ለፌዴራል እና ለክልል ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የሕዝብ እንደራሴዎችን ለመምረጥ የሚከናወነው መጪው አገር አቀፍ ምርጫ ከተደጋጋሚ መስተጓጎሎች በኋላ የድምጽ መስጫ ዕለቱ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲደረግ ቀን ተቆርጦለት ዝግጅቶቹ ቀጥለዋል፡፡ ይህ ምርጫ ከዓመት በፊት ማለትም በሕገ-መንግሥታዊ ትርጉም ከመራዘሙ በፊት ካለው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር፤ በትግራዩ ጦርነት፣ በሰላምና ደህንነት ስጋቶቹ፣ የተዳከመው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣ የተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች እስር፣ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እና የውጪ አገራት ጫና ያደበዘዘው ይመስላል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን፤ ድህረ-2010 የታዩት የሕግ እና የተቋማት ማሻሻያዎች፣ አንጻራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የሲቪክ ምሕዳሮች ስፋት የዘንድሮውን ምርጫ በጉጉት ተጠባቂ እንዲሆን ማድረጋቸው አልቀረም፡፡
ምርጫ 2013 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳውን ይፋ ካደረገበት ወርኃ ጥር ጀምሮ እስካሁን ድረስ በርከት ያሉ የቅድመ-ምርጫ ተግባራት ተከናውነውበታል። ከእነዚህ መካከል የምርጫ ቁሳቁሶች ዝግጅት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ የእጩዎች ምዝገባ፣ የመራጮች ትምህርት እና የመራጮች ምዝገባ ተጠቃሽ ክንውኖች ናቸው።
በእነዚህ ወሳኝ የቅድመ-ምርጫ ክንውኖች ውስጥ የተነሱት እና በቀሩት ጊዜያትም ሊነሱ የሚችሉት በተለይም የሕግ ጉዳዮች የዘንድሮውን ምርጫ የተለየ መሆንነት አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ለአብነት እንኳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ያስከተለው ውዝግብ፣ ከፌዴራሉና ከሌሎቹ ክልሎች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ቀን ተለይቶ የነበረው የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ምክር ቤቶች ምርጫ ጉዳይ፣ የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች የምርጫ ጣቢያዎች ውዝግብ፣ የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ምርጫ እና አነጋጋሪው የእጩዎች ምዝገባ የፍርድ ቤቶች ክርክር የዘንድሮው ምርጫ በቀጣይ ለሚከናወኑ ምርጫዎች አስቀምጦ የሚያልፈው ልምምድ ቀላል የሚባል አለመሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡
ወሳኝ የምርጫ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ልዩ ልዩ ተቋማት መካከል ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤቶች እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በእስካሁኖቹ የምርጫ ሂደቶች ያሳዩት ጥረት የምንመኘውን ነጻ፣ ትክክለኛ እና ተዓማኒ ምርጫ ወደፊት ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ ናቸው። በዚያው ልክ ግን በሒደቶቹ ውስጥ የታዩ የጎሎ ክፍተቶች የዘንድሮውን ጨምሮ በቀጣይ ለሚደረጉትም ምርጫዎች የራሳቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም።
በመሆኑም፤ ከእስካሁኑ የቅድመ-ምርጫ ክንውኖች መካከል የታዩ ጉልህ ክፍተቶችን በመለየት የሚሻሻሉበትን መንገድ መወያየት ይበጃል በማለት፤ በዚህ ጽሁፍ በመራጮች ምዝገባ ወቅት በስፋት ስለተስተዋለው የመራጮች በምርጫ ለመሳተፍ ፍላጎት ማጣት (Voters Apathy) ምክንያቶችና ከፖለቲካዊ መፍትሔዎች ባሻገር ሊወሰዱ የሚገቡ የፖሊሲ አማራጮች ዙሪያ አንዳንድ ሀሳቦች እናነሳለን።
የመራጮች ምዝገባ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ለመክፈት በነበረ መዘግየት እና በምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት ችግሮች ምክንያት የዕጩዎች ምዝገባ በታሰበለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ በሁሉም ክልሎች ከመጋቢት 16 - ሚያዚያ 16 2013 ዓ.ም ድረስ እንዲከናወን ተወስኖ እንደነበር አይዘነጋም። ይህም ቀደም ሲል ከየካቲት 22 - መጋቢት 21 ድረስ እንዲከናወን እቅድ ተይዞለት የነበረውን የመራጮች ምዝገባ ክንውን እቅድ በሦስት ያህል ሳምንታት እንዲዘገይ አድርጎታል።
ከዚህ ማሻሻያ በኋላም ምዝገባው በልዩ ልዩ ምክንያቶች በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ባለመከናወኑ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች እስከ ግንቦት 6 ድረስ፣ በጥቂት የምርጫ ክልሎች ደግሞ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም ሆኗል። የዚህ መስተጓጎል ደግሞ አስቀድሞ ግንቦት 28 ይደረጋል ተብሎ የነበረውን የድምጽ መስጫ ቀን ወደ ሰኔ 14 እንዲገፋ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ አልፏል፡፡
የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮም ሆነ በተደጋጋሚ እንዲራዘም ከተደረገ በኋላ የመራጮች በምርጫው የመሳተፍ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ተቀዛቅዞ ታይቷል። ምርጫ ቦርድ እስካሁን የመጨረሻውን ቁጥር ይፋ ባያደርግም፤ ግንቦት 4 ባወጣው መረጃ መሠረት በዘንድሮው ምርጫ የተመዘገበው አጠቃላይ የመራጮች ብዛት ቁጥር 36.2 ሚሊዮን ገደማ ነው፡፡ ይህ የመራጭ ቁጥር ብዛት የመጨረሻው መጠን በግልጽ እስኪታወቅ ድረስ ካለፉት ሁለት አገር አቀፍ ምርጫዎች አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም ተደርጎ በነበረው ምርጫ በምርጫው የተሳፈው ጠቅላላ ብዛት 31.9 ሚሊዮን ሲሆን፤ በ2007 ዓ.ም ደግሞ 36.8 ሚሊዮን ያህል ነው፡፡
ሒደቱን በቅርበት ለታዘበ ሰው ገዢው ፓርቲ ዓለም አቀፍ ጫናውን በመፍራት እና የምርጫውን ተዓማኒነት አብዝቶ የፈለገው በመሆኑ የታችኛውን የመንግሥት መዋቅር ለመራጮች ምዝገባ ተልዕኮ በስፋት ባያሠማራ ይሔን ያህል ቁጥርም ለመመዝገቡ እርግጠኛ መሆን የሚቻል አይመስልም፡፡ ይሔኛውም አካሄድ ልክ በሶማሌ ክልል እንደታየው ዓይነት ተጨማሪ ችግር ማስከተሉ አልቀረም፡፡
በአጠቃላይ የተመዘገበው መራጭ ቁጥር ብዛት ቀደም ብለው የተደረጉት ምርጫዎች ተዓማኒነት እጅግ አናሳ የነበረ መሆኑ፣ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር እድገት እና ያለፉት ዓመታት የተፈጠረው በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ የሆነ ማኅበረሰብ ከግምት በማስገባት እጅግ አነስተኛ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ቁጥሩ ምርጫ ቦርድ ምዝገባውን ከመጀመሩ አስቀድሞ ከሰራው ትንበያ አንጻር እንኳ ሲተያይ ያልተጠበቀ ነው፡፡
ምርጫ በአንዲት ሉዓላዊት አገር ያሉ እድሜያቸው ለመምረጥ የደረሱ ዜጎች ኁሉ እንዲሳተፉበት የሚጠበቅ (universal suffrage) የፖለቲካ ተሳትፎ ማረጋገጫ ሒደት ነው። ይህ ቅድመ-ሁኔታ በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የሕግ ሰነዶች ውስጥ እውቅና ካላቸው መሠረታዊ የምርጫ አላባዎች ውስጥ ቀዳሚው ነው። የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 54 ልብ ይሏል፡፡
በዚህም ምክንያት የመራጮች ምዝገባ የአንድን ምርጫ ቅቡልነት ከሚወስኑት የምርጫ ሒደቶች መካከል ወሳኝ ሒደት እንደመሆኑ እድሜያቸው ለመምረጥ የደረሱ ዜጎች ኁሉ በምርጫው መሳተፋቸውን ማረጋገጥ ተገቢና አስፈላጊ ነው። ይህን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ገዳቢ ያልሆኑ የመራጭነት መስፈርቶች፣ ምቹና ለመራጩ ማኅበረሰብ ቅርብ የሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ማደራጀት (Accessible and proximate polling stations)፣ ቀልጣፋ የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት፣ የሲቪክ እና መራጮች ትምህርት ተደራሽት የመሳሰሉት ነገሮች መሠረታዊ ናቸው፡፡
ይሁንና ግን፤ በሌሎችም አገራት እንደሚስተዋለው መራጮች በምርጫ ለመሳተፍ ፍላጎት ማጣት (Voters Apaty) ያሳያሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር በተለይም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በብዙ አገራት ዘንድ በስፋት ታይቷል። ለአብነት ያህል በፈረንጆቹ 2019 በደቡብ አፍሪካ ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ከ1999 ወዲህ ዝቅተኛው የመራጭ ቁጥር የተሳተፈበት ሆኖ አልፏል፡፡ ምክንያቱ ይለያይ እንጂ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በካናዳ፣ በናይጄሪያ እና በኡጋንዳም አጋጥሟል፡፡
በዘርፉ የተሠሩ በርከት ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት መራጮች በምርጫ ሂደት ላይ ፍላጎት የሚያጡት በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው የመገለል ስሜት (alienation) ሲሆን፤ ሁለተኛው በአብዛኛው የቀጥታ ዴሞክራሲ በሚከተሉ አገራት ዜጎች ተደጋጋሚ ምርጫ እንዲያደርጉ ሲደርግ የሚመጣ የተሳትፎ ስሜት መቀዝቀዝ ወይም Voter fatigue የሚባለው ነው።
ዜጎች የፖለቲካ ስርዓቱ ምንም የሚፈይድላቸው ነገር እንደሌለ ሲሰማቸው እና ለመለወጥ የሚያደርጉት ሙከራ ፍሬ አልባ እንደሆነ ሲያስቡ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የፍላጎት ማጣት ሊሰማቸው ይችላል። ስር የሰደደ ሙስና፣ ከፍተኛ የሆነ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የኑሮ ውድነት የመሳሰሉት ችግሮች ዜጎች በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጡና ፈጽሞ ተስፋ እንዲቆርጡ ምርጫን ከመሳሰሉ ሰላማዊ የትግል ስልቶች ይልቅ ለአመጻ ድርጊቶችና ሕዝባዊ እምቢተኝነቶች የሚገፋፉ ናቸው። ይህን ዓይነቱ የመገለል ስሜት ሲያጋጥም ዜጎች በተለይም አምባገነን መንግስታት ለይስሙላ በሚያከናውኗቸው ምርጫዎች ላይ አለመሳተፍን በሥርዓቱ ላይ ኩሪፊያቸውን እንደመግለጫ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ ለትንሹም ለትልቁም ጉዳይ ተደጋጋሚ ምርጫዎችን ማድረግም ዜጎች ለምርጫ ያላቸውን ተነሳሽነት ያደክመዋል፣ ጨርሶም ፍላጎት እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር ከላይ እንደጠቀስነው ከውክልና ዴሞክራሲ ይልቅ የቀጥታ ዴሞክራሲን በሚከተሉ አገራት በስፋት የሚታይ ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ አሜሪካ በዚህ ዓይነቱ ችግር በተደጋጋሚ ከተፈተኑ አገሮች መካከል ተጠቃሽ ናት፡፡
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመለስ፤ በዘንድሮው አገር አቀፍ ምርጫ የታየው የመራጮች ፍላጎት ማጣት የልዩ ልዩ ሁኔታዎች ድምር ውጤት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ‹‹ይወክሉኛል የምላቸው ተወካዮች የሉም›› ከሚለው አንስቶ፣ ‹‹ምን ደህና ፓርቲ አለና ነው››፣ ‹‹መረጥኩ አልመረጥኩ አሸናፊው ይታወቃል››፣ ‹‹ምርጫው ምንም ለውጥ አያመጣም››... እስከሚሉት ድምጾች ድረስ በሒደቱ የሚያደርጉት ተሳትፎ ትርጉም አልባ ነው ብለው የሚያምኑት በርካቶች መሆናቸውን ያሳያል።
ዜጎች እንዲህ ዓይነቱን እምነት እንዴት፣ መቼ እና ከምን አመጡት የሚለውን ዘርዘር ባሉ ጥናቶች መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመን፤ አንዳንዶቹን ግን እዚህ ለማንሳት እንሞክር፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ፣ በደርግ እና በኢሕአዴግ ሥርዓቶች ውስጥ ልዩ ልዩ ምርጫዎችን አድርገናል፡፡
ከኢሕአዴግ ወዲህ ያሉትን አምስት አገር አቀፍ ምርጫዎች ያየነ እንደሆነ፤ ነጻ፣ ትክክለኛ እና ተዓማኒ ብሎም ስልጣን በነጻ ሕዝባዊ ፈቃድ ብቻ መመስረት እንደሚኖርበት የተቀመጡትን መሠረታዊ የምርጫ እና ዴሞክራሲ መርሆዎች የተጣሱበት የይስሙላ ምርጫዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ምረጫ 97 ቅድመ-ምርጫ በነበሩት ክስተቶች በበጎ ተጠቃሽ የነበረ ቢሆንም፤ ድህረ-ምርጫ ባስተናገዳቸው ዓይነተ-ብዙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ጠቅላላ ሒደቱን ጥላሸት የቀባ ሆኖ አልፏል፡፡
ከእንዲህ ዓይነቱ ደካማ ልምምድ ባሻገር የምርጫ ሕጉ ክፍተቶች እና የአስፈጻሚ ተቋሙ አድርባይነት ዜጎችን ለእንዲህ ዓይነቱ ስሜት ገፋፊ እርሾ ነው፡፡ የምርጫ ሕጉ የሚከተለው በዜጎች ድምጽ አባካኝነቱ የሚተቸው የአብላጫ ድምጽ ሥርዓት፣ የመራጮች ምዝገባ ሒደቱን ቀላል፣ ምቹ እና አካታች ከማደረግ አኳያ እንዲሁም ከድምጽ አሰጣጥ፣ ቆጠራ እና ውጤት አገላለጽ አንጻር የነበሩት የቴክኒክ ውስንነቶች በዚህ አነጻር ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ ከተሰጠው ተልዕኮ በተቃራኒ ለአንድ ፓርቲ ወገንተኝነቱን በሚያሳይ፣ ግልጽነት በጎደለው እና ዝርክርክ አሠራሮችን ይከተል የነበረው ምርጫ ቦርድም ዜጎች በምርጫ ሒደት ላይ ላሳደሩት ደካማ ዝንባሌ ዋነኛው ተጠያቂ ነው፡፡
ከእንዲህ ዓይነቶቹ ታሪካዊ እና መዋቅራዊ ዝንፈቶች ባሻገር፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችም ለምርጫ ፍላጎት ማጣቱ ቀላል የማይባል አስተዋጽዖ ማድረጋቸውም አልቀረም፡፡ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ያለው ከፍተኛ የሆነ የጸጥታና የደህንነት ስጋት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ ሲቪል ማኅበራትና የመሳሰሉት ወሳኝ የምርጫ ተዋንያን ደካማ እንቅስቃሴዎችም ዜጎች ለዘንድሮው ምርጫ ፍላጎት ማጣት የወዲያው ሰበብ የሆናቸው ይመስለኛል።
ምን ተሻለ?
የዜጎችን ስነ-ዜጋዊ ክህሎቶች እና ባህሪያት ማሳደግ ለእንዲህ ዓይነቱ ችግር መፍትሔ በማዋጣት ረገድ ያለው ድርሻ ከፍ ያለው ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ዜጎች ፖለቲካዊም ሆነ ሲቪል ጉዳዮችን የመገምገም እና አቋም የመያዝ ብሎም ተሳትፎ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ ዜጎች ይኼን መሰሉ ስነ-ዜጋዊ ክህሎት (Civic skill) እና መረዳት ሲኖራቸው እንደ ምርጫ ላሉት አገራዊ የሆኑ ጉዳዮች የሚሰጡት ትኩረት ከፍ ያለ እንዲሆን ያስችላል፡፡ ስነ-ዜጋዊ ክህሎቶች ደግሞ በምርጫ ላይ በራስ ፍላጎት መሳተፍን በመሰሉ ስነ-ዜጋዊ ባህሪያት መገለጻቸው የዜጎችን ሙሉ ተሳትፎ ለማረጋገጥ አስፈላጊ ናቸው፡፡
ለዚህ ተልዕኮ ደግሞ ምርጫ ቦርድ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙኃን እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሲቪክ እና መራጮች ትምህርት ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ በዘንድሮው ምርጫ የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ ፈቃድ ከወሰዱ 167 ድርጅቶች መካከል በገጽ ለገጽ ስልጠናም ሆነ በሌሎች አማራጮች ትምህርቱን የሰጡት 86 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ በገንዘብ እጥረት፣ በሰው ኃይል ውስንነትና በመሳሰሉት ምክንያቶች ትምህርቱን አልሰጡም፡፡ ይህ ደግሞ በቀጣይ የሲቪክ ማኅበራቱን አቅም ማሳደግ፣ አዳዲስ የመራጮች ትምህርት ስልቶችን መንደፍ እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በዚህ ዙሪያ እንዲሠሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረጂ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የጎረቤት አገር ኬንያን ተሞክሮ መቅሰም ቢቻል በዘርፉ ብዙ ርቀት መሄድ ያስችላል፡፡ በኬኒያ የሚገኙ የሲቪክ ማኅበራት ለ2017 ፕሬዜዳንታዊ ምርጫ አስቀድሞ ወጣቶችን ማዕከል ባደረገና የዲጅታል አገልግሎት አማራጮችን ተጠቅመው በሠሩት የመራጮች ትምህርት እንቅስቃሴ በምርጫው ቀደም ካሉት ምርጫዎች አንጻር ከፍተኛውን የወጣት መራጮች ቁጥር ለማስመዝገብ ችለዋል፡፡
ከሲቭል ማኅበረሰብ ድርጀቶች በተጨማሪ በአዲሱ የምርጫ ሕግ የመራጮች ትምህርትን እንዲሰጡ እውቅና የተሰጣቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በአሁኑ ምርጫ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ባይታይም፤ በቀጣይ ግን በመራጮች ሆነ በሲቪክ ትምህርቶች ብዙ የሚጠበቅባቸው ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ መገናኛ ብዙኃን የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማሳደግም አስፈላጊ ነው፡፡
ዜጎችን ለምርጫ ፍላጎት እንዲያጡ ሰበብ የሚሆኑ የምርጫ ሥርዓቶችን እና አሠራሮችን ማስተካከልም መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች መካከል ነው፡፡ በአዲሱ የምርጫ ሕግ አዋጅ 1162/2011 ዝግጅት ወቅት ስምምነት ተደርጎበት የነበረው የምርጫ ስርዓቱን ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት መለወጥ በብዙ አንጻር ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም፤ የምርጫ ሥርዓቱን ከአብላጫ ወደ ተመጣጣኝ ድምጽ የምርጫ ሥርዓት ለመቀየር ሕገ-መንግስታዊ ማሻሻያም የሚያስፈልገው በመሆኑ ዝግጅቱ ማድረጉ አስፋለጊ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር ግን፤ በሌሎች አገራት እንደሚታየው የምርጫ ምዝገባውን ማዘመን፣ ማቅለል እና ቀልጣፋ ማድረግ በዘላቂነት ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በየአምስት ዓመቱ ከሚደረጉ የመራጮች ምዝገባዎች ይልቅ ልደት እና ሞትን በተደራጀ መልኩ ከሚሰንደው የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሥርዓት ወይም ከሌሎች አማራጭ ሥርዓቶች ጋር በማስተሳሰር ቋሚ የሆነ ብሔራዊ የመራጮች ቋት በማዘጋጀት ሒደቱን ማቅለል ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡