ተጨማሪ ማስታወሻ፡‘መንግስት ወይም ለሕዝብ አገልግሎት የቆመ መስሪያ ቤት ላይ’ ግዴታ የሚጥሉ ዉሎች በምን አይነት ቅርጽ መሆን አለባቸዉ?
ሰበር ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 11270 የሚቀራረብ ጭብጥ አጋጥሞት ነበር፡፡ በዚህ መዝገብ የሚሟገቱት የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት እና አንድ የቀድሞ ሰራተኛዉ ናቸዉ፡፡ ጥያቄዉ ጉዳዩ በአዋጅ ቁጥር 42/83 ይሸፈናል ወይ የሚል ነበር፡፡ ይህን የተመለከተዉ ሰበር ችሎቱ በመጋቢት 23 ቀን 1997 በሰጠዉ ዉሳኔ እንዲህ ብሏል፡፡
ለዚህ ጉዳይ አግባብነት ያለዉና የአመልካች መስሪያ ቤትን ያቋቋመዉ አዋጅ ቁ.266/76 በአንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ መስሪያ ቤቱ የመንግስት መስሪያ ቤት እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ይህም ማለት በመርህ ደረጃ አመልካች መስሪያ ቤት አስተዳደራዊ ስራዎችን የሚሰራ ሆኖ በአጋጣሚ ግን ከምርት ዉጤቶቹና ከአገልግሎት ዋጋ ገቢ ያገኛል፡፡ የመስሪያ ቤቱን በጀትም የተመለከትን እንደሆነ በአብዛኛዉ ከመንግስት ከሚሰጥ አመታዊ ድጋፍ እንደሚገኝ የማቋቋሚያዉ አዋጅ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ 1 ይገልጻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መስሪያ ቤት በትምህርት ሚኒስቴር ስር ሆኖ በመቋቋሙ አስተዳደራዊ ስራዎችን ከመስራት በቀር በትርፍ ስራ ላይ ሊሰማራ እንደማይችል እንረዳለን፡፡ በመጨረሻም በአንቀጽ 9 ንኡስ ቁጥር 2/ሀ/ ላይ እንደተመለከተዉ መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችን የሚቀጥረዉ፤ የሚያስተዳደረዉም ሆነ የሚያባርረዉ በመንግስት ሰራተኞች ሕግ ነዉ፡፡
በአጠቃላይ መስሪያ ቤቱ ተጠሪ በተሰናበተበት ጊዜ በዋናነት አስተዳደራዊ ስራዎችን የሚሰራ በመሆኑ እና በጀቱንም በዋናነት ለመንግስት በየአመቱ የሚያገኝ በመሆኑ አመልካች መስሪያ ቤት በአዋጅ ቁ.42/85 የሚሸፈን አልነበረም፡፡
በመሆኑም ይህ ችሎት በአመልካች እና በተጠሪ መካከል ያለዉን ግንኙነት የሚገዛዉ አዋጅ ቁ.42/85 አይደለም ሲል ወስኗል፡፡ በዚህም አቤቱታ የቀረበባቸዉን የስር ፍ/ቤቶች ዉሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ.348(1) መሰረት ሽሮታል፡፡
የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት በኋላ ላይ እንደ ልማት ድርጅት መልሶ ተደራጅቷል፡፡ በፊት ግን የራሱ የሕግ ሰዉነት ያለዉ ድርጅት ሲሆን የሚተዳደረዉ በትምህርት ሚኒስቴር ስር ሲሆን እንቅስቃሴዎቹን በየአመቱ በሚወሰን በጀት ይሸፍናል፡፡ ሰበር ችሎቱም ድርጀቱ በትምህርት ሚኒስቴር ስር የሚተዳደርና በአመታዊ በጀት የሚደገፍና ምንም እንኳ ገቢ ቢያመጣም የአስተዳደር ስራ የሚሰራ መስሪያ ቤት በሚል ወስኗል፡፡
ይህን ዉሳኔ እላይ ሰበር ችሎቱ ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅትን አስመልክቶ ከሰጠዉ ዉሳኔ ጋር ማነጻጸር ይቻላል፡፡ የትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅትን የአስተዳደር ስራ የሚሰራ የመንግስት ስራ ብሎ የሚሰይመዉ ከሆነ ለምን ኪራይ ቤቶችን እንደዛ እንደማይለዉ ግልጽ አይደለም፡፡ ሁለቱም የራሳቸዉ የሕግ ሰዉነት ያላቸዉ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ አንዱ ተጠሪነቱ ለትምህርት ሚኒስቴር ሲሆን ሌላኛዉ ለስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ነበር፡፡ ሁለቱም አመታዊ በጀታቸዉን በመንግስት ያስቀስናሉ፡፡ ሁለቱም ገቢዎች ይኖሩዋቸዋል፡፡ ሰለዚህ ለምን የተለየ ስያሜ (characterization) አስፈለገ? ለነገሩ እላይ እንዳልኩት 1724 በወይም የተያያዙ ሁለት ሀረጎች ናቸዉ፡፡ መንግስት መስሪያ ቤት ላይ ግዴታ የሚጥል ወይም ለሕዝብ አገልግሎት የተቋቋመ መስሪያ ቤት ላይ ግዴታ የሚጥል፡፡ ከዚህ ተነስተን 1724 የአስተዳደር ስራ የሚሰራ የመንግስት መስሪያ ቤትን ብቻ ነዉ የሚመለከተዉ ማለት አንችልም፡፡ የአስተዳደር ስራ የሚሰራ ከሆነ ጥሩ በዚህ ሕግ ይገዛል፤ ለሕዝብ አግልግሎት የተቋቋመ መስሪያ ቤት በሚለዉ፡፡ በዚህ አባባልም እንኳ፤ እላይ እንደተባለዉ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የአስተዳደር ስራ የሚሰራ ድርጅት ሊባል ይችላል፡፡
የአስተዳደር ስራ የሚሰራ ባይሆንም እንኳ የመንግስት የልማት ድርጅት ቢሆንም እንኳ ይህ ድርጅት የሚዋዋለዉ ዉል በመንግስት ላይ ግዴታ የሚጥል ነዉ ሊባል ይችላል፡፡ ለዚህ መቃወሚያ ሊሆን የሚችለዉ የልማት ድርጅቶች ምንም እንኳ በመንግስት ባለቤትነት ስር ቢሆንም ሃላፊነታቸዉ ዉስን ነዉ፡፡ በመሆኑም እነሱ የሚፈጥሩት/የሚያመጡት ሃላፊነት ካላቸዉ ካፒታል አልፎ መንግስትን አይመለከትም ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ክርክር ተቀባይነት ካገኘ፤ 1724 የሚመለከተዉ ዉስን ሃላፊነት የሌላቸዉን የመንግስት ድርጅቶችንና የአስተዳደር ስራ የሚሰሩትን ሊባል ይችላል፡፡
መጠሪያቸዉ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ድርጅቶች በሁለቱ ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ አንደኛዉ፤ በበጀት የሚንቀሳቀሱና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ በተለይ የሕዝብ አስተዳደር ሊባል የሚችል ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፤ ቢሮዎች፤ ኮሚሽኖች፤….. እየተባሉ ይጠራሉ፡፡ ሌሎቹ ድርጅቶች የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚባሉትና በቦርድ የሚተዳደሩት ናቸዉ፡፡ አልፎ አልፎ በመንግስት የበጀት ድጋፍ ሊደረግላቸዉ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነዉ የመክሰር አደጋ ላይ ሲሆኑ ብቻ ነዉ፡፡ ከዛ ዉጭ ግን በመንግስት መነሻ ካፒታል ተወስኖላቸዉ ይንን እየተጠቀሙና በገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አግልግሎት በማቅረብ የሚንቀሳቀሱ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ቢከስሩ ሃላፊነታቸዉ ዉስን ነዉ፤ማለትም ካላቸዉ ካፒታል ዘሎ መንግስትን መጠየቅ አይቻልም፡፡ የሰበር ችሎቱ ዉሳኔ በግልጽ ባይሆንም 1724 የመጀመሪያዎቹን አይነት ድርጅቶች ይመለከታል የሚል ነዉ፡፡
ያም ቢሆን ግን እንደኔ እንደኔ፤ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ልክ እንደ ትምህርት መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ሁሉ የአስተዳደር መሰሪያ ቤት ሊባል ይገባ ነበር፡፡
አንዳንድ ከሁለቱም ለመመደብ የሚያስቸግሩ ድርጅቶች ሊኖሩ ይችላሉ--እኔ ለምሳሌ የምርት ገበያ ድርጅትን አዉቃለዉ፡፡
ሰበር ችሎቱ ለምን እንደዛ ወሰነ?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ምክኒያቱን ግልጽ ስላላደረገ፡ ነገር ግን እዚህ ላይ ማየት ያለብን የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በ1724 ይካተታል ብሎ መወሰን የሚኖረዉን አንድምታ ነዉ፡፡
1724 ለጉዳዩ የሚዉል ድንጋጌ ነዉ የሚባል ከሆነ የዚህ አባባል ቅጥያ የሚሆነዉ ይህ ድርጅት የሚዋዋለዉ ዉል በጽሁፍና በባለስልጣን ፊት መሆን አለበት፡፡ በጽሁፍ ሲባል በሁለት ምስክሮች መረጋገጥ አለበት፡፡ ከዉሳኔዉ መግቢያ ማየት እንደሚቻለዉ በዉሉ ላይ ምስክሮችም አልፈረሙበትም፤ በባለስልጣንም ፊት አይተደረገም፡፡ ይህ ማለት፤ ዉሉ እንከን ያለዉ እንደዉም የዉል ረቂቅ ነዉ፡፡
ታዲያ ኪራይ ቤቶች ከሰረ ማለት ነዉ? ግለሰቡ በነጻ ቤቱን ተጠቅሞ ሄደ ማለት ነዉ? ይህ ማለት አይደለም፡፡ ድርጅቱ ግለሰቡ የተጠቀሰዉን ቤት እንደተጠቀመበት ማስረዳት ከቻለ ከዉል ዉጭ አላግባብ መበልጸግ በሚለዉ ሊጠይቀዉ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን ማስረዳት ይኖርበታል፡፡
ታዲያ ልዩነቱ ምን ላይ ነዉ፤ የዉል መኖርና አለመኖሩ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ልዩነቱ የማስረዳት ሸክሙና መጠየቅ የሚቻለዉ ክፍያን ይመለከታል፡፡ ሕጋዊ ዉል አለዉ የሚባል ከሆነ ዉሉ ላይ የተጠቀሰዉን ክፍያ መጠየቅ ይቻላል፡፡ እንዲሁም ተከራዩ ንብረቱን ስለመጠቀሙ ማስረዳት አይኖርበትም፡፡ ነገር ግን ዉል ከሌለ በቁጥር 2162 መሰረት መጠየቅ የሚችለዉ ግለሰቡ ባገኝዉ ጥቅም ልክ ነዉ፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments