መቸም አሁን ለእናንተ ላወጋችሁ ያሰብኩትን ነገር በድሮ በዚያ በጥንት ጊዚያት ለነበሩ ሰዎች ብተርክላቸው ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም ይሉኝ እንደነበረ አምናለሁ፡፡ ይህንን ጽሁፍ በተለያየ መልኩ አግኝታችሁ ወይም ያነበቡት አጋርተዋችሁ ስለዚህ ጉዳይ በደንብ የምታውቁ መኖራችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ አንዶቻችሁ ግን ወቼ ጉድ! አሁን የሰዎችን ማንነት መሰረቅም ተጀምርዋል ነው የምትለን;! የምትሉ አትጠፉም ብየ እገምታለሁ፡፡ ለዚህም ምላሼ አዎ! የሰውን ማንነት መሰረቅ ተጀምርዋልና ማንነታችሁ እንዳይሰረቅ ጠንቀቅ በሉ ነው የምላችሁ፡፡ እንዴት ሆኖ ይሰረቃል በልስቲ አውጋን የሚል ከሆነ ቀጣዩ ጥያቄያችሁ በደስታ ይሄው እላለሁ፡፡
በቅድሚያ እንዴት ይሰረቃል ለምን አላማ ሲባል ይሰረቃል የሚለውን ከመመልከታችን በፊት ለመሆኑ ማንነት ስንል ምን ማለታችን ነው የሚለውን እንመልከት፡፡ አንድ ሰው ለመተዋወቅ ወይም ደግሞ ከእኛ የሚፈልገው አገልግሎት ኑሮት እኔ እገሌ እባላለሁ! በማለት ራሱን ሊያስተዋውቀን ይችል ይሆናል፡፡ እኛም እንደነገሩ አስፈላጊነትና ግዴታ የተባለው ሰው ስለመሆኑ በተለያየ መልኩ እንዲያስረዳን ልንጠይቀው እንችላለን፡፡ በሌላ አነጋገር እገሌ ስለመሆንህ ማስረጃ አቅርብልን ልንለው እንችላለን፡፡ ይሄው ብሎ ማንነቱን የሚገልጽ ወረቀት መታወቂያ ወይም ከዚህ ተመሳሳይነት ያለው ማስረጃ ሊያቀርብልን ይችላል፡፡ እኛም አሁንም እንደነገሩ አስፈላጊነት የተባለው ሰው ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለማረጋገጥ የተቀበልነውን ማስረጃ አገላብጠን ልንመለከተው እንችል ይሆናል፡፡ ታዲያ እርሱ ማን እንደሆነ ምን እንደሚሰራ የት እንደሚኖር ጾታውን እድሜውን የቤተሰቡን ሁኔታ ዜግነቱ እናም የመሳሰሉትን መረጃዎች ከተቀበልነው ሰነድ ልናይ እንችላለን፡፡ ከዚህ በህዋላ ግለሰቡ እርሱ ራሱን መሆን አለመሆኑን ካረጋገጥን በህዋላ ከእኛ የሚጠበቅ ነገር ሲኖር ተፈላጊውን አገልግሎት ወይም ትብብር ልናደርግለት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ምን እያልን ነው ያለነው አንድን ሰው ማንነቱን እንድንለይ ሊያደርጉን የሚችሉ መስፈርቶች ከሀገር ሀገር የሚለያዩ ቢሆኑም በአብዛኛው የሚከተሉት መስፈርቶች የአንድ ግለሰብ ማንነቱ ሊያስረዱን የሚችሉ መታወቂያዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የግለሰቡን ስም፣ የስራ ወይም የመኖሪያ አድራሻው፣ ዜግነቱ የመታወቂያ ወይም የፓስፖርት ቁጥሩ፣ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥሩ፣ የባንክ አካውንት ቁጥሩ፣ የመንጃ ፈቃዱን የትምህርት ደረጃው፣ የተሰማራበትን የስራ መስክ፣ እድሜው፣ የትውልድ ቀንና ቦታውን ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ስለሆነም አንድ የማንነት ስርቆት ወንጀል ፈጻሚ እነዚህንና ሌሎች የራሱን ማንነት ደብቆ የሌላ ሰውን ማንነት ለመላበስ/ለመምሰል የሚያስፈልጉ ከላይ የተመለከትናቸውን የማንነት መገለጫዎችን ልቅም አድርጎ በመውሰድ/በመስረቅና ለዚህ አጋዥ የሚሆነውን ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ወይም እንዲዘጋጅለት በማድረግ ማንነቱን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በመቀየር በሰረቀው ሰው ስምና ማንነት ወንጀል መስራት ይጀምራል፡፡ ይህም ማለት የማንነት ስርቆት ማለት የአንድ ግለሰብ መለያ መስፈርቶች ሊሆኑ የሚችሉትን መስፈርቶችን በመጠቀም የወንጀሉ ሰለባውን ተመሳስሎ ህገወጥ ድርጊት የመፈጸም ወንጀል ነው፡፡ የዚህ አይነት የወንጀል ድርጊት ቀደም ብሎ የነበረና የቆየ ወንጀል ድርጊት ቢሆንም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋትንና ስራዎች በአብዛኛው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መከናወናቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ድርጊቱ ሊስፋፋ ችልዋል፡፡
በማንነት ስርቆት የተሰማሩ ሰዎች የሚከተሉት ዘዴዎችን በመጠቀም የግለሰቦችን ይሁን የተቅዋማት መረጃዎችን ይወስዳሉ/ይሰርቃሉ፡፡ የመጀመሪያው ማህበራዊ ምህንድስና (social engineering) የሚባለው ዘዴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ እንደ ቫይረስና አሳሳች ሶፍትዌሮችን በመጠቀም መረጃዎችን የመሰብሰብ ተግባራት ያከናውናሉ፡፡ ማህበራዊ ምህንድስና (social engineering) የሚባለው በአካል ከግለሰቡ ከራሱ ወይም እርሱን ከሚያውቁ ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመተዋወቅ ስለ ግለሰቡ ማንነት አስፈላጊ መረጃዎችን የመሰብሰብ ሂደት ነው፡፡ በዚህም ግለሰቡ ማን እንደሆነ ምን እንደሚሰራ የት እንደሚኖር እና ለወንጀል ድርጊታቸው ያስፈልጉናል የሚልዋቸውን ሌሎች መረጃዎችና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ወደ ወንጀል ድርጊታቸው ይገባሉ፡፡
ቫይረስንና አሳሳች ሶፍትዌሮችን በተመለከተ በዚህ የወንጀል ድርጊት የተሰማሩ ሰዎች ለወንጀል ድርጊታቸው የሚያግዝዋቸውን ልዩ ልዩ የኮምፒውተር ቫይረስ አይነቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የኮምፒውተር ቫይረሶች በተለያዩ መንገዶች እንዲሰራጩ ተደርገው የግለሰቦችንና ተቅዋማትን መረጃ ለእነዚህ ህገ ወጥ ግለሰቦች እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ ጋር የሚቀራረብም ሌላ ዘዴም አለ፤ ይሄውም፣ በኢሌትሮንክስ መልእክት አመካኝነት ይሁን ወይም ደግሞ ግለሰቡ የሚጠቀምባቸውን ድህረ-ገጾችን በማስመሰል፡፡ አዳዲስ ድህረገጾችን በትግበራ ላይ እንዲውሉ በማድረግ አሳስቶ እንዲጠቀም ማድረግ ነው ይህም በእንግሊዘኛው አጠራር “fishing” የሚባለው ዘዴ ነው፡፡ በዚህም የወንጀል ሰለባው ስለራሱ ማንነት የሚመለከቱ መረጃዎችን በተዘጋጀለት የሀሰት ቅጽ ላይ እንዲሞላ በማድረግ በተለይም ደግሞ የመጠቀሚያ ስሙንና የይለፍ ቃሉን በቀላሉ ለመሰብሰብ ያስችላችዋል፡፡ ወይም ደግሞ ከግለሰቡ ይሁን ተቅዋሙ ጋር ግንኙነት ካለው የኢለትሮንክስ መልእክት የተላለፈ በማስመሰል፡፡ እርሱ ብቻ የሚያውቃቸውን እንደ የይለፍ ቃልና የመጠቀሚያ ስሙን እንዲሞላ ቅጽ በመላክና እንዲሞላ በማድረግ አስፈላጊ የሆኑትን መረጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ አላማው የግለሰቡን የይለፍ ቃልና ሌሎች መረጃዎችን ለመውሰድ ነው፡፡
ህገ-ወጦቹ ዋና ትኩረታቸው የግለሰቦች የሂሳብ ደብተሮች፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይቶችን፣ የጨረታ ማእከሎችን እንዲሁም የክሬዲት ካርዶችን እንደሆኑ ይገለጻል፡፡ ምክኒያቱም ደግሞ በአብዛኛው አላማቸው በቀላሉ ገንዘብ መዝረፍ ስለሆነ ነው፡፡
በዚህ የወንጀል ድርጊት በቀዳሚነት የአሜሪካ ዜጎች የጥቃት ሰለባዎች መሆናቸውንና በዚህም ምክንያት በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የክሬዲት ካርዶች እንደሚሰረቁ ከሀገሪቱ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም በየእለቱ የዚህ ሀገር የገንዘብ ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ደንበኞችን ተመሳስለው በሚገቡ ህገ ወጦች እንደሚጠቁ ነው፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ህገ ወጦች የሀገሪቱ ተቅዋማትና ዜጎች ከፍተኛ ገንዘባቸውን በማጣት ላይ መሆናቸውን ይገለጻል፡፡
ለዚህም ሳይሆን አይቀርም የዚህ ሀገር መንግስት ከሌሎች ሀገሮች በቀደመ መልኩ ይህን አድራጎት በከፍተኛ ደረጃ የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት ሆኖ እንዲደነገግ የወሰነው፡፡ በአመሪካ የማንነት ስርቆት በማከናወን የወንጀል ድርጊት የሚፈጽሙትን የሚቀጣ ህግ የወጣው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1998 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በወጣው ህግ እስከ 15 አመት ድረስ የሚያስቀጣ ወንጀል ሆኖ ተደንግጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወንጀሉ እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ ይህ ተጠናክሮና የበለጠ በወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ ጠበቅ ብሎ እንዲወጣ በማሰብ ይመስላል በ2004 ህጉ ተሻሽሎ ቀደም ሲል ከነበረው ቅጣት በተጨማሪ ድርጊቱ የተፈጸመው የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ወይም በሌላ ሀገር ላይ ከፍ ያለ ጉዳትን ሊያስከትል የሚችል ወንጀል ሆኖ ሲገኝ ተጨማሪ ቅጣት እንዲጣልባቸው በአዲሱ የተሻሻለው ህግ ተደንጓል፡፡ አሁን ግን የዚህችን አገር አርአያ በመከተል ብዙ ሀገሮች በህጋቸው የማንነት ስርቆት በወንጀል ህጋቸው ውስጥ በማካተት ወንጀለኞች ከወንጀል ድርጊታቸው ለማቆም ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
የማንነት ስርቆት በሀገራችንስ ምን ይመስላል ብለን ስንመለከት ምንም እንክዋን በሀገራችን በኤሌክትሮኒክስ የሚሰራጨው ገንዘብና የገንዘብ ተቋማት በእንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ከሌሎች ያደጉት ሀገራት አንጻር ሲታይ አነስተኛ ሊባል የሚችል በመሆኑ ምክንያት ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ስለመድረሱ የሚታይና የሚነገር ባይኖርም ነገር ግን ወንጀለኞች ቦታና አጋጣሚ እስከተመቻቸላቸው ድረስ በየትኛውም ሀገር ቢሆን የትኛውም ወንጀል ከመፈጸም ወደ ኋላ የሚሉበት ጊዜ የለም፡፡
በመሆኑም ምን ጊዜም ቢሆን የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰዱ ለነገ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አይሆንም፡፡ ምክኒያቱም ደግሞ በህገ-ወጦች የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የዚህ ሰለባ የሆኑ ዜጎች፡ ከሚደርስባቸው የገንዘብና የኢኮኖሚ ውድቀት ባሻገር የስነ-ልቦና፣ የስም መጥፋት የክብር መጉደፍ፣ ባልሰሩት ወንጀል የመወንጀልና የመሳሰሉት ችግሮች በወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎች አመካኝነት ሊደርስባቸው የሚችልበት አጋጣሚ ያለ በመሆኑ ነው፡፡
ከዚህ ባሻገር በሀገራችን ያሉ የገንዘብ ተቅዋማት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን እምነት ከፍ አድርገው ተጠቃሚ እንዲሆኑና ደንበኞቻቸውን ተገቢ የሆነውን ግልጋሎት በአስተማማኝ ሁኔታ መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ተመሳስለው ዘረፋ ከሚፈጽሙ ወንጀለኞች ጥበቃ ሊደረግላቸው ስለሚያስፈልግ የማንነት ስርቆት የሚከላከል ህግ ተጠናክሮ በስራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡
ምክኒያቱም በአብዛኛው የወንጀሉ ዋና ትኩረት የገንዘብ ተቋማት ከመሆናቸው አንጻር በእነዚህ ተቋማት የሚደረግ ጥቃት ደግሞ በኀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ እንዲሁም የጉዳቱ ሰላባዎች በዘራፊዎች ወንጀል የተሰራባቸው መሆኑን የሚያውቁት በጣም ዘግይተው ስለሆነ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ አስቸጋሪ ስለሚሆን የቅድመ-ጥንቃቄ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከሁሉም በላይ ለማንነት ወንጀል ትኩረት እንዲሰጠው የሚያስገድደው ምክኒያት ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው ጉዳት የደረሰባቸው አንድ አንድ የገንዘብ ተቋማት በደንበኞቻቸውና በአቋቋሟቸው የተቋማቱ ባለቤት እንዲሁም በፈቃድ ሰጪው ያላቸውን ስምና ዝና ጎድፎ ለኪሳራ እንዳይጋለጡ በመፍራት ወንጀል እንደተፈጸመባቸው እያወቁም ቢሆንም ለሚመለከተው አካል ስለጉዳዩ ሪፖርት የማድረግ ፍላጎታቸው አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለወንጀለኞቹ መልካም አጋጣሚ ስለሚሆንላቸው የወንጀል ድርጊታቸውን በስፋት እንዲያከናውኑ ያበረታታቸዋል፡፡ ስለሆነም የዚህ አይነት ወንጀል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወሰድበት ይገባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ይሁን ከሀገር ውጪ የሚሰሩ ድህረ-ገጾች የታወቀ ህጋዊ ግልጋሎት ሳይኖራቸውና ከሚመለከታቸው አካላት ፈቃድ ሳያገኙ ህጋዊ ስራ የሚሰሩ አስመስለው ልዩ ልዩ መልእክቶችን ለኢንተርኔት ወይም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች እንዲደርሳቸው በማድረግ አታልለው የግለሰቦችን የሚስጢር ቃላት፣ ማንነታቸው የመጠቀሚያ ስማቸው (user name) የባንክ ቁጥራቸው፣ ገንዘባቸውን የሚጠቀሙበትን አይነትና ሰነድ እንዲሁም ማንኛውም የማይመለከታቸው በሀሰት ወይም አስመስለው በማቅረብ መረጃዎችን የሚሰበስቡ አልያም ለመሰብሰብ ሙከራ የሚያደርጉ ድህረገጾች ካሉ ተከታትሎ ድህረገጻቸውን ወይም መልእክት የሚያስተላልፉበትና የሚቀበሉበትን መሳሪያ በጥቅም ላይ እንዳያውሉ መከላከል ይገባል፡፡ ይህ ማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ ተጠቃሚው እንዳይታለል በማንኛውም መገናኛ ዘዴ ጉዳዩን በተመለከተ ለህዝቡ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የገንዘብ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ከሚያደርጉት ጥንቃቄ አንዱ ተመሳሳይ ድህረ-ገጽ ያለመኖሩን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲሁም ደንበኞቻቸው በማንኛውም ጊዜ የዚህ አይነት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል የማሳወቅ ስራ ሊሰሩ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ከደንበኞቻቸው ጋር በምን አይነት መንገድ እንደሚገናኙ ግልጽ አሰራር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አሰራራቸውም ለአጭበርባሪዎች በር የሚከፍት አሰራር ስላለመሆኑ ሊፈተሽ ይገባል፡፡
ከእኛስ ምን ይጠበቃል; ምንም እንክዋን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማችን በስራችን ከፍተኛ የሆነ እምርታ እንድናስመዘግብ የሚያግዙን ቢሆኑም ነገር ግን ብዙ ጊዜ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ጥንቃቄ የተሞላበትና በአግባቡ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከዚህም በላይ እኛን ብቻ የሚመለከቱ መረጃዎች እንደ ይለፍ ቃል፣ የመጠቀሚያስሞች ከእኛ ውጪ ለማንኛውም አካል ማስተላለፉ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍለን የሚችል ጉዳይ በመሆኑ ለማንኛውም ወገን አሳልፈን ላለመስጠት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ከዚህ ውጪ የወንጀሉ ሰለባ መሆናችን ጥርጣሬ ሲያድርብን ወዲያውኑ የይለፍ ቃሎቻችንን መለወጥ በቀላሉ ተደራሽ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግና ለሚመለከተው አካል ጥርጣሬዎቻችንን ማቅረብና የመሳሰሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ ራሳችንን ከማንነት ስርቆት ቀበኞች መከላከል ይኖርብናል እላለሁ፡፡
ያላችሁን ሀሳብ አስተያየት በኢሜል አድራሻዬ