Font size: +
17 minutes reading time (3372 words)

አዲሱ የፀረ ሙስና ሕግ በግል ኩባንያወች ላይ ተፈፃሚነቱና የሕግ አንድምታው

“Nothing will unlock Africa’s economic potential more than ending the ‘Cancer of Corruption”

Barack H. Obama, US President key note to African Union July 28 2015

 መግቢያ

ሙስና የአለማችን ብሎም የሀገራችን ስጋት እና የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሀገራትም የሙስና ትግሉን ከግብ ለማድረስ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት እንቅስቃሴውን ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

በተለያዩ የፍልስፍና፤ ኃይማኖታዊና ግብረ-ግባዊ (ሞራላዊ) አስተምህሮች እንደተመለከተው ሙስና ማለት የመንግሥትን ሥልጣን ወይም ሀላፊነት ለግል ጥቅም ማዋል እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡

ሙስና ከየት መጣ እንዴት አደገ የሚሉ ጉዳዮችንና ታሪካዊ ዳራውን እንደሚከተለው በወፍ በረር አስቃኛለሁ፡፡ ሙስና በአለማችን መታወቅ የጀመረው የመንግሥት መዋቅር በጥንታዊት ግሪክ ከጀመረበት ጊዜ እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ፡፡ ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ አርስጣጣሊስ (Aristotle) በወቅቱ የነበረውን ብልሹ መንግሥታዊ አሠራርና ንቅዘት በመቃወም ጉዳዩን “ሙስና/Corruption” በማለት እንደሰየመው እነዚሁ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ሲሲሮ (Cicero) የተባለው ፈላስፋ በበኩሉ ሙስና የሚባለው በመንግሥት ሥልጣን ወይም ኃላፊነት የሚደረግ ብልሹ አሠራር ብቻ ሳይሆን ጉቦ መስጠትና መቀበል እንዲሁም መጥፎ ምግባርን ልማድ ማድረግንም እንደሚጨምር ጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያም ሙስና ስር ሰዶ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆንም የፀረ ሙስና ትግሉ ግን በቅርብ እንደተጀመረ መገንዘብ ይቻላል፤ በተለይም በ1987ዓ.ም የተቀረፀው የሲቪል ሰርቪስ ፕሮግራም እንደሚያመለክተው የሲቪል ሰርቪሱ ዋነኛ ተግዳሮት ሙስናና ብልሹ አሠራር እንደሁነ በወቅቱ የተካሄደው ጥናት ጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራሙ እንደሚጠቁመው ሙስና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ጥቂቶችን ተጠቃሚ ሰፊውን ሕዝብ ደግሞ ለጉስቁልና የሚዳርግ፣ በመንግሥት የሚሰበሰብ ቀረጥና ግብር እንዲቀንስ በማድረግ የልማት ሥራዎችን የሚያደናቅፍ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን የሚገታ እና የመንግሥት አስተዳደር ተደራሽነትንና ጥራትን በመቀነስ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለው ተአማኒነት እንዲቀንስ የሚያደርግ ወንጀል መሆኑን በማስቀመጥ ወደመፍትሔ ፍለጋ ሄዷል፡፡

በመሆኑም ተመራጭ ከሆኑ መፍትሔዎች መካከል ራሱን የቻለ ማዕከላዊ አካል ማቋቋም አንዱ መሆኑ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ ይህ ማዕከላዊ አካል የሥነ ምግባር ትምህርት የማስፋፋት፣ ሙስናን የመከላከል፣ ከሕብረተሰቡ በሚደርሱ ጥቆማዎችና በራስ ተነሳሽነት የሙስና ወንጀሎችን የመመርመር እና አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ሥልጣንና ኃላፊነቶች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡

ይህንንም ወደ ተግባር ለመቀይር በማሰብ የፌዴራል የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሚል መጠሪያ በአዋጅ ቁጥር 235/1993 በይፋ ተቋቁሟል፡፡ የማቋቋሚያ አዋጁን ከኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ጋር እንዲጣጣም በማስፈለጉ በአዋጅ ቁጥር 433/1997 ተሻሽሏል፡፡ በያዝነው ዓመትም የግሉ ዘርፍና ሕዝባዊ ድርጅቶች የሚፈፅሟቸውን የሙስና ወንጀሎች ማካተት በማስፈለጉ በማሻሻያ አዋጅ ቁ. 883/2007 እንደገና ተሻሽሏል፡፡

በሀገራችን የፀረ ሙስና እንቅሰቃሴን ከግብ ለማድረስ በማሰብ በርከት ያሉ ሕጎችና አዋጆች እንዲሁም ደንቦች ወጥተዋል ከነዚህም መካከል፡-ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁ. 239/1993፤ የተሻሻለው ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ 434/1997 ብሎም አዲሱ ማሻሻያ አዋጅ ቁ. 882/2007፤ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ቁ. 414/1997፤ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች አሠራር ደንብ ቁ. 144/2000፤ የኃብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ 668/2002፤ የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ 699/2003፣ ኢትዮጵያ የፈረመችው የአፍሪካ ሕብረት የሙስና መከላከያና መዋጊያ ኮንቬንሽንና የተባሩት መንግስታት ድርጅት የፀረ ሙስና ስምምነት እንዲሁም አዲሱ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁ. 881/2007 ናቸው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሁሉንም የኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ሕጎችን መዳሰስ ባይሆንም ለአንባቢው ጠቆም አድርጎ ለማለፍ ነው፡፡ ጸሐፊው በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው አዲስ በወጣው የሙስና ወንጀሎች አዋጅ.በቁ. 881/2007 ላይ ሲሆን አዋጁም የግል ድርጅቶች በሚፈፅሟቸው የሙስና ወንጀሎች መፈፀሙ የሕግ አንድምታው ምን እንደሆነ እና ከአዋጅ ቁ 882/2007 አንጻር የሙስና ዋስትና ጉደይ (bail) መመልከት ነው፡፡ ጽሑፋም ሙሉ ነው ባይባልም አንዳንድ ነገሮችን ጠቆም ያደርጋል፤ ጸሐፊውን ሁሌም የሚያሳስበው ነገር ሕግና አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም የሚለው መርህ ነው፡፡ (የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 81) ማንም ሰው ሕግን ቢያወቅ ኖሮ ወንጀል አይፈፅምም ነበር ስለዚህ ሙስና ላይ የወጡ አዲስ ሕጎችንም ማወቅ ተገቢ ነው፡፡

የሙስና መገለጫው: ኪራይ ሰብሳቢነት (rent-seeking)

ስለ ሙስና ትርጓሜ የተለያዩ ተቋማት ና አካላት የተያዩ ገለፃ ሰጥተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አለማቀፋ የሙስና ጠቋሚ ተቋም (Transparency international) እንደሚለው ከሆነ፡-ሙስና ማለት በአደራ የተሠጠን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል /corruption is abuse of entrusted power for private gain/ ተቋሙ ይጠቁማል፡፡

ለታዳጊ ሀገራት ደህነት ቅነሳ ፕሮግራም ብድር በመስጠት የሚታወቀው የአለም ባንክ /world bank/ በበኩሉ ስለሙስና የሚከተለውን ነጥብ አስቀምጧል፡፡ ሙስና ማለት የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል /corruption is abuse public power for private benefits/ ነው ይላል፡፡

ከላይ የተቀመጡት ሁለቱ ትጓሜዎች ከትችት አለመለጡም ለምን ቢባል አንድም ሙስናን የገለፁበት መንገድ በሥልጣን ያለግባብ መጠቀም /abuse of power/ አንፃር ብቻ ነው፡፡ ይህም የተለያዩ የሙስና ዓይነቶች እንደ ጉቦ፤ ማጭበርበር፤ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት መያዝ ወዘተ… ያላካተተ በመሆኑ፤ በሌላ በኩል ሙስና የሚፈፀመው ለግል ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ሦስተኛ ወገንንም ለመጥቀም ሲባል ሊፈፀማ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱት የሙስና ትርጓሜወች ወሱኑነት ይታይባቸዋል፡፡

የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁ.881/2007 በተለይ ሙስናን ቃል በቃል ከመተርጎም ይልቅ ‘የሙስና ወንጀሎች’ ምን አንደሚይዙ እንዲሁም የሙስና ባሕርይ እና መገለጫውን ጭምር ይናገራል፡፡ አዋጁ በአንቀጽ 4(2) ላይ፡-

“ማነኛውም የመንግሥት ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ወይም ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ የተሰጠውን ኃላፊነት ወይም ተግባር ማድረግ የሚገባውን እንዳያደርግ ወይም ማድረግ የማይገባውን እንዲደረግ ከሌላ ሰው ላይ ጥቅም የተቀበለ እንደሆነ፤ የጠየቀ ወይም በማናቸውም ሥልጣኑን ያላግባብ ከተጠቀመ፤ የማይገባ ጥቅም ለመስጠት ቃል የገባ፣ ያቀረበ፣ የሰጠ ወይም ለማቅረብ የተስማማ፤ ለወደፊት ከሚደረግ የመንግሥት ወይም ሕዝባዊ ሥራ የማይገባ ጥቅም የሰጠ ወይም የተቀበለ በሙስና ወንጀል ፈጻሚነት ተጠያቂ ይሆናል 

በዚህ ጸሐፊ ዕምነት ከላይ በአዋጁ የቀረበው መርህ የሙስና ወንጀል ምን ሊይዝ ይገባል ለሚለው እንደመነሻ ከመሆን በዘለለ ሙስናን ሙሉ በሙሉ አይገልፅም፡፡

ሌላው ስለ ሙስና መገለጫ ሲነሳ መረሳት የሌለበት አንድ ነጥብ አለ፡፡ እሱም ኪራይ ሰብሳቢነት/rent-seeking/ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ እ.ኤ.አ በ1974 አኒ ክሩገር በተባለች የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የተሰየመ ነው፡፡ በርግጥ ኪራይ ሰብሳቢነት ማለት የምጣኔ ኃብት ቃል ነው፣ አንዳንዴም ፓለቲከኞች ይጠቀሙበታል፡፡ ታዲያ ኪራይ ሰብሳቢነት ምንድን ነው?

እንደ ምጣኔ ኃብት ድርሳነት ከሆነ ኪራይ ሰብሳቢነት ማለት ያለውን ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ ስም በመጠቀም አንዳችም ምርታማነት (factors of production) ሳይጨምሩ የኢኮኖሚ ጥቅም ማካበት ወይም ኪራይ መውሰድና መቃረም ነው፡፡

ይህ ኪራይ ሰብሳቢነት ታዲያ በሙስና ላይም ይሰራል፡፡ ፉዚል ለጢፍ (2006) እንደሚሉት ከሆነ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በሕግ የተሰጠውን ሥራ በሚከነውንበት ጊዜ ነገር ግን ፈቃጅ ሥልጣን (discretionary power) ሲሆን ይህንን ክፍተት በመጠቀም ጉቦ ወይም ጥቅም ሲያካብቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ግብር ሰብሳቢ ባለስልጣናት በተለይ ቁርጥ ግብር ደረጃ “ሐ” ብንወስድ ለባለሥልጣኑ ፈቃጅ (discretionary) ሥልጣን ስላለው ወደ ኪራይ ሰብሳቢነት ይመራዋል፡፡

አሁን አሁን ግን በተለያዩ መድረኮችና መገናኛ ብዙኃን የምንሰማው ሙስና የሚለው ቃል እየተረሳ ወደ ዘመኑ ቃል ኪራይ ሰብሳቢነት እየተቀየረ ነው፡፡ ነገር ግን ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የተለያዩ ነገር ግን ተቀራራቢ ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው፡፡ ስለሆነም ኪራይ ሰብሳቢነት አንዱ የሙስና መገለጫ ነው፡፡

የሙስና መንስዔውና ውጤቱ

ሙስና የተለያዩ መነሻ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን ወደ ዝርዝር መንስዔዎች ከማምራታችን በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገር የተለመደ አባባል እናንሳ ይህም፡- “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”  ከዚህ አባባል የምንረዳው ባህሉ በራሱ ማንም ሰው ቢሆን ወደ ሥልጣን ሲወጣ በግልጽ ባይሆንም በተዘዋዋሪ /tacitly accepted/ ሙስና እንደሚፈፅም በመገንዘብና በማመን ጭምር ነው፡፡ ለምን ቢባል ማንም ሰው ከሥልጣን ሲወርድ እናዳሻው ኪራይ የመሰብሰቡ ዕድሉ ስለሚጠብበት ይመስላል ይህ አባባል አስቀድሞ በአበው ቀደምት የተነገረው፡፡

የሙስና መነሻወች አያሌና ውስብስብ ናቸው፤ በጥናት የተረጋገጡ የሙስና መንስዔዎች ግን የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.     ኢኮኖሚያዊ ምክንያት፡- ሙስናን ጨምሮ ለሌሎች የኢኮኖሚ ወንጀሎች መፈፀም እንደመነሻነት የሚወሰደው የኢኮኖሚ ችግር ወይም ድህነት ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ “Rethinking the existing legal mechanisms of controlling corruption  in Ethiopia, 1998,” በመሚለው ጽሑፋቸው  ገፅ 4 ላይ እንደጠቆሙት በኢኮኖሚ መቸገር /Economic deprivation/ አንዱና ዋናው የሙስና መንስዔ ነው፡፡ በድሀና ታዳጊ አገራት ውስጥ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራር ላይ ያሉትን ጨምሮ የወር ደምወዛቸው ጥሩ ኑሮ ለመኖር ስለማይበቃቸው ወደ ሙስና እንደሚያመሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሌላው ምጣኔ ኃብታዊ ምክንያት ደግሞ የሰው ልጅ ያልተገደብ ፍላጎትና አለጠግብባይነት /Personal greed/ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

2.    ፖለቲካዊ ምክንያት፡- በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተገኛተው ባሰሙት ንግግር ላይ ያሰማሩበት ነገር ቢኖር በአፍሪካ ተቋማት ላይ ስር የሰደደውን “የሙስና ካንሰር” ማጥፋት አለብን፡፡ ከዚህም ንግግራቸው የምንገነዘበው ቢኖር ውጣ ውረድ የበዛባቸው (ቢሮክራቲክ የሆኑ) ግልፅኝነት የጎደላቸው ልማዶች መቅረት እንዳለባቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ለምን ቢባል የመንግሥት አሠራር ግልፅኝነትና ተጠያቂነት በተቋማት ውስጥ ከሌለ ሙስና ይንሰራፋል፡፡ (የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 12 ይመለከተዋል፡፡) ሌላው እንደ ፖለቲካዊ ምክንያት ሊነሳ የሚችለው ነገር ቢኖር የሕግ ሥርዓቱ በራሱ ለባለስልጣናት ሰፊና ፈቃጅ ሥልጣን (discretionary power) መስጠቱ ለሙስና መዛመት በር ከፋች ነው፡፡ (ለምሳሌ የገቢ ግብር አዋጅ ቁ. 286/1994 አንቀጽ 68 በቁርጥ ግብር ስብሰባ ወቅት ከፍተኛ ችግር ይታያል፡፡)

3.  ባሕላዊ ምክንያት፡- በኢትዮጵያ በተለይ ባህሉና ልማዱ ለሙስና መንሰራፋትና መስፋፋት የበኩሉን ድርሻ  ያበረክታል፡፡ ለምን ቢባል በሀገራችን የተለመዱ አባባሎች አሉ ለአብነት ያህልም “ሀገር ስትዘረፍ፤ አብረህ ዝረፍ ” ወይም ደግሞ “ሲሻር ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል፡፡” በማለት ሹመኛን ወይም ባለሥልጣንን ባህሉ ሙስና እንዲፈፀም ያበረታታል፡፡ ሁለቱም አባባሎች በማህበረሰባችን ስር የሰደዱና የሰረፁ ናቸው፡፡

የሙስና መንሰራፋት የተለያዩ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅኖዎችና ውጤቶቸ አሉት፡፡ ሙስና በፖለቲካው ዘርፍ አሉታዊ ተፅኖወች ያሳድራል፤ ለአብነት ያህልም ሙስና የሕግ የበላይነትና የዴሞክረሲያዊ ዕሴቶችን ይሸረሽራል፣ የፖለቲካ ተሳትፎን ይቀንሳል፣ አደር ባይነት ያስፋፋል /encourages opportunism/፣ የሕዝብ አመኔታን ያሳጠል ብሎም የፖለቲካ አለመረጋጋትን ጭምር ያስከትላል፡፡

በማህበራዊ ምህዳሩም ሙስና የተለያዩ ችግሮች ያስከትላል፤ ከነዚህም መካከል ህብረተሰቡ አብሮ የመሥራት ባህሉን ይሸረሽራል፣ የማህበረሰቡን ሞራላዊ ዕሴቶች ያዳክማል፣ ከፍተኛ ማህበራዊ አለመመጣጠንን /social inequality/ በተለይ በሀብታሞችና በድሆች መካከል ይፈጥራል እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት ያዳክማል፡፡

በመጨረሻም ሙስና ምጣኔ ኃብቱን ያኮላሻል፣ የሀገር ልማትን ያቀጭጫል፣ በተለይም የሀገርን ምዋዕለ-ነዋይ ያዳክማል /hampers investment/፣ የሀገር ኃብት በጥቂት ስግብግቦች እጅ ሥር እንዲወድቅ ያደርጋል ብሎም የዋጋ ንረት ያስከትላል በመሆኑም ድህነትን ያስከትላል፡፡

የግሉ ዘርፍ በሙስና ወንጀል መጠየቅና የፍትሐዊነት ጥያቄ

የግሉ ዘርፍ ሲባል ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነ እንዲሁም መንግሥት ከሚመራው ክፍለ ኢኮኖሚ ውጪ በግል ባለቤትነት የተያዘና በገበያ መውጣትና መውረድ የሚወሰን ምጣኔ ኃብት ነው፡፡ ታዲያ በግሉ ዘርፍ የሚሰተዋሉ የሙስና ድርጊቶች በወንጀል መቅጣት ተገቢ ነውን?

በአንድ በኩል መንግሥት ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ገበያው እራሱን እንዲመራ የተደረገበትን ሁኔታ እናገኛለን፡፡ በዚህ ለውጥም ታዲያ የግል ዘርፋ ያለመንግሥት ጣለቃገብነት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡ የግሉን ዘርፍ በሙስና ወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ተገቢነት የለውም ለምን ቢባል ከፕራይቬታይዜሽን ፅንሰ ሃሳብ ጋር ይጣረሳል፡፡ (Kicenski: 2002)

በሌላ በኩል ሙስና የግል ዘርፋን እድገት ሲያቀጭጭ እናያለን ለአብነት ያህልም የንግድ ውድድርን ያጠፋል፣ ትንንሽ የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ ያደረጋል እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ያደበዝዛል፡፡

በመጨረሻም በወንጀል ሕግ ድርሳናት የታወቀ መርሆ አንስቼ የትኛው ክርክር ሚዛን ይደፋል የሚለውን ለአንባቢው እተዋለሁ፡፡ Principle of Ultima ratio/ የመጨረሻ ውሳኔ መርሆ አንደሚለው አንድ ድርጊት በወንጀልነት የሚፈረጀው የሚያደረሰው ጉዳት ታላቅ ሲሆን ነው/great damage/ ዳሩ ግን ጉዳቱ ትንሽ ከሆነ በዲሲፕሊን ወይም በሌላ ርምጃ ሊታረም ይችላል፡፡ ስለሆነም በግል ዘርፋ የሚፈፀመወው የሙስና ወንጀል የሚያደርሰው የጉዳት መጠን ከባድና አሳሳቢ ከሆነ ተጠያቂነቱ መፍትሔም ጭምር ነው/ Criminalization as a panacea/ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በሙስና የግሉን ዘርፍ ተጠያቂ ማድረግ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ (Dr.zaksaite: Corruption in private sector)

የአዲሱ የፀረ ሙስና ሕግ ቱርፋቶች

ኢትዮጵያ የፀረ መስና ትግሉን ለማፋፋም በማሰብ በ2007ዓ.ም የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁ. 881/2007 በማለት ማወጇ የቅርብ ወራት ትዝታ ነው፡፡ አዲሱን ሕግ ከማውጣት በስተጀርባ የሚከተሉት ምክንያቶች በመነሻነት ይነሳሉ፡፡

     I.        በወንጀል ሕጉ በአፈፃፀም ወቅት የተስተዋሉ ግልጸኝነት የሚጎድላቸውን ድንጋጌዎች ግልጽ ማድረግና ማሻሻል በማስፈለጉ፤

    II.        ሙስና በግሉ ዘርፍ ተፈጽሞ ሲገኝ በበቂ ሁኔታ የሚገዛ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩና ማሻሻል በማስፈለጉ፤

  III.      ሀገራችን ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውና ያፀደቀቻቸው የተባበሩት መንግሰታት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላለያና መዋጊያ ኮንቬንሽን በግል ዘርፍ ተቋማት ውስጥ የሚፈፀመው ሙስና በወንጀልነት ስለተፈረጀና በፈራሚ ሀገሮች ላይ ግዴታ የሚጥል በመሆኑ፤

  IV.        በመጨረሻም አንድ ወጥ የሆነ አጠቃላይ ሕግ /Comprehensive/ አዋጅ ማውጣት ማስፈለጉ ናቸው፡፡

አዋጁ በግሉ ዘርፍ ተፈፃሚ መሆኑ

ከላይ የተቀመጡትን ዓላማዎች ለማሳካት የወጣው አዋጅ በግሉ ሴክተር ተፈፃሚነቱ ከአዋጁ መግቢያ ጀምሮ ተመልክቷል፤ ታዲያ በዚህ አጋጣሚ የሚነሳው ጉደይ “የግል ዘርፍ ወይም ሕዝባዊ ድርጅት” ምንን ያካትታል? የሚለው ነጥብ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ አዋጁ የግል ዘርፍ በማለት ፋንታ ህዝባዊ ድርጅት የሚለው ሀረግ ይቀናዋል፡፡ በመሆኑም ጸሐፊው ሁለቱንም ሀረጋት እያቀያየረ ተጠቅሟል፡፡ ወደ ጉዳዩ ስንመለስ አዋጁ በአንቀጽ 2(4) ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው፡-

“ህዝባዊ ድርጅት ማለት በማነኛውም አግባብ ከአባላት ወይም ከህዝብ የተሰበሰበ ወይም ለሕዝባዊ አገልግሎት ታስቦ የተሰበሰበ ገንዘብ፤ ንብረት ወይም ሌላ ኃብትን የሚያስተዳድር አካልንና አግባብነት ያለው ኩባንያን የሚያካትት የግል ዘርፍ ሲሆን ነገር ግን የሚከተሉትን፡- የሀይማኖት ድርጅትን፣ የፖለቲካ ፓርቲን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅትን እንዲሁም ዕድርና ተመሳሳይ ባህላዊ ወይም ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው ማህበርን አያካትትም፡፡”

ከላይ በአዋጁ ከቀረበው ትረጓሜ መረዳት የሚቻለው ህዝባዊ ድርጅት ለማለት አንድም ከአባላት መዋጮ (contributions) እንደሚያሰፈልግ መገንዘብ ይቻላል በሌላ በኩል ደግሞ የተሰበሰበውን ማስተዳደርን ጭምር ያካትታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕዝባዊ ድርጅት አግባብነት ያለውን ኩባንያን የሚጨምር ሲሆን አዋጁ አግባብነት ያለው ኩባንያ የሚለውን ሀረግ ትርጉም የሰጠው ሲሆን ይህም ማለት በህዝባዊ ድርጅት የተቋቋመ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ሲሆን እንደዚህ ዓይነት ኩባንያ ከሌሎች ጋር የሚያቋቁመውን የሽርክና ማህበርን ይጨምራል፡፡

እዚህ ላይ ማስታወል ያለብን ነጥብ ቢኖር በአንድ በኩል የግል ዘርፍ የሚለው በንግድ ሕጉ አንቀጽ 212 ላይ የተዘረዘሩትን ከስድስት ያላነሱ የንግድ ማህበራትን እንድ ተራ የሽርክና ማህበር፣ የሕብረት ሽርክና ማህበር፣ ሁለት ዓይነት ኃላፊነት ያለበት ማህበር፣ የእሽሙር ማህበር፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና የአክሲወን ማህበርን እንደሚጨምር ለምን ቢባል እነዚህ የንግድ ማህበራት ከአባላት በሚሰበሰብ ካፒታል ነውና የሚመሠረቱት (የን/ሕ/ቁ 211) እንዲሁም በኢንቨስትመንት ውሎች በሚፈጠሩ ማህበራት ላይ አዲሱ የፀረ ሙስና ሕግ እንደሚፈጸም ከአዋጁ አንቀጽ 2(6) እንግሊዘኛ ቅጅ መረዳት ይቻላል“…joint ventures established by such company in association with others.”

በሌላ በኩል ህዝባዊ ድርጅት የሚለው ሀረግ በአዋጅ ቁ 147/1992 በሚገዙት ህብረት ሥራ ማህበራት /Cooperatives/ ላይም እንደሚፈጸም መረዳት እንችላለን፡፡

ሌላው ህዝባዊ ድርጅት ሚለው በፍ/ሕ/ቁ 404 ና ተከታዮቹ ያሉትን ማህበራትንም (associations) ይጨምር ይሆን? በእርግጥ ከአዋጁ ተቃራኒ ምንባብ (acontrario) መረዳት እንደሚቻለው ከኃይማኖታዊ፤ ፖለቲካዊ፤ አለማቀፋዊና ባህላዊ ድርጅት ውጪ አዋጁ በማንኛውም ድርጅት ሊፈጸም እንደሚችል ነው ነገር ግን በኢፈዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 2 የተቀመጠው የሕጋዊነት መርሆ (principle of Legality) በመጠኑም ቢሆን የአተረጓጎማችንን ዳራ ጠበብ ያደረገዋል ለምን ቢባል ፍርድ ቤት ሕገ ወጥነተ በሕግ ያለተቀመጠን ድርጊት እንደወንጀል ሊቆጥረውና ቅጣት ሊወስን እንደማይችል እሙን ነው፡፡ (የወንጀል ሕግ አንቀጽ 2(2))፡፡

ቢሆንም ግን አዋጁ “ለህዝባዊ አገልግሎት የተሰበሰበ ኃብት” የሚለውን ሀረግ ትርጉም ለመስጠት በሞከረበት ክፍል ላይ ማህበራት ወይም በጎ አድራጉት ድርጅትን ሊጨመር እንደሚችል ነው፡፡

“ለህዝባዊ አገልግሎት የተሰበሰበ ኃብት” ማለት የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ወይም ህብረተሰቡን በአጠቃላይ ለመርዳት ወይም ለመደገፍ ወይም ለማበረታታት ወይም ለማልማት ታስቦ የተሰበሰበ ወይም ለዚሁ ዓላማ እንዲውል በማነኛውም መንገድ የተገኘ እና በበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ማህበር የሚተዳደር ወይም የመሚንቀሳቀስ ገንዘብ፤ ንበረት ወይም ኃብት ነው፡፡ (አዋጅ ቁ 881/2007 አንቀጽ 2(7))

በዚህ አጋጣሚ ሀገራችን ኢትዮጵያ የፈረመችውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ስምምነት (United Nation Convention against Corruption) አንቀጽ 12 ላይ  በግሉ ዘርፍ /private sector/ ለሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ሀገራት ሕግ በማውጣት መቅጣት እንደሚችሉ ከማስቀመጥ በዘለለ የግል ዘርፍ ምንድን ነው ምን ዓይነት ድርጅቶችን ያቅፋል የሚሉ ነጥቦችን አልዳሰሰም በእርግጥ እንዲዳስስም አይጠበቅበትም፡፡ የተ.መ.ድ. ፀረ ሙስና ስምምነት አንቀጽ 12 እንዲህ ይነበባል፡-

“Each State Party shall take measures, in accordance with the fundamental principles of its domestic law, to prevent corruption involving the private sector, enhance accounting and auditing standards in the private sector and, where appropriate, provide effective, proportionate and dissuasive civil, administrative or criminal penalties for failure to comply with such measures.”

ከዚህም የምንረዳው ኢትዮጵያን ጨምሮ እያንዳንዱ ፈራሚ ሀገር በግሉ ዘርፍ የሚፈፀመውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል በመጀመሪያ ደረጃ ግልጽ የኦዲትና የሒሳብ ሥርዓት መዘረጋት አስፈላጊም ሲሆን ተመጣጣኝ የፍትሐብሔር፣ የወንጀል እንዲሁም አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ሙስናን መከላከል ነው፡፡ 

ሌላው ትኩረታችን ስለ ግሉ ዘርፍ ትርጓሜ ስንነጋገር መረሳት የሌለበት ነጥብ ኢትዮጵያ ያፀደቀችው የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላከያና መዋጊያ ስምምነት (African Union Convention on Preventing and Combating Corruption also called “Maputo convention”) ነው፡፡ ይህ የማፑቶ ስምምነት አንቀጽ 1 ላይ የግል ዘርፍ/ Private Sector ምን እንደሆነ ትልቅ ሽፋን ሠጥቶታል፡፡ አንቀጹም እንዲህ ይነበባል፡-

“Private Sector means the sector of a national economy under private ownership in which the allocation of productive resources is controlled by market force rather than public authorities and other sectors of the economy not under public sector or government.”

ይህም ማለት የግል ዘርፍ ሲባል መንግሥት ከሚመራው ክፍለ ኢኮኖሚ ውጪ በግል ባለቤትነት የተያዘና በገበያ መውጣትና መውረድ የሚወሰን ምጣኔ ኃብት ነው፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ሕግ አውጪ ይህንን የማፑቶ ስምምነት መሠረት ባደረገ መልኩ ትርጉም ሰጥቶ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ለምን ቢባል በአዋጁ አንቀጽ 2(4) ላይ የተሰጠው ትርጉም ግልፅነት ይጎድለዋልና፡፡

ሌላው አዲሱ የፀረ ሙስና ሕግ በኃይማኖታዊ ድርጅቶች አይፈፀምም ማለት በኃይማኖታዊ ድርጅት ውስጥ ሆነው የተራድኦና በጎ አድራጎት ሥራ የሚሠሩትን አይፈጸምም ማለት አይደለም፡፡ ይህም በአዋጁ አንቀጽ 2(9) ላይ በግልፅ ተመልክቷል፤ ለምሳሌ፡-የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የልማት ተራድኦ ድርጅት የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት ቢኖር አዋጁ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ስለሆነም በተባለው የተራድኦ ድርጅት ውስጥ ሙስና ቢፈፀም አዋጁ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

አዋጁ ጊዜዊ ሥራን በሚሠሩ ሠራተኞች ጭምር ተፈፃሚ መሆኑ

እንደሚታወቀው አዲሱ የፀረ ሙስና ሕግ በመንግሥታዊና በግል ዘርፍ ተፈፃሚ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ታዲያ ይህ ሲሆን የመንግሥት ሠራተኞች ወይም የግል ድርጅት ሠራተኞች ሙስና በሚፈፅሙበት ወቅት እንደሚጠየቁ ከአዋጁ መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ ጊዜዊ ሠራተኞች ጭምር በአዋጁ መካተታቸው ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ የሚደረገውን ጥረት አንድ እርምጃ ከፍ እንደሚያደረገው እሙን ነው፡፡በአዋጁ ትርጉም አንቀጽ 2(12) መሠረት ጊዜዊ ሠራተኛ ማለት በቋሚነት ሳይቀጠር በክፍያ ወይም ያለክፍያ በሙሉ ጊዜ ወይም በትርፍ ጊዜ የመንግሥትን ወይም የግልን መ/ቤት ሥራ የሚያከናወን ሲሆን ተለማማጅን (apparantice) ይጨምራል፡፡

የሕግ ሰውነት የተሰጣቸው አካላት የሙስና ወንጀል ተጠያቂነት መሻሻሉ

ሌላው አዋጅ ካመጣቸው ቱርፋቶች መካከል ሳይጠቀስ የማይታለፈው ነገር ቢኖር የሕግ ሰውነት የተሠጣቸው ድርጅቶች በሙስና ወንጀል የሚጠየቁበት አግባብ ነው፡ይህም ማለት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 90(3) የተቀመጠው ቢኖርም የሙስና ወንጀሉ የእሥራት ቅጣት ብቻ በሚደነግግ ጊዜ የገንዘብ ቅጣቱ የሚወሰነው በሕግ የተቀመጠው የገንዘብ መጠን ሲባዛ እያንዳንዱ የቅጣት ዓመት ነው፡፡ለአንባቢው ግልፅ ለማደረግ በመጀመሪያ  የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 90(3) እንመልከት፡-

በሕጉ ልዩ ክፍል ውስጥ የእሥራት ቅጣት ብቻ በተደነገገ ጊዜና ተቀጪው የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት በሆነ ጊዜ እስከ አምስት ዓመት ቀላል እሥራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር አስር ሺ፤ እስከ አምስት ዓመት ፅኑ እሥራት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር ሃያ ሺ፤እስከ አስር ዓመት ለሚያስቀጣ ወንጀል እስከ ብር ሃምሳ ሺ ፤ከአስር ዓመት ፅኑ እሥራት በላይ ለሚያስቀጣ ወንጀል ሲሆን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ(1) እስከ ተመለከተው ከፍተኛ ወሰን ለመድረስ በሚችል መቀጮ ይቀጣል፡፡

አዲሱ ሕግም በአንቀጽ 5 ላይ ያስቀመጠውን ነገር ስንመለከት የሕግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት በሙስና ወንጀል ተካፋይ ሆኖ ሲገኝ፡-

     I.        በቀላል እሥራት ለሚያስቀጣ ለእያነዳንዱ የቅጣት ዓመት ሃያ ሺህ ብር፤

    II.        ከአምስት ዓመት በታች ፅኑ እሥራት ለሚያስቀጣ ለእያንዳንዱ የቅጣት ዓመት ሰላሣ ሺህ ብር፤

  III.        ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት ፅኑ እሥራት ለሚያስቀጣ ለእያንዳንዱ የቅጣት

 ዓመት ሃምሳ ሺህ ብር፤

  IV.        ከአሥር ዓመት በላይ ፅኑ እሥራት ለሚያስቀጣ ለእያንዳንዱ የቅጣት ዓመት ሰማንያ ሺህ ብር መቀጮ እንዲከፍል ይወሰንበታል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር የቅጣቱ ጉዳይ በቁርጥ የተቀመጠ ሳይሆን የመቀጮው መጠን የሚወሰነው በቅጣት አመቱ ብዜት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ካምፓኒ ስድስት ዓመት ፅኑ እሥራት የሚያስቀጣ ወንጀል ፈፀመና በሕጉ መቀጮ ብቻ ተቀመጠ እንበል በአንቀጽ 5(3) መሠረት ለእያንዳንዱ የቅጣት ዓመት ሃምሳ ሺህ ብር ሲባዛ በስድስት ዓመት በድምሩ ሶስት መቶ ሺህ ብር ይቀጣል ማለት ነው፡፡

ይህም የወንጀል ሕጉን የቅጣት ዓላማ ከግምት ውስጥ ያላስገባና የቅጣት ተመጣጣኝነት መርሆ /Principle of Proportionality/ ያላገናዘበ ይመስላል፡፡

ጥቅም የማግኘት ወይም የመጉዳት ሀሳብ የማስረዳት ሸክም መቅረቱና የሕግ ግምት/Presumption/ መውሰዱ

እንደሚታወቀው በማስረጃ ሕጋችን የሕግ ግምት ሲኖር ግምቱ የተወሰደለት አካል በጉዳዩ ላይ ማስረዳት ሳይጠበቅበት ወደ ሌሎች መብቶቹ ያመራል፡፡ በተያዘወም ጉዳይ ዐቃቤ ሕግ የተከሳሹን የመጉዳት ሀሳብ ወይም ጥቅም ማግኘት ማስረዳት ሳይጠበቅበት ወደ ግዙፋዊ ፍሬ ነገር ያመራል፡፡ ይህ ግምት ግን ሊቀለበስ እንደሚችል /rebuttable presumption/ ከአዋጁ አንቀጽ 3 መረዳት እንችላለን ለምን ቢባል ተከሳሽ ተቃራኒ ማስረጃ ካቀረበ ግምቱ ውድቅ ይሆነልና፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግም አንቀጽ 403 ላይም ይገኛል፡፡

የሙስና ወንጀሎችን በዝርዝር ለማስቀመጥ መሞከሩ

አዋጁ የሙስና ወንጀሎችን በዝርዝር መደንገጉ ጥሩ ነገር በመሆኑ ይበል የሚያሰኘው ነገር ነው፡፡ አዋጁ የሙስና ወንጀሎችንም ከ አንቀጽ 9-33 የደነገገ ሲሆን ሕጉም በዋናነት በሥልጣን አላግባብ መገልገል (አንቀጽ 9) ላይ ያስቀመጠ ሲሆን በቅጣት መጠንም ከወንጀል ሕጉ ከበድ ያለበትን ሁኔታ እናገኛለን፤ ሌላው ጉቦ መቀበል (አንቀጽ10)፤ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ወይም ገንዘብ መያዝ (አንቀጽ 21)፤ በሰነድ ማጭበርበር/forgery/(አንቀጽ 23-24) ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የዋስትና ጉዳይ (Bail) መሻሻሉ

ዋስትና በወንጀል ሕግ ፍልስፍና ከፍርድ በፊት ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ የሚለቀቅበት መንገድ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ስለዋስትና ምንነት ቴርነስ ኢጅማን የተባሉ የዘርፉ ሙሁር የሰጡትን ትርጉም እንመልከት፡-

bail is a release from custody, pending a criminal trial, of a defendant on balancing of competing interests and on the premise that a specified predetermined amount of money will be paid if he absconds”.

ዋስትና ማለት አንድ ተከሳሽ ከተያዘበትና ከታሰረበት ቦታ በቂ ገንዘብ በማቅረብና ሁለት ተፃራሪ ጥቅሞችን ማለትም የተከሳሹን ነፃነትና የህዝብ ጥቅምን ከግምት በማስገባትና በማጣጣም የሚለቀቅበት መንገድ ነው፡፡

የጽሑፉ ዓላማ ስለ ዋስትና ማብራራት ባይሆንም ስለ ዋስትና ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ በተለያዩ ሕጎችና አዋጀች ያሉትን በወፍ በረር ቃኘት ለማድረግ ነው፡፡ ጠቆም አድርጎ ለማለፍ ያህል የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 19(6) ላይ የተያዙ ሰወች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው፡፡ ዳሩ ግን በሕግ የተቀመጡ የዋስትና ሁኔታወችና ገደቦች እንደተጠበቁ ሆነው፡፡ ከነዚህም መካከል የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግም ለአጠቃላይ ወንጀሎች ዋስትናን በተመለከተ ፖሊስ በፅኑ እሥራትና መሰል የማያስቀጣ ከሆነ የዋስትና ወረቀት በማስፈረም ተጠርጣሪን በአንቀጽ 28 መሠረት ሊለቀው ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ፍርድ ቤት በአንቀጽ 63 ተከሳሹ የተከሰሰበት ወንጀል የሞት ቅጣትን ወይም አሥራ አምስት ዓመት ወይም በላይ የሆነ ፅኑ እሥራት የማያስቀጣው ከሆነ እንዲሁም በአንቀጽ 67 ያሉ ቅደመ ሁኔታወች ከግምት በማስገባት በዋስትና ሊለቀቅ ይችላል፡፡

ወደ ልዩ ሕጎችም ስናመራ የአደገኛ ቦዘኔነት መቆጣጠሪያ አዋጅ 384/1996 አንቀጽ 6(3) ላይ በአደገኛ ቦዘኔነት ተጠርጥሮ የተያዘ ሰው በዋስትና አይለቀቅም ይላል፡፡ ሌላው ሙስናን በተመለከተ የወጣው የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁ.4 34/1997 አንቀጽ 4 ላይ የሚከተለውን ደንግጓል፡-

“በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡ ሆኖም የተከሰሰበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም፡፡”

በመጨረሻም አዲሱ ማሻሻያ አዋጅ ቁ. 882/2007 አንቀጽ 2 ላይ የቀድሞውን ድንጋጌ ተክቶ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“በሙስና ወንጀል የተያዘ ሰው በዋስ እንዲለቀቅ ለፍርድ ቤት ማመልከት ይችላል፡፡ ሆኖም የተከሰሰበት ወይም የተጠረጠረበት ወንጀል ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ፅኑ እሥራት ሊያስቀጣ የሚችል ከሆነ በዋስትና መለቀቅ አይችልም፡፡ ከአራት ዓመት በላይ እና ከአስር ዓመት በታች የሚያስቀጡ ተደራራቢ ወንጀሎች ሲኖሩም እየተደመሩ ከአሥር ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ከሆነ ዋስትና ያስከለክላል”

ለምሳሌ አቶ እንቶኔ የአንድ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የግል ተበዳይን ጉዳዩን ያለአግባብ ማጓተቱ ሳያንሰው ጉዳዩን ለመፈፀም ጉቦ ቢቀበል፤ አቶ እንቶኔ ተደራራቢ ወንጀል ፈፅመ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በአዲሱ አዋጅ ቁ 881/2007 አንቀጽ 18 መሠረት ያላግባብ ጉዳይን ማጓተት ነው እንበልና በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሠረት አራት ዓመት እንዲሁም ለጉቦ ደግሞ በአንቀጽ 10 መሠረት ሰባት ዓመት ያስቀጣዋል ብለን እናስብ፤ ስለዚህ የአቶ እንቶኔን የዋስትና ጉዳይ ስንመረምር በተደራራቢ ወንጀሎች በድምሩ አሥራ አንድ ዓመት የሚቀጣ ቢሆን ዋስትና ይከለከላል፡፡ እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት ነገር በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሠረት ሰለሚወሰን በተወሰነ መልኩ የዳኞች ፍቅደ ሥልጣን /discretion/ ይኖራል፡፡

አዲሱ ማሻሻያም አንዳንዶች እንደሚሉት ተደራራቢ ወንጀሎች /concurrent crimes መበራከትና መንሰራፍታቸው ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ መንግሥት ሙስናን ለመግታት ያሳየው ቀርጠኝነት ነው ይላሉ፡፡ ያም ተባለ ይህ ዋስትና የመጨረሻ ፍርድ ውሳኔ ስላይደለ ሌሎች መብቶችንም ማየት አማራጭ መንገድ ነው፡፡

መደምደሚያ

ሙስና አሁን አሁን በአለም ዓቀፍ መድረክም ሆነ በሀገራችን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተለያዩ የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ትግበራ ላይ ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ ሙስና በመንግሥትም ሆነ በግል ዘርፍ ሲፈፀም ተጠያቂነት እያስከተለ ነው፡፡ ሙስና በተለያዩ የፍልስፍና፤ ኃይማኖታዊና ግብረ ገባዊ (ሞራላዊ) አስተምህሮች እንደተመለከተው፤ ሙስና ማለት የመንግሥትን ሥልጣን ወይም ሀላፊነት ብሎም የሕዝባዊ ድርጅቶችን ኃብት ወይም ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን፡፡

 

በመጨረሻም አዲሱ የፀረ ሙስና ሕጋችንም የተጠቃለለ ሕግ በማውጣት ረገድ የበኩሉን መወጣቱን ጭምር መግለፅ ይቻላል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የፀረ ሙስና ስምምነተቶችን መሠረት ያደረገ መሆኑ ጥሩ ጅማሮ ነው ምንም እንኳ የሕግ ሰውነት በተሰጣቸው አካላት ላይ የቅጣት መጠኑ የተጋነነና ከበድ ያለ ቢሆንም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብትን በመተርጎም በኩል ስለታየው ችግር
የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት እና ተግባራዊ አፈፃፀሙ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 24 November 2024