- Details
- Category: የንግድ ችሎት ውሳኔዎች
- Abyssinia Law | Making Law Accessible! By
- Hits: 4042
የኮ/መ/ቁ 161457 - የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር እና አፍሪካ ጁስ ቲቪላ አ/ማ
የመ/ቁጥር 161457
ቀን 29/04/12
ዳኛ፡- አሸናፊ ለሜቻ
ከሳሽ፡-የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር፡- ነ/ፈ ምህረቱ መኮንን፡- ቀረቡ
ተከሳሽ፡- አፍሪካ ጁስ ቲቪላ አ/ማ፡- አልቀረቡም
መዝገቡ ለዛሬ የተቀጠረው ለምርመራ ተብሎ ሲሆን ተመርምሮ ተከታዩ ፍርድ ተሰቷል፡፡
ፍርድ
በዚህ መዝገብ የነበረዉን ክርክር ይህ ፍርድ ቤት ተመልክቶ ሰኔ 6 ቀን 2009 ዓ/ም ዉሳኔ የሰጠ ቢሆንም ከሳሽ በተሰጠዉ ዉሳኔ ቅር በመሰኘት ይግባኛዉን ለፌዴራል ክፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበዉ የፌ/ከ/ፍ/ቤትም ጉዳዩን ሲመለከት ቆይቶ ይህ ፍርድ ቤት የሰጠዉን ዉሳኔ በመ/ቁ 202266 በቀን 21/10/2010 ዓ/ም በመሻር በነጥብ የመለሰዉ በመሆኑ በድጋሚ ለችሎት ቀርቧል፡፡
ከሳሽ ባቀረቡት የክስ አቤቱታ ከአፍሪካ ጁስ ቢቪ ጋር በፈጸሙት የኢንቨስትመንት ውል መሰረት አፍሪካ ጁስ ቲቪላ አ/ማህበርን ህዳር 16/2001 ዓ/ም የመሰረቱ መሆኑን ከሳሽ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር በእጁ የነበረውን ቲቪላ የእርሻ ልማት ንብረቶችን በአይነት ያዋጣ መሆኑን አፍሪካ ጁስ ቢቪ የተባለው የተከሳሽ ባለአክሲዮን ደግሞ በአሜሪካ ዶላር ሊያዋጣ ከሚጠበቅበት ጠቅላላ ክፍያ ውስጥ 25 በመቶዉን በቅድሚያ ከፍሎ ቀሪውን መዋጮ ደግሞ ኩባንያው ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ ዶላር በተከታታይ ዓመታት ለመክፈል የተስማማ መሆኑን ይሁን እንጂ አፍሪካ ጁስ ቢቪ በገባዉ ግዴታ መሰረት ግዴታዉን ያልተወጣ መሆኑን ተከሳሽ ከንግድ ህጉና ከማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ውጪ ለከሳሽ ጥሪ ሳያደርግ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ተድርጎ የተከሳሽ ማህበር ካፒታል ከህግ አግባብ ወጭ እንዲያድግ ዉሳኔ የተሰጠ መሆኑን፤ስብሰባዉ የተጠራው በከሳሽ እና በአፍሪካ ጁስ ቢቪ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በኦዲተሮች የተጠራ ስብሰባ ሆኖ ሳለ የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ መደረጉ አግባብነት የሌለዉ መሆኑን ገልጸዉ ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ሕገወጥ ተብሎ እንዲወሰንላቸዉ፤ተከሳሽ ማህበር እንዲያድግ ዉሳኔ የተሰጠዉ ከህግ አግባብ ወጭ ስለሆነ እንዲሻር እንዲወሰንላቸዉ፤የተከሳሽ ማህበር የኦዲት ሪፖርቱ ባለሰክሲዮኖች በጠቅላላ ጉባኤ ባልተገኙበት የፀደቀ በመሆኑ እንዲሻር እንዲወሰንላቸዉ፤በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ የፀደቀው የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ እንዲታገድ እንዲወሰንላቸዉ እንዲሁም በዚህ ክስ ምክንያት የደረሰባቸዉን ወጪና ኪሳራ ተከሳሽ እንዲተከላቸዉ እንዲወሰንላቸዉ ዳኝነት ጠይቋል፡፡
ከሳሾች ክሱን ያስረዱልኛል ያሏቸውን የሰነድ ማስረጃዎች አቅርበዋል የሰዉ ምስክሮችም ቆጥረዋል፡፡
ተከሳሽ በከሳሽ የቀረበዉ የክስ አቤቱታ ከነአባሪዎቹ ድርሶት የመከላከያ መልሱን ያቀረበ ሲሆን ባቀረበዉ የመከላከያ መልስም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የፍሬ ነገር መልስ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሽ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት የስር ነገር ስልጣን የለዉም እንዲሁም ክሱም የቀረበዉ ቃለ ጉባኤዉ ከጸደቀ ከሶስት ወር በኃላ ስለሆነ የቀረበዉ ክስ በይርጋ ቀሪ ነዉ በማለተ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያቀረቡ ሲሆን በፍሬ ነገሩ ላይ በሰጡት መልስ በከሳሽ ህገ ወጥ ነዉ የተባለዉ ስብሰባ ባሰክሲዮኖች ሰዓትና ቦታው ላይ ተስማምተውበት በኦዲተሮች የተጠራ ስብሰባ መሆኑን አፍሪካ ጁስ ቢቪ የሚጠበቅበትን ክፍያ ታህሳስ 2006 ዓ/ም የተከፈለ መሆኑን እንዲሁም ክፍያውም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በብሄራዊ ባንክ እውቅና ያገኘ መሆኑን በከሳሽ እንዲሻር የተጠየቀዉ ቃለ ጉባኤ የከሳሽ ተወካዮች በተሳተፉበት በሙሉ ድምጽ የፀደቀና የተመዘገበ በመሆኑ ስለሆነ ሊሻር አይገባዉም በማለት መልሱ ሰጥቷል፡፡
ፍ/ቤቱም ሕዳር 29 ቀን 2012 ዓ/ም በዋለው ችሎት ክስ የሰማ ሲሆን በዚህም መሰረት ግራ ቀኙ ክስና መልሳቸዉን አጠናክረዉ ተከራክረዋል፡፡
የግራ ቀኙ ክርክር ከላይ የተመለከተዉን ሲመስል ፍ/ቤቱም ተከሳሽ ማህበር ሕዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በደረገዉ ሰብሰባ የማህበሩን ካፒታል በማሳደግ፤የማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በመጽደቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር በመተካት ዉሳኔ ያስተላለፈበት ቃለ ጉባኤ ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም የሚለዉን ነጥብ እንደሚከተለዉ መርምሯል፡፡
እንደመረመረዉም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 212/1/ሠ ላይ ከተዘረዘሩት የንግድ ማህበራት መካከል አንዱ አክሲዮን ማህበር ሲሆን አክሲዮን ማህበር ላይ ተፈጻሚነት የላቸዉ ድንጋጌዎች ድግሞ በንግድ ሕጉ በጠቅላለዉ ስለ ንግድ ማህበራት የተደነገጉት ድንጋጌዎች ማለትም ከአንቀጽ 210-218 እንዲሁም አክሲዮን ማህበርን ብቻ የሚመለከቱ በንግድ ህጉ ከአንቀጽ 305-509 የተመለከቱት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የጸደቀዉ ቃለ ጉባኤ ሊሻር ይገባል ወይስ አይገባም ለሚለዉ ነጥብ ምላሽ ከመስጣታችን በፊት ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የተደረገው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የተካሄደዉ ለባለ አክሲዮኖች በሕግ አግባብ ጥሪ ተድርጎ ነዉ ወይስ አይደለም እንዲሁም ዉሳኔዎቹ የተላላፉት በንግድ ህጉ የተቀመጡት ቅደመ ሁኔታዎች ተሟልተዉ ነዉ ወይስ አይደለም የሚሉትን ነጥቦች ማየቱ ጠቃሚ ነዉ፡፡
በአክሲዮን ማህበር የባለአክሲዮች ጠቅላላ ጉባኤ ሁለት አይነቶች ሲሆነ እነርሱም የባለአክሲዮኖች መደበኛ እና ደንገተኛ የባለአክሲዮች ጠቅላላ ጉባኤ ስለመሆናቸዉ በንግድ ሕጉ 390 ተደንግጓል፡፡
በንግድ ህጉ አንቀጽ 388 እንደተደነገገዉ በህግ አግባብ የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ ተድርጎ የተላላፉ ዉሳኔዎች ሁሉንም የማህበሩ አባላት ሊያስገደዱ እንደሚችሉ የተመለከተ ሲሆን ባለአክስዮኖች የማህበሩ ባለአክሲዮን በመሆናቸዉ የተገናጸፉትን መብቶች ማለትም በጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሚተላላፉ ዉሳኔዎች ላይ ድምጽ የመስጠት መብታቸዉን ሊነፈጉ የማይገባ ስለመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 389 ተደንግጓል፡፡
በንግድ ሕጉ አንቀጽ 391/1 መሰረት ጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ ማድረግ የሚችሉት ዳይሬክተሮች፣ ኦዲተሮች፣ሂሳብ አጣሪዎች ወይም አስፈላጊ ሲሆን ፍ/ቤቱ የሚሰይማቸዉ አካላት ስለመሆናቸዉ ተመልክቷል፡፡በዚህ ድንጋጌ መሰረት በመርህ ደረጃ የባለአክሲዮኖችን ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ግዴታና ስልጣን ያላቸው ዳይሬክሮች ሲሆኑ ኦዲተሮች፤ሂሰብ አጣዎች እና በፍርድ ቤት የሚሰየሙ አካላት በልዩ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠሩ እንዲችሉ አግባብነት ያላቸዉ የንግድ ህጉ ድንጋዎች የሚያስረዱ ሲሆን ኦዲተሮች በንግድ ሕጉ አንቀጽ 377/1 እና 351/4 የተገለጹት ሁኔታዎች ሲከሰቱ ማለትም ዳይሬክተሮች ጠቅላላ ጉባኤ በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ስብሰባ ሳይጠሩ የቀሩ እንደሆነ ኦዲተሮች በዳይሬክቶረቹ ቦታ ተተክተው ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠሩ እንደሚችሉ ዳይሬክተሮች በተለያዩ ምክንያቶች ስልጣን ላይ ከሌሉ የማህበሩ ኦዲተሮች የባለአክሲዮኖን ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት እንደሚችሉ ተድንግጓል፡፡
ዳይሬክተሮች የማህበሩ የሂሳብ ዓመት በተጠናቀቀ በአራት ወር ጊዜ ዉስጥ መደበኛ ጠቅላላ የባለአክሲዮች ስብሰባ መጥራት ያላባቸዉ መሆኑን ይህ የአራት ወር ጊዜ አስከ ስድስት ወር በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ ሊራዘም እንደሚችል በንግድ ህጉ አንቀጽ 418 ተመልክቷል፡፡ የባለአክሲዮች ጠቅላላ መደበኛ ስብሰባ ከመደረጉ አስራ አመስት ቀናት ቀደም ብሎ የማህበሩ ባለ አክሲዮኖች ለመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርበዉን የማህበሩን የሂሰብ ሚዛን፤የትርፍ እና ኪሳራ መገልጫ እንዲሁም የኦዲተር ሪፖረት ማግኝት ያለባቸዉ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 418 የተመለከተ ሲሆን በመደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚከናወኑ ተግባራት በንግድ ህጉ አንቀጽ 419 የተገለጹ ሲሆን እነዚህም የማህበሩን ሂሳብ ሚዛን፤የትርፍ እና የኪሳራ መገለጫ እንዲሁም የኦደተሮችን ሪፖርት መርምሮ ማጽደቅ ወይም ወድቅ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 419(2) ሰር የተገለጹት ሌሎች ተግባሮችም ይከናወናሉ፡፡
ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ከመደረጉ 15 ቀናት ቀደም ብሎ የማህበሩ ባለአክሲዮኖች በደንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤዉ ሊተላላፉ የታሰቡትን የዉሳኔ ሀሳቦችሰ እና የኦዲተር ሪፖርት ሊያገኙ የሚገባ ስለመሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 422 የተደነገገ ሲሆን የአክሲዮን ማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ሊሻሻሉ የሚችሉት በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 423 በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በተለይም የማህበሩን ዜገነት ለመቀየረ እንዲሁም ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸዉን እንዲያሳደጉ በቀረበ የዉሳኔ ሀሳብ ላይ ሁሉም ባአክሲዮች መገኝት ወይንም መወከል ያለባቸዉ መሆኑን እነዚህን የዉሳኔ ሀሳቦችም በባለአክሲዮኖች በሙሉ ደምጽ ካልተደገፉ ተቀባይነት የሌላቸዉ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 425 ተድንግጓል፡፡
የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤም ሆነ ደንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ የሚደረገበት መንግድ በንግድ ህጉ አንቀጽ 392 የተደነገገ ሲሆን ለባለአክሲዮኖች የሰብሰባ የጥሪ ማስታወቂያ ከ15 ቀናት በፊት ቀድሞ ብሎ ሊደረሳቸዉ የሚገባ መሆኑ እንዲሁም በሰብሰባ ላይ ወይይት የሚደረግባቸዉ አጀንዳዎች በጥሪ ማስታወቂያ ላይ መገለጽ ያለባቸዉ ስለመሆኑ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 395፤396 እና 397 መረዳት የሚቻል ሲሆን አንድ ስበሰባዉ አይነት ምለዓት ጉባኤ ካልተሟለ እና አሰፈላጊዉ ደምጽ ካላተገኘ በአጀንዳ ላይ የተገለጹትን የዉሳኔ ሀሳቦች ለማጽደቅ የማይቻል ስለመሆኑ በንግድ ህጉ 399(1) ተመልክቷል፡፡
ሌላዉ መነሳት ያለበት ነጥብ በንግድ ህጉ አንቀጽ 415 የማህበሩ ባለአክሲዮኖች የሚያካሂዱት ኢንፎርማል ጠቅላላ ጉባኤ ሲሆን ይህም የማህበሩ ሁሉም ባለአክሲዮኖች የተገኙ እንደሆነ ወይንም የተወከሉ እንደሆነ በስምምነት ምንም አይነት ቀድመ ሁኔታ ሳያስፈልግ ጠቅላላ ጉባኤ ሊያካሂዱ የሚችሉ መሆኑን በዚህ አይነት ሁኔታ በሚካሄድ ጠቅላላ ጉባኤም ማናቸዉንም አይነት ዉሳኔ ሊያስተላልፍ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
ከላይ ለማብራረት ከተሞከሩት ደንጋጌዎች አንጻር የተያዘዉን ጉዳይ ስንመለከተ ተከሳሽ ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በተደረገዉ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከሳሽ እንዲሳተፍ ጥሪ አድርጊያለሁ በማለት ክርክር ያቀረበ ቢሆንም እራሱ ተከሳሽ ካቀረበዉ ማስረጃ ለመመለከት እንደሚቻለዉ ጥሪ የተደረገዉ ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ/ም ሲሆን ሰብሰባዉ የተካሄደዉ ድግሞ ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም ነዉ፡፡ ከዚህም መረዳት የሚቻለዉ ተከሳሽ በንግድ ህጉ አንቀጽ 395 እና በማህበሩ መተዳዳሪያ ደንብ መሰረት ከሳሽ በጠቅላላ ጉባኤዉ ላይ እንዲሳተፍ በህጉ አግባብ ከስበሳዉ 15 ቀናት ቀደም ብሎ ጥሪ ያላደረገ መሆኑን ነዉ፡፡ ተከሳሽ ለከሳሽ ከአስራ አምስት ቀናት በፊት የጥሪ ማስታወቂያዉ እንዲደርሰዉ ያልተደረገዉ ቀደም ሲል ሁሉም ባለአክሲዮኖች በተገኙበት ሰብሰባ ላይ የሰብሰባዉ ቦታ እና ሰብሰባዉ የሚካሄደበት ቀን በመወሰኑ ነዉ በማለት ክርክር ያቀረበ ቢሆንም ይህን ፍሬ ነገር በማስረጃ ከላማረጋገጡም በላይ ከላይ የተጠቀሰዉ ደንጋጌ ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ከመደረጉ በፊት ከ15 ቀናት በፊት በህጉ በተመለከተዉ ሁኔታ ጥሪ ሊደረግላቸዉ የሚገባ መሆኑን በአስገዳኝነት የሚደነግግ በመሆኑ ባለ አክሲዮኖቹ ቀደም ብሎ በነበረዉ ስበሰባ ላይ የሰብሰባ ቀኑን መወሰናቸዉ ተከሳሽ ከላይ በተጠቀሰዉ ድንጋጌ መሰረት እና በማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ መሰረት ከስበሰባዉ 15 ቀናት ቀደም ብሎ ለባለአክሲዮኖች ጥሪ የማደረግ ግዴታዉን የሚያስቀር አይደለም፡፡
ተከሳሽ ማህበር በጠራዉ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ወይይት የሚደረግባቸዉ አጀንዳዎች በጥሪ ማስታወቂያ ላይ መገለጽ ያለበት ስለመሆኑ ከንግድ ህጉ አንቀጽ 395፤396 እና 397 መረዳት የሚቻል ቢሆንም ተከሳሽ ማህበር ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በአካሄደዉ ጠቅላላዉ ጉባኤ የማህበሩን ካፒታል በማሳደግ፤የማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በመጽድቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር በመሻር በሌላ ዳሬክትር ተክቷል፡፡ እነዚህን የስብሰባ አጀንዳዎች ተከሳሽ ለከሳሽ በላከዉ የጥሪ ማስታወቂያ ላይ ያልተገለጹ መሆናቸዉን ተከሳሽ ካቀረበዉ ማስረጃ መረዳት የሚቻል ሲሆን በማህበሩ ኦዲተሮች ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ/ም የተጠራዉ ሰብሰባ አጀንዳም በባአክሲዩኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትን ለመፈታት ስለመሆኑ በጥሪ ማስታወቂያዉ በግልጽ ስፍሯል፡፡ ይህም የሚያሳየዉ ተከሳሽ ማህበር ከላይ የተገለጹትን ዉሳኔዎች ያስተላለፈዉ በንግድ ህጉ እና በማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ የተቀመጡትን ቅደመ ሁኔታዎች ሳያሟላ መሆኑን መገንዘብ ይቻልል፡፡
ተከሳሽ የማህበሩን የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ አድርጊያለሁ በማለት የሚከራከረዉ የማህበሩ ኦዲተሮች ጥቅምት 24/2009 ዓ.ም ለማህበሩ ባለአክሲዮኖች ጥሪ ያደረጉትን ደብዳቤ መነሻ በማደረግ ሲሆን ኦዲተሮቹ ስብሰባ የጠሩት በባአክሲዩኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት የኦዲት ሪፖርት ለመስራት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ኦዲተሮች በንግድ ሕጉ አንቀጽ 377/1 እና 351/4 መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠሩ የሚችሉት የማህበሩ ዳይሬክተሮች በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ስብሰባ ሳይጠሩ የቀሩ እንደሆነ ወይንም የማህበሩ ዳይሬክተሮች በተለያዩ ምክንያቶች ስልጣን ላይ በሌሉ ጊዜ መሆኑን መገንዘብ የሚቻል ቢሆንም ተከሳሽ የስብሰባ ጥሪ በኦዲተሮች የተከናወነዉ ከላይ የተገለጹት ሁኔታዎች ተክስተዉ ስለመሆኑ ያቀረበዉ ክርክርም ሆነ ማስረጃ የለም፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ በኦዲተሮች የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ የተደረገ ስለሆነ ስብሰባዉ ህጋዊ ነዉ በማለት ያቀረበዉ ክርክር የህግ መሰረት ያለዉ አይደለም፡፡
አንድ ባለአክሲዩን በባአክሲዩኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የመገኘት ድምፅ የመስጠት የማህበሩን ውሳኔ የመቃወም ካልፈለገ በስተቀር ፍጽማዊ መብቱ (Inherent right) መሆኑን የንግድ ሕጉ አንቀጽ 389 የሚደነግግ ሲሆን የንግድ ሕጉ አንቀጽ 388 ደግሞ የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ገዥ የሚሆነው በሕግ አግባብ ሲደረግ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ ማህበር የከሳሽ መብትን በመገድብ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ/ም የተለያዩ ዉሳኔዎች ያስተላላፈ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
በመጨረሻም የአክሲን ማህበሩ መመሰረቻ ጽሁፍ እና መተዳደሪያ ደንብ ሊሻሻሉ የሚችሉት በድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 423 በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን በተለይም የማህበሩን ዜገነት ለመቀየረ እንዲሁም ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸዉን እንዲያሳደጉ በቀረበ የዉሳኔ ሀሳብ ላይ ሁሉም ባአክሲዮች መገኝት ወይንም መወከል ያለባቸዉ መሆኑን እነዚህን የዉሳኔ ሀሳቦችም በባለአክሲዮኖች በሙሉ ደምጽ ካልተደገፉ ተቀባይነት የሌላቸዉ መሆኑ በንግድ ህጉ አንቀጽ 425 ተድንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ በተያዘዉ ጉዳይ ከሳሽ በጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኘ ስለመሆኑ እንዲሁም የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ ድምጽ የሰጠ ስለመሆኑ በተከሳሽ በኩል የቀረበ ማስረጃ የለም ከዚህም መረዳት የሚቻለዉ ተከሳሽ ማህበር የማህበሩ ካፒታል እንዲያድግ ያደረገዉ የንግድ ህጉ አንቀጽ 425ን በሚቃረን መልኩ መሆኑን መገንዘብ የሚቻል ከመሆኑም በላይ በንግድ ህጉ አንቀጽ 467 እንደተደነገገዉ የማህበሩ ሙሉ ካፒታል ክፍያ ሳይፈጸም የማህበሩን ካፒታል አዳዳስ አክሲዮኖችን ለሽያጭ በማቅርብ ማሳደግ የማይቻል ስለመሆኑ ገልጽ ከልከላ የተቀመጠ ሆኖ ሳለ የተከሳሽ ማህበር ሙሉ ካፒታል በባለአክሲዮኖች ሙሉ ለሙሉ ሳይከፍል አዳዳስ አክሲዮኖችን ለሽያጭ በማቅርብ የማህበሩ አክሲዮን እንዲያድግ መደረጉ አግባብነት የሌለዉ በመሆኑ ተቀባይነት የለዉም፡፡
ሲጠቀለልም ተከሳሽ ማህበር ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም የማህበሩን ካፒታል በማሳድግ፤ የማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በማጽደቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር አንዲሻሩና በምትካቸዉ ሌላ ዳሬክተር በመሾም ዉሳኔዎች ያስተላለፈዉ በንግድ ህጉ ስለ ጠቅላላ ጉባኤ አጠራር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች የማህበሩን መተዳዳሪያ ደንብ ሳያከብር በመሆኑ፤ዉሳኔዎቹ የተላላፉት ዉሳኔዎቹን ለማስተላላፍ የሚያስፈልገዉ ምላዓት ጉባኤ እና የሚያሰፈልገዉ ድምጽ ሳይሟል በመሆኑ እንዲሁም የሰብሰባ ጥሪ ለማድረግ ስልጣን የተሰጠዉ አካል ጥሪ ሳያድርግ የተላላፉ ዉሳኔዎች በመሆናቸዉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ማህበር ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም በአካደዉ ስበሰባ ያስላለፋቸዉ ዉሳኔዎች እና የተያዘዉ ቃለ ጉባኤ በንግድ ህጉ አንቀጽ 416(5) መሰረት ተሸሯል፡፡
ዉሳኔ
- ተከሳሽ የማህበሩን ካፒታል በማሳድግ፤vየማህበሩን ኦዲት ሪፖርት በማጽደቅ እንዲሁም የማህበሩን ዳሬክተር አንዲሻሩና በምትካቸዉ ሌላ ዳሬክተር በመሾም ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ/ም ያስተላላፋቸዉ ዉሳኔዎች እና ቃለ ጉባኤዉ እንዲሻር ተወሰኗል፡፡
- ወጪና ኪሳራ ተከሳሽ ለከሳሽ በቁርጥ ብር 3,000 (ሶስት ሺህ) ይክፈል፡፡
ትዕዛዝ
- ይግባኝ ለጠየቀ ግልባጭ ይሰጥ፡፡
- መዝገቡ ተዘግቷል ወደ መዝገብ ቤት ይመለስ፡፡