ቅሬታ መሰረት ነው፡፡

አመልካች ይከራከር የነበረው የተጨማሪ እሴት ታክስ መከፈል ያለበት ከውጭ በገባ ዕቃ ዋጋ ላይ ብቻ በመመስረት ሳይሆን በጉምሩክ በተገመተ የዕቃ ዋጋ መሰረት መሆን አለበት በማለት ሲሆን በዚሁ አግባብ በተጠሪ ላይ የተጣለው ታክስ፣ወለድ እና መቀጫ በአግባቡ ነው በማለት ነው፡፡ (በድምሩ 549040.30 /አምስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሺ ከአርባ ብር ከሰላሳ ሳንቲም)

ከላይ ከተመለከተው ክርክር በተጨማሪ አመልካች አጥብቆ ሲከራከር የነበረው ድርጅቱ ታክስ ለመሰወር እና ለማሸሽ የሽያጩን ታክስ ለማሳነስ እና የታክስ ክሬዲት/ተመላሽ ከፍ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ ሞክሯል፣በመሆኑም የተጣለበት ታክስ ተገቢ በመሆኑ ውሳኔው ሊጸና ይገባል በሚል ሲሆን የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/94 አንቀፅ 15 መሰረት በማድረግ ተጠሪ የጉምሩክ ቀረጥ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ የከፈለበትን ሳይሆን አነስተኛ ዋጋ ያለውን/chamberized invoice/ መሰረት በማድረግ የሂሳብ መዝገብ መያዙ ተገቢ ስላልሆነ ለዕቃዎቹ ቀረጥ እና የተጨማሪ እሴት ታክስ የከፈሉበትን ዋጋ መሰረት በማድረግ የሂሳብ መዝገባቸው ይስተካከል በሚል ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በሌላ በኩል የተጠሪ የሂሳብ አያያዝ ከላይ የተመለከተው ስህተት የሚታይበት ቢሆንም በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/94 አንቀጽ 15 ላይ አመልካች ታክስ የሚከፈልበትን የግብይት እሴት ተጠሪ ከዳንበኛው፣ከሌላ ከማናቸውም ሰው የተቀበለው ወይም ለመቀበል የሚችለውን መሰረት በማድረግ መወሰን እንዳለበት በግልፅ የተደነገገ በመሆኑና አመልካች ተጠሪ ያቀረበው የገበያ ዋጋ የተሣሣተ መሆኑን ያላጣራ በመሆኑ አመልካች በሂሳብ አያያዙ የታየውን ልዩነት በመመልከት ብቻ ግብሩን ከፍ አድርጎ መወሰኑ ተገቢ ባለመሆኑ የተጠሪ የግብይት ዋጋ የተሣሣተ መሆን አለመሆኑን በገበያ ጥናት ወይም በመረጃ ላይ ተመስርቶ ይወስን በማለት ጉባኤው በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 343/1/ ለአመልካች መልሶ የነበረ ሲሆን አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኝት ይግባኝ ለፌደራል ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ውሳኔው በመፅናቱ ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሟል በሚል አቤቱታ አቅርቦ ነበር፡፡

ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በአመልካች ቀርቦ የነበረው አቤቱታ በአጭሩ የግበር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ የተጠሪ የሂሳብ አያያዝ ስህተት ያለበት ነው በሚል ከወሰነ በኃላ  አመልካች ግብሩን በገበያ ጥናት ወይም በመረጃ ላይ ተመስርቶ አጣርቶ ይወስን በማለት የሰጠው ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ሆኖ ሳለ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት እና ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔው መጽናቱ መሰረታዊ የህግ ስህተት በመሆኑ በዚህ ሰበር ሰሚ ችሎት ታይቶ ሊታረም ይገባል በሚል ነው፡፡ 

አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፡-

  • የፌደራል ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ አመልካች ዕቃውን የሸጠበት ዋጋ የተሳሳተ ዋጋ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በገበያ ጥናት ወይም በመረጃ አረጋግጦ እንዲወስን የሰጠው ውሳኔ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማፅናታቸው ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን የመረመረ ሲሆን ምንም እንኳ ተጠሪ በጉምሩክ የተገመተ ዋጋ በሽያጭ እንደተገኘ ገቢ ተቆጥሮ የዕቃ ዋጋ አስተሳሰብ መያዝ የለበትም ብሎ ቢከረከርም የግብር ይግባኝ ሰሚው ጉባኤ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/94 አንቀጽ 15/1/ መሰረት በማድረግ ተጠሪ ሂሳቡን ‘chambrized invoice’ መሰረት በማድረግ መያዙ ስህተት ነው በማለት የጉምሩክ ቀረጥ በተከፈለበት(custom value) ሂሳብ ያስተካክል በማለት በአዋጁ አንቀፅ 15/1/ መሰረት የተሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት ያልተፈፀመበት ነው በማለት ያፀና 2ኛው የክርከር ነጥብ እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡
  • አመልካች እና ተጠሪ አጥብቀው የሚከራከሩበት 2ኛው ነጥብ ተጠሪ ዐቃውን በመሸጥ የተጨማሪ እሴት ታክስ ሰብስቤበታለሁ የሚለው ዋጋ በሚመለከት ሲሆን ይህን ነጥብ በሚመለከት የሰበር ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩን የተመለከተው በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/1994 አንቀፅ 12/1/ መሰረት ሲሆን በህጉ ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልበት ግብይት እሴት የሚወሰነው ታክስ ከፋዩ ላቀረባቸው ዕቃዎች ወይም ለሸጣቸው አገልግሎቶች/ማናቸውም ቀረጥ፣ታከስ ወይም ሌሎች ክፍያዎችን ጨምሮ ከደንበኛው ወይም ከማናቸውም ሌላ ሰው የተቀበለውን ወይም ለመቀበል የሚችለውን ዋጋ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ተጠሪ ዕቃዎቹን ለደንበኞች በመሸጥ ዋጋ ተቀብዬበታለሁ የሚለውን ዋጋ ለአምካች አሳውቋል፡፡ አመልካች ተጠሪ ያቀረበውን ዋጋ በማስተካከል መወሰን እንደሚችል የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/94 አንቀፅ 13 ላይ ተመልክቷል፡፡ሆኖም አመልካች የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ የሚችለው በይሆናል ወይም በግምት ላይ ብቻ በመመስረት ሳይሆን በአንቀፅ 13/1 ላይ የተመለከቱት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙና በተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ላይ የተጠቀሰው ዋጋ የተሣሣተ ሲሆን ወይም በተጨማሪ እሴት ታክስ ማስታወቂያ ላይ የተገለፀው የተጨማሪ እሴት ታከስ የተሣሣተ ሲሆን እንደሆነ የአዋጁ አንቀፅ 13/2 ላይ ተደንግጓል፡፡

ከዚህ አንፃር አመልካች የተጠሪን ዋጋ ውድቅ ያደረገበትን አግባብ ችሎቱ ሲመለከት በተጠሪ የቀረበው ዋጋ የተሳሳተ ስለመሆኑ በገበያ ጥናት እና በመረጃ ለማረጋገጥ ምንም አይነት ጥረት አለማድረጉንና አመልካች የሂሳብ አያያዙ ስህተት መሆኑን ብቻ መሰረት በማድረግ የተጨማሪ እሴት ታከስ አስተካክሎ የወሰነ መሆኑን ፍሬ ጉዳይ እና ማስረጃ የመመዘን ስልጣን ያለው የግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ አረጋግጧል፡፡ ስለሆነም አመልካች በአዋጅ 285/94 አንቀፅ 13/2 ላይ በተመለከተው አግባብ በተጠሪ የቀረበው ዋጋ የተሳሳተ መሆኑን በገበያ ጥናት ወይም በመረጃ ሳያረጋግጥ እና በህግ ላይ የተመለከተውን ግዴታ ሳይወጣ ታክስ የሚከፈልበት ግብይት እሴት በማስተካከል የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ባለመሆኑ የፌደራል ግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባኤ፣የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ሊፀና ይገባል በማለት ወስኗል፡፡  

ከላይ በፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በኮ/መ/ቁ-36860 ከተሰጠው ውሳኔ መረዳት የሚቻለው በፍትሐብሔር ጉዳይ እንኳ ታክስ የሚከፈልበት ግብይት እሴትን ለመለየት ታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት የታክስ ከፋይ የሂሳብ አያያዝ ስህተት አለው በማለት ብቻ በግምት ግበር መጣል እንደማይገባ፣ግብር ከፋይ ያቀረበው የዕቃ ሽያጭ ዋጋ ትክክል አለመሆኑን በገበያ ጥናት እና በማስረጃ ሳያረጋግጥ የቀረበው ዋጋ ከማምረቻ ዋጋ፣ታክስ ከፋዩ ራሱ ካቀረበው ዋጋና ከገበያ ዋጋ አንፃር ያነሰ ነው በሚል በታክስ ከፋይ የሚቀርበውን ዋጋ ውድቅ በማድረግ ታክስ ከፍ ተደርጎ የሚወሰንበት አግባብ ተገቢ ያለመሆኑ በፍርዱ ላይ በግልፅ የተመለከተ መሆኑ ነው፡፡

ከዋጋ በታች ሽያጭ ማከናወን እና የወንጀል ተጠያቂነት

ከዋጋ በታች ሽያጭ ከማከናወን ጋር በሚገናኝ በምርመራ ኦዲት የሚዳሰሱ ግኝቶች በዋናነት ታክስ ከፋዮች ከማምረቻ/ገበያ ዋጋ በታች ሽያጭ ያከናውናሉ በሚል መነሻ ሲሆን በአብዛኛው የዕቃ ዋጋ ንፅፅር የሚደረገው ታክስ ከፋዮች በሌሎች የታክስ ዘመናት ላይ የሚያቀርቡትን ዋጋ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ዋጋን በሚመለከት በታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት የሚወሰኑ ግኝቶች የገበያ ጥናት ተደርጎ መሆን አለመሆኑ በማጣራት መወሰን ያልተለመደ ሲሆን ከላይ በፍትሐብሔር ጉዳይ ከቀረበው ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ፍትሐብሔራዊ ውጤት ብቻ ያለውን ታክስ በግብር ከፋዮች ላይ ጥሎ ለመሰበሰብ እንኳ የገበያ ጥናት እና በቂ ማስረጃ መሰረት ማድረግ እንደሚኖርበት ከሰበር ውሳኔው መረዳት ይቻላል፡፡

ከዋጋ በታች ሽያጭ ከማከናወን ጋር በተያያዘ ሊታወቅ የሚገባ ዋናው ጉዳይ የታክስ ስወራ ወንጀል ሆነተብሎ የሚፈፀም ወንጀል መሆኑ ሲሆን ይህ ግኝት የወንጀል ውጤት ሊኖረው የሚችለው ታክስ ከፋዮች ሆነብለው ታክስ ለማጭበርበር ዋጋ መሳነሳቸውን የሚያሳይ ግዙፋዊ የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር (affirmative act of evasion) ማሳየት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ግዙፋዊ የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር ግብር ከፋዮች ዋጋቸውን ያሳነሱት ታክስ ለመሰወር በማሰብ ስለመሆኑ በግልፅ የሚያሳይ ማስረጃ ሲሆን ከዋጋ በታች ሽያጭ ከማከናወን ጋር በተገናኘ የምርመራ ኦዲት ሪፖርቶች የገበያ ጥናት እና ማስረጃን መሰረት በማድረግ የማይሰሩ ከሆነ ግዙፋዊ የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባርም ሆነ የታክስ ስወራ የሀሳብ ከፍል ማሳየት አይቻልም፡፡

በተጨማሪም አንድ ነጋዴ መንግስትን ለማጭበርበር በማሰብ ከማምረቻ ዋጋ በታች በመሸጥ ከስሮ ከትክክለኛ የገበያ ዋጋ በታች ወይም ከማምረቻ ዋጋ በታች ይሸጣል ተብሎ መታሳቡ ምክንያታዊ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ጉዳዩን ሀገራችን ከምትከተለው የነፃ ገበያ መርህ አንፃር ሲታይ የዕቃ ዋጋ በገበያ ይወሰናል ተብሎ በሚታመንበት ሀገር ታክስ ከፋዩ ከዚህ በፊት በቀረበው ዋጋ መሰረትም ሆነ ሌሎች ነጋዴዎች በሚሸጡት ዋጋ መሸጥ ይኖርብኃል በሚል በታክስ ከፋይ ላይ የወንጀል ክስ ማቅረብ የአመክንዮ መሰረት የለውም፡፡

  • ከጉምሩክ ዋጋ በታች መያዝ፡-

በአስመጪነት የንግድ ዘርፍ የንግድ ስራ የሚያከናውኑ ግብር ከፋዮች ዕቃ ወደ ጉምሩክ ክልል በሚያስገቡበት ወቅት የዕቃ ግዢ ዋጋ (commercial invoice) ለጉምሩክ የሚያቀርቡ ሲሆን ይህ በሚቀርብበት ወቅት ባለስልጣን መ/ቤቱ የግዢ ዋጋውን ትክክለኛነት ሲጠራጠር የአስመጪዎችን የግዢ ዋጋ ላይቀበል ይችላል፡፡ አስመጪዎች ያቀረቡት የግዢ ዋጋ/ኢንቮይስ ዋጋ/ ውድቅ ከተደረገ በኃላ ታክስና ቀረጥ በጉምሩክ ዋጋ መሰረት የሚሰላ ይሆናል፡፡

 በተጨሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/94 አንቀፅ 15/1 መሰረት አስመጪዎች ዕቃቸውን ለሽያጭ ሊያቀርቡ የሚገባው በጉምሩክ ዋጋ መሰረት ዋጋ በመገንባት መሆኑ በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ታክስ እና ቀረጡን በሲዲ ዋጋ መሰረት ከፍለው ሳለ አስመጪዎች ለሀገር ውስጥ ሽያጭ ዋጋቸውን በራሳቸው የግዢ ዋጋ መሰረት ገንብተው ሽያጭ ካከናወኑና ይህንኑ ዋጋ ለባለስልጣን መስሪያቤቱ ካስታወቁ ባለስልጣን መ/ቤቱ የአስመጪውን የዋጋ ግንባታ ውድቅ በማድረግ ዋጋውን በጉምሩክ ዋጋ መሰረት በማስተካከል ታክስ ይጥልል፡፡

ከዚህ ግኝት ጋር በሚገናኝ በጥለቀት ሊመረመር የሚገባ ጉዳይ አንድ አስመጪ የገዛበትን ዋጋ በሚመለከት የግዢ ሰነድ ካቀረበ በኃላ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን መ/ቤት የቀረበው የእንቮይስ ዋጋ ያነሰ የግዢ ዋጋ ነው በሚል ዋጋውን ውድቅ በማድረግ በሲዲ ዋጋ መሰረት ታክስ እና ቀረጥ ቢያሰላ ይህ ተግባር አስመጪው የግዢ ዋጋውን አሳንሷል በሚል በአስመጪው ላይ የወንጀል ተጠያቂነት ሊያስከትል ይችላል ወይስ አይችልም የሚል ነጥብ ሲሆን ባለስልጣን መ/ቤቱ በአስመጪዎች የሚቀርበውን የግዢ ዋጋ ውድቅ የሚያደርገው አስመጪው ያቀረበው ዋጋ ትክክለኛ የግዢ ዋጋ ስለመሆኑ ውጭ ካለው አምራች(ከሻጩ) ድርጅት የተሰጠውና በአስመጪው አማካኝነት የቀረበው የግዢ ሰነድ ትክክለኛ አለመሆኑ በማረጋገጥ ሳይሆን ከማነፃፀሪያ ዋጋ/cd value/ አንፃር ሲታይ የቀረበው ዋጋ አንሶ በመገኘቱ ነው፡፡

በአስመጪው የቀረበው የግዢ ዋጋ ትክክለኛ የግዢ ዋጋ አለመሆኑ ወይም ታክስና ጉምሩክ ለማጭበርበር የቀረበ ሀሰተኛ የግዢ ዋጋ ስለመሆኑ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በአስመጪዎች የቀረበ ዋጋ በአሃዝ ሲታይ ከሲዲ ዋጋ አንሶ መገኘቱን ብቻ መሰረት በማድረግ ታክስና ጉምሩክ ለማጭበርበር የቀረበ ዋጋ ነው ለማለት አያስችልም፡፡ የታክስ ስወራ ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት ግዙፋዊ የታክስ ስወራ ተግባር መኖር ያለበት ሲሆን ከላይ በተያዘው ከጉምሩክ ዋጋ በታች መያዝን በሚመለከት የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር ውጤት ሊኖረው የሚችለው በአስመጪ የቀረበው ዋጋ ትክክለኛ የግዢ ዋጋ አለመሆኑ በሚረጋገጥበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ሲሆን ተጭበርብሮ የሚቀርብ የግዢ ሰነድ በግልፅ ግዙፋዊ የታክስ ስወራ ወንጀል መኖሩን ያሳየናል፡፡

በአጠቃላይ ከታክስ አንፃር የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/1994 አንቀፅ 15/1 እና የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 መሰረት ታክስ እና ቀረጥን ለመጣል የጉምሩክ ዋጋን መሰረት መድረጋቸውና በዚሁ አግባብ ታክስ መጣላቸው የሚነቀፍ በይሆንም ከወንጀል ተጠያቂነት አንፃር ሲታይ በአስመጪ የሚቀርበው ዋጋ ትክክለኛነት ልታይ የሚገባው ከአምራች ድርጅት የሽያጭ ዋጋ አንፃር ሊሆን ይገባል፡፡

ወጪን መሰረት በማድረግ

የወንጀል ተግባር መኖሩን የሚያሳይ የኦዲት ግኝት በበኃሪው ተጠርጣሪው ግብር ለመሰወር የሚያደርገውን ህገ-ወጥ ተግባራትን በግልጽ የሚያማለክት ሲሆን በአብዛኛው ከግዢና ከሽያጭ ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ወጪን በሚመለከት አንድ ድርጅት የግብር ስወራ ተግባር ፈጸመ የሚባለው ወጪን በማናር ግብር የሚጣልበት ገቢ እንዲያንስ በማድረግ ሲሆን ይህ ተግባር የወንጀል ይዘት አለው ለማለት ግን ግብር ከፋዩ ያቀረበው ወጪ ያልወጣና የፈጠራ ወጪ ስለመሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡

የፈጠራ ወጪ በበኃሪው በሀሰተኛ ሰነድ ወይም በሌሎች ህገ-ወጥ ደረሰኞች ተደግፎ የሚቀርብ ሲሆን ከላይ እንደተገለፀው ዐቃቤ ህግ ወጪዎቹ ህገ-ወጥ መሆናቸውን፣የወጪዎቹን ህገ-ወጥነት ለመደበቅ የቀረበ ሀሰተኛ ሰነድ/ሌሎች የተቀነባበሩ የሀሰት ተግባራት/ መኖራቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ 286/94 አንቀጽ 20 ላይ እንደተመለከተው ግብር ከፋዮች ወጪያቸውን ማረጋገጥ እስከቻሉ ድረስ ለንግድ ስራው ዋስትና ለመስጠትና እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል የወጣውን ወጪ ተቀናሽ እንደሚደረግ የተመለከተ ሲሆን ማረጋገጥ ካልተቻለ ውድቅ እንደሚደረግ በግልጽ ያሳያል፡፡

ከታክስ ኦዲት ጋር በሚገናኝ ወጪዎች ውድቅ የሚሆኑበት የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን በዋናነት ወጪዎች ውድቅ የሚሆኑት ደጋፊ ሰነድ የለላቸው ወጪ፣በታክስ ህጎች እንደ ወጪ እንዲያዝ ያልተፈቀደ ወጪ፣ያልወጣ ወጪ ሆኖ እንደ ወጣ በማስመሰል የቀረበ ወጪ ናቸው፡፡

  1. ደጋፊ ሰነድ ያልቀረበላቸው ወጪዎች

ከላይ እንደተገፀው ለንግድ ስራ ዋስትና ለመስጠት የሚወጡ ወጪዎች ማረጋገጥ እስከተቻለ ድረስ ተቀናሽ የሚደረጉ ሲሆን ግብር ከፋዮች ተገቢውን የሂሳብ ሰነድ ባለመያዛቸው ምክንያት ወጪዎች ስለመውጣት የሚያረጋግጥ ሰነድ ያልቀረበ ከሆነ ደጋፊ ሰነድ አልቀረበም በሚል ውድቅ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ግኝት ጋር ተያይዞ ሊታወቅ የሚገባው እነኚህ ወጪዎች ውድቅ የሚደረጉት ወጪዎቹ ሙሉ በሙሉ አልወጡም በሚል ድምዳሜ ሳይሆን ታክስ ከፋዩ ስለመውጣታቸው በደጋፊ ሰነድ ህጉ በሚፈቅደው አግባብ አላረጋገጠም በሚል ነው፡፡

በመሆኑም አነኚህ ወጪዎች አለመውጣታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ተከሳሽ ወጪዎቹን ለታክስ በለስልጣን ያቀረበው ሆነብሎ ታክስ ለማጭበርበር ነው በሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አያስችልም፡፡ የሀሳብ ክፍል ማስረዳት የማይቻል ከሆነ ደግሞ ይህ ግኝት የወንጀል የክስ መሰረት ሊሆን አይችልም፡፡

  1. ያልተፈቀዱ ወጪዎች

ያልተፈቀዱ ወጪዎች ታክስ ከፋዮች በህግ እንደ ወጪ እንዳይያዝላቸው የተከለከለ ወጪ ሲሆን ታክስ ከፋዮች እነኚህን ወጪ ቢያወጡ እንኳ በታክስ ህግ የተከለከለ በመሆኑ ባለስልጣን መ/ቤቱ ውድቅ ያደርጋቸዋል፡፡

በፌደራል የገቢ ግበር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀፅ 27 መሰረት ተቀናሽ የማይደረጉ ወጪዎች በግልፅ የተመለከቱ ሲሆን ለአብነት ለመጥቀስ ያክል፣

  • በጥፋት ምክንያት የተከፈለ የጉዳት ካሳና መቀጫ፣
  • የግል ፍጆታ ወጪዎች፣
  • የመድን ዋስትና ሽፋን ያለው ጉዳትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

እነዚህ ወጪዎች በአንድ በኩል በመሰረታዊ የሂሳብ መርሆ የተፈቀዱ ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ታክስ ከፋዮች ለገቢዎች ባለስልጣን መ/ቤት የሚያቀርቡት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘትና ለንግድ እንቅስቃሴያቸው ዋስትና ለመስጠት የወጣ ወጪ ነው በሚል ነው፡፡

በመሰረታዊ የሂሳብ መርሆ (General accounting principle) እንደ ወጪ እንዲያዙ የማይከለከሉ ወጪዎች በእኛ ህግ የተከለከለ ወጪ በሚሆንበት ወቅት አንድ ታክስ ከፋይ ወጪውን በወጪ ሰንጠረዥ ሞልቶ ቢመጣ ወጪውን ውድቅ ከማድረግ ውጭ ታክስ ከፋዩ ታክስ ለማጭበርበር ያቀረበ ወጪ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡

በፀኃፊው እመነት በመሰረታዊ የሂሳብ መርሆ የሚፈቀዱ ነገር ግን በሀገራት የታክስ ህግ መሰረት የተከለከሉ ወጪዎች በታክስ ከፋዮች በታክስ ማስታወቂያ ላይ ተሞልተው ሲቀርቡ ውድቅ አድርገን ታክስ ከመጣል ባለፈ የወንጀል ውጤት ሊያስከትሉ አይገባም፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ ታክስ ከፋዮች እነኚህ ወጪዎች የተከለከሉ መሆናቸውን እያወቁ ታክስ ለመሰወር በማሰብ ከሌሎች ወጪዎች ጋር በመቀላቀል ለታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት የሚያቀርቡበት አጋጣሚ በርካታ ሲሆን ታክስ ከፋዮች ወጪያቸውን እንዲያረጋግጡ እድል ሲሰጣቸው በመጀመሪያ የቀረበው ወጪ ትክክለኛ ባለመሆኑ ለማረጋገጥ የሚሞክሩት ሀሰተኛ ሰነድን በመጠቀም ነው፡፡

አነዚህ ሀሰተኛ ደረሰኞች ያልወጣን ወጪ ለመደገፍ ሆነተብሎ መጪን ለማናር የሚቀርቡ በመሆናቸው በወንጀል ምርመራ ከተደረሰባቸው በታክስ ክርክር ሂደት እንደ ሌሎች ወጪዎች የወንጀሉን ግዙፋዊ የወንጀል ተግባርና የታክስ ከፋዮችን የሀሳብ ክፍል ለማስረዳት አዳጋች አይሆንም፡፡

በአጠቃላይ ያልተፈቀዱ ወጪዎችን በሚመለከት ወጪዎቹ በታክስ ማስታወቂያ ላይ ተሞልተው የሚቀርቡት ለታክስ ሰብሳቢ መ/ቤት በመሆናቸው ዐቃቤ ህግ ደግሞ በታክስ ስወራ ወንጀል የታክስ ስወራ ሀሳብ ክፍል ስለመኖሩ ማስረዳት ያለበት በመሆኑ ዐቃቤ ህግ ክስ ከማቅረቡ በፊት እነዚህ ወጪዎች የቀረቡበትን አለማና ሁኔታ እንዲሁም ተከሳሽ ሆነብሎ ወጪውን በማናር ታክስ ለመሰወር በማሰብ የወንጀል ተግባሩን ስለመፈፀሙ በተገቢ ሁኔታ መመርመር ይኖርበታል፡፡

  ያልወጡ ወጪዎች (fictitious expenses)

ታክስ ከፋዮች የንግድ ስራቸውን ለማስቀጠልና ለንግዳቸው ዋስትና ለመስጠት ወጪ ማውጣታቸው የሚታመን ቢሆንም አንዳንድ ታክስ ከፋዮች ታክስ ለማጭበርበር በማሰብ ሆነብለው ያላወጡትን ወጪ እንዳወጡ በማስመሰል ከታክስ ባለስልጣን እንደ ወጪ ተቀናሽ በማድረግ ሊከፈል የሚገባ ታክስ በመቀነስና በመደበቅ የዜጎችን ሀብት በመዝረፍ ስራ ላይ የተሰማሩ ታክስ ከፋዮች መኖራቸው ግልፅ ነው፡፡

በነዚህ ታክስ ከፋዮች የሚቀርቡ ወጪዎች ከመሰረቱ በትክክል ያልወጣ ወጪ ለማስያዝ በማሰብ ሲሆን ወጪያቸውን ለማስረዳት የሚቀርቡ ሰነዶችም ሀሰተኛ ደረሰኞች ናቸው፡፡

ወጪዎች ያለወጡ ወጪዎች ስለመሆናቸው የምናረጋግጠው ከሶስተኛ ወገን በሚገኝ ማስረጃና በታክስ ከፋዮች በሚቀርቡ ሀሰተኛ ደረሰኞች ሲሆን ዐቃቤ ህግ እነዚህ ወጪዎች በትክክል አለመውጣታቸው በእርግጠኛነት ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

  • ቆጠራን በማሳነስ የሚጣል ታክስ

በመርህ ደረጃ ቆጠራን መሰረት በማድረግ የሚሰሩ የምርመራ ኦዲት ግኝቶች የታክስ ስወራ ወንጀል ውጤት የለቸውም ብሎ መደምደም የማይቻል ሲሆን በዚህ ፅሁፍ በዋናነት መመልከቱ አስፈላጊ የሚሆነው ቆጠራን መሰረት በማድረግ የሚሰሩ የምርመራ ኦዲት ግኝቶች የታክስ ስወራ ወንጀል ውጤት ሊኖራቸው የሚችልበትን አግባብ መለየት ላይ ነው፡፡

በፅሁፉ መግቢያ ላይ እንደተገለፀው የታክስ ስወራ ወንጀል ተፈፅሟል ለማለት ሶስት መሰረታዊ የታክስ ስወራ ወንጀል ፍሬ ነገሮች ማለትም

  1. የታክስ ስወራ ወንጀል ግዙፋዊ ተግባር(affirmative act of tax evasion)
  2. የስወራ ተግባሩ ሆነተብሎ ታከስ ለማጭበርበር የተፈፀመ መሆኑና(intent to defraud) እና
  3. በመንግስት የሚፈለግ የበሰለና የተሰወረ ታክስ መኖሩ ሊረጋገጥ ይገባል(tax due and owing by the tax authority) መሟላት የሚገባ ሲሆን የቆጠራ ውጤት መሠረት ተደርጎ የሚሰራ የምርመራ ኦዲት ግኝት የወንጀል ይዘት አለው ወይስ የለውም የሚለውን ለመለየት ይረዳን ዘንድ የተያዘውን ጉዳይ ከታክስ ስወራ ወንጀል ግዙፋዊ ተግባር (affirmative act of tax evasion) ጋር አያይዞ በምሳሌ አስደግፈን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

ለምሳሌ ያክል PPT private limited company ከ2003 እስከ 2007 የታክስ  ዘመን በ2009 ዓ.ም  ኦዲት በሚደረግበት ወቅት የ2004 ታክስ ዘመን ending inventory 200 ነው ብሎ ቢያሳውቅና በ2005 ending inventory 0 ከሆነ ድርጅቱ በ2004 ያሳወቀውን (200 ) ዕቃ በ2005 የታክስ ዘመን እንደሸጠ በመቁጠር ነው ታክስ የሚጣልበት፡፡ ድርጅቱ ኦዲት የተደረገው በ2009 ዓ.ም በመሆኑ የ2004 እና 2005 ታክስ ዘመናት የድርጅቱን የዕቃ ፍሰት በአካላዊ ቆጠራ የሚታወቅበት አግባብ አይኖርም፡፡

ለታክስ ሲባል ባለስልጣን መ/ቤቱ በዚህ አግባብ ታክስ ጥሎ መሰብሰብ ተገቢ ቢሆንም ከወንጀል አንፃር ግን ታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት ታክስ ከፋዩ በ2004 የታክስ ዘመን ያቀረበው የመጨረሻ ቆጠራ ውጤት ካመኖሩ ባለፈ በ2005 የታክስ ዘመን ዕቃዎቹ መሸጣቸውንና ለማን እንደተሸጠ መለየት መቻል ይኖርብናል፡፡ ከላይ ከተመለከተው ምሳሌ አንፃር ስንመለከት ታክስ ከፋዩ ድርጅት ዕቃውን ሽጦት ሊሆን ይችላል ከሚል ድምዳሜ ባለፈ በተግባር ከገዢ ወይም ከማናቸውም ሶስተኛ ወገን ዕቃው ስለመሸጡ ያልተረጋገጠ ከሆነ የታከስ ስወራ ግዙፋዊ ተግባር ማሳየት የማይቻል በመሆኑ ተመሳሳይ ግኝቶች የወንጀል ውጤት ሊያስከትሉ አይገባም፡፡

ከላይ ከተመለከተው በተጨማሪ የቆጠራ ኦዲት ግኝት ውጤቱ የተሰራው ኦዲተሮች ባደረጉት ምርመራ ያገኙትን መረጃ መሰረት በማድረግ ሳይሆን ታክስ ከፋዩ ራሱ ያቀረበውን የቆጠራ ውጤት መሰረት በማድረግ በመሆኑ ታክስ ከፋዩ የማጭበርበር ሀሳብ ቢኖረው ኖሮ ልዩነት ሊኖረው የሚችለውን ቆጠራ ለባለስልጣን  መ/ቤቱ ያቀርባል ተብሎ አይታሰብም፡፡

ከቆጠራ ጋር በተያያዘ ሌላኛው የምርመራ ኦዲት ግኝት አካላዊ የዕቃ ቆጠራን መሰረት በማድረግና የሶስተኛ ወገን መረጃን መሰረት በማድረግ ዕቃ መጉደሉ ብቻ ሳይሆን ለማን እንደተሸጠ በማረጋገጥ የሚሰራ ኦዲት ግኝት ሲሆን አኒህ ግኝቶች ከቀረበው የቆጠራ ውጤትና ሽያጭ ጋር በሚለያይበት ወቅት የታክስ ስወራ ወንጀል ውጤት ሊያስከትል የሚችልበት አግባብ ስለመኖሩ ሊታወቅ ይገባል፡፡

 

  • የገቢ ግብር እና የተጨማሪ እሴት ታክስ ንፅፅር ግኝት

ንፅፅርን መሰረት በማድረግ የሚሰራ የምርመራ ኦዲት ግብር ከፋዮች ለገቢ ግብር እና ለተጨማሪ እሴት ታክስ ያሳወቁትን ገቢ/ሽያጭ መሰረት በማድረግ ሲሆን ለዚህ ግኝት መነሻ የሚሆነው ታክስ ከፋዮች ለገቢ ግበር እና ለተጨማሪ እሴት ታክስ በሳወቁት ገቢ/ሽያጭ መካከል ልዩነት ሲኖር ነው፡፡

የዚህ ንፅፅር ዋነኛው አለማ ታክስ ከፋዮች ግብራቸውን ከማጨበርበር ተግባር በፀዳ መልኩ እየከፈሉ መሆን አለመሆናቸው ለማረጋገጥ ሲሆን ታክስ ከፋዮች ለአንዱ የታክስ አይነት ያሳወቁትን ገቢ/ሽያጭ ለሌላኛው የታክስ አይነት ከላሳወቁና ሽያጩ/ገቢው ታክስ የሚከፈልበት ገቢ ሆኖ ከተገኘ የታክስ ሰብሰቢው ባለስልጣን መ/ቤት የተደበቀ ታክስ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ የንፅፅር ኦዲት ይሰራል፡፡

የንፅፅር ኦዲት ግኝት መሰረት ከታክስ ነፃ የሆነ ግብይት እስከሌለ ድረስ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈልበት ግብይት እና ገቢ ግብር የሚከፈልበት ገቢ መሰረታቸው (base) ተመሳሳይ በመሆኑ የሚገለፅ ገቢ/ሽያጭ እኩል መሆን ይኖርበታል በሚል መነሻ ሲሆን ታክስ ከፋዮች በየወሩ ለ12 (አስራ ሁለት) ወራት ለተጨማሪ እሴት ታክስ ባሳወቀው ሽያጭና በተመሳሳይ የታክስ ዘመን ታክስ ከፋዩ ለገቢ ግብር ያሳወቀው ገቢ መካከል ልዩነት ሲኖር በልዩነቱ ላይ ታከስ ይጣላል፡፡

ከንፅፅር ኦዲት ጋር በሚገናኝ በአብዛኛው የሚነሳው ክርከር የንፅፅር ኦዲት የወንጀል ውጤት ሊያስከትል ይገባል ወይስ አይጋም የሚል ሲሆን የወንጀል ውጤት ሊያስከትል አይገባም የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡት መከራከሪያ በዋናነት ከሀሳብ ክፍል ጋር የሚገናኝ ነው፡፡

በእነዚህ ወገኖች የሚቀርበው መከራከሪያ የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ በተመሳሳይ የታክስ መሰረት ላይ የሚጣሉ የታክስ አይነቶች ቢሆኑም በነዚህ የታክስ አይነቶች መካከል ልዩነት በሚኖርበት ወቅት ልዩነቱ  ሊደረስበት የሚችለው በልዩ ምርመራ ኦዲት በተደረገ ምርመራ ሳይሆን ታክስ ከፋዩ የሚያቀርበውን የታክስ ማስታወቂያ መሰረት በማድረግ ነው፡፡አንድ ታክስ ለማጭበርበር የሚያስብ ታክስ ከፋይ መሰረቱ ተመሳሳይ በሆነና ለአንድ ታክስ ሰብሳቢ መ/ቤት የሚገለፀውን ታክስ ማጭበርበር በማስብ ለተጨማሪ እሴት ታክስ አመቱን ሙሉ ሲከፍል የነበረውን ለገቢ ግበር ደብቋል በሚል ድምዳሜ ክስ የሚቀርብበት አግባብ ስነ-አመክንዮ መሰረት የለውም በሚል ክስ ሊቀርብ አይገባም በማለት የሚከራከሩ ሲሆን የክርክራቸው መቋጫ በንፅፅር ኦዲት  የማጭበርበር ሀሳብ ማስረዳት አይቻልም የሚል ነው፡፡

የንፅፅር ኦዲት የክስ መሰረት ሊሆን ይገባል በሚል የሚከራከሩት ወገኖች እንደመከራከሪያ የሚያቀርቡት ነጥብ የሁለቱም ታክስ መሰረት ተመሳሳይ እስከሆነ ድረስ ታክስ በልዩነት ያልተገለፀ ገቢ ኖሮ በንፅፅር የተጣለ ታክስ ካለ ምንጩ ታክስ ከፋይ ከደበቀ ገቢ በመሆኑ ክስ ሊቀርብበት ይገባል የሚል ነው፡፡

በመሰረቱ ታክስ ስወራ ታክስ ለማስከፈል የሚቀርብ ክስ አይደለም፡፡ ታክስ ስወራ ወንጀል ክስ አለማው ለታክስ ስርዓቱ አደጋ የሆኑትን ታክስ ከፋዮች ቀጥቶ በማስተማር የታክስ ተገዢነትን ማረጋገጥ ሲሆን የታክስ ስወራ ወንጀል ጉዳይ በሚነሳበት ወቅት በዋናነት ሶስቱ የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር በአንድነት ሊኖሩ ይገባል፡፡

ንፅፅርን መሰረት በማድረግ በሚሰሩ የምርመራ ኦዲት ላይ የሚገለፁ ግኝቶች በዋናነት በአሃዝ የሚገለፅ የገቢ/ሽያጭ ልዩነት ሲሆን ይህ ልዩነት ታክስ ከፋዩ ለሁለቱ የታክስ አይነቶች የገለፀው ገቢ/ሽያጭ እንደሚለያዩ ከማሳየት ውጭ በተግባር የሚታይ ግዙፋዊ የታክስ ስወራ ወንጀል ፍሬ ነገር ስለመኖሩ ማሳየት አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል የንፅፅር ኦዲት መሰረት የልዩ ምርመራ ኦዲት በራሱ ምርመራ ደረሰበትን ግኝት መሰረት በማድረግ ሳይሆን በታክስ ከፋይ የሚቀርበውን የታክስ መግለጫ መሰረት በማድረግ በልዩነት ላይ ታክስ የሚጣለት የታክስ ስሌት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለፀው በታክስ ስወራ ወንጀል በዋናነት ሲጣራ የሚገባው የታክስ ከፋዮች የሀሳብ ክፍል ሲሆን በተያዘውም ጉዳይ አንድ ግብር ከፋይ ታክሱን ለተመሳሳይ የገቢ ሰብሳቢ መ/ቤት አንደሚያስታውቅ እያወቀ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሲያስታውቅ የነበረውን ገቢ ለገቢ ግብር አላስታወቀም በሚል በልዩነት ላይ የተጣለውን ታክስ መሰረት በማድረግ ታክስ ለመሰወር በማሳብ የታክስ ስወራ ወንጀል ፈፅሟል ብሎ ለመደምደም አያስችልም፡፡ በሌላ በኩል ይህ ታክስ ከፋይ ታክስ ለመሰወር ቢያስብ ኖሮ ገቢውን/ሽያጩን በሁለቱም ታክስ አይነቶች ለባለስልጣን መ/ቤቱ ያስታውቃል ተብሎ አይታሰብም፡፡

በፀኃፊው እምነት ገቢ ሰብሳቢው መ/ቤት ይህን ልዩነት መሰረት በማድረግ ታክስ ጥሎ ገቢ መሰብሰቡ ተገቢ ቢሆንም ግኝቱ ለታክስ ስወራ ወንጀል ከሚያስፈልገው የሀሳብ ክፍል አንፃር ሲታይ ማስረዳት የማይቻልና ግዙፋዊ የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባርም ጭምር ማሣየት የማይቻል በመሆኑ ከላይ የተመለከቱት የግብር ስወራ መሰረታዊ ፍሬ ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ ይህ ግኝት ከፍትሐብሔር ተጠያቂነት ባለፈ የወንጀል ክስ ውጤት ሊኖረው አይገባም፡፡

  • ድርጅት ከመዝጋት/ከምዝገባ ስረዛ ጋር ተያይዞ ከሚጣል ታክስ ጋር የተገናኙ ግኝቶች

ታክስ ከፋዮች ድርጅታቸውን በሚዘጉበት ወቅት ወይም የተጨማሪ እሴት ታክስ ምዝገባ ስረዛ እንዲደረግላቸው ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መ/ቤት በሚያመለክቱበት ወቅት ኦዲት የሚደረጉ ሲሆን በኦዲት ወቅት በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ 285/94 አንቀፅ 4/4 መሰረት የካፒታል ዕቃዎችን ጨምሮ በታክስ ከፋዩ እጅ የሚገኝ ማንኛውም ዕቃ እንደተሸጠ ተቆጥሮ ታክስ የሚሰላበት እንደሆነ በግልፅ የተደነገገ ሲሆን ይህ የሚፈፀምበት አግባብ በመመሪያ 24/2001 ላይ በግልፅ ተመልክቷል፡፡

በመመሪያ 24/2001 መሰረት የሚሰራ የኦዲት ግኝት በልዩ ምርመራ ኦዲት ሪፖርት ላይ ያልተገለፀ ገቢ በሚል የሚገለፅ ሲሆን ይህ ግኝት በዚህ መልኩ የሚገለፀው በታክስ ከፋዮች ሽያጭ ተከናውኖ ያልተገለፀ ገቢ ኖሮ ሳይሆን ታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት የመዝጋት ጥያቄ ላቀረበው ድርጅት የእርጅና ቅናሽ ይዝለት የነበረ በመሆኑ በታክስ ከፋዮች እጅ የሚገኙ የካፒታል ዕቃዎች እንደተሸጠ ዕቃ ተቆጥሮ ታክስ ሊከፈልበት ስለሚገባ ነው፡፡ በመሆኑም በታክስ ከፋይ የተደረገ የታክስ ስወራ ወንጀል ተግባር ባለመሩ ይህ ግኝት የታክስ ስወራ ወንጀል ውጤት ሊኖረው አይችልም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

‘ጠባቂ የሌለው ጠበቃ’ ጥቂት ስለ ኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያዎች ማህበር
የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ (Stop Payment Order) የሚሰጠው መቼ እና ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024