- Details
- Category: Quick Links
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 83102
አዋጅ ቁጥር 1/1987 - የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት
አዋጅ ቁጥር 1/1987
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ
ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ መዋሉን ለማሳወቅ የወጣ አዋጅ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መርጠው በላኳቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት ኀዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥትን ያጸደቁ በመሆኑ የሚከተለው ታውጇል፡፡
-
አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ "የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አዋጅ ቁጥር 1/1987" ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
-
ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ ስለመዋሉ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ በመሉ በሥራ ላይ ውሏል፡፡
-
አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ የጸና ይሆናል፡፡
አዲስ አበባ ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም.
መግቢያ
እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች:-
በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኀበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤
ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ፣ የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰብ መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ካለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን በመሆኑ፤
ኢትዮጵያ ሀገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር በመሆንዋ፤ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤
መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤
ጥቅማችንን፣ መብታችንና ነፃነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኀበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤
በትግላችንና በከፈልነው መሰዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፤
ይህ ሕገ መንግሥት ከዚህ በላይ ለገለጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት በሕገ መንግሥት ጉባዔ ዛሬ ኀዳር 29 ቀን 1987 አጽድቀነዋል፡፡
ምዕራፍ አንድ
ጠቅላላ ድንጋጌዎች
አንቀጽ 1 - የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ
ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል፡፡
አንቀጽ 2 - የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን
የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የተወሰነው ነው፡፡
አንቀጽ 3 - የኢትዮጵያ ስንደቅ ዓላማ
- የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሐል ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል። ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ፡፡
- ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል፡፡
- የፌዴራሉ አባሎች የየራሳቸው ስንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል። ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ፡፡
አንቀጽ 4 - የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንጸባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 5 - ስለ ቋንቋ
- ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት የመንግሥት እውቅና ይኖራቸዋል፡፡
- አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል፡፡
- የፌዴሬሽኑ አባሎች የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ ይወስናሉ፡፡
አንቀጽ 6 - ስለዜግነት
- ወላጆቹ/ወላጆቿ ወይም ከወላጆቹ/ከወላጆቿ አንደኛቸው ኢትዮጵያዊ/ኢትዮጵያዊት የሆነ/የሆነች የኢትዮጵያ ዜጋ ነው/ናት፡፡
- የውጭ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
- ዜግነትን በሚመለከት ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 7 - የፆታ አገላለጽ
በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ በወንድ ፆታ የተደነገገው የሴትንም ፆታ ያካትታል፡፡
ምዕራፍ ሁለት
የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች
አንቀጽ 8 - የሕዝብ ሉዓላዊነት
- የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡
- ይህ ሕገ መንግሥት የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው፡፡
- ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 9 - የሕገ መንግሥት የበላይነት
- ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡
- ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኀበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡
- በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡
- ኢትዮጵያ ያጸደቃቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡
አንቀጽ 1ዐ - ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች
- ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡
- የዜጎች እና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡
አንቀጽ 11 - የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት
- መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡
- መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡
- መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡
አንቀጽ 12 - የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት
- የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት፡፡
- ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል፡፡
- ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት ይችላል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
ምዕራፍ ሦስት
መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች
አንቀጽ 13 - ተፈጻሚነትና አተረጓጎም
- በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡
- በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሠነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ፡፡
ክፍል አንድ
ሰብዓዊ መብቶች
አንቀጽ 14 - የሕይወት፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት
ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰሰ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡
አንቀጽ 15 - የሕይወት መብት
ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት አለው። ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡
አንቀጽ 16 - የአካል ደህንነት መብት
ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡
አንቀጽ 17 - የነፃነት መብት
- በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን/ቷን አያጣም/አታጣም፡፡
- ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም፡፡
አንቀጽ 18 - ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ
- ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡
- ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ አይችልም። ለማንኛውም ዓላማ በሰው የመነገድ ተግባር የተከለከለ ነው፡፡
- ማንኛውም ሰው በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታን ለማሟላት ማንኛውንም ሥራ እንዲሠራ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 "በኃይል ተገዶ ወይም ግዴታን ለማሟላት" የሚለው ሐረግ የሚከተሉትን ሁኔታዎች አያካትትም፤
ሀ) ማንኛውም እስረኛ በእስራት ላይ ባለበት ጊዜ በሕግ መሠረት እንዲሠራ የተወሰነውን ወይም በገደብ ከእስር በተለቀቀበት ጊዜ የሚሠራውን ማንኛውም ሥራ፣
ለ) ማንኛውም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለት ሰው በምትክ የሚሰጠውን አገልግሎት፣
ሐ) የማኀበረሰቡን ሕይወት ወይም ደህንነት የሚያሰጋ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ወይም አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ የሚሰጥ ማንኛውንም አገልግሎት፣
መ) በሚመለከተው ሕዝብ ፈቃድ በአካባቢው የሚፈጸመውን ማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ የልማት ሥራ፡፡
አንቀጽ 19 - የተያዙ ሰዎች መብት
- ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተያዙ ሰዎች የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲነገራቸው መብት አላቸው፡፡
- የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት አላቸው፣ የሚሰጡት ማንኛውም ቃል ፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል መረዳት በሚችሉት ቋንቋ እንደተያዙ ወዲያውኑ ማስገንዘቢያ እንዲሰጣቸው መብት አላቸው፡፡
- የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው። ይህም ጊዜ ሰዎቹ ከተያዙበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም። ወዲያውኑ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑ ተለይቶ እንዲገለጽላቸው መብት አላቸው፡፡
- የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የሕግ አስከባሪ በጊዜው ገደብ ፍርድ ቤት በማቅረብ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ የአካል ነፃነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው። ሆኖም ፍትሕ እንዳይጓደል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የተያዘው ሰው በጥበቃ ስር እንዲቆይ ለማዘዝ ወይም ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ሊፈቅድ ይችላል። የሚያስፈልገውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ሲወስን ኃላፊ የሆኑት የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣኖች ምርመራውን አጣርተው የተያዘው ሰው በተቻለ ፍጥነት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያለውን መብት የሚያስከብር መሆን አለበት፡፡
- የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማሰረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም። በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
- የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት አላቸው። ሆኖም በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ ይችላል፡፡
አንቀጽ 20 - የተከሰሱ ሰዎች መብት
- የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው። ሆኖም የተከራካሪዎቹን የግል ሕይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ ይችላል፡፡
- ክሱ በቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገራቸው እና ክሱን በጽሑፍ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
- በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፣ በምስክርነት እንዲቀርቡም ያለመገደድ መብት አላቸው፡፡
- የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸው ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
- በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
- ክርክሩ በሚታይበት ፍርድ ቤት በተሰጠባቸው ትእዛዝ ወይም ፍርድ ላይ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡
- የፍርዱ ሂደት በማይገባቸው ቋንቋ በሚካሄድበት ሁኔታ በመንግሥት ወጪ ክርክሩ እንዲተረጎምላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 21 - በጥበቃ ስር ያለና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት
- በጥበቃ ስር ያለና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡
- ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 22 - የወንጀል ሕግ ወደኋላ ተመልሶ የማይሠራ ስለመሆኑ
- ማንኛውም ሰው የወንጀል ክስ ሲቀርብበት የተከሰሰበት ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ ድርጊቱን መፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ ወንጀል መሆኑ በሕግ የተደነገገ ካልሆነ በስተቀር ሊቀጣ አይችልም። እንዲሁም ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ ለወንጀሉ ተፈጻሚ ከነበረው የቅጣት ጣሪያ በላይ የከበደ ቅጣት በማንኛውም ሰው ላይ አይወሰንም፡፡
- የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ቢኖርም፣ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡
አንቀጽ 23 - በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት ስለመከልከሉ
ማንኛውም ሰው በወንጀል ሕግና ሥነ ሥርዓት መሠረት ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሳኔ ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና አይከሰስም ወይም አይቀጣም፡፡
አንቀጽ 24 - የክብርና የመልካም ስም መብት
- ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ የመከበር መብት አለው፡፡
- ማንኛውም ሰው የራሱን ስብዕና ከሌሎች ዜጎች መብቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ በነፃ የማሳደግ መብት አለው፡፡
- ማንኛውም ሰው በማንኛውም ስፍራ በሰብዓዊነት እውቅና የማግኘት መብት አለው፡፡
አንቀጽ 25 - የእኩልነት መብት
ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፣ ብሔረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኀበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋሰትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 26 - የግል ሕይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት
- ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱ፣ ግላዊነቱ፣ የመከበር መብት አለው። ይህ መብት መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል፡፡
- ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚጻጻፋቸው፣ በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች፣ እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም፡፡
- የመንግሥት ባለሥልጣኖች እነዚህን መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው። አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ብሔራዊ ደህንነትን፣ የሕዝብ ሰላም፣ ወንጀልን በመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ በመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነፃነት በማስከበር ዓላማዎች ላይ በተመሰረቱ ዝርዝር ሕጎች መሠረት ካልሆነ በስተቀር የእነዚህ መብቶች አጠቃቀም ሊገደብ አይችልም፡፡
አንቀጽ 27 - የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት
- ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት አለው። ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡
- በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 2 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የማያስችሏቸው የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም ይችላሉ፡፡
- ማንኛውንም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም፡፡
- ወላጆችና ሕጋዊ ሞግዚቶች በእምነታቸው መሠረት የሃይማኖታቸውንና የመልካም ሥነ ምግባር ትምህርት በመስጠት ልጆቻቸውን የማሳደግ መብት አላቸው፡፡
- ሃይማኖትንና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደህንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች፣ ነፃነቶች፣ እና መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ይሆናል፡፡
አንቀጽ 28 - በስብዕና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች
- ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፤ የሰው ዘር የማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፣ ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም። በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡
- ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሱትን ወንጀሎች ፈጽመው የሞት ቅጣት ለተፈረደባቸው ሰዎች ርዕስብሔሩ ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ሊያሻሽለው ይችላል፡፡
ክፍል ሁለት
ዴሞክራሲያዊ መብቶች
አንቀጽ 29 - የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት
- ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡
- ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው። ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡
- የኘሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙሃን፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል። የኘሬስ ነፃነት በተለይ የሚከተሉትን መብቶች ያጠቃልላል፤
ሀ) የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን፣
ለ) የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት ዕድልን፡፡
- ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሀሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ኘሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡
- በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በማያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፡፡
- እነዚህ መብቶች ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሀሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነት በአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ሕጎች ብቻ ይሆናል። የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ሕጋዊ ገደቦች በነዚህ መብቶች ላይ ሊደነገጉ ይችላሉ። የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በሕግ የሚከለከሉ ይሆናሉ፡፡
- ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡
አንቀጽ 30 - የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ - የማቅረብ መብት
- ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና፣ አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው። ከቤት ውጭ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ወይም በመካሔድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ሰላምን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉ፡፡
- ይህ መብት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጎች መሠረት ተጠያቂ ከመሆን አያድንም፡፡
አንቀጽ 31 - የመደራጀት መብት
ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኀበር የመደራጀት መብት አለው። ሆኖም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገ ወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ይሆናሉ፡፡
አንቀጽ 32 - የመዘዋወር ነፃነት
- ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው፡፡
- ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብት አለው፡፡
አንቀጽ 33 - የዜግነት መብቶች
- ማንኛውም ኢትዮጰያዊ/ኢትዮጵያዊት ከፈቃዱ/ከፈቃዷ ውጭ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን/ዜግነትዋን ሊገፈፍ ወይም ልትገፈፍ አይችልም/አትችልም። ኢትዮጰያዊ/ኢትዮጵያዊት ዜጋ ከሌላ ሀገር ዜጋ ጋር የሚፈጽመው/የምትፈጽመው ጋብቻ ኢትዮጰያዊ ዜግነቱን/ዜግነትዋን አያስቀርም፡፡
- ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የኢትዮጵያ ዜግነት በሕግ የሚያስገኘውን መብት፣ ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት አለው፡፡
- ማንኛውም ዜጋ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን የመለወጥ መብት አለው፡፡
- ኢትዮጵያ ከአጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በማይቃረን መንገድ በሚወጣ ሕግ እና በሚደነግግ ሥርዓት መሠረት የኢትዮጵያ ዜግነት ለውጭ ሀገር ሰዎች ሊሰጥ ይችላል፡፡
አንቀጽ 34 - የጋብቻ የግልና የቤተሰብ መብቶች
- በሕግ ከተወሰነው የጋብቻ ዕድሜ የደረሱ ወንዶችና ሴቶች በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ ወይም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው የማግባትና ቤተሰብ የመመሥረት መብት አላቸው፡፡ በጋብቻ አፈጻጸም፣ በጋብቻው ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት አላቸው። በፍቺም ጊዜ የልጆችን መብትና ጥቅም እንዲከበር የሚያደርጉ ድንጋጌዎች ይደነግጋሉ፡፡
- ጋብቻ በተጋቢዎች ነፃና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ ይመሰረታል፡፡
- ቤተሰብ የኀብረተሰብ የተፈጥሮ መሠረታዊ መነሻ ነው። ከኀብረተሰብና ከመንግሥት ጥበቃ የማግኘት መብት አለው፡፡
- በሕግ በተለይ በሚዘረዘረው መሠረት በሃይማኖት፣ በባሕል የሕግ ሥርዓቶች ላይ ተመስርተው ለሚፈጸሙ ጋብቻዎች እውቅና የሚሰጥ ሕግ ሊወጣ ይችላል፡፡
- ይህ ሕገ መንግሥት የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሃይማኖቶች ወይም በባሕሎች ሕጎች መሠረት መዳኘትን አይከለክልም። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 35 - የሴቶች መብት
- ሴቶች ይህ ሕገ መንግሥት በአረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች በመጠቀም ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡
- ሴቶች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡
- ሴቶች በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው። በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፣ በማኀበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ተቋሞች ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪና ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው፡፡
- ሴቶች ከጎጂ ባሕል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር አለበት። ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ወይም በአዕምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ሕጎች፣ ወጎችና ልማዶች የተከለከሉ ናቸው፡፡
- ሀ) ሴቶች የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የማግኘት መብት አላቸው ።የወሊድ ፈቃድ ርዝመት ሴቷ የምትሠራውን ሥራ ሁኔታ፣ የሴቷን ጤንነት፣ የሕፃኑንና የቤተሰቡን ደህንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በሕግ ይወሰናል፡፡
ለ) የወሊድ ፈቃድ በሕግ በሚወሰነው መሠረት ከሙሉ የደመወዝ ክፍያ ጋር የሚሰጥ የእርግዝና ፈቃድን ሊጨምር ይችላል፡፡
- ሴቶች በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በኘሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም፣ በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ኘሮጀክቶች ሀሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
- ሴቶች ንብረት የማፍራት፣ የማስተዳደር፣ የመቆጣጠር፣ የመጠቀምና የማስተላለፍ መብት አላቸው። በተለይ መሬትን በመጠቀም፣ በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርና በመቆጣጠር ረገድ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው። እንዲሁም ውርስን በሚመለከት በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው፡፡
- ሴቶች የቅጥር፣ የሥራ እድገት የእኩል ክፍያና ጡረታን የማስተላለፍ እኩል መብት አላቸው፡፡
- ሴቶች በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት መረጃ እና አቅም የማግኘት መብት አላቸው፡፡
አንቀጽ 36 - የሕፃናት መብት
- ማንኛውም ሕፃን የሚከተሉት መብቶች አሉት፤
ሀ) በሕይወት የመኖር፣
ለ) ስምና ዜግነት የማግኘት፣
ሐ) ወላጆቹን ወይም በሕግ የማሳደግ መብት ያላቸውን ሰዎች የማወቅና የእነሱንም እንክብካቤ የማግኘት፣
መ) ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርቱ፣ በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠሩ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ፣
ሠ) በትምህርት ቤቶች ወይም በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋሞች ውስጥ በአካሉ ከሚፈጸም ወይም ከጭካኔና ኢሰብዓዊ ከሆነ ቅጣት ነፃ የመሆን፡፡
- ሕፃናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግሥታዊ ወይም በግል የበጎ አድራጎት ተቋሞች፣ በፍርድ ቤቶች፣ በአስተዳደር ባለሥልጣኖች ወይም በሕግ አውጪ አካላት የሕፃናት ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት፡፡
- ወጣት አጥፊዎች፣ በማረሚያ ወይም በመቋቋሚያ ተቋሞች የሚገኙ፣ በመንግሥት እርዳታ የሚያድጉ ወጣቶች፣ በመንግሥት ወይም በግል እጓለማውታን ተቋሞች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከአዋቂዎች ተለይተው መያዝ አለባቸው፡፡
- ከጋብቻ ውጭ የሚወለዱ ሕፃናት በጋብቻ ከተወለዱ ሕፃናት ጋር እኩል መብት አላቸው፡፡
- መንግሥት ለእጓለማውታን ልዩ ጥበቃ ያደርግላቸዋል በጉዲፈቻ የሚያድጉበትን ሥርዓት የሚያመቻቹና የሚያስፋፉ እንዲሁም ደህንነታቸውንና ትምህርታቸውን የሚያራምዱ ተቋሞች እንዲመሰረቱ ያበረታታል፡፡
አንቀጽ 37 - ፍትሕ የማግኘት መብት
- ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተውን ውሳኔ ወይም ፍርድ፤
ሀ) ማንኛውም ማኀበር የአባላቱን የጋራ ወይም የግል ጥቅም በመወከል፣
ለ) ማንኛውንም ቡድን ወይም ተመሳሳይ ጥቅም ያላቸውን ሰዎች የሚወክል ግለሰብ ወይም የቡድን አባል የመጠየቅና የማግኘት መብት አለው፡፡
አንቀጽ 38 - የመምረጥና የመመረጥ መብት
- ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የሚከተሉት መብቶች አሉት፤
ሀ) በቀጥታ እና በነፃነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ፣
ለ) ዕድሜው 18 ዓመት ሲሞላ በሕግ መሠረት የመምረጥ፣
ሐ) በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ። ምርጫው ሁሉ አቀፍ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሰረተና በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡
- በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሠራተኞች፣ በንግድ፣ በአሠሪዎችና በሙያ ማኀበራት ለተሳትፎ ድርጅቱ የሚጠይቀውን ጠቅላላና ልዩ የአባልነት መስፈርት የሚያሟላ ማንኛውም ሰው በፍላጎቱ አባል የመሆን መብቱ የተከበረ መሆን አለበት፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 በተመለከቱት ድርጅቶች ውስጥ ኃላፊነት ቦታዎች የሚካሄዱ ምርጫዎች ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይፈጸማሉ፡፡
- የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እና 3 ድንጋጌዎች የሕዝብን ጥቅም ሰፋ ባለ ሁኔታ የሚነኩ እስከሆነ ድረስ በሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡
አንቀጽ 39 - የብሔሮች ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት
- ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡
- ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ፣ እና ባሕሉን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው፡፡
- ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው። ይህ መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፡፡
- የብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ከሥራ ላይ የሚውለው፤
ሀ) የመገንጠል ጥያቄ በብሔር፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ የሕግ አውጪ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ የድምፅ ድጋፍ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ፤
ለ) የፌዴራሉ መንግሥት የብሔር፣ የብሔረሰቡ ወይም የሕዝቡ ምክር ቤት ውሳኔ በደረሰው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠያቂው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፤
ሐ) የመገንጠሉ ጥያቄ በሕዝብ ውሳኔው በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፤
መ) የፌዴራል መንግሥት መገንጠሉን ለመረጠው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤት ሥልጣኑን ሲያስረክብ፤
ሠ) በሕግ በሚወሰነው መሠረት የንብረት ክፍፍል ሲደረግ ነው፡፡
- በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ "ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ" ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን ባህርይ የሚያሳይ ማኀብረሰብ ነው። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡
አንቀጽ 40 - የንብረት መብት
- ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ/መሆኗ ይከበርለታል/ይከበርላታል። ይህ መብት የሕዝብን ጥቅም ለመጠበቅ በሌላ ሁኔታ በሕግ እስካልተወሰነ ድረስ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም ወይም የሌሎችን ዜጎች መብቶች እስካልተቃረነ ድረስ ንብረትን የመሸጥ፣ የማውረስ ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል፡፡
- ለዚህ አንቀጽ ዓላማ "የግል ንብረት" ማለት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ወይም ሕጋዊ ሰውነት በሕግ የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ማኀበራት ወይም አግባብ በአላቸው ሁኔታዎች በሕግ በተለየ በጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማኀበረሰቦች በጉልበታቸው፣ በመፍጠር ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና የተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት ነው፡፡
- የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፡፡
- የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው። አፈጻጸሙን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ይወጣል፡፡
- የኢትዮጵያ ዘላኖች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነፃ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙ በሕግ ይወሰናል፡፡
- የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና፣ ሕዝቦች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
- ማንም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬት ላይ ለሚገነባው ቋሚ ንብረት ወይም ለሚያደርገው ቋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለው ይህ መብት የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ፣ የመሬት ተጠቃሚነቱ ሲቋረጥ ንብረቱን የማንሳት፣ ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠየቅ መብትን ያካትታል ዝርዝር አፈጻጸሙ በሕግ ይወሰናል፡፡
- የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመወሰድ ይችላል፡፡
አንቀጽ 41 - የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊና የባሕል መብቶች
- ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመስማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፡፡
- ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው፡፡
- የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማኀበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብት አላቸው፡፡
- መንግሥት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማኀበራዊ አገልግሎቶች ለሕዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሀብት ይመድባል፡፡
- መንግሥት የአካል እና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋዊያንና ያለወላጅ ወይም ያለአሳዳጊ የቀሩ ሕፃናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ያደርጋል፡፡
- መንግሥት ለሥራ አጦችና ለችግረኞች ሥራ ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ ይከተላል፤ እንዲሁም በሚያካሄደው የሥራ ዘርፍ ውስጥ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሥራ ኘሮግራሞችን ያወጣል ኘሮጀክቶችን ያካሄዳል፡፡
- መንግሥት ዜጎች ጠቃሚ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
- ገበሬዎችና ዘላን ኢትዮጵያውያን በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸውና ለምርት ካደረጉት አስተዋጽኦ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ተገቢ ዋጋ ለምርት ውጤቶቻቸው የማግኘት መብት አላቸው። መንግሥት የኢኮኖሚ የማኀበራዊና የልማት ፖሊሲዎችን በሚተልምበት ጊዜ በዚህ ዓላማ መመራት አለበት፡፡
- መንግሥት የባሕልና የታሪክ ቅርሶችን የመንከባከብና ለሥነጥበብና ለስፖርት መስፋፋት አስተዋፅዖ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
አንቀጽ 42 - የሠራተኞች መብት
- ሀ) የፋብሪካና የአገልግሎት ሠራተኞች፣ ገበሬዎች፣ የእርሻ ሠራተኞች፣ ሌሎች የገጠር ሠራተኞች፣ ከተወሰነ የኃላፊነት ደረጃ በታች ያሉና የሥራ ጠባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ለማሻሻል በማኀበር የመደራጀት መብት አላቸው። ይህ መብት የሠራተኛ ማኀበራትንና ሌሎች ማኀበራትን የማደራጀት፣ ከአሠሪዎችና ጥቅማቸውን ከሚነኩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የመደራደር መብትን ያካትታል፡፡
ለ) በንዑስ አንቀጽ (ሀ) የተመለከቱት የሠራተኛ ክፍሎች ሥራ ማቆምን ጨምሮ ቅሬታቸውን የማሰማት መብት አላቸው፡፡
ሐ) በንዑስ አንቀጽ (ሀ) እና (ለ) መሠረት እውቅና ባገኙት መብቶች ለመጠቀም የሚችሉት የመንግሥት ሠራተኞች በሕግ ይወሰናሉ፡፡
መ) ሴቶች ሠራተኞች ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡
- ሠራተኞች በአግባቡ የተወሰነ የሥራ ሰዓት ዕረፍት የመዝናኛ ጊዜ፣ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የዕረፍት ቀኖች፣ ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በዓላት እንዲሁም ጤናማና አደጋ የማያደርስ የሥራ አካባቢ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
- እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚወጡ ሕጎች በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት እውቅና ያገኙትን መብቶች ሳይቀንሱ የተጠቀሱት ዓይነት የሠራተኛ ማኀበራት ስለሚቋቋሙበትና የጋራ ድርድር ስለሚካሄድበት ሥርዓት ይደነግጋሉ፡፡
አንቀጽ 43 - የልማት መብት
- የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአጠቃላይም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በተናጠል የኑሮ ሁኔታቸውን የማሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡
- ዜጎች በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይም አባል የሆኑበትን ማኀበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ ሀሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
- መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባቸው ስምምነቶችም ሆኑ የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች የኢትዮጵያን የማያቋርጥ እድገት መብት የሚያስከብሩ መሆን አለባቸው፡፡
- የልማት አንቅስቃሴ ዋና ዓላማ የዜጎችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 44 - የአካባቢ ደህንነት መብት
- ሁሉም ሰዎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው፡፡
- መንግሥት በሚያካሄዳቸው ኘሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግሥት በቂ እርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ መዘዋወርን ጨምሮ ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
ምዕራፍ አራት
የመንግሥት አወቃቀር
አንቀጽ 45 - ሥርዓተ መንግሥት
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሥርዓተ መንግሥት ፓርላሜንታዊ ነው፡፡
አንቀጽ 46 - የፌዴራል ክልሎች
- የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡
- ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው፡፡
አንቀጽ 47 - የፌዴራል መንግሥት አባላት
- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት የሚከተሉት ናቸው፡፡
- የትግራይ ክልል
- የአፋር ክልል
- የአማራ ክልል
- የኦሮሚያ ክልል
- የሱማሌ ክልል
- የቤንሻንጉል/ጉሙዝ ክልል
- የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል
- የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል
- የሐረሪ ሕዝብ ክልል
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከቱት ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፡፡
- የማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ሥራ ላይ የሚውለው፤
ሀ) የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልል ምክር ቤት ሲቀርብ፤
ለ) ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፤
ሐ) ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔሩ በብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፤
መ) የክልል ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብ፤
ሠ) በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክሪሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው፡፡
- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት እኩል መብትና ሥልጣን አላቸው፡፡
አንቀጽ 48 - የአከላለል ለውጦች
- የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወሰናል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የቀረበ ጉዳይ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
አንቀጽ 49 - ርዕሰ ከተማ
- የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡
- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት ይሆናል፡፡
- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወከላሉ፡፡
- የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፣ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
ምዕራፍ አምስት
የሥልጣን አወቃቀር እና ክፍፍል
አንቀጽ 50 - ስለ ሥልጣን አካላት አወቃቀር
- የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡
- የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች የሕግ አወጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡
- የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው። የክልል ከፍተኛ የሥልጣን አካል የክልሉ ምክር ቤት ነው፤ ተጠሪነቱም ለወከለው ክልል ሕዝብ ነው፡፡
- ክልሎች፤ በክልልነትና ክልሎች አስፈላጊ ሆነው በሚያገኙአቸው የአስተዳደር እርከኖች ይዋቀራሉ። ሕዝቡ በዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች በቀጥታ ይሳተፍ ዘንድ ለዝቅተኛ እርከኖች በቂ ሥልጣን ይሰጣል፡፡
- የክልል ምክር ቤት በክልል ሥልጣን ስር በሆኑ ጉዳዩች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል ነው። ይህንን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያዘጋጃል፣ ያጸድቃል፣ ያሻሽላል፡፡
- የክልል መስተዳድር የክልል ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ነው፡፡
- የክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡
- የፌዴራሉ መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በዚህ ሕገ መንግሥት ተወስኗል። ለፌዴራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት። ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራሉ መንግሥት መከበር አለበት፡፡
- የፌዴራል መንግሥት በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 51 ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባሮች እንዳስፈላጊነቱ ለክልሎች በውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡
አንቀጽ 51 - የፌዴራል መንግሥት ሥልጣንና ተግባር
- ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል፤ ይከላከላል፡፡
- የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፤ ያስፈጽማል፡፡
- የጤና፣ የትምህርት፣ የባሕልና ታሪካዊ ቅርስ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሀገር አቀፍ መመዘኛዎችና መሠረታዊ የፖሊሲ መለኪያዎችን ያወጣል ያስፈጽማል፡፡
- የሀገሪቱን የፋይናንስ፣ የገንዘብ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ያወጣል ያስፈጽማል፡፡
- የመሬት፣ የተፈጥሮ ሀብትና የታሪክ ቅርሶች አጠቃቀምና ጥበቃን በተመለከተ ሕግ ያወጣል፡፡
- የሀገርና የሕዝብ የመከላከያና የደህንነት እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፡፡
- ብሔራዊ ባንክን ያስተዳድራል፤ ገንዘብ ያትማል፤ ይበደራል፤ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ልውውጥን ይቆጣጠራል። ክልሎች ከውስጥ ምንጮች ሰለሚበደሩበት ሁኔታ ሕግና መመሪያ ያወጣል፡፡
- የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን ይወስናል፤ ፖሊሲውንም ያስፈጽማል፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ይዋዋላል፤ ያጸድቃል፡፡
- የአየር፣ የባቡር፣ የባሕር መጓጓዣ፣ የፖስታና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች እንደዚሁም ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ክልሎችን የሚያገናኙ አውራ መንገዶችን ያስፋፋል፣ ያስተዳድራል፣ ይቆጣጠራል፡፡
- ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጡት የገቢ ምንጮች ክልል ግብርና ቀረጥ ይጥላል፤ ያስተዳድራል፤ የፌዴራል መንግሥት በጀት ያረቃል፤ ያጸድቃል፤ ያስተዳድራል፡፡
- ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ክልሎችን የሚያሰተሳስሩ ወይም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ወንዞችና ሃይቆችን አጠቃቀም ይወሰናል፣ ያስተዳድራል፡፡
- በክልሎች መካከል የሚደረግን የንግድ ግንኙትና የውጭ ንግድን ይመራል፤ ይቆጣጠራል፡፡
- በፌዴራል መንግሥት ገንዘብ የተቋቋሙ አንድ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚሸፍኑ የአገልግሎት ተቋሞችን ያስተዳድራል፤ ያስፋፋል፡፡
- ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሠረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል፡፡
- በዚህ ሕገ መንግሥት የተረጋገጡትን የፖለቲካ መብቶች ለማስፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ሕጎች ያወጣል፡፡
- በሀገሪቱ በአጠቃላይም ሆነ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፣ አዋጁን ያነሳል፡፡
- የዜግነት ጥያቄ ይወስናል፡፡
- የኢምግሬሽንና የፓስፖርት ወደ ሀገር የመግቢያና የመውጫ ጉዳዮችን፤ ስለስደተኞችና ስለ ፖለቲካ ጥገኝነት ይወሰናል፤ ይመራል፡፡
- የፈጠራና የድርሰት መብቶችን ይፈቅዳል፤ ይጠብቃል፡፡
- አንድ ወጥ የመለኪያ ደረጃዎችና የጊዜ ቀመር ያወጣል፡፡
- የጦር መሣሪያ ሰለመያዝ ሕግ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 52 - የክልል ሥልጣንና ተግባር
- በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራሉ መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የክልሎች ሥልጣንና ተግባር የሚከተሉትን ያጠቃልላል፤
ሀ) ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራል፤ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል፤ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፤ ይከላከላል፤
ለ) የክልል ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎችን ያወጣል፣ ያስፈጽማል፤
ሐ) የክልሉን የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፣ ያስፈጽማል፤
መ) የፌዴራሉ መንግሥት በሚያወጣው ሕግ መሠረት መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ያስተዳድራል፤
ሠ) ለክልሉ በተወሰነው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ ይጥላል፤ ይሰበስባል፤ የክልሉን በጀት ያወጣል፤ ያስፈጽማል፤
ረ) የክልሉን መስተዳድር ሠራተኞች አስተዳደርና የሥራ ሁኔታዎች በተመለከተ ሕግ ያወጣል፤ ያሰፈጽማል፤ ሆኖም ለአንድ የሥራ መደብ የሚያስፈልጉ የትምህርት፣ የሥልጠናና የልምድ መመዘኛዎች ከአጠቃላይ የሀገሪቱ መመዘኛዎች ጋር የተቀራረቡ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡
ሰ) የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፣ ይመራል፣ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃል፡፡
ምዕራፍ ስድስት
ስለፌዴራሉ መንግሥት ምክር ቤቶች
አንቀጽ 53 - የፌዴራል መንግሥት ምክር ቤቶች
የፌዴራሉ መንግሥት ሁለት ምክር ቤቶች ይኖሩታል፤ እነዚህም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ናቸው፡፡
ክፍል አንድ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
አንቀጽ 54 - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ፡፡
- የምክር ቤቱ አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ። የተለየ ውክልና ያስፈልጋቸዋል ተብሎ የታመነባቸው አናሳ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ይሆናሉ። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
- የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር የሕዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት በማድረግ ከ550 የማይበልጥ ሆኖ ከዚህ ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች ከ209 የማያንስ መቀመጫ ይኖራቸዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይደነጋጋሉ፡፡
- የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዥነታቸውም፤
ሀ) ለሕገ መንግሥቱ፤
ለ) ለሕዝቡ፤ እና
ሐ) ለሕሊናቸው፤
ብቻ ይሆናል፡፡
- ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰሰም። አስተዳደራዊ እርምጃም አይወስድበትም፡፡
- ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም፡፡
- ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሠረት ከምክር ቤት አባልነቱ ይወገዳል፡፡
አንቀጽ 55 - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት ለፌዴራሉ መንግሥት በተሰጠው የሥልጣን ክልል ሕጎችን ያወጣል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከተው አጠቃላይ ድንጋጌ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ሕግ ያወጣል፤
ሀ) የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት፤ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ ወይም ከአንድ ክልል በላይ የሚያስተሳስሩ ወንዞችና ሃይቆች አጠቃቀምን በተመለከተ፤
ለ) በክልሎች መካከል የሚኖረውን የንግድ ልውውጥ፤ እንዲሁም የውጭ ንግድ ግንኙነትን በተመለከተ፤
ሐ) የአየር፣ የባቡርና የባሕር መጓጓዣ፤ የፖስታና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን እንዲሁም ሁለት ወይም ከሁለት በላይ ክልሎችን የሚያገናኙ አውራ መንገዶችን በተመለከተ፤
መ) በዚህ ሕገ መንግሥት የተደነገጉትን የፖለቲካ መብቶች አፈጻጸምን እንዲሁም ምርጫን በተመለከተ፤
ሠ) የዜግነት መብትን፤ የኢምግሬሽን፤ የፓስፖርትን፤ ወደ ሀገር የመግቢያና የመውጫ ጉዳዮችን እንዲሁም የስደተኞችና የፖለቲካ ጥገኝነት ጉዳዮችን በተመለከተ፤
ረ) አንድ ወጥ የመጠን መለኪያ ደረጃና የጊዜ ቀመርን በተመለከተ፤
ሰ) የፈጠራና የሥነጥበብ መብቶችን በተመለከተ፤
ሸ) የጦር መሣሪያ መያዝን በተመለከተ፡፡
- የሠራተኛ ጉዳይ ሕግ ያወጣል፡፡
- የንግድ ሕግ(ኮድ)ያወጣል፡፡
- የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ያወጣል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ክልሎች በፌዴራሉ መንግሥት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በግልጽ ባልተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡
- አንድ የኢኮኖሚ ማኀበረሰብን ለመፍጠር ሲባል በፌዴራል መንግሥት ሕግ እንዲወጣላቸው የሚያስገድዱ ለመሆናቸው በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የታመነባቸው የፍትሐብሔር ሕጎችን ያወጣል፡፡
- የፌዴራል መንግሥት፤ የሀገርና የሕዝብ መከላከያ፤ የደህንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን ይወስናል። በሥራ አፈጻጸማቸው ረገድ የሚታዩ መሠረታዊ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችና የሀገርን ደህንነት የሚነኩ ጉዳዮች ሲከሰቱ ያጣራል፤ አስፈላጊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ያደርጋል፡፡
- በአንቀጽ 93 በተመለከተው መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፣ የሕግ አስፈጻሚው የሚያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተመልክቶ ይወስናል፡፡
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያቀርብለት የሕግ ረቂቅ መሠረት የጦርነት አዋጅ ያውጃል፡፡
- የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊ፣ የልማትን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን፤ የፋይናንስና የገንዘብ ፖሊሲን ያጸድቃል፤ ገንዘብን፤ የብሔራዊ ባንክ አስተዳደርን፤ የውጭ ምንዛሪንና ልውውጥን በተመለከተ ዝርዝር ሕግ ያወጣል፡፡
- ለፌዴራል መንግሥት በተከለለው የገቢ ምንጭ ክልል ግብርና ታክስ ይጥላል። የፌዴራል መንግሥት በጀት ያጸድቃል፡፡
- የሕግ አስፈጻሚው አካል የሚዋዋላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያጸድቃል፡፡
- የፌዴራል መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኞችን፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላትን፤ የኮሚሽነሮችን፤ ዋናው ኦዲተርን እንዲሁም የሌሎች ሹመታቸው በምክር ቤቱ መጽደቅ ያለበትን ባለሥልጣኖች ሹመት ያጸድቃል፡፡
- የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያቋቁማል፤ ሥልጣንና ተግባሩን በሕግ ይወስናል፡፡
- የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን ያቋቁማል፤ ተቋሙን የሚመሩ አባላትን ይመርጣል፤ ይሰይማል። ሥልጣንና ተግባሩን በሕግ ይወስናል፡፡
- በማንኛውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይችል ሲቀር፤ በራሱ አነሳሽነትና ያለክልሉ ፈቃድ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፤ በተደረሰበት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመሪያ ይሰጣል፡፡
- ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት ባለሥልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ሥልጣን አለው፡፡
- ለሕግ አስፈጻሚው አካል በተሰጠ ማንኛውም ሥልጣን ላይ የምክር ቤቱ አባላት በአንድ ሦስተኛ ድምፅ ሲጠይቁ ምክር ቤት ይወያያል። ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው፡፡
- ምክር ቤቱን የሚመራ አፈጉባዔና ምክትል አፈጉባዔ ይመርጣል፤ ለምክር ቤቱ ሥራ የሚያስፈልጉትን ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያዋቅራል፡፡
አንቀጽ 56 - የፖለቲካ ሥልጣን
በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል/ ያደራጃሉ፤ ይመራል/ይመራሉ፡፡
አንቀጽ 57 - ስለሕግ አጸዳደቅ
ምክር ቤቱ መክሮ የተሰማማበት ሕግ ለሀገሪቱ ኘሬዚዳንት ለፊርማ ይቀርባል፤ ኘሬዚዳንቱ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ይፈርማል። ኘሬዚዳንቱ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ካልፈረመ ሕጉ በሥራ ላይ ይውላል፡፡
አንቀጽ 58 - የምክር ቤቱ ስብሰባና የሥራ ዘመን
- ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከተገኙ ምልዓተ ጉባዔ ይኖራል፡፡
- የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እሰከ ሰኔ ሠላሳ ነው፡፡ በመካከሉም ምክር ቤቱ በሚወስነው ጊዜ የአንድ ወር ዕረፍት ይኖረዋል፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሒዶ ይጠናቀቃል፡፡
- ምክር ቤቱ ዕረፍት ላይ በሚሆንበት ጊዜ የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል። ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ስብሰባ እንዲጠራ ከጠየቁ አፈጉባዔው ስብሰባ የመጥራት ግዴታ አለበት፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች በግልጽ ይካሔዳሉ፤ ሆኖም በምክር ቤቱ አባላት ወይም በፌዴራል የሕግ አሰፈጻሚ አካል በዝግ ስብሰባ እንዲደረግ ከተጠየቀና ከምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ከደገፉት ዝግ ስብሰባ ሊደረግ ይችላል፡፡
አንቀጽ 59 - የምክር ቤቱ ውሳኔዎችና የሥነ ሥርዓት ደንቦች
- በዚህ ሕገ መንግሥት በግልጽ በተለይ ካልተደነገገ በስተቀር ማናቸውም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በምክር ቤቱ አባላት የአብላጫ ድምፅ ነው፡፡
- ምክር ቤቱ ስለ አሠራሩና ስለ ሕግ አወጣጡ ሂደት ደንቦችን ያወጣል፡፡
አንቀፅ 60 - ስለምክር ቤቱ መበተን
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሔድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፡፡
- በጣምራ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጀቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክር ቤቱ የነበራቸውን አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተበትኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉ የፖለቲካ ድርጀቶች ሌላ ጣምራ መንግሥት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመሥረት እንዲቻል ኘሬዚዳንቱ የፖለቲካ ድርጀቶችን ይጋብዛል። የፖለቲካ ድርጀቶቹ አዲስ መንግሥት ለመፍጠር ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻሉ ምክር ቤቱ ተበትኖ አዲስ ምርጫ ይደረጋል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ወይም 2 መሠረት ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ ምርጫ መደረግ አለበት፡፡
- ምርጫው በተጠናቀቀ በሠላሳ ቀናት ውስጥ አዲስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን ይጀምራል፡፡
- የሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከተበተነ በኋላ ሀገሪቱን የሚመራው ሥልጣን ይዞ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት ወይም የፖለቲካ ድርጀቶች ጣምራ የዕለት ተዕለት የመንግሥት ሥራ ከማከናወንና ምርጫ ከማካሔድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ሕጎችን መሻርና ማሻሻል አይችልም፡፡
ክፍል ሁለት - የፌዴሬሽን ምክር ቤት - አንቀጽ 61 - የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት
- የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የሚልኩዋቸው አባላት የሚወክሉበት ምክር ቤት ነው፡፡
- እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፤ በተጨማሪም የብሔር ወይም ብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል፡፡
- የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በክልል ምክር ቤቶች ይመረጣሉ፤ የክልል ምክር ቤቶች በራሳቸው ወይም በቀጥታ በሕዝብ እንዲመረጡ በማድረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል እንዲወከል ያደርጋሉ፡፡
አንቀጽ 62 - የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር
- ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን ያደራጃል፡፡
- የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብትን በተመለከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ላይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይወስናል፡፡
- በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው የሕዝቦች እኩልነትና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር ያደረጋል፡፡
- ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በጣምራ የተሰጡትን ሥልጣኖች ያከናውናል፡፡
- በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ ይፈልጋል፡፡
- የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር ይወሰናል፡፡
- በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ይለያል፡፡
- ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል፡፡
- የምክር ቤቱን የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች ያቋቁማል፡፡
- ምክር ቤቱ የራሱን አፈጉባዔና ምክትል አፈጉባዔ ይመርጣል፤ የራሱን የሥራ አፈጻጸምና የውስጥ አሰተዳደር ደንብ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 63 - የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መብት
- ማንኛውም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል በማናቸውም የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በሚሰጠው አስተያየት ወይም ድምፅ ምክንያት አይከሰስም፤ አስተዳደራዊ እርምጃም አይወሰድበትም፡፡
- ማንኛውም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፣ በወንጀልም አይከሰስም፡፡
አንቀጽ 64 - ውሳኔዎችና የሥነ ሥርዓት ደንቦች
- የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ምልዓተ ጉባዔ የሚኖረው ከአባላቱ ሁለት ሦስተኛው የተገኙ እንደሆነ ነው። ማናቸውም ውሳኔ የሚያልፈው ስብሰባ ላይ ከተገኙት የምክር ቤቱ አባላት ከግማሽ በላይ ድምፅ ሲደገፍ ብቻ ነው፡፡
- አባላት ድምፅ መስጠት የሚችሉት በአካል ሲገኙ ብቻ ነው፡፡
አንቀጽ 65 - ስለ በጀት
የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጀቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ያስወስናል፡፡
አንቀጽ 66 - የምክር ቤቱ አፈጉባዔ ሥልጣን
- የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አፈጉባዔ የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ይመራል፡፡
- ምክር ቤቱን በመወከል ጠቅላላ የአስተዳደር ሥራዎችን ይመራል፡፡
- ምክር ቤቱ በአባሎቹ ላይ የወሰነውን የዲስኘሊን እርምጃ ያስፈጽማል፡፡
አንቀጽ 67 - ስብሰባና የሥራ ዘመን
- የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰበሰባል፡፡
- የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 68 - በሁለቱም ምክር ቤቶች አባል መሆን የማይቻል ስለመሆኑ
ማንኛውም ሰው በአንድ ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል ሊሆን አይችልም፡፡
ምዕራፍ ሰባት
ስለ ሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት
አንቀጽ 69 - ስለኘሬዚዳንቱ
ኘሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ርዕስ ብሔር ነው፡፡
አንቀጽ 70 - የኘሬዚዳንቱ አሰያየም
- ለኘሬዚዳንትነት እጩ የማቅረብ ሥልጣን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡
- የቀረበው እጩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከተደገፈ ኘሬዚዳንት ይሆናል፡፡
- የምክር ቤት አባል ኘሬዚዳንት ሆኖ ከተመረጠ የተወከለበትን ምክር ቤት ወንበር ይለቃል፡፡
- የኘሬዚዳንቱ የሥራ ዘመን ስድስት ዓመት ይሆናል። አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለኘሬዚዳንትነት ሊመረጥ አይችልም፡፡
- የሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት ምርጫ በዚሀ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ከጸደቀ በኋላ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የጋራ ስብሰባው በሚወስነው ጊዜ ስብሰባው ፊት ለሕገ መንግሥቱና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለውን ታማኝነት በሚቀጥሉት ቃላት ይገልጻል፡፡
"እኔ ............. በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኘሬዚዳንት በመሆን ሥራዬን ስጀምር የተጣለብኝን ከፍተኛ ኃላፊነት በታማኝነት ለመፈጸም ቃል እገባለሁ።"
አንቀጽ 71 - የኘሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር
- የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑን ምክር ቤት ዓመታዊ የጋራ ስብሰባ ይከፍታል፡፡
- በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቃቸውን ሕጎችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ያውጃል፡፡
- ሀገሪቷን በውጭ ሀገሮች የሚወክሉትን አምባሳደሮችና ሌሎች መልዕክተኞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ይሾማል፡፡
- የውጭ ሀገር አምባሳደሮችንና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ ይቀበላል፡፡
- በሕግ መሠረት ኒሻኖችና ሽልማቶችን ይሰጣል፡፡
- በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕግ በተወሰነው መሠረት ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጎችን ይሰጣል፡፡
- በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደርጋል፡፡
ምዕራፍ ስምንት
የሕግ አስፈጻሚ አካል
አንቀጽ 72 - ስለ አሰፈጻሚነት ሥልጣን
- የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡
- ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥት ተግባራቸው በጋራ ለሚሰጡት ውሳኔ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
- በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሌላ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ነው፡፡
አንቀጽ 73 - የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰያየም
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል፡፡
- በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ያገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች የመንግሥት ሥልጣን ይረከባል/ይረከባሉ፡፡
አንቀጽ 74 - የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ተግባር
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ርዕስ መስተዳድር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነው፡፡
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባሎችን ከሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ወይም ለሥራው ብቃት ካላቸው ሌሎች ግለሰቦች መካከል ለሕዘብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርቦ ሹመታቸውን ያስጸድቃል፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፡፡
- የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይመራል፣ ያስተባብራል፣ ይወክላል፡፡
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ይከታተላል፡፡
- የሀገሪቱን የውጭ ፖሊሲ በበላይነት ያስፈጽማል፡፡
- ኮሚሸነሮችን፣ የማዕከላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንትና ምክትል ኘሬዚዳንትን እና ዋና ኦዲተርን መርጦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን ያሰጸድቃል፡፡
- የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብቃት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 እና 7 ከተዘረዘሩት ውጭ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሲቪል ሹመቶችን ይሰጣል፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው ሕግ ወይም በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን ለኘሬዚዳንቱ አቅርቦ ያሰጣል።
- ስለ ሀገሪቱ ሁኔታ፣ በመንግሥት ስለተከናወኑ ተግባራትና ስለወደፊት ዕቅዶች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየወቅቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
- በዚህ ሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጎች የተሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናል፡፡
- ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፣ ያስከብራል፡፡
አንቀጽ 75 - ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣
ሀ) በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፤
ለ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶት ይሠራል፡፡
ሐ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል፡፡
አንቀጽ 76 - የሚኒስትሮች ምክር ቤት
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሚኒስትሮችና በሕግ በሚወሰን መሠረት ሌሎች አባሎች የሚገኙበት ምክር ቤት ነው፡፡
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሚወሰነው ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ ነው፡፡
አንቀጽ 77 - የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጡ ሕጎችና የተሰጡ ውሳኔዎች በሥራ መተርጎማቸውን ያረጋግጣል፣ መመሪያዎችን ይሰጣል፡፡
- የሚኒስቴሮችንና በቀጥታ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑ ሌሎች የመንግሥት አካላትን አደረጃጀት ይወስናል፣ ሥራቸውን ያስተባብራል፣ ይመራል፡፡
- የፌዴራሉን መንግሥት ዓመታዊ በጀት ያዘጋጃል፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፣ ሲጸድቅም ተግባራዊነቱን ያረጋግጣል፡፡
- የገንዘብና የፋይናንስ ፖሊሲን ተግባራዊነት ያረጋግጣል፣ ብሔራዊ ባንክን ያስተዳድራል፣ ገንዘብ ያትማል፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ይበደራል፣ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ልውውጥን ይቆጣጠራል፡፡
- የፈጠራና የኪነ ጥበብ መብቶችን ያስጠብቃል፡፡
- የኢኮኖሚያዊ፣ የማኀበራዊና የልማት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን ይነድፋል፣ ያስፈጽማል፡፡
- አንድ ወጥ የመለኪያ ደረጃዎችንና የጊዜ ቀመር ያወጣል፡፡
- የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያወጣል፣ ያስፈጽማል፡፡
- ሕግና ሥርዓት መከበሩን ያረጋግጣል፡፡
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፤ በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው የጊዜ ወሰን ውስጥ፣ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስጸድቃል፡፡
- የጦርነት ጉዳዮችን ጨምሮ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ የሕግ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡትን ሌሎች ተግባሮች ያከናውናሉ፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚሰጠው ሥልጣን መሠረት ደንቦችን ያወጣል፡፡
ምዕራፍ ዘጠኝ
ስለ ፍርድ ቤቶች አወቃቀርና ሥልጣን
አንቀጽ 78 - ስለ ነፃ የዳኝነት አካል
- ነፃ የዳኝነት አካል በዚህ ሕገ መንግሥት ተቋቁሟል፡፡
- የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የዳኝነት አካል የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይሆናል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ሆነ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሀገሪቱ በሙሉ ወይም በከፊል እንዲደራጅ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሊወሰን ይችላል። ጉዳዩ በዚህ አኳኋን ካልተወሰነ የፌዴራል ከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ለክልል ፍርድ ቤቶች ተሰጥቷል፡፡
- ክልሎች፤ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች፣ የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና የክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ይኖራቸዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
- የዳኝነት ሥልጣንን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ወይም በሕግ የመዳኘት ሥልጣን ከተሰጠው ተቋም ውጭ የሚደረግ በሕግ የተደነገገን የዳኝነት ሥርዓት የማይከተል ልዩ ፍርድ ቤት ወይም ጊዜያዊ ፍርድ ቤት አይቋቋምም፡፡
- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የሃይማኖትና የባሕል ፍርድ ቤቶችን ሊያቋቁሙ ወይም እውቅና ሊሰጡ ይችላሉ። ይህ ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት በመንግሥት እውቅና አግኝተው ሲሰራባቸው የነበሩ የሃይማኖቶችና የባሕል ፍርድ ቤቶች በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት እውቅና አግኝተው ይደራጃሉ።
አንቀፅ 79 - የዳኝነት ሥልጣን
- በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡
- በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተጽዕኖ ነፃ ነው፡፡
- ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በመሉ ነፃነት ያከናውናሉ። ከሕግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም፡፡
- ማንኛውም ዳኛ ከዚህ በታች በተመለከቱት ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር በሕግ ከተወሰነው የጡረታ ዕድሜ ከመድረሱ በፊት ከፈቃዱ ውጭ ከዳኝነት ሥራው አይነሳም፤
ሀ) የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በዳኞች የዲሲፕሊን ሕግ መሠረት ጥፋት ፈጽሟል ወይም ጉልህ የሆነ የሥራ ችሎታና ቅልጥፍና አንሶታል ብሎ ሲወሰን፣ ወይም
ለ) በህመም ምክንያት ተግባሩን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን አይችልም ብሎ ሲወስን፣ እና
ሐ) የጉባዔው ውሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በክልል ምክር ቤቶች ከግማሽ በላይ ድምፅ ሲጸድቅ፡፡
- የማንኛውም ዳኛ የጡረታ መውጫ ጊዜ አይራዘምም፡፡
- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌዴራሉን መንግሥት የዳኝነት አካል የሚያስተዳድርበትን በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስወስናል፣ ሲፈቀድም በጀቱን ያስተዳድራል፡፡
- የክልል የዳኝነት አካሎች በጀት በየክልሉ ምክር ቤቶች ይመደባል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራሉን የከፍተኛና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ደርበው ለሚሠሩት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችና የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የበጀት ማካካሻ ይሰጣል፡፡
አንቀጽ 80 - የፍርድ ቤቶች ጣምራነትና ሥልጣን
- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
- የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ጉዳይ ላይ የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል። በተጨማሪ የፌዴራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተጠቀሰው ቢኖርም፣
ሀ) የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን ይኖረዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
ለ) የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን በክልል ጉዳዮች የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን ይኖረዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
- የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በክልሉ ከሚኖረው የዳኝነት ሥልጣን በተጨማሪ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
- የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣኑ መሠረት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርበው ይግባኝ በክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይታያል፡፡
- የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌዴራል የዳኝነት ሥልጣኑ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርበው ይግባኝ በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይታያል፡፡
አንቀጽ 81 - ስለዳኞች አሿሿም
- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንትና ምክትል ኘሬዚዳንት በፌዴራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡
- ሌሎች የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን በተመለከተ በፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የቀረቡለትን እጩዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያሾማል፡፡
- የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንትና ምክትል ኘሬዚዳንት በክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቅራቢነት በክልል ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡
- የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቅራቢነት በክልሉ ምክር ቤት ይሾማሉ። የክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የዳኞችን ሹመት ለምክር ቤቱ ከማቅረቡ በፊት የፌዴራሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በእጩዎቹ ላይ ያለውን አስተያየት መጠየቅና አስተያየቱን ከራሱ አስተያየት ጋር በማያያዝ ለክልሉ ምክር ቤት የማቅረብ ኃላፊነት አለበት። የፌዴራሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አስተያየቱን በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ካላቀረበ የክልሉ ምክር ቤት ሹመቱን ያጸድቃል፡፡
- የክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች በክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አቅራቢነት በክልሉ ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡
- በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ዳኞች የዲሲፕሊንና የዝውውር ጉዳይ በሚመለከተው የዳኞች አስተደደር ጉባዔ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 82 - የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አወቃቀር
- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በዚህ ሕገ መንግሥት ተቋቁሟል፡፡
- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አሥራ አንድ አባላት ይኖሩታል። አባላቱም የሚከተሉት ናቸው፤
ሀ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት ሰብሳቢ፤
ለ) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ኘሬዚዳንት፣ ምክትል ሰብሳቢ፤
ሐ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ኘሬዚዳንት የሚሾሙ በሙያ ብቃታቸውና በሥነምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎች፤
መ) የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ከአባላቱ መካከል የሚወክላቸው ሦስት ሰዎች፡፡
- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሥራ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ የሚያስችለው መዋቅር ሊዘረጋ ይችላል፡፡
አንቀጽ 83 - ሕገ መንግሥቱን ስለመተርጎም
- የሕገ መንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል፡፡
- የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርብለት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ላይ በሰላሳ ቀናት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፡፡
አንቀጽ 84 - የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሥልጣንና ተግባር
- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን ይኖረዋል። በሚያደርገው ማጣራት መሠረት ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሣብ ያቀርባል፡፡
- በፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ሕጎች ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳና ጉዳዩም በሚመለከተው ፍርድ ቤት ወይም በባለጉዳዩ ሲቀርብለት መርምሮ ለመጨረሻ ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ያቀርባል፡፡
- በፍርድ ቤቶች የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ሲነሳ፣
ሀ) ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሳያገኘው ሲቀር ጉዳዩን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ይመልሳል፤ በአጣሪ ጉባዔው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ባለጉዳይ ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ ምከር ቤት በይግባኝ ማቅረብ ይችላል፡፡
ለ) የትርጉም ጥያቄ መኖሩን ያመነበት እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የሚሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመጨረሻ ውሳኔ ያቀርባል፡፡
- የሚመራበትን ሥነ ሥርዓት አርቅቆ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ያቀርባል፣ ሲፈቀድም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
ምዕራፍ አሥር
የብሔራዊ ፖሊሲ መርሆዎችና ዓላማዎች
አንቀጽ 85 - ዓላማዎች
- ማንኛውም የመንግሥት አካል ሕገ መንግሥቱን፣ ሌሎች ሕጎችንና ፖሊሲዎችን ሥራ ላይ ሲያውል በዚህ ምዕራፍ በተመለከቱት መርሆዎችና ዓላማዎች ላይ መመሥረት አለበት፡፡
- በዚህ ምዕራፍ ውስጥ "መንግሥት" ማለት እንደየሁኔታው የፌዴራል መንግሥት ወይም የክልል መስተዳድሮች ማለት ይሆናል፡፡
አንቀጽ 86 - የውጭ ግንኙነት መርሆዎች
- የኢትዮጵያን ሕዝቦች ጥቅም የሚያስጠብቅና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስከብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማራመድ፡፡
- የመንግሥታትን ሉዓላዊነትና እኩልነት ማክበር፣ በሌሎች ሀገሮች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አለመግባት፡፡
- የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ጥቅምና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ፡፡
- የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩና የሕዝቦቿን ጥቅም የማይፃረሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶችን ማክበር፡፡
- ከጎረቤት ሀገሮችና ከሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች ጋር በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ኀብረትና የሕዝቦች ወንድማማችነትን ማጎልበት፡፡
- በሀገሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ፡፡
አንቀጽ 87 - የመከላከያ መርሆዎች
- የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦች እና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅዖ ያካተተ ይሆናል፡፡
- የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ይሆናል፡፡
- የመከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፡፡
- የመከላከያ ሠራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ ይሆናል፡፡
- የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል፡፡
አንቀጽ 88 - ፖለቲካ ነክ ዓላማዎች
- መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ላይ በመመሥረት ሕዝቡ በሁሉም ደረጃዎች ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት፡፡
- መንግሥት የብሔሮችን፣ የብሔረሰቦችን፣ የሕዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚህ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸው እኩልነት አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት፡፡
አንቀጽ 89 - ኢኮኖሚ ነክ ዓላማዎች
- መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገሪቱ የተጠራቀመ ዕውቀትና ሀብት ተጠቃሚዎች የሚሆኑበትን መንገድ የመቀየስ ኃላፊነት አለበት፡፡
- መንግሥት የኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል እኩል ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግና ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡
- የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ እንዳይደርስ መከላከልና አደጋው ሲደርስም ለተጎጂው እርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ ማድረግ፡፡
- በእድገት ወደኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች መንግሥት ልዩ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
- መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን በሕዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለሕዝቡ የጋራ ጥቅምና እድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
- የሀገር ልማት ፖሊሲዎችና ኘሮግራሞች በሚዘጋጁበት ወቅት መንግሥት ሕዝቡን በየደረጃው ማሳተፍ አለበት። የሕዝብንም የልማት እንቅስቃሴዎች መደገፍ አለበት፡፡
- መንግሥት በሀገር ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት የሚሳተፉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት፡፡
- መንግሥት የሠራተኛውን ሕዝብ ጤንነት ደህንነትና የኑሮ ደረጃ ለመጠበቅ መጣር አለበት፡፡
አንቀጽ 90 - ማኀበራዊ ነክ ዓላማዎች
- የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት የንጹህ ውሃ፣ የመኖሪያ፣ የምግብና የማኀበራዊ ዋስትና እንዲኖረው ይደረጋል፡፡
- ትምህርት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ አመለካከቶች እና ከባሕላዊ ተፅዕኖዎች ነፃ በሆነ መንገድ መካሔድ አለበት፡፡
አንቀጽ 91 - ባሕል ነክ ዓላማዎች
- መንግሥት መሠረታዊ መብቶችንና ሰብዓዊ ክብርን ዴሞክራሲንና ሕገ መንግሥቱን የማይቃረኑ ባሕሎችና ልማዶች በእኩልነት እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ የመርዳት ኃላፊነት አለበት፡፡
- የሀገር የተፈጥሮ ሀብቶችንና የታሪክ ቅርሶችን መጠበቅ የመንግሥትና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው፡፡
- መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ኪነጥበብን ሳይንስና ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ግዴታ አለበት፡፡
አንቀጽ 92 - የአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ዓላማዎች
- መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት፡፡
- ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአካባቢውን ደህንነት የማያናጋ መሆን አለበት፡፡
- የሕዝብን የአካባቢ ደህንነት የሚመለከት ፖሊሲና ኘሮግራም በሚነደፍበትና ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የሚመለከተው ሕዝብ ሁሉ ሀሳቡን እንዲገልጽ መደረግ አለበት፡፡
- መንግሥትና ዜጎች አካባቢያቸውን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው፡፡
ምዕራፍ አሥራ አንድ
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
አንቀጽ 93 - ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
- ሀ) የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፡፡
ለ) የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ። ዝርዝሩ ክልሎች ይህን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ በሚያወጧቸው ሕገ መንግሥቶች ይወሰናል፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1(ሀ) መሠረት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤
ሀ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል፡፡
ለ) ከላይ በንዑስ አንቀጽ(ሀ) ስር የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጁ በታወጀ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡
- በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው እስከ ስድስት ወራት ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደረግ ይችላል፡፡
- ሀ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሠረት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
ለ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ፣ እስከማገድ ሊደርስ የሚችል ነው፡፡
ሐ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
- በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል፡፡ ቦርዱ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚጸድቅበት ጊዜ ይቋቋማል፡፡
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች አሉት፤
ሀ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፣
ለ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፣
ሐ) ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሀሳብ መስጠት፣
መ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፣
ሠ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ማቅረብ፡፡
አንቀጽ 94 - የፋይናንስ ወጪን በሚመለከት
- የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች በሕግ የተሰጧቸውን ኃላፊነቶችና ተግባሮች ለማከናወን የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በየበኩላቸው ይሸፍናሉ፣ ሆኖም ማናቸውም ክልል በውክልና ለሚፈጽመው ተግባር የሚያስፈልገው ወጪ ሌላ ስምምነት ከሌለ በቀር ውክልናውን በሰጠው ወገን ይሸፈናል፡፡
- የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የተመጣጠነ እድገት እንቅፋት ካልሆነ በስተቀር ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለመልሶ ማቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለክልሎች ብድርም ሆነ እርዳታ ሊሰጥ ይችላል። የፌዴራሉ መንግሥት ክልሎች ለሚያስፈልጋቸው ወጪ የሚያደርገውን ድጎማ በሚመለከት ኦዲትና ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
አንቀጽ 95 - የፋይናንስ ገቢን በሚመለከት
የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሚዋቀረውን የፌዴራል አደረጃጀት የተከተለ የገቢ ክፍፍል ያደርጋሉ፡፡
አንቀጽ 96 - የፌዴራል መንግሥት የታክስና የግብር ሥልጣን
- የፌዴራል መንግሥት በወጪና ገቢ ዕቃዎች ላይ የጉምሩክ ቀረጥ፣ ታክስና ሌሎች ክፍያዎች ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
- በፌዴራል መንግሥትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተቀጣሪዎች ላይ የሥራ ግብር ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
- በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት ሥር በሆኑ የልማት ድርጅቶች ላይ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የሥራ ግብር፣ የሽያጭና የኤክሳይስ ታክስ ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
- በብሔራዊ የሎተሪ እና ሌሎች የዕድል ሙከራ ገቢዎች ላይ ታክስ ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
- በአየር፣ በባቡርና በባሕር ትራንስፖርት ገቢዎች ላይ ታክስ ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
- በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት ሥር በሚገኙ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ገቢ ላይ ግብር ይጥላል፣ ይሰበስባል፣ ኪራይ ይወስናል፡፡
- የፌዴራል መንግሥት አካላት ከሚሰጧቸው ፈቃዶችና፣ አገልግሎቶች፣ የሚመነጩ ክፍያዎችን ይወስናል፣ ይሰበስባል፡፡
- የሞኖፖል ታክስ ይጥላል፣ ይሰበስባል፡፡
- የፌዴራል የቴምብር ሽያጭ ቀረጥ ይጥላል፣ ይሰበሰባል፡፡
አንቀጽ 97 - የክልል መስተዳድሮች የታክስና የግብር ሥልጣን
- ክልሎች በክልል መስተዳድርና በድርጅት ተቀጣሪዎች ላይ የሥራ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበሰባሉ፡፡
- የመሬት መጠቀሚያ ክፍያ ይወሰናሉ፣ ይሰበሰባሉ፡፡
- በግል የሚያርሱና በህብረት ሥራ ማኀበራት በተደራጁ ገበሬዎች ላይ የእርሻ ሥራ ገቢ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
- በክልሉ በሚገኙ ግለሰብ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ትርፍ ግብርና የሽያጭ ታክስ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
- በክልሉ ውስጥ በውሀ ላይ ከሚደረግ ትራንስፖርት በሚገኝ ገቢ ላይ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
- በክልል መስተዳድር በግል ባለቤትነት ስር ካሉ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች በሚገኝ ገቢ ላይ ግብር ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ በባለቤትነታቸው ስር ባሉ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ላይ ኪራይ ያስከፍላሉ፡፡
- በክልል መስተዳድር ባለቤትነት ስር በሚገኙ የልማት ድርጅቶች ላይ የንግድ ትርፍ፣ የሥራ ግብር፣ የሽያጭና ኤክሳይስ ታክስ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
- በአንቀጽ 98 ንዑስ አንቀጽ 3 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በማዕድን ሥራዎች ላይ የማዕድን ገቢ ግብር፣ የሮያሊቲና የመሬት ኪራይ ክፍያዎች ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
- በክልል መስተዳድር አካላት ከሚሰጡ ፈቃዶችና አገልግሎቶች የሚመነጩ ክፍያዎች ይወሰናሉ፣ ይሰበሰባሉ፡፡
- ከደን የሚገኝ የሮያሊቲ ክፍያ ይወሰናሉ፣ ይሰበሰባሉ፡፡
አንቀጽ 98 - የጋራ የታክስና የግብር ሥልጣን
- የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች በጋራ በሚያቋቁሟቸው የልማት ድርጅቶች ላይ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የሥራ ግብር፣ የሽያጭና የኤክሳይስ ታክስ በጋራ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
- በድርጅቶች የንግድ ትርፍ ላይ እና በባለ አክሲዮኖች የትርፍ ድርሻ ላይ ግብርና የሽያጭ ታክስ በጋራ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
- በከፍተኛ የማዕድን ሥራዎችና በማናቸውም የፔትሮሊየምና የጋዝ ሥራዎች ላይ የገቢ ግብርና የሮያሊቲ ክፍያዎች በጋራ ይጥላሉ፣ ይሰበስባሉ፡፡
አንቀጽ 99 - ተለይተው ስላልተሰጡ የታክስ እና የግብር ሥልጣኖች
በዚህ ሕገ መንግሥት ተለይተው ያልተሰጡ ታክስና ግብር የመጣል ሥልጣኖችን በሚመለከት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ይወሰናሉ፡፡
አንቀጽ 100 - የታክስና የግብር አጣጣል መርሆዎች
- ክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት ታክስና ግብር በሚጥሉበት ጊዜ የሚጠየቀው ታክስና ግብር ከምንጩ ጋር የተያያዘና በአግባቡ ተጠንቶ የተወሰነ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
- በመካከላቸው የሚኖረውን መልካም ግንኙነት የማይጎዳና ከሚቀርበው አገልግሎት ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
- ለትርፍ የቆመ ድርጅት ካልሆነ በስተቀር ክልሎች በፌዴራሉ መንግሥት ንብረት ላይ፣ የፌዴራሉ መንግሥትም በክልሎች ንብረት ላይ ግብር ወይም ቀረጥ የማስከፈል ሥልጣን አይኖራቸውም፡፡
አንቀጽ 101 - ዋናው ኦዲተር
- ዋናው ኦዲተር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል፡፡
- ዋናው ኦዲተር የፌዴራሉን የሚኒስቴርና ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ሂሳቦች በመቆጣጠር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመደበው ዓመታዊ በጀት፣ በበጀት ዓመቱ ለተሠሩት ሥራዎች በሚገባ መዋሉን መርምሮ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
- ዋናው ኦዲተር የመሥሪያ ቤቱን በጀት በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ያስጸድቃል፡፡
- የዋናው ኦዲተር ዝርዝር ተግባር በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 102 - የምርጫ ቦርድ
- በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፡፡
- የቦርዱ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
አንቀጽ 103 - የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን
- የሀገሪቱን የሕዝብ ቁጥር በየጊዜው የሚያጠናና ቆጠራ የሚያካሂድ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ይኖራል፡፡
- የኮሚሽኑ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡
- ኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ፣ አስፈላጊ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ይኖሩታል፡፡
- የኮሚሽኑ ዓመታዊ በጀት በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል፡፡
- የሕዝብ ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሔዳል። በውጤቱም መሠረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ይወሰናል፡፡
- የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ስለሥራው አፈጻጸም በየጊዜው ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል፡፡
አንቀጽ 104 - የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብን ስለማመንጨት
አንድ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሀሳብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ የደገፈው፣ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ የደገፈው ወይም ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ አንድ ሦስተኛው የክልል ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የደገፉት ከሆነ ለውይይትና ለውሳኔ ለመላው ሕዝብና የሕገ መንግሥቱ መሻሻል ለሚመለከታቸው ክፍሎች ይቀርባል፡፡
አንቀጽ 105 - ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል
- በዚህ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ ሦስት የተዘረዘሩት መብቶችና ነፃነቶች በሙሉ፣ ይህ አንቀጽ፤ እንዲሁም አንቀጽ 104 ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኋን ብቻ ይሆናል፤
ሀ) ሁሉም የክልል ምክር ቤቶች የቀረበውን ማሻሻያ በድምፅ ብልጫ ሲያጸድቁት፣
ለ) የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቀው፣ እና
ሐ) የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቀው ነው፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ከተዘረዘሩት ውጭ ያሉት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ሊሻሻሉ የሚችሉት በሚከተለው አኳኋን ብቻ ይሆናል፤
ሀ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት፣ እና
ለ) ከፌዴሬሽኑ አባል ክልል ምክር ቤቶች ውስጥ የሁለት ሦስተኛ ክልሎች ምክር ቤቶች በድምፅ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው፡፡
አንቀጽ 106 - የመጨረሻ ሕጋዊ እውቅና ስላለው ቅጂ
የዚህ ሕገ መንግሥት የአማርኛ ቅጂ የመጨረሻው ሕጋዊ እውቅና ያለው ሰነድ ነው፡፡