መግቢያ
በኢፌዲሪ ህገመንግስትም ይሁን ኢትዮጵያ በአፀደቀቻቸው አለማቀፋዊ የሰበዓዊ መብት ስምምነቶች እንዲሁም በሌሎች አዋጆች ላይ የተቀመጡ አያሌ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተፈፃሚነት እንዲኖራቸው በህግ እና በስርዓት የሚመሩ፤ ዋና ግባቸው እና የሥራ መለኪያቸው ህግ እና ሥርዓትን ማስከበር የሆኑ ተቋማት መኖራቸው ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ቅድመ ሁኔታ ነው። እነዚህ ተቋማት እርስ በራሳቸው በሚኖራቸውም ግንኙነት ግልፅ የሆነ የሚና ወይም የተግባር ልዩነት ሊኖራቸው የተገባ መሆኑም የሚታመን ነው። በዚህ መርህ ውስጥ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አፈፃፀምን በሚመለከት ቀዳሚ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የመንግስት አካላት ውስጥ በተለይም የህግ አስፈፃሚው እና የህግ-ተርጓሚው ሚና በእጅጉ የሚልቅ ነው። እነዚህ ተቋማት በሌሎች ሀገራት ላይ ያላቸው መስተጋብር እና ጤናማ የሆነ ውድድር የዜጎች የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተሻለ እንዲከበሩ አስተዋፅኦ አድርጓል።
እንዳለመታደል ሆኖ የሀገራችን ተቋማት በእጅጉ በግልሰቦች እና በተለያዩ ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎች ውስጥ የወደቁ በመሆናቸው የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አፈፃፀም ላይ ብዙ ጥሰቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸው ማስረጃ የማይጠየቅበት እውነት ነው። ከእነዚህ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ውስጥ በኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 19 (4) ላይ በግልፅ የተደነገገው በፖሊስ የተያዙ ሰዎች በተያዙ በአርባ ስምንት ሰዓት ፍርድ ቤት የመቅርብ መብት እንዳላቸው ተገልጧል። በመቀጠልም የህገመንግስቱ አንቀፅ 19(6) የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት እንዳላቸው በመርህ ደረጃ ደንግጓል። ይህ መርህ ሊጣስ የሚችለውም በህግ በተደነገጉ በልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ ሲጠይቅ እንደሆነ በግልፅ ተደንግጓል።
የዚህ አጭር የፁሁፍ ምልከታም ይህንን ህገ-መንግስታዊ መብት የሆነውን የዋስትና መብት አፈፃፀምን በተመለከተ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በፖሊስ በኩል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብት ላይ የሚያሳለፏቸው ብይኖች ላይ፤ ብይኑን አላስፈፅምም ይግባኝ እላለሁ በሚል በሚቀርቡ የይግባኝ አቤቱታዎችን ለመገምገም ያለመ ሲሆን የእነዚህ ይግባኞችን የህግ መሰረትም ይፈትሻል።
የዋስትና መብት እና በዋስትና ላይ የሚቀርብ ይግባኝ አግባብነት ባላቸው የኢትዮጵያ ህጎች እንዴት ይታያል?
የዋስትና መብት በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት
በፖሊስ የተያዘ ሰው ዋስትና የማግኘት ህገ-መንግስታዊ መብት አለው። ይህ የሰብዓዊ መብት አካል ነው። በኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 19 (6) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው የተያዘ ሰው በዋስ የመፈታት መብት አለው። በመሰረቱ ማንኛውም ሰው በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 17 (1) ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በሕግ ከተደነገገ ሥርዓት ውጭ ሊያዝ፤ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታስር እንደማይገባው ተቀምጧል። ይሁን እንጂ የህግ ሥነ-ስርዓትን ተከትሎ የተያዘ ሰው ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ በሚቆጠር በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅርብ መብት እንዳለውም ተደንግጓል። የተያዘው ሰው ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤት ፍትህ እንዳይጓደል ባለመ መልኩ በጥበቃ ስር እንዲቆይ ለማዘዝ ወይም ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ሲጠየቅ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ ሊፈቅድ እንደሚችል ሲደነግግ የተያዘው ሰውም ፍርድ ቤቱ የአካል ነፃነቱን እንዲያስከብርበት ሊጠይቅ እንደሚችለክ በግልፅ ተቀምጧል። በእነዚህ ጊዜያት መካከል ነው የዋስትና መብት በእጅጉ አስፈላጊ የሚሆነው። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የሕገ-ምንገስቱ አንቀፅ 19(6) ላይ ፍርድ ቤቶች በህግ የተደነገገ ሁኔታዎች ላይ የዋስትና መብትና ላለመቀበል ስልጣኑ የተሰጣቸው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ዋስትና ፈቅደው የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ሊያዝዙ እንደሚችሉም ተደንግጓል። በመሆኑም በፖሊስ ተይዞ ፍርድ ቤት የቀረበን ሰው ፍርድ ቤቶች በመርህ ደረጃ የዋስትና መብቱን የማስጠበቅ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን የዋስትና መብትን ሊከለክሉ የሚችሉት አግባብነት ባላቸው ግልፅ ድንጋጌዎች ብቻ ነው። በዚህ መሰረት ከላይ ተይዞ የቀረበው ግለሰብ የሚያቀርበው የዋስትና ጥያቄ በዋስትና የመፈታት ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው በመሆኑ በልዩ ሁኔታ በግልፅ በሌላ ተቃራኒ የህግ ድንጋጌ ካልኖረ በቀር ተቀባይነት ያለው ጥያቄ ነው።
የዋስትና መብት እና በዋሰትና ላይ የሚደረግ ይግባኝ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ሕግ
እንደሚታወቀው ሕገ-መንግስት ዝርዝር የህግ ጉዳዮችን የሚይዝ ሰነድ ባለመሆኑ ከላይ በተጠቀሰው የሕገ-መንግስት አንቀፅ (19(6)) ዋስትናን የሚመለከቱ ሌሎች ህጎችን ከሕገ-መንግስቱ ውጭ ባሉ ሌሎች አዋጆች ላይ ማሰስ የግድ ይላል። ከእነዚህ ህጎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው በ1954 ዓ/ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ህጉ ነው። በዚህ አዋጅ አንቀፅ 29(1) እንደተደነገገው ፖሊስ የጠረጠረውን ግለሰብ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን በዚህ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር 2 ላይም በአዋጁ አንቀፅ 59 አስፈላጊውን ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ተጠቅሷል። የሥነ-ሰርዓት ህጉ አንቀፅ 59 በፖሊስ አንድ ግለሰብ ተይዞ ሲቀርብለት አግባብነት ያለውን ውሳኔ ለመወሰን ሁለት አማራጮች ተቀምጠውለታል። እነዚህም አማራጮች የዋስትና መብት አስጠብቆ የተያዘውን ሰው በዋስትና መልቀቅ ወይም በማረፊያ ቤት በእስር እንዲቆይ መወሰን የሚሉት ናቸው። እነዚህ አማራጮች ያለምንም ቅደመ ሁኔታ በፍርድ ቤቱ ይሁንታ የሚመረጡ ሳይሆኑ ህጋዊ ቅደመ ሁኔታዎች የተቀመጡላቸው ናቸው። በፖሊስ በኩል የተያዘው ሰው በማረፊያ ቤት ውስጥ እንዲቆይ ፍርድ ቤቱን መጠየቅ የሚችል ሲሆን የዚህ ጥያቄ አላማም መርማሪ ፖሊሱ ምርመራውን እስኪያጠናቅቅ በቂ ጊዜ ለመስጠት ያለመ መሆን ይኖርበታል። ይህም ጊዜ በእያንዳንዱ ቀጠሮ የሚሰጠው ተጨማሪ ጊዜ ከ14 ቀናት መብለጥ እንደሌለበት በዚሁ የሥነ-ሰርዓት ህጉ አንቀፅ 59(3) ተደንግጓል።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የፖሊስን ጥያቄ ተቀብሎ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጥ አስገዳጅ ድንጋጌ በዚሁ አዋጅ ላይ አልተጠቀሰም። በተጨማሪም የዋስትና መብትን የሚያስከለክሉ ሁኔታዎች በተለይም በሥነ-ሰርዓት ህጉ አንቀፅ 63 ጀምሮ በጠቀሱት አንቀፆች ላይ በግልፅ ካልተቀመጡ በስተቀር ፍርድ ቤቱ ዋስትናን ማረጋገጥ ይኖርበታል። በዋናነት የዋሰትና ጥያቄ በተያዘ ሰው በኩል የቀረበለት ፍርድ ቤት በሥነ-ሰርዓት ህጉ አንቀፅ 66 በሰፈረው መሰረት በዋስትና ላይ የሚሰጠውን ውሳኔ በ48 ሰዓት ውስጥ የመስጠት ግዴታ አለበት። በዚህ ውሳኔ ሂደትም የአቃቢ ህግን ወይም የመርማሪ ፖሊሱን አስተያየት ሊሰማ ይችላል። ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ተቀብሎ የተያዘው ሰው እንዲለቀቅ ከወሰነ አብሮ ዋስትና የተፈቀደበትን ቅድመ-ሁኔታም ማስቀመጥ ይኖርበታል (ቅደመ ሁኔታዎች የሰው ዋስትና ማቅረብ ወይም ገንዘብ ተቀማጭ ዋስትና ሊሆን ይችላል)። በዚህ መሰረት የተያዘው ሰው ፍርድ ቤቱ ያስቀመጣቸውን የዋስትና ቅድመ ሁኔታዎች ካሟላ የተያዘው ሰው ከእስሩ መለቀቅ እንዳለበት የሥነ-ስርዓት ህጉ አንቀፅ 72 ላይ በግልፅ ደንግጓል። በተቃራኒው ፍርድ ቤቱ በተያዘው ሰው የቀረበውን በዋስ ልለቀቅ አቤቱታ ካልተቀበለው ሥነ-ስርዓት ህጉ አንቀፅ 75 ላይ የይግባኝ አማራጭ አስቀምጧል። በመሆኑም አንድ በፍርድ ቤት ዋስትና የተከለከለ በፖሊስ ማረፊያ ቤት ውስጥ የሚገኝ ሰው አግባብነት ላለው ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ በማቅረብ የዋስትና መብቱን ለማረጋገጥ ሁለተኛ እድል ተቀምጦለታል።
በዚህ መሰረት ጥያቄ የሚሆነው ፍርድ ቤቱ በፖሊስ የተያዘን ሰው የዋስትና ጥያቄ ተቀብሎ እንዲለቀቅ ውሳኔ በሚያሳልፍበት ወቅት ፖሊስ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንዲያቀርብ የሥነ-ስርዓት ህጉ ይፈቅድለታል ወይስ አይፈቅድም? የሚለው ነው። ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው አንድን ሰው የያዘ የፖሊስ መኮነን እና በዚህ ፖሊስ የተያዘ አንድ ሰው ሁለት ተፃራሪ ፍላጎቶች አሏቸው። ፖሊስ ምርመራዪን እስከማጠናቀቅ የያዝኩት ግለሰብ በቁጥጥሬ ውስጥ መቆየት አለበት የሚለው ሲሆን የተያዘው ሰው ደግሞ በዋስትና ለመለቀቅ ሕገ-መንግስታዊ መብቴ ይከበርልኝ የሚለው ፍላጎት ነው። ከላይ እንዳየነው የተያዘው ግለሰብ የዋስትና መብቱ በፍርድ ቤት ተቀባይነት ካላገኘ ይግባኝ የማለት መብት እንዳለው በግልፅ ተደንግጓል። በፖሊስ በኩል የተያዘው ሰው ፍርድ ቤት ካቀረበ በኋላ ምርመራውን ካላጠናቀቀ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ሊጠይቅ እንደሚችል የሥነ-ስርዓት ህጉ አንቀፅ 59(2) ላይ በግልፅ ተደንግጓል። ይሁን እንጂ ይህንን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበል የተያዘውን ሰው ዋስትና ጠብቆ በዋስትና እንዲለቀቅ ውሳኔ ከሰጠ ፖሊስ ይግባኝ የማለት መብትን ይህ ድንጋጌ አይሰጠውም። ይህንን ጥያቄ በዚህ ፁሁፍ ቁጥር ሶስት ላይ በይበልጥ የተብራራ ቢሆንም ከስር እንደምናያቸው ሌሎች ልዩ ሁኔታዎች እስከሌሉ ድረስ በዋስትና ጉዳይ ላይ ለተያዘው ሰው የተሰጠው ይግባኝ የማለት መብት ለፖሊስ አልተሰጠውም። በዚህ መሰረት አንድ ፍርድ ቤት የአንድን የተያዘን ሰው የዋስትና መብት ተቀብሎ ውሳኔ ከሰጠ ቀጣዩ ሥነ-ሰርዓት የሚሆን በአንቀፅ 72 ላይ የተቀመጠው ነው። በዚህ አንቀፅ ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ፍርድ ቤት የተያዘን ሰው በዋስትና ለመልቀቅ ውሳኔ ካሳለፈ በውሳኔው ላይ የተቀመጡ መስፈርቶች ወይም ቅደመ ሁኔታዎች እስከተሟሉ ድረስ የተያዘው ሰው መለቀቅ አለበት። በመሆኑም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ሕጉ ፍርድ ቤት ዋስናን በተመለከተ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንዲያቀርብ የሚፈቅድ ድንጋጌ የለውም።
የዋስትና መብት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012
የቀደሞው ፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ከመወደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ህግ ሰፋ ያለ ሥልጣን ለመርማሪ ፖሊስ የሰጠ ሲሆን በፖሊስ የተያዘ ሰው ያለውን የዋስና መብትም በእጅጉ የሚያጣብቡ የህግ ድንጋጌዎችን ያቀፈ ነበር። ይህንን አዋጅ በመሻር የፀደቀው የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በተለይም በፖሊስ የሚያዙ ዜጎችን መብት ከማስከበር አኳያ ግልፅ ድንጋጌዎች አካትቶ ወጥቷል። በተለይም ይህ አዋጅ በአንቀፅ 45 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ወይም ተከሶ በማቆያ ቤት ወይም በማረሚያ ቤት ያለ ሰው በህገ መንግስቱ፤ በኢትዮጵያ በፀደቁ አለም አቀፍ ስምምነቶች እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች የተቀመጡ መብቶች መከበር እንዳሉባቸው በግልፅ ተቀምጧል። በተጨማሪም በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 39(3) ላይ በተገለፀው መሰረት ፍርድ ቤቶች በሽብር ተጠርጥሮ የተያዘን ወይም የተከሰሰን ሰው ከአያያዙ ጋር በተያያዘ በሚያነሰው የመብት ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት ተግቢውን ትዕዛዝ መስጠት እንዳለባቸው ተደንግጓል።
ከላይ ከተጠቀሱት ድንጋጌዎች ውጭ በዚህ አዋጅ መሰረት ፖሊስ በሽብር ጠርጥሮ የያዘውን ሰው ፍርድ ቤት የዋስትና መብቱን በማክበር በዋስ እንዲፈታ በሚሰጠው ውሳኔ ወይም ብይን ላይ ይግባኝ እንዲል የሚያስችለው የህግ ድንጋጌ አዋጁ ላይ አልተካተተም።
ፖሊስ በተደጋጋሚ የዋስትና መብት መከበር ላይ የሚያቀርበው ይግባኝ በትኛው የህግ መሰረት ነው?
የዚህ አጭር ፁሁፍ ዋንኛ አላማ ፖሊስ በተለያዩ የወንጀል ጉዳዮች ላይ በሚስጡ በዋስትና የመለቀቅ ውሳኔዎች ላይ የሚያቀርበው የይግባኛ አቤቱታ የህግ መሰረት አለው ወይስ የለውም? የሚለው ጥያቄ ላይ አስተያየት መስጠት ነው። የፁሁፉ ዋና መነሻ ሃሳብም ፖሊስ በተደጋጋሚ በሚያቀርባቸው የይግባኝ አቤቱታዎች በተለይም የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎች በህገ-መንግስቱ የተሰጣቸውን የዋስትና መብት በእጅጉ እያጣበበ የመጣ አሰራር መሆኑ፤ ፍርድ ቤቶች የተያዙ ሰዎችን መብት ለማስከበር ያላቸውን ሚና በእጅጉ የሸረሸረ ተግባር ስለሆነ፤ ፖሊስ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን በበላይ ፍርድ ቤቶች ሳያሳግድ አላስፈፅምም በማለቱ፤ ፖሊስ እነዚህን ክፍተቶች በመጠቀም አላስፈላጊ እንግልቶችን የተያዙ ሰዎች ላይ እንዲፈጥር በር የሚከፍት በመሆኑ እና ዜጎች የፍትህ ስርዓቱ ላያ ያላቸውን አመኔታ እንዲቀነስ (እንዲጠፋ) የሚያደርግ አዝማሚያ ስለሚኖረው ግልፅ የሆነ ውሳኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ በመሆኑ ነው።
በዚህ መሰረት ፖሊስ ፍርድ ቤቶች ለተያዙ ሰዎች የሚፈቅዱትን በዋስ የመለቀቅ መብትን በመቃወም በተለያዩ ጉዳዮች የሚያቀርበውን የይግባኝ አቤቱታ የትኛውን ህግ መሰረት ተደርጎ ነው ለሚለው ጥያቄ ከአብዛኞቹ የወንጀል ጉዳዮች እንደተረዳሁት ይህ የይግባኝ አቤቱታ መሰረት የሚያደርገው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ህግ አንቀፅ 74ን መሰረት ያደረገ ነው። ይህ አንቀፅ እንደሚከተለው ይነበባል።
አንቀፅ 74 አዲስ ነገር
በዋስትና ወረቀት እንዲለቀቅ ውሳኔ በተሰጠ ጊዜ ያልተገለፀ አዲስ ነገር የተገኘ እንደ ሆነ ፍርድ ቤቱ በማናቸውም ጊዜ ቢሆን በሥልጣኑ ወይም በማናቸውም ባለጉዳይ አመልካችነት ተከሳሹ በዋስትና ወረቀት የተለቀቀበት ሁኔታዎች (ግዴታዎች) እንደገና ተመልክቶ የተለቀቀው ተከሳሽ አዲስ ዋሶች እንዲያመጣ ወይም በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ለማዘዝ ይችላል።
በመሆኑም ጥያቄ መሆን ያለበት ይህ ድንጋጌ ፖሊስ ፍርድ ቤት በዋስትና መብት ላይ በሚሰጡት ዋስትና ላይ ለበላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንዲያቀርቡ በቂ የህግ መሰረት ሊሆን ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለው ነው። የዚህን ድንጋጌ ዝርዝር ንባብ ብንመለከት 1ኛ) በፍርድ ቤት የተረጋገጠ የዋስትና መብት እንደገና ሊታይ የሚችለው በመጀመሪያ ጥያቄው ሲቀርብ ያልነበረ ግን ዋስትናው ከተከበረ በኋላ የታወቀ አዲስ ነገር ሲኖር ነው። ይህ ማለት ዋስትናው በተሰጠበት እና አዲስ ነገር በተገኘበት መካከል ምክንያታዊ የጊዜ ልዩነት እንዲኖር ይገመታል። ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለፍርድ ቤት ካቀረበ በኋላ አሉኝ የሚላቸውን የጥርጣሬ ምክንያቶች ለፍርድ ቤት አስረድቶ፤ የተያዘው ሰውም የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ለፍርድ ቤት ጥያቄውን ሲያቀርብ ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄውን ከተቀበለ ወዲያውኑ ፖሊስ አዲስ ነገር ስላለኝ የሚልበት አመንክዮ የህግ መሰረት አይኖረውም።
2ኛ) ፍርድ ቤቱ በማለት የተገለፀው የይግባኝ ፍርድ ቤቱን ሳይሆን እራሱ ብይኑን ያሳለፈው ተመሳሳይ ፍርድ ቤት ነው። የይግባኝ ሥነ-ስርዓት እና ለራሱ ለፍርድ ቤቱ በአቤቱታ ያልተካተተ ፍሬ ነገር አለ በሚል አቤቱታ ማቅረብ ሁለት የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች እንደሆኑ የሥነ-ስርዓት ህግ መሰረታዊ ድንጋጌዎች ያስረዱናል። ከላይ በተገለፀው አንቀፅ ላይ የተየጠቀሰው የይግባኝ መብት ሳይሆን ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንዲያሻሽል ወይም እንዲለውጥ በራሱ በፍርድ ቤቱ ወይም በመርማሪ ፖሊስ በኩል ለራሱ ውሳኔውን ለሰጠው ፍርድ ቤት የሚቀርብ ጥያቄ ነው።
ከላይ በቀረቡት ሁለት አንኳር የህግ ምክንያቶች የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ስርዓት ህጉ አንቀፅ 74 ፖሊስ ለተያዙ ሰዎች ፍርድ ቤት የሚያረጋግጠውን የዋስትና መብት ላይ ይግባኝ እንዲያቀርብ የህግ መሰረት አለው ብሎ መከራከር አስቸጋሪ ያደርገዋል። በዚህ መሰረት ፖሊስ በተደጋጋሚ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን ወደ ጎን በመተው የዋስትና መብት የተከበረላቸውን የተያዙ ሰዎችን ይግባኝ እላለሁ በሚል ከበላይ ፍርድ ቤት በብዙ ጉዳዮች ላይ የስር ፍርድ ቤት ብይንን ሳያሳግድ እንኳን አለመልቀቁ አንድም ፖሊስ የፍርድ ቤት ስልጣንን የሚጋፋ አሰራር እየሰራ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን በሌላ በኩል በፖሊስ የተያዙ ሰዎች ዋሰትና ህገ-መንግስታዊ መብትን በእጅጉ የሚጋፋ ህገ-ወጥ ድርጊት ያደርገዋል።
ማጠቃለያ
የዋሰትና መብት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ህገ-መንግስታዊ መብቶች ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ሰብዓዊ መብቶች አንዱ ነው። የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት ለዚህ መብት ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን ፍርድ ቤቶችም በዚህ መብት መከበር ላይ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ይሁን እንጂ ከህግ አስፃሚው በተለይም በፖሊስ በኩል ይሄንን ሰብዓዊ እና ህገ-መንግስታዊ መብትን በእጅጉ የሚሸረሽሩ ተግባራት ሲፈፀሙ ይስተዋላል። በተለይም በፖሊስ ተይዞ ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስትና መብት ተከብሮለት በፍርድ ቤቱ እንዲለቀቅ የታዘዘን ሰው ፖሊስ በዋስትናው ብይን ላይ ለበላይ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ እላለሁ በሚል ትዕዛዙን አላስፈፅምም የሚልበት አሰራር የህግ-መሰረት የሌለው እና የተያዘን ሰው ህገ-መንግስታዊ መብት በእጅጉ የሚጥስ ተግባር ነው።
ከዚህ በተጨማሪም አንድ ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ ሊሽር የሚችለው በዚሁ ፍርድ ቤት ሰንሰለት ውስጥ በላዩ የሚገኘው ፍርድ ቤት ሆኖ ሳለ ፖሊስ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በአግባቡ በበላይ ፍርድ ቤት ሳያሳግ እና ይግባኝ ለማለትም ምንም አይነት የሥነ-ስርዓት ህግ ሳይፈቅድለት የተያዙ ሰዎችን የዋስትና መብት እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አለማክበሩ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ መገመት ቀላል ነው። በመሆኑም በተለይም ጉዳዩ የሚመለከተው የፍትህ ሚኒስቴር አስፈላጊ የሚለውን እርምጃ በተለይም የግንዛቤ ማሰጨበጫ ስራዎች (ችግሩ የሚመነጨው ከግንዛቤ ክፍተት ነው በሚል ከቅን ልቦና በመነጨ እሳቤ) በተለይም ለመርመራ ስራ ላይ ለተሰማሩ የፖሊስ አባላት ካልሰራ በእዚህ አግባብ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ተጠናክረው መቀጠላቸው አይቀርም። ጉዳዩ የሚቀርብለት በተለይም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶችም በዚሁ አግባብ ይግባኝ የሚያቀርቡ ፖሊሶች ላይ በህገ-ወጥ መንገድ ሰውን አስረው የሚያቀርቡትን አቤቱታ ከመስማት ይልቅ የሥር ፍርድ ቤት ትፅዛዝን ባለመፈፀማቸው አስፈላጊውን አስተማሪ ቅጣት እንዲወስን ለሥር ፍርድ ቤት ጉዳዩን ቢመልሱ የተሻለ የመብት መከበር ለማየት እንችላለን።