ስለ ዜግነት አዎጁ በፃፍኩት ጽሑፍ ላይ አቶ ግዛዉ ለገሰ የተባሉ የሕግ ባለሙያ የፃፉት ምላሽ ደርሶኝ ተመለከትኩት፡፡ (የአቶ ግዛው ለገሰ ጽሑፍን ለማግኘት ይህንን ይጫኑ፡፡ ) በመጀመሪያ ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ እንደመሆናቸውም ብሎም ጽሑፉን ያወጡት እሳቸው ስላልተስማሙበት የሕግ ጽሑፍ ምላሽ ለመስጠት እንደ መሆኑ አቶ ጀዋር መሐመድን ለመደገፍ አልፃፍኩትም ለማለት አቶ ጀዋር የራሱ ጉዳይ ብለው ጽሑፉን መጀመራቸው፤ በጽሑፉ ውስጥ ለተነሱ እያንዳንዱ ክርክሮች ተገቢውን የሕግ ክርክር ከማንሳት ይልቅ በአመዛኙ በተራ የአዋቃለሁ ባይነት ጉራ ተሞልተው እኩይ ሴራ የሚሉ ያልተገቡ ቃላቶች መጠቀማቸው ብሎም በጽሑፉ ውስጥ ለድምዳሜቸው ማስረጃ አድርገው ስላቀረቡት የሕግ ግምት (presumption of law) ምንነት ያሉት ነገር አለመኖሩ እና ሃሳባቸው ልክ ስለመሆኑ የሚደግፍ የሕግ አስተምሮ ሳይጠቅሱ በደፈናው የሕግ ግምት ያልገባው የሚል የወረደ ምላሽ መስጠታቸው ከሙያ ሥነ-ምግባር የወጣ ተራ ብሽሽቅ የመሰለ መውረድ ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ የመጀመሪየው ጽሑፍ በግልፅ ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት ላይ ብቻ አተኮሮ እንደተፃፈ በተገለፀበት ሁኔታ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ስለሌላቸው እንደ በሕግ ዜግነት ስለማግኘት የመሳሰሉ ለምላሹ ፋይዳ በሌላቸው ዝርዝሮች ላይ ማተኮራቸውም አስቀድመው ላልተስማሙበት ጽሑፍ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በቂ እድል ነፍጓቸዋል ጊዜያቸው አጥንቱን በመጋጥ ላይ መዋል ሲገባው መረቅ ለመጠጣት ውሏል፡፡
እንግዲህ ከዚህ ቀጥየ የአቶ ግዛው የክርክር ነጥቦችን በእኔ መረዳት በሕግ እና በክርክር መርሆች አይን ስሁት መሆናቸውን እንደሚከተለው አሰረዳለሁ፡፡ ትክክለኛው እና አሳማኙ ክርክር የማን ነው የሚለው መዳረሻ የአንባቢ እንጂ የጸሐፊዎች ባለመሆኑ እንደ አቶ ግዛው የኔ ሃሳብ የጉዳዩ ዳርቻ ነው የሚል ትዕቢት አይዳዳኝም፡፡ በጉዳዩ ላይ ስፅፍም የጉዳዩ ትኩረት ማግኘት ትኩረት ከመሳቡ ውጭ የተለየ አትኩሮት ለጉዳዩ እንደሌለኝ በቅንነት ስገልፅ ይህን ማመን ወይም መጠራጠር በእጃችሁ ነው፡፡
የአቶ ግዛው ጽሑፍ አልፋ እና ኦሜጋ በዜግነት አዋጁ ላይ የተጠቀሱት ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች የሕግ ግምት በመሆናቸው ያለምንም የተለየ ሥርዓት ዜግነት ያሰጣሉ ቅድመ ሁኔታዎቹ አልተሟሉም ካለ ማስረጃ የማቅረብ ሃላፊነት (የማስረዳት ሸክም) የኮሚቴው ነው የሚል ነው፡፡
አዎ በርግጥም አንድ ኢትዮጵያዊ የነበረ ሰው ኢትዪጵያዊ ዜግነቱን በመተው ምክንያት መልሶ ለማግኘት ከፈለገ በሕጉ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ወይም እንደሳቸው አገላለፅ መስፈርቶች ሦስት ናቸው እነሱም
- ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በመምጣት መደበኛ መኖሪያውን በኢትዮጵያ ውስጥ መመስረት፤
- ይዞት የነበረውን የሌላ ሀገር ዜግነት መተው እና
- ዜግነቱ እንዲመለስለት ለኢሚግሬሽን እና ስደተኞች ባለስልጣን(ኤጀንሲ) ማመልከት፤
በፅሁፌ ላይ በዝርዝር እንዳብራራሁት ኢትዮጵያዊ ውስጥ መደበኛ ኑሮን ማድረግ፤ ዜግነትን መተው የሚሉ የሕግ ቃላቶች ተራ ቃላቶች ሳይሆን በርካታ ራሱን የቻለ ጽሑፍ የሚወጣቸው የሕግ ቃላት ናቸው፡፡ በርግጥ መሟላታቸውም የሚረጋገጠው በማስረጃ በመሆኑ እነዚህን መስፈርቶች በሌላ ስልጣን ባለው አካል ሳይረጋገጡ አመልካቹ እንደ ራሱ አስተሳሰብ እና እምነት ተሟልተዋል ብሎ ሲያስብ በቃ ተሟልተዋል ስለዚህ ዜግነቱን አግኝቷል የሚል ክርክር ስለ ከሰሰ ብቻ ተፍርዶልኛል ብሎ እንደሚያስብ ተሟጋች፤ ስለ ተፈተነ አልፊያለሁ እንደሚል ተማሪ ያለ ሃሳብ ነው፡፡
ለምሳሌ የሌላ ሀገር ዜግነትን መተው የሚለውን ቅድመ ሁኔታ እንመልከት ራሳቸው ፀሀፊው የኢትዮጵያ ዜግነት እንዲሁ በቀላሉ ትቻለሁ ስላልክ አትተወውም በማለት ይከራከራሉ፡፡ አዎ ዜግነትን መተው እንዲሁ ትቻለሁ በማለት ብቻ አይሆንም፡፡ ይልቁንስ ሕጉ የሚጠይቀውን የመተው መመዘኛ ማሟላት ይጠይቃል፡፡ መተው ደግሞ የሚረጋገጠው በማስረጃ ነው፡፡ ማስረጃውን እንዲያረጋግጥ በአዋጁ አንቀፅ 232/ ሐ መሰረት ግልፅ እና ብቸኛ ስልጣ የተሰጠው ደግሞ የዜግነት ኮሚቴው ነው፡፡ ያልተረጋገጠ ቅድመ ሁኔታ እንደተሟላ አይቆጠርም ነው ለማለት የፈለኩት፡፡ ራሳቸው ጸሐፊው ቅድመ ሁኔታዎቹ ይረጋገጡ አጭበርባሪ ስላለ ይሉና ተሟልተው ከተገኙ ምን ይሆናል? ብለው ይጠይቁና ምንም ዜግነቱን ያገኛል ብለው ምላሽ የሰጣሉ፡፡ አጭብርባሪ ሊኖር ይችላል ብለው፤ መሟላታቸው ይረጋገጥ ብለው፤ ከተሟላ ወይም ካልተሟላ ምን ይሆናል ብለው ጠይቀው፤ የኮሚቴውንም የማረጋገጥ ስልጣን ተቀብለው ካልተሟሉ ኢትዮጵያዊ አይሆንም ከተሟላ ይሆናል ብለው ደምድመው የኮሚቴውን ቅድመ ሁኔታዎቹ መመሟላታቸውን ወይም አለመሟላታቸውን ማረጋገጡ እንደ እንድ ዜግነትን መልሶ ለማግኘት መሰረታዊ ነገር ሆኖ በፅሁፌ ወስጥ መካተቱን መቃወም በልባቸው ያማኑትን በአደባባይ እንደ መካድ ያለ ለራስ የክርክር አካሄድ አለመታመን (fallacious act) ነው፡፡
እንግዲህ እራሳቸውም ያልካዱትን የቅድመ ሁኔታዎቹ መሟላት ራሱ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን መሳት ቅድመ ሁኔታ ምንድ ነው የሚለውን መሰረታ ሃሳብም መሳት ይመስለኛል፡፡ ከተሟሉ ማለት በሌላ አገላለፅ ሲቀመጥ ኮሚቴው መሟላታቸውን ሲያረጋግጥ ማለት እንጅ ቅድመ ሁኔታዎቹ ራሳቸውን በራሳቸው አሟልተው ሲገኙ ማለት አይደለም፡፡ (ጉዳይ ተራ ለመረዳት የቀለለ በመሆኑ በመሃል በመሃል ጽሑፉን ለማቋረጥም ይዳዳኛል) የሚያረጋግተው ደግሞ ኮሚቴው ከሆነ ያላኮሚቴው ማረጋገጥ ዜግነትን መልሶ ማግኘት የለም፡፡
ከዚህ በላይ ቅድመ ሁኔታ ካለ ራሳቸው የሕጉ ቅድመ ሁኔታዎች ብቻ ናቸው፡፡ ቅድመ ሁኔታዎቹ ከተሟሉ ኮሚቴ ዜግነቱን መልሶ እንዲሰጥ ምክረ ሃሳብ የማቅረብ የሕግ ግዴታ አለበት ይህ ካልሆነ ውሳኔውን በፍርድ ቤት አቅርቦ የኮሚቴውን ስህተት በማሳየት ማሻር ይቻላል፡፡ የሕጉን መመዘኛ ትቶ (ሦስቱ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው ተረጋግጦ እያለ) ዜግነትን የሚከለክል አካል ካለ ጉዳዩ የሕግ የበላይት ጥሰት እንጅ የቅድመ ሁኔታ መሟላት አለመሟላት አይሆንም፡፡
ሁላችንም ስለ አንድ ጉዳይ የየራሳችው እምነት እና መረዳት አለን ግን የየግል እምነታችን የሌሎች እውነት ሊሆን ስላማይችል እና ፍትህንም በራሳችን እጅ መውሰድ ልክ ስላለሆነ ሁሌም ከመብት ጋራ የተያያዘን አንድ ነገር መሟላት አለመሟላቱን መሆን አለመሆኑን የሚያረጋግጥ አካል መኖሩ የግድ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፍርድ ቤት፤ ቦርድ፤ ጉባኤ፤ ኮሚቴ ገላጋይ፤ አሸማጋይ የሚሉ ተቋማት ያስፈለጉን፡፡ የአንድ ሰው ከመብቱ ጋራ የተያያዙ እምነቶችን ልክንት የሚያረጋግጡ ተቋማት የሉም ማለት ደግሞ እውነትን አንፃራዊ በማድረግ የማይስማማ እኔ ነኝ ልክ በሚል ማህበረስብ መሞላት ነው፡፡
የጸሐፊው የክርክራቸው ብቸኛ ማስረጃ የሕግ ግምት (presumption of law) ነው፡፡ የሕግ ግምት ባለ ጊዜ ሁሉ ደግሞ ሕጉ የገመተው ነገር የሚጠቅመው ወገን ማስረጃ የማቅረብ ሸክሙ እንደ ግምቱ አይነት ይቀልለታል፡፡ አዎ የሕግ ግምት ህጋዊነት እና ተቀባይነት ያለው የክርክር ማስረጃ ነው፡፡ በሕግ እንደሚታወቀው የሕግ ግምት በማስረጃ የሚፈርሱ (rebuttable) እና የማይፈረሱ (irrebutable) የሕግ ግምቶች ተብለው በሁለት መሰራታዊ ጎራ ይከፈላሉ፡፡ አንዳንንድ ግምቶች ደግሞ መሰረታዊ ነገሮችን (basic facts) በማስረጃ አስረድተህ ቀሪዎቹን የማስረዳት ሸክምህን ደግሞ ወደ ሌላ ሰው የምታዞርበት ሲሆን ሌለኞቹ የሕግ ግምቶች ደግሞ ምንም አይነት ማስረጃ ሳታቀርብ (witout basic facts) በሕጉ ግምት ብቻ የምትጠቀምበት የሕግ ግምት አይነት ነው፡፡
ለምሳሌ በማስረጃ ከሚስተባበሉ የሕግ ግምቶች አንዱ በትዳር ውስጥ የተፈራ ንብረት የተጋቢዎች የጋራ ንብረት እንደሆነ ይቆጠራል የሚለው የቤተሰብ ሕጉ ግምት ነው፡፡ ነገር ግን እዚ ጋር ንብረቱ የጋራ ነው እያለ የሚከራከረው ወገን ምንም አይነት የማሰረዳት ሸክም የለበትም ማለት አይደለም ቢያስ ትዳር መኖሩን ሲያረጋግጥ ነው የሕግ ግምቱ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልው፡፡ በሌላ በኩል ማንኛውም ተከሳሽ በሕግ ፊት ንፁሁ ሆኖ የመቆጠር መብት አለው እዚህ ላይ ያለምንም ክርክር እና ማስረጃ የተከሰሰ ሰው ጥፋተኛ እስኪባል ንፁህ ነው ስለዚህ ቢያምስ ማስረጃ ሌለኛው ወገን አቃቤ ሕግ ማለት ነው ማስረጃ አቅርቦበት ጥፋተኛ እስኪባል ድረስ ንፁህ ነው፡፡ ነገር ግን ጥፋት የፈፀመ መሆኑ በማስረጃ ሲረጋገጥበት የሕጉ ግምት ቀሪ ሆኑ ጥፋተኛ ይባላል፡፡ በማስረጃ ጭራሽ ከማይስተባበሉ ግምቶች ውስጥ ደግሞ ከ9 አመት በታች ያለ ልጅ በወንጀል ተጠያቂ አይሆንም የሚለው ሊጠቀስ ይቸላል፡፡ ምንም አይነት ማስረጃ በልጁ ላይ ቢቀርብ ወንጀለኛ አይደለም፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ለጉዳዩ ብቻ ተገቢነት ያለው የሕግ ግምት መርህ፡፡ ነገር ግን ፀሀፊው ለክርክራቸው አይነተኛ ማስረጃ ያደረጉትን የሕግ ግምት መርህ (presumption of law) ባልተረዳ እና ለመረዳትም እንድል ባልሰጠ መልኩ 2 መሰረታዊ ስህተት ሰርተዋል፡፡
የመጀመሪያው በርግጥ ጸሐፊው የሕግ ግምት ያሏቸው የሕጉ ቅድመ ሁኔታዎች የሕግ ግምት ናቸው? መልስ‹› አይደሉም፡፡
ምክንያቱም የሕግ ግምቶች በመሰረታዊ ባህሪያቸው የሕግ ግምት ተጠቃሚውን የማስረጃ ሸክም የሚያቀሉ እንጅ የማስረዳት ሸክም የሚጥሉ አይደሉም፡፡ ራሳቸው ጸሐፊው እንዳመኑት ሕጉ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን መለሶ ለማግኘት ሶስት መስፈርት ወይም ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ ቅድመ-ሁኔታም እንበለው መስፈርት እነዚህን ማሟላት ሸክም አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር፤ የሌላ ሐገር ዜግነትን መተው፤ ለባለ ስልጣኑ ማመልከት የሚባሉ ሸክሞች፡፡ እነዚህ ሸክሞቹን ካላቀለለ አንድ ሰው ኢትዪጵያዊ ዜግነቱን መልሶ ሊያገኝ አይችልም ምክንያቱም በሕጉ መሰረት የቅድመ ሁኔታዎቹ መሟላታቸው የግድ ነው፡፡
ስለዚህ ፀኃፊው የሕግ ግምት ያልሆኑ ይልቁንስ በግዴታነት እንዲሟላ የተቀመጡ ዝርዝር ጉዳዮችን እንደ ሕግ ግምት መውሰዳቸው ስህተት ነው፡፡ የሕግ ግምቶች በአመዛኙ እንደሆነ ይቆጠራል የሚል ቃል ወይም ሌላ አቻ ግዴታ አስቀሪ ቃላት ይጠቀማሉ እንጅ እንዲህ ካደረገ እንዲህ ይሆናል የሚል ሸለክም አይጥሉም፡፡
ሁለተኛው እና መሰረታዊው ስህተት ዜግነትን መለሶ ለማግኘት ቅድመ ሁኔታ ናቸው ብሎ ሕግ የገለፃቸው ነገሮች ከተሟሉ አለቀ ደቀቀ የሚለው ክርክራቸው ነው፡፡ በርግጥ መሟላት ማለት ምን ማለት ነው? መሟላቱን የሚያረጋግጥው ራሱ አመልካቹ ነው ወይስ ኮሚቴው? ለሚሉ ጥያቄዎች ራሳቸው የሚያረጋግጠው ኮሚቴው መሆኑን ተቀብለው መልሰው ከተሟሉ ኮሚቴው ምንም አያደርግም ብለው መከራከራቸው በቀደመ ፅሁፌ ከሶስቱ በአዋጅ አንቀፅ 22 ላይ ከሰፈሩ መመዘኛዎች በተጨማሪ የዜግነት ይመለስልኝ ጥያቄው ለኮሚቴው ቀርቦ ተቀባይነት ካገኘ የሚል መመዘኛ መጨመሬ ከየትም አንቅቼየው ሳይሆን ሶስት ቅድመ ሁኔታዎች ካሉና መሟላት ካለባቸው መሟላታቸውንም የሚያረጋግጥ በሕግ ስልጣን የተሰጠው አካል ካለ አንድ ፍሬ ነገር በዚህ አካል ፊት ቀርቦ ካላተረጋገጠ ቃላቱን ቀለል ለማድረግ ኮሚቴው ካላረጋገጠ የሕጉ ቅድመ-ሁኔታዎች አልተሟሉም ማለት ነው፡፡ ራሳቸውም ፀሀፊውም በግልፅ ቋንቋ ካልተሟላ ኢትዮጵያዊ አይደለም በማለት በይነዋል፡፡ ስለዚህ የሕጉን ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት የቅድመ ሀኔታዋቹ ቅድመ-ሁኔታ ነው፡፡ ለዚህም ነው በ4ኛነት እንዲቀመጥ ያደረኩት፡፡
ፀኃፊው በአንድ የጽሑፉ ክፍል ተራ ቁጥረ 8 ላይ ሕጉ በደም የተገኘን ዜግነትን መልሸ ልስጥ ብል ይሳቅብኛል ብሎ አፍሮ ጉዳዩን በተለይ ሁኔታ ይዞታል ይሉናል፡፡ ዜግነቱ አያስፈልገኝም ብሎ በራሱ ምርጫ ትቸዋለሁ ብሎ የተወው ራሱ አመልካቹ ሆኖ እያለ ስለ አመልከቹ ሕጉ ሲያፍር ማሳብ የሚያሳፍረው ጸሐፊውን እንጅ ሕጉን ሊሆን አይችልም፡፡ ሕጉ ቢያፍር ኖሮ መለሰህ ስጠኝ ሲባል እንደ ወረዳ ያለ ቅደመ ሁኔታ በሰጠ ነበር፡፡ ሶስት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች እንድያስቀምጥ ያስገደደው ይህው አለማፈሩ ነው፡፡ ለዚያም ነው በርካታ ተቋማት የሚሳተፉበት ኮሚቴ ቅድመ ሁኔታዎቹ መሟላታቸውን እንዲያረጋግጡ ስለጣን የሰጣቸው፡፡
የሕግ ክርክር ተራ የቃላት መደርደር አይደለም፡፡ ሕግ ትርጉም ይሻል፡፡ ሕግ ሲተረጎም የሕግ አውጭውን ፍላጎት፤ የሕጉን አጠቃላይ መንፈስ፤ የቀደመው እና የተከተለውን አንቀፅ ዝምድና መተንተን ይጠይቃል፤ ዝም ብሎ ብሏል ብሏል የሚሉት የሰፈር አታካራ አይደለም፡፡ ሕግ አንድ እና ወጥ የሆነ መድምደሚያ ላይኖረው ይችላል የአንድ ክርክር ጥሩነት የሚመዘነው በልክነቱ ሳይሆን ልክ ለመሆን ባቀረበው ምክንያታዊነት እና ህጋዊ ድጋፍ እንጂ እኩይ፣ ሴራ፣ ንፉግ የሚሉ የዝቅታ ቃላት መደርደር አይደለም፡፡
አሁንም ለምክንያታዊ እና ጨዋ የሕግ ክርከሮች ዝግጁ ነኝ፡፡ የቀደመ ጽሑፌ መግቢያም የዜግነት ሕጉ የግል መረዳት በሚል የሚጀምረው በሌላ አግባብ ለሚነሱ ጠንካራ የሕግ ክርክሮች ቦታ በመስጠቴ የተነሳ የተጨመረ ነው፡፡
የቀደመውን ጽሑፍ የመናገር ነፃነቴን ለመጠቅም፤ ቢጠቅም መረዳቴን ለሌሎች ለማካፈል ለወይይት እና ለሃሳብ ግብዣ ፃፍኩትን እንጅ ማንንም ለመጉዳት ወይም ማንንም ለመጥቀም አልፃፍኩትም፡፡ ይህኛውንስ የአቶ ግዛውን ያልገቡ ያልተገሩ ቃላት ለመተቸት የቀደመ እምነቴንም ይበልጥ ላብራራ ፃፍኩት፡፡
ማሳሰቢያ! በዚህ ጽሑፍ የተመለከተው ሃሳብና ይዘት የጻሐፊው ብቻ ነው፡፡