የሰ/መ/ቁ. 243973
ጥቅምት 06 ቀን 2017 ዓ/ም
ፍርድ
- ጉዳዩ ውርስን የሚመለከት ሲሆን የወራሽነት ማስረጃ ማውጣት ተፈጻሚ በሚሆነው የይርጋ ድንጋጌ ተፈጻሚነት ላይ ያለውን ውጤት የሚመለከት ነው፡፡ አመልካቾች የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት የሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል የሰበር አቤቱታ በማቅረባቸው የተደረገ ክርክር ነው፡፡ አመልካቾች የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ/ም ጽፈው ባቀረቡት ክስ የወላጆቻቸውን ሟች አቶ መሀመድ የሱፍ እና ሟች ወ/ሮ ዘምዘም አሊ /በ20/02/2009 ዓ/ም የሞቱ/ የውርስ ሀብት የሆኑትን የገጠር መሬትና ቤት ለመካፈል ዳኝነት የጠየቁ ሲሆን ተከስሽ የነበሩት ተጠሪ የይርጋ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ ጉዳዩ ሰበር ችሎት የደረሰው የሟች እናታቸውን የውርስ ሀብት በሚመለከት ሲሆን የሥር ወረዳ ፍርድ ቤት አመልካቾች የወራሽነት ማስረጃ ያወጡ ቢሆንም የውርስ ሀብቱን በመያዝ አልተጠቀሙበትም፣ የውርስ ሀብቱ ከተጠሪ ከተያዘ ሦስት ዓመት ያለፈው በመሆኑ በፍ/ሕ/ቁ. 1000/1/ መሠረት ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት ወስኗል፡፡ ጉዳን በይግባኝ የተመለከተው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 38533 እና 44237 በሰጠው ትርጉም ወራሽ የሆነ ሰው የወራሽነት ማስረጃ ካወጣ የሚቀረው የውርስ ሀብት ክፍፍል በመሆኑና የውርስ ሀብት ክፍፍል በማናቸውም ጊዜ ስለሚጠየቅ የሟች እናታቸው ውርስ ሀብት ጥያቄ በይርጋ ቀሪ አይደለም በሚል በሥረ-ነገሩ እንዲወሰን ጉዳዩን መልሷል፡፡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ግራቀኙን አከራክሮ የፍ/ሕ/ቁ. 1000(1) ድንጋጌ ይዘት የሚያስገነዝበው ከሳሽ የሆነ ሰው መብቱን እና የውርስ ንብረቱ በተከሳሹ መያዛቸውን ባወቀ በሦስት ዓመት ጊዜ ካለፈ በኋላ የሚያቀርበው ክስ በይርጋ ቀሪ እንደሚሆን ነው፡፡ አመልካቾች የእናታቸው ወራሽ ስለመሆናቸው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማስረጃ ያወጡ ቢሆንም የውርስ ሀብቱን ከተጠሪ ጋር አብረው ያልያዙ ከመሆኑም በላይ ተጠሪ ንብረቱን በያዘው በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ክስ ያላቀረቡ በመሆኑ ክሱ በይርጋ ቀሪ ነው በማለት የከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔን በመሻር የወረዳ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቷል፡፡ የክልሉ ሰበር አጣሪ ችሎት የአመልካቾችን ሰበር አቤቱታ ባለመቀበል ሰርዟል፡፡
- የሰበር አቤቱታው የቀረበው በዚህ ውሳኔ ነው፡፡ አመልካቾች መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ/ም ጽፈው ያቀረቡት የሰበር አቤቱታ ይዘቱም፡- የወራሽነት ማስረጃ ህጉ በሚያዘው ጊዜ ያወጣ ወራሽ የውርስ ድርሻ ክፍፍል በማናቸውም ጊዜ ሊጠይቅ እንደሚችል በመዝገብ ቁጥሮች 38533 እና 44237 ትርጉም የተሰጠበት በመሆኑ ክሱ በይርጋ የሚታገድ አይደለም በመሆኑም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔው ተሽሮ የስር ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ሊጸና ይገባል የሚል ነው፡፡
- የሰበር ሰሚው ችሎትም የአመልካቾችን የሰበር አቤቱታ መርምሮ አመልካቾች የወራሽነት መብታቸውን በህግ በተመለከተ ጊዜ ውስጥ ያረጋገጡ መሆናቸውን ገልፀው ያቀረቡት ክርክር ታልፎ የዳኝነት ጥያቄያቸው በይርጋ ይታገዳል ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገብ ቁጥር 44237 እና በሌሎች ተመሳሳይ መዛግብት የተሰጠውን ትርጉም የተከተለ መሆን አለመሆኑን፤ እንዲሁም አከራካሪው ይዞታ የገጠር መሬት ከመሆኑ አንፃር ጉዳዩ በክልሉ የገጠር መሬት ህጉ የተመለከተውን መሠረት በማድረግ የተወሰነ መሆን አለመሆኑን ተጣርቶ መወሰን የሚገባው በመሆኑ ተጠሪዎች መልስ እንዲሰጡበት ታዟል ፡፡
- ተጠሪ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም የሰጡት መልስ ይዘት በአጭሩ፡- አመልካቾች የሟች እናታቸው ወራሽነት ማስረጃ በህግ በተደነገገው ጊዜ ውስጥ ያሳወጁ ቢሆንም የውርስ ይገባኛል ክርክሩ በወራሾች መካከል እንደመሆኑ በተጠሪ ንብረቱን ከያዘበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር በ 3 ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠየቅ ሲገባቸው ጥያቄ ያቀረቡት ግን እናታችን ከሞተች ከ 4 ዓመት በኋላ በመሆኑ ክሱ በ3 ዓመት ይርጋ የሚታገድ ነው፣ ክርክር የተነሳበት ቤት የተጠሪና የአመልካቾች ወላጆች በህይወት እያሉ በ16/09/1998 ዓ/ም ለተጠሪ በስጦታ ውል አስተላልፈውልኝ ውሉም በሚመለከተው የመንግስት አካል ጸድቆና ተመዝግቦ በስሜ የካርታ ተሰርቶ ተሰጥቶኝ ግብርም እየገበርኩ እየተጠቀምኩበት ያለሁ ሲሆን፣ አመልካቾች ቤቱ በስጦታ መተላለፉን እያወቁ ያቀረቡት ክርክር ስለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡ ፡ የስር ፍርድ ቤቶች የሰጡት ውሳኔ በወቅቱ በስራ ላይ የነበረውን የክልሉን የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 133/1998 እና ደንብ ቁጥር 51/1999 መሰረት አድርገው የወሰኑት ውሳኔ ነው፤ አመልካቾች የወራሽት ማስረጃውን ብቻ መሰረት አድርገው ያቀረቡት ክርክር ተገቢነት የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም የአመልካቾች አቤቱታ ውድቅ ሊደረግ ይገባል የሚል ነው፡፡ አመልካቾች በሰጡት የመልስ መልስ ያቀረቡትን የሰበር አቤቱታ በማጠናከር ተከራክረዋል፡፡
- የግራ ቀኙ ክርክር እና በየደረጃው ባሉ ፍ/ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ በአጭሩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የወራሽነት ማስረጃ አስቀድሞ ማውጣት የውርስ ንብረቱን ለመረከብ ወይም ለመከፋፈል የሚቀርብ ክስ በይርጋ መብቱ ሳይታገድ በማናቸውም ጊዜ ለማቅረብ የሚያስችል ሕጋዊ ውጤት ያለው መሆን አለመሆኑን ከተገቢው ሕግ ጋር በማገናዝብ እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡
- በውርስ ጉዳይ የውርስ ንብረት ለመካፈል ወይም ንብረት ወይም ድርሻ ለመጠየቅ የሚቀርብ ክስ ከይርጋው ጊዜ ጋር በተያያዘ ሁለት ተቃራኒ አቋም የሚንጸባረቅባቸው አስገዳጅ የሰበር ውሳኔዎች አሉ። አንደኛው በመ/ቁ. 186329 (የመ/ቁ. 26422፣ 20295፣ 26422፣ ወዘተ ጨምሮ) የተሰጠው ውሳኔ የፍ/ሕ/ቁ. 1000 መሰረት በማድረግ ሶስት ዓመት የይርጋ ጊዜ የሚቀበል ሲሆን ሁለተኛው በመ/ቁ. 205248 (መ/ቁ. 44237፣38533 ወዘተ ጨምሮ) የጊዜ ገደብ የሌለው መብት አድርጎ የሚወስድ ነው፡ ፡ ከዚህ በተጨማሪ በተያዘው ጭብጥ ዙሪያ የይርጋ ጊዜው የሚሰላበት ጊዜ፣ ክሱ የሚቀርበብት ጊዜ፣ በማን ላይ እንደሚቀርብ እና ማን እንደሚያቀርብ፣ ወዘተ ጋር በተያያዘ መጠነኛ ልዩነት የሚታይባቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ በአንድ በኩል ይህ ክስ በሶስት ዓመት መቅረብ አለበት በሌላ በኩል የጊዜ ገደብ የለውም የሚሉ ተቃራኒ ውሳኔዎች በአስገዳጅነት ጸንተው ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩ በሰባት ዳኞች ችሎት እንዲታይ የተደረገው ይህን ቅራኔ በማስቀረት ወጥ የሆነ ትርጉም ለመስጠት ነው፡፡
- ችሎቶቹ የሰጡት የሕግ ትርጉም ስለሆነ ለወሰዱት አቋም ዋቢ ያደረጉዋቸውን የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1000 እና 1062 ድንጋጌዎችን መመለከት ይገባል፡፡ የፍ/ሕ/ቁ. 1062 ወራሾች በማናቸውም ጊዜ የውርስ ሐብት እንዲከፋፈል መጠየቅ እንደሚችሉ የሚደነግግ አንቀጽ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚሆነው የውርስ ማጣራት ተከናውኖ ካለቀ በኋላ ነው፡፡ ከፍ/ሕ/ቁ. 1053 ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው የውርስ ማጣራት መጠናቀቅ ተከትሎ የሚተርፈው ንብረት ከወራሽ ሐብት ጋር የሚቀላቀል ወይም በወራሾች በጋራ የሚያዝ ይሆናል፡፡ አንቀጽ 1062 ይህን ታሳቢ ያደረገ ድንጋጌ ሲሆን የጋራ የሆነ ንብረትን ለመከፋፈል የሚቀርብ ጥያቄን የሚመለከት ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሱት መዝገቦች የሚታየው ጉዳይ ግን የተጣራ ንብረት ላይ ድርሻ እንዳለው ተረጋግጦ ክፍፍል የሚጠይቅን ሳይሆን የወራሽነት ማስረጃ ይዞ የውርስ ጥያቄ የሚያነሳን ሰው የሚመለከት በመሆኑ በፍሬ ነገርም ሆነ በሕግ ይዘት ልዩነት ባለበት ሁኔታ ለአንድ ዓይነት ጉዳይ በተለያየ መዝገብም ቢሆን የተለያየ ይዘትና ዓላማ ያላቸውን የፍ/ህ/ቁ. 1062 እና 1000 መሰረት አድርጎ መወሰን የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡
- በመሰረቱ የፍ/ሕ/ቁጥር 1062 የሚናገረው ስለክፍያ ጊዜ ሲሆን በይዘቱ ስለይርጋ ሳይሆን የጋራ ወራሾች ውርሱን እንከፋፈል ብለው የሚጠቁበትን ጊዜ፣ ማብቂውን ሳይሆን መጀመሪያን የሚበይን ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ተፈጻሚ የሚሆነው ውርሱ ከተጣራ በኃላ በመሆኑ በዚህ ጊዜ ወራሾችም ሆነ የውርሱ ሐብት ተለይቷል፣ በጋራ የሚያዘውና የግል የሚሆነው ታውቋል፣ ዕዳም ሆነ የኑዛዜ ስጦታዎች ተከፍለዋል፡ ፡ ስለዚህ የቀረበው የተጣራ የውርስ ሐብት የጋራ በመሆኑ ድንጋጌው የሚያወራው ይህ በጋራ የተያዘ ሐብት ስለሚከፋፈልበት ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ጉዳዩ በነጠላ ውርስን ሳይሆን የጋራ ባለሐብትነትም የሚጨምር (ቁጥር 1060ን ይመለከቷል) ስለሚሆን ይህ ጉዳይ በፍ/ሕ/ቁ. 1000 የሚሸፈን አይሆንም፡ ፡ ጥያቄው የሚነሳው የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳው ሰው ወራሽነቱ እንዲታወቅለት እንዲሁም የተያዘ ንብረት እንዲመለስለት የሚያቀርበው ክስን በተመለከተ የሚነሳ የይርጋ ክርክር እንዴት መፈታት አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህ ነጥብ ደግሞ የወራሽነት ምስክር ወረቀት እና የውርስ ጥያቄ ያላቸውን መስተጋብር፣ ዓላማና ውጤትን በሚገባ መረዳትን የሚጠይቅ በመሆኑ ከዚህ እንደሚከተለው ምርመራ አድርገናል፡፡
- በፍ/ሕ/ቁጥር 996 የተመለከተው የምስክር ወረቀት የሚፈጥረው መብት በአንቀጽ 1062 የጋራ ባለሐብት መሆንን የሚጨምር ስለመሆኑ የሚነሳው ጥያቄ በውሳኔዎቹ መካከል ለሚታየው ተቃርኖ መነሻ ነው፡፡ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ምንነት፣ የሚፈጥረው መብት ከውርስ ንብረት ጋር የሚያነብረው ትስስር በግልጽ መታወቅ በዚህ ዙሪያ ያለውን ብዥታ ለማጥራትና አከራካሪ ለሆነው ነጥብ እልባት ለመስጠት ያስችላል፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 996-998 ያሉት ድንጋጌዎች የ1900 የጀርመን የፍትሐብሔር ሕግ መሰረት ተደርጎ የተቀረጹ መሆናቸውን በኢትዩጵያ የውርስ ሕግ ላይ የተደረጉ ንጽጽራዊ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የሕጉ ምንጭ መሆኑ መቻሉ የሚፈጥረው ተጠባቂ መመሳሰል በመኖሩን ምክንያት የጀርመን ሕግ የወራሽነት የምስክር ወረቀቱ ያለውን አገልግሎት ማየቱ የሰነዱን ዓላማ ለመረዳት ፍንጭ ይሰጣል፡፡ በሕጉ ይዘት ረገድ የሚሰጠው የምስክር ወረቀት በሁለቱም አገሮች ወራሽነትንና የውርስ ድርሻን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ (የጀርመን የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2353 ይመለከቷል)፡፡ ነገር ግን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ወራሾች በዚህ የውርሱ ሂደት ደረጃ ያላቸው መብት ስለሚለያይ የምስክር ወረቀቱ አገልግሎትም ሆነ ውጤት የተለያየ ነው፡፡ በጀርመን ሕግ መሰረት ውርስ የውርስ ሐብቱ በአጠቃላይ ለወራሾች መተላለፍን የሚያስከትል (Universal succession) ስለሆነ የወራሽነት ማስረጃው ይህን እውነት የሚከተል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህን ሰነድ የያዘ ወራሽ የንብረት መብት የሚያስገኝለት ከመሆኑም በላይ የባንክ ሂሳቦችን እና ሌሎች ንብረቶችን ለመድረስ ወይም ለመያዝም ሆነ የግብይት አካል ለማድረግ የሚችልበት ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ወራሹ በምስክር ወረቀቱ ላይ ከተመለከተው ውጭ በመብቱ ላይ ምንም ገደብ አይኖርበትም፡፡ (የጀርመን የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 2365-2367 መመልከት ይቻላል፡፡)
- የወራሽነት ማስረጃ ሕጋዊ ባህሪ የአንድ አገር ውርስ ሕግ ከሟች ወደ ወራሾች ንብረት ለማስተላለፍ የሚከተለውን መንገድ ላይ የሚመሰረት ነው፡፡ ከንብረት መተላለፍ ጋር በተያያዘ የንጽጽራዊ ሕግ ጸሐፍት ሶስት ዓይነት የውርስ ሐብት ማስተላለፊያ መንገዶች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ አንደኛው ከላይ የተጠቀሰው ሞትን ተከትሎ ንብረቱ ወዲያውኑ ለሕጋዊ ወራሾች የሚተላለፍበት (direct and immediate accrual of the inheritance) ሲሆን ሁለተኛው ንብረቱ የወራሾች ፈቃደኝነት ተረጋግጦ የሚደረግ ዝውውር (direct accrual upon acceptance) ነው፡፡ ሶስተኛው የንብረት መተላለፊያ መንገድ የውርስ ንብረቱ በጊዜያዊነት በሌላ ሰው እጅ ቆይቶ የማጣራት ሂደቱ ካለቀ በኋላ የሚደረግ ዝውውር (indirect devolution of the inheritance through an intermediary) ነው፡፡
- ከነዚህ መንገዶች የኢትዩጵያ ሕግ የሚዛመደው የእንግሊዝ ሕግ ጽንሰ ሀሳብ (a concept of English law) ተብሎ የሚታወቀው ከሶስተኛው ጋር ሲሆን የጀርመን ሕግ ግን የመጀመሪያውን ስልት ይከተላል፡ ፡ ሁለቱ አማራጮች በቀጥታ ለወራሾች የውርስ ሐብት የሚደርሱበት ሲሆን የኢትዮጵያ ሕግ የተከተለው ሶስተኛው መንገድ ግን በመሐል ሶስተኛ ወገን በአጣሪነት ተሳትፎበት የተረፈውን ንብረት የሚያስተላልፍበት አካሄድ ነው፡፡ ይህ አማራጭ የፍትሐብሔር ሕጉ በጸደቀበት ወቅት በሲቪል ሕግ ስርዓት በሚከተሉ አገሮች ብዙም ያልተለመደውን የአደራ ጠባቂ (trust) ጽንሰ ሐሳብ ላይ የሚመሰረት በመሆኑና የኢትዮጵያ ሕግ በሲቪል ሎው የሕግ ስርዓት ባልተለመደ ሁኔታ የኮመን ሎው ተቋም የሆነውን የአደራ ጠባቂ (trust) ተቋም እውቅና የሚሰጥ (የፍ/ሕ/ቂ 516 ተከታዩቹ) በመሆኑ ሕጉ ወጥና መስተጋብር እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዩጵያ ሕግ የውርስ ንብረት የሚያስተላለፍበት መንገድ የድንጋጌው ምንጭ እንደሆነ ከሚጠቀሰው የጀርመን ሕግ (እንዲሁም ከበርካታ የአውሮፓ አገሮች ሕግ) በተለየ ሁኔታ ስለሆነ የወራሽነት የምስክር ወረቀቱም አገልግሎትና ውጤት በተመሳሳይ መልኩ የተለያየ ነው፡፡
- በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 996 እንደተመለከተው የኢትዮጵያ የውርስ ሕግ ከይዘት አንጻር በተመሳሳይ ሁኔታ በፍርድ ቤት የሚሰጠው የምስክር ወረቀት ወራሽነትንና ወራሽነቱ የተረጋገጠለት ሰው ከውርስ የሚያገኘውን ድርሻ የሚመለከት ቢሆንም በውጤት ደረጃ ግን ወራሽ ስለመሆን ግምት የሚያስወስድ ብቻ ነው (የፍ/ሕ/ቁ. 997)፡፡ ከላይ ከተገለጸው ንብረት የማስተላለፍ ስልት አኳያ ወራሾች ወዲያውኑ በውርስ ንብረቱ ላይ መብት እንደማይኖራቸው ግልጽ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕጉ የምስክር ወረቀቱ ማስረጃ ከንብረት ጋር በተያያዘ የሚፈጥረው መብት ስለመኖሩ የሚናገረው ነገር የለም፡፡ ሆኖም በቀጥታ የውርስ አካል የሆነ ንብረት ላይ መብት ባይፈጥርም ከሌሎች ወራሾች አንጻር በምስክር ወረቀቱ ድርሻው ከተለየ በውርስ ሐብቱ ላይ በድርሻው ልክ ባለሐብት መሆንን ያስከትላል የሚል አንድምታ በፍርድ ቤት ውሳኔዎች ውስጥ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም በውጤት ደረጃ የሚሰጠው የምስክር ወረቀት ግምት ሊያስወስድ ከመቻሉ ባለፈ በሕጉ ከንብረት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ውጤት እንደሚኖረው አለመጠቀሱ እንዳለ ሆኖ የውርስ ማጣራት አልቆ የተረፈው ንብረት የጋራ መሆኑ ከተረጋገጠ በኃላ ንብረት ክፍፍል በሚጠየቅበት ጊዜ የወራሾችን ትክክለኛ ድርሻ የሚለየው በጋራ በሚመረጥ ሰው ወይም በፍርድ ቤት በሚሾም ባለሙያ ሊሆን እንደሚችል መመልከቱ የመጨረሻ ውሳኔ ተደርጎ የሚወሰድ አለመሆኑን ያሳያል (የፍ/ህ/ቁ 1083 ይመለከቷል፡፡) ከዚህም በወራሽነት ማስረጃ ላይ የሚመለከተው ድርሻ ከቀረበው ማስረጃ የሚወሰድ ግምት መሆኑን እንጂ የንብረት መብት ለመፍጠር ዓላማ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
- የወራሽነት የምስክር ወረቀት በፍርድ ቤት የሚሰጥ በሕጉ አነጋገር ወራሽነትንና የውርስ ድርሻን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ይህን ሰነድ የያዘ ሰው የውርስ ድርሻውን መጠየቅ ካልቻለ በተለይም በሕግ ከሟች ጋር ባለው ዝምድና መሰረት የወራሽነት ደረጃ ከመታወቅ ባለፈ በሰነድ ወራሽነቱ የታወቀለትና ድርሻው የተለየት ሰው የንብረት መብቱን መጠየቅ መቻል እንዳለበት የመቀበል አቋም መኖሩን ከውሳኔዎች መረዳት ያቻላል፡፡ ከላይ በቀረበው ትንታኔ በመያዝ ይህ ሰነድ ከውርስ ሐብት ጋር በቀጥታ የማይገናኝ ከሆነ በፍርድ ቤት የመሰጠቱ ፋይዳና በሕጉ ምን መብት እንደሚያስገኝ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የውርስ ንብረቱ የተለየ ሐብት ተደርጎ የሚቆጠር ቢሆንም ጥቅም ያላቸው ወራሾች (የፍ/ሕ/ቁ. 1060) በመሆናቸው የወራሽነት መብት ከተረጋገጠ ተያይዞ የሚገኘው ጥቅም መከበረ አለበት የሚል አተያይን የሚቀበሉ ውሳኔዎች አሉ:: ከላይ እንዳየነው ሰነዱ ከንብረት ጋር የማይገናኝ እና ግምት ለመውሰድ ዓላማ የሚያገለግል በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በሕጉም የሚፈጠረው መብት ከዚህ የተለየ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ውርሱ እንደተከፈተ ወራሾች የሚኖራቸው መብት የመውረስ መብት እንደሆነ ከፍ/ህ/ቁ. 1124(1) መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህ መብት በከፊልም ሆነ በሙሉ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ መብት ከንብረት ጋር የማይገናኝ እና ንብረት ላይ የማያርፍ መሆኑ ከቁጥር 1124 (2) ድንጋጌ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የወራሽነት የምስክር ወረቀት የሚያስገኘው መብት የመውረስ ወይም የወራሽነት መብት ብቻ ነው፡፡ የወራሽነት መብት ውርስ በማጣራት ሂደት ለመሳተፍ እና ከውርስ ማጣራት የሚገኘውን ሐብት ለመካፈል የሚያስችል እና የውርስ መጣራትን የማይጠብቁ መብቶችን (እንደ ጡረታ ክፍያ፣ የሰራተኛ ጉዳት ካሳ፣ በተወሰነ ሁኔታ የሕይወት መድን ክፍያ፣ ወዘተ) ለመጠቀም የሚያስችል ነው፡፡
- የወራሽነት መረጋገጥ ተከትሎ ወራሽ የሆነ ሰው የውርስ ሐብቱ ላይ መብት የሚገኘው የማጣራት ሂደቱ መጠናቀቅን ተከትሎ መሆኑን በፍ/ህ/ቁ.1053 የተገለጸ ሲሆን የክፍፍል ጥያቄ የሚቀርበው ይህ ሁኔታ ሲሟላ መሆኑ በፍ/ሕ/ቁ. 1062 ተመልክቷል፡፡ ሕጉ በውርስ መከፈትና በውርስ ማጣራት መጠናቀቅ መካከል ያለውን ሁኔታ የሚገዛበትን ድንጋጌዎች አካቷል፡፡ የመጀመሪያው መርሕ ውርሱ እስከሚጣራ ድረስ የተለየ ንብረት ሆኖ እንደሚቆጠር በፍ/ሕ/ቁ. 942 የተደነገገ ሲሆን ለገንዘብ ጠያቂዎች ደግሞ ዋስትናቸው ሆነ ይቀጥላል (የፍ/ሕ/ቁ. 943)፡፡ የሞት መከሰትን ተከትሎ የሟች ወራሾች አጣሪ እንደሆኑ የሚቆጠሩ (የፍ/ሕ/ቁ. 947) ሲሆን የሚኖራቸው መብት ንብረት ጋር ሊደርስ የሚችለው ከውርስ ማጣራት መጠናቀቅ በኋላ መሆኑን ከፍ/ሕ/ቁ.1053 መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው ወራሽ ተብለው ሊለዩ የሚችሉ ሰዎች በውርስ ሐብት ላይ ጥቅም ቢኖራቸውም ውርሱ ተጣርቶ ከመጠናቀቁ በፊት በውርስ ንብረት ላይ ወራሾች መብት አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ንብረት ላይ የማያርፍ ከዛ በመለስ ያለ የወራሽነት መብት የሚያስገኝ በመሆኑ ከንብረት መብት ጋር አያይዞ ውጤት መስጠት አያስችልም፡፡
- ከዚህም በላይ በውርስ ማጣራት ሂደት በውርሱ ሐብት የሚደርሳቸውን ሰዎች መለየት ዋና ተግባር በመሆኑ ይህ ሰነድ ከማስረጃነት ያልዘለለ በሚፈጠረው ወራሽነት ደረጃም ሆነ ድርሻ ላይ ጥያቄ ሊቀርብበት የሚችል ነው፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጥቅም ባለው ሰው ጥያቄ ሲነሳበት የምስክር ወረቀቱ ሊሰረዝ የሚችል የመጨረሻ ፍርድ ተብሎ ሊወሰድ የማይችል ነው (የፍ/ሕ/ቁ. 998 ይመለከቷል)፡፡ስለዚህ የምስክር ወረቀቱ በራሱ የንብረት መብት የመፍጠር ዓላማ ያለው ባለመሆኑ አንድ ሰው ይህን ማስረጃ በመያዙ ብቻ የንብረት መብት ጥያቄ ለማንሳት የሚያስችለው ስላልሆነ የፍ/ሕ/ቁጥር 1062 ለሚታየው ጉዳይ ተገቢነት ያለው ድንጋጌ አይሆንም፡፡ የሆነ ሆኖ በመሬት ላይ ያለውን እውነት ያየን እንደሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ወራሽነትን በማረጋገጥ ከሚሰጡት ማስረጃ ባለፈ የውርስ ድርሻን በምስክር መረቀቱ ላይ የማይጠቅሱ በመሆኑ በሕጉም ሆነ ባለው አሰራር ድርሻን መሰረት አድርጎ ሊነሳ የሚችል የንብረት መብት ጥያቄ አይኖርም፡፡
- በፍ/ሕ/ቁ. 1000 የተመለከተውን የይርጋ ጊዜ ከወራሽነት የምስክር ወረቀት ጋር በማያያዝ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ መብቱን የሚያስከብር ሰው የንብረት ጥያቄ ለማቅረብ ገደብ የሌለበት ተደርጎ የተሰጡ ውሳኔዎች አሉ፡፡ ይህን አቋም ለመፈተሽና ለተያዘውም ጭብጥ ግልጽነት እንዲረዳ የወራሽነት የምስክር ወረቀትና የወራሽነት ጥያቄ ያላቸውን መስተጋብር ግልጽ ማድረግ ይገባል፡፡ ሁለቱም ሐሳቦችን የያዙት ድንጋጌዎች በሕግ መድብሉ አንድ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የይርጋ ጊዜው የተነሳው ግን ከወራሽነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በአጠቃለይ የወራሽነት የምስክር ወረቀትን በተመለከተ በተጠቀሰው በሕግ መድብሉ ክፍል የተደነገገ የይርጋ ገደብ የለም፡፡ አንቀጽ 1000 በግልጽ የሚናገረው የወራሽነት ጥያቄ ተቀባይነት የማያገኝበትን ጊዜ ነው፡፡ ጊዜው ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሁኔታ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ የወራሽነት ጥያቄ ከወራሽነት የምስክር ወረቀት እንዲሰጠ ከሚቀርብ ማመልከቻ ያለውን ልዩነት ማየት ተገቢ ነው፡፡ የወራሽነት የምስክር ወረቀት ስሙ እንደሚናገረው የምስክር ወረቀት ሲሆን በተግባር ፍርድ ቤቶች አንድ ሰው ከሟች ጋር ባለው ዝምድና ወይም በኑዛዜ መነሻነት ወራሽ መሆኑን በማረጋገጥ የሚሰጡት ውሳኔ ነው፡፡ ይህ ማስረጃ የህግ ሁኔታን የሚያረጋግጥ በውጤቱም ሕጉ የሚወሰደውን ግምት የሚያረጋግጥ እንጂ በተከራካሪ ወገኖች መካከል ላለ ክርክር መፍትሔ የሚሰጥ አይደለም፡፡
- የወራሽነት ጥያቄ (petitio hereditatis) ጥንታዊ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን አንድ ሰው ከሟች ንብረት ለመውረስ የሚያቀርበው ክስ ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 999 እንደሚያስቀምጠው ደግሞ አንድ ሰው ወራሽነቱ እንዲታወቅለትና የተወሰዱት የውርስ ንብረቶች እንዲመለስለት የሚያቀርበው ክስ ነው፡ ፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ክሱ ሁለት ነገሮች የሚረጋገጥበት ነው፡፡ የመጀመሪያው የህግ ሁኔታ (status) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የንብረት መብት ነው፡፡ የመጀመሪያውን ብቻውን ያየን እንደሆነ በቁጥር በፍ/ሕ/ቀ. 996 ሊስተናገድ የሚችል ሲሆን የወራሽነት ጥያቄ ግን ከዚህም የሚዘል በመሆኑ የንብረት ክርክርም በውስጡ ይይዛል፡፡ የክሱን ውጤትም ተከሳሹ በእጁ ያለውን ንብረት እንዲመልስ መደረጉ መሆኑ በፍ/ሕ/ቁ. 1001 መመልከቱ ትኩረቱ ንብረት ላይ መሆኑ ያረጋግጣል፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ወራሽ መሆንን ለማረጋገጥና የውርስ ንብረት ለማስለቀቅ የሚቀርብ ክስ ነው፡፡
- የይርጋ ጊዜው ቅድመ ሁኔታ ስናይ ይህን ልዩነት ከግምት ያስገባ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ ክሱ እንዲቀርብ የተመለከተው ጊዜ መነሻ ከሳሽ መብቱንና የውርስ ንብረቶችቹ በተከሳሹ መያዛቸውን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ የክሱ ይዘት ወራሽነት እና ንብረትን የሚመለከት የመሆኑን ያህል ይርጋውም እነዚህን መብቶች ከግምት የሚያስገባ ነው፡፡ ከሳሽ ስለአንደኛው ፍሬ ነገር (ስለወራሽነት መብቱ እና ስለንብረቱ) እውቀት ኖሮት ስለሌላኛው ላያውቅ ወይንም ስለሁለቱም ላያውቅ ይችላል፡፡ስለመብቱ አውቆ ስለንብረቱ ላያውቅ የሚችልበት አጋጣሚ አንዱ የወራሽነት ምስክር ወረቀት ይዞ ስለንብረቱ ወይም ንብረቱ በማን እጅ እንደተያዘ ላያውቅ ይችላል፤እነዚህ ፍሬ ነገሮች ለስሌት መነሻ መሆናቸው የተመለከተ ቢሆንም ሕጉ ሟች ከሞተበት ወይም ከሳሽ ስለመብቱ መስራት ከቻለበት ቀን አንስቶ በአስራአምስት ዓመታት ውስጥ የወራሽነት ክሱን ካላቀረበ ክሱ በይርጋ እንደሚታገድ በንዑስ 2 ደንግጓል፡፡ ስለዚህ የይርጋ ድንጋጌ ይዘትም የሚያወራው ስለምስክር ወረቀቱ ሳይሆን ስለወራሽነት ጥያቄ (petitio hereditatis) ነው፡፡
- ተቃራኒ ውሳኔ በተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች ለወራሽነት የምስክር ወረቀት የተሰጠው ውጤት የተለያየ ሲሆን የዚህ ማስረጃ መኖር ወራሽ ተደርጎ ከመገመት ባለፈ የንብረት መብት የማይፈጥር በመሆኑ ሰነዱ በህጉ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ውጤት መስጠት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል የወራሽነት ጥያቄ በጽንሰ ሐሳብም ሆነ በውጤት የተለየ በመሆኑና በይዘቱ በተመለከተው አግባብ የሚቀርብ ጥያቄ የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት በመሆኑ የይርጋ ጊዜው ተፈጻሚነት በወራሽነት ጥያቄ ላይ ነው፤ስለሆነም የወራሽነት ማስረጃ መያዝ አለመያዝ ልዩነት ሳይኖረው በተጠቀሰው የሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የወራሽነት ጥያቄ ካልቀረበ ክሱ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የወራሽነት ጥያቄ የጊዜ ገደብ የለውም በሚል የተሰጡ የሰበር ውሳኔዎች ከዚህ በላይ በቀረቡ ዝርዝር ምክንያቶች መለወጥ አለባቸው።
- ከዚህ በላይ ከቀረበው ትንታኔ አንጻር በዚህ መዝገብ የሚታየውን ጉዳይ ስናይ አመልካቾች የወላጅ እናታቸው ሟች ወ/ሮ ዘምዘም አሊ የውርስ ሀብት የሆኑትን የገጠር መሬትና ቤት ለመካፈል ዳኝነት የጠየቁ ሲሆን ተከስሽ የነበሩት ተጠሪ ክሱ በፍ/ሕ/ቁ. 1000/1/ መሠረት የሦስት ዓመት ጊዜ ካለፈው በኋላ የቀረበ ክስ በመሆኑ ይርጋ የታገደ ነው ሲሉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ በሥር ፍርድ ቤት በተደረገ ክርክርና ማጣራት አመልካቾች የወራሽነት ምሰክር ወረቀት ያወጡ ቢሆንም የውርስ ሀብቱን በመያዝ አልተጠቀሙበትም፣ የውርስ ሀብቱ ከተጠሪ ከተያዘ ሦስት ዓመት ያለፈው ስለመሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የቀረበው የውርስ ንብረት ጥያቄ ክስ በፍ/ሕ/ቁ. 1000/1/ መሠረት በሦስት ዓመት ጊዜ ገደብ በይርጋ ቀሪ ነው ተብሎ የተሰጠው ውሳኔ ሕጉን የተከተለ በመሆኑ የተፈጸመ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት አላገኘንበትም፡፡ ስለሆነም ተከታዩ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ውሳኔ
- የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 0337041 ታህሳስ 24 ቀን 2015 ዓ/ም፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 0111934 ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ/ም፤ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 52932 መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ/ም የሰጠውን ውሳኔ በመሻር እና የወረባቦ ወረዳ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 01221544 ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ/ም የሠጠውን ውሳኔ በማጽናት፤ የሠጡት ውሳኔ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 17/2015 አንቀጽ 9(1)(ሀ) መሰረት ፀንቷል።
- የሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁ. 205248 (መ/ቁ. 44237፣ 38533 ወዘተ) የወራሽነት የምስክር ወረቀት የያዘ ሰው በማንኛውም ጊዜ የውርስ ንብረት ጥያቄ ማንሳት ይችላል በማለት የሰጠው ትርጉም ተለውጧል፡፡
- በሌላ ልዩ ሕግ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የወራሽነት ጥያቄ በፍ/ሕ/ቁ. 1000 በተመለከተው የጊዜ ገደብ በይርጋ ይታገዳል፡፡ የውርስ ማጣራት ተጠናቆ ንብረቱ የጋራ ባልሆነበት ሁኔታ የወራሽነት ምስክር ወረቀት በመያዝ ብቻ የፍ/ሕ/ቁ. 1062 መሰረት በማድረግ ያለጊዜ ገደብ የክፍፍል ጥያቄ ሊነሳ አይችልም የሚል ትርጉም ተሰጥቷል፡፡
- ግራቀኙ ተከራካሪዎች በዚህ ችሎት ክርክር የደረሰባቸውን ወጭና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ ብለናል፡፡
ትእዛዝ
- የውሳኔው ግልባጭ ለሥር ፍርድ ቤቶች ይተላለፍ፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደመዝገብ ቤት ይመለስ፡፡