Font size: +
11 minutes reading time (2151 words)

የማይደፈረውን ፍርድ ቤት መድፈር

በአንጌሳ ኢቲቻ የተጻፈውን ‹‹ችሎት መድፈር፡- ሕጉና የአሠራር ግድፈቶች›› የሚለውን ሳነብ እ.አ.አ በታኅሣስ 2013 በተመሳሳይ ርዕስ የጻፍኩትን ለአንባብያን ለማካፈል ወደድኩ፡፡ በዚህ ጽሑፌ ፍርድ ቤት መድፈር ምን ማለት ነው? የኢትዮጵያ ሕግ ስለ ፍርድ ቤት መድፈር ምን ይላል? የሕጉ ዓለማስ ምንድነው፣ የወንጀሉ አወሳሰን ልዩ ባህርይስ እንዴት ይታያል፣ በአፈጻጸም የሚታዩ ችግሮች ምንድናቸው የመሚለውን እዳስሳለሁ፡፡

በወቅቱ የሪፖርተር ጋዜጣ ይዞት የወጣው ከፍርድ ቤት ጋር የተያያዙ ሁለት ዜናዎች አንባቢውን በተለይም የሕግ ባለሙያዎችን የሚያስገርም ነበር፡፡ የመጀመሪያው ዜና አንድ የፖሊስ አባል የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኛን በማመናጨቅና ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው መታሠራቸውና ሌሎቹ ፖሊሶች ጉዳይ በቀጠሮ ላይ መሆኑ ነው፡፡ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐብሔር የቤተሰብ ችሎት ውስጥ የተፈጸመው ይህ ወንጀል ለየት የሚያደርገው ሕግን ለማስከበር አስፈጻሚውን በሚወክለው በፖሊስ መፈጸሙ ብቻ አይደለም፡፡ ፖሊሶቹ ያሳዩት ባህርይና ኃላፊዎቹ የሰጡት መልስ የበለጠ አስገራሚ ነበር፡፡ ፖሊሶቹ በጊዜው የዳኝነት ሥራ ስታከናውን የነበረችይቱን ዳኛ ‹‹አንመጣም››፣ ‹‹አንቀርብም››፣ ‹‹ስቀርብ ትፈትሽኛለሽ››፣ ‹‹ነገርኩሽ እኮ›› ወዘተ. በማለት ፍርድ ቤቱን ዝቅ የሚያደርግ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን መተማመን የሚያሳጣና ሌሎች ዳኞችን የሚያሳቅቅ ነው፡፡ የፍርድ ቤት መድፈር በአብዛኛው በተከራካሪ ወገኖች፣ በቤተ ዘመዶቻቸው፣ በጋዜጠኞች ወዘተ. ተፈጸመ ተብሎ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ችሎቱን ለማስከበር በተሰማሩት የፖሊስ አባላት መፈጸሙ ግን የበለጠ ግርምት ይፈጥራል፡፡ በጊዜው የፖሊስ ኃላፊው ‹‹ልጆቹ ጥፋት ያጠፉት ልጆች ስለሆኑ ነውና ይቅርታ ይደረግላቸው›› የሚለው ደግሞ፣ የፖሊስ ተቋሙ በፍትሕ አደባባይ፣ የሚበሳጭና የሚናደድ ተከራካሪ በሚኖርበት፣ ኅብረተሰቡ በብዛት አንዱን ነቅፎ ለሌላው ወግኖ በሚቆምበት ቦታ የሚመድባቸውን ፖሊሶች የትምህርትና የልምድ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ ነው፡፡ ሁለተኛው ዜና የከፍተኛው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በአዲስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት የመጣሱ ዜና ነው፡፡ በፍርድ ቤት በተያዘ አንድ ጉዳይ ፍርድ ቤቱ እንዳይፈርስ የእግድ ትዕዛዝ የሰጠበትን የንግድ ቤት የእግድ ትዕዛዙ ደርሶት ክፍለ ከተማው ቤቱን የማፍረሱ ዜና እጅጉን አስደንጋጭ ነው፡፡

እነዚህ ሁለት ዜናዎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የተጋረጡትን ፈተናዎች አመላካች ናቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አንዱ እንደመሆናቸው ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃና ኃላፊነት ተሰጥቷአቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን አስፈጻሚውን ለመቆጣጠር ባልቻሉ መጠን ህልውናቸው ላይ አደጋ ይፈጥራል፡፡ በሁለቱ ዜናዎች ፍርድ ቤቱ የተደፈረው በአስፈጻሚው አካል እንደመሆኑ መጠን የፍትሕ ተቋሙ ተመሳሳይ ጥሰቶች እንዳይኖሩ ተግቶ ሊሥራ እንደሚገባው አመላካች ነው፡፡ በአስፈጻሚው አካል ክብር ያልተሰጠው ፍርድ ቤት በተራ ዜጋው ክብር ይሰጠዋል ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ተመሳሳይ ድርጊቶች በፍርድ ቤቶች ወይም በዳኞች ላይ የሚፈጸሙ ከሆነ ፍርድ ቤቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ክብርና መተማመን ማጣታቸው አይቀርም፡፡ የራሱን መብት የማያስከብር ፍርድ ቤት የሌላውን ዜጋ መብት እንዲያስከብር መጠበቅ ሞኝነት መሆኑ ነጋሪ አይፈልግም፡፡

ከላይ በመጀመሪያው ዜና ለመረዳት እንደሚቻለው ፍርድ ቤቱ ክብሩን ከሚያስጠብቅበት ዘዴ አንዱ ሕጉ ከፍርድ ቤት መድፈር ወንጀል ጋር በተያያዘ ለፍርድ ቤቱ የተሰጠው ሥልጣን ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን ፍርድ ቤትን የመድፈር ወንጀል ምንነት፣ ባህርያትና አፈጻጸሙን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ አገራችንን ጨምሮ በብዙ የሕግ ሥርዓት ፍርድ ቤትን መድፈር በአብዛኛው ከመናገርና ሀሳብን ከመግለጽ መሠረታዊ መብት ጋር በንጽጽር ይታያል፡፡ በፍርድ ቤት በሚታዩ ጉዳዮች ላይ በተለይ ጋዜጠኞች በሚጽፏቸው ጽሑፎች፣ በሚሠሯቸው ዜናዎች ወይም በሚያቀርቧቸው ትችቶች ፍርድ ቤትን ደፍረዋል በሚል ክስ ሲቀርብባቸው ይስተዋላል፡፡ ይህ ሥርዓት በአንድ በኩል የፍርድ ቤትን ክብር ማስጠበቅ የሚጠይቅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ወይም ሀሳብን የመግለጽ መሠረታዊ መብትን እንዳይጥስ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ በተግባር ሁለቱን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መጠበቅ ከባድ በመሆኑ ብዙ አከራካሪ ጭብጦች ይነሱበታል፡፡ በዚህ ጽሑፍ እነዚህ ከመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ጋር የተያይዙትን ነጥቦች አንዳስስም፡፡ የተነሳንበት አውድም አይፈቅድልንም፡፡ ስለዚህ ትኩረታችን ሕጉ ስለ ፍርድ ቤት መድፈር የሚለው ነገር በደምሳሳው ማየት ይሆናል፡፡

 ፍርድ ቤት መድፈር ምን ማለት ነው?

የቃሉ ትርጉም እንደሚያመላክተው ‹‹ፍርድ ቤት መድፈር›› በሕገ ወጥነት ወይም ባለመታዘዝ የፍርድ ቤትን ክብር፣ ሞገስ ወይም ሥልጣን የመተላለፍ፣ የመጣስ፣ ያለማክበር ድርጊትን የማያሳይ ነው፡፡ በሕግ ባለሙያዎች መዝገበ ቃላት (Blacks law dictionary) ፍርድ ቤት መድፈር የሚከተለው ፍቺ ተሰጥቶታል፡፡

“Any act which is calculated to embarrass, hinder, or obstruct the court in the administration of justice, or which is calculated to lessen its authority or dignity. Committed by a reason who does any act in willful contravention of its authority or dignity or tending to impede or frustrate the administration of justice, or by on who, being under the court’s authority as a party to a proceeding therein, willfully disobeys its lawful orders or fails to comply with an undertaking which he has given”

በዚህ ረዘም ያለ ትርጉም መሠረት ፍርድ ቤት መድፈር ማለት የፍርድ ቤትን ሥልጣንና ክብር ዝቅ ለማድረግ ወይም የፍትሕ አስተዳደሩን ለማደናቀፍ፣ ለማወክ ወይም ክብሩን ለማዋረድ ታስቦ የሚፈጸም ድርጊት ነው፡፡

ፍርድ ቤት መድፈር ሁለት ዓይነት ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱ በፍርድ ቤቱ የተሰጠ ትዕዛዝን ባለማክበር የሚመጣ ፍትሐብሔራዊ ይዘት ያለው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ፍርድ ቤቱ የመጥሪያ፣ የእግድ፣ የምስክርነት ወዘተ. ትዕዛዝ እንዲያከብር የላከለት ሰው ወይም በፍርድ ቤት ቀርቦ ሊፈጽመው የሚገባው ፍትሐ ብሔራዊ ግዴታን ያልተወጣ ሰው ችሎቱን በመድፈሩ የሚጠየቅበት ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት መድፈር የሚጠየቅ ሰው በአብዛኛው በተከራካሪ ወገን ጠያቂነት በፍርድ ቤት የሚታይ ሲሆን ዋና ዓላማውም ግለሰቡን መቅጣት ሳይሆን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዲፈጽም ማስቻል ነው፡፡ በውጭ አገሮች የሕግ ሥርዓት በቤተሰብ ሕግ ቀለብ መቁረጥ ያለበት ወላጅ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ግልጽ ትዕዛዝ ካላከበረ በዚህ ፍትሐ ብሔራዊ ችሎት መድፈር (Civil contempt) ይጠየቃል፡፡

ሁለተኛው ፍርድ ቤትን የመድፈር የወንጀል ተግባር (Criminal Contempt) የሚባለው ሲሆን የፍርድ ቤቱ ክብርና ሥልጣን በግለሰቡ ድርጊት ሲጣስ የፍርድ ቤቱን ክብር ለማስመለስ በፍርድ ቤቱ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ ፍርድ ቤትን የመድፈር ወንጀልን መቅጣት ለፍርድ ቤቱ ክብር ለመጠበቅ ግለሰቡን ለመቅጣት ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በተግባር የሁለቱን (Civil and criminal contempt) መለየት አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢኖርም በቅጣቱ ዓላማና ቅለትና ክብደት መለየት ይቻላል፡፡ ከላይ በመግቢያችን የተመለከትነው የፖሊሶቹ ጉዳይ ከወንጀል (Criminal Contempt) እንደሚወድቅ መረዳት ይቻላል፡፡

ከወንጀሉ አፈጻጸም አንፃርም ፍርድ ቤትን መድፈር ቀጥታ (direct) ወይም ቀጥታ ያልሆነ(indirect) ሊሆን ይችላል፡፡ ቀጥታ የሚባለው ፍርድ ቤቱ ወይም ዳኛው ችሎት እያስቻለ፣ ዳኛው ባለበትና እየሰማው የሚፈጸም ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ወንጀል በአብዛኛው ለተከሳሹ መጥሪያ ሳይደርሰው ወዲያውኑ (Summarily) የሚፈጸም ሲሆን ዳኛው ከሳሽ፣ ምስክር እና ዳኛ በመሆን ጥፋተኝነቱንና ቅጣቱን ይወስናል፡፡ ቀጥተኛ ያልሆነው ግን የመድፈር ድርጊቱ የሚፈጸመው ዳኛው በማይመለከተውና በማይሰማው ሁኔታ ነው፡፡ በልደታ ምድብ ችሎት ዳኛዋ እየሰማችው ፖሊሶቹ ‘አንመጣም’፣ ‘አንቀርብም’ ወዘተ. እያሉ የፈጸሙት ድርጊት ቀጥተኛ በሚባለው ምድብ የሚወድቅ ሲሆን ጉዳዩም የታየው ወዲያውኑ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በፍርድ ቤት የተከናወኑን የችሎት ሒደት ተገቢ ባልሆነ መንገድ የዘገበ፣ የተቸ ወይም ተገቢ ያልሆነ መደምደሚያ በጋዜጣው ለሕዝብ ያቀረበ ጋዜጠኛ ደግሞ ችሎትን በመድፈር ወንጀል ከተጠየቀ ድርጊቱ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተፈጸመ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ዳኛው እያየው ወይም እየሰማው የተፈጸመ ባለመሆኑ ተከሳሹ መጥሪያ ደርሶት ሊቀጣ ይችላል፡፡

 የኢትዮጵያ ሕግ ምን ይላል?

ፍርድ ቤት መድፈርን የተመለከተው የኢትዮጵያ ሕግ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉና በወንጀል ሕጉ ላይ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ዘጠነኛ መጽሐፍ ከአንቀጽ 480-482 ፍርድ ቤትን ለማስከበር ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸውን ሥልጣን በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የማንኛውም ፍርድ ቤት ችሎት ዳኛ ፍርድ ቤቱንና የዳኝነት ሥራ አካሄድ ሥነ ሥርዓትን ለማስከበር ማናቸውንም አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ እንዲወስድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህንን ለማስፈጸም ለፍርድ ቤቱ ችሎት ክብር ወይም ለዳኝነቱ ሥነ ሥርዓት መልካም አመራር ተቃራኒ የሆነ ጠባይ የሚያሳየውን ማንኛውንም ተከራካሪ ወገን ወይም ጠበቃ ወይም በችሎት ውስጥ የሚገኘውን ማንኛውንም ሰው ተቃራኒ ተግባር በሚሠራበት ጊዜ በያዘው መዝገብ ላይ የገንዘብ መቀጮ ሊወስንበት ይችላል፡፡

የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 481 እና የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 449 ለፍርድ ቤት መድፈር ዝርዝር ትርጉም የሚሰጡ ሲሆን የአፈጻጸሙ ሥርዓትና ቅጣቶቹንም ደንግገዋል፡፡ ፍርድ ቤት መድፈር በወንጀል ሕጉ በተሰጠው ትርጉም መሠረት ‹‹በፍርድ ቤት ምርመራ በሚደረግበት ወይም በፍርድ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ ፍርድ ቤቱን ወይም ዳኛውን መሳደብ፣ ማወክ፣ ማፌዝ፣ መዛት ወይም የፍርድ ቤቱን ሥራ በማንኛውም ሌላ መንገድ ማወክ›› የፍርድ ቤት መድፈር የሚባል ሲሆን ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሦስት ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ፍርድ ቤት መድፈር ከችሎት ውጭም ሲፈጸም የሚያስቀጣ መሆኑ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 449(2) ተደንግጓል፡፡ ፍርድ ቤቶች አከራካሪ የሆነ ቦታን ለመመልከት በአካል ከፍርድ ቤት ውጭ ሥራቸውን ሲያከናውኑ፣ በተዘዋዋሪ ችሎት ወይም ከያዙት መዝገብ ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤቱ ውጭ የተፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ የፍርድ ቤቱን ሥራ የሚያውኩ ከሆነ በፍርድ ቤት መድፈር ሊያስጠይቁ ይችላሉ፡፡

የሕጉ ዓላማ

ፍርድ ቤትን መድፈር በሕግ እንዲያስቀጣ የሆነበት የራሱ ዓላማ አለው፡፡ በአብዛኛው ፍርድ ቤት መድፈር ዳኞች ለራሳቸው የግል ጥቅም ሲሉ ግለሰቦችን የሚቀጡ እንደሆነ ማሰብ በኅብረተሰቡ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም ዳኛው በግለሰብ ማንነቱ ላይ ብቻ የተቃጣን ድርጊት እንደማንኛውም ሰው ክስ አቅርባ ሊጠይቀው የሚገባ እንጂ ከዳኛው ጋር የተያያዘ ተግባር ሁሉ ፍርድ ቤትን መድፈር ላይሆን ይችላል፡፡ ፍርድ ቤትን መድፈር በሕግ የተካተተበት ዓላማ የፍርድ ቤቱን ክብር ለመጠበቅ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ሕልውና ለመጠበቅ እንዲሁም ኅብረተሰቡ በዳኝነት አካሉ (በፍርድ ቤት) ላይ ያለውን መተማመን ለመጠበቅ ታስቦ ነው፡፡ የዳኝነት አካሉ ከሕግ አውጪውና ከሕግ አስፈጻሚው ጋር በፖለቲካ፣ በሕዝብ ገንዘብ አስተዳደርና በወታደራዊ አመራር እንደማይወዳደር ግልጽ ነው፡፡ ለፍርድ ቤት ህልውና መሠረት በሕዝብ መታመን ሲሆን ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ሕዝቡ እገዛ ያደርግለታል፡፡ በዚህ መነሻነት ፍርድ ቤቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን መተማመን የሚቀንስ ተግባር በሙሉ በሕግ ሊቀጣ ይገባል፡፡ ፍርድ ቤትን የመድፈር ድርጊቶች በዚህ ሥር የሚወድቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤትን መድፈር ዳኛውን በግለሰብ ማንነቱ ለመጠበቅ ታስቦ ሳይሆን የዳኝነት ተቋሙን ክብር ለመስጠት ታስቦ ነው፡፡ የቅጣቱ ዓላማም ተመሳሳይ ነው፡፡ የፍርድ ቤቱን ክብር ያዋረደው ግለሰብ እንዲቀጣ፣ ሌሎች ከተቀጣው ሰው ድርጊት ተምረው ለፍርድ ቤቶች ክብር እንዲሰጡ ማድረግና የፍርድ ቤቱን የሕዝብ ታማኝነት ማስቀጠል ነው፡፡

የወንጀሉ አወሳሰን ልዩ ባህርይ

በብዙ አገሮች የፍርድ ቤት መድፈር የሚታይበት ሁኔታ፣ መድፈር የሚባሉ ድርጊቶች፣ አወሳሰኑ የሚመራበት ሥርዓት በዝርዝር ተደንግጐ እናስተውላለን፡፡ በእኛም አገር የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ የተወሰኑ ሥርዓቶችን ከማስቀመጥ በተጨማሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ተጨማሪ ዝርዝር ደንቦችን ሊያወጣ እንደሚችል በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 482 ላይ ተመላክቷል፡፡ ይህ ደንብ ባለመውጣቱ የአገራችን ፍርድ ቤት መድፈር ወንጀል አካሄድ ግልጽነት የሚጐድለውና ተመሳሳይ አፈጻጸም እንዳይኖረው ሆኗል፡፡

በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 480 እንደተመለከተው ፍርድ ቤቱ የፍርድ ቤት መደፈር ወንጀልን ለመመልከት የተለየ የወንጀል መዝገብ መክፈት አያስፈልገውም፡፡ ዳኛው በያዘው መዝገብ ላይ ጥፋተኛነቱንና ቅጣቱን መዝግቦ መፍረድ ይቻላል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ግልጽ ይመስላል፡፡ ጉዳዩን የያዘው ዳኛ ለድርጊቱ ቅርብ በመሆኑ፣ የማወክ ተግባሩም በተያዘው መዝገብ ላይ በመፈጸሙ ሌላ መዝገብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የሚታይበት ሥርዓት ወዲያወኑ (summarily) እንደሆነ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 481ም ሆነ የወንጀል ሕጉ 449 በግልጽ ይደነግጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥርዓት የተከሳሹ የመስማት መብት ተገድቦ፣ ሙሉ የክስ ሒደት ሳይቀጥል በፍጥነት ኃላፊነትና ቅጣት የሚወሰንበት ነው፡፡ በፍርድ ቤት መድፈር ወንጀል ጊዜ ከሳሽ፣ ምስክርና ዳኛው በችሎቱ የተሰየመው ራሱ ዳኛው ይሆናል፡፡ ይህ ሥርዓት በሥነ ሥርዓት ሕጉ አምስተኛ መጽሐፍ ከተደነገጉት ውስጥ አንዱ በአጭር ሁኔታ የሚፈጸም ሥርዓት (summary procedure) ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ተከሳሹ መከላከያ ሊያቀርብባቸው አይችሉም ተብለው ግምት የሚወሰደባቸው (እንደ ቼክ ልኩ ተወስኖ የታወቀ ክስ) በአጭር ሥርዓት የሚታዩበት ሁኔታ አለ፡፡ የፍርድ ቤት መደፈር በዚሁ ምድብ የሚታይ ነው፡፡ ልዩነቱ በሌሎች ጉዳዮች ተከሳሹ በፍርድ ቤት ፈቃድ የመከላከል መብት ሊኖረው የሚችል ሲሆን በፍርድ ቤት መደፈር ግን ይህ መብት ለተከሳሹ መኖሩ አልተመለከተም፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ የሚታይ ከሆነ ብቻ የተከሳሹ የመከላከል መብት እንደሚጠበቅለት ማሰብ ይቻላል፡፡ በፍርድ ቤት መድፈር የሚፈጸም አጭር (ወዲያውኑ) የሚታይ ሥርዓትን መከተል ለችሎቱ ዳኛ የተተወ ምርጫ ይመስላል፡፡ ሕግጋቱ ‹‹ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሳያደርግ ወዲያውኑ በጥፋተኛው ላይ ቅጣት ሊወስን ይችላል፡፡›› ሲል መደንገጉ የችሎቱን ምርጫ ያመለክታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ድንጋጌ በቂ ዝርዝር መመሪያዎች ከሌሉት በዳኞች ያላግባብ ጥቅም ላይ ሊወሉ እንደሚችሉ ማሰብ ይቻላል፡፡ በሌሎች አገሮች የዳኛው ጉዳዩን ወዲያው የመመልከት ሥልጣን ገደቦች አሉበት፡፡ ዳኛውን ራሱ ባለበት ጉዳይ ከሳሽም ምስክርም ማድረግ ከተፈጥሮ ፍትሕ (natural justice) ጋር ከመቃረኑ በላይ ለዳኛው ግላዊ አተያይ (subjective perception) ተፅዕኖ ውስጥ እንዲወድቅ ስለሚያደርግ አንዳንድ የሕግ ሥርዓት ገደቦች ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የፍርድ ቤት መደፈር ወዲያውኑ እንዲታይ የሚደረገው ይህን ማድረግ የፍርድ ቤቱ ክብር ልዕልና ለማስከበር ፍጹም አስፈላጊ ሲሆንና የጥፋተኛው ድርጊትም ክብደት ሲኖረው ነው፡፡ በተጨማሪም የወንጀሉ መፈጸም ከበቂ ጥርጣሬ በላይ (beyond reasonable doubt) ሲረጋገጥ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ላለመፈጸሙ የተወሰነ ጥርጣሬ ካለው ጉዳዩ በመደበኛ ሥርዓት እንዲመራ ሊያደርገው ይገባል፡፡ በእኛ አገር ዳኞች ላይ እንዲህ ዓይነት ገደብ የለም፡፡ ይህ ገድብ አለመኖሩ በተለይ ጉዳዩ የመገናኛ ብዙኃንን የሚመለከት ሲሆን መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን (ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብትን) ሊጥስ ስለሚችል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው መረዳት ይገባል፡፡

በአፈጻጸም የሚታዩ ችግሮች

ፍርድ ቤትን የመድፈር ወንጀል በብዛት ከሚያጋጥሙ ክስተቶች መካከል መሆናቸውን ለመገንዘብ በየዕለቱ በፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች መዋል በቂ ነው፡፡ ከአፈጻጸሙ የሚመነጩት ችግሮች ከሦስት ወገን ሊታዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ የመጀመሪያውና በጣሙን የተለመደው የችግሩ ምንጭ የዳኞች ግላዊ አተያይ ነው፡፡ ዳኞች በጽንሰ ሀሳብ ላይ ያላቸው አመለካከት የተለያየና ወጥነት የሌለው መሆኑ አንዱ ፍርድ ቤት መድፈር ነው የሚለውን ሌላው አይደለም ሲል ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ ስሜታዊ የሆነ ዳኛ የሰውነት ንቅናቄን፣ አለባበስን፣ ተገቢ የሥነ ሥርዓት ተቃውሞን ሁሉ መድፈር ነው የሚል ደረጃ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የራሱን ስሜት እንጂ ሕጉ ፍርድ ቤቱን ወይም የፍትሕ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ያሰበውን ዓላማ ማስተዋል የሚሳነው አለ፡፡ አሁን አሁን እንጂ ባርኔጣ ማድረግ፣ እጅን ኪስ ውስጥ አስገብቶ ችሎት መከታተል፣ ከፍርድ ቤት ውጭ ከዳኛው ጋር የተደረገ የግል ንትርክ፣ እግርን አጣምሮ ችሎት መከታተል ወዘተ. ፍርድ ቤትን እንደ መድፈር የሚቆጠርበት እሳቤ እንደነበር ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡ ፍርድ ቤቶች የፍርድ ቤት መደፈር ወንጀሎች የሚቀጡበት አካሄድም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ አንዱ በግሳጼ ያለፈውን ሌላው በአንድ ወር የእስራት ቅጣት፤ አንዱ በ1000 ብር የገንዘብ ቅጣት ያለፈውን ሌላው በስድስት ወር እስራት ቅጣት የሚወስንበት አጋጣሚ አለ፡፡

ሁለተኛው የችግሩ ምንጭ ተገቢ ዝርዝር መመርያ (ማኑዋል) ያለመኖሩ ጉዳይ ነው፡፡ የመጀመርያውም ችግር ከሕጉ ዝርዝር አለመኖሩ ጋር ተያይዞ በሚመጣ የግንዛቤ ልዩነት የሚፈጠር ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር  ሥነ ሥርዓት ሕጉ ፍትሕ ሚኒስቴር የፍርድ ቤት መደፈር ወንጀል አተያይ ሥርዓትን በደንብ የመወሰን ሥልጣን ቢሰጠውም የወጣ መመሪያ የለም፡፡ በአሁኑ አወቃቀር ይህ ሥልጣን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲሆን ፍርድ ቤቱ መመሪያ በማውጣት የወንጀሉን ዓይነት በየፈርጁ፣ በአጭር ሥርዓተ መታየት የለበትንና የሌለበትን ምን ምን ተግባራት ፍርድ ቤት መድፈር እንደሆኑ የወንጀል ሕጉን መነሻ በማድረግ ካልደነገገ የዳኞች የሥልጣኑን ገደብ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ ያለው ጉዳይ በተለይ በመመሪያው አለመኖር የመረጃ ነፃነትን አደጋ ላይ እንዳይጥል ሥጋት አለ፡፡ የዚህን ችግር ስፋት በሌላ ጽሑፍ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

ሦስተኛው የአፈጻጸም ችግር ከግንዛቤ እጥረት የሚመጣ ነው፡፡ ደኞች በአንድ በኩል ሌሎች አካላት (ተከራካሪዎች፣ ጠበቆች፣ ዓቃቢያነ ሕግ፣ ፖሊሶች ወዘተ.) ፍርድ ቤትን መድፈር ምን እንደሆነ፣ ዓላማው፣ የሚፈቀደውና የማይፈቀደውን ለይቶ ሥልጠና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ዳኛውን ከመብቱ በላይ ሕጉን በመተርጎም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እንዳይጥስ፣ ሌላው ዜጋም መብቱን ባለማወቅ ሲሳቀቅ እንዳይኖር ይጠቅማል፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞ ፌዴራል ዳኛ ኅብረተሰቡ በፍርድ ቤት ችሎት ሲቆም ስሙን ሲጠየቅ የሚጠፋው፣ እጆቹን የሚያስቀምጥበትን ቦታ እንኳን የሚያጣ፣ በላብ የሚጠመቅ ባለጉዳይ እንዳጋጠማቸው ተሞክሮአቸውን ሲገልጹ ፀሐፊው ያስታውሳል፡፡ ይህ የሚመጣው ከግንዛቤ ማነስ ነው፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ባለድርሻ አካላት ስለ ዳኝነት አካሉ ሥልጣንና ኃላፊነት በሚገበ በቂ ግንዛቤ ካላገኙ ሕዝባዊ ፍትሕ መስጠት ለፍርድ ቤቶቻችን አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን የፖሊሶቹና የክፍለ ከተማው ጉዳይ ከመረመርን የችግሩ ምንጭ ሕግን ካለማወቅ ወይም አውቆ ካለመተግበር መሆኑን መገመት አያስቸግርም፡፡ ፖሊስ ሕግ አያውቅም ካልን ሌላ ዜጋውማ ሊያውቅ እንደሚችል ማሰብም ያስቸግራል፡፡ ፍርድ ቤት አዘውትሮ መዋል የፍርድ ቤቶቹን ክብር የሚያሳጣ ሊሆን አይገባውም፡፡ ከተፈጠረው ጉዳይ ተነስተን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ኃላፊነት ካሰብን ሰፊ መሆኑ አይቀርም፡፡ ፖሊሶች ሕግን አውቀው የሚያከብሩ፣ የሚያስከብሩ፤ ለሕዝብና ለሕዝብ ተቋማት ከበሬታ ያላቸው፣ መብታቸውንና ግዴታቸውን አውቀው እንዲፈጽሙ የማድረግ የተቋሙ ግዴታ ትኩረት የሚፈልግ ነው፡፡  

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በኢትዮጵያ ሕግ የግል የኮንስትራክሽን ውሎች ምንነት፣ የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮ...
ችሎት መድፈር፡- ሕጉ እና የአሠራር ግድፈቶች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 23 November 2024