- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 4454
የኮ/መ/ቁ 171480 - አቶ አብዲሳ በየነ ያደታ እና እነ ዶ/ር አበበ ደምስስ (2 ተከሳሾች)
የኮ/መ/ቁ 171480
የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ/ም
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡- አቶ አብዲሳ በየነ ያደታ
ተከሳሾች፡- 1ኛ) ዶ/ር አበበ ደምስስ
2ኛ) ፍቅር ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረዉ ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡
ፍርድ
ለዚህ ፍርድ መነሻ የሆነዉ ከሳሽ የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ/ም በተጻፈ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ሲሆን ይዘቱም 2ኛ ተከሳሽ ማህበር በአራት አባላት በብር ሶስት ሚሊዮን ካፒታል የተቋቋመ መሆኑን ከሳሽ በማህበሩ ዉስጥ ብዛታቸዉ 1,000 የሆኑ እያንዳንዳቸዉ የብር 1,000 ዋጋ ያላቸዉ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸዉ መሆኑን ከሳሽ ወደ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሲቀላቀሉ የነበራቸዉን የመድኃኒት አቅራቢ ደንበኞቻቸዉን ወደ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር በማዛወር ማህበሩ ስራ እንዲጀምር ያደረጉ መሆኑን የማህበሩም ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነዉ በቃለ ጉባኤ ተሾመዉ ማህበሩን ዉጤታማ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ መሆኑን ይሁን እንጂ 1ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ስራ አስኪያጅነታቸዉ ሃላፊነታቸዉን በንግድ ህጉ፤ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት መወጣት ሲጠበቅባቸዉ እነዚህን ወደ ጎን በማደረግ ከሂሳብ አሰራር ዉጭ የማህበሩን ገንዘብ ገቢ እና ወጪ የሚያደርጉ መሆኑን፤ ያለ ከሳሽ እውቅና ገንዘብ ከግለሰብ ተብድሪያለሁ በሚል ማህበሩን ባለዕዳ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ መሆኑን፤ የማህበሩ ግማሽ ካፒታል በሚሆን በብር 1.5 ሚሊዮን የቅንጦት መኪና ገዝተዉ የሚጠቀሙ መሆኑን፤ ይህ 1ኛ ተከሳሽ የቅንጦት መኪና የገዙበት መኪና ኤልሲ(LC) ለመክፈት በባንክ ተቀምጦ የነበረ ገንዘብ መሆኑን፤ ይህም ገንዘብ ወጪ በመደረጉ ኤልሲ(LC) ሳይከፈት ቀርቶ ከውጭ መግባት የነበረባቸዉ መድኃኒቶች ሳይገቡ የቀሩ መሆኑን በዚህም ምክንያት ከማህበሩ ዋና መድሃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር የነበረዉ የስራ ግኑንነት የተቋረጠ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር በተጨማሪ ፋክት፤ ጽጌረዳ ክሊኒክ እና ጽጌረዳ ዳይሊሲስ ሴንተር የተባሉትን ተቋማት በዋና ስራ አስኪያጅነት የሚመሩ መሆኑን በዚህም ምክንያት የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሰራተኞችን በአግባቡ የማይቆጣጠሩ መሆኑን፤ ለማህበሩ ስራም በቂ ትኩረት የማይሰጡ መሆኑን፤ አፋጣኝ ስራዎችም በሚኖሩ ጊዜ የማይገኙ መሆኑን፤ በሰነዶች ላይ የማይፈርሙ መሆኑን፤ በመጋዘን ዉስጥ የሚገኙትን መድሃኒቶች በመሸጥ ለግል ጥቅማቸዉ ያዋሉ መሆኑን፤ በማህበሩ ስምም ሌሎች ስራዎችንም የሚሰሩ መሆኑን፤ የሂሳብ ሪፖርት እንዲሰጡ ሲጠየቁ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸዉን፤ ማህበሩ ትርፍ ያተረፈ ቢሆንም ትርፍ የሌለ በማስመሰል ትርፍ እንዳይከፋፍል የሚያደርጉ መሆኑን፤ ስብሰባ ጠርተዉ የማያውቁ መሆኑን፤ ከሳሽን ያለበቂ ምክንያት ከስራ አሰናብተዉ በማህበሩ ቅጥር ግቢ እንዳይገኙ የከለከሉ መሆኑን ገልጸዉ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነታቸዉ ተሽረዉ ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ እንዲሾም እንዲወሰንላቸዉ፤ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ በሂሳብ አጣሪ ተጣርቶ ትርፍ በድርሻቸዉ ልክ እንዲከፈላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ፤ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያሉት የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዝገቢያ ሰነዶች ኮፒ እንዲሰጣቸዉ እንዲወሰንላቸዉ፤ የማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅ በመሆናቸዉ ወደ ማህበሩ ቅጥር ግቢ ገብተዉ ስራዎችን እንዲሰሩ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉ ወጪና ኪሳራ እንዲተካላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሽ ክሱን ያስረዱልናል ያሏቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል፡፡ የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡
ከሳሽ ያቀረቡት የክስ አቤቱታ ለተከሳሾች ደርሶ ተከሳሾች በሰጡት መልስ ከሳሽ ለ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ያመጣቸዉ የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች የሌሉ መሆኑን፤ ከማህበሩ ጋር ይሰሩ የነበሩትንም መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ከሳሽ ከማህበሩ በዲሲፕሊን ከተባረረ በኃላ ከማህበሩ ጋር እንዳይሰሩ በማድረግ ኪሳራ ያደረሱ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን የሚመሩት በንግድ ህጉ፤ በማህበሩ መመስረቻ እና በመተዳደሪያ ደንብ መሰረት መሆኑን ከሳሽ ባቀረቡት ክስ ላይ የተገለጹትን ህገ ወጥ ተግባራት ፈጽሟል ተብለዉ በወንጀል ያልተቀጡ መሆኑን ከማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ውጭም የተበደሩት ገንዘብ የሌለ መሆኑን፤ አለ አግባብ ወጪ ያደረጉትም ገንዘብ የሌለ መሆኑን፤ የቅንጦት መኪና ያልገዙ መሆኑን፤ የማህበሩን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ያልፈጸሙ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ ከአንድ በላይ ማህበር መምራታቸዉ ብቃታቸዉን ከሚያሳይ በቀር ህግ ወጥ ተግባር አለመሆኑን፤ ከአንድ በላይ ማህበር መምራት እንዲችሉ በህግ የተፈቀደ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ የከሳሽን ድርሻ ለመስጠት የገቡት ግዴታ የሌለ መሆኑን፤ 1ኛ ተከሳሽ በማህበሩ መጋዘን ዉስጥ የሚገኙ መድኃኒቶችን የሸጡ ስለመሆኑ የቀረበ ማስረጃ የሌለ መሆኑን፤ ከሳሽ የማህበሩ አባል ባልሆኑበት ሁኔታ ትርፍ ክፍፍል እና ስብሰባ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረብ የማይችሉ መሆኑን፤ ከሳሽ የማህበሩ ደንበኞች ከማህበሩ እንዲወጡ ያደረጉ መሆኑን፤ ከሳሽ በማህበሩ፤ በሰራተኛዉ እና በስራ አመራር መካከል የኢንዱስትሪ ሰላም እንዳይኖር ያደረጉ መሆኑን፤ የአለቃ ትዕዛዝ የማይቀበሉ መሆኑን፤ በስራ ገበታ ላይም የማይገኙ መሆኑን፤ በስራ አጋጣሚ በእጃቸዉ የገባዉን ቼክ በመጠቀም የ1ኛ ተከሳሽን ስም እና ዝና ያጎደፉ መሆኑን ገልጸዉ የከሳሽ ክስ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
ተከሳሾች ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸዉን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቧል፡፡ የሰዉ ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክስና መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡
የግራ ቀኙ ጠቅላላ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍርድ ቤቱም ቀጥሎ የተመለከተዉን ጭብጦች በመያዝ መዝገቡን እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡
1ኛ) 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነት ተሽረዉ በምትካቸዉ ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ ሊሾም ይገባል ወይስ አይገባም?
2ኛ) የ2ኛ ተከሳሽ ማህበሩ ሂሳብ በሂሳብ አጣሪ ተጣርቶ ከሳሽ በድርሻቸዉ ትርፍ ሊከፈላቸዉ ይገባል ወይስ አይገባም?
3ኛ) ከሳሽ ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያሉት የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዘገቢያ ሰነዶች ኮፒ ሊሰጣቸዉ ይገባል ወይስ አይገባም?
4ኛ) ከሳሽ በማህበሩ ቅጥር ግቢ ዉስጥ እንዳይገኙ እና ስራ እንዳይሰሩ የተጣለባቸዉ ክልከላ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም?
የመጀመሪያዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሾች ከሳሽ የማህበሩ አባል አይደለም በመሆኑም የማህበሩ ስራ አስኪያጅ እንዲሻር ሊጠይቅ አይገባም በማለት ክርክር አቅርቧል፡፡ ከሳሽ የማህበሩ አባል ናቸዉ ወይስ አይደሉም የሚለዉን ነጥብ በተመለከተ ይህ ፍርድ ቤት ሰኔ 6 ቀን 2010 ዓ/ም በዋለዉ ችሎት ከሳሽ አባል መሆናቸዉን በማረጋገጥ ብይን ሰጥቷል ይህ ብይን በይግባኝ አልተሻረም አልተለወጠም፡፡ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የማህበሩ አባላት ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ/ም በተያዘ እና በፌዴራል የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ጽ/ቤት በተመዘገበ ቃለ ጉባኤ የማህበሩ አባል እና ስራ አስኪያጅ የሆኑት 1ኛ ተከሳሽ በማህበሩ ዉስጥ ከነበራቸዉ 1,500 አክሲዮኖች 500 አክሲዮኖችን፤ ወ/ሮ ክብነሽ ስብስቤ ከነበራቸዉ 750 አክሲዮኖች ዉስጥ 250 አክሲዮችን እንዲሁም ህጻን ዳንኤል አበበ ከነበራቸዉ 750 አክሲዮን ዉስጥ 250ዉን በድምሩ 1,000 አክሲዮኖች በሽያጭ ለከሳሽ የተላለፈ መሆኑን የቀረበዉ ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡ ይህ ቃለ ጉባኤ ስለመሻሩ በተከሳሾች በኩል የቀረበ ማስረጃ የለም፡፡ ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ዉስጥ በባላ አክሲዮንነት በማህበሩ አክሲዮን መዝገባ ላይ እስከ ተመተዘገቡ ድረስ እንደ ማንኛዉም የማህበሩ አባል ለዉሳኔ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ ድምጽ የመስጠት፤ ስራ አስኪያጅ ጥፋት ከፈጸመ ስራ አስኪያጅ እንዲሻር፤ የማህበሩ ሂሳብ እንዲጣራ እና የማህበሩን ሰነዶች ለመመልከት ለመጠየቅ መብት አላዉ፡፡ (የንግድ ህጉ 522፤ 527(5)፤ 533፤ 534፤ 537 ይመለከታቸዋል)፡፡
ተከሳሾች አጥብቀዉ የሚከራከሩት ከሳሽ ከማህበሩ ጋር በገባዉ ግዴታ መሰረት ሶስት የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች ከማህበሩ ጋር ቋሚ ውል እንዲዋዋሉ አላደረገም፡፡ በብድር ዉሉ መሰረትም ክፍያዉን አልከፈለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ከሳሽ ስራ አስኪያጅ ይነሳልኝ የሚል ዳኝነት ሊጠይቅ አይችልም በማለት ነዉ፡፡ በርግጥ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር እና ከሳሽ በቀን 1/11/2008 ዓ/ም ባደረጉት የብድር ውል ስምምነት ማህበሩ ለከሳሽ ብር አንድ ሚሊዮን ያበደረ መሆኑን አከፋፈሉን በተመለከተ ደግሞ ከሳሽ ከማህበሩ ጋር ጃኖ፤ ፋርኮ እንዲሁም ሌላ አንድ የመድሃኒት አምራች ድርጆቶች ጋር ስምምነት እንዲፈጽም ካደረገ ከሳሽ በብድር ከወሰደዉ ብር አንድ ሚሊዮን ላይ ብር 500,000 እንደከፈለ የሚቆጠር መሆኑን ቀሪዉ 500,000 ደግሞ የሚከፈለዉ ከሳሽ ከተከሳሽ ማህበር በድርሻዉ ከሚያገኘዉ ትርፍ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች ከሳሽ ጃኖ፤ፋርኮ እንዲሁም ኤሮፒያን ኤጅብሺያን ከሚባሉ መድሃኒት አምራች ድርጅቶች ጋር 2ኛ ተከሳሽ ውል እንዲፈጽም ያደጉ መሆኑን መስክረዋል፡፡ በተከሳሾች በኩል የቀረቡትም ምስክሮች ማህበሩ ጃኖ እና ፋርኮ ከሚባሉ የመድሃኒት አቅራቢዎች መድሃኒት ለሁለት ዙር በውክልና ያስመጣ መሆኑን መስክረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፋርኮ ፋርማሲውቲካልስ 2ኛ ተከሳሽ ማህበርን 2ኛ የሀገር ዉስጥ አከፋፋይ ያደረገ መሆኑን ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በቁጥር ኢቲኤች/ፒኤችአር/001/2016 በቀን 3/13/2008ዓ/ም፤ የጃኖ ፋርማሲዉቲካልስ ኃ/የተ/የግል/ማህበር በቀን 8/2/2009 ዓ/ም ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በጻፈዉ ድብዳቤ 2ኛ ተከሳሽ ማህበርን 1ኛ ወኪል ያደረገ መሆኑን የገለጸበትን፤ ለዚህ ለተደረገዉ የአከፋፋይ ውክልና ውልም 50 የአሜሪካን ዶላር ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን የተከፈለ መሆኑን የሚያስረዱ ማስረጃዎች ከሳሽ አቅርቧል፡፡
በተመሳሳይ የኤሮፒያን እና ግብጻያዉን መድሃኒት አምራች እና አከፋፋይ 2ኛ ተከሳሽ ማኅበርን በኢትዮጵያ ዉስጥ 2ኛ ወኪል አከፋፋይ ያደረጋቸዉ መሆኑን ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን በቀን 6/1/2009 ዓ/ም በጻፈዉ ደብዳቤ የገለጸበትን እንዲሁም ለወኪል ስምምነት ክፍያም ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒትና የጤና አንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን 50 የአሜሪካን ዶላር የከፈለ መሆኑን የሚያስረዱ ማስረጃዎች ከሳሽ አቅርቧል፡፡
ተከሳሽ ባቀረበዉ ክርክር ከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ቢያንስ ከ5-10 አመት ከማህበሩ ጋር በቋሚነት እንዲሰሩ ውል ማዋዋል ነበረበት በሚል ክርክር ያቀረቡ ሲሆን ከሳሽ እና 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ባደረጉት የብድር ውል ላይ ከሳሽ የገባዉ ግዴታ ከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ጋር ተገቢዉን ስምምነት እንዲያደረጉ ማድረግ የሚል ሲሆን ተገቢዉ ስምምነት የሚለዉ ቃል ግልጽ አይደለም ይህ ከሆነ ደግሞ ውሉ ትርጉም የሚያስፈልገዉ ሲሆን ውሉ ሊተረጎም የሚገባዉ በፍ/ሕ/ቁ 1731 እና 1732 በተደነገገዉ መስረት የግራ ቀኙን መተማመንና ቅን ልቦና፤ ፍትሕን እንዲሁም ልማዳዊ አሰራርን መሰረት በማድረግ ነዉ፡፡
ከዚህ አንጻር የተያዘዉ ጉዳይ ሲታይ ከሳሽ ግዴታ የገባዉ 2ኛ ተከሳሽ ማህበርን ውጭ ከሚገኙ የመድሃኒት አምራች ድርጅቶች ጋር ተገቢዉን ውል እንዲዋዋል ማድረግ ሲሆን ተገቢው ውል/ስምምነት ደግሞ መድኃኒት አምራቾቹ የሚያቀርቡትን መድሃኒተች/ምርቶች በውክልና ማከፋፈል እንዲችል የሚያደርግ ውል እንዲፈጸም ማድረግ ተብሎ ሊተረጎም ይገባዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ከላይ የተጠቀሱትን የመድሃኒት አምራቾችን ምርት በውክልና እንደዲያከፋፍል ውክልና ተሰጥቷል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ ከላይ የተጠቀሱት የመድኃኒት አምራች ድርጅቶች የሚያመርቱትን መድኃኒት ለማከፋፈል ውክልና የተሰጣቸዉ ከሆነ ደግሞ በዘርፉ በተለመደዉ አሰራር መሰረት ከሳሽ ተገቢዉ የውል ስምምነት እንዲፈጸም ያደረጉ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ተከሳሾች ይህን ውክልና አናውቀዉም በማለት የተከራከሩ ቢሆንም ተከሳሽ እራሱ ያቀረባቸዉ ምስክሮች በሀገር ዉስጥ መድሃኒት ለማከፋፈል ከኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒትና የጤና እንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ የሚያስፈልግ መሆኑን እንዲሁም የውጭ መድሃኒት ሀገር ዉስጥ ማከፋፈል የሚቻለዉ አከፋፋዩ ከኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒትና የጤና አንክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ፈቃድ ሲያገኝ መሆኑን እንዲሁም ማህበሩ ከጃኖ እና ከፋርኮ የመጡ ምርቶችን ሲያከፋፍል የነበረ መሆኑ መስክረዋል፡፡ ይህም የሚያሳየዉ ከሳሽ በገባዉ ግዴታ መሰረት ግዴታዉን የተወጣ መሆኑን ነዉ፡፡ በሌላ በኩል የተከሳሾች ምስክሮች በሰጡት ምስክርነት ከሳሽ ከላይ ከተጠቀሱት የመድኃኒት አምራች ድርጅቶች ጋር ከ5-10 ሊቆይ የሚችል ስምምነት እንዲደርግ ማድረግ ነበረበት በማለት የምስክርነት ቃል ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ በዉሉ ላይ ከሳሽ ከ5-10 አመት ድርስ ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ውል እንዲገቡ ለማድረግ ግዴታ አልገባም፡፡ የተደረገዉ ውልም ይህን አያመለክትም የተከሳሾች ምስክሮችም ከ5-10 አመት ድርስ ሊያዋውል ይገባል በማለት የሰጡት ምስክርነት የግል አስታያየታቸዉ መሆኑን ከመግለጻቸዉም በላይ በዚህ አይነት ስራ ላይ የቆዩ ባለመሆናቸዉ እና በዘርፉም እውቅት የሌላቸዉ ከመሆኑ እንጻር እንዲሁም በማህበሩ ዉስጥ የመድሃኒት ኢምፖርት ላይ በብቸኝነት ሲሰራ የነበረዉ ከሳሽ መሆኑ በተከሳሾች ምስክሮችም የተረጋገጠ በመሆኑ፤ ማህበሩም ከሳሽ በአባልነት ከመቀላቀሉ በፊት መድሃኒት አስመጥቶ የማያውቅ መሆኑ ሲታይ ከ5-10 አመት ድረስ ማዋዋል ነበረበት በማለት የሰጡት የምስክርነት ቃል እምነት የሚጣልበት አይደለም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ከሳሽ ከ5-10 ዓመት የሚቆይ ቋሚ ውል ማዋዋል ነበረበት በማለት ያቀረቡት ክርክር በተደረገዉ ውል ላይ ያልተገለጸ እና ከሳሽም እንዲያውቀዉ ያልተደረገ ስለሆነ በፍ/ሕ/ቁ 1780(2) መሰረት ከ5-10 አመት ድረስ የሚቆይ ውል ከላይ የተጠቀሱት መድኃኒት አምራቾች ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር እንዲፈጸሙ ለማድረግ ግዴታ ገብቷል ሊባሉ አይችሉም ይህን እንዲፈጽሙም ሊገደዱ አይችልም፡፡
ከሳሽ በበድር ዉሉ መስረት የገባዉ ግዴታ ቀሪዉን ብር 500,000 የሚከፈለዉ ከትርፍ ክፍፍል ላይ ተቀናሽ እየተደረገ መሆኑን ውሉ ስለሚገልጽ እና የግራ ቀኙ ምስክሮችም እስካሁን ድረስ ማህበሩ የትርፍ ክፍፍል አድርጎ የማያውቅ መሆኑን ስለመሰከሩ ከሳሽ ቀሪዉን 500,000 ከትርፍ የመክፍል ግዴታዉን አልተወጣም ሊባል አይችልም፡፡
1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነዉ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 8 መሰረት የተሾሙ መሆኑን በማስረጃነት የቀረበዉ የመመስረቻ ጽሁፍ ያስረዳል፡፡ በመመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ስራ አስኪያጅ ከስራ አስኪያጅት ስልጣኑ ሊሻር የሚችለዉ በንግድ ህጉ 527(1) እና 536(2) መሰረት ከማህበሩ ባለአክሲዮኖች መካከል በሶስት አራተኛ ድምጽ ባላቸዉ ባለአክሲዮኖች ሲደገፍ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌም ተፈጻሚነት ያለዉ የማህበሩን ስራ አስኪያጅ በጠቅላላ ጉባኤ ለመሻር በቀረበ ጊዜ ሲሆን በሌላ በኩል እንድ ስራ አስኪያጅ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ የተሾመ ቢሆንም ስራ አስኪያጁ ከስልጣኑ እንዲነሳ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥፋቶች እስካሉ የማህበሩ አባላት ስራ አስኪያጁ በፍርድ ቤት ዉሳኔ እንዲሻር መጠየቅ እንደሚቻሉ በንግድ ህጉ አንቀጽ 527(5) ተመልክቷል፡፡
በመሆኑም ከሳሽ የማህበሩ አባል መሆናቸዉ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ፤ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ሶስት የመድሃኒት አምራች ድርጅቶችን ያዋዋሉ በመሆኑ በዚህ ረግድ ያለባቸዉን ግዴታ የተወጡ በመሆኑ፤ ከትርፍ የሚከፈለዉን እዳቸዉ እንዲከፈል ያልተደረገዉ ትርፍ ለአባላት ባለመከፋፈሉ መሆኑ ስለተረጋገጠ እንዲሁም ከሳሽ የማህበሩ አባል እንደመሆናቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ጥፋት የፈጸሙ እንደሆነ ከስራ አስኪያጅነት ስልጣናቸዉ እንዲነሱ ዳኝነት ለመጠየቅ የንግድ ህጉ የሚፈቅድ በመሆኑ ተከሳሾች ከሳሽ ስራ አስኪያጅ እንዲነሳ ሊጠይቁ አይገባም በማለት ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡
ፍርድ ቤቱም 1ኛ ተከሳሽ ከስራ አስኪያጅነት ሊያሽራቸዉ የሚችል ጥፋት ፈጽሟል ወይስ አልፈጸሙም የሚለዉን ነጥብ ከሳሽ በ1ኛ ተከሳሽ ተፈጽሟል ከተባሉት ተግባራት አንጻር እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡
የአንድ ማህበር ስራ አስኪያጅ ሆኖ የተሾመ ሰዉ ህግን፤ የማህበሩን መመስረቻ ጽሁፍ እንዲሁም መተዳደሪያ ድንብ መሰረት አድርጎ ሊሰራ አንደሚገባ ግልጽ ነዉ፡፡
ከዚህ አንጻር 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር በተጨማሪ ሌሎች ሶሰት ድርጅቶችን ማለትም ጽጌረዳ ዲያሊሲስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ ጽጌራዳ ቁጥር 1 ክሊንክን እንዲሁም ፋክት የጤና መገልገያዎች ማምረቻ እንዱስትሪን በስራ አስኪያጅነት የሚመሩ መሆኑን እራሳቸዉ በሰጡት ምስክርነት ከማረጋገጣቸዉም በላይ በሌሎች ምስክሮች የተረጋገጠ ፍሬ ነገር ነዉ፡፡
በአዋጅ ቁጥር 980/2010 አንቀጽ 41 መሰረት ማንኛዉም ሰዉ ከአንድ በላይ የንግድ ማህበራትን በአንድ ጊዜ በስራ አስኪያጅነት ሊመራ እንደማይችል ተመልክቷል፡፡
ህግ አውጪዉ ይህን ደንጋጌ ሲደነግግ ሊያሳከዉ ያሰበዉ ዓላም ያለ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መንፈስም መረዳት የሚቻለዉ ከአንድ በላይ የንግድ ማህበር በስራ አስኪያጅነት የሚመራ ሰዉ ለየ ማህበራቱ በቂ ጊዜ ላይሰጥ እንደሚችል፤ የማህበሩን እንቅስቃሴ በተገቢዉ መጠን ክትትል ሊያደርግ የማይችል መሆኑን እንዲሁም ሌሎች ያልተገቡ ተግባራት እንዳይከሰቱ በማሰብ ጭምር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ ህግን በጣሰ መልኩ ከአንድ በላይ የሆኑ የንግድ ማህበራትን እየመሩ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ማህበሩን በሚፈለገዉ መጠን ክትትል እያደረጉ እና አስፈላገዉን ጊዜ እየሰጡ እያስተዳደሩት ነዉ ለማለት አይቻልም፡፡ በተለይም 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩ የተለያዩ ጉዳዮችን እንዲያከናውን ለማስቻል በባዶ ወረቅት ላይ እየፈረሙ በስራ ቦታ ላይ የማይገኙ መሆኑ መረጋገጡ ሲታይ ለማህበሩ በቂ ጊዜ ሰጥተዉ ማህበሩን እየመሩ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል የ1ኛ ተከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 525(1) መሰረት ከአንድ በላይ የሆኑ ድርጅቶችን በስራ አስኪያጅነት ለመምራት ይችላሉ በማለት ክርክር ያቀረቡ ቢሆንም ይህ ድንጋጌ አንድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አንድ ወይም ከአንድ በላይ ስራ አስኪያጆች ሊኖሩት እንደሚችል የሚያመለክት ድንጋጌ እንጂ አንድ ስራ አስኪያጅ ከአንድ በላይ የንግድ ማህበራትን በስራ አስኪያጅነት መምራት የሚችል ስለመሆኑ የሚደንግግ ድንጋጌ አይደለም፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ በዚህ ረግድ ያቀረቡትን ክርክር ፍርድ ቤቱ አልተቀበለዉም፡፡
ሌላዉ 1ኛ ተከሳሽ በ1.4 ሚሊዮን ብር ለእርሳቸዉ መጓጓዣ የገዙ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን አንድ ስራ አስኪያጅ እያንዳንዱ የሚፈጽዉ ተግባር የማህበሩን አላማ በሚያሳካ መልኩ ሊፈጽመዉ እንደሚገባ ከንግድ ህጉ እና ከማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ ለመመልከት ይቻላል፡፡ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ካፒታል ሶስት ሚሊዮን በሆነበት ሁኔታ፤ ይህ መኪና የተገዛበት ገንዘብ ለኤሊሲ (LC) ፕሮሰስ ተቀምጦ የነበረ መሆኑ እንዲሁም ማህበሩ ዕቃ የሚያመላልሰዉ በኪራይ በተገኘ በሌሎች ሰዎች ተሽከርካሪ በሆነበት ሁኔታ 1ኛ ተከሳሽ ተሽከርካሪዉን የገዙት የማህበሩን አላማ ለማሳካት ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ ይልቁንም ማህበሩ ከወጭ መድሃኒት እያስመጣ የሚሸጥ እንደመሆኑ የኤሊሲ ፕሮሰሱ እንዲቋረጥ መደረጉ በማህበሩም ሆነ በማህበሩ አባላት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነዉ፡፡ መኪናዉ የተመዘገበዉ በማህበሩ ስም ቢሆንም 1ኛ ተከሳሽ መኪናዉን የገዙት ለማህበሩ ጥቅም ነዉ ሊባል አይችልም፡፡ ግዥዉም የማህበሩን አቅም ያላገነዘበ ነዉ፡፡ በመሆኑም 1ኛ ተከሳሽ መኪናዉን ለግል ጥቅማቸዉ ነዉ የገዙት ከሚባል በቀር ለማህበሩ ጥቅም ነዉ የገዙት ሊባል አይችልም፡፡
ከሳሽ የማህበሩ ሂሳብ በተደጋጋሚ እንዲሰጠዉ ጠይቆ በ1ኛ ተከሳሽ የተከለከለ መሆኑን የቀረቡት የከሳሽ ምስክሮች አስረድተዋል፡፡ ይህም ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 537 የተጠበቀለትን መብት የሚጥስ ተግባር ነዉ፡፡ 1ኛ ተከሳሽም የማህበሩን ሂሳብ የሚያሳይ ሪፖርት ለከሳሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይህን አለማድረጉም 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን በህግ፤ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፉ እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የተጣለባቸዉን ሃላፊነት ያልተወጡ መሆኑን ነዉ፡፡
ከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ ስብሰባ አይጠራም፤ ስብሰባ እንዲጠራልኝም ስጠይቅ ስብሰባ እንዲደረግ አያደርግም የሚል ክርክር ያቀረበ ሲሆን በንግድ ህጉ 532 የማህበሩ አባላት ቁጥር ከ20 በላይ ከሆነ በመተዳደሪያ ደንቡ በተገለጸዉ ቀን ስብሰባ/ጉባኤ ሊደረግ እንደሚገባ የተመለከተ ሲሆን ሌሎች ጉባኤዎችን/ስብሰባዎቸን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ፤ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በሌለበት የማህበሩ ተቆጣጣሪዎች ወይም በማህበሩ ዉስጥ ከግማሽ በላይ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸዉ የማህበሩ አባላት ሊጠሩ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ከሳሽ በ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ዉስጥ ከግማሽ በላይ ድርሻ የሌላቸዉ በመሆኑ ስብሰባ እንዲጠራ ሊያድርጉ አይችሉም፡፡ ይሁን እንጂ በ2ኛ ተከሳሽ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 6.1 መሰረት የማህበሩ የሂሳብ አመት ከተዘጋ ከአራት ወር ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ የማህበሩ የሂሳብ አመት ደግሞ ከሐምሌ 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ እንደሆነ በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10 ተገልጻል፡፡ ይህ ጉባኤ እንዲደረግ ጥሪ የማድረግ ግዴታ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ነዉ፡፡ 1ኛ ተካሳሽ ስብሰባ የማይጠሩ መሆኑን በከሳሽ ምስክሮች የተረጋገጠ ሲሆን በ1ኛ ተከሳሽ በኩል የቀረቡት ምስክሮች 1ኛ ተከሳሽ ስብሰባ ሲጠሩ የነበራ እና ጉባኤዉም ሲካሄድ የነበረ መሆኑን በሚገልጽ መልኩ ምስክርነታቸዉን ሰጥተዉ በከሳሽ ምስክሮች የተሰጠዉን የምስክርነት ቃል አላስተባበሉም፡፡
ከሳሽ 1ኛ ተከሳሽ 2ኛ ተከሳሽ ማህበር ትርፍ እያስመዘገበ ባለበት ሁኔታ በአባላት መካከል ትርፉ እንዳይከፋፈል አድርጓል በማለት ክርክር ያቀረቡ ሲሆን በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 7 መሰረት ዓመታዊ ትርፍ በአባላቱ መካከል የሚከፋፈል መሆኑ የተመለከተ ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩ ትርፍ ያገኘ መሆኑን ሳይክዱ ትርፍ ያልተከፈፈለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የከሳሽም ሆኑ የተከሳሾች ምስክሮች ማህበሩ ያስመዘገበዉ ትርፍ በአባላት መካከል ያልተከፋፈለ መሆኑን መስክረዋል፡፡ ይህም የሚያሳየዉ 1ኛ ተከሳሽ የማህበሩ ወኪል እንደመሆናቸዉ መጠን በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ሃላፊነታቸዉን ያልተወጡ መሆኑን ነዉ፡፡
ሲጠቃለልም 1ኛ ተከሳሽ ማህበሩን የምመራዉ በህግ፤ በመመስረቻ ጽሁፍ እንዲሁም በመተዳዳሪያ ደንቡ መሰረት ነዉ በማለት ክርክር ያቅርቡ እንጂ ማህበሩን በህግ፤ በመተዳደሪያ ደንቡ እና በመመስረቻ ጽሁፉ መሰረት የማይመሩ መሆኑን ከአንድ በላይ የንግድ ማህበራትን በስራ አስኪያጅነት የሚመሩ መሆኑ በመረጋገጡ፤ 1.4 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መኪና መግዛታቸዉ የማህበሩን አላማ ለማሳካት ሊባል የማይችል በመሆኑ፤ ከሳሽ የሂሳብ ሪፖርት እንዲሰጠዉ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸዉ በመረጋገጡ፤ ማሕበሩ ትርፍ ያስመዘገበ ቢሆንም አመታዊ ትርፍ በማህበሩ አባላት መካከል እንዲከፈፈል ያላደረጉ መሆኑ በመረጋገጡ እንዲሁም የማህበሩ አባላት ዓመታዊ ጉባኤ/ስብሰባ እንዲደረግ የማያደርጉ መሆኑ በመረጋገጡ፤ እነዚህም ድርጊቶች በንግድ ህጉ አንቀጽ 527(5) መሰረት ስራ አስኪያጁን ለመሻር የሚያበቁ በቂ ምክንያቶች በመሆናቸዉ 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነት ሊሻሩ ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡
2ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ተከሳሾች የማህበሩ ሂሳብ በገለልተኛ የሂሳብ አጣሪ/ባለሙያ ተጣርቶ የሚያውቅ ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ከሳሽም የማህበሩ ባለድርሻ እንደመሆኑ መጠን የማህበሩ ሂሳብ እንዲጣራ የመጠየቅ በህግ የተሰጠዉ መብት አለዉ፡፡ በመሆኑም የ2ኛ ተከሳሽ ሂሳብ በገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ ሊጣራ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡ ከሳሽ የጠየቁትን የትርፍ ክፍፍል የማህበሩ ሂሳብ ተጣርቶ ከቀረበ በኃላ የሚወሰን ነዉ፡፡
3ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 537 መሰረት የማህበሩን የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዝገቢያ ሰነዶች የማግኘት መብት አለዉ፤ ተከሳሾች እነዚህን ሰነዶች ለከሳሽ የሰጡ ስለመሆኑ ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ስለሆነም ተከሳሾች የማህበሩን የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዘገቢያ ሰነዶች ኮፒ ለከሳሽ ሊሰጡ ይገባል ተብሎ ተወስኗል፡፡
4ኛዉን ነጥብ በተመለከተ ከሳሽ የማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅ እንደሆኑ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ/ም የተያዘዉ እና በሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ምዝገባ ጽ/ቤት የተመዘገበዉ ቃለ ጉባኤ ያስረዳል፡፡ ይህ ቃለ ጉባኤ ደግሞ ቀደም ሲል የነበረዉን የማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ የሚያሻሽል እንዲሁም ቀደም ሲል የነበሩትን የማህበሩን ምክትል ስራ አስኪያጅ ሽሮ በከሳሽ የሚተካ ነዉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ/ም በማህበሩ አባላት የተያዘዉ ቃል ጉባኤ የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ አካል ተድርጎ የሚቆጠር ነዉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሳሽን ከማህበሩ ምክትል ስራ አስኪያጅነት መሻር የመተዳደሪያ ደንቡን እንደማሻሻል የሚቆጠር በመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 536(2) መሰረት ከማህበሩ አባላት በሶስት አራተኛ ድምጽ ሊደገፍ ይገባል፡፡ በሌላ አነጋገር 1ኛ ተከሳሽ ከሳሽን ከምክትል ስራ አስኪያጅነት ስልጣናቸዉ የማሰናበት ህጋዊ ስልጣን የላቸዉም፡፡ በመሆኑም ከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ በመሆናቸዉ፤ ተከሳሾች በማስረጃት ያቀረቡት የፍርድ ቤት ዉሳኔዎችም ከሳሽ ከቴክኒካል ማናጀርነታቸዉ የተሰናበቱ መሆኑን እንጂ ከምክትል ስራ አስኪያጅነታቸዉ የተሰናበቱ መሆኑን የማያሳይ በመሆኑ እንዲሁም ከሳሽ የማህበሩ አባል በመሆናቸዉ የማህበሩን እንቅስቀሳሴ የመከታተል ህጋዊ መብት ስላላቸዉ ተከሳሾች ከሳሽ ወደ ማህበሩ ቅጥር ግቢ እንዳይገባ እና በምክትል ስራ አስኪያጅነት የስራ ድርሻዉ ስራ እንዳይሰራ የሚያደርጉትን ክልከላ ሊያቆሙ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡
በመጨረሻም ተከሳሾች የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ፤ መተዳደሪያ ደንብ፤ ግራ ቀኙ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 199809 በሚያደርጉት ክርክር የቀረበዉ ክስ እና መልስ፤ ግራ ቀኙ አድርጓል የተባለዉን የብድር ውል፤ የማህበሩን የሂሳብ አያያዝ እና የኦዲት ሪፖርት፤ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 173410 የቀረበዉ የወንጅል ክስ መዝገብ እንዲሁም ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የተሰናበተዉ የዲሲፕሊን ጥፋት ፈጽሞ መሆኑን ያስረዳልናል በማለት በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145 መሰረት እንዲቀርቡላቸዉ የጠየቁ ሲሆን የማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ በከሳሽ በኩል የቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች እነዚህ በከሳሽ በኩል የቀረቡት የማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ትክክለኛ ቅጂ አይደሉም በማለት ያቀረቡት ክርክር የለም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እነዚህ ሰነዶች በድጋሚ እንዲቀርቡ የሚታዘዝበት የህግ አግባብ ካለመኖሩም በላይ ሰነዶቹ በማህበሩ የሚገኙ ከመሆኑ አንጻር በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለማስቀርብ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145(2) እና 145(3) ስር የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያሟሉ አይደሉም፡፡ በነዚህም ምክንያቶች ፍርድ ቤቱ ከላይ የተጠቀሱትን ማስረጃዎች ሳያስቅርብ ቀርቷል፡፡ እንዲሁም ግራ ቀኙ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 199809 በሚደርጉት ክርክር የቀረበዉ ክስ እና መልስ እንዲሁም ግራ ቀኙ አድርጓል የተባለዉን የብድር ውል ተከሳሾች ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝላቸዉ ጠይቀዉ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝ የተደረገ በመሆኑ በድጋሚ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145 እንዲቀርቡ የሚታዘዝበት አግባብ ስለሌለ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች በዚህ ረግድ ያቀረቡትን ጥያቄ አልተቀበለዉም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሾች በ1ኛ ተከሳሽ ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 173410 የቀረበዉ የወንጅል ክስ መዝገብ እንዲሁም ከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር የተሰናበተዉ የዲሲፕሊን ጥፋት ፈጽሞ መሆኑን ያስረዳልናል በማለት ፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 145 መሰረት እንዲቀርብላቸዉ የጠየቁትን ማስረጃዎች ለተያዘዉ ጉዳይ ትክክልኛ ፍርድ ለመስጠት የማይረዱ ለአስረጂነትም ተገቢነት የሌላቸዉ ማስረጃዎች በመሆናቸዉ የተከሳሾች ጥያቄ ተገቢነት የሌለዉ ሆኖ ስለተገኘ ፍርድ ቤቱ ሳያስቀርባቸዉ ቀርቷል፡፡
ዉሳኔ
- 1ኛ ተከሳሽ ከ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ስራ አስኪያጅነት ከዛሬ ጀምሮ ተሽሯል፡፡
- የምድቡ ሬጅስተራር ጽ/ቤት የማህበሩ አባላት ገለልተኛ ስራ አስኪያጅ እንዲመርጡ የማህበሩን ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራ ባለሙያ ይመድብ፡፡
- የ2ኛ ተከሳሽ ማህበር ሂሳብ በገለልተኛ የሂሳብ አጣሪ እንዲጣራ ተወስኗል፡፡ በመሆኑም የምድቡ ሬጅስተራር ገለልተኛ የሂሳብ ባለሙያ እንዲመድብ ታዟል፡፡
- ተከሳሾች የማህበሩን የሂሳብ ሪፖርት ሰነዶች እና የንብረት መመዝገቢያ ሰነዶች ኮፒ ለከሳሽ ይሰጡ፡፡
- ተከሳሾች ከሳሽ ወደ ማህበሩ ቅጥር ግቢ እንዳይገባ እና በምክትል ስራ አስኪያጅነት የስራ ድርሻዉ ስራ እንዳይሰራ የሚያደርጉትን ክልከላ ሊያቆሙ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡
- ከሳሽ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅርብ መብቱ ተጠብቋል፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ ለጠየቀ መዝገቡ ተገልብጦ ይሠጠው፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡
የማይነበብ የዳኛ ፊርማ አለበት