በአሁኑ ወቅት በስፋት ተቀባይነት ካገኙ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በወንጀል ተከሰው ለጠበቃ የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች የሕግ ድጋፍ መስጠት አንዱ ነው። በመሆኑም ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት የተከሰሱ ሰዎች ካሏቸው ሕገ-መንግስታዊ መብቶች ቀዳሚው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለምን ቢሉ በዓለማቀፋዊም ይሁን በአሕጉራዊ ስምምነቶች እንዲሁም በዝርዝር ብሄራዊ ሕጎች እውቅና የተሰጣቸውና ጥበቃ የሚደረግላቸው የተከሰሱ ሰዎች መብቶች የሚከበሩበት በመሆኑ ነው።
የተከሰሱ ሰዎች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ሊከበሩላቸው የሚገቡ በርካታ መብቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ በዳኝነት አካላት ፊት በእኩልነት የመታየት፣ ጥፋተኝነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ንፁህ ተደርገው የመገመት፣ ፍትሀዊ በሆነና በግልጽ ችሎት የመዳኘት፣ የተፋጠነ ፍርድ የማግኘትና ይግባኝ የማቅረብ መብቶች ይገኙበታል። በተጨማሪም ክሱን በጽሁፍ የማግኘት፣ ተከሳሾች በራሳቸው ላይ ያለመመስከር፣ የመከላከያ ምስክሮችንና ማስረጃዎቻቸውን የማቅረብ፣ ለአቃቤ ሕግ ምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ የማቅረብ፣ እንዲሁም በመንግሥት እጅ የሚገኙ ማስረጃዎችን የማግኘት መብቶቻቸውም ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው።
ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ በበርካታ ሕገ-መንግስታት፣ በዓለማቀፋዊና በአሕጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች እውቅና ያገኙ መብቶች ብዙውን ጊዜ ሲከበሩ ሳይሆን ሲጣሱ ነው የሚታየው። ይህም የሚሆነው ለእነዚህ መብቶች መከበር መሰረታዊ የሆነው የተከሰሱ ሰዎች ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት ሕጉ ላይ በተቀመጠው ልክ በተግባር እየተፈጸመ ባለመሆኑ ነው።
ከዚህም በመነሣት የመብቱን መከበርና አለመከበር በማየት ብቻ መሠረታዊ የተከሰሱ ሰዎች መብቶች መከበራቸውንና መጣሳቸውን መገንዘብ ይቻላል። በመሆኑም ይህ ጽሑፍ በዚህ መነሻነት ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት በተለያዩ ሕጎች ያለውን ጠቅላላ ገጽታ በቀጣዮቹ ሁለት ክፍሎች ለመዳሰስ ይሞክራል።
ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት ሕጋዊ መሰረት
ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት በተለያዩ ሀገሮች ሕገ-መንግሥታት በተለያየ መልኩ ሠፍሮ ይገኛል። የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገሮችን ለአብነት ስንመለከት እንደ ቦትስዋና ያሉ ሀገሮች የተከሰሱ ሰዎች በራሳቸው ወጪ ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆሙ ያደርጋሉ። ሌሎችም እንደ ሱዳን ያሉ ሀገሮች በከባድ ወንጀሎች ለተከሰሱ ሰዎች ብቻ በመንግሥት ወጪ የሕግ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ይፈቅዳሉ።
እንደ ላይቤሪያ ባሉ ሀገሮች ደግሞ በየትኛውም የወንጀል ዓይነት የተከሰሱ ሰዎች በራሳቸው አቅም በሕግ ጠበቃ ለመወከል ካልቻሉ በመንግሥት ወጪ በሕግ ባለሙያ የመታገዝ መብት ይሰጣቸዋል። አብዛኞቹ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገሮች ግን የተከሰሱ ሰዎች ተከላካይ ጠበቃ እንዲያገኙ የሚፈቅዱት ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ ነው። ከዚህም ባሻገር በወንጀል ጉዳይ ለተከሰሱ ሰዎች የመከላከል መብታቸውን የሚፈቅዱ ነገር ግን በማን ወጪ የሚለውን በግልጽ በሕገ-መንግሥታቸው ያላመላከቱ ወደ ሃያ የሚሆኑ ሀገሮች በአሕጉ ራችን መኖራቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።
ተግባራዊ አፈጻጸሙ ገና ብዙ የሚቀረውና ከሀገር ሀገር የሚለያይ ቢሆንም፣ ከዚህ በላይ በተገለጸው መሰረት ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። ይሁን እንጂ ይኸው መብት ተፈጻሚነት የሚኖረው በየትኛው የክርክር ሂደት ማለትም በቅድመ-ክስ፣ በክስ ወይም ከክስ በኋላ እንደሆነ ከላይ ለአብነት የተጠቀሱት ሕገ-መንግሥታት የሚሉት ነገር የለም። በመሆኑም የመብቱ ሕገ-መንግሥታዊነት የይስሙላ እንዳይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭራል።
ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብትና ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች
በወንጀል ጉዳዮች ክርክር ጊዜ ተከላካይ ጠበቃ በመንግሥት ወጪ ማቆም በራሱ መብትና ለሌሎች የተከሰሱ ሰዎች መብቶች መከበር ዓይነተኛ ቅድመ-ሁኔታ መሆኑ አያጠያይቅም። ይህም መብት የሚመነጨው በበርካታ ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ ከተደነገጉት እንደ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ ንጹሕ ሆኖ የመገመት መብት፣ ሚዛናዊ የፍርድ ሂደትና በሕግ ፊት እኩል መሆን ካሉ መሰረታዊ መርሕዎች ነው። በብዙ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የተገለጸው የፍትሕ ተደራሽነትም ለተከሰሱ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች መጠበቅ ያለው ሚና ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።
ሀ. ሁሉን አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ
ይህ መግለጫ በሀገሮች ላይ የአስገዳጅነት ውጤት ባይኖረውም በርካታ ሕገ-መንግሥታትና የሰብአዊ መብት ሰነዶች የሚተረጎሙት እሱን መነሻ አድርገው መሆኑ አይታበልም። በመሆኑም መግለጫው በአንቀጽ 11 (1) በወንጀል የተከሰሰ ማንኛውም ሰው ክሱ በይፋ በሚሰማበት ግልጽ ፍርድ ቤት በሕግ መሰረት የመከላከል መብቱ እንዲጠበቅለት በጥቅል ሁኔታ አስቀምጧል።
በዚሁ መግለጫ አንቀጽ 10 መሰረት “ማንም ሰው በመብቶቹና ግዴታዎቹ እንዲሁም በተከሰሰበት ማንኛውም ጉዳይ ውሳኔ ለማግኘት ሙሉ የእኩልነት መብቱ ተጠብቆ ነጻ በሆነና አድልዎ በሌለበት ፍርድ ቤት ሚዛናዊና ይፋ የሆነ ፍርድ የማግኘት መብት አለው”፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻለው መግለጫው ለተከራካሪዎች እኩልነትና ለሚዛናዊ ፍርድ በግልጽ ጥበቃ የሚሰጥ መሆኑን ነው፡፡ ሚዛናዊ የፍርድ ሒደት የሚኖረው ደግሞ ግለሰቦች በግልጽ በሚታወቅ ሕግ የተከሰሱበትን ነገር ተረድተው በሕግ ባለሙያ እገዛ ከተከራከሩ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።
ለ. የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለማቀፍ ስምምነት
ተከላካይ ጠበቃ በመንግሥት ወጪ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ ዓለማቀፋዊ ከሆኑ ስምምነቶች ውስጥ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ስምምነቱ በአንቀጽ 14 (1) ሰዎች ሁሉ በፍርድ ቤቶችና በዳኝነት አካላት ፊት በእኩልነት መታየት አለባቸው በማለት ጥበቃ ሲሰጥ በንኡስ አንቀጽ 3 /መ/ ራሱ በተገኘበት የመዳኘት፣ ራሱን በግል ወይም በመረጠው ጠበቃ የመከላከል፣ ጠበቃ ከሌለው ትክክለኛ ዳኝነት የሚጓደል ሆኖ ሲገኝና የገንዘብ አቅሙ የማይፈቅድ ሲሆን ሳይከፍል ጠበቃ ወይም የሕግ አማካሪ ዕርዳታ የማግኘት መብት እንዳለው ያረጋግጣል።
ይህ ስምምነት በወንጀል ጉዳይ የተከሰሱ ድሃ ሰዎች በመንግሥት ወጪ የሕግ ጠበቃ እንዲያገኙ ፈራሚ ሀገሮች ላይ ግዴታ የሚጥል ቢሆንም፣ የስምምነቱ አንቀጽ 14 (3) /መ/ በሁለት መስፈርቶች የታጠረ ነው ማለት ይቻላል። ይኸውም ተከሳሹ በመንግሥት ወጪ ጠበቃ የሚቆምለት በግሉ ለማቆም አቅም ከሌለውና ፍትሕ የሚጓደል ሲሆን ነው የሚሉት ሲሆኑ ለሀገሮች ሰፊ ፍቅድ ሥልጣን የሚሰጡ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅድ ሥልጣን የስምምነቱ ፈራሚ ሀገሮች እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው በጠቅላላ አስተያየት ቁጥር 32 ማብራሪያ ሰጥቷል። በማብራሪያውም መሰረት ሀገሮች ፍትሕ የሚጓደል ሲሆን የሚለውን ሲተረጉሙ የወንጀሉን ከባድነትና እስከ ይግባኝ የመሄድ እድሉን ሁሉ ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል። በተጨማሪም ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ተከሳሾች በየትኛውም የክርክር ሂደት የሕግ ጠበቃ በመንግሥት ወጪ ሊቆምላቸው ይገባል ይላል። ሆኖም ግን በቀላል ወንጀሎች ጊዜም ፍትሕ ሊዛባ የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ማብራሪያው ግምት ውስጥ አላስገባም።
ማብራሪያው በተጨማሪነት እንደሚገልጸው በመንግሥት ወጪ የሚቆም ማንኛውም ተከላካይ ጠበቃ አቅም ያለውና የያዘውን ጉዳይ ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል መሆን አለበት። ሌላው በማብራሪያው የተካተተው ነጥብ የሕግ ባለሙያው ምስክሮች በሚሰሙበት ጊዜ የግድ መገኘት ያለበት ከመሆኑም በላይ ከተከሳሹ ጋር በመመካከር ካልሆነ በቀር በሞት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ተከሳሹ ሳያውቅ የይግባኝ መብቱ ሊቋረጥ አይገባም። እንደዚሁም ፍርድ ቤትን ጨምሮ ማንኛውም አካል በመንግሥት ወጪ የሚቆመውን የሕግ ባለሙያ ሥራ ማደናቀፍ አይኖርበትም። ማብራሪያው ሲያጠቃልል ሀገሮች በዚህ አግባብ ካልሠሩ ስምምነቱን እንደመጣስ ያስቆጥርባቸዋል።
ሐ. የሕጻናት መብቶች ዓለማቀፍ ስምምነት
ይኸው ስምምነት ለሕጻናት ሊሰጣቸው ስለሚገባ የሕግ ድጋፍ በተወሰነ መልኩ ይደነግጋል። በዚህም መሰረት የስምምነቱ አንቀጽ 37 /መ/ ማንኛውም ነፃነቱን እንዲያጣ የተደረገ ሕጻን የሕግ እርዳታ ባፋጣኝ ማግኘት እንዳለበት ይገልጻል።
አንቀጽ 40 (2) ደግሞ በወንጀል የተከሰሰ ማንኛውም ሕፃን ለቀረበበት ክስ መከላከያ አዘጋጅቶ ለማቅረብና ጉዳዩ በሚሰማበት ጊዜ የሕግ እርዳታ ያገኛል ይላል። ይሁንና እነዚህ ድንጋጌዎች ጥቅል ከመሆናቸው ባለፈ በወንጀል የተከሰሱ ሕጻናት በመንግሥት ወጪ የሕግ ጠበቃ ሊቆምላቸው የሚገባ መሆኑን በግልጽ አያመላክቱም።
መ. የአስገዳጅነት ውጤት የሌላቸው ዓለማቀፋዊ ሰነዶች
ከዚህ በላይ ከተብራሩት ዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት በመንግሥት ወጪ የሚሰጥ የሕግ ድጋፍን የሚመለከቱ በርካታ ሰነዶች አውጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ በጠበቆች ሙያ ላይ የሚያተኩረው መሰረታዊ መርሕ (UN basic principles on the role of lawyers) አንዱ ሲሆን በመጀመሪያውና በስድስተኛው መርሕ የፍትሕን ተደራሽነት በእኩል ለሁሉም ዜጎች ለማረጋገጥ መንግሥታት በየትኛውም የክርክር ሂደት በራስ ወጪ ተከላካይ ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ ተከሳሾች ነፃ የሕግ ድጋፍ መስጠት ይቻላቸው ዘንድ በቂ በጀት ሊመድቡ እንደሚገባ ይገልጻል። መርሕ 1 በተለይ ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው የሚለውን በመያዝ ሀገሮችም ሆኑ የሕግ ሙያው በራሱ በሕግ ባለሙያ የመታገዝ መብት ያለምንም የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቀለም፣ የጾታ፣ የሁኔታ ወዘተ ልዩነትና አድልዎ ሳይደረግበት ለማንኛውም ሰው ተደራሽ መሆን አለበት ሲል ያስቀምጣል።
የተባበሩት መንግሥታት በወንጀል የፍትሕ ሥርዓትና በነፃ የሕግ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ ያወጣው መርሕና መመሪያም (UN principles and guidelines on access to legal aid in criminal justice systems) በተመሳሳይ በመርሕ 3 በወንጀል ጉዳዮች የሕግ ጠበቃ በራሳቸው ወጪ ማቆም የማይችሉ ሰዎች ከተያዙበት እስከ ክርክሩ መጨረሻ ሂደት ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ እንደ ጉዳዩ አጣዳፊነትና ውስብስብነት እንዲሁም እንደ ቅጣቱ ክብደት በሕግ ባለሙያ ሊታገዙ የሚገባ መሆኑን አስቀምጧል። በመርሕ 2 መሰረት ደግሞ የነፃ ሕግ ድጋፉን ሥርዓት ለማጠናከር ሀገሮች አስፈላጊውን የሰው ኃይልና በጀት ማሟላት ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በመርሕ 2 እንደተገለጸው ሀገሮች ነፃ የሕግ ድጋፍ የመስጠት ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብ ዝርዝር ሕግ ማውጣት ያለባቸው ሲሆን የሚወጣውም ሕግ ተደራሽ፣ ውጤታማ፣ ዘላቂና ተአማኒነት ያለው መሆን አለበት።
ይሁን እንጂ እነዚህ ሰነዶች እንደ ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ሁሉ ሀገሮች ላይ አስገዳጅ ግዴታ የሚጥሉ አይደሉም። ነገር ግን ሀገሮች የሕግ ማእቀፍ ሲያዘጋጁም ሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲነድፉ ለመነሻነት የሚጠቅሙ ወሳኝ ሰነዶች መሆናቸው አይካድም። በመሆኑም ሰነዶቹ ዓለማቀፉ ሕብረተሰብ በወንጀል ጉዳዮች ስለሚሰጥ ነፃ የሕግ ድጋፍ ወቅታዊ አቋሙን የገለጸባቸው በመሆናቸው ከአስገዳጅነት የዘለለ አስተዋፅኦ አላቸው ተብሎ ይታመናል፡፡
ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብትና አሕጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች
በወንጀል ጉዳይ የተከሰሱ ሰዎች የቀረበባቸውን ክስ ለመከላከል ከሚያስችሏቸው በርካታ አማራጮች አንዱ በመንግሥት ወጪ የሚሰጥ የሕግ ድጋፍ መሆኑን ከፍ ብሎ የተገለጹት ዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ያስረዳሉ። በዚህ ረገድ አሕጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችስ ምን ይላሉ? የሚለው ደግሞ በሚከተለው ዳሰሳ ይመለሳል።
አሕጉሮችም እንደ ሀገሮች ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን የሚፈርሙ ሲሆን በየአሕጉራቸው ደግሞ በአባል ሀገሮች ላይ ተፈጻሚነትና አስገዳጅነት ያላቸው የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን በራሳቸው ሥልጣን ያወጣሉ። በዚህም መሰረት በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ አሕጉሮች ወጥተው ሥራ ላይ ያሉ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል።
የአፍሪካ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች
ሀ. የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር
ይህ ቻርተር ከአሕጉ ራችን የሰብአዊ መብት ሰነዶች ቀዳሚው ነው። ቻርተሩ በአንቀጽ 7 (1) /ሐ./ እንደሚደነግገው ጸንተው በሚገኙ ስምምነቶች፣ ሕጎችና ልማዶች ዋስትና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶቹን የሚጥሱ ድርጊቶች ሲፈጸሙበት ማንም ሰው በራሱ ወይም በመረጠው አማካሪ አማካኝነት ሥልጣን ላላቸው ብሔራዊ አካላት በደሉ እንዲሰማለት የማድረግ መብት አለው፡፡
እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ራሱ ለመረጠው ጠበቃ የሚከፍለው ገንዘብ ባይኖረውስ የሚለው ሲሆን በቻርተሩ አንቀጽ 2 መሰረት ይሄው ድንጋጌ ለሁሉም አፍሪካዊያን በእኩልነትና አድልዋዊነትን ባስወገደ ሁኔታ ተፈጻሚነት እንዲኖረው በወንጀል ጉዳይ ለተከሰሱና በራሳቸው አቅም ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ ሰዎች በመንግሥት ወጪ የሕግ ባለሙያ እገዛ እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ መተርጎም ይኖርበታል። አለበለዚያ ድንጋጌው ፅንሰ-ሀሳባዊ ሆኖ ከሚቀር በቀር ትርጉም አይኖረውም።
በተጨማሪም የቻርተሩ አንቀጽ 4 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለው ይገልጻል። ይሁንና አሕጉሩ የሞት ፍርድን ተግባራዊ የሚያደርጉ በርካታ አባል ሀገሮች ያሉበት ከመሆኑ አንጻር “የመብቶች ሁሉ እናት” የሚባለው ይህ መብት ያለ አግባብ በሚካሄድ የክርክር ሂደት ሊታጣ ይችላል። በመሆኑም መንግስት ቢያንስ እስከ ሞት ሊያስቀጡ በሚችሉ ከባድ የወንጀል ጉዳዮች ለተከሰሱ ሰዎች በነጻ ጠበቃ የማቆም ግዴታ ውስጥ ካልገባ የመብቱ መከበር ከወረቀት የዘለለ አይሆንም።
ለ. የአፍሪካ ሕጻናት ደህንነትና መብቶች ቻርተር
ይህ ቻርተር በአንቀጽ 17 በወንጀል ጉዳይ ከሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍ ጋር የተያያዙ የተወሰኑ ድንጋጌዎችን ይዟል። በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) መሰረት ማንኛውም የተከሰሰ ወይም ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሕጻን ከልጅነቱ አኳያ ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ የማግኘት መብት አለው።
በተለይም ደግሞ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) /ሐ/ እንደሚለው የተከሰሱ ሕጻናት መከላከያቸውን ሲያዘጋጁም ሆነ ሲያቀርቡ የቻርተሩ አባል ሀገሮች የሕግና ሌላም ተገቢ እገዛ መስጠት አለባቸው። ስለሆነም የወንጀሉና የቅጣቱ ዓይነት ምንም ይሁን ምን ሀገሮች በወንጀል ጉዳይ የተከሰሱ ሕጻናት በሕግ ባለሙያ እንዲወከሉ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ከዚህ ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል።
ሐ. የአስገዳጅነት ውጤት የሌላቸው አሕጉራዊ ሰነዶች
ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት ቻርተሮች በተጨማሪ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን በወንጀል ጉዳይ የሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዱ በዛ ያሉ የመፍትሔ ሀሳቦችን /Resolutions/ አውጥቷል። ከእነዚህም ውስጥ የዳካር መግለጫ፣ ሚዛናዊ የፍርድ ሂደት መብትና የሕግ እገዛ መርሕዎችና መመሪያዎች እንዲሁም የላሎንጌ መግለጫ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1999 ዓ.ም የወጣው የዳካር መግለጫ /Dakar Declaration resolution on the Right to a Fair Trial and Legal Aid in Africa/ የሚያተኩረው በሚዛናዊ የፍርድ ሂደት መብትና ነጻ የሕግ ድጋፍ ላይ ሲሆን በአንቀጽ 9 የፍትሕ ተደራሽነት ሚዛናዊ የፍርድ ሂደት መብት ወሳኝ አካል መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል። በመሆኑም መግለጫው መንግሥታት በወንጀል ጉዳዮች የሚሰጥን ነጻ የሕግ ድጋፍ ማረጋገጥ አለባቸው ሲልም ከፍተኛ ኃላፊነት ይጥልባቸዋል።
በዚሁ አንቀጽ እንደተጠቀሰው አብዛኞቹ በወንጀል ጉዳይ የሚከሰሱ ሰዎች የተለያዩ የሕግ አገልግሎቶችን ለማግኘት ፍርድ ቤቶችም ሆኑ የሕግ ሙያተኞች የሚያስከፍሏቸውን ከፍተኛ ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል አቅም የላቸውም። ስለዚህ ሚዛናዊ የፍርድ ሂደት መብት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ካስፈለገ መንግሥታት ለድሃ ሰዎች ነጻ የሕግ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ውስጥ መግባት አለባቸው።
የመግለጫው የመፍትሔ ሀሳብ በአጽንዖት እንደሚለው የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር አባል ሀገሮች በወንጀል ጉዳይ ለተከሰሱ ድሃ ሰዎች ነጻ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡባቸውን መንገዶች በአስቸኳይ ሊመረምሩ ይገባል። ይህም ተከላካይ ጠበቆችንና የተለያዩ የነጻ ሕግ ድጋፍ ማዕቀፎችን ይጨምራል። በመግለጫውም ሆነ በመፍትሔ ሀሳቡ በጥቅል እንደተቀመጠው መንግሥታት ከጠበቆችና ከሙያ ማኅበራት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከሰብአዊ መብት ድርጅቶችና ከፍርድ ቤቶች ጋር በመተባበር ለድሃ ሰዎች የሚሰጠውን ነጻ የሕግ ድጋፍ ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በ2001 ዓ.ም ደግሞ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን የዳካር መግለጫን መሰረት ያደረጉ ሚዛናዊ የፍርድ ሂደት መብትና የሕግ እገዛ መርሕዎችና መመሪያዎች /Principles and Guidelines on the Rights to a Fair Trial and Legal Assistance in Africa/ አውጥቷል። መርሕዎቹም በብሔራዊ ሕጎች ሊካተቱ የሚገቡ ከነጻ የሕግ ድጋፍ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ይጠቁማሉ።
በእነዚህ መርሕዎች አንቀጽ 5 /ሰ/ መሰረት መንግሥታት የሕግ ባለሙያዎችን ተደራሽነት ለሁሉም ዜጎች ያለምንም አድልዎ የሚያረጋግጡ አስተማማኝ አሠራሮችን ሊከተሉ ይገባል። በተጨማሪም መንግሥታትና የሕግ ባለሙያ ማኅበራት የኅብረተሰቡን ንቃተ-ሕሊና በማሳደግ እንዲሁም በሕግ የተሰጡ መብቶቹንና ግዴታዎቹን በማስገንዘብ የሕግ ባለሙያዎች መሰረታዊ መብቶችንና ነጻነቶችን ለማስጠበቅ ያላቸውን ሚና የማሳወቅ ኃላፊነት አለባቸው።
የመርሕዎቹ አንቀጽ 5 /ሸ/ በወንጀል ክርክር ጊዜ ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ ለተከሳሾቹ በመንግሥት ወጪ የሕግ ባለሙያ እገዛ መሰጠት እንዳለበት ሲደነግግ ፍትሕ የሚጓደለው መቼ ነው? የሚለውን ለመወሰን ሁለት ዓይነት መስፈርቶችን አስቀምጧል። እነዚህም የወንጀሉ አደገኛነትና የቅጣቱ ከባድነት ናቸው። ለትክክለኛ ፍትሕ ሲባል ይግባኝን ጨምሮ ማናቸውም ከባድ ጉዳዮች ምን ጊዜም የጠበቃ እገዛ ያስፈልጋቸዋል።
ይኸው ተመሳሳይ አንቀጽ በመንግሥት ለሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍ የሚመደቡ የሕግ ባለሙያዎች ማሟላት የሚገቧቸውን መስፈርቶችም ይዘረዝራል። በዚህም መሰረት ባለሙያዎቹ ብቁ መሆን ይኖርባቸዋል። ከያዙት ጉዳይ አኳያም አስፈላጊውን የሥራ ልምድና ክሕሎት ሊይዙ ይገባል። እንደዚሁም በማንኛውም የመንግሥት አካል ፊት ሙያዊ ነጻነታቸውን ማስጠበቅ የሚችሉ መሆን አለባቸው።
በ2004 ዓ.ምም ኮሚሽኑ በወንጀል የፍትሕ ሥርዓት ነጻ የሕግ ድጋፍን ተደራሽ የሚያደርግ የላሎንጌ መግለጫንና የድርጊት መርሐ-ግብር /Lilongwe Declaration on Accessing Legal Aid in the Criminal Justice System in Africa and Plan of Action/ ያወጣ ሲሆን መግለጫው በአንቀጽ 1 በወንጀል የፍትሕ አስተዳደር ለሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍ እንደ መብት ዕውቅና ይሰጣል።
ይኸው አንቀጽ ነጻ የሕግ ድጋፍ የሕግ ምክርን፣ የፍርድ ቤት ውክልናን፣ የንቃተ-ህግ ትምህርትንና የሽምግልና ስራን በሚያካትት መልኩ ሰፍቶ መተርጎም እንዳለበትም ይገልጻል። እንደዚሁም በነጻ የሕግ ድጋፍ አሰጣጡ ሂደት የሚሳተፉ አጋር አካላት ውስጥ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሀይማኖታዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማህበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራትና የትምህርት ተቋማት መካተት እንዳለባቸው ያስገነዝባል።
በተጨማሪም በዚህ አንቀጽ መሰረት መንግሥታት ውጤታማና ግልጽ ነጻ የሕግ ድጋፍ ለድሃ ዜጎቻቸው መስጠት ይችሉ ዘንድ በቂ በጀት መመደብና እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ነጻ የሕግ ድጋፉ በየትኛውም የወንጀል ክርክር ሂደት መሰጠት ያለበት መሆኑን ደግሞ የመግለጫው አንቀጽ 3 ይደነግጋል።
ሀገሮች ነጻ የሕግ ድጋፍ የመስጠት ግዴታቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸው ወጥ መንገድ የለም። ይሁንና ሁሉንም ዓይነት የነጻ ሕግ ድጋፍ አሰጣጥ ዘዴዎች አቀናጅቶና አደራጅቶ የመምራት ኃላፊነት አለባቸው። በመግለጫው አንቀጽ 6 እንደተጠቀሰው መንግሥታት ለድሃ የኅብረተሰብ ክፍሎች የፍትሕ ተደራሽነትን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያግዟቸው ብዙ የነጻ ሕግ ድጋፍ አሰጣጥ መንገዶች አሉ።
ከእነዚህም ውስጥ በመንግሥት ወጪ የሚቋቋሙ የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤቶች፣ የፍትሕ ማዕከላት፣ የጠበቆች ማኅበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕግ ትምህርት ቤቶች ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ለነጻ የሕግ ድጋፉ የትኛውም ዘዴ ቢመረጥ አገልግሎቱን ከሚሹ ተገልጋዮች ፍላጎት አኳያ መደራጀት ይኖርበታል።
በመግለጫው አንቀጽ 9 ሥር እንደተመለከተው በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የሚሰጠው ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት በለጋሾች ዕርዳታ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም በማንኛውም ጊዜ ሊቋረጥ ይችላል። በዚህም ምክንያት ዘለቄታ ያለው የነጻ ሕግ ድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።
ነገር ግን ከዚህ በላይ የተተነተኑት ሰነዶች እንደ ቻርተሮቹ የአስገዳጅነት ውጤት የላቸውም። ሆኖም ሰነዶቹ የአፍሪካ ኅብረት በወንጀል ጉዳዮች ስለሚሰጥ ነፃ የሕግ ድጋፍ የያዘውን አቋም በግልጽ ያሳውቃሉ። ስለዚህ የአሕጉሩን አባል ሀገሮች ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ለማዘጋጀት በመነሻነት የማገልገል ሚና አላቸው።
ሀ. የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት
ይህ ስምምነት በአንቀጽ 6 (3) /ሐ./ ማንኛውም በወንጀል የተከሰሰ ሰው ራሱን በራሱ ወይም በመረጠው ጠበቃ ወይም ለጠበቃ የመክፈል አቅም ከሌለው ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ መንግሥት በነጻ በሚያቆምለት ጠበቃ የተከሰሰበትን ጉዳይ የመከላከል መብት አለው ሲል ይደነግጋል። ሆኖም አንቀጹ ፍትሕ የሚጓደለው መቼ ነው? ተብሎ ለሚነሣ ጥያቄ በቂ መልስ የሚሰጥ አይደለም።
በመሆኑም የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ የሚለውን ድንጋጌ ሲተረጉም ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው መስፈርቶች አሉ። እነሱም የጉዳዩ ውስብስብነት፣ የቅጣቱ ከባድነትና ተከሳሹ ራሱን ለመከላከል ያለው አቅም የሚሉት ሲሆኑ እነዚህን መስፈርቶች በአግባቡ መመዘን ከተቻለ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት ወሳኝነት አላቸው።
በተጨማሪም የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንደሚለው በወንጀል ጉዳይ የተከሰሱ ሰዎች የሕግ ጠበቃ ከሌላቸው በሚዛናዊ የፍርድ ሂደት የሚኖራቸውን መብቶች አውቀው ሊያስከብሩ አይችሉም። ስለሆነም ኮሚሽኑ በጠበቃ የመታገዝ መብት ለሌሎች መብቶች መከበር ዋና መሰረት መሆኑን ያረጋግጣል።
ለ. የአሜሪካ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት
የአሜሪካ የሰብአዊ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀጽ 8 (2) /መ/ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ራሱን በራሱ የመከላከል ወይም በመረጠው ጠበቃ የመታገዝና ከጠበቃው ጋር በነጻነት ብቻውን የመገናኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል። በተጨማሪም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) /ሠ./ በወንጀል የተከሰሰው ሰው የተከሰሰበትን ጉዳይ በራሱ ወይም በመረጠው ጠበቃ አማካኝነት ለመከላከል የማይችል በሆነ ጊዜ በመንግሥት ወጪ የሚቆም ጠበቃ የማግኘት የማይገሰስ መብት አለው ሲል በግልጽ ያስቀምጣል።
በዚህ ድንጋጌ ውስጥ በሌሎች ስምምነቶች የተለመደው ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ የሚለው ጥቅል አነጋገር አልተካተተም። ይህም መሰረታዊ ነጥብ ስምምነቱን የሚያስፈጽሙና የሚተረጉሙ አካላት በጥቅል ድንጋጌው ሳቢያ የሚቸገሩበትን ሁኔታ ያስቀራል። ጠቅለል ሲልም የስምምነቱ አባል ሀገሮች በወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ በመንግሥት ወጪ ጠበቃ የማቆም ግዴታ ያለባቸው መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብትና የኢትዮጵያ ሕጎች
ሀገራችን ሁሉንም ሰብአዊ መብቶች ለማክበር፣ ለመጠበቅና ለማሟላት አለማቀፋዊ፣ አሕጉራዊና አገራዊ ግዴታ አለባት። ይህን ግዴታዋን ለመወጣትም በርካታ አሕጉራዊና ዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብት ሰነዶችን ፈርማለች። ከእነዚህ ሰነዶች በተጨማሪ አሉን የምንላቸው ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብትን የሚመለከቱ ሀገራዊ ሕጎች እንደሚከተለው ተብራርተዋል።
ሀ. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት
ከወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ መርህዎች መካከል አንዱና አስፈላጊው የተከሳሾች የሕግ ምክር የማግኘት መብት ሲሆን በሃገራችን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ውስጥም ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት ያለው ነው። ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 20 (5) ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ “የተከሰሱ ሰዎች ‹‹በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው” በማለት ደንግጓል።
በዚህ ድንጋጌ መሠረት በመንግሥት ወጪ ጠበቃ እንዲቆምለት የሚጠይቀው ሰው ክስ የቀረበበትና አቅም የሌለው መሆን ሲገባው በፍርድ ቤቱ እይታ ‹‹ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታም” ሊያጋጥም ግድ ይላል። መብቱ ለተከሰሱ ሰዎች ብቻ መሰጠቱ የተያዙ ሰዎችና በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች በመንግሥት ወጪ ጠበቃ እንዲቆምላቸው መጠየቅ የማይችሉ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ከዚህም ሌላ ድንጋጌው ግልጸኝነት ስለሚጎድለው መንግሥት የሕግ ጠበቃ የሚያቆመው በየትኛው የክርክር ሂደትና በየትኛው የወንጀል ዓይነት ለተከሰሱ ሰዎች እንደሆነ በግልጽ አያመላክትም። በተጨማሪም አቅም የሌለው ማን ነው? እና ፍትሕ የሚጓደለውስ መቼ ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ባለመሆኑ አፈጻጸሙ ላይ ችግሮች ይስተዋሉበታል።
ለ. የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋምያ አዋጅ ቁጥር 25/1988
በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ (5) ከተጠቀሰው ድንጋጌ ባሻገር በመንግሥት ወጪ ስለሚቆም ተከላካይ ጠበቃ ውስን ድንጋጌዎችን የያዙ ሌሎች ሕጎች አሉ። በዚህ ረገድ ተጠቃሹ የፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1988 ዓ.ም ሲሆን በአንቀጽ 16 (2) /በ/ ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት የተከላካይ ጠበቆችን ቢሮ የማደራጀት ኃላፊነት እንዳለበት በግልጽ ደንግጓል።
በዚህም መሰረት የሙሉ ጊዜ ተቀጣሪ የሕግ ባለሙያዎችን የያዘ የተከላካይ ጠበቆች ቢሮ ተደራጅቶ በወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች በችሎት ቀርቦ የመከራከር፣ የማማከርና ሰነድ የማዘጋጀት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ ቢሮው ከተቋቋመ ሃያ ዓመት ቢሆነውም ያሉት ባለሙያዎች ቁጥር ማነስ፣ የሥራ መብዛት፣ ጠንካራ የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥርዓት አለመኖርና አገልግሎቱ በከባድ ወንጀል ለተከሰሱ ብቻ የሚሰጥ መሆኑ በሕግ ባለሙያ የመታገዝ መብትን ከማረጋገጥ አንጻር ገና ብዙ ይቀረዋል።
ሐ. የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 27/1988
ከፌደራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋምያ አዋጁ በተጨማሪ በመንግሥት ወጪ ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብትን የሚመለከት ድንጋጌ የያዘ ሌላም አዋጅ አለ። ይህም አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 343/1995 ማሻሻያ የተደረገለት የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 27/1988 ዓ.ም ሲሆን ተፈጻሚነቱ በመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ብቻ ነው።
ይኸው አዋጅ በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ (2) ከ5 ዓመት በማያንስ እስራት በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ ሰው በራሱ አቅም ተከላካይ ማቆም ካልቻለ መንግስት ተከላካይ የሚመድብለት መሆኑን ይደነግጋል። በመሆኑም ድንጋጌው በነጻ ለሚሰጥ የሕግ ድጋፍ መሰረት ከመጣሉ ባለፈ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ (5) ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ በሚል የተቀመጠውን ጥቅል ድንጋጌ ሕግ አውጪው እንዴት መተርጎም እንዳሰበ ለመረዳት ያስችላል።
መ. የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ
ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከተጠቀሱት መሰረታዊያን ሕጎች በፊት ለዘመናት ሥራ ላይ የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግም በቁጥር 61 የተያዘ ወይም የታሰረ ወይም በጊዜ ቀጠሮ ያለ ሰው ጠበቃውን የመጥራትና የማማከር መብት እንዳለው ይገልጻል። በተለይ ደግሞ አካለ መጠን ያላደረሱ ወጣቶች በጠበቃ መወከል እንዲችሉ በቁጥር 174 ሥር በተወሰነ መልኩ የተቀመጠ ነገር አለ።
ይኸውም አካለ መጠን ያልደረሱ ወጣቶች ከአሥር ዓመት በላይ ጽኑ እስራት ወይም በሞት በሚያስቀጣ ወንጀል በተከሰሱ ጊዜ ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት የሚረዳቸው ጠበቃ የማዘዝ ኃላፊነት አለበት። ሆኖም ድንጋጌው ሁሉንም በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች የሚመለከት ባለመሆኑና በመንግሥት ወጪ ሊቆም ስለሚችል ጠበቃ የሚለው ነገር ስለሌለ በወንጀል ጉዳዮች ለሚሰጥ ነጻ የሕግ ድጋፍ ጉልህ አስተዋጽዖ አላበረከተም።
ሠ. የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ
ለዘመናት ሥራ ላይ ከነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በተሻለ በቅርቡ የወጣው የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ በመንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ስለመወከል እመርታዊ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል። በፖሊሲው በግልጽ እንደተቀመጠው፣ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማነት፣ ፍትሐዊነት፣ ቀልጣፋነት፣ ተደራሽነትና ሚዛናዊነት ለማረጋገጥ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ከቀረበባቸው ክስ ራሳቸውን ለመከላከል በሚያስችላቸው ደረጃ በጠበቃ መወከላቸውን መርማሪው አካል፣ ዐቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው።
በተጨማሪም እነዚህ የፍትሕ አካላት በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ወይም ጠበቃቸው በማንኛውም የፍርድ ሂደት ከዐቃቤ ሕግ በእኩል ደረጃ ጉዳያቸውን የማሰማት መብታቸው በሚረጋገጥበት መልኩ የሥነ ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። በተለይም ጉዳያቸው የሚታይበት ፍርድ ቤት ወይም ችሎት ይህንን መብት ከማስከበር አንፃር የጎላ ሚና ሊጫወት የሚገባ መሆኑን ፖሊሲው አጽንዖት ሰጥቷል።
ከዚህም ባለፈ በፖሊሲው መሰረት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ባለሙያዎች፣ ጠበቆች ወይም የጠበቆች ማኅበር ጠበቃ ለማቆም አቅም ለሌላቸው ተከሳሾች ነፃ የሕግ አገልግሎት የሚሰጡበትን ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነት አለበት። በዋናነት ደግሞ የተከሳሾችን መብት ለማስከበርና በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ተከሳሾች በበቂ ሁኔታ መወከላቸውን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የተከላካይ ጠበቆች ተቋም ሊኖር እንደሚገባ ይገልጻል። ምንም እንኳ ፖሊሲው ጸድቆ ከወጣ አምስት ዓመታት ያለፉት ቢሆንም ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ የተሽመደመደውን የተከላካይ ጠበቆች ቢሮ የሚተካ ነፃና ገለልተኛ የተከላካይ ጠበቆች ተቋም ለማቋቋም አሁንም አልረፈደም።
ረ. የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ /ረቂቅ/
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲውን ተፈጻሚነት ሊያፋጥኑ የሚችሉ ፍንጮች በመታየት ላይ ናቸው። ከእነዚህም ቀዳሚው የወንጀል ስነ-ሥርዓት ሕግ ተሻሽሎ ለመውጣት መቃረቡ ነው። የጽሑፉ አዘጋጅ በስነ-ሥርዓት ሕጉ ረቂቅ ውይይት ላይ የተሳተፈ ሲሆን በረቂቅ ሕጉ በመንግሥት ወጪ የሚቆም ተከላካይ ጠበቃን የሚመለከቱ በርካታ ቁምነገሮች መካተታቸውን አስተውሏል።
ከበርካታዎቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ማንኛውም የፍርድ ሒደት የዐቃቤ ሕግን፣ የግል ከሳሽንና የተከሳሽን እኩልነት በሚያረጋግጥ መልኩ መካሄድ እንዳለበት ረቂቅ ሕጉ ይደነግጋል። በጥፋተኝነት ድርድርም /plea bargaining/ ይሁን በክስ ክርክር ወቅት በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ጠበቃ ለማቆም የገንዘብ አቅም የሌላቸው መሆኑ ከተረጋገጠና በዚህም ምክንያት ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም በመንግሥት ወጪ ጠበቃ ይመደብላቸዋል ይላል።
የተከላካይ ጠበቆች ዝርዝር ተግባርና ኃላፊነትም በረቂቅ ሕጉ ተመላክቷል። እንደ ፖሊሲው ሁሉ ረቂቅ ሕጉም ተከሳሾች ነፃ የሕግ አገልግሎት ስለሚያገኙበት አግባብ ሥርዐት የመዘርጋቱን ኃላፊነት ለቀድሞው ፍትሕ ሚኒስቴር ለአሁኑ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰጥቷል። ይሁንና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከተከራካሪ ወገኖች አንዱ በመሆኑ ጠንካራ የሕግ ሥርዓት ሊዘረጋ ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ ማስነሣቱ አይቀርም። ስለሆነም በወንጀል ፍትሕ ፖሊሲው ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንደሚቋቋም የተገለጸው የተከላካይ ጠበቆች ተቋም ኃላፊነቱን ቢወስድ የሚሻል ይሆናል።
በወንጀል የተከሰሱ አቅም የሌላቸው ሰዎች ተከላካይ ጠበቃ በመንግሥት ወጪ የማግኘት መብት ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ወጪ የተመደበላቸው ጠበቃ በሕግ መሠረት ሙያውን፣ እውቀቱንና ልምዱን በመጠቀም ኃላፊነቱን ሳይወጣ በቀረ ጊዜ በሌላ እንዲተካ ፍርድ ቤቱን የመጠየቅ መብትም በረቂቅ ሕጉ ተሰጥቷቸዋል። ከዚህም ሌላ ፍርድ ቤቶች ክስ መስማት ከመጀመራቸው በፊት ተከሳሾች አቅም በማጣታቸው ምክንያት በጠበቃ ያልተወከሉ መሆኑንና ያለጠበቃ ቢከራከሩ ፍትሕ ይዛባል ብለው ሲያምኑ በመንግሥት ወጪ ጠበቃ እንዲመደብላቸው ማዘዝ ይጠበቅባቸዋል። እንደዚሁም (ተከሳሾች ጠበቃ ያገኙት ከክሱ መሰማት ጥቂት ቀናት በፊት ከሆነ ለዝግጅት የሚሆን በቂ ቀጠሮ መስጠት ይኖርባቸዋል።
ሰ. የሰበር ውሳኔ
ተከላካይ ጠበቃ ከማግኘት መብት ጋር ተያይዞ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ እዚህ ላይ ማንሣቱ ተገቢ ይሆናል። ለችሎቱ የቀረበው ጉዳይ ከሶማሌ ክልል ሲሆን ተከራካሪዎቹ ከሳሽ የጅጅጋ ዞን ዐቃቤ ሕግና ተከሳሽ ሻምበል ሁሴን አሊ ናቸው። ተከሳሽ የተከሰሱት በከባድ ግድያ ወንጀል ሆኖ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲሰጡም ይሁን የከሳሽ ምስክሮች በሚሰሙበት ጊዜ ፍርድ ቤቱ የመደበላቸው ጠበቃ ተገኝቶ አልተከራከረላቸውም። ሆኖም ፍርድ ቤቱ የከሳሽ ጠበቃ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ሳይፈጥር ወይም ሌላ ጠበቃ ሣይተካ ክርክሩን አስቀጥሎ አመልካች በሞት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ተከሳሹ ይግባኛቸውን ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ግራ ቀኙ እንዲከራከሩ ቢደረግም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በተከሳሽ ላይ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠውን የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሣኔ ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል። ከዚያም ተከሳሹ በክርክሩ ሂደት በጠበቃ የመወከል መብታቸው ባለመጠበቁ ምክንያት መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት የሰበር ይግባኛቸውን ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበዋል።
ሰበር ሰሚ ችሎቱም ተከሳሽ የተከሰሱበት ጉዳይ ከባድ መሆኑ እየታወቀ በጠበቃ ሣይወከሉ ክርክሩ መካሄዱና ውሣኔ መሰጠቱ ባግባቡ መሆን ያለመሆኑን በጭብጥነት ይዞ መርምሯል። ከዚያም በኋላ ፍርድ ቤቶች ተከሣሾች በመረጡት ጠበቃ የመወከል ሕገ--መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ በቂ ጊዜ ከመስጠት በተጨማሪ ይኸው መብት እንዳላቸውም በችሎቶቻቸው ሊገልጹላቸው የሚገባ መሆኑን አስምሮበታል። ይህም ብቻ ሣይሆን ተከሣሾች ብቃት ባለው ጠበቃ መወከላቸውን ማረጋገጥም የፍርድ ቤቶች የስራ ድርሻ እንደሆነ በውሳኔው አስፍሯል።
ከዚህም በላይ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር የተከሰሱ ሰዎችን በተመለከተ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግሥት የተካተቱት መብቶች ወዲያውኑ ሊተገበሩ የሚገቡ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 13/1/ ስር በተገለጸው አግባብ በወንጀል የተከሠሡ ሠዎችን ሕገ--መንግሥታዊ መብቶች የዳኝነት አካሉ የማክበርና የማስከበር ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ያለበት መሆኑን በማስገንዘብና የተከሠሡ ሰዎችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ በዳኛው ትከሻ የወደቀ ስለመሆኑ ሊስተዋል ይገባል በማለት የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ሽሯል።
በአጠቃላይ የወንጀል ፖሊሲውም ይሁን የወንጀል ስነ-ሥርዓት ረቂቅ ሕጉ እንዲሁም የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው ውሳኔ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን ፍትሐዊነት፣ ሚዛናዊነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ መሟላት ከሚገባቸው መሰረታዊ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የሆነውን ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት ወደፊት ለማራመድ ያስችላሉ ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ለዚህ ደግሞ እንደመነሻ ሆነው ያገለገሏቸው በቀደሙት ክፍሎች የተብራሩት የአስገዳጅነት ውጤት ያላቸውና የሌላቸው አሕጉራዊና ዓለማቀፋዊ ሰነዶች መሆናቸው አያጠራጥርም።
የሁሉም ክልሎች ሕገ-መንግሥታት አንቀጽ 20 ንዑስ (5) ከፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ተመሳሳይ አንቀጽ ጋር ቃል በቃል ይመሳሰላል። በድንጋጌውም መሰረት በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ለጠበቃ ከፍለው የቀረበባቸውን ክስ ለመከላከል አቅም የሌላቸው ከሆኑና በዚህም ምክንያት ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው”። ይሁን እንጂ ሕገ-መንግሥታቱ በጠበቃ ስለመወከል ጥቅል ድንጋጌ ከማስቀመጥ የዘለለ መብቱ እንዴት እንደሚፈጸም ያስቀመጡት ግልጽ አቅጣጫ የለም።
የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲውም ተከላካይ ጠበቆች የሚሰጡትን ነጻ የሕግ ድጋፍ አስመልክቶ የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የሕግ ሥርዓት የመዘርጋት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ፖሊሲው ከጸደቀ አምስት ዓመታትን ቢያስቆጥርም በክልላችን ፍርድ ቤቶች የሚሠሩ ተከላካይ ጠበቆች ወጥ በሆነና በተደራጀ የሕግ ሥርዓት እየተመሩ አይደለም። ስለሆነም የክልሉ ተከላካይ ጠበቆች የሚሰጡት አገልግሎት የሚመራው በዘፈቀደ ነው ማለት ይቻላል።
ከዚህም ባለፈ የሕገ-መንግሥታቱን ጥቅል ድንጋጌም ሆነ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲውን መሰረት አድርገው የወጡ ሙሉ በሙሉ ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብትን የሚመለከቱ ሕጎች በክልሎች የሉም። ይህ ሲባል ግን በተለያዩ ሕጎች በተበታተነ መልኩ በጠበቃ ስለመወከል የሚያወሱ ውስን ድንጋጌዎች የሉም ማለት አይደለም።
በዚህ ርእሰ-ጉዳይ ዙሪያ የሚጻፉ ጽሁፎች ተከላካይ ጠበቃ የሚያስፈልጋቸውን ድሃ ሰዎች ለመወሰን የቀረበባቸው ክስ ውስብስብነት፣ የቅጣቱ ክብደትና የሚያስከትለው ኢፍትሀዊነት ግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ ያመለክታሉ። በራሳቸው አቅም ጠበቃ ለማቆም የማይችሉ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በመንግሥት ወጪ ሊቆምላቸው እንደሚገባ ከዚህ በላይ ከተብራሩት ሕግጋት መረዳት ይቻላል። ነገር ግን ድህነት እንዴት እንደሚለካ በሕግጋቱ የተባለ ነገር የለም።
ድህነትን በተመለከተ ነጻ የሕግ ድጋፍ የሚሰጡ አገሮች በመንግስት ወጪ ጠበቃ ሊቆምላቸው የሚገባቸውን ሰዎች ለመለየት የገንዘብ አቅምን በግልፅ ወስነው ያስቀምጣሉ። ለምሳሌ በታንዛኒያ የገንዘብ አቅም የሌላቸው ናቸው ተብለው ነጻ የሕግ ድጋፍ የሚሰጣቸው ሰዎች በአማካይ ከ82 የአሜሪካ ዶላር ያነሰ ወርሀዊ ገቢ የሚያገኙ ናቸው። በደቡብ አፍሪካ ደግሞ ነጻ የሕግ ድጋፍ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ዜጎች በሀገሪቱ ገንዘብ /ራንድ/ በወር ከ5,500 በታች የሚያገኙ ሊሆኑ ግድ ይላል።
ድህነት በኢትዮጵያስ እንዴት ይለካል? ለሚለው ጥያቄ በቂ ምላሽ የሚሰጥ ኢትዮጵያ የፈረመችው አሕጉራዊም ይሁን ዓለማቀፋዊ ስምምነት ብሎም ሀገራዊ ህግ የለም። በዚህ ጽሑፍ ክፍል አንድ ላይ የተጠቀሱት ብሄራዊ ሕጎችም ቢሆኑ ተከላካይ ጠበቃ የሚያስፈልገውን ትክክለኛ ድሃ ሰው ለመወሰን የሚያስችሉ አይደሉም። ከዚህም የተነሳ ነጻ የሕግ ድጋፉ ጠበቃ ለማቆም አቅም ለሌላቸው ዜጎች ሳይሆን በተቃራኒው ላሉ የሚሰጥበት እድል ይኖራል።
በሌሎች ክልሎች ያለውን ሁኔታ ማካተት ባይቻልም በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ ግን ከሀገራዊው ይለያል። ምክንያቱም ነጻ የሕግ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን በጥብቅና አሰጣጥ፣ ምዝገባና በጠበቆች ስነ-ምግባር ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 58/2000 ዓ.ም አንቀጽ 9 ንኡስ አንቀጽ (1) አማካኝነት መለየት ይቻላል። በዚህም መሰረት ነፃ የሕግ ድጋፍ ማግኘት የሚችሉት ወርሃዊ የገቢ መጠናቸው ከብር 240 በታች የሆነባቸው ሰዎች ናቸው።
እነዚህ ሰዎች በወር ከ240 በታች ከሚያገኙት ገቢም በተጨማሪ በትርፍነት ሊወሰድ የሚችል የማይንቀሳቀስና የሚንቀሳቀስ ሃብት የሌላቸው መሆን አለባቸው። ይህንንም የሚያሳይ በሶስት ምስክሮች የተረጋገጠ ማስረጃ ከሚኖሩበት ቀበሌ ማህበራዊ ፍ/ቤት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ አይነት ጥብቅ መስፈርት በደንቡ መውጣቱ ነጻ የሕግ ድጋፍ በዘፈቀደ እንዳይሰጥ ያደርጋል፤ ለዚህ የተገቡ ትክክለኛ ተጠቃሚዎችን በመለየቱ ጊዜ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንም ይፈታል።
ይሁን እንጂ ያለንበት ነባራዊ እውነታ 240 ብር ወርሀዊ ሳይሆን እለታዊ ገቢ እየሆነ መምጣቱን ያሳያል። በመሆኑም ነጻ የሕግ ድጋፍ መሰጠት ያለበት በወር ከ240 ብር በታች የሆነ ገቢ ለሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው የሚለውን ህግ ፈቃጅ ሳይሆን ከልካይ ያስመስለዋል። ስለዚህ ነጻ የሕግ ድጋፍ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ሰዎች ለመለየት የሚያስችል የገንዘብ አቅም በግልፅ ወስኖ ማስቀመጡ ተገቢ ሆኖ ሳለ የገንዘብ መጠኑን በእጅጉ ማሳነስ ግን ነጻ የሕግ ድጋፉን መልሶ እንደመከልከል አስቆጥሮታል፡።
ነገር ግን የዚህ ደንብ ተፈጻሚነት በግል ጠበቆች ላይ በመሆኑ በደንቡ የተቀመጠውን መሥፈርት አቅም ለሌላቸው የወንጀል ተከሳሾች በመንግሥት ወጪ ተከላካይ ጠበቃ ለማቆም መጠቀሙ የሚከብድ ይሆናል። በተግባር እየተሠራ ያለውም ደንቡን መሰረት ተደርጎ አይደለም። የጽሑፉ አቅራቢ በርካታ የክርክር መዛግብትን ለማየት የቻለ ሲሆን ፍርድ ቤት ለወንጀል ተከሳሾች ተከላካይ ጠበቃ የሚመድበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ የግል ጠበቃ ለማቆም አቅም ያላቸውና የሌላቸው መሆኑን ጠይቆ በሚሰጡት መልስ ላይ ተመስርቶ ብቻ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።
ከፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ጋር ተመሳሳይ የሆኑት የክልሎች ሕግጋተ-መንግሥትም ይሁኑ ሀገራችን የፈረመቻቸው አሕጉራዊና ዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች በጠበቃ ተወክለው ለመከራከር አቅም ለሌላቸው የወንጀል ተከሳሾች መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ሊያቆምላቸው ይገባል ከሚሉ በስተቀር መብቱ ተግባራዊ የሚደረግበትን የክርክር ሂደት አያመላክቱም። በዚህ ጉዳይ በክፍል አንድ የተጠቀሱት የአስገዳጅነት ውጤት የሌላቸው አሕጉራዊና ዓለማቀፋዊ ሰነዶች የተሻሉ እንደሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት በወንጀል የፍትሕ ሥርዓትና በነፃ የሕግ ድጋፍ ተደራሽነት ላይ ያወጣው መርሕና መመሪያ እንዲሁም የአፍሪካ ሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ያወጣው የላሎንጌ መግለጫና የድርጊት መርሐ-ግብር ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት በየትኛውም የወንጀል ክርክር ሂደት መሰጠት እንዳለበት መደንገጋቸውን ለአብነት ያህል መጥቀሱ በቂ ይሆናል። ስለዚህ እነዚህ ሰነዶች የተከላካይ ጠበቆችን የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት በመነሻነት የማገልገል ሚና ቢኖራቸውም በቀደመው ክፍል ከተገለጹት የተበታተኑ ድንጋጌዎች ውጪ የመንግሥት ጠበቃ የሚቆምበትን የወንጀል የክርክር ሂደት የሚያሳይ በክልሎች የወጣ አንድም ሕግ የለም።
በአማራ ክልል ያለውን ለአብነት ስናይ የተሻሻለው የክልሉ ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አዋጅ ቁጥር 209/2006 ዓ.ም በአንቀጽ 2 (8) ተከላካይ ጠበቃን ሲተረጉም በክልሉ ፍርድ ቤቶች በከባድ ወንጀል ተከሰውና ጠበቃ አቁመው መከራከር ለማይችሉ ሰዎች በጠበቃነት ተወክሎ የሚከራከር ባለሙያ መሆኑን ቢገልጽም በወረዳ ፍርድ ቤት በከባድ ወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች ቆሞ የሚከራከር የመንግሥት ጠበቃ እንደሌለ ተረጋግጧል። በከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚገኙትም ቢሆኑ አዳዲስ የወንጀል ጉዳዮችን እንጂ ከወረዳ የሚመጡትንም ይሁን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሄዱ ይግባኞችን አይቀበሉም፤ አያዘጋጁም። ስለሆነም በወረዳና በይግባኝ የክርክር ሂደት ሕገ-መንግሥታዊ የሆነው ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት መብት እየተከበረ አይደለም ለማለት ያስደፍራል።
ተከላካይ ጠበቃ የሚያስቆሙ የወንጀል ዓይነቶች
በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በራሳቸው አቅም ጠበቃ አቁመው መከራከር የማይችሉ ከሆነና በዚህም ምክንያት ፍትሕ የሚጓደል ሲሆን በመንግሥት ወጪ የሚቆም ጠበቃ የማግኘት ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው የክልሎችም ይሁኑ የፌደራሉ ሕግጋተ-መንግሥት ያረጋግጣሉ። ይሁን እንጂ አንዳቸውም ፍትሕ የሚጓደለው መቼ እንደሆነ በግልጽ አያስረዱም። እንደዚሁም የመንግሥት ጠበቃ የሚያስፈልጋቸውን የወንጀል ዓይነቶች ለይተው አላስቀመጡም።
ስለሆነም ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ የሚለውን ጥቅል ድንጋጌ በተመለከተ የሕግ አውጪውን ሀሳብ የሚጠቁሙ መሥፈርቶችንና ዝርዝር ሕጎችን መፈለግ የግድ ይላል። ይኸው ጥቅል ድንጋጌ ሲተረጎም ግምት ውስጥ ሊገቡ የሚገቡ በብዙ የሕግ ባለሙያዎች ተቀባይነት ያገኙ ሦስት ዓይነት መሥፈርቶች አሉ። እነሱም የጉዳዩ ውስብስብነት፣ የቅጣቱ ከባድነትና ተከሳሹ ራሱን ለመከላከል ያለው አቅም የሚሉት ናቸው። ስለዚህ እነዚህን መስፈርቶች በአግባቡ መመዘን ከተቻለ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት የሚከብድ አይሆንም።
ከመሥፈርቶቹ በተጨማሪ ሕግ አውጪው ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ የሚለውን እንዴት መተርጎም እንዳሰበ የሚያሳዩ ውስን ሀገራዊና ክልላዊ አዋጆች ይገኛሉ። ከእነዚህ ቀዳሚው የመከላከያ አዋጅ ቁጥር 27/1988 ዓ.ም ሲሆን ከ5 ዓመት በማያንስ እስራት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል የተከሰሰ ሰው ተከላካይ የማቆም አቅም ከሌለው መንግሥት ተከላካይ ይመድብለታል በማለት ይደነግጋል። ይህም ድንጋጌ ከሦስቱ መሥፈርቶች የቅጣቱ ከባድነት ለሚለው ትኩረት በመስጠት ፍትሕ መቼ ሊጓደል እንደሚችል ለመጠቆም ይሞክራል።
የተሻሻለው የኦሮምያ ክልል ፍርድ ቤቶች ማቋቋምያ አዋጅ ቁጥር 141/2000 ዓ.ምም ተመሳሳይ ድንጋጌ ይዟል። ይህም አዋጅ በአንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ (2) ከ5 ዓመት በማያንስ እስራት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በመንግሥት ወጪ ጠበቃ ሊቆምላቸው እንደሚገባ ይገልጻል። በዚህም አዋጅ ትኩረት የተሰጠው ከጉዳዩ ውስብስብነትና ተከሳሹ ራሱን ለመከላከል ያለው አቅም ከሚሉት መሥፈርቶች ይልቅ ለቅጣቱ ከባድነት እንደሆነ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
ምንም እንኳን እነዚህ አዋጆች በመንግሥት ወጪ ጠበቃ የሚያስቆሙ የወንጀል ዓይነቶችን ለይተው ቢያስቀምጡም ከ5 ዓመት በታች በሆነ እስራት በሚያስቀጡ ወንጀሎች ክርክር ጊዜ ፍትሕ ሊጓደል አይችልም ወደሚል አቋም ስለሚወስዱ ምሉዕነት ይጎድላቸዋል። ለምን ቢሉ የፍትሕ መጓደል ከጉዳይ ጉዳይ ስለሚለያይና በቀላል ወንጀል ለተከሰሱ ሁልጊዜም ፍትሕ አይጓደልም በከባድ ወንጀል ለተከሰሱ ደግሞ ሁሌም ፍትሕ ይጓደላል ብሎ ለመደምደም ስለማይቻል ነው።
የተሻሻለው የትግራይ ክልል ፍርድ ቤቶች ማቋቋምያ አዋጅ ቁጥር 243/2006 ዓ.ም ደግሞ በአንቀጽ 6 (2) በወንጀል ተከሶ በራሱ ጠበቃ ሊቀጥር አቅም የሌለው መሆኑን ማስረጃ ለማቅረብ የሚችልና ያለ ጠበቃ ቢከራከር ፍትሕ ሊጓደልበት ይችላል የሚባል ከሆነ ፍርድ ቤት በመንግሥት ወጪ ተከላካይ ጠበቃ ይመድብለታል ይላል። በተጨማሪም በአንቀጽ 13 (4) የተከላካይ ጠበቆች ደጋፊ የሥራ ሂደት በወረዳ ፍርድ ቤት ደረጃ እንደሚደራጅ ያስቀምጣል።
ከዚህ በመነሣት ይህ አዋጅና ከፍ ብሎ የተጠቀሱት አዋጆች በተወሰነ መልኩ ልዩነት እንደሚታይባቸው መናገር ይቻላል። ምክንያቱም ይህ አዋጅ ፍትሕ ይጓደላል ብሎ የሚያስበው በቅጣቱ ከባድነት ሳይሆን ተከሳሹ ጠበቃ ለመቅጠር አቅም በማጣቱ ነው። ይህም ሲባል ተከሳሹ በየትኛውም የወንጀል ዓይነት ቢከሰስ በግሉ ጠበቃ አቁሞ ለመከራከር የማይችል መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ ካቀረበ ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል። ለዚህም ነው አዋጁ የተከላካይ ጠበቆችን የሥራ ሂደት በወረዳ ፍርድ ቤት እንዲደራጅ ያደረገው።
ሆኖም አዋጁ በራሳቸው ጠበቃ ሊቀጥሩ የማይችሉ የወንጀል ተከሳሾች የሚለዩበትንና የሚመለመሉበትን መሥፈርት ለይቶ አያስቀምጥም። ከዚህም የተነሣ በአዋጁ መሰረት ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ የሚለውን ጥቅል ድንጋጌ በአግባቡ ተርጉሞ ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት ያስቸግራል። በተጨማሪም የድህነት ማስረጃው ከየት ተቋም እንደሚመጣ የሚገልጸው ነገር ስለሌለ በአፈጻጸሙ ላይ ችግር ማስከተሉ አይቀርም።
ወደ አማራ ክልል ስንመጣ የመንግሥት ጠበቃ የሚቆመው በክልሉ ፍርድ ቤቶች በከባድ ወንጀል ለተከሰሱ ሰዎች መሆኑን ከፍ ሲል ያየነው ለተከላካይ ጠበቃ የተሰጠው ትርጓሜ ያስረዳል። ከባድ የሚባሉት የወንጀል ዓይነቶች ከ10 ዓመት በላይ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች እንደሆኑ ደግሞ በተሻሻለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወንጀል የሥራ ሂደት ቢፒአር ሰነድ ላይ ተመልክቷል። ይህም ሁኔታ ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ የሚለው በአማራ ክልል የሚመዘነው በቅጣቱ ከባድነት መሆኑን ያሳያል።
በዚህም አለ በዚያ ከዚህ በላይ የተብራሩት ሕጎች ፍትሕ ሊጓደል የሚችለው መቼ ነው የሚለውን ጥያቄ በበቂ ሁኔታ አይመልሱም። ምክንያቱም በከባድና ቀላል ወንጀሎች እንደቅደም ተከተላቸው ሁልጊዜ ፍትሕ ይጓደላል አይጓደልም ብሎ ለመደምደም ይከብዳል። በከባድ ግድያ ክርክር ሂደት ፍትሕ ላይጓደልና በቀላል ስርቆት ጊዜ ደግሞ ፍትሕ ሊጓደል እንደማይችል ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻልም። ስለዚህ ፍትሕ የሚጓደል ሆኖ ሲገኝ የሚለውን ጥቅል ድንጋጌ እንደየ ጉዳዩ ዓይነት እያዩ ለመተርጎም የሚያስችል የሕግ ሥርዓት ሊኖር የግድ ይላል።
ለማጠቃለል የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) እንደሚለው “ድህነት ለመብቶች መጣስ ያጋልጣል። መልሶ ደግሞ ለተጣሱት መብቶች መከበር ኃይል ያሳጣል።” በመሆኑም ለዚህ ዓይነቱ ዕንቅፋት ዓይነተኛ መፍትሔ ለሆነው ለፌደራሉና ለክልሎች ሕግጋተ-መንግሥት አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 5 ድንጋጌ ማስፈጸሚያነት የሚያገለግሉ ዝርዝር ሕጎችን ማውጣቱ ለነገ የማይሉት የቤት ሥራ መሆን አለበት።