By muluken seid hassen on Thursday, 30 December 2021
Category: Family Law Blog

ጋብቻ በሚፈርስበት ወቅት የባልና ሚስት የንብረት ክፍፍል ሥነ-ሥርዓት ከሰበር ውሳኔዎች ጋር ተገናዝቦ የቀረበ

መግቢያ

ጋብቻ የተፈጸመበት ስነ-ስርዓት ማናቸውም አይነት ቢሆንም የጋብቻ መፍረስ የሚያስከትለው ውጤት ተመሳሳይ ነው፡፡ ጋብቻ ከተጋቢዎቹ አንዱ ሲሞት ወይም በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ ወይም ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች አንዱ በመጣሱ ምክንያት በሕግ ጋብቻው እንዲፈርስ ሲወሰን ወይም የፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ ሊፈርስ ይችላል፡፡

ጋብቻው ከፈረሰ በኋላ የጋር ንብረትን በተመለከተ በተጋቢዎች ስምምነት፤ በጋብቻ ውላቸው ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ክፍፍሉ ይከናወናል፡፡  

በዚህ አጭር ጽሁፍ የጋራ ንብረት ክፍፍልን በተመለከተ አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዩች መካከል የትኞቹ ንብረቶች የተጋቢዎቹ የጋራ ንብረት ይባላሉ፤ ተጋቢዎቹስ ምን ያህል ምጣኔ ድርሻ በንብረቶቹ ላይ ይኖራቸዋል፤የጋር ንብረት ክፍፍል ጥያቄስ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊቀርብ ይገባዋል የሚሉ ነጥቦችን  የፌዴራሉ የቤተሰብ ህግ እና ከተመረጡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ውሳኔ አንጻር ዳሰሳ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤትነት የሚገኘው አስቀድሞ በሚከናወን የቁጠባ መርሀ ግብር አማካኝነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ሰው ጋብቻ ከመመስረቱ በፊት ለኮንዶሚኒየም ቤት እጣ ምዝገባ ያደርግና ቁጠባውን ሲቆጥብ ቆይቶ የቤቱ እጣ በጋብቻ ጊዜ ከወጣና የቤቱ ባለቤት የሚያደርገው የሽያጭ ውል በጋብቻ ውስጥ እያለ ሊፈጽም ይችላል፡፡ እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ ቀድሞ የተመዘገበው እና ቁጠባውን ሲቆጥብ የነበረው ተጋቢ ጋብቻው በሚፈርስበት ወቅት የኮንዶሚኒየም ቤቱ የግል ሀብቴ ነው በማለት ክርክር የሚያቀርበ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ የቤቱ እጣ የወጣው እንዲሁም የሽያጭ ውሉ የተፈረመው በጋብቻ ውስጥ ስለሆነ ቤቱ የግል ሳይሆን የጋር ሀብት ነው በሚል ክርክር የሚያቀርቡ አሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ጽንፍ የያዙ ክርክሮች የሕግ ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ በሰበር መ/ቁጥር 51893 በቅጽ 11 ላይ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በትርጓሜውም “ ለኮንዶሚኒየም ቤት አንደኛው ተጋቢ ከማግባቱ በፊት ተመዝግቦ እጣው በጋብቻ ጊዜ የወጣ ከሆነ እና የቤቱ ባለቤት የሚያደርጋቸው የሽያጭ ውል በጋብቻ ውስጥ እያሉ ከተፈጸመ የኮንዶሚኒየም ቤቱ በቤተሰብ ህግ አንቀጽ 62(2) መሰረት በጋብቻ ጊዜ በግብይት የተገኘ ሊባል የሚችል ስለሆነ የጋራ ኃብት ነው ” በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የቅድመ ክፍያን በተመለከተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 75562 በቅጽ 13 ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በትርጓሜውም “ አንዱ ተጋቢ በጋብቻው ጊዜ ስሙ ከተመዘገበና እጣውም ጋብቻው ጸንቶ ባለበት ጊዜ ከደረሰ ( ከወጣ) በቤቱ ላይ የሚገኘውን መብት እና ግዴታ የተጋቢዎቹ ነው፡፡ የቅድመ ክፍያን ጋብቻ ከፈረሰ በኋላ በአጭር ጊዜ ወይም ወዲያውኑ በመክፈሉ ውሉም ጋብቻው ፈርሶ የንብረት ክፍፍል ባልተደረገበት ሁኔታ ከሚመለከተው አካል ጋር እጣው በስሙ የወጣለት ተጋቢ በመፈራረሙ ብቻ ንብረቱ በዚሁ ቅድመ ክፍያውን ለከፈለውና ውሉን ለተዋዋለው ተጋቢ የግል ንብረት ነው የሚባልበት የህግ አግባብ የለም” ማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

Liku Worku

ይህንን ጽሑፍ እያነበቡ ስለሆነ እጅግ ደስተኞች ነን፤ ጽሑፍ ጠቃሚ ነው ብለው ካሰቡ ለሌሎች ያጋሩ፤

በጊ ቆይታ ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ስም የነበረ ቤትን በጋብቻ ውስጥ ጥንዶቹ አድሰው ሊኖሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይህን መሰል አጋጣሚ በሚኖርበት ሁኔታ ጋብቻው በፍቺ ሲፍርስ የጋራ ንብረት ክፍፍልን በተመለከተ ቤቱ ላይ በትዳር ውስጥ የተደረገው እድሳት እና ቤቱ ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ስም ተመዝገቦ የሚገኝ መሆኑን በመጥቀስ የጋራ ወይስ የግል ሊባል ይገባል ሚሉ ክርክሮች በተለያዩ ችሎቶች ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ ለእነዚህ ክርክሮች እልባት ለመስጠት በሰበር ችሎት በመ/ቁ 4216 በቅጽ 10 እና በሰ/መ/ቁ ቅጽ 6 ላይ የሕግ ትርጓሜ ተሰጥቷል፡፡ ትርጓሜውም “ ንብረቱ ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ስም የነበረ ቢሆንም በቤቱ ላይ በጋብቻ ውስጥ እድሳት ከተደረገ እድሳቱ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ አኳሀን የተደረገ መሆኑን በልዩ አዋቂ በማረጋገጥ እድሳቱ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ቤቱ የግል ሳይሆን የጋራ ነው ” በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው የሰበር ውሳኔ መገንዘብ የሚቻለው ምንም እንኳ ቤቱ ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ስም የተመዘገበ ቢሆንም ጋብቻ ከተመሰረተ በኋላ በቤቱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ አኳሀን እድሳት ተደርጎ እንደሆነ ቤቱ የባልና ሚስቱ የጋራ ሀብት ይሆናል፡፡ የተደረገው እድሳት መሰረታዊ ለውጥ የማያመጣ የሆነ እንደሆነ በትዳር ውስጥ እያሉ ለተደረገው እድሳት የእድቱን ወጪዎች ብቻ ባልና ሚስቱ የሚካፈሉ ሆኖ ቤቱ ከጋብቻ በፊት ያፈራው ተጋቢ የግል ሀብት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የተደረገው እድሳት መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጭብጥ ለማጥራት ፍርድ ቤቶች ሊሰሙ ሚገባው የሠው ማስረጃ ስለግንባታ ሙያ እውቀትና ክህሎት ያለው የሙያ ምስክር ሊሆን ይገባል፡፡

3 ለት ሚስቶች ባሉ ጊዜ የሚኖር የንብረት ክፍፍል ስነ-ስርዓት

በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 11 ላይ እንደተገለጸው ማንኛውም ሰው አስቀድሞ በጋብቻ የተሳሰረ ከሆነ ይኸው ጋብቻው ጸንቶ ባለበት ጊዜ ሌላ ጋብቻ መፈጸም አይችልም፡፡ ጋብቻውም ተፈጽሞ የተገኘ እንደሆነ በአንቀጽ 17 እና 18/1/ሐ/ መሰረት ጋብቻ ከፈጸመው ሰው ጋር የቀደመ ጋብቻ አለኝ የሚለው ተጋቢ ወይም አቃቤ ሕግ የመቃወም መብት አላቸው፡፡ ሆኖም ግን መቃወሚያ ሳይቀርብበትና በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች አማካኝነት አንድ ሰው ሁለት እና ከዚያ በላይ ሚስቶች አግብቶ የሚኖርብት አጋጣሚ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ መሰል የትደር ግንኙነት የሚኖር ሰው ጋብቻው ለጋብቻ መፍረስ ምክንያት ከሆኑት መንገዶች በአንዱ የፈረሰ እንደሆነ የጋራ ንብረት ክፍፍልን በተመለከተ በልየው እና በሚስቶቹ እንዲሁም ሚስቶቹ እርስ በእርሳቸው ክርክር ማድረጋቸው አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን መሰል ጉዳይ በሚኖርበት ጊዜ የንብረት ክፍፍል በምን አግባብ ሊከወን ይገባል የሚለው ነጥብ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መ/ቁ 45548 በቅጽ 13 ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በትርጓሜውም መሰረት …

ጋብቻው በፍቺ ይም በሌሎች ጋብቻ ለማፍረስ በቤተሰብ ህጉ በተጠቀሱ ምክንያቶች የፈረሰ እንደሆነ ሶስቱም የግል ንብረታቸውን የግል መሆኑን በማስረዳት የየግላቸውን ንብረት መውሰድ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነው ኃብትና ንብረት በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የተጋቢዎቹ የጋራ ኃብት እንደሆነ ይገመታል፡፡ ሁለቱም ሚስቶች እስከተባሉ ድረስ በህጉ መንፈስና ሃይል ከባለቤታቸው ጋር በጋራ ያፈሩትን ንብረት እኩል የመካፈል መብት አላቸው ለንብረቱ መፈራት አንደኛዋ ተጋቢ ከሌላኛው ተጋቢ በተለየ ሁኔታ በቀጥታ አስተዋጽኦ ያደረገች መሆኑን ማስረዳት ከቻለች ከሌላኛዋ ተጋቢ የተሻለ መብት ሊኖራ ይገባል፡፡ በመሆኑም ሁለቱ ሚስቶች በየራሳቸው ጥረት ከባለቤታቸው ጋር ያፈሩትን ንብረት እኩል መብት ስላላቸው መካፈል አለባቸው፡፡ አንደኛው ተጋቢ ከሌላኛ ተጋቢ በልዩ ጥረት የሰራቸውን ልትካፈል አይገባም፡፡ በመሆኑም አንደኛዋ ሚስት ከባሏ ጋር በጥረቷ የሰራቸው ቤት (ንብረት) ካለ ከባለቤቷ ጋር እኩል ተካፍላ እኩሌታው ደግሞ ሌላኛይቱ ሚስት ከባሏ ድርሻ ግማሹን መካፈል ትችላለች፡፡

በፌዴራሉ የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 90(1) 91(1) (2) እንደተገለጸው በመርህ ደረጃ የጋራ ንብረት ለባልና ሚስቱ በእኩል የሚከፈል ይሆናል፡፡ ንብረቱን በእኩል ለመካፈል የማይቻል ሆኖ የተገኘ እንደሆነ ልዩነቱ በገንዘብ እንዲካካስ ይደረጋል፡፡ በአንቀጽ 92 ላይ በተገለጸው አኳሀን ንብረቱ በአይነት መካፈል የሚችል እንደሆነ በአይነት ሊካፈል ይገባል፤በአይነት መካፈል ያልቻለ እንደሆነ አንደኛው ተጋቢ ለሌላኛው ተጋቢ የድርሻውን ግምት ሰጥቶ ቤቱን ሊያስቀር ይችላል፡፡ይህ አማራጭ ግን በተጋቢዎቹ መልካም ፈቃድና ስምምነት ላይ የሚመሰረት ነው፡፡ ባልና ሚስቱ ያላቸውን ቤት በገበያ ዋጋ ግምቱን አንደኛው ተጋቢ ለሌላው በመስጠት ቤቱን እንዲያስቀሩ ፈቃደኛ ካልሆኑ በሁለቱ የጋራ ስምምነት በገበያ ዋጋ ተሸጦ የሽያጩን ገንዘብ እኩል እንዲካፈሉ ይህም ካልተቻለ በፍርድ አፈጻጸም መምሪያ በኩል በሐራጅ ተሸጦ ገንዘቡን እኩል እንዲካፈሉ በማለት ፍርድ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በተግባር የሚስተዋለው በአፈጻጸም ወቅት የግራ ቀኙ የጋራ ንብረት የሆነው ቤት በክፍለ ከተማ መሀንዲስ በኩል እንዲገመት በማድረግ ግምቱ መሰረት ተደርጎ የሚከወን የክፍፍል ስነ-ስርዓት መኖሩ ነው፡፡ ይህን መሰል አሰራር ከዚህ በላይ ከተገለጸው ከሕጉ አንድምታ ጋር የማይጣጣም ከመሆኑም በላይ በውጤት ደረጃም ቢሆን የመሀንዲስ ግምትና የገበያ ዋጋ ልዩነት እንደላው የሚታመን ስለሆነ የአፈጻጸም ትዕዛዙ በአንቀጽ 92 ላይ የተገለጸውን የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ያደረገ አይደለም በማለት ሰበር በቅጽ 7 በመ/ቁ 28019 ላይ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

በትዳር ውስጥ ባልና ሚስቶች በሁለት የተለያዩ ቦታዎች ( ለምሳሌ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ) ከተማዎች ቤት ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ጥንዶች መሀከል ያለው ጋብቻ በፍቺ ውሳኔ በመፍረሱ ምክንያት ግራ ቀኙ የንብረት ክፍፍል ጥያቄ በሚያነሱበት ወቅት ንብረቱን በምን መልኩ መካፈል እንዳለባቸው ሰበር በቅጽ 11 በመ/ቁ 49171 ላይ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ትርጓሜውም “ ክፍፍሉ መደረግ ያለበት ቅድሚያ ሁለቱ ቤቶች በገበያ ዋጋ መሰረት የሚያወጡት ዋጋ እንዲታወቅ ተደርጎ ግራ ቀኙ ወገኖች የገበያ ዋጋውን መሰረት በማድረግ በአይነት ለመካፈል ስምምነት ላይ ከደረሱ የበለጠ ዋጋ ያለውን ቤት የሚወስደው ወገን ገበያ ባስገኘው ዋጋ መሰረት ሌላኛውን ወገን ልዩነቱን በገንዘብ እንዲያካክስ በማድረግ፤ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ቤቶቹ ተሸጠው ገንዘቡን እንዲከፋፈሉ በማድረግ ነው” የሚል ነው፡፡

አንድ አንድ ይዞታዎች ሲከፈሉ የየራሳቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሊሰጣቸው በማይቻልበት ጊዜ ተነጻጻሪ ካርታ ተሰርቶላቸው ይዞታዎቹ ሊካፈሉ የሚችሉበት አሰራር አለ፡፡  የባልና ሚስቱ ቦታ በአይነት ሲከፈል ቤቶቹ በፕሮፖርሽን (በተነጻጻሪ) መከፋፈል እንደሚችሉ በሚመለከተው አካል ሲገለጽ ችሎቱ በዚሁ አግባብ ክፍፍሉ እንዲከናወን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በጽ 22 በመ/ቁጥር 141427 ላይ አስገዳጅ የህግ ትርጓሜ የሠጠ ሲሆን ትርጓሜውም “የባልና ሚስት ንብረት ክፍፍልን በተመለከተ ለአፈጻጸም የቀረበ አከራካሪ ቤት ሊከፈልም ሆነ ፍርድ ያረፈባቸው ቤቶች ከዋናው ቤት ተነጥለው ሊሸጥ የማይችል ሲሆን ሊከፈል የሚችለው በፕሮፖርሽን ( በተነጻጻሪ) ካርታ ነው በማለት በባለሙያ አስተያየት በተሰጠበት ሁኔታ በዚሁ አግባብ ክፍፍሉ ሲደረግ የበለጠ ይዞታ ያደረሰው ወገን ለሌላኘው ወገን ግምቱን እንዲከፍል በማድረግ መፈጸም ይገባል” የሚል ነው፡፡

ጋብቻ በማናቸውም መንገድ ሲፈርስ ጥንዶቹ የጋራ ንብረት ያፈሩ እንደሆነ ንብረቱን የመካፈል መብት እንዳላቸው በቤተሰብ ህግ ከአንቀጽ 90 እስከ 93 ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ጥያቄ ጋብቻው በፈረሰ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊቀርብ እንደሚገባው በቤተሰብ ህጉ ላይ አልተመካከተም፡፡ በቤተሰብ ህጉ ላይ የጊዜ ገደብ አልተቀመጠም ማለት በጋብቻ ውስጥ የተፈራ የጋርም ሆነ የግል ንብረት ሳይካፈሉ ለረጅም ጊዜ ቆይተው ጥያቄውን ማቅረብ ይችላሉ ማለት አይደለም፡፡ የህጉ አላማም ይህ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ይህን ክፍተት ለመሙላት ሰበር በቅጽ 5 በመ/ቁ 29386 ላይ ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን በዚህም መሰረት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1845 ላይ በተጠቀሰው የ10 አመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የክፍፍሉ ጥያቄ ካልቀረበ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡

  

Related Posts

Leave Comments