የዘገየ ፍርድ
እኔ አንቺን ስጠብቅ
ጠበኩሽ እኔማ…….
እዚያው ሰፈር ቆሜ
በአክሱም ቁመና በላሊበላ ዕድሜ
እግሮቼን ተክዬ ቀኔን አስረዝሜ
ትመጫለሽ ብዬ በቆምኩበት ስፍራ
ስንት ነገር መጣ ስንት ነገር ሄደ
ስንት ጊዜ ነጋ ስንቴ ጎህ ቀደደ
በቀጠርሽኝ ስፍራ ስጠብቅሽ ቆሜ
ስንት ሳቅ አለፈ ስንትና ስንት እንባ
ስንቴ ክረምት ሆነ ስንቴ ጸደይ ጠባ……..
ታገል ሰይፉ
መግቢያ
ዋስትና በሕገ መንግሥትም ሆነ የሕገ መንግስቱ የበታች በሆኑ በርካታ ሕጎች የታፈረና የተከበረ መሠረታዊው ከሆነው የሰው ልጅ የመዘዋወር ነፃነትና ንፁሕ ሆኖ የመገመት መብት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሰብዓዊ መብት ነው፡፡ የሰው ልጅ እንደፈለገ ለመዘዋወር ሁለት እግሮች የተሰጡት፤ በአንድ ቦታ ተወስኖ እንዳይቀመጥ ሰዋዊ ተፈጥሮ ነፃ አድርጎ የፈጠረው ይህን ተፈጥሮውንም አብዝቶ የሚወድ ነፃ ፍጡር ነው፡፡ ይህ ፍጡር አሳማኝ የሆነ ማስረጃ በማቅረብ አንዳች ወንጀል መፈፀሙ ካልተረጋገጠበት በስተቀር ንፁህ ሆኖ የመቆጠር መብትም አለው፡፡
ይህ ከላይ ከፍ ሲል የተገለፀው ነፃ ሰው በሕግ ከመዘዋወር ሊከለከል፤ በአንድ በተለየ ስፍራ ታስሮ ሊቀመጥ የሚችለው ለጠቅላላው ህዝብ ጥቅም ሲባል፣ የጠቅላላውን ህዝብ ጥቅም ከአደጋ ለመጠበቅ ከፍተኛ የሆነ ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝ ምንአልባት የተጠርጣሪውን የዋስትና መብት ማክበር ይህን የጠቅላላውን ህዝብ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ይህንን የጠቅላላውን የሕዝብ ጥቅም ለመታደግ ሲባል ብቻ አስቀድሞ በተቀመጠ ሕግ ሊገደብ የሚችል መሠረታዊ መብት ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ መነሻ ከመነሻው የዋስትና መብትን መገደብ ሕገ መንግሥታዊ ነው ወይስ አይደለም የሚል ሳይሆን ክርክርን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ የሚያስችል ሥርዓት (speedy trial) መዘርጋቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አንድ ወንጀል ፈፅሟል በሚል ክስ ስለቀረበበት ወይም ሊቀርብበት ስለሚችል ብቻ ዋስትና መከልከል ሕገ መንግሥታዊ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡
ፈጣን ፍትሕ እንደ መብት
አንድ ሰው ዋስትና ተከልክሎም ይሁን ሳይከለከል በወንጀል ምክንያት በመከሰሱ ምክንያት ስሙ ከአቶ/ወሮ/ት ወይም ከመአረግ ስሙ ወደ ተከሳሽነት ሲለወጥ በሕግ ከተደነገጉልት በርካታ መብቶች አንዱ በተከሰሰበት ጉዳይ በአጭር ግዜ ፍርድ የማግኝት መብት ነው፡፡ ይህም በሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 20 እንዲሁም ኢትዮጵያ በመፈረም የህጓ አካል ባደረገችው የአለም አቀፉ የሲቪል እና የፖለቲካ ስምምነት (ICCPR) አንቀፅ 14(3) (ሐ) መሠረት ተገቢ በሆነ አጭር ግዜ ውስጥ ፍርድ የማግኝት መብት ተረጋግጧል፡፡ ይህ መብት በሕግ ገደብ እንደሚደረገባቸው ሌሎች መብቶች ገደብ ያልተደረገበት ፍርድ ቤቶች ከምንም በላይ ስለመረጋጋጡ ሊተጉለት የሚገባ መሠረታዊ መብት ነው፡፡ የዚህ መብት መከበር መሠረታዊ ጥቅም ለተከሳሹ ብቻ ሳይሆን በወንጀል ምክንያት ተጎጅ ለሆነው ተበዳይ፤ በተራዘመ ክርክር ምክንያት ለሚወጣው የመንግሥትና የግለሰቦች ጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜም ጭምር ነው፡፡
ይህን መብት የሚደነግገው የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 20 (1) ይህ መብት ብቻውን የቆመ ሳይሆን በአጭር ግዜ ፍትሕ የማግኝት መብት መረጋገጥ ያለበት በግልፅ ችሎትም ጭምር ስለመሆኑ ይደነግጋል፡፡ ምክንያቱም የተከሳሹ ነፃ መውጣትም ሆነ መቀጣት የፍረድ ቤቱ ወይም ጉዳዩ የሚመለከታችው ሰዎች ብቻ ሳይሆን የጠቅላላ ማህብረስቡ ጉዳይ ነው፡፡ ጠቅላላው ማህበርስቡ የተከሳሹ ባግባቡ ነፃ መውጣት በፍርድ ቤቶች ላይ ያላቸውን መተማመን ብሎም ወንጀል እስካልሰሩ ድረስ ደህንነታቸው አደጋ ላይ እንደማይወድቅ ማረጋገጫቸው ነው፡፡ ባግባቡ የተከሳሽ መቀጣት ደግሞ ንብረታቸውን፣ ህይወታቸውን፣ አካላቸውን ማንም እየተነሳ እንዳይደፍረው ማስፈራሪያ ተደፍሮ ሲገኝም የእርምት መወስጃ መንገዳቸው ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሕ በአደባባይ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ሲሰጥ መመልከት መብት ነው፡፡ ተከሳሹ በርግጥ በቂ ማስረጃ ቀርቦበታል? ተከሳሽ የሚለው ይደመጣል? የችሎት ሰርዓቱ ሕጉን መሰርት አድርጎ ይመራል? ተከሳሽ አጥፊ መሆኑ ከተረጋገጠ በርግጥ የሚገባውን አግኝቷል ? እነዚህ ምላሾች በአደበባይ በግልፅ ችሎት ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ሲሰጥ ፍትሕ በማህበረሰቡ ሰነድ ህያው ትሆናለች፡፡ ስምና ሀሳብ ከመሆን አልፋ በርግጥ የምትሰማ፣ የምትዳሰስ ትሆናለች፡፡ ይህ መብት በዋስ ሆኖ ጉዳዩ ውጭ ሆኖ ለሚከታተለውም ዋስትና ተከልክሎ በማረፊያ ቤት ለሚገኝ እስረኛም የሚሰራ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ማጠንተኛ ዋስትና ተከልከሎ ማረሚያቤት ስላለ እስረኛ ብቻ ትኩረት ያደርጋል፡፡
በኛ ሀገር የሕግ ሥርዓት አንድ ሰው በተጠረጠረበት ወንጀል ሊከሰስ የሚችል ከሆነ ወይም ከተከሰሰ የተከሳሹ ግላዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምንም ከመነሻው ወዲያውኑ ዋስትና የሚያስከለክሉ በርካታ የወንጀል አይነቶች አሉ፡፡ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 882 አንቀፅ 3 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው አንድ ሰው ከ10 አመት ፅኑ እስራት በላይ በሚያስቀጣ የሙስና ወንጀል የተያዘ ወይም የተከሰሰ እንደሆነ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥ በመገኘቱ ብቻ ከፍ ሲል የተገለፀውን መሠረታዊ የዋስትና መብቱን ከጅምሩ ያጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሕግ በግልፅ በመደንገግ ወይም በችሎቶቹ የተለየ አቋም ክስ በመቅረቡ ወይም ምርመራ በመጀመሩ ምክንያት ዋስትና የሚስከልክሉ ሕጎች እየተበራከቱ ሲሆን ለምሳሌነትም የሽብር ወንጀል፤ ከ15 አመት በላይ የሚያስቀጣ ሆኖ ሰው የሞተበት የትኛውም ወንጀል እንዲሁም በሕግ ዋስትና ለማስከልክል ምክንየት የሆኑ የፍሬ ነገር ምክን ያቶች በመኖራቸው ፍርድ ቤቶች በሕግ በተሰጣቸው ስልጣን ዋስትና የሚከለክሉባቸው ወንጀሎችና ወንጀለኞች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለይም በአሁኑ ሰአት ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ወንጀሎች ምክንያት በጊዜ ቀጠሮ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የግዜ ቀጠሮ እስረኞችን (ዋስትና ተከልክለው ወይም ዋስትና ማስያዝ ባለመቸላቸው በእስር ሆነው ፍረዳቸውን የሚጠባበቁ እስረኞች) ብዛት ማየት በቂ ነው፡፡
ይህ ሁኔታ ከፍ ሲል የዋስትና መብት ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል ሊገደብ ስለመቻሉ ከተነገረው ጋር የሚስማማ ይሁንም አይሁንም ጉዳዩን በአጭር ጊዜ አይቶ ለመወሰን የሚያስችል የሰው ሀይል አሰራር እና ሥርዓት ስለመኖሩ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ አንድን ሰው በሕግ ከጅምሩ የዋስትና መብቱን መከልከል የሕገ መንግስቱን አንቀፅ 20 እንዲሁም ኢትዮጲያ በመፈረም የህጓ አካል ያደረገችውን የአለም አቀፉን የሲቪል እና የፖለቲካ ስምምነት (ICCPR) አንቀፅ 14 (3) (ሐ) የሚጥስ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱም ይሁን የአለም አቀፍ ስምምነቱ አቀራረብ ግልፅ እና ቅልብጭ ያለ ሲሆን ይኸውም ማንኛውም ሰው በአጭር ጊዜ ፍትሕ የማግኘት መብት አለው ወይም ካላስፈላጊ የፍትሕ መዘግየት የተጠበቀ ነው፡፡
ይህ መሠረታዊ መብት ነው እጅግ በተለመደ ሁኔታ የዘገየ ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል (justice delayed is justice denied) በሚል በሕግ ምሁራን በተደጋጋሚ ሲገለፅ የሚሰማው፡፡ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ተብሎም ይቀጣ ድርጊቱን አልፈፀመም ተብሎም ነፃ ይለቀቅ መሠረታዊው ነገር ተከሳሹ ነፃ የወጣውም ሆነ የተቀጣው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው የሚለው ነው? የሰው ልጅ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ውስጥ የማወቅ ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ያለው መሆኑን ሳይታበል በጊዜው ያልተሰጠ ፍርድ በተለይ በወንጀል ችሎቶች በሚፈፅሙ ስህተቶች እና መዘግየቶች የካሳ ሥርዓት ባላዘረጋጀ እንደ ኢትዮጲያ ባለች ሀገር ውስጥ ለረዥም ጊዜ ታስረው ነፃ የወጡ ወይም ሊቀጡ ከሚገባቸው ጊዜ በላይ በእስራት የተቀጡ ሰዋች ማየት በተለይም በፀረ ሙስናና በአንዳንድ ሌሎች ችሎቶች እየተለመደ ያለ ጉዳይ ሆኗል፡፡
የዚህ ጽሑፍ መነሻም በነዚህ ችሎቶች ዋስትና ተከልክለው ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ተከሳሾች ጉዳያቸው የሚያልቀው እጅግ በተራዘመ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
የጽሑፍ አቅራቢ በበርካታ የፀረ ሙስና የክስ ሂደቶች መታዘብ የቻለው አንድ ጉዳይ በትንሹ ከ1 አመት እስከ 2 አመት ከ6 ወር ድረስ በአማካኝ ይወስዳል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የዳኞች በስራ ጫና ወስጥ ሆነው ስራ መስራት፤ በርካታ ተከሳሾችን በአንድ መዝገብ ማከራከር፤ የክርክር ግልባጭ በወቅቱ አለመድረስ፤ የዳኛ አለመሟላት፤ በአጠቃላይ አስተዳደራዊ የሆኑ እና ያልሆኑ የሆኑ እንደ ፀኃፊ እጥረት፤ የክርክር መገልበጫ ማሽኖች እና ባለሙያዎች በበቂ መጠን አለመኖር፤የዳኞች ቁጥር እና የጉዳዮች ፍስት አለመጣጣም የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በነዚህና በዚህ ጽሑፍ ባልተጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች በታሰሩበት ግዜ ከአምስት እና ከስድስት ጊዜ በላይ ጉዳያቸው ቀጠሮ የማያስፈልገው ቢሆነም ክፍ ሲል የተገለፁተ ምክንያቶች እስኪስተካከሉ ወይም እስኪሟሉ ለበርካታ ወራት እና አመታት ጭምር ታስረው በነፃ የወጡ አንቀፅ ተቀይሮ ወይም በሌላ ምክንያት አነስተኛ ቅጣት ተቀጥተው መቀጣት ከሚገባቸው በላይ የተቀጡ በርካታ ተከሳሾች ያሉ ሲሆን በዚህ ሂደት ከተገኘ ፍርድ ተጠርጣሪው ሊረካ እንደማይችል፤ ጥቅሙ አደጋ ላይ ወድቋል የተባለው ህዝብም ሆነ ይህንን የጠቅላላውን ህዝብ ጥቅም በመወከል ሕግ የሚያወጣው ሕግ አውጪም ፍላጎት እንዳልተሳካ ግልጽ ነው፡፡
በአንድ ችሎት በአንድ ቀን በርካታ መዝገቦች መቆለላቸው፤ የዳኞች ቁጥር በችሎቱ ከሚመሩ መዝገቦች ጋር የማይጣጣም መሆኑ፤ የየችሎት ክርክሮች ግልባጭ በጊዜ አለመገልበጥ፣ ዓ/ሕግ ተገቢውን ትጋት አድርጎ ምስክሮች ማቅረብ አለመቻሉ ብቻ ተከሳሹን የማይመለከቱ ይልቁንስ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን የሚያጣብቡ ነገር ግን የሚመለከታቸው አካላት የሚገባቸው ባለማድረጋቸው አንድ ተከሳሽ በአመት ውስጥ ለስድስት እና ስባት ግዜ ብቻ እየተቀጠረ ከነዚህ ቀናት ውጭ ያሉት 359 ቀናት ጉዳዩ ሳይታይ የቀጠሮውን መድረስ እየጠበቀ የሚያባክናቸው ብኩን ቀናቶቹ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ የፍርድ ስራውን ለመስራት አስፈላጊ የሆነውን ወይም ጉዳዩን ለመፈፀም ወይም ለፍርድ ስራው አስፈላጊ የሆነው ነገር እንዲቀርብ ለማድረግ ፍ/ቤቶች ተገቢው ጊዜ መሰጠት የለባቸውም እየተባለ ሳይሆን የሚሰጡ ቀጠሮዎች በስነሥርዓት ህጉ አንቀፅ 94 መሠረት አስፈላጊ ከሆኑ ቀጠሮዎች ውጭ ተከሳሽ የሱ ወይም የክሱ ምክንያት ባልሆነ አስተዳደራዊ ምክንያት፣ የዳኛ እጥረት፣ የመዝገብ ብዛት፣ የሙያተኛ ቸልተኝነት ምክንያት ቁጭ ብሎ መጠበቅ አይገባመው ለማለት ነው፡፡ በተለይም በስነሥርዓት ህጉ ላይ አንድ እስረኛ እጁ በተያዘ በ48 ሰዓት ውስጥ አቅራቢያው ወደ ሚገኝ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት፡፡ የዋስትና ጉዳዩም በ48 ሰዓት ውስጥ እልባት ሊያገኙ ከሚገባቸው መሠረታዊ መብቶች ውስጥ ስለመሆኑ በተደነገገበት ሁኔታ ይሄ በፍጥነት ወደ ፍ/ቤት እንዲመጣ የተደረገ ተከሳሽ በመጣበት አኳኳን በፍጥነት ጉዳዩ ከፍ/ቤት መጨረስ አለመቻሉ በሕግ በተለያየ መልክ በጥብቅ ሁኔታ የተደነገገውና ሕገመንግስታዊ መሠረት ያለውን ፈጣን ፍርድ የማግኝ መብት እንደመጣስ የሚቆጠር ተግባር ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች አንድ ጉዳይ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ አለመጠናቀቁ ሲረጋገጥ ክስ ውድቅ የሚሆንበት ስረአት ያለ ሲሆን ይህ ስርዓት በኛ ሀገር ባይኖርም ሕገ መንግስቱ ለማክበር ሲባል ሕገመንግሰቱን በተለይም ከሰባአዊ መብት ጋር የተያያዙ የሕገ መንግስቱን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ሃላፊነት በፍረድ ቤቶች በራሳቸው፤ በሕግ አውጭው፤ በአስተዳድር አካሎች፤ የበጅት ጉዳይ በሚመለከታቸው ሕግ አስፈፃሚዎች ላይ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 13 ላይ በግልፅ የተደነገገ በመሆኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን መፍታት ወይም ከጅምሩ ፈጣን የፍርድ ሂደት ስለመኖሩ ሳይረጋገጥ ክስ አለመመስረት ተመስርቶም ከሆነ ውድቅ ማድረግ ሕገ ምንግሥቱን ለማክበርም ሆነ ለማስከበር ያሉት ሁለት አማራጮች ናቸው፡፡
እንደዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ሀሳብ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ የሚያስችል ሥርዓት ባልተዘረጋበት ስለመኖሩም እርግጠኛ ባልተሆነበት የፍትሕ ስርዓት ውስጥ ከመነሻው ዋስትና የሚያስከለክሉ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ከፍ ሲል የተገለፀውን ሕገመንግስታዊ መብት የሚፃረር ተግባር ነው፡፡ የተጠርጣሪው በዋስ የመፍታት መብት ለህዝቡ ጠቅላላ ጥቅም ሲባል በሕግ የሚገደብ ቢሆንም ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የተገደበን የዋስ መብት ሕገመንግስታዊ ባልሆነና የጠቅላላው ህዝብም ፍላጎት ባልሆነ የተራዘመ የፍትሕ ሂደት ይበልጥ ተገድቦ እንዲቆይ ማድረግ ፍፁም ሕገመንግስታዊ ሊሆን አይችልም፡፡
መደምደሚያ
የጽሑፍ መልእክት ግልፀ ነው ይሄውም ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ፍርድ የማግኘት መብት ሕገመንግስታዊ እስከሆነ ድረስ የፍርድ ስራ ከመጀመሩ በፊት የተከሳሹን ጉዳይ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ለመጨረስ የሚያስችል ሁለንተናዊ ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ በተለይም ተከሳሹ ዋስትና የተከለከለ ከሆነ ፈጣን የሆነፈጣን የሆነ ፍርድ መሰጠቱ አስቀድሞ ካልተረጋገጠ በስተቀር የክሱን መሰማት መጀመር የለበትም ምክያቱም ይህ ሁኔታ መኖሩ ሳይረጋገጥ ክርክሩን መጀመር የሕገመንግስቱ አንቀጽ 20 መጣስ ነው፡ ሕገመንግስቱ ከሚጣስ የክሱ አለመጀመር አስር እጅ አብዝቶ ይሻላልና፡፡
በመሆኑም ከጅምሩ የዋስ መብት በሚከለክሉ ወንጀሎች ሁሉ የተፋጠነ ፍትሕ /የፍርድ ሒደት/ መኖሩ ካልተረጋገጠ በስተቀር ዋስትና መከልከል ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያት:
- ከጅምሩም የዘገየ ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል፡፡
- ከመነሻው ሊከለከል የማይገባውን ነገር ግን ለህዝብ ጥቅም ሲባል በሕግ የተገደበን መብት ለተራዘመ ጊዜ እንደተገደበ ማቆየት በራሱ ፍትሕ አይደለም፡፡
- አንድ ሰው ለረዥም ጊዜ ታስሮ ቆይቶ በመጨረሻም በሚሰጠው ፍርድ የሚደርስበት ጉዳት ለሁለንትናዊ ለውጡ የሚጠቀምባቸው ግዚያት ክህይዎቱ ተቆርጠው መቅረት፡፡ ከመታሰሩ በፊት የሰበስበው ሀብት የገንባው ማህበራዊ ትስስርና ቤተስቡ መበተን፤ ከፈጥሮው ጋር የሚሰማመው የመዘዋወር ነፃነቱ ተገድቦ መቆየት ሊካስ የማይችል ይካስ ቢባል እንኳ ይህንን ማድረግ የሚያስችል የሕግ ስርዓት ባለመሆሩ ከማንኛውም ዋስትና ከሚያስከለክል ወንጀል ክስ በፊት የተፋጠነ የፍርድ ሂደት መኖሩ ፍጹም መረጋገጥ አለበት፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments