ዳኛ እግዜር! ዳኛ ከችሎት ይነሳ!
ሀገሬው የዳኝነትን ሥራ (ፍትሕ መስጠት) ሃሳባዊ በማድረግ ደረጃውን ከፍ ሲያደርገው “ዳኛ እግዜር!” ይላል፡፡ ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላትም ዳኛ ማሪያም! ተሙዋጋች በዳኛ ፊት ቆሞ ሲአመለክት ዳኛ እግዚአብሔር! ያሳይህ ዳኛ ማርያም ወይም ሲሙአገት ጭብጥ የያዘውን አስመስካሪውን ዳኛ የምስክሮቹን ቃል ለማሳሰብ ተዘከረኝ ዳኛ ማሪያም ይላል በማለት ይገልፀዋል፡፡ እንደ ፕልቶ ያሉ ሃሳባውያን (idealist) ፈላስፎች “ፍትሕ” ሃሳባዊ ተፈጥሮ ያለው፣ ከሰብዓዊ ባህርይ ውጪ የሆነ እና አሁን ባለው ዓለም (physical world) ሳይሆን በጊዜ እና በቦታ ባልተገደበው ሃሳባዊ ዓለም የሚገኝ እንደመሆኑ ስሙ ብቻ የሚታየውን ሃሳብ ቅርፅ ወዳለው ድርጊት በሕግ መልክ ሆነ በሌላ ዘዴ ወደ ዚህኛው ዓለም ሊመልሱት እና ሊፈፅሙት የሚችሉት እውነተኛው ሃሳብ የሚታያቸው ሰዎች ናቸው ይላል፡፡ እንግዲህ ሀገሬው “ዳኛ እግዜር” ሲል በፍትሕ ላይ ሃሳባዊ መሆኑ ነው፡፡ “ፍትሕ ከፈጣሪ ነው” ብሎ ለሚያምን ማህበረሰብ ሰው በፈራጅነት ቦታ ቁጭ ብሎ ሲያገኘው በአገረኛ ዘዬ ኧረ! ዳኛ እግዜር! ቢል አይገርምም፡፡ ሌላው ሀገሬው በፍትሕ ላይ ሃሳባዊ ለመሆኑ መገለጫ የሚሆነው ለዳኛ ሲሰጠው የነበረው ልዩ ቦታ ነው፡፡ የአንድ ማህበረሰብ ወግ እና ሥርዓት የሚቀዳው ካለው አካባቢያዊ የእምነት እና አስተሳሰብ መሠረት አድርጎ ነው፡፡ ለማሳያ ያህል ከፍትሐ ነገስቱ አንድ ነገር አንጠልጥለን እንውጣ፡፡
ፍትሐ ነገስቱ አንቀጽ 43 ዳኛ የፍርድን ልዩነት የሚያውቅ፣ አዕምሮው ያማረለት፣ ከድንቁርና የራቀ በአዕምሮውም መራቀቅ የጭንቅና የተሰወረውን ወደ ፍርድ ፍፃሜ መግለፅ የሚደርስ ይሁን፤ ነፃነት ያለው ይሁን፤ ራሱን ለማስተዳደር ሥልጣን ያለው ያልሆነ ሰው ሌሎችን ሊያስተዳድር አይቻለውምና፤ ዳኞች በፍርድ ጊዜ የማያደሉ ፊት አይተው መማለጃ (ጉቦ) የማይቀበሉ ይሁኑ፤ መማለጃ (ጉቦ) እውነትን እንዳያዩ የብልሆችን ዓይን ያሳውራልና፤ የቀናውንም ፍርድ ይለውጣልና በማለት ይገልፀዋል፡፡
ፍትሐ ነገስቱ ከአፄ ዘርዐያቆብ ንግስና ዘመን ከ1444 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ሁለተኛው ሕገ መንግሥት ተረቆ በአዋጅ ሥራ ላይ እስከዋለበት 1948 ዓ.ም ድረስ ለብዙ ዘመናት በሥራ ላይ የዋለ እንደመሆኑ ማህበረሰባዊ ቅቡልነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ህዝቡ ለዳኛ የሚሰጠው ስብዕናም ከፍትሐ ነገስቱ የተቀዳ እና ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ መልኩ የመጣ ነው፡፡ በአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ለዳኛ ስብዕና ያለው ግልፅ መረዳት (pereception) የሚመነጨው ፍትሕን ወደ ተግባር ሊያወርዱት የሚችሉት የተለየ ሥነ-ምግባር እና ያማረ ረቂቅ የሆነ አእምሮ ያለቸው ስዎች መሆን አለባቸው ከሚለው እሳቤ ነው፡፡ ሀገሬው ዳኞች ከመረመሩ ይናገራል ምድሩ፤ ይገኛል ነገሩ በማለት ያዳንቅ የነበር እና ዳኛው የረገጠውን ዲካ (ዱካ) እኔም ረገጥኩት በማለት ሀሴት ያደርግ የነበረው ለዳኝነት ሙያ በነበረው ልዩ ምልከታ እንጅ ዳኛ የተለዬ ፍጡር ስለነበር አልነበረም፡፡
ታዲያ ሀገሬው ዳኛ ወጥ ሲረግጥ ሲያይ አብሮ ወጥ አይረግጥም፡፡ ዳኛ እግዜር! ብሎ ባሞካሸበት አፉ “ዳኛ ሲገኝ ተናገር፤ ውሃ ሲጠራ ተሻገር” የሚል ስንኝ ቋጥሮ በተግባር የለህም ይልሃል፡፡ ህዝብ አይደለም ለመሰሉ ፍጡር ባስ ሲልበት ለአምላኩ አይመለስም፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጦ ፈጣሪውን “ወይ ፍረድ! ወይ ውረድ!” በማለት ምሬቱን ያሰማል፡፡ በደርግ ዘመነ መንግስት መልሶ ማልማት የሚባል የግዳጅ ሰፈራ ነበር፡፡ በሰፈራው ምክንያት ህዝቡ ከስር ጀምሮ እየተቀባበለ ሲገነባው የኖረው ማህበራዊ ሕይዎቱ ዓይኑ እያዬ ሲናድ ከጎረቤቱ እና ከልጁ የመሰረተው ማህበራዊ እሴት ሲበጣጠስ ዳቦ ከማጣቱ በላይ ከባድ ህመም ሆነበት፡፡ እውነትም ዳቦ ከማጣት በላይ ማንነታችን የተመሰረተበትን ማህበራዊ እሴት መናጋቱ የከፋ ነው፡፡ ለፈጣሪው ርሃብ በጎበኘው ድምፁ “ኧረ እንዳላየህ እንዳልሰማህ ዝም አትበል! የፍትሕ ያለህ!” በማለት የዘወትር ልመና ቢያስተጋባም ወዲያውኑ ምላሽ የለም፡፡
አንጋጦ ፍትሕን ጠይቆ እንዳሰበው ምላሽ ያላገኘው ሃገሬው
“አሻቅቤ ባዬው ሰማዩ ቀለለኝ፤
አንተንም ሰፈራ ወሰዱህ መሰለኝ፡፡”
በማለት ምፀት በሚሰል ስሩ ግን ምርር ባለ አነጋገር የገለፀበትን ሁኔታ ስናስብ ማህበረሰባችን ያለፈበትን ረቀቂ የመታዘብ እና የመተቸት የስነ ልቦና ደረጃ እንድንመረምር ገፊ ምክንያት ይሆነናል፡፡ ዳኛ በዳኝነት ሥራው እና ተክለ ስብዕናው በህዝብ ዓይን ውስጥ የመግባት እድሉ የሰፋ እና መመዘኛውም መሰረት የያዘ ረቂቅ እንደመሆኑ ሁሌም ለትቺት ሆነ ለሙገሳ ኢላማ ውስጥ ነው፡፡ ሳሩን አይቶ ገደሉ ለተሸፈነበት በሬ አይ የሆድ ነገር ከማለት የዘለለ ሀዘኔታ አያገኝም፡፡ በሩን እየከፈተ ሰውን ሌባ የሚል፤ ግመሉን ፈቶ አላህን የሚያማርር “ግመልህንም እሰር፤ አላህንም እመን!” ከማለት ውጭ ሌላ የሥነ-መለኮት ትምህርት የሚያስፈለግው አይደለም፡፡ ዳኝነት ፀጋ እንጅ መድን (immunity) አይደለም፡፡ ተቆጥሮ የተሰጠውን ግዴታ ሲሰፍር ያጎደለ በሰፈረው ቁና የትም ይሰፈራል፡፡ የማህበረሰብ ውልን (social contract) በውዴታ ግዴታ ተቀብሎ “እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ!” ለሚል ሻጋታ ምሽግ ጊዜው ቦታ ያለው አይመስልም፡፡ ከግዴታ ጀርባ ተጠያቂነት ደጀን መቆሙ ለቀልድ አይመችም፡፡ ሁሉም ለሚጥለው አሻራ ሃላፊ ነው፡፡ ዳኛውም ምስለኔውም እምነት ከታጣበት ወራጅ ነው፡፡
ዳኛ ከችሎት ይነሳልኝ!
ዳኛ የማህበረሰቡ አካል እንደመሆኑ ከዘወትር ኩነቶች አያመልጥም፡፡ ትላንት ዳኛ እግዜር! በተባለበት ምግባሩ ዛሬ ዳኛ ከችሎት ይነሳልኝ! የሚያስብል ያልተገባ አካሄድ ከሄደ ይማርህ ብሎ ኧረ ይድፋህ! ማለት ነውር የለውም፡፡ በመስኩ ያጠኑ ሃሳባውያን “Law without remedies is like a broken pencil (pointless)” በማለት የሚገልፁት በግርድፉ ሕግ መፍትሔን ካልወለደ ልክ እንደ ስለት አልባ እርሳስ ዱልዱም ነው ለማለት ሲፈልጉ ነው፡፡ ባለፍነው አሰራር ዳኛ በአድሎ በዘመድ አዝማድ እና በተራ ጥቀመኘነት እንዲሁም ሌሎች መሰል ምክንያቶች ፍርድ ሊያጋድድ ይችላል ተብሎ ሲታሰብ ዳኛው ከችሎት የሚነሳበት አኳኋን በሕግ ሽፋን የነበረው ቢሆንም በትግበራ ወጥነት አልነበረውም፡፡ የቀደመውና የተሻረው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት (አብክመ) የፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 11/1988 አንቀፅ 11 ዳኛ አንድን ጉዳይ እንዳያይ በሕግ የተከለከለ በሚሆንበት ጊዜ እና ጉዳዩን እንዳይመለከት አቤቱታ በሚቀርብበት ጊዜ አፈፃፀሙ በሕግ በተወሰነው መልኩ ይሆናል በማለት አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም በክልሉ ደረጃ የተሻሻለው የአብክመ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 223/2007 ሥራ ላይ እስኪውል ዳኛ ከችሎት የሚነሳበት ሥነ ሥርዓት በሕግ የተወሰነ ነገር አልነበረውም፡፡ ይህንን ክፍተት ተከትሎ በፍርድ ቤቶች ዳኛ ከችሎት የሚነሳበት ሁለት ዓይነት አሰራሮች መያዝ ጀምሮ የነበረበት ሁኔታ አለ፡፡ አንደኛው አሰራር ዳኛ ከችሎት እንዲነሳ አቤቱታ በሚቀርብበት ጊዜ ጉዳዩን በአስተዳደራዊ ጉዳይ መፍታት ነው፡፡ ይህም ማለት አቤቱታው የቀረበለት የፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ የቅሬታውን ምክንያት ተመልክቶ አሳማኝ ካልሆነ ባለጉዳዩን የማግባባት ሥራ መሥራት ወይም ጉዳዩ በሌላ ዳኛ እንዲታይ ማስተላፍን የሚጨምር ሲሆን በተጨማሪም ቅሬታው የቀረበለት ዳኛ ዝርዝር ምክንያቱን ሳያጤን ሆነ ሳይመለከት ቅሬታ መቅረቡን ብቻ መሠረት አድርጎ ከችሎት በመነሳት በሌላ ችሎት የሚታይበት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ቅሬታ የቀረበላቸው ዳኞች ተከራካሪው ቅር እያለው ጉዳዩን ለመመልከት ባለመፈለግ ብቻ ከችሎት ሲነሱ የነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡
ሁለተኛው አሰራር የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 ዳኛ ከችሎት የሚነሳበት ሥነ ሥርዓት በተደነገገው መልኩ አቤቱታውን ማስተናገድ ነው፡፡ የዚህ አሰራር ምንጭ አንድ ጉዳይ በክልል ሕግ ባልተሸፈነ ጊዜ የፌደራል ሕጎች ተፈፃሚነት ያላቸው በመሆኑና የክልል ፍርድ ቤቶች አደረጃጀትም እንደ ፌደራል ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው እስከሆነ ድረስ የፌደራል አዋጁ ተፈፃሚ ሊሆን ይገባዋል ከሚል እሳቤ ነው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 27 እስከ 29 ያሉ ድንጋጌዎች አንድ ዳኛ ከችሎት ሊነሳ የሚቸልባቸውን ምክንያቶች፣ ከችሎት የሚነሳበትን ሥነ ሥርዓት እና በባለጉዳዮች ያቀረቡት ምክንያቶች ከችሎት የማያስነሱ ሆነው በተገኙ ወቅት አቤቱታውን ባቀረበው ወገን ላይ ስለሚጣለው ኪሳራና ቅጣት የሚናገሩ ናቸው፡፡ በዚህ አዋጅ አንድ ዳኛ ከችሎት የሚያስነሱ ምክንያቶች መኖራቸውን አውቆ በገዛ ፍቃዱ ከችሎት ባልተነሳበት ወቅት ይመለከተኛል የሚለው ወገን አቤቱታውን ጉዳዩን ለያዘው ዳኛ ያቀርባል፡፡ አቤቱታው የቀረበለት ዳኛ ምክንያቱ ካሳመነው ከችሎት የሚነሳ ሲሆን ምክንያቱ በቂ ሆኖ ካላገኘውና ካልተቀበለው በዚያው ፍርድ ቤት በሚገኝ ሌላ ችሎት የምክንያቱ በቂነት እንዲወሰን ያስተላልፋል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት ችሎትም የምክንያቱን በቂነት በመመርመር ዳኛው ሊቀጥል ወይም ሊነሳ የሚገባ መሆኑን በመወሰን በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ስለመሆኑ አዋጁ ይናገራል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ተፈፃሚ የነበረው የፌደራል ፍርድ ቤቶች አሰራር ነበረ ቢሆንም በ2007 ዓ.ም በአብክመ ምክር ቤት ፀድቆ በሥራ ላይ የዋለው የተሻሻለው የፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 223/2007 ግልፅ የሆነ ድንጋጌ ይዞ ወጥቷል፡፡ ተሻሽሎ በቀረበው አዋጅ አንጽ መሠረት የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ በተቀመጠው መሠረት የዳኝነት ይነሳልኝ ጥያቄው የሚስተናገደው ጉዳዩ ለሚመለከተው ዳኛ ቅሬታውን በማቅረብ ዳኛው ሲያምንበት ከችሎት በመነሳት ምክንያቱ ካላሳመነው በተመሳሳይ ደረጃ ለሚገኘው ሌላ ችሎት በመላክ ማስወሰን ነው፡፡ የቀረበው ምክንያት በሌላ ችሎትም ተቀባይነት ካጣ በነበረው ችሎት ጉዳዩ የሚቀጥል ሲሆን የሚሰጠውም ውሳኔ የመጨረሻ ነው፡፡ የዳኝነት ይነሳልኝ ምክንያት የቀረበለት ዳኛ ምክንያቱ ካላሳመነው ጉዳዩ የሚመረመረው በተመሳሳይ ባለ ችሎት እንጅ በይግባኝ ሰሚ ደረጃ አይደለም፡፡
ለምን በተመሳሳይ ደረጃ በሚገኝ ችሎት?
በፍርድ ሥራ በስር ፍርድ ቤት እና በይግባኝ ሰሚ ችሎት መካከል ልዩነቱ መሠረት ያደረገው የሥረ ነገር ክብደትን እና የባለሙያዎችን አቅም ነው፡፡ በይግባኝ ሰሚ ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች በስር ፍርድ ቤት ካሉት የተሻለ አቅም እና ልምድ ይኖራቸዋል ተብሎ ሰለሚታሰብ በስር ፍርድ ቤት ደረጃ የሚሰጡ ውሳኔዎችን ባላቸው የተሻለ አቅም እና ልምድ በሚገባ ሊያርሙት ይገባል በሚል መነሻ የተዘረጋ አሰራር ነው፡፡
ዳኝነት ከችሎት ይነሳልኝ የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ምክንያቱ አላሳመነኝም የሚል ዳኛ የሰጠው ውሳኔ በተመሳሳይ ደረጃ በሚገኝ ሌላ ችሎት ከይግባኝ ስርዓት አቀራረብ በተለዬ መልኩ ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ያገኛል፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ ሰሚ ደረጃ አለመታየቱ ለምን በተመሳሳይ ደረጃ በሚገኝ ችሎት ይታያል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህንን ጉዳይ ለመመለስ በቅድሚያ የዳኝነት ይነሳልኝ የሚሉ ጥያቄዎች የሚቀርቡበትን መነሻ ሀሳብ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ በሕጉ በዝርዝር የተቀመጡት ምክንያቶች ይዘታቸው ሲታይ ከባለጉዳይ አያያዝ፣ የገለልተኝነት ስሜት፣ ከዳኛ ጋር የነበረ የጥቅም ግጭት ጋር በቀጥተኛነት የተያያዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች በተገልጋዩ አካል በሚሰጠው ፍትሕ ላይ ታማኝነት እንዳይኖረው የሚያደርግ ስሜት በሚፈጠሩበት ወቅት ጥያቄው ይቀርባል፡፡ አንድ ችግር በተፈጠረበት አእምሮ መፍትሔው ሊገኝ አይችልም እንዲሉ ልሂቃን የአሻጥረኝነቱን ሆነ የአድሎአዊነቱን ችግር በፈጠረው አካል ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በሌላ ገለልተኛ አካል ምክንያቱ ቢመረመር የተሻለ ይሆናል በሚል እሳቤ ነው፡፡ ነገሩ ዳኛ ቢያዳላ በዳኛ፤ አህያ ሲያጋድል በመጫኛ እንደማለት ነው፡፡የችግሮቹን አሳማኝነት ለመገንዘብ በምክኒያታዊ ሰው እይታ መመለከት እንጅ ሌላ የተለየ አቅምን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ዳኛ ከችሎት እንዲነሳበት የቀረበው ምክንያት በቅሬታ አቤቱታ አቅራቢው እምነት ላይ እውነት ተፅዕኖ የሚያመጣ መሆኑን በባለጉዳዩ ቦታ ሆኖ በመመልከት ውጤቱን መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ በምክንያታዊ ሰው እይታ የሚመመዘን ስለሆነ ጉዳዩን ወደ ይግባኝ ሳይመራ በተመሳሳይ ችሎት እንዲታይ ሕጉ ያስቀመጣል፡፡
እንደ መውጫ!
ከሕጉ በተጨማሪ ህዝብ ዳኝነት ላይ የራሱ የሆነ መተክሎች/መርሆዎችን (principle) አሉት፡፡ የሰው አገሩ ምግባሩ የሚለው ብሂል መሠረቱ ምግባር ከምድሩና ከሸንተረሩ በላይ መመኪያ እና መታመኛ በመሆኑ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ምግባርን አይቶ የሚጥል እና የሚያነሳ እንደመሆኑ በዳኝነት ሥራ ላይ ያሉትን መተክሎች የሚያነቃንቅበትን ሰው ይጠየፋል፡፡ እንደ ተከበሩ ለመኖር ህዝባዊ ግዴታን ከማክበር በዘለለ የአንድን ህዝብ የታሪክ ዳራ በማጥናት ህዝብ በዳኝነት ላይ የጣለውን እሳቤ ማክበር ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ካለበለዚያ…
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments