“በሕግ አምላክ” ካለ ሀገሬው ውልክፍ የለም፡፡ ሕግ የማኅበረሰብ የውል ገመዱ ነው፡፡ ሕግ የአንድ ሃገር ባህል፣ ልማድ፣ የኑሮ ዘይቤ ካስማና ባላ ነው፡፡ ሕግ ያለ ሰው፣ ሰው ያለ ሕግ ምሉዕነት የለውም፡፡ ሕግ ፈራጅ ነው በዳዩን ይቀጣል፤ ተበዳዩን ይክሳል፡፡ ሕግ አድራጊ ፈጣሪ ነው ይሾማል፤ ይሽራል፡፡ ሕግ ለጋስም ንፉግም ነው ይሰጣል፤ ይነሳል፡፡ ሕግ የእግር ብረት ሆኖ እግር ከወረች ያስራል፤ ሕግ ቁልፍ ሆኖ ይፈታል፡፡ ሕግ መንገድ ነው ያገናኛል፤ ያለያያል፡፡ሕግ ወረትን አያዉቅም፤ሕግ ዘላቂነትን የሚያልም የሩቅ ተጓዥ ነዉ፡፡ ሕግ አዉጪዎች ካልባለጉ ሕግ አይባልግም፡፡ ሕግ እንደ ፈጣሪ አይደለም፤ መረን የሚለቀዉ ሲመቸን የምናከብረዉ ሳይመቸን የምንጥሰዉ አድርግን ያወጣነዉ ቀን ነዉ፡፡
የአንድ ማኅበረሰብ አደገኛነት ለሕግ በሚሰጠው ቦታ ይለካል፡፡ ፈሪሃ ሕግ ያለው ሰው በሕግ አምላክ ለሚለው ምልጃ ተገዥ ነው፡፡ በሕግ አምላክ እና የዳኛ ያለህ መንትዮች ናቸው፡፡ ሀገራቸውም በሚያከብራቸው ነው፡፡ ውልደታቸው በአንድ ቢሆንም በሕግ አምላክ ከዳኛ ያለህ ይቀድማል፡፡ ሁሉም ቃል ነበር፤ ሕግ ቃል፣ ዳኛ ደግሞ ሥጋ ነው፡፡ ሕግ ያለ ዳኛ፣ ዳኛ ያለ ሕግ ዱዳ ናቸው፡፡ ቃሉ ይነገር ዘንድ አንደበት ግድ ይላል፡፡ የሕጉን ቃል የዳኛው አንደበት ይናገረዋል፡፡ ሀገሬው “በሕግ አምላክ፣ ተዳኘኝ” ሲሉት በጄ ያላለውን በቁራኛ ሥርዓት በአልፎ ሂያጁ አስፈጻሚነት ዳኛ ፊት ይገትረዋል፡፡ ያኔም ቃሉ ይነገር ነበር፡፡ ይሄ ጊዜ ሕልም ይመስላል፡፡
ዳኛ ሕግን በመተላለፍ በታሰረው ሰው ፣ በከሳሽና ተከሳሽ መሀከል ያለውን ነገር መርምሮ የሚበይን የሚፈርድ ወይም ተዳኘኝ ቁም ሲሉት አልዳኝም ያለውን ሰው በርሰት በጉልበት የሚጣሉ ሰዎችን በግድ አቁሞ ከቁራኛ ሥርዓት ጀምሮ ከፍ ባለ የችሎትሥርዓት የሚዳኝ የሚገባዉን ፍትሕ የሚዳኝ ነበር፡፡ የመዳኘት ስራ ለዳኛ የተሰጠ ነው፡፡ ያኔ ዳኛው ከስሜቱ ይፋታል፡፡ ቃሉን ለመተርጎም ሰውነቱን ይረሳል፡፡ ቀልቡን ለህሊናው አንደበቱን ለህጉ ቃል ያስገዛል፡፡ በፍርድ ሥራ ዳኛው የጋራ “የወል” ነው፡፡
ከሳቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ዳኛ የወል ዳኛ” የሚለውን የወል ምሰሶ የመሀል እንደሚባል፣ ምሰሶ በግድግዳና በግድግዳ መሃል እንደሚሆን ዳኛም ባዕድና ዘመድን ሳይለይ ለሁሉም ስለሆነ በበደለው ላይ ፈርዶ የሚቀጣ ለተበደለው የበደሉትን ነገር ዐይቶ የሚያስክስ ነው” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ለዚህ ነው በፍርድ ሥራ ዳኛው ዙሪያውን በእኩል እንደተወጠረ ብራና ሊሆን ይገባዋል የሚባለው፡፡
“በሕግ አምላክ! በሕግ” በተባለ ማኅበረሰባዊ ግንብ የታነፀ የሕዝብ ሥነ ልቦና ዳኛ የወል ዳኛ ልክ በግድግዳ መሀከል እንደቆመ ምሰሶ ሚዛናዊ ሆኖ መቆም ካቃተው ግንቡ ፈራሽ ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ የሆነው ግንብ መፍረሱ ብቻ አይደለም አደጋው ዋና ጉዳቱ ፍርስራሹ የሚያዳፍናቸው እሴቶች ተመልሰው ለመገንባት የሚያዳግቱ በመሆናቸው ነው፡፡ ሕግ የማኅበረሰብ ውል መጠበቂያ እንደመሆኑ የሕጉ አፎች በአግባቡ ካልተከፈቱ ውሉ ይፈርሳል፡፡ አንዱ የአንዱን ፍላጎት አክብሮ መንቀሳቀስ፣ የተፈቀደውን እያደረጉ የተከለከለውን መጠየፍ የውሉ አካል ነው፡፡ ውሉ ከፈረሰ ሁሉም ነገር በየዕለቱ እንደምንመለከተዉ “ጨዋታው ፈረሰ …” የሚለዉን የልጆች ጨዋታ እንድናስታዉስ ያደርገናል፡፡ ሥርዓት ዓልበኝነት በመንገስ የነበረውን አዎንታዊ እሴት ያጠፈዋል፡፡ እያጠፋዉም መሆኑን ማመን አለብን፡፡ አሁን ላይ ከምናስበዉ በላይ ነገሮች ተቀያይረዋል፡፡ በፍትሕ የምናምን ሰዎች ለፍትሕ፣ለእዉነት ስንል መድከም እንደሌለብን፣ፍትሕ የምንላት ቀብጥ፣እዉነት የምንለዉ የፍትሕ ክንድ ሲዝል ከማየት አልፈን ደግመን ደጋግምን ታዝበናል፡፡ የፍትሕ ተገማችነት ለአንድ ማኅበረሰብ ብርቱ ጉዳዩ ነበር፡፡ አሁን ላይ ስናስበዉ ይሄ ነገር ቅንጦት ይሆን ብለን ከማሰብ አልፈን ሌሎች ፍትሕን ሊያሰፍኑ የሚችሉ አማራጮችን እንድናማትር አድርጎናል፡፡ ፍትሕ ተገማችነቱም በባላደራው የሕግ ተርጓሚ አካል ጥንካሬ ይወሰን ነበር፡፡ አሁን ላይ ማን ነዉ እምነት ያለዉ? ለፍትሕ ጠበቃ የሚባለዉ ክፍል የደነበሸዉን የፍትሕን ሥርዓት ከማገዝ ይልቅ ሀሜትና ሽሙጡ ላይ ዉድድር ነዉ፡፡ ፍትሕ ብቻዋን ትቆም ይመስል ፍትሕን ሊያስፍኑ የቆሙ ዓቃቤያነ ሕግ፣ፍትሕን ሊሰጡ የተሰየሙ ዳኞች፣ፍትሕን ሊያግዙ የቆሙ ጠበቆች ከተለየ ማኅበረሰብ የተፈጠሩ ይመስል ችግሩን ከመደብ ልዩነት በላይ ከፍ ብሏል፡፡ ይህን ነገር እንደ ቀላል የሚመለከት ሰዉ ካለ በጣም የዋህ ነዉ፡፡ የዚች ሀገርን ችግር ለማንም ቆረሰን በድርሻ የምናከፋፍለዉ አይደለም፡፡ ሀቀኛዉም ሌባዉም ከማኅበረሰቡ ዉስጥ ነዉ፡፡ ስለፍትሕ ስናወራ አንዱን ወገን ባለዕዳ አንዱን ወገን ባለመብት ልናደርግ አንችልም፡፡ ሚዛናዊ ሆነን ካየነዉ እንዲያዉ ሀገሪቱ ላይ ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንደነገሰ ካሰብነዉ ጥፋቱ በየደጁ ነዉ፡፡ የምንመጻደቅበትን ሙያ እንድንንቅ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል፤ተከስተዋል፡፡ ለዚህ ነዉ ሁሉም በቆመበት መርህ የወል መሆን እንዳለበት የማምነዉ፡፡ ከሁሉ ግን የሚያሳስበዉ ሕግ ተርጓሚ የተባለዉ ወገን እጅ መንሻ ለሚያቀርቡለትና ኃይሉን ለተቆጣጠረው ወገን የሚያሸረግድ ከሆነ ሀገር ትጠፋለች፤ ተገማች ፍትሕ ሊኖር አይችልም፡፡
ማኅበረሰቡ በሕግ አምላክ በሚለው ምልጃ ፀንቶ እንዲኖር የሁሉም ባለድርሻ አካል ሚና አስፈላጊ ቢሆንም የሕግ ተርጓሚው ወይም ዳኞች ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ዳኛ ሚዛኑን ከሳተ ሀገር የሚባለዉን ውል ያቆመው አካል ያዝናል፡፡ ዳኛ ትክክል የሕጉን ቃል እንደወረደ እየተረጎመ እንኳን ማህበረሰቡ ጥያቄ ከማንሳት ወደ ኋላ አይልም፡፡ በተከራካሪው ላይ ለሕጉ አፍ ሆኖ የፈረደውን ዳኛ ሕግ ፈረደበኝ ከማለት ዳኛ ፈረደብኝ የሚባልበት ጊዜ የትየሌሌ ነው፡፡ ፍርድ የሚያስደስተው ወገን ያለውን ያህል የሚያሳዝነው እልፍ ነው፡፡ በዳኝነት ያለው ጣጣ ለጉድ ነው፡፡ ለዚህም የዳኝነት ሥርዓቱ ከማንም በላይ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ዳኛ የወል መሆን እጣ ፈንታ ያመጣበት ሸክም እንደሆን መታመን ይኖርበታል፡፡
ቀደም ባለዉ ጊዜ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ የሚነገርና እውቁ ከበደ ሚካኤል የፃፈውን ምሳሌ ከዚህ ላይ ማንሳታችን ጥሩ ይሆናል፡፡ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ አንድ ባለእጅ ነበር፡፡ ባለእጁ የሀገሬውን ማረሻ፣ ማጭድ፣ መጥረቢያ፣ቢለዋና ሌሎች መሳሪዎችን እየሰራ እሱም በሙያው ሰውም በገንዘቡ ጥቅም እየተለዋወጡ ሲኖሩ ባለእጁ በነፍስ ግድያ ተከሶ ዳኛ ፊት ይቀርብና ይሙት በቃ ይፈረድበታል፡፡ ሀገሬውም ፍርዱን ሲሰማ ለስራ የሚያገግለንን መሳሪያ እየሰራ ቀጥ አድርጎ የያዘን ሰው ይሙት ከተባለ እኛ ምን ተስፋ ይኖረናል? ማንስ የምንገለገልበት መሳሪያ ይሰራልናል? በማለት አቤት አሉ፡፡ አቤቱታውን የተቀበለው ሀገረ ገዥ “ነፍስ የገደለ ሰው የግድ መቀጣት አለበት፡፡ ይህም የማይሻር ፍርድ ነው” በማለት ሲመልሳቸው ሀገሬው እንግዲህ ፍርዱ የማይሻር ከሆነማ በእኛው ወረዳ ሁለት ሸማኔዎች አሉ፡፡ ለእኛ አንድ ሸማኔና አንድ ቀጥቃጭ በቂያችን ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥቃጩ ፋንታ ከሁለቱ ሸማኔዎች ዕጣ አውጥታችሁ የወጣበትን አንደኛውን ግደሉት እንጂ ቀጥቃጩ ምንም ቢሆን አይገደልም ብለው ዳኛውን አፋጠው ያዙት እየተባለ ይነገራል፡፡
ይሄኔ ነው ዳኛ የወልነቱን በማስመስከር ዙሪያን እንደተወጠረ ብራና መሆንን የሚጠይቀው፡፡ ዳኛው የወል ነው የሚባለው ለብዙሃኑ ጫጫታ ብቻ ጆሮ በመስጠትና ለባለጊዜዎች፣ለአምባገነኖች፣ለባለገንዘቦች አፋሽ አጎንባሽ በመሆን አይደለም፡፡ የወል ዳኛ ለመሆን የተጎጅም፣ የሸማኔው መሆንን ይጠይቃል፡፡ ይህንን የመሰለ የጥቅም ግጭት ነው ፈተናው፡፡ ፈተናው የሚታለፈው ስሜትን በማድመጥ፣ ጉልበት፣ገንዘብ እና ስልጣን ላለው አካል ተገዥ ሎሌ በመሆን አይደለም፡፡ መንገዱ የህሊናን ብርሃን ወገግ አድርጎ ድቅድቁን አድርባይነትን፣ የአሻጥረኝነት መንፈስ ወደ ግራ በመተው ቀኙን የሕጉን ቃል በመከተል ፍትሕን መተርጎም ስንችል ነዉ፡ ዳኝነት እንዲህ ካልሆነ “የወል ዳኛን” “ውሃ ወራጅ ዳኛ” ይተካዋል፡፡ ጊዜውም ለጭንቅ ቀን የሚሆን የወል ዳኛ ሆይ ሀገርህ ወዴት ነው? የሚባልበት የፍለጋ ዘመን ይመስላል፡፡
ማስታወሻ፡- “ውኃ ወራጅ ዳኛ” ማንኛውም ሰው ውኃ ቀጂን፣ አልፎ ሂያጅን በግብታዊነት የሚዳኝ የጊዜ ዳኛ ነው (ከሳቴ ብርሃን የአመርኛ መዝገበ ቃላት)፡፡