Font size: +
4 minutes reading time (881 words)

ጥቂት ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የኢትዮጵያ መስፈርት ከአለምፍ ሕግ ጋር ሲቃኝ

ሀገሮች የዜጎቻቸውን የንብረት፣ የህይወት በአጠቃላይ የስብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅና ለማረጋገጥ የተለያየ ሕጎችን ያወጣሉ፡፡ እነዚህም ሕጎች ከሕገ-መንግስቱ (የየሃገሩ የበላይ ህግ) ጨምሮ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ያካትታል፡፡ በእነዚህ ሕጎች የተደነገጉት መብቶችን ማራመድ አንዳንድ ጊዜ የሌላውን ሰው መብትና ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡ በእንደዚህ ሁኔታ ላይ ሲሆን ሕግ እነዚህ መብቶች ላይ ገደብ (limitation) ያስቀምጣል፡፡ ይህ የመብት ገደብ ዘለቄታና በቋሚነት የሚፀና ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በሕገ- መንግስታችን አንቀፅ 29 ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተደንግጓል ፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ አንቀፅ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ወጣት ዜጎችን እና የሌሎች ሰዎች መብትና ክብር ለመጠበቅ ሲባል በህግ ሊገደብ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህ የመብት ገደብ ሲሆን ተፈፃሚነቱም በዘለቄታዊነት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የመብት ገደብ ነገሮች ተፈጥሮዊና በተለመደው ሥርዓት ላይ እያሉ የሚተገበር ነው፡፡

በአንፃሩ አንድ ሀገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (state of emergence) የምታውጀው አንድን ክሰተት ባለው ነባርዊና በተለምዶ በተዘረጋው ሥርዓት መቆጣጣር ሳይቻል ሲቀር እንዲሁም የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ሲያጋጥም ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም በሕግ የተደነገጉ መብቶችን ሁሉ ተግባራዊ ላድርግ ማለት አዳጋች አንዳንዴም የማይቻል ሊሆን ይችላል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሰፊው የስብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሊገደቡ ይችላሉ፡፡ ይህ የመብት ገደብ ከላይ ከጠቀስነው የመብት ገደብ የሚለየው ነገር ቢኖር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የመብት ገደብ ዘላቄታዊ ሳይሆን ጊዜያዊ ነው፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ እና በዚህም የተነሳ መብቶች ሊገደብ እንደሚችሉ እውቅና ይሰጣሉ፡፡ እነዚህም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች  ይህንን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ መብት ሲሰጡ በተመሳሳይ መልኩ ምን ምን የሥነ-ሥርዓት (procedural requirements) እና የይዘት (substantive requirements) መስፍርቶችን መሟላት እንዳለባቸው ደንግገዋል፡፡

  1. የይዘት መስፈርቶች

ሀ. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  እጅግ አስፈላጊ መሆን አለበት (necessity test)

አንድ ሀገር በማንኛው ጊዜ መንግስት በዘፈቀደ ተነስቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አይችልም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ከማወጅ ውጪ ሌላ የተሻለ አመራጭ ሳይኖር ሲቀር ነው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ የሚቻለው፡፡ በዚህ ጊዜ ፈታኙ ጥያቄ መቼና በምን ሁኔታ ላይ ነው አስፈላጊ ነው ወይም አይደለም የምንለው?  ለዚህ ጥያቄ አንድ ወጥ መልስ መስጠት ባይቻልም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚከተሉትን እንደ አስፈላጊ ሁኔታ ይቆጥሯቸዋል፡፡ እነዚህም የተፈጥሮ አደጋ፣እርስ በርስ ጦርነት ወይም ግጭት፣  ተላላፊ ወረርሽኝን እንደ ምሳሌ(illustrative list) ወስደው አስፈላጊ ሁኔታዎች ናቸው ይሏቸዋል፡፡

ለ. የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆን አለበት (threatening the existence of the nation)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ሌላው  መስፈርት የገጠመው አደጋ ሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተን መሆን አለበት ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚምታታው ሀሳብ መንግስትና ሀገር የሚለው ነው፡፡ መንግስት የሀገር አንድ ቁንፅል አካል ነው እንጂ እራሱን ችሎ ሀገር ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም የመንግሰት ሥልጣኑ አደጋ ላይ ሲወድቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣል አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ አጠያያቂ ነገር ይከሰስታል፡፡ የአንድን ሃገር ህልውና የሚፈታተን ሁኔታ አጋጥሟል ብሎ የሚወስነው ማነው? በምን መለኪያ? የሚሉ ጥያቄዎች ይከሰታሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት ስለ ሃገሩ ነባራዊ ሁኔታ የተሻለ የሚያወቀው የሃገሩ መንግስት እና አስተዳደር ስለሆን የጉዳዮን ክብደትና ቅለት የመመዘን መብት ተሰጥቷታል (principle of margin of appreciation)

ሐ) አዋጁ ተመጣጣኝ መሆን አለበት (proportionality test)

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊፈታ ያለመው ችግርና የሚገድበው መብት መመጣጠን አለባቸው፡፡ ይህም በስሩ የጂኦግራፌያዊ መመጣጠን፣ የመብት ገደብ መመጣጠን እና የጊዜ ርዝመት መመጣጠን ያካትታል፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ የአማራ ክልል ወረዳዎች ተላለፊ ወረርሽን ቢከሰት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ ማድረግ አላስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም የችግሩ ቦታ አንድ የተወሰነ አካባቢ ሆኖ በችግሩ ምንም ያልተጠቁትን አካባቢዎች ማካተት ምክንያታዊነትና ተመጣጣኝ ያሳጣዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከችግሩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ለምሳሌ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ቢገደብ ይህ የመብት ገደብ ተመጣጣኝነቱን ያሳጣዋል፡፡ የጊዜ ርዝመት ተመጣጣኝነት ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈፃሚ መሆን ያለበት ችግሩ እስኪቀርፍ ብቻ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዘብ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በቀድሞ መሪ ሆሰኒ ሙባርክ  የሥልጣን ዘመን ግብፅ ለ 31 ዓመታት ያህል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነበረች፡፡ ይህም ከጊዜ ርዝመት ተመጣጣኝነት መርህ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡

መ) አዋጅ እኩል ተፈፃሚ መሆን አለበት (equality test)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ዘርን፣ ሀይማኖት፣ ፆታን፣  እድሜን፣ ቀለምን እና ሌሎች ምክንያታዊ ያልሆኑ መስፈርቶች መሰረት ልዩነት  መደረግ የለበትም፡፡

ሠ) በአዋጅ የማይጣሱ መብቶችን ማክበር አለበት (non-derogablity test)

ከላይ ለማተት እንደተሞከርው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በባህሪው መብቶች ላይ ገደብ የሚጥል ነው፤ ነገር ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ቢሆን የማይጣሱ መብቶች አሉ፡፡ እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፤ በህይወት የመኖር መብት፣በባርነት ያለመግዛት መብት፣  ከኢስብአዊ አያያዝ ነፃ መሆን፣  እንደሰው የመቆጠር መብት ይገኙበታል፡፡

  1. የሥነ-ሥርዓት መስፈርቶች

አንድ ሀገር ከይዘት  በተጨማሪ የሥነ-ሥርዓት መስፈርቶችንም ማሟላት እንዳለባት ተደነግጎል፡፡ የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች ሁለት መልክ ያለው ሲሆን ይህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአዋጅ መደንገግ እንዳለበት እንዲሁም አዋጁ ለሁሉም በሚገባ መልኩ ግልፅ፣ የማያሻማና ተደራሽ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በዘለለም አዋጁ መታወጁን ለሌሎች ሀገራት ማሳወቅ እንደሚገባ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅሀፊ በማሳውቅ ነው፡፡ከላይ የተዘሩት ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና ሕጋዊነት የሚኖረው፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በአንቀፅ 93 ላይ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጠቃላይ ሁኔታ ደንግጓ ይገኛል፡፡አንቀፅ 93 (1) (ሀ) መሰረት የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ-መንግስታዊ  ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከስት በተለመደው የሕግ ማስከበር ስርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሲደርስ የፌደራል የሚኒስትሮች ም/ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ስልጣን አለው፡፡ ይህ ተመሳሳይ መብት ለክልሎች ተሰቷል ፡፡ በሕገ-መንግስታችን ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያቶች ሁሉም የተዘረዘሩ በመሆን ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ማካተት አይቻልም፡፡ የዓለም አቀፍ ህጎች የዘረዘሩት ጥቂቶቿንና ለምሳሌነት (illustrative list) ሲሆን የእኛ ሀገር ሕገ-መንግስት ግን ዝግ ዝርዝር (exhaustive list) ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመብት ገደብን ስለሚያስከትል የዝግ ዝርዝር (የተገደበ ዝርዝር) መርህ በእጁጉ የዜጎችን መብት የሚያስጠብቅ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

አንቀፅ 93 (4) (ሐ) ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢሆን የማይገደቡ መብቶች የጠቀሰ ሲሆን እነዚህም አንቀፅ 1 (የኢትዮጵያ መንግስት ስያሜ )፣ አንቀፅ 18( ኢሰባአዊ አያያዝ ሰለመከልከል)፣ አንቀፅ 25( የእኩልነት መብት) እና አንቀፅ 39 (1) (2) (የብሔሮች፣  ብሔረሰቦች፣  ሕዝቦች መብት) ናቸው፡፡ ከአለም አቀፍ መስፈርት በተቃርነ መልኩ በርካታ መብቶች  ማለትም በህይወት የመኖር መብት፣ እንደሰው የመቆጠር መብት፣ በውል ምክንያት የወንጀል እስር እንዳይኖርና ሌሎች መብቶችን ሳያካትት ቀርቷል፡፡

ጠቅለል ስናደርገው የአለም አቀር ስምምነተች አንድ ሀገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ መብት ቢኖራትም በቅድሚያ መሞላት ያለባቸው የይዘትና የሥነ ሥርዓት ሁኔታ እንዳሉ ይደነግጋል፡፡ ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀፅ 93 የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት ደንግጓ ቢገኝም በአንዳንድ ጉዳዮች ከአለም አቀፍ ስምምነት በጋር መጣረስ ይታይበታል፡፡  

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Hammering Labor Rights: Succinct Summary of the Dr...
Tax Evasion under Ethiopian Tax Laws - Conceptual ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024