ፍርድ

ከሣሽ በሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም በተፋጠነ ስነ-ስርዓት ጽፈው ባቀረቡት የክስ አቤቱታ በከሳሽ እቁብ ሰብሳቢነት በየሳምንቱ እሁድ በሚሰበሰበው ዕቁብ ሙሉ እጣ ብር 3,000 ግማሽ እጣ በወር 1,500 እሩብ እጣ ብር 750 ለመክፈል በመስማማት ከ18/07/2008 ዓ/ም ጀምሮ በእቁብተኛው ሙሉ ፈቃድ እንደተቋቋመ በዚህም 1ኛተከሳሽ በሙሉ እጣ ተመዝግበው ሲከፍሉ ቆይተው ሙሉ እጣ ደርሷቸው ብር 393,000 (ሶስት መቶ ዘጠና ሶስት ሺህ) መተማመኛ ሰነድ ፈርመው እንደወሰዱ ሆኖም ተከሳሽ የእቁቡን ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ በየሳምንቱ መክፈል ከሚገባቸው ገንዘብ ውስጥ  የ9 እቁብተኛ 3,000 × 9 = 27,000 (ሀያ ሰባት ሺህ) ሳይከፍሉ እንደቀሩ በመሆኑም ተከሣሽ ይህንን ቀሪውን የእቁብ ክፍያ ከነወለዱ እንዲከፍሉ፤ በዚህ ክስ ምክንያት ያወጡትን ወጪና ኪሣራም እንዲተኩ እንዲወሰንላቸው ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ በማስረጃነትም የሠነድ ማሰረጃን አያይዘው አቅርበዋል፡፡

 

ተከሳሽ ክሱ ከፍ/ቤቱ መጥሪያ ጋር  ቢደርሳቸውም የመ/ማስፈቀጃ ያላቀረቡ በመሆኑ ፍ/ቤቱ የመከላከል መብታቸውን አልፎታል፡፡ ፍ/ቤቱም ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ለከሳሽ ሊከፍሉ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ጭብጥ በመያዝ መዝገቡን እንደሚከተለው መርምሯል፡፡

ከሣሽ ክስ ያቀረቡት ተከሣሽ ከሣሽ በሚሰበስቡት እቁብ አባል ሆነው እጣ ወጥቶላቸው ገንዘቡን ፈርመው የወሰዱ ሲሆን መክፈል ከሚገባቸው የእቁብ ገንዘብ ውስጥ ብር 27,000 (ሀያ ሰባት ሺህ) ስላልከፈሉ ቀሪውን የእቁብ ገንዘብ ሊከፍሉ ይገባል በማለት ሲሆን ተከሣሽ በከሣሽ እቁብ ሰብሳቢነት ይሰበሰብ በነበረው እጣ ወጥቶላቸው ብር 393,000 (ሶስት መቶ ዘጠና ሶስት ሺህ) የወሰዱ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ቀርቧል፡፡

     እቁብ የአገራችን የሆነ በተለየ ሁኔታ በስፋት የተለመደ በቁጥር የተወሰኑ ሰዎች ስምምነት በማድረግና ለስምምነቱም ተገዢ በመሆን በቡድን ሆነው በተወሰነ ጊዜ የተወሰነ የገንዘብ መጠን በመሰብሰብ በየዙሩ የተሰበሰበውን ገንዘብ ስምምነት ያደረጉት ሰዎች በየተራ የሚወስዱበት ባህላዊ የሆነ የቁጠባ ማህበር ሲሆን ይህም በአባላቱ መካከል በተደረገው የውል ስምምነት መሰረት አባላቱ መወጣት ያለባቸውን ግዴታ ማለትም የእቁብ ገንዘቡን የመክፈል እቁብ ወጥቶላቸው ገንዘብ የወሰዱ ከሆነም የወሰዱትን የእቁብ ገንዘብ ሙሉ እስኪመለስ ድረስ ገንዘቡን የመክፈል ግዴታ ያለባቸው ናቸው፡፡ ይህንንም ከፍ/ብ/ህ/ቁ 1678 እና 1731/1 ድንጋጌዎች ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ተከሣሽ  በታህሳስ 9 ቀን 2009 ዓ/ም ብር 393,000 (ሶስት መቶ ዘጠና ሶስት ሺህ) የእቁብ ገንዘብ የወሰዱ መሆኑን የቀረበው የሰነድ ማስረጃ የሚያስረዳ ሲሆን  ተከሳሽ ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ በየሳምንቱ የእቁብ ገንዘቡን የመጣል ግዴታ ያለባቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ተከሳሽ ይህን ግዴታቸውን ሳይወጡ ከቀሩ ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድ ከሳሽ ክስ ለማቅረብ የሚችሉ ሲሆን በዚህ አግባብም ነው ከሳሽ ያልተከፈለው የእቁብ ገንዘብ እንዲከፈል ክስ ያቀረቡት፡፡ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 284 ላይ እንደተመለከተው በተፋጠነ ስነ-ስርዓት ለቀረበ ክስ ተከሣሽ ቀርበው መከላከያ ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸው ሳያመለክቱ የቀሩ እንደሆነ ወይም በህጉ ላይ በተቀመጠው የማስፈቀጃ ግዜ ማስፈቀጃ ያላቀረቡ እንደሆነ ከሣሽ የጠየቀው ገንዘብ ሊወሰንለት እንደሚገባ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 285/2/ ላይ ተደንግጎ የሚገኝ ሲሆን በያዝነው ጉዳይ ተከሳሽ ክሱ የደረሳቸው ቢሆንም የመከላከያ ማስፈቀጃ ያላቀረቡ በመሆኑ ገንዘቡን ሊከፍሉ የማይገባበትን ምክንያት በመጥቀስ የቀረበ መከላከያ የሌለ ሲሆን በዚህም ገንዘቡን ሊከፍሉ የማይገባበት ምክንያት የሌለ በመሆኑ ተከሳሽ ክስ የቀረበበትን ገንዘብ ከነወለዱ ለከሣሽ ሊከፍሉ ይገባል ሲል ፍ/ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

ውሳኔ

  1. ተከሳሽ ብር 27,000 (ሀያ ሰባት ሺህ) ክስ ከቀረበበት ከሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከሚታሠብ 9% ወለድ ጋር ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡
  2. ወጪና ኪሣራ በተመለከተ ከሣሽ ለዳኝነት የከፈሉትን ብር 1,022 ፣ ለቴምብር ቀረጥ ብር 5 ፣ ለጠበቃ አበል በጥብቅና ውሉ ላይ የተመለከተውን በማሻሻል ክስ የቀረበበት የገንዘብ መጠን 10% ብር 2,700 ተከሣሽ ለከሣሽ ይክፈሉ፡፡

ትዕዛዝ

  1. ይግባኝ መብት ነው፡፡
  2. መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡